Wednesday, April 5, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ ---ክፍል ፲፰


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 28/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በተለይም መተርጉማኑን በመንቀፍ እና የማይገባ ስም በመለጠፍ እነርሱ ሊቅ የሆኑ የሚመስላቸው አንዳንድ “ለጋ ቅባቶች” በራሳቸው መንገድ መጻሕፍትን ሲተረጉሙ ስመለከት አዝናለሁ፡፡ በእውነት ለእልህና ለንትርክ ከሆነ እኮ ሁላችንም አንተማመንም መቼም ቢሆን አንግባባም፡፡ እነርሱ የሚያነሧቸውን የተወሰኑትን ክፍሎች ጠቅለል አድርገን እንመልከታቸው እስኪ፡፡
“እግዚአብሔር” ማለት እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው ብለው ይተረጉማሉ፡፡ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አግዚአብሔር እንደሚባሉ አይረዱም፡፡ በዚህም የተነሣ “እግዚአብሔር ይቤለኒ” ፤ “ዘቀብኦ እግዚአብሔር መንፈሰ ቅዱሰ ወኃይለ”፤ “መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ ወአስተፍስሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ”፤ “በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ” ወዘተ የሚሉ ዐረፍተ ነገሮችን ሲተረጉሙ “እግዚአብሔር” የሚለው ለአብ ብቻ እንደሆነ አድርገው ነው፡፡ በዚህ ትርጓሜ ደግሞ መስማማት ይከብዳል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ምእ 96÷6 ላይ ነባቤ መለኮት ጎርጎርዮስ የተናገረውን ወስዶ  “አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ ስለ አብ ስለ ወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ” ብሏል ፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ እግዚአብሔር ሲል “አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ” ማለቱ እንደሆነ ማወቅና መረዳት አለብን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በመለኮት በባሕርይ በአገዛዝ በመፍጠር በማሳለፍ አንድ ነው፡፡ ከላይ ባነሣናቸው ጥቅሶች ውስጥ ያለውን “እግዚአብሔር” የሚለውን ቃል ሊቃውንቱ ሲተረጉሙት “እግዚአብሔርነትህ” ብለው ነው፡፡ ምክንያቱም ተለይቶ ለአብ የተጻፈ አይደለምና፡፡ ለምሳሌ “በእንተዝ ቀብአከ እግዚአብሔር አምላክከ” የሚለውን  የዳዊት መዝሙር ይዘን “እግዚአብሔር” የሚለው የአብ ልዩ ስም አድርገን ከተረጎምነው ወደ ክህደት እንደምንገባ አስተውሉ፡፡ “እግዚአብሔር አምላክከ” ሲል ምን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ አምላክህ ብለህ ልንተረጉመው ነውን፡፡ በፍጹም አይደለም! ሊቃውንቱ ይህን ደስ በሚል መልኩ የጠመመውን አቅንተው የጎደለውን መልተው ተርጉመውታል፡፡ ሙሉ ትርጓሜውን በክፍል ፲፮ ተመልክተነዋል፡፡ እዚህ ላይ ማንሣት የምሻው “እግዚአብሔር አምላክከ” የሚለውን ቃል ትርጉም ብቻ ነው፡፡ ሊቃውንቱ “እግዚአብሔርናከ አምላክናከ፤ እግዚአብሔርነትህ አምላክነትህ” ብለው ተርጉመውታል፡፡ ታዲያ “እግዚአብሔር” የሚለው ለአብ ልዩ መጠሪያ የምናደርገው በምን መልኩ ነው፡፡
ልብ ማለት ያለብን ነገር ምንድን ነው ለ “አብ” የሚነገሩ ነገሮች በስም ተለይተው እንደሚቀመጡ ነው፡፡ ይህም ማለት በሥላሴ ዘንድ የአካል ሦስትነት የባሕርይ አንድነት አለ፡፡ በባሕርይ ግብራቸው አንድ ሲሆኑ በአካል ግብራቸው ግን ይለያያሉ፡፡ የአብ አካል ግብሩ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ አካል ግብር የተለየ ነው፡፡ የወልድም እንዲሁ የመንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ የአካል ግብራቸው የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ወልድ በተለየ አካሉ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ የምወደው የምወልደው ልጅ እርሱ ነው አለ፡፡ በመለኮታዊ ግብራቸው ግን አንድ ናቸውና አንዱ በሌላው ሊጠሩበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ  “ፈጣሪየ ኢየሱስ ክርስቶስ” ስንል አብ እና መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪያችን አይደሉም ብለን አይደለም፡፡ በመለኮታዊ ግብራቸው አንድ ስለሆኑ አብ ስንል ወልድን መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው፡፡ ወልድ ስንልም አብን መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስንልም አብን ወልድን ማለታችን ነው፡፡ ለምሳሌ ሐዋ 9÷5 ላይ ሳውልን “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ” አለው፡፡ ይህን ማለቱ “ኢየሱስ ክርስቶስን” ስላሳደደው ሳይሆን “በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት የሚያምኑ ክርስቲያኖችን ስላሳደደ” ነበር፡፡ በአምላክነት በመመለክ አንድ ናቸውና ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው እንጅ ለአብ ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ ስም አይደለም፡፡ መጻሕፍትንም ስንተረጉም በዚሁ መንገድ ነው እንጅ “እግዚአብሔር” የሚለውን ሁሉ በመጠቅለል ለአብ ብቻ እየሰጠን አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሐዋርያው ጴጥሮስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” ማለቱ በባሕርይ ግብራቸው አንድ መሆናቸውን ለማሳየት እንጅ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ” ብሎ ያዘዘውን ትእዛዝ መጣሱ አይደለም፡፡ በመለኮታዊ ግብራቸው አንድ ስለሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲል በአብ በራሱ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማለቱ ነው፡፡  እንዲህ ንባብን ከምሥጢር ጋር ካላስማማነው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል “የብረት ቆሎ” ነው ልቆርጥምህ ብትለው ጥርስህ ይሰበራል እንጅ ቆሎ ሆኖ አይቆረጠምልህም፡፡ ስለዚህ እልሁን እና ትእቢቱን ትተን በፍቅር እና በትህትና ሆነን እስኪ መጻሕፍትን እናንብብ ሊቃውንቱን እንጠይቅ፡፡ በሱባዔ የሚመለሰውን ደግሞ በጾም በጸሎት እንጠይቅ፡፡ እምነት ከእግዚአብሔር ሲሰጥ እንጅ በራሳችን አንዳች ነገር አናደርግም፡፡ እምነት ለተመረጠ ሰው፤ አምላክ ለመረጠው ሰው ለእርሱ ብቻ የሚረዳ ምሥጢር ነው፡፡
ትርጓሜን ለራሳችን ካደረግን መናፍቅ ከሀዲ ለመሆን ሮሜ 8÷34 ብቻ በቂ ነው፡፡ እርሱን ማስፋት ይቻላል፡፡ “ስለእኛ የሚማልደው” በሚለው ቃል ስንቶች እንደጠፉ አታውቁምን፡፡ ታዲያ ለመጥፋት ጥቅስ መጥቀስ ያስፈልጋልን፡፡ መጥፋት የሚሻ ሰው ያለጥቅስ መጥፋት ይችላል፡፡ ለመጥፋት ለምን ምክንያት እንፈልጋለን፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment