Thursday, April 6, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ (ተፈጸመ)---ክፍል ፲፱


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 29/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እስካሁን ድረስ በዚህ ርእስ ዐሥራ ስምንት ያህል ክፍሎችን ተመልክተናል፡፡ ይህን መጻፍ ያስፈለገኝ የቅብዓትን አስተምህሮ ማወቅ ለሚፈልግ ሰው ሁሉ እንዲብራራለት እና መጥፋት ቢፈልግ እንኳ ሳያውቅ እንዳይጠፋ በማሰብ ነው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በግቢ ጉባዔያት ውስጥ ተማሪዎችን በመረበሽ ትምህርቱ እንዲስተጓጎል በድብቅ በመደራጀት በእልህ የሚንቀሳቀሱ ተማሪዎች በመኖራቸው የተነሣ የተረበሹ ተማሪዎች የቅብዓትን እና የተዋሕዶን ልዩነቱን አስረዳን በማለታቸው እነርሱ እውነታውን ይዘው እንዲጸኑ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ ይህን ያደረግሁት ግን እግዚአብሔር በሚያውቀው ለስድብ እና ለዛቻ አልያም እልህ ይዞኝ አይደለም አዋቂ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ብየም አይደለም ይህን ለማድረግ የተመቻቸ ሁኔታ ስላለኝ እንጅ ስንት ሊቃውንት ያሉባት ቤተክርስቲናችን ለዚህ ከንቱ ትምህርት መልስ መስጠት አቅቷቸው እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ ምናልባትም ዘንድሮ ባይሆንም በቀጣይ ዓመት “ይህ መጽሐፍ በሲኖዶስ ተወግዞ ተገቢውን ምላሽም እንደሚያገኝ” ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ “ጎጃም ውስጥ በተለይም በለየናቸው ጥቂት አካባቢዎች” እየተዘራ ያለው ይህ “ምንፍቅና” እንደሚያከትምለትም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን በቅርብ ቀን ስላሳተሙት “ዝክሪ እና ጳውሊ” መጽሐፉ እንደደረሰን የምንመለስበት ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ “አይዞህ ባይ” ያላቸው እንደሆነ ብናውቅም እግዚአብሔር ካልፈቀደ አንዳች አይደረግምና ዝም ማለትን እንመርጣለን፡፡ አንድም እነዚህ መጻሕፍት በመውጣታቸው ደስ ይለኛል፡፡ አቶ ዘመንፈስ የተባለ መናፍቅ “ተግሳጽና ምክር” በሚል መጽሐፍ ምንፍቅናውን ባይገልጥ ኖሮ ድንቅ የሆነው መጽሐፍ “ኰኲሐ ሃይማኖት” ታትሞ ባላየነው ነበር፡፡ ዳግመኛም ዶ.ር አባ አየለ ተክለሃይማኖት የተባለ ካቶሊካዊ መነኩሴ “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባሕርያት የምታምነው ትምህርት” ብሎ ክህደትን ባይጽፍ ኖሮ “መድሎተ አሚንን” ያህል መጽሐፍ ባላገኘንም ነበር፡፡ ዛሬም የእነዚህን መጻሕፍት መውጣት ተከትሎ ምናልባትም “መልአከ ብርሃናት” ቢነሡ ድንቅ ድንቅ መጻሕፍትን እንመለከትባቸው ይሆናልና በመውጣታቸው ደስ ይለኛል፡፡
********************************************************************************************
ማጠቃለያ፡- በመጨረሻም እነዚህን ክፍሎች ስጽፍ በውስጥ መስመር ለጠየቃችሁኝ ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ፡፡
1.  በቅብዓት ካህን ክርስትና የተነሣ ሰው መጠመቅ አለበት የለበትም ለሚለው ጥያቄ መልሴ መጠመቅ አለበት የሚል ነው፡፡
2.  ጥምቀት አንዲት ናት ለምን ተጠመቁ ትላለህ ላላችሁኝ፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 3 ቁጥር 24 ላይ “ወለእመቦ ብእሲ ዘተወክፈ ጥምቀተ እምዓላውያን ኢኮነ ምእመነ፤  ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም” ይላል እላለሁ፡፡ ስለዚህ ከቅብዓት ካህናት ጥምቀትን የተጠመቀ ሰው አማኒ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ከቅብዓት ካህናት የተጠመቀው ጥምቀት አይቆጠርም ማለት ነው፡፡ ካልተቆጠረ ደግሞ ጥምቀት አንዲት ናት የሚለው አይሻርም፡፡
3.  በልጅነት ጥምቀቱ አምነን እንጠመቃለን ግን የምንኖርበት አካባቢ ቅብዓቶች ይበዙበታል እንዴት መኖር እንችላለን ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ይኼ አያሳስባችሁ ይልቁንስ ተጠመቁ እና የጠመቃችሁን አባት አማክሩ መፍትሔ እዚያ ታገኛላችሁ፡፡
4.  የቅብዓት ቤተክርስቲን የለም ሁሉም የተዋሕዶ ቤተክርስቲን ናቸው ታዲያ ካህኑ ምንም ሆነ ምን እዚያ መቁረብ መጠመቅ ምን ችግር አለው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ይህ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የተዋሕዶ ናት ብለህ አንተ መቅደስ ገብተህ ቀድሰህ ማቁረብ ትችላለህን ብየ እጠይቅሃለሁ፡፡ ይህንንም ተወውና መቸም የእኛ ቤተክርስቲያን ናት ብለህ አንድ ሙስሊም ቀድሶ ላቁርብህ ቢልህ ጥምቀትንም አጠምቃለሁ ቢል እውነት ነው ብለህ ትቀበለዋለህን፡፡
5.  እኔ ቤተሰቦቼ ቅብዓቶች ናቸው እኔ ግን የምጾምም የምቆርብም እንደተዋሕዶዎች ነው፡፡ በቃ ሙሉ በሙሉ ተዋሕዶ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛዋ እምነት ተዋሕዶ እንደሆነች ስላመንሁ፡፡ ታዲያ በ40 ቀኔ የተነሣሁት ክርስትና የተጠመቅሁት ጥምቀት በቂ አይደለምን፡፡ ባልጠመቅስ ምን ችግር አለው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል ማር 16÷16” አንተ ያመነ የሚለውን እንጅ የተጠመቀ የሚለውን አላሟላህምና ይፈረድብሃል፡፡ ምግባር ትሩፋት መሥራት ከማመን ከመጠመቅ በኋላ ነው፡፡
6.  የቅብዓት ካህናትን መስቀል ብሳለም ምን ችግር አለው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ሳታውቁ ካደረጋችሁት ችግር የለውም ግን አይጠቅምም እላለሁ፡፡ መስቀሉ መስቀል የሚሆነው መስቀሉን መያዝ የሚገባው ሰው ከያዘው ብቻ ነው፡፡ ገባችሁ አባባሌ! እስላሙ መስቀል ይዞ ላሳልምህ ቢለኝ አልሳለምም ምክንያቱም እንጨት እንደመሳም ይቆጠራልና፡፡ “ይፍቱኝ አባቴ” የምለውስ እርሱ ከታሰርኩበት የኃጢአት ሰንሰለት መፍታት ይቻለዋልን እርሱ ራሱ “እሡር፤ የታሠረ” አይደለምን ነው፡፡
7.  ከቅብዓት አማኞች ጋር መብላት መጠጣት ኃጢአት ነውን ላላችሁኝ፡፡ መልሴ እርሱን የንስሐ አባቶቻችሁን አማክሩ እላለሁ፡፡ ይህን የጠየቃችሁኝ እኮ አብረውን ስላደጉ ብቻ ሳይሆን በአንድ ቤተክርስቲያን ስለምንጠቀም ጭምር እንጅ የለየላቸውን መናፍቃንን እና አህዛብን በተመለከተ ይህን አትጠይቁም ነበር፡፡ ከእስላም ከካቶሊክ ከፕሮቴስታንት አማኞች ጋር እንዴት ነው የምናደርገው ልክ እንደዚያ ብናደርግ እላለሁ እንደኔ፡፡ ነገር ግን በእልህ እና በትእቢት አናድርገው፡፡
8.  ቤተክርስቲያኒቱ የእኛ ናት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን” ነው የምትባል ታዲያ እነዚህ ቅባቶች እዚህ ውስጥ ምን ይሠራሉ ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ጥገኝነት ቢያስደስታቸው እኛም ቤታችንን ማጽዳት የማንችል ደካሞች ስለሆንን ነው እላለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ በ1990ዎቹ አካባቢ ለፍትሕ ሚኒስቴር “እኛ መገንጠል እንፈልጋለን” ብለው አመልክተው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በሉ እንግዳውስ ቤተክርስቲያናችን የእኛ ናት እናንተ ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ ውጡ ሲባሉ መውደቂያ ቦታ መጠጊያ ታዛ ቢያጡ ዝም አሉ ረገቡ፡፡ ከዚያም በየገዳማቱ ወድቀው ምንፍቅናቸውን መዝራት ጀመሩ፡፡ ድሮ በድብቅ ነበር ዛሬ ግን መጽሐፍ እስከመጻፍ የደረሰ ድፍረት እና ወኔ አገኙ፡፡
9.  የቅብዓት ካህናት ሥልጣነ ክህነት የሚቀበሉት ከማን ነው ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ክህነት የሚቀበሉት ከእኛ ጳጳሳት ነው፡፡ ለዚህም እኮ ነው ስልጣነ ክህነት የላቸውም የምንለው፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ የሚል ሰው መናፍቅ ነው” እያሉ እየተሳደቡ “ክህነት ለማምጣት ሲሉ ግን በተዋሕዶ ከበረ ብለው በጳጳሱ ፊት በውሸት ይመሠክራሉ” ታዲያ መንፈስ ቅዱስ በውሸት ይወሰዳልን አይወሰድም፡፡ ስለዚህም ስልጣነ ክህነት የላቸው ብለን እንናገራለን፡፡
10. የንስሐ አባቴ የቅብዓት ካህን ነው ምን ላድርግ ላላችሁኝ፡፡ መልሴ ክህነት የለውምና የንስሐ አባት ሊሆን አይችልም፡፡ የንስሐ አባታችሁ እንዲሆን ካስፈለገ ግን በተዋሕዶ ይመን እና የልጅነት ጥምቀትን ይጠመቅ፡፡ ስለዚህ የንስሐ አባት አታድርጉት ምክንያቱም እርሱ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ብላ ከምታስተምር ቤተክርስቲናችን ኅብረት አንድነት የለውምና፡፡
11.  ተዋሕዶ ትክክለኛ እንደሆነች አውቃለሁ ነገር ግን የአባቴ እና የእናቴን እምነት አልቀይርም ላላችሁኝ፡፡ መልሴ እርሱ መብታችሁ ነው እላለሁ፡፡ እምነት አምላክ ለፈቀደለት እንጅ ላልፈቀደለት አይሰጥምና አምላክ ፈቃዱ ይሁንላችሁ እላለሁ፡፡ ነገር ግን አባት እና እናቱ እንጨት ጠርበው ደንጊያ አለዝበው ያመልኩ የነበሩት አብርሃም እናት እና አባቱን ትቶ እግዚአብሔርን እንደተከተለ እነግራችኋለሁ፡፡ እምነት ላይ የእናቴ የአባቴ የሚባል ነገር የለም፡፡ አውቀህ ተረድተህ የምትጓዝበት መንገድ ነው እንጅ፡፡
12. ልደት ታህሳስ 28 የምታከብሩ ለምንድን ነው፡፡ ጌታ የተወለደው በ29 አይደለምን ላላችሁኝ፡፡ ትክክል ናችሁ ጌታ የተወለደው ታህሳስ 29 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን በዓሉ ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ገና ታህሳስ 28 ይከበራል ይኸውም ሥርዓት ቀኖና ስለተሠራለት ነው፡፡ ይህ በዓሉን የምናከብርበት ዕለት እና ቀን እንጅ በየዓመቱ ይወለዳል ማለት አይደለም፡፡ ታዲያ ልደቱ ታህሳስ 28 ቀርቶ መስከረም 1 ቀን ይከበር ቢባልስ አናደርገውም ነበርን እናደርገው እናከብረው ነበር፡፡
13. ልደት በ1 ቀን ቀድሞ ከተከበረ ለምን ግዝረት ጥምቀት በአንድ በአንድ ቀን ቀድመው አይከበሩም ላላችሁ፡፡ መልሴ ሥርዓት ቀኖና ለተሠራለት ብቻ ሥርዓቱን ቀኖናውን ጠብቀን እናከብራለን፡፡ ይህ ደግሞ መሠረተ እምነት አይደለምና አያጨቃጭቅም፡፡ ይህን ለመጠየቅ በመጀመሪያ በተዋሕዶ ማመን አለብን፡፡ ነገር ግን አመናችሁም አላመናችሁም ዶግማ እና ቀኖና ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ እንድትረዱ አሳስባችኋለሁ፡፡ ለምሳሌ ጥንተ ስቅለቱ ዐርብ ዕለት መጋቢት 27 ነው፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ስቅለትን የምናከብረው ዐርብ ሚያዝያ 6/2009 ዓ.ም ነው ይህ ለምን ሆነ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ዐርብ ስላልቀቀ ትክክል ነው ብላችሁ ከተቀበላችሁት ግን በዓመቱ ውስጥ (በ2009 ዓ.ም) ስንት ዐርቦች አሉ ብለን እንጠይቃችኋለን፡፡
**************************************************************************************************
በመጨረሻም ያላችሁን ማንኛውንም ዓይነት አስተያየት፣ ጥያቄ በሚከተሉት አድራሻዎች ማድረስ ትችላላችሁ፡፡
ኢሜይል፡ melkamuby@gmail.com
በፌስ ቡክ ገጼ፡ facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid
እስካሁን ያስተላለፍኳቸውን ትምህርቶችንም በዚሁ ድረ ገጽ ላይ ያገኙታል፡፡
***************************************************************************************
በሰፊው ለማንበብ ሃይማኖተ አበውን እና መድሎተ አሚንን አንብቡ!!!
**************************************************************************************
መልካም ሰሙነ ሕማማት ይሁንልን፡፡ ይህ ሳምንት የመጨረሻችን በረከቱን የምንቀበልበት ነውና አብዝተን ልንጾም ልንጸልይ ይገባል፡፡ አምላካችን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም በፍቅር በአንድነት በኅብረት ያድርሰን፡፡ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” በምትለው የሐዋርት እምነት ያጽናን፡፡ ለተሳሳቱት ሁሉ ቀናውን መንገድ አሳይቶ በቸርነቱ ይመልስልን፡፡ አሜን ወአሜን፡፡ ለይኩን ለይኩን፡፡
*******************************************************************************************
ከትንሣኤ በኋላ በሌሎች ትምህርቶች እንገናኛለን እስከዚያው ድረስ ቸርነቱ ይጠብቀን ረድኤት በረከቱ አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ተፈጸመ፡፡

No comments:

Post a Comment