Thursday, April 6, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ (ተፈጸመ)---ክፍል ፲፱


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 29/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እስካሁን ድረስ በዚህ ርእስ ዐሥራ ስምንት ያህል ክፍሎችን ተመልክተናል፡፡ ይህን መጻፍ ያስፈለገኝ የቅብዓትን አስተምህሮ ማወቅ ለሚፈልግ ሰው ሁሉ እንዲብራራለት እና መጥፋት ቢፈልግ እንኳ ሳያውቅ እንዳይጠፋ በማሰብ ነው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በግቢ ጉባዔያት ውስጥ ተማሪዎችን በመረበሽ ትምህርቱ እንዲስተጓጎል በድብቅ በመደራጀት በእልህ የሚንቀሳቀሱ ተማሪዎች በመኖራቸው የተነሣ የተረበሹ ተማሪዎች የቅብዓትን እና የተዋሕዶን ልዩነቱን አስረዳን በማለታቸው እነርሱ እውነታውን ይዘው እንዲጸኑ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ ይህን ያደረግሁት ግን እግዚአብሔር በሚያውቀው ለስድብ እና ለዛቻ አልያም እልህ ይዞኝ አይደለም አዋቂ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ብየም አይደለም ይህን ለማድረግ የተመቻቸ ሁኔታ ስላለኝ እንጅ ስንት ሊቃውንት ያሉባት ቤተክርስቲናችን ለዚህ ከንቱ ትምህርት መልስ መስጠት አቅቷቸው እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ ምናልባትም ዘንድሮ ባይሆንም በቀጣይ ዓመት “ይህ መጽሐፍ በሲኖዶስ ተወግዞ ተገቢውን ምላሽም እንደሚያገኝ” ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ “ጎጃም ውስጥ በተለይም በለየናቸው ጥቂት አካባቢዎች” እየተዘራ ያለው ይህ “ምንፍቅና” እንደሚያከትምለትም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን በቅርብ ቀን ስላሳተሙት “ዝክሪ እና ጳውሊ” መጽሐፉ እንደደረሰን የምንመለስበት ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ “አይዞህ ባይ” ያላቸው እንደሆነ ብናውቅም እግዚአብሔር ካልፈቀደ አንዳች አይደረግምና ዝም ማለትን እንመርጣለን፡፡ አንድም እነዚህ መጻሕፍት በመውጣታቸው ደስ ይለኛል፡፡ አቶ ዘመንፈስ የተባለ መናፍቅ “ተግሳጽና ምክር” በሚል መጽሐፍ ምንፍቅናውን ባይገልጥ ኖሮ ድንቅ የሆነው መጽሐፍ “ኰኲሐ ሃይማኖት” ታትሞ ባላየነው ነበር፡፡ ዳግመኛም ዶ.ር አባ አየለ ተክለሃይማኖት የተባለ ካቶሊካዊ መነኩሴ “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባሕርያት የምታምነው ትምህርት” ብሎ ክህደትን ባይጽፍ ኖሮ “መድሎተ አሚንን” ያህል መጽሐፍ ባላገኘንም ነበር፡፡ ዛሬም የእነዚህን መጻሕፍት መውጣት ተከትሎ ምናልባትም “መልአከ ብርሃናት” ቢነሡ ድንቅ ድንቅ መጻሕፍትን እንመለከትባቸው ይሆናልና በመውጣታቸው ደስ ይለኛል፡፡
********************************************************************************************
ማጠቃለያ፡- በመጨረሻም እነዚህን ክፍሎች ስጽፍ በውስጥ መስመር ለጠየቃችሁኝ ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ፡፡
1.  በቅብዓት ካህን ክርስትና የተነሣ ሰው መጠመቅ አለበት የለበትም ለሚለው ጥያቄ መልሴ መጠመቅ አለበት የሚል ነው፡፡
2.  ጥምቀት አንዲት ናት ለምን ተጠመቁ ትላለህ ላላችሁኝ፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 3 ቁጥር 24 ላይ “ወለእመቦ ብእሲ ዘተወክፈ ጥምቀተ እምዓላውያን ኢኮነ ምእመነ፤  ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም” ይላል እላለሁ፡፡ ስለዚህ ከቅብዓት ካህናት ጥምቀትን የተጠመቀ ሰው አማኒ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ከቅብዓት ካህናት የተጠመቀው ጥምቀት አይቆጠርም ማለት ነው፡፡ ካልተቆጠረ ደግሞ ጥምቀት አንዲት ናት የሚለው አይሻርም፡፡
3.  በልጅነት ጥምቀቱ አምነን እንጠመቃለን ግን የምንኖርበት አካባቢ ቅብዓቶች ይበዙበታል እንዴት መኖር እንችላለን ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ይኼ አያሳስባችሁ ይልቁንስ ተጠመቁ እና የጠመቃችሁን አባት አማክሩ መፍትሔ እዚያ ታገኛላችሁ፡፡
4.  የቅብዓት ቤተክርስቲን የለም ሁሉም የተዋሕዶ ቤተክርስቲን ናቸው ታዲያ ካህኑ ምንም ሆነ ምን እዚያ መቁረብ መጠመቅ ምን ችግር አለው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ይህ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የተዋሕዶ ናት ብለህ አንተ መቅደስ ገብተህ ቀድሰህ ማቁረብ ትችላለህን ብየ እጠይቅሃለሁ፡፡ ይህንንም ተወውና መቸም የእኛ ቤተክርስቲያን ናት ብለህ አንድ ሙስሊም ቀድሶ ላቁርብህ ቢልህ ጥምቀትንም አጠምቃለሁ ቢል እውነት ነው ብለህ ትቀበለዋለህን፡፡
5.  እኔ ቤተሰቦቼ ቅብዓቶች ናቸው እኔ ግን የምጾምም የምቆርብም እንደተዋሕዶዎች ነው፡፡ በቃ ሙሉ በሙሉ ተዋሕዶ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛዋ እምነት ተዋሕዶ እንደሆነች ስላመንሁ፡፡ ታዲያ በ40 ቀኔ የተነሣሁት ክርስትና የተጠመቅሁት ጥምቀት በቂ አይደለምን፡፡ ባልጠመቅስ ምን ችግር አለው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል ማር 16÷16” አንተ ያመነ የሚለውን እንጅ የተጠመቀ የሚለውን አላሟላህምና ይፈረድብሃል፡፡ ምግባር ትሩፋት መሥራት ከማመን ከመጠመቅ በኋላ ነው፡፡
6.  የቅብዓት ካህናትን መስቀል ብሳለም ምን ችግር አለው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ሳታውቁ ካደረጋችሁት ችግር የለውም ግን አይጠቅምም እላለሁ፡፡ መስቀሉ መስቀል የሚሆነው መስቀሉን መያዝ የሚገባው ሰው ከያዘው ብቻ ነው፡፡ ገባችሁ አባባሌ! እስላሙ መስቀል ይዞ ላሳልምህ ቢለኝ አልሳለምም ምክንያቱም እንጨት እንደመሳም ይቆጠራልና፡፡ “ይፍቱኝ አባቴ” የምለውስ እርሱ ከታሰርኩበት የኃጢአት ሰንሰለት መፍታት ይቻለዋልን እርሱ ራሱ “እሡር፤ የታሠረ” አይደለምን ነው፡፡
7.  ከቅብዓት አማኞች ጋር መብላት መጠጣት ኃጢአት ነውን ላላችሁኝ፡፡ መልሴ እርሱን የንስሐ አባቶቻችሁን አማክሩ እላለሁ፡፡ ይህን የጠየቃችሁኝ እኮ አብረውን ስላደጉ ብቻ ሳይሆን በአንድ ቤተክርስቲያን ስለምንጠቀም ጭምር እንጅ የለየላቸውን መናፍቃንን እና አህዛብን በተመለከተ ይህን አትጠይቁም ነበር፡፡ ከእስላም ከካቶሊክ ከፕሮቴስታንት አማኞች ጋር እንዴት ነው የምናደርገው ልክ እንደዚያ ብናደርግ እላለሁ እንደኔ፡፡ ነገር ግን በእልህ እና በትእቢት አናድርገው፡፡
8.  ቤተክርስቲያኒቱ የእኛ ናት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን” ነው የምትባል ታዲያ እነዚህ ቅባቶች እዚህ ውስጥ ምን ይሠራሉ ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ጥገኝነት ቢያስደስታቸው እኛም ቤታችንን ማጽዳት የማንችል ደካሞች ስለሆንን ነው እላለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ በ1990ዎቹ አካባቢ ለፍትሕ ሚኒስቴር “እኛ መገንጠል እንፈልጋለን” ብለው አመልክተው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በሉ እንግዳውስ ቤተክርስቲያናችን የእኛ ናት እናንተ ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ ውጡ ሲባሉ መውደቂያ ቦታ መጠጊያ ታዛ ቢያጡ ዝም አሉ ረገቡ፡፡ ከዚያም በየገዳማቱ ወድቀው ምንፍቅናቸውን መዝራት ጀመሩ፡፡ ድሮ በድብቅ ነበር ዛሬ ግን መጽሐፍ እስከመጻፍ የደረሰ ድፍረት እና ወኔ አገኙ፡፡
9.  የቅብዓት ካህናት ሥልጣነ ክህነት የሚቀበሉት ከማን ነው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ክህነት የሚቀበሉት ከእኛ ጳጳሳት ነው፡፡ ለዚህም እኮ ነው ስልጣነ ክህነት የላቸውም የምንለው፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ የሚል ሰው መናፍቅ ነው” እያሉ እየተሳደቡ “ክህነት ለማምጣት ሲሉ ግን በተዋሕዶ ከበረ ብለው በጳጳሱ ፊት በውሸት ይመሠክራሉ” ታዲያ መንፈስ ቅዱስ በውሸት ይወሰዳልን አይወሰድም፡፡ ስለዚህም ስልጣነ ክህነት የላቸው ብለን እንናገራለን፡፡
10. የንስሐ አባቴ የቅብዓት ካህን ነው ምን ላድርግ ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ክህነት የለውምና የንስሐ አባት ሊሆን አይችልም፡፡ የንስሐ አባታችሁ እንዲሆን ካስፈለገ ግን በተዋሕዶ ይመን እና የልጅነት ጥምቀትን ይጠመቅ፡፡ ስለዚህ የንስሐ አባት አታድርጉት ምክንያቱም እርሱ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ብላ ከምታስተምር ቤተክርስቲናችን ኅብረት አንድነት የለውምና፡፡
11.  ተዋሕዶ ትክክለኛ እንደሆነች አውቃለሁ ነገር ግን የአባቴ እና የእናቴን እምነት አልቀይርም ላላችሁኝ፡፡ መልሴ እርሱ መብታችሁ ነው እላለሁ፡፡ እምነት አምላክ ለፈቀደለት እንጅ ላልፈቀደለት አይሰጥምና አምላክ ፈቃዱ ይሁንላችሁ እላለሁ፡፡ ነገር ግን አባት እና እናቱ እንጨት ጠርበው ደንጊያ አለዝበው ያመልኩ የነበሩት አብርሃም እናት እና አባቱን ትቶ እግዚአብሔርን እንደተከተለ እነግራችኋለሁ፡፡ እምነት ላይ የእናቴ የአባቴ የሚባል ነገር የለም፡፡ አውቀህ ተረድተህ የምትጓዝበት መንገድ ነው እንጅ፡፡
12. ልደት ታህሳስ 28 የምታከብሩ ለምንድን ነው፡፡ ጌታ የተወለደው በ29 አይደለምን ላላችሁኝ፡፡ ትክክል ናችሁ ጌታ የተወለደው ታህሳስ 29 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን በዓሉ ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ገና ታህሳስ 28 ይከበራል ይኸውም ሥርዓት ቀኖና ስለተሠራለት ነው፡፡ ይህ በዓሉን የምናከብርበት ዕለት እና ቀን እንጅ በየዓመቱ ይወለዳል ማለት አይደለም፡፡ ታዲያ ልደቱ ታህሳስ 28 ቀርቶ መስከረም 1 ቀን ይከበር ቢባልስ አናደርገውም ነበርን እናደርገው እናከብረው ነበር፡፡
13. ልደት በ1 ቀን ቀድሞ ከተከበረ ለምን ግዝረት ጥምቀት በአንድ በአንድ ቀን ቀድመው አይከበሩም ላላችሁ፡፡ መልሴ ሥርዓት ቀኖና ለተሠራለት ብቻ ሥርዓቱን ቀኖናውን ጠብቀን እናከብራለን፡፡ ይህ ደግሞ መሠረተ እምነት አይደለምና አያጨቃጭቅም፡፡ ይህን ለመጠየቅ በመጀመሪያ በተዋሕዶ ማመን አለብን፡፡ ነገር ግን አመናችሁም አላመናችሁም ዶግማ እና ቀኖና ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ እንድትረዱ አሳስባችኋለሁ፡፡ ለምሳሌ ጥንተ ስቅለቱ ዐርብ ዕለት መጋቢት 27 ነው፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ስቅለትን የምናከብረው ዐርብ ሚያዝያ 6/2009 ዓ.ም ነው ይህ ለምን ሆነ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ዐርብ ስላልቀቀ ትክክል ነው ብላችሁ ከተቀበላችሁት ግን በዓመቱ ውስጥ (በ2009 ዓ.ም) ስንት ዐርቦች አሉ ብለን እንጠይቃችኋለን፡፡
**************************************************************************************************
በመጨረሻም ያላችሁን ማንኛውንም ዓይነት አስተያየት፣ ጥያቄ በሚከተሉት አድራሻዎች ማድረስ ትችላላችሁ፡፡
ኢሜይል፡ melkamuby@gmail.com
በፌስ ቡክ ገጼ፡ facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid
እስካሁን ያስተላለፍኳቸውን ትምህርቶችንም በዚሁ ድረ ገጽ ላይ ያገኙታል፡፡
***************************************************************************************
በሰፊው ለማንበብ ሃይማኖተ አበውን እና መድሎተ አሚንን አንብቡ!!!
**************************************************************************************
መልካም ሰሙነ ሕማማት ይሁንልን፡፡ ይህ ሳምንት የመጨረሻችን በረከቱን የምንቀበልበት ነውና አብዝተን ልንጾም ልንጸልይ ይገባል፡፡ አምላካችን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም በፍቅር በአንድነት በኅብረት ያድርሰን፡፡ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” በምትለው የሐዋርት እምነት ያጽናን፡፡ ለተሳሳቱት ሁሉ ቀናውን መንገድ አሳይቶ በቸርነቱ ይመልስልን፡፡ አሜን ወአሜን፡፡ ለይኩን ለይኩን፡፡
*******************************************************************************************
ከትንሣኤ በኋላ በሌሎች ትምህርቶች እንገናኛለን እስከዚያው ድረስ ቸርነቱ ይጠብቀን ረድኤት በረከቱ አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ተፈጸመ፡፡

Wednesday, April 5, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ ---ክፍል ፲፰


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 28/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በተለይም መተርጉማኑን በመንቀፍ እና የማይገባ ስም በመለጠፍ እነርሱ ሊቅ የሆኑ የሚመስላቸው አንዳንድ “ለጋ ቅባቶች” በራሳቸው መንገድ መጻሕፍትን ሲተረጉሙ ስመለከት አዝናለሁ፡፡ በእውነት ለእልህና ለንትርክ ከሆነ እኮ ሁላችንም አንተማመንም መቼም ቢሆን አንግባባም፡፡ እነርሱ የሚያነሧቸውን የተወሰኑትን ክፍሎች ጠቅለል አድርገን እንመልከታቸው እስኪ፡፡
“እግዚአብሔር” ማለት እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው ብለው ይተረጉማሉ፡፡ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አግዚአብሔር እንደሚባሉ አይረዱም፡፡ በዚህም የተነሣ “እግዚአብሔር ይቤለኒ” ፤ “ዘቀብኦ እግዚአብሔር መንፈሰ ቅዱሰ ወኃይለ”፤ “መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ ወአስተፍስሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ”፤ “በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ” ወዘተ የሚሉ ዐረፍተ ነገሮችን ሲተረጉሙ “እግዚአብሔር” የሚለው ለአብ ብቻ እንደሆነ አድርገው ነው፡፡ በዚህ ትርጓሜ ደግሞ መስማማት ይከብዳል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ምእ 96÷6 ላይ ነባቤ መለኮት ጎርጎርዮስ የተናገረውን ወስዶ  “አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ ስለ አብ ስለ ወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ” ብሏል ፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ እግዚአብሔር ሲል “አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ” ማለቱ እንደሆነ ማወቅና መረዳት አለብን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በመለኮት በባሕርይ በአገዛዝ በመፍጠር በማሳለፍ አንድ ነው፡፡ ከላይ ባነሣናቸው ጥቅሶች ውስጥ ያለውን “እግዚአብሔር” የሚለውን ቃል ሊቃውንቱ ሲተረጉሙት “እግዚአብሔርነትህ” ብለው ነው፡፡ ምክንያቱም ተለይቶ ለአብ የተጻፈ አይደለምና፡፡ ለምሳሌ “በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ” የሚለውን  የዳዊት መዝሙር ይዘን “እግዚአብሔር” የሚለው የአብ ልዩ ስም አድርገን ከተረጎምነው ወደ ክህደት እንደምንገባ አስተውሉ፡፡ “እግዚአብሔር አምላክከ” ሲል ምን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ አምላክህ ብለህ ልንተረጉመው ነውን፡፡ በፍጹም አይደለም! ሊቃውንቱ ይህን ደስ በሚል መልኩ የጠመመውን አቅንተው የጎደለውን መልተው ተርጉመውታል፡፡ ሙሉ ትርጓሜውን በክፍል ፲፮ ተመልክተነዋል፡፡ እዚህ ላይ ማንሣት የምሻው “እግዚአብሔር አምላክከ” የሚለውን ቃል ትርጉም ብቻ ነው፡፡ ሊቃውንቱ “እግዚአብሔርናከ አምላክናከ፤ እግዚአብሔርነትህ አምላክነትህ” ብለው ተርጉመውታል፡፡ ታዲያ “እግዚአብሔር” የሚለው ለአብ ልዩ መጠሪያ የምናደርገው በምን መልኩ ነው፡፡
ልብ ማለት ያለብን ነገር ምንድን ነው ለ “አብ” የሚነገሩ ነገሮች በስም ተለይተው እንደሚቀመጡ ነው፡፡ ይህም ማለት በሥላሴ ዘንድ የአካል ሦስትነት የባሕርይ አንድነት አለ፡፡ በባሕርይ ግብራቸው አንድ ሲሆኑ በአካል ግብራቸው ግን ይለያያሉ፡፡ የአብ አካል ግብሩ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ አካል ግብር የተለየ ነው፡፡ የወልድም እንዲሁ የመንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ የአካል ግብራቸው የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ወልድ በተለየ አካሉ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ የምወደው የምወልደው ልጅ እርሱ ነው አለ፡፡ በመለኮታዊ ግብራቸው ግን አንድ ናቸውና አንዱ በሌላው ሊጠሩበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ  “ፈጣሪየ ኢየሱስ ክርስቶስ” ስንል አብ እና መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪያችን አይደሉም ብለን አይደለም፡፡ በመለኮታዊ ግብራቸው አንድ ስለሆኑ አብ ስንል ወልድን መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው፡፡ ወልድ ስንልም አብን መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስንልም አብን ወልድን ማለታችን ነው፡፡ ለምሳሌ ሐዋ 9÷5 ላይ ሳውልን “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ” አለው፡፡ ይህን ማለቱ “ኢየሱስ ክርስቶስን” ስላሳደደው ሳይሆን “በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት የሚያምኑ ክርስቲያኖችን ስላሳደደ” ነበር፡፡ በአምላክነት በመመለክ አንድ ናቸውና ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው እንጅ ለአብ ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ ስም አይደለም፡፡ መጻሕፍትንም ስንተረጉም በዚሁ መንገድ ነው እንጅ “እግዚአብሔር” የሚለውን ሁሉ በመጠቅለል ለአብ ብቻ እየሰጠን አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሐዋርያው ጴጥሮስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” ማለቱ በባሕርይ ግብራቸው አንድ መሆናቸውን ለማሳየት እንጅ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ” ብሎ ያዘዘውን ትእዛዝ መጣሱ አይደለም፡፡ በመለኮታዊ ግብራቸው አንድ ስለሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲል በአብ በራሱ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማለቱ ነው፡፡  እንዲህ ንባብን ከምሥጢር ጋር ካላስማማነው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል “የብረት ቆሎ” ነው ልቆርጥምህ ብትለው ጥርስህ ይሰበራል እንጅ ቆሎ ሆኖ አይቆረጠምልህም፡፡ ስለዚህ እልሁን እና ትእቢቱን ትተን በፍቅር እና በትህትና ሆነን እስኪ መጻሕፍትን እናንብብ ሊቃውንቱን እንጠይቅ፡፡ በሱባዔ የሚመለሰውን ደግሞ በጾም በጸሎት እንጠይቅ፡፡ እምነት ከእግዚአብሔር ሲሰጥ እንጅ በራሳችን አንዳች ነገር አናደርግም፡፡ እምነት ለተመረጠ ሰው፤ አምላክ ለመረጠው ሰው ለእርሱ ብቻ የሚረዳ ምሥጢር ነው፡፡
ትርጓሜን ለራሳችን ካደረግን መናፍቅ ከሀዲ ለመሆን ሮሜ 8÷34 ብቻ በቂ ነው፡፡ እርሱን ማስፋት ይቻላል፡፡ “ስለእኛ የሚማልደው” በሚለው ቃል ስንቶች እንደጠፉ አታውቁምን፡፡ ታዲያ ለመጥፋት ጥቅስ መጥቀስ ያስፈልጋልን፡፡ መጥፋት የሚሻ ሰው ያለጥቅስ መጥፋት ይችላል፡፡ ለመጥፋት ለምን ምክንያት እንፈልጋለን፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፲፯



© መልካሙ በየነ

መጋቢት 27/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እስከዚህ ድረስ የቅብዓትን አስተምህሮ ከተዋሕዶ አስተምህሮ ጋር የተለያየ እንደሆነ በሚገባ ተመልክተና



ል፡፡ በዚህ በቅብዓት እምነት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞች እና እህቶች እኔ የምጽፈውን ሁሉ ሲቃወሙ ስመለከት ስለእውነት ከልቤ አዝናለሁ፡፡ እኔ ደካማ እና ኃጢአተኛ እውቀት የሌለኝ ምሥጢር ያልጠነቀቅሁ እንደሆንሁ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን እየጻፍኩት ያለሁት ከራሴ አንቅቼ በመፈላሰፍ ወይም በራሴ መንገድ በመተርጎም አይደለም፤ አባቶቻችን በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ያለውን ቃል በቃል እየገለበጥሁ እንጅ፡፡ ታዲያ አባቶቻችን ያስተማሩንን ትምህርት የጻፉልንን መጻሕፍት ካልተቀበልን ሌላ ማን ሊያስተምረን ነው?
እኔ በጣም ደስ የሚለኝ ነገር አለ እርሱም በመጽሐፍ ላይ ተመስርቶ መከራከር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን ምንም ወደማይጠቅም ስድብ እና እልህ ማምራት ይሆናል መንገዳችን፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም ለምንም የማይጠቅም ከንቱነት ነው፡፡ መቃወም ያለበት ሰው መቃወም ያለበት እኔን አይደለም የተጻፈውን ትምህርት ብቻ ነው፡፡ ይህንንም እኔ አደርገው እንደነበረው ሁሉ መጽሐፍ ይዘን መሆን አለበት፡፡ አንዳንዶች መጽሐፉ ሳይኖራቸው “ወልደ አብ” ላይ ተጽፎ ስለተመለከቱት ብቻ ይጠቅሱታል፡፡ ነገር ግን ያ የተባለው ጥቅስ መጽሐፍ ላይ አይገኝም፡፡ ቄርሎስ እንዲህ አለባችሁሳ ስላቸው ይህ እኮ በሥጋ ርስት ነው ይላሉ፡፡ ኤጲፋንዮስ እንዲህ አለባችሁሳ ስላቸው ደግሞ በባሕርይማ ሁሉም አንድ ናቸው ይላሉ፡፡ ብቻ እኔ የምላቸውን ነገር ላለመቀበል ሲሸሹ ሲሸሹ እያየኋቸው ገደል ሲገቡ ተመለከትሁ እና አዘንሁ፡፡ በእውነት አንድ እውነት እስኪ እንመልከት፡፡
አብ ወላዲ አስራጺ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ ብለን እናምናለን፡፡ እነርሱ ደግሞ ከዚህ በተጨማሪ ምን ይላሉ አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ፡፡ በስም በግብር በአካል በገጽ ስንመለከት አብ አብን እንጅ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን አይሆንም፡፡ ወልድም ወልድን እንጅ አብን እና መንፈስ ቅዱስን አይሆንም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስን እንጅ አብን እና ወልድን አይሆንም፡፡ (አብ) አብ የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (ወልድ) ወልድ ከተባለበት (መንፈስ ቅዱስም) መንፈስ ቅዱስ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡  (ወልድ) ወልድ የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (አብ) አብ ከተባለበት (መንፈስ ቅዱስም) መንፈስ ቅዱስ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ (መንፈስ ቅዱስ) መንፈስ ቅዱስ  የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (አብ) አብ ከተባለበት (ወልድም) ወልድ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ይህ ሦስትነት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የአካል  መጠሪያ ስም ነው፡፡ አብ የራሱ የሆነ የተለየ አካል አለው ወልድም እንዲሁ መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፡፡ የአካል መቀላቀል የአካል አንድ መሆን የአካል ተዋሕዶ የላቸውም “ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮቱ” እንዲል፡፡ ስለዚህ በአብ ስም ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡ በወልድ ስምም አብ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አብ እና ወልድ አይጠሩበትም፡፡ ምክንያቱም አካላቸው ለየራሳቸው ነውና አንድም በባሕርይ እንጅ በአካል አንድነት የላቸውምና አንዱ በሌላኛው ስም አይጠሩበትም፡፡
ሌላው የአካል የግብር ሦስትነት ነው፡፡ ሥላሴ በአካል ግብር ሦስትነት የየራሳቸው የሆነ ስም አላቸው፡፡ ይህም ወላዲ፤ ተወላዲ፤ ሰራጺ ነው፡፡  አብ ወላዲ ቢባል እንጅ እንደ ወልድ ተወላዲ እንደመንፈስ ቅዱስ ሰራጺ አይባልም፡፡ ወልድም ተወላዲ ቢባል እንጅ እንደ አብ ወላዲ እንደመንፈስ ቅዱስ ሰራጺ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ሰራጺ ቢባል እንጅ እንደ አብ ወላዲ እንደ ወልድ ተወላዲ አይባልም፡፡ የአካል ግብር ስም አንዱ ለአንዱ አይሰጥም አንዱ በአንዱ አይጠራም፡፡ አብም ወላዲ ሲባል ይኖራል ወልድም ተወላዲ ሲባል ይኖራል መንፈስ ቅዱስም ሰራጺ ሲባል ይኖራል እንጅ አንዱ ለአንዱ መጠሪያ አይሆንም፡፡ በአካል ግብር ስም መቀላቀል እና መፋለስ የለባቸውም፡፡ ምንም እንኳ ሥላሴ በባሕርይ በአገዛዝ በሕልውና በመፍጠር በማሳለፍ አንድ ይሁኑ እንጅ በወላዲነት በተወላዲነት በሰራጺነት ግን አንድ አይደሉም፡፡ በመለኮት በባሕርይ አንድ ናቸው ብለን አብ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ፤ ወልድ ወላዲ  ተወላዲ ሰራጺ፤ መንፈስ ቅዱስ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ አንልም፡፡
በቅብዓት አስተምህሮ ውስጥ ግን እኛ የማንቀበለው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚል የአካላት የግብር ስም አላቸው፡፡ ይህም የአካላት የግብር ስም አንዱ ለአንዱ መሆን ይችላል፡፡ መፋለስ እና መቀላቀል አለበት፡፡ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይህ የሥላሴ የግብር ስም ተፋልሶ አለበት፡፡ በእርግጥ ወደዚህ ያመጣናቸው በክርክር ነው፡፡ ሲጀምሩ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ነበር ያሉን፡፡
ከዚያ ቄርሎስ  ስምዐት 124÷34 “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ
ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ..” ይላልሳ፡፡ “ለሊሁ ቀባዒ” የተባለ ማንን ነው ስንላቸው ወልድን ነው አሉን፡፡ ታዲያ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ለምን ትላላችሁ አልናቸው፡፡ እነርሱ ግን በባሕርይማ አንድ ናቸውና ሁሉም ቀባዒ ናቸው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የምንል በሥጋ ርስት ብቻ ነው አሉ፡፡ ስለዚህ “አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቀባዒ” ናቸው ይላሉ ብለን ደመደምን፡፡ ይህም በመለኮት አንድ ስለሆኑ ነው በሥጋ ደግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ነው ይላሉ፡፡ አስቡት ለሥላሴ አካል የግብር ስማቸው አንድነት አለው፡፡ ይህ ማለት አብ ቀባዒ መለኮት ወልድ ተቀባዒ መለኮት መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ መለኮት በማለት የመለኮትን አንድነት ወደ ሦስትነት የሚከፍል አስተምህሮ ነው፡፡ ምክንያቱም “ቀባዒ ተቀባዒ ቅብዕ” የሚለው የባሕርይ ግብራቸው አይደለምና፡፡ የባሕርይ ግብር ከሆነ በሥጋ ርስት በመለኮት ርስት በምንም ዓይነት ርስት ውሰዱት አንድ ነው አይለወጥም አይቀየርምም፡፡ እነርሱ ግን በመለኮት ርስት ሁሉም “ቀባዒ” ናቸው በሥጋ ርስት ድግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ናቸው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ!!! ቀባዒ መለኮት አብ በሥጋ ርስት ቀባዒ ሆነ፤ ቀባዒ መለኮት ወልድ በሥጋ ርስት ተቀባዒ ሆነ፣ ቀባዒ መለኮት መንፈስ ቅዱስ በሥጋ ርስት ቅብዕ ሆነ ማለታቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሐሰት ክህደትም ነው፡፡ “ቅብዕ” ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙ “ክብር” ማለት ነውና፡፡ አብ ቀባዒ ሲሉ አብ አክባሪ ወልድ ተቀባዒ ሲሉ ወልድ ተከባሪ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሲሉ መንፈስ ቅዱስ ክብር ሆኑ ማለት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ስም የአካል ስም ነው፡፡ ታዲያ በአካል አንዱ አክባሪ አንዱ ከባሪ አንዱ ክብር ይሆን ዘንድ ይህን ክህደት ማን አስተማራችሁ ብለን እንጠይቃቸው፡፡
ከዚህ ስህተታቸው የምንረዳው ነገር የሚከተለውን ነው፡፡
1.   የአካላት ግብር ስም ሁለት ጊዜ እንደተሰጣቸው ነው፡፡ ዘመን ሳይቆጠር ቀድሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቀባዒ” ነበር ማለት ነው፡፡
2.   ድኅረ ዓለም ወልድ በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ደግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ሆኑ ማለት ነው፡፡
3.   ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ምእራፍ 2 ቁጥር 154 ላይ “ለአጽንዖተ ክልዔሆሙ፤ አብን መንፈስ ቅዱስን በጥንተ ስማቸው ለማስጠራት በጥንተ ግብራቸው ለማጽናት” የሚለው ትምህርት ተቀባይነትን አላገኘም ማለት ነው፡፡
4.   አብ ከቀባዒነት ወደ ቀባዒነት፤ ወልድ ከቀባዒነት ወደ ተቀባዒነት፤ መንፈስ ቅዱስ ከቀባዒነት ወደ ቅብዕነት እንደተለወጡ የሚያሳይ መሆኑ፡፡
ስለዚህ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚለው የግብር ስም በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ተቀባይነት የሌለው ከንቱ ፍልስፍና ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ብለን አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንዲህ እናምናለን፡፡ እንዲህም እንታመናለን፡፡
ቃል ሥጋን በተዋሐደበት ጊዜ ረቂቅ በሆነ ጥበብ ሥጋ አምላክ ሆኗል፡፡ አምላክ ሰው ሆነ ፤ ሰውም አምላክ ሆነ ማለት ስለዚህ ነው፡፡ “ተዋሕዶ ክብርን አያሳልፍም” የሚለው ፍልስፍና ግን ሊቁ ቄርሎስ በመሰለው የጋለ ብረት ተሸንፏል፡፡ ሥጋን ከበረ ማለታችን “ሥጋ አምላክ ሆነ” ለማለት ብቻ የሚነገር መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ከተዋሕዶ በኋላ  “ሥግው ቃልን፤ ኢየሱስ ክርስቶስን” አክባሪው ማነው ተከባሪውስ ማነው እያልን አንድነትን ከፍለን ልንጠይቅ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም በሥጋው ከበረ ስንል በመለኮቱ ንድየት አደረበት ማለት ስለሆነ ይህ ክህደት ነው፡፡
ከመጻሕፍት ለመሸሽ ሲሞክሩ ራሳቸውን ወደ ጉድጓድ ወረወሩ የምላችሁም ለዚሁ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ትምህርተ መለኮትን የማያፋልስ “ይህ ቃል ምን ተብሎ ቢተረጎም ነው” ማለት አለብን፡፡ ያማ ካልሆነ ሁላችን “መናፍቅ” የምንሆንበትን ጥቅስ በመሰብሰብ መጥፋታችን አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ውዳሴ ማርያም ላይ ብዙ ቦታ “ኃደረ ውስተ ከርስኪ” የሚል ቃል አለ፡፡ ይህንን ቃል  ይዘን “ኅድረት” ልንል ግን አይገባንም “ኃደረ” ያለውን “ተዋሐደ” ብለን እንተረጉማለን እንጅ፡፡ “ቃል ሥጋ ኮነ” የሚለውንም የወንጌል ቃል ይዘን “ተለወጠ” ልንል አይገባንም፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ በአግባቡ ካልተተረጎመ በጥሬው ከተመለከትነውና በራሳችን ፈቃድ ከተረጎምነው ክህደት አይደለምን ነው እንጅ፡፡ አሁን የሚሻለን የቀደሙ አባቶቻችን ከዕብራይስጥ፤ ከጽርእ፤ ከዐረብኛ ወዘተ ወደ ግእዝ የመለሱልን እንዴት ነው አባቶቻችንንስ ግእዙን ወደ አማርኛ የመለሱት እንዴት ነው፡፡ አንድምታውንስ እንዴት ነው ያመሠጠሩት ብለን በትህትና መጻሕፍትን መመልከት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሊቃውንቱን በመዝለፍ የሚሰጥ እና የሚታደል ጸጋ እግዚአብሔር የለም፡፡ አንድ ሰው (ገብረ መድኅን እንዳለውን ማለቴ ነው) በጻፈው ልብ ወለድ የፈጠራ ጽሑፍ (ወልደ አብ) ላይ ተመሥርተው ያንን ደጋግሞ ማነብነብ ከንቱነት ነው፡፡ “እውነቱን መርምሩ የሚበጀውንም ያዙ” የሚለውን ጠቃሚ ትምህርት እንጠቀምበት፡፡
በመጨረሻም!!! ዛሬ መጋቢት 27 ጥንተ ስቅለት ነው፡፡ ዘንድሮ 2009 ግን ስቅለት የሚከበረው ሚያዝያ 6 ነው ታዲያ ልደት ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ ታህሳስ 28 ለምን ተከበረ የምትሉ ወገኖች ስቅለት ለምን ጥንተ ቀኑን ለቀቀ ብላችሁ ጠይቁ እስኪ፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

Monday, April 3, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፲፮


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 26/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


1.  ኢሳ 61÷1 “መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ አስተፍሥሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ”
“መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ ወአስተፍስሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ”
ስለሱ ነዳያን ትሩፋንን ደስ አሰኛቸው ዘንድ በኔ ያደረ መንፈሰ ረድኤት ላከኝ ይላል ኢሳይያስ ወእፈውሶሙ ለቁስላነ ልብ፣ በቁስለ መከራ የተያዙትን አድናቸው ዘንድ፤ ወእስብክ ሎሙ ግዕዛነ ለፂውዋን፣ ለተማረኩት ነጻነትን አስተምራቸው ዘንድ ማለት ሚጠትን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ፡፡ ወይርአዩ እውራን፤ እውራነ ልቡና እስራኤል ያዩ ዘንድ ላከኝ፡፡ ወእስምዮ ለዓመተ እግዚአብሔር ኅሩየ፤ ዕለተ ሚጠትን የተመረጠ እለው ዘንድ ወለዕለተ ፍዳ ኅሪተ፤ ዕለተ ፍዳም ያላት ዕለተ ሚጠት ናት የባቢሎን ሰዎች ፍዳን ስለተቀበሉባት ዕለተ ፍዳ አላት፡፡ ወአስተፍሥሆሙ ለልህዋን፤ ሰባ ዘመን ያዘኑትን ደስ አሰኛቸው ዘንድ፡፡ ወአሀቦሙ ክብረ ለእለ ይላህውዋ ለጽዮን፣ ኢየሩሳሌምን አጥተው ላዘኑ ሰዎች ክብረ ሥጋን እሰጣቸው ዘንድ፡፡
ወህየንተ ሐመድ እፍረተ ትፍሥሕት ለእለ ይላህው፣ ትቢያ ይበንባቸው ስለነበረ ፈንታ ላዘኑ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ ሽቱን እሰጣቸው ዘንድ፤ ወልብሰ ክብር ህየንተ መንፈስ ትኩዝ፣ ሰባ ዘመን ስለአዘነ ልብ ፈንታ ደስ አሰኘው ዘንድ ፈነወኒ፣ ላከኝ፣ አንድም መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ አስተፍሥሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ፣ ያዋሐደኝ በህልውናዬ ያለ የእግዚአብሔር የባሕርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድም ሳይናበብ መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ፤ በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሀደኝ እግዚአብሔር አብ ምእመናንን አስተምር ዘንድ ላከኝ፣ አንድም መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላእሌየ ብሎ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ተረጉሞታልና ብሎ የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌየ በእኔ ህልው ነው፣ ወዘበእንቲአሁ ቀብዐኒ፣ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ምእመናንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ፡፡
2.  ዳን 9÷24
“ወይትቀባዕ ቅዱሰ ቅዱሳን፣ ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታ ይከብራል፣ የባህርይ ክብሩን ገንዘብ ያደርጋል፤ አእምር ወለቡ እምፀአተ ቃሉ ዘታወሥእ፣ ንገረው የሚለኝ ቃሉ ከመውጣቱ የተነሳ የምትመልሰውን እወቅ፤ አንድም እምጸአተ ቃል ዘአወስአከ ንገረው የሚለኝ ቃል ከመውጣቱ የተነሳ የምመልስልህን እወቅ፡፡ አንድም እምፀአተ ቃሉ ዘታወሥእ ንገረው የሚለኝ አካላዊ ቃሉ ከመምጣቱ የተነሳ የምትመልሰውን እወቅ፤ አንድም እምጸአተ ቃል ዘአወሥአከ አካላዊ ቃል ከመምጣቱ የተነሣ የምመልስልህን እወቅ ወትትሐነፅ ኢየሩሳሌም እስከ ክርስቶስ ንጉሥ፣ ኢየሩሳሌም ጌታ እስቲወለድ ድረስ በመፍረስ በመታነፅ ቤተ መቅደስ በመሆን ቆይታ ቤተክርስቲያን በመሆን ትታነፃለች ሰብአተ ሰንበታተ ስሳ ወክልዔተ ሰንበታተ ሰባት ሱባኤ ስድሳ ሁለት ሱባኤ ቆይታ፡፡
3.  ሐዋ 10÷38 “ዘቀብኦ እግዚአብሔር መንፈሰ ቅዱሰ ወኃይለ”
“ዘቀብኦ እግዚአብሔር መንፈሰ ቅዱሰ ወኃይለ”
እግዚአብሔርነቱ ኃይሉ ሕይወቱ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ የመረጠው የሾመው፡፡ ውእቱ መጽአ ከገሊላ ወደ ይሁዳ በመምህርነት መጥቶ ወረድኦሙ ለእለ ይተዔገሎሙ ሰይጣን፤ ሰይጣን ድል አድርጓቸው የነበሩትን እንዳዳነ ታውቃላችሁ እስመ በዘአመከርዎ ክህለ ረድኤቶሙ ለሕሙማን ወረድነ በከመ ምክረ ፈቃዱ እንዲል፡፡ እስመ እግዚአብሔር ምስሌሁ እግዚአብሔር በህልውናው ነውና፡፡

4.    ሮሜ 1÷2-4 “በእንተ ወልዱ ዘተወልደ ወመጽአ እም ዘርአ ዳዊት በሥጋ ሰብእ ወአርአየ ከመ ወልደ እግዚአብሔር ውእቱ በኃይሉ ወበመንፈሱ ቅዱስ”
“ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያቲሁ ወበመጻሕፍቲሁ ቅዱሳት በእንተ ወልዱ ዘተወልደ”
አካል ዘእም አካል፣ ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ የልጁን ነገር ፤ ስለ ተወለደ ስለ ልጁ፤ በዳዊት “ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ” መዝ 2÷7፤ በነገሥት “አነ እከውኖ አባሁ ወውእቱ ይከውነኒ ወልድየ” 2ኛ ነገ 7÷14፤ በሰሎሞን “እምቅድመ አድባር ወአውግር ወለደኒ” ምሳሌ 8÷25፤ በነቢያት በመጻሕፍት  ያናገረ የአብን ነገር ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ የተገኘች ክታብ (መልእክት)  ሐተታ  መጻሕፍት፣ ነቢያት የሚላቸው ልዩ ናቸውን ቢሉ ነቢያት ያላቸው ሳሉ የተናገሩት፡፡ መጻሕፍት የሚላቸው ከሞቱ በኋላ የተጻፉት ናቸው፡፡ ይህማ ሳሉ የተናገሩት ከሞቱ በኋላ ቢጻፍ ልዩ ነውን ብሎ ነቢያት የሚላቸው አድሮ ያናገራቸው፡፡ መጻሕፍት የሚላቸው በዘፈቀደ ታይቶ ያጻፋቸው ናቸው፡፡ ቅዱሳት ንጹሐት ክቡራት ሲል ነው፡፡ ርኩሳት መጻሕፍተ ጥንቆላ አሉና ከዚያ ሲለይ ንጹሐት አለ፡፡ ምኑናት መጻሕፍተ ደብዳቤ አሉና ከዚያ ሲለይ ክቡራት አለ፡፡
“ወመጽአ እም ዘርዐ ዳዊት በሥጋ ሰብእ”
በሥጋ ከዘርዐ ዳዊት ስለተወለደ ስለ ልጁ፤ የተወለደ የልጁን ነገር በኢሳይያስ “ትወጽእ በትር እምሥርዎ እሴይ  ወየዐርግ  ጽጌ እምጉንዱ” “ወይቀውም ሥርዎ እሴይ ወዘተወልደ እምኔሁ ይከውን ንጉሠ ለአሕዛብ“ ኢሳ 11÷1 እና 10፤ በዳዊት “ እስመ እምፍሬ ከርስከ አነብር ዲበ መንበርከ” መዝ 132÷1 ብሎ በነቢያት በመጻሕፍት ያናገረ የአብን ህግ ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ  ሐተታ ሥጋ እንስሳ አለና ከዚያ ሲለይ ሥጋ ሰብእ አለ፡፡ ምነው ዘርዐ ዳዊት ያለው አይበቃምን ቢሉ ነፍስን እንደነሣ ለማጠየቅ ፤ ያውስ ቢሆን “ዘርዐ አብርሐም አልዐለ” እንዲል (ዮሐንስ አፈወርቅ) ዘርዐ ዳዊት ያለው አይበቃምን ቢሉ  በከዊን ሲል ነው፡፡

“ወአርአየ ከመ ወልደ እግዚአብሔር በኃይሉ ወበመንፈሱ ቅዱስ”
“ዘተወልደ ወዘአርአየ” ብሎ ለወልድ ይቀጽላል፡፡ ኃይሉ ሕይወቱ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ከዘርዐ ዳዊት በመወለዱ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ ስላሳየ ፣ ስለ ልጁ ያሳየ፣ የልጁን ሕግ ወንጌልን ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ ሐተታ፡፡ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያስረዳልና፡፡ “ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኃራዊ ልደት”  እንዲል (ሃይማኖተ አበው ዘሱኑትዩ)  አንድም በኃይሉ በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና በመወለዱ ፡፡
“ወበመንፈሱ ቅዱስ” 
መንፈስ ቅዱስን በዮርዳኖስ በርግብ አምሳል በእራሱ ላይ በማኖሩ፡፡ “አሜሃ ስምዐ ኮነ መንፈስ በዮርዳኖስ ከመ ወልድ ዘበአማን ወአምላክ ዘበአማን” እንዲል ቄርሎስ አንድም በኃይሉ ሦስት አመት ሦስት ወር ባደረገው ተአምራት፡፡

ወበመንፈሱ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን በመስደዱ፡፡ አንድም፡ “ዘአቅደመ ወዘአርአየ” ብሎ ለአብ ይቀጽላል፡፡ “በኃይሉ ከመ ወልደ እግዚአብሔር አርአየ በመንፈስ ቅዱስ”  በባሕርዩ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ መንፈስ ቅዱስን በእራሱ ላይ በማኖሩ ያሳየ የልጁን ነገር፡፡ አንድም “በመንፈስ ቅዱስ ከመ ወልደ እግዚአብሔር አርአየ በኃይሉ” በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመወለዱ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ በግብሩ፣ በነገሩ አሳየ አለ፡፡  በነገሩ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ” ብሎ፡፡ በግብሩ መንፈስ ቅዱስን በርግብ አምሳል በእራሱ ላይ በማኖሩ ያሳየ የልጁን ነገር በኢሳይያስ “ቁልዔየ ፍቁርየ ዘሰምረቶ ነፍስየ ወአነብር መንፈስየ ላዕሌሁ ወየአርር መንፈሰ እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘበእንቲሁ ቀብዓኒ” ብሎ ያናገረ የአብን ሕግ ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ የተላከች ክታብ፡፡
5.  1ኛ ዮሐ 2÷22
“ወመኑ ውእቱ ሐሳዊ ዘእንበለ ዘይክህድ ወይብል እስመ ኢየሱስ ኢኮነ መሢሐ” ኢየሱስ መሢሕ አይደለም ከሚል ሰው በቀር የሚል ሰው ነው እንጅ ያለሱ ሐሰተኛ ማን ነው፡፡ አንድም ኅድረት ከሚል ከንስጥሮስ በቀር ሐሰተኛ ማነው የለም፡፡ ሐተታ ምነው ሥጋ አምላክ አይደለም ብሏል እንጅ፡፡ ቃል መሲሕ አይደለም ብሏልና እንዲህ አለ ቢሉ ቃልንስ መሢሕ ቢሆን ሥጋን አምላክ ባለ ነበር ቀንጃ ተዋሕዶን አለ፡፡
6.  1ኛ ዮሐ 5÷1
“ኩሉ ዘየአምን ከመ ኢየሱስ ውእቱ መሢሕ እምነ እግዚአብሔር ተወልደ” ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነ አለ ሥጋን እንደ ተዋሐደ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማረ፡፡ አንድም የተወለደ ነው፡፡ “ወኩሉ ዘያፈቅሮ ለወላዲ ያፈቅር ዘኒ ተወልደ እምኔሁ” ወላዲውን አብን የሚወደው ተወላዲውን ወልድን ይወደዋል፡፡ አንድም ወላዲውን ወልድን የሚወድ ተወላዲውን ምእመንን ይወዳል፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡