© መልካሙ በየነ
መጋቢት
27/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እኔ በጣም ደስ የሚለኝ ነገር አለ እርሱም በመጽሐፍ ላይ
ተመስርቶ መከራከር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን ምንም ወደማይጠቅም ስድብ እና እልህ ማምራት ይሆናል መንገዳችን፡፡ ይህ ደግሞ
ለማንም ለምንም የማይጠቅም ከንቱነት ነው፡፡ መቃወም ያለበት ሰው መቃወም ያለበት እኔን አይደለም የተጻፈውን ትምህርት ብቻ ነው፡፡
ይህንንም እኔ አደርገው እንደነበረው ሁሉ መጽሐፍ ይዘን መሆን አለበት፡፡ አንዳንዶች መጽሐፉ ሳይኖራቸው “ወልደ አብ” ላይ ተጽፎ
ስለተመለከቱት ብቻ ይጠቅሱታል፡፡ ነገር ግን ያ የተባለው ጥቅስ መጽሐፍ ላይ አይገኝም፡፡ ቄርሎስ እንዲህ አለባችሁሳ ስላቸው ይህ
እኮ በሥጋ ርስት ነው ይላሉ፡፡ ኤጲፋንዮስ እንዲህ አለባችሁሳ ስላቸው ደግሞ በባሕርይማ ሁሉም አንድ ናቸው ይላሉ፡፡ ብቻ እኔ የምላቸውን
ነገር ላለመቀበል ሲሸሹ ሲሸሹ እያየኋቸው ገደል ሲገቡ ተመለከትሁ እና አዘንሁ፡፡ በእውነት አንድ እውነት እስኪ እንመልከት፡፡
አብ ወላዲ አስራጺ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ
ብለን እናምናለን፡፡ እነርሱ ደግሞ ከዚህ በተጨማሪ ምን ይላሉ አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ፡፡ በስም በግብር በአካል
በገጽ ስንመለከት አብ አብን እንጅ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን አይሆንም፡፡ ወልድም ወልድን እንጅ አብን እና መንፈስ ቅዱስን አይሆንም፡፡
መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስን እንጅ አብን እና ወልድን አይሆንም፡፡ (አብ) አብ የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (ወልድ) ወልድ
ከተባለበት (መንፈስ ቅዱስም) መንፈስ ቅዱስ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ (ወልድ) ወልድ የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (አብ) አብ ከተባለበት (መንፈስ
ቅዱስም) መንፈስ ቅዱስ ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ (መንፈስ ቅዱስ) መንፈስ ቅዱስ የተባለበት ጥንት የሌለው ጊዜ፤ (አብ) አብ ከተባለበት (ወልድም) ወልድ
ከተባለበት ጥንት ከሌለው ጊዜ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ይህ ሦስትነት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የአካል መጠሪያ ስም ነው፡፡ አብ የራሱ የሆነ የተለየ አካል አለው ወልድም እንዲሁ
መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፡፡ የአካል መቀላቀል የአካል አንድ መሆን የአካል ተዋሕዶ የላቸውም “ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮቱ”
እንዲል፡፡ ስለዚህ በአብ ስም ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡ በወልድ ስምም አብ እና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም፡፡ በመንፈስ
ቅዱስ ስምም አብ እና ወልድ አይጠሩበትም፡፡ ምክንያቱም አካላቸው ለየራሳቸው ነውና አንድም በባሕርይ እንጅ በአካል አንድነት የላቸውምና
አንዱ በሌላኛው ስም አይጠሩበትም፡፡
ሌላው የአካል የግብር ሦስትነት ነው፡፡ ሥላሴ
በአካል ግብር ሦስትነት የየራሳቸው የሆነ ስም አላቸው፡፡ ይህም ወላዲ፤ ተወላዲ፤ ሰራጺ ነው፡፡ አብ ወላዲ ቢባል እንጅ እንደ ወልድ ተወላዲ እንደመንፈስ ቅዱስ ሰራጺ አይባልም፡፡
ወልድም ተወላዲ ቢባል እንጅ እንደ አብ ወላዲ እንደመንፈስ ቅዱስ ሰራጺ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ሰራጺ ቢባል እንጅ እንደ አብ
ወላዲ እንደ ወልድ ተወላዲ አይባልም፡፡ የአካል ግብር ስም አንዱ ለአንዱ አይሰጥም አንዱ በአንዱ አይጠራም፡፡ አብም ወላዲ ሲባል
ይኖራል ወልድም ተወላዲ ሲባል ይኖራል መንፈስ ቅዱስም ሰራጺ ሲባል ይኖራል እንጅ አንዱ ለአንዱ መጠሪያ አይሆንም፡፡ በአካል ግብር
ስም መቀላቀል እና መፋለስ የለባቸውም፡፡ ምንም እንኳ ሥላሴ በባሕርይ በአገዛዝ በሕልውና በመፍጠር በማሳለፍ አንድ ይሁኑ እንጅ
በወላዲነት በተወላዲነት በሰራጺነት ግን አንድ አይደሉም፡፡ በመለኮት በባሕርይ አንድ ናቸው ብለን አብ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ፤ ወልድ
ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ፤ መንፈስ ቅዱስ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ አንልም፡፡
በቅብዓት አስተምህሮ ውስጥ ግን እኛ የማንቀበለው
“አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚል የአካላት የግብር ስም አላቸው፡፡ ይህም የአካላት የግብር ስም አንዱ ለአንዱ
መሆን ይችላል፡፡ መፋለስ እና መቀላቀል አለበት፡፡ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይህ የሥላሴ የግብር ስም ተፋልሶ አለበት፡፡
በእርግጥ ወደዚህ ያመጣናቸው በክርክር ነው፡፡ ሲጀምሩ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ነበር ያሉን፡፡
ከዚያ ቄርሎስ
ስምዐት 124÷34 “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ
ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ …
ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር
መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው
እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ..” ይላልሳ፡፡ “ለሊሁ ቀባዒ” የተባለ ማንን ነው ስንላቸው ወልድን ነው አሉን፡፡ ታዲያ
“አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ለምን ትላላችሁ አልናቸው፡፡ እነርሱ ግን በባሕርይማ አንድ ናቸውና ሁሉም ቀባዒ
ናቸው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የምንል በሥጋ ርስት ብቻ ነው አሉ፡፡ ስለዚህ “አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ
ቀባዒ” ናቸው ይላሉ ብለን ደመደምን፡፡ ይህም በመለኮት አንድ ስለሆኑ ነው በሥጋ ደግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ
ቅብዕ” ነው ይላሉ፡፡ አስቡት ለሥላሴ አካል የግብር ስማቸው አንድነት አለው፡፡ ይህ ማለት አብ ቀባዒ መለኮት ወልድ ተቀባዒ መለኮት
መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ መለኮት በማለት የመለኮትን አንድነት ወደ ሦስትነት የሚከፍል አስተምህሮ ነው፡፡ ምክንያቱም “ቀባዒ ተቀባዒ
ቅብዕ” የሚለው የባሕርይ ግብራቸው አይደለምና፡፡ የባሕርይ ግብር ከሆነ በሥጋ ርስት በመለኮት ርስት በምንም ዓይነት ርስት ውሰዱት
አንድ ነው አይለወጥም አይቀየርምም፡፡ እነርሱ ግን በመለኮት ርስት ሁሉም “ቀባዒ” ናቸው በሥጋ ርስት ድግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ
ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ናቸው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ!!! ቀባዒ መለኮት አብ በሥጋ ርስት ቀባዒ ሆነ፤ ቀባዒ መለኮት
ወልድ በሥጋ ርስት ተቀባዒ ሆነ፣ ቀባዒ መለኮት መንፈስ ቅዱስ በሥጋ ርስት ቅብዕ ሆነ ማለታቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሐሰት ክህደትም
ነው፡፡ “ቅብዕ” ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙ “ክብር” ማለት ነውና፡፡ አብ ቀባዒ ሲሉ አብ አክባሪ ወልድ ተቀባዒ ሲሉ ወልድ ተከባሪ
መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሲሉ መንፈስ ቅዱስ ክብር ሆኑ ማለት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ስም የአካል ስም ነው፡፡ ታዲያ
በአካል አንዱ አክባሪ አንዱ ከባሪ አንዱ ክብር ይሆን ዘንድ ይህን ክህደት ማን አስተማራችሁ ብለን እንጠይቃቸው፡፡
ከዚህ ስህተታቸው የምንረዳው ነገር የሚከተለውን
ነው፡፡
1.
የአካላት ግብር ስም ሁለት ጊዜ እንደተሰጣቸው ነው፡፡ ዘመን ሳይቆጠር ቀድሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ
ቅዱስ ቀባዒ” ነበር ማለት ነው፡፡
2.
ድኅረ ዓለም ወልድ በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ደግሞ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ”
ሆኑ ማለት ነው፡፡
3.
ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ምእራፍ 2 ቁጥር 154 ላይ “ለአጽንዖተ ክልዔሆሙ፤ አብን መንፈስ ቅዱስን በጥንተ
ስማቸው ለማስጠራት በጥንተ ግብራቸው ለማጽናት” የሚለው ትምህርት ተቀባይነትን አላገኘም ማለት ነው፡፡
4.
አብ ከቀባዒነት ወደ ቀባዒነት፤ ወልድ ከቀባዒነት ወደ ተቀባዒነት፤ መንፈስ ቅዱስ ከቀባዒነት ወደ ቅብዕነት
እንደተለወጡ የሚያሳይ መሆኑ፡፡
ስለዚህ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ
ቅዱስ ቅብዕ” የሚለው የግብር ስም በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ተቀባይነት የሌለው ከንቱ ፍልስፍና ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ
ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ብለን አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንዲህ እናምናለን፡፡ እንዲህም እንታመናለን፡፡
ቃል ሥጋን በተዋሐደበት ጊዜ ረቂቅ በሆነ
ጥበብ ሥጋ አምላክ ሆኗል፡፡ አምላክ ሰው ሆነ ፤ ሰውም አምላክ ሆነ ማለት ስለዚህ ነው፡፡ “ተዋሕዶ ክብርን አያሳልፍም” የሚለው
ፍልስፍና ግን ሊቁ ቄርሎስ በመሰለው የጋለ ብረት ተሸንፏል፡፡ ሥጋን ከበረ ማለታችን “ሥጋ አምላክ ሆነ” ለማለት ብቻ የሚነገር
መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ከተዋሕዶ በኋላ “ሥግው ቃልን፤
ኢየሱስ ክርስቶስን” አክባሪው ማነው ተከባሪውስ ማነው እያልን አንድነትን ከፍለን ልንጠይቅ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም በሥጋው ከበረ
ስንል በመለኮቱ ንድየት አደረበት ማለት ስለሆነ ይህ ክህደት ነው፡፡
ከመጻሕፍት ለመሸሽ ሲሞክሩ ራሳቸውን ወደ
ጉድጓድ ወረወሩ የምላችሁም ለዚሁ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ትምህርተ መለኮትን የማያፋልስ “ይህ ቃል ምን ተብሎ ቢተረጎም ነው”
ማለት አለብን፡፡ ያማ ካልሆነ ሁላችን “መናፍቅ” የምንሆንበትን ጥቅስ በመሰብሰብ መጥፋታችን አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ውዳሴ ማርያም
ላይ ብዙ ቦታ “ኃደረ ውስተ ከርስኪ” የሚል ቃል አለ፡፡ ይህንን ቃል ይዘን “ኅድረት” ልንል ግን አይገባንም “ኃደረ” ያለውን “ተዋሐደ” ብለን
እንተረጉማለን እንጅ፡፡ “ቃል ሥጋ ኮነ” የሚለውንም የወንጌል ቃል ይዘን “ተለወጠ” ልንል አይገባንም፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ በአግባቡ
ካልተተረጎመ በጥሬው ከተመለከትነውና በራሳችን ፈቃድ ከተረጎምነው ክህደት አይደለምን ነው እንጅ፡፡ አሁን የሚሻለን የቀደሙ አባቶቻችን
ከዕብራይስጥ፤ ከጽርእ፤ ከዐረብኛ ወዘተ ወደ ግእዝ የመለሱልን እንዴት ነው አባቶቻችንንስ ግእዙን ወደ አማርኛ የመለሱት እንዴት
ነው፡፡ አንድምታውንስ እንዴት ነው ያመሠጠሩት ብለን በትህትና መጻሕፍትን መመልከት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሊቃውንቱን በመዝለፍ
የሚሰጥ እና የሚታደል ጸጋ እግዚአብሔር የለም፡፡ አንድ ሰው (ገብረ መድኅን እንዳለውን ማለቴ ነው) በጻፈው ልብ ወለድ የፈጠራ
ጽሑፍ (ወልደ አብ) ላይ ተመሥርተው ያንን ደጋግሞ ማነብነብ ከንቱነት ነው፡፡ “እውነቱን መርምሩ የሚበጀውንም ያዙ” የሚለውን ጠቃሚ
ትምህርት እንጠቀምበት፡፡
በመጨረሻም!!! ዛሬ መጋቢት 27 ጥንተ ስቅለት ነው፡፡
ዘንድሮ 2009 ግን ስቅለት የሚከበረው ሚያዝያ 6 ነው ታዲያ ልደት ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ ታህሳስ 28 ለምን ተከበረ የምትሉ
ወገኖች ስቅለት ለምን ጥንተ ቀኑን ለቀቀ ብላችሁ ጠይቁ እስኪ፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment