Wednesday, May 24, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፰



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 17/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

፲ኛ አንቀጽ
ለሥላሴ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ እንደሌላቸው ይናገራል፡፡
ጥያቄ:- ለሥላሴ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ አለው ካልተባለ፣ አካለ ጎደሎ ያሰኛል እንጂ፣ በአካል ፍጹማን ያሰኛልን? መልስ:- ልብ ቃል እስትንፋስ በአካል ሕልው ሆኖ ለአካል ሕይወት የሚሆን የባሕርይ ከዊን ነው እንጂ፣ እርሱ እራሱ እንደ ዓይንና እንደ ጀሮ፣ እንደ አፍና እንደ አፍንጫ፣ እንደ እጅና እንደ እግር በቅርጽ የሚለይ አካል አይደለምና አካለ ጎደሎ አያሰኝም:: ይህንም ሌላ ምስክር ሳንፈልግ በራሳችን ሕላዌ እናስረዳለን:: ሰው በሞተ ጊዜ ልቡና ቃሉ እስትንፋሱ ይለዩታል፤ በአካል ያለው ሕይወት ስለተለየው እገሌ ሞተ ይባላል እንጂ አካሉ ጎደለ አይባልም:: አካሉም ከፍጹምነቱ ሳይጎድል በአልጋ ላይ ተኝቶ ይታያል:: ኋላም በመግነዝ ተይዞ ፍጹም አካሉ ወደ መቃብር ይወርዳል:: ኋላም በትንሣኤ ዘጉባኤ ነፍሱ ካለችበት መጥታ ስታድርበት፣ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ያለው ሕያው ሆኖ ይነሣል:: ማስረጃ:- ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው:- ንባብ:- `በቀዳሚ ንፍሐተ ቀርን ይትጋባእ ፀበለ ሥጋ ዘተዘርወ፤ ወበዳግም ንፍሐተ ቀርን ይሰፊያ አዕፅምት ምስለ ሥጋ፤ ወይከውን በድነ ፍጹመ ዘእንበለ አንሰሕስሆ፣ በሣልስ ንፍሐተ ቀርን ይትነሥኡ ሙታን ከመቅጽበተ ዓይን” ትርጉም:- “በመጀመሪያው አዋጅ ተለያቶ ተበትኖ የነበረ አጥንትና ሥጋ ይሰበሰባል፤ በሁለተኛው አዋጅ አጥንት ከሥጋ ጋር ተያይዞ የማይንቀሳቀስ ፍጹም አካል ያለው በድን ይሆናል፤ በሦስተኛው አዋጅ ሙታን እንደ ዓይን ቅጽበት ይነሣሉ” እንዳለ:: (ሐዳፌ ነፍስ) እንዲህ ከሆነ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ በነፍስ አካል ያለ በሥጋ ሕይወት የሚሆን የባሕርይ ከዊን ነው እንጂ፤ እርሱ እራሱ አካል እንዳይደለ ይታወቃል:: “የእርሱስ አካል የነፍስ አካል ነው”  በማለት አንዳንድ ሰዎች የተሳሳቱበትን ምክንያት በሚከተለው መስመር ገልጠን እናሳያለን:: በሥጋ አካል ከደረት በታች ከሆድ በላይ ልብ የተባለ ሥጋዊ አካል አለና፣ በዚህ ምክንያት ልብ አካል ነው ይላሉ፤ ልብ የተባለበትን ምሥጢሩን ግን አልተረዱትም፤ ልብ ማለት የነፍስ ስም ነው:: ማስረጃ ዮሐንስ አፈወርቅ:- ንባብ:- “እስመ ነፍስ ትሰመይ ልበ ወልቡና” ትርጉም:- “ነፍስ ልብ ልቡና ትባላለች” ብሏል:: /ድርሳን ፪ኛ/ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያም አስራ አንደኛ:- ንባብ:- “ወልቡ ለብእሲ መንፈሱ ወውእቱ ፩ ምስለ ነፍሱ እንተ ሃለወት በሥጋሁ::” ትርጉም:- “የሰው ልቡ ነፍሱ ነው ይኸውም በሥጋው ካለች ነፍሱ ጋራ አንድ ነው” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩)  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፳፭ ቁ. ፳፮ እንዲህ የተባለች ነፍስ ተዋሕዶ ዕውቀትዋን ስለሣለችበት “በስመ ኅዳሪ ይጸዋዕ ማኅደር” እንደተባለ ማኅደር በኀዳሪው ስም መጠራት ልማድ ነውና፣ በማኅደርነቱ ልብ ተብሏል እንጅ፣ ልብ መባል የራሱ ስም አይደለም:: እርሱስ እንደ ሳንባና ጉበት ያለ አካል ነው:: አንዳንድ ሰዎች የነፍስ የዕውቀቷ ሰሌዳ የሆነ ይህ አካል ልብ በመባሉ ተሳስተው በየራሳቸው ልብ የሚባል አካል ከሌላቸው፣ ሥላሴ በአካል ፍጹማን አይባሉም እያሉ የስህተት ቃል ይናገራሉ፤ ይልቁንም በልብ አስጠግተው ምክንያት የሌላቸውን ቃልንና እስትንፋስን እንደ አካል አድርገው “በየራሳቸው ቃል፣ እስትንፋስ ከሌላቸው አካለ ጎደሎ ያሰኛል” ማለታቸውን አስተዋይ ልቡና ያለው ሰው እውነት ብሎ ሊቀበለው የማይቻል ነው::
፲፩ኛ አንቀጽ
መለኮት ከአካል የማይለይ አንድ ሲሆን፣ ወልድ ሰው ሆነ በተባለ ጊዜ፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ይናገራል፡፡
መለኮት ከአካል የማይለይ አንድ ነው ብለን፣ ወልድ ሰው ሆነ ስንል፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር በምትባል ጥበብ ሆነን፣ የረቀቀውን በማጉላት፣ የጎደለውን ለመሙላት እየመረመርን፣ መላልሰን እናስረዳለን:: ለሥላሴ በግብር የሚጠሩባት ባሕርይ የምትባል አሐቲ ጠባይዕ አለቻቸው፤ ግብሯም ሕይወትነት ነው:: ነገሩን ኋላ በአሥራ ሁለተኛው አንቀጽ እናመጣዋለን:: የዚህችም ጠባይ ጥንታዊና መሠረታዊ የሚሆን ስምዋ ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የማይችል ነው:: አለመቻሉንም ሲአስረዳ ዮሐንስ አፈወርቅ በ፪ኛው ድርሳኑ:- ንባብ:- “እስመ ሶበ ኢረከበ ስመ ዘይኤምር ኀበ ባሕርይሁ ብህለ በዝንቱ አስማት፤ እስመ ኢዕበይ ወኢስብሐት ይኤምሩ ኀበ ውእቱ ስም ዘፈቀደ ይዝክሮ፤ ወባህቱ ስእነ ረኪቦቶ በከመ እቤ ቀዳሚ ከመ ንሕነ ንኄሊ በእንተ ብዙኀ ግብራቲሁ ወንስዕን ፈክሮ ወነጊረ በእንቲአሁ፤ እወ ካዕበ ወኢ ዝስም ዘውእቱ እግዚአብሔር ኢይኤምር እንከ ኀበ ውእቱ ባሕርይ፣ ወፍጹመ ኢይትከሀል ይርከቡ ስሞ ለዝኩ ባሕርይ፤ ኢታንክር ኦ ፍቁር በእንተ ዝንቱ፤ ኅድግሰ ባሕርየ እግዚአብሔር ልዑል፤ ለመልአክኒ ጥቀ ኢይትረከብ ስመ ባሕርይሁ:: ወበእንተ ነፍስኒ ከማሁ ይመስለኒ፤ እስመ ብሂለ ነፍስ ኢይኤምር ኀበ ስመ ባሕርይሃ፤ … ወአልቦ እንከ ስም ዘይትአወቅ ለባሕርይሃ” ትርጉም:- “ባሕርዩን የሚያስረዳ ስም ባያገኝ፣ ዕበይ ስብሐት በማለት የባሕርይ ስሙን ተናገረ:: ዕበይ ስብሐት ማለት ሊናገረው የወደደውን የባሕርይ ስሙን ምንም ባያስረዳ አስቀድሜ እንደተናገርሁ እኛ ብዙውን ሥራውን እንድንመረምር ሥራውን ተረድተን መናገርም እንዳይቻለን የባሕርይ ስሙን ማግኘት ባይቻለው ይህን ተናገረ እንጅ:: ዳግመኛም ይህ ስም ይኸውም እግዚአብሔር ማለት የማይመረመር ባሕርይውን እንዳያስረዳ እውነት ነው፤ የዚያን ባሕርይ ስሙን ማወቅ ፍጹም አይቻልም:: ወዳጅ ሆይ ስለዚህ ነገር አታድንቅ የልዑል እግዚአብሔርስ የባሕርይ ስሙ ይቅርና የመላእክስ እንኳ የባሕርይ ስሙ አይታወቅም፤ የነፍስም ነገር እንደዚሁ ይመስለኛል፤ ነፍስ መባል የባሕርይ ስሟን አያስረዳምና፤ እንግዲያስ ለባሕርይዋ የሚታወቅ ስም የለም” ብሏል:: ይህችም ጠባይ በልብነቷ ከዊን ከወላዲ አካል ስትኖር መቅደም፣ መከተል፣ ጥንት፣ ፍጻሜ ሳይኖርባት፣ በቃልነቷ ከዊን በተወላዲ አካል፣ በእስትንፋስነቷ ከዊን በሰራጺ አካል የነበረች ያለች የምትኖር ናት:: ማስረጃ:- ከአረጋዊ መንፈሳዊ ንባብ:- “አብሰ ጠባይዕ ውእቱ፤ ወልድኒ ወመንፈስ ቅዱስ ኃይላቲሁ፤ አልቦኬ ዘይኄሊ በእንተ አካላት ስቡሓት ከመ ፩ዱ ይቀድም እምነ ፩ዱ እስመ ጠባይዒሆሙ ሀሎ ዕሩየ እንበለ ጥንት” ትርጉም:- “አብ የእውቀትና የሕይወት መገኛ ልብ ነው፤ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ግን ኃይሉን የሚገልጥባቸው አእምሮና ሕይወት ናቸው፤ ከሚመሰገኑ አካላትም አንዱ ከአንዱ እንዲቀድም፣ የሚያስብ አይኑር፤ መገኛቸው አብ ሳይቀድም ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ዕሩይ ሆኖ ነበርና (ኑሯልና)” ብሏል:: ይህ ዕሪና የዘመን ነው:: /ድርሳን ፳፪ኛ/ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ኬራኮስም ፴፫ኛ: ንባብ:- “ወ፫ቱ አካላት ዕሩያን በኩሉ ግብር፤ እስመ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እምኔሁ ለአብ፣ ወጥንተ ቅድምና እሙንቱ ዘከመ አብ፣ ወአሐቲ ቅድምናሆሙ ለሥላሴ” ትርጉም:- “ሦስቱ አካላት በሥራው ሁሉ አንድ ናቸው፤ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተገኝተዋልና፣ እንደ አብ ቅድምና ያላቸው ጥንት ናቸውና፣ የሦስቱም ቅድምና አንዲት ናት” ብሏል:: (ሃይ.አበው ክፍል ፩) በሦስቱ አካላት አለች ማለታችንም በራስዋ መከፈል፤ በከዊንዋ መለየት ሳይኖርባት፤ በሕልውና ነው፤ ሕልውናውም ሦስቱን አካላት ማገነዘብ ነው:: ሃይማኖተ አበው ዘኪራኮስ ምዕ ፺፩ ቁ.፭ ማስረጃ ከዮሐንስ አፈወርቅ ንባብ:- “እስመ አርአያ ባሕርይ ካልዕ ውእቱ እምቀዳሚ ሥርው፤ ወባህቱ ኢፍሉጥ ውእቱ ክዋኔሁ በግዕዘ ጠባይዕ ወስምረት፣ ዘእንበለ በአካል ባህቲቱ” ትርጉም:- “አብን የሚመስል ወልድ፤ በቅድምና ከተገኘበት ከአብ ልዩ ነው፤ ነገር ግን ልዩነቱ በአካል ብቻ ነው እንጂ፤ በባሕርይ ሥራና በፈቃድ አይደለም” እንዳለ:: /ድርሳን ፪/ ማስረጃ ከአረጋዊ መንፈሳዊ ንባብ:- “ወአልቦ ጊዜ አመ ነበረ እንበለ አእምሮ ወሕይወት::” ትርጉም:- “ያለ እውቀትና ያለ ሕይወት የኖረበት ጊዜ የለም” ብሏል:: /ድርሳን ፳፪ኛ/ ዳግመኛም ንባብ:- ዳግመኛም “ነጽርኬ ዘተብህለ በእንተ አበ ኩሉ ከመ መሰልዎ በዛቲ ባሕር እንተ ትትገሠሥ፤ ለወልድኒ ዘይሴባህ በኀበ ኩሉ መሰልዎ በርጥበተ ማይ፤ ወለመንፈስ ቅዱስኒ ዘይሴባህ በሁከተ ማይ በውስተ ባሕር፤ ለመኑ ይትከሀሎ ከመ ይፍልጥ ኃይለ ባሕር እምነ ጠባይዒሁ፤ ይተከሀሎኑ ከመ የሀሉ ባሕር እንበለ ርጥበት፤ ወዘእንበለ ተሀውኮ:: ወለመኑ ይተከሀሎ ይፍልጥ ሁከተ እምነ ማይ ወባሕር ወያቅማ በባህቲታ፤ ለማይኒ ወለርጥበት በበባህቲቶሙ:: አው መኑ ዘርእየ አሐደ እምኔሆሙ እንዘ ይቀውም በባህቲቱ፣ ዘእንበለ በትሥልስቱ፤ እስመ ፩ እሙንቱ እንዘ ፫ቱ:: ወእንዘ ፫ አሐዱ ይትበሀሉ:: ወሶበሂ ይትኔጸር ወይትሌለይ በ፫ አካላት፣ ይትሔለይ ምስለ ኃይላቲሁ፤ ወኢይትሌለዩ ኃይላቲሁ እምጠባይዒሁ፤ ወጠባይዒሁ እምኃይላቲሁ፤ ወከመዝ እሔሊ በእንተ ጠባይዓት ስቡሐት::” ትርጉም:- “የሁሉ መገኛ አብን ነፋስ በሚያማታት ባሕር ባለች በውሃ እንደ መሰሉት እወቅ፤ በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን ወልድንም በውሃ እርጥበት እንደመሰሉት፤ በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን መንፈስ ቅዱስንም፣ በባሕር ባለ በውሃ ሁከት ይመሰላል (ይመስላል):: የባሕርን ኃይል ከጠባዩ መለየት ለማን ይቻለዋል? ባሕር ያለ እርጥበትና ያለ መታወክ ሊኖር ይቻላልን? ሁከትን ከእርጥበትና ከስፋት ለይቶ ለብቻዋ ማቆም ለማን ይቻለዋል? ስፋትንና እርጥበትንስ ከሁከት ለይቶ ለብቻቸው ማቆም ለማን ይቻለዋል? ከእነዚህስ አንዱን ብቻውን ቁሞ ያየው ማን ነው? በሦስትነቱ ነው እንጂ:: ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸውና፣ ሦስት ሲሆኑም አንድ ይባላሉና፣ ሦስት ኲነታት እንዳለ ቢታይ ቢታሰብም፣ ስፍሐት ኃይሉን የሚገልጥባቸው እርጥበትና ሁከትም ከስፍሐት አይለዩም:: ስፍሐትም ከርጥበቱና ከሁከቱ:: ስለተመሰገኑ ጠባያትም እንዲሁ እናገራለሁ” ብሏል:: /ድርሳን ፴፯ኛ/ በዚህ ጊዜ ጠባይዓት የተባሉት ኩነታት እንደሆኑ፤ አንዲት ጠባይም ሦስትነት ባለው ከዊን፣ በሦስት አካላት እንዳለች ያስተውሏል:: እንዲህም ሲሆን፣ ተወላዲ ቃለ እግዚአብሔር በተወላዲነት ፀንቶ ቢኖር አካሉ ባለች የጠባይ ከዊን ሰው ሆነ እንላለን ጠባይ የሌለው አካል የለምና:: ይህንም የሚያስረዳ ኪራኮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያ:- ንባብ:- “ኢይደሉ ይኩን ሕላዌ ዘእንበለ አካል፤ ወኢይደሉ ይትረከብ አካል ዘእንበለ አምሳሉ፤ ዘውእቱ አርአያሁ::” ትርጉም:- “ባሕርይ ያለ አካል ሊኖር አይችልም፤ አካልም አካልን ከሚመስለው ከጠባይ ጋር ነው እንጂ፣ ብቻውን ሊገኝ አይችልም፤ ይኸውም መታወቂያው ነው” ብሏል:: (ክፍል ፩ ሃ. አበው) ሃይማኖተ አበው ዚኪራኮስ ምዕ ፺፩ ÷ ፳፰ ክፍል ፩ እንዲህም ባልን ጊዜ ጠባይ ተከፍሎ ባይኖርባት፣ በከዊን በሦስቱ አካላት ትገኛለች ብሏልና፣ ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ማስተዋል ነው:: መለኮት፣ አምላክ ማለት፣ የጠባይ ስማቸው አይደለም:: በአንድነት ፈጥረው ስለገዙ መለኮት ስለተመለኩም አምላክ የሚያሰኛቸው በአንድነት የሚጠሩበት የባሕርይ ግብር ስማቸው ነው እንጅ:: እንዲህም ከሆነ ዘንድ ዮሐንስ አፈውርቅ:- “የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ አይገኝም” ብሎ ነግሮናልና፣ ልዩነት እንዳለበት በሰባተኛው አንቀጽ ለይተን ካሳየነው ምክንያት በቀር፤ እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት ምስጢሩ አንድ ነው:: ይህንም የሚያስረዳ ዮሐንስ ዘእስክንድርያ:- ንባብ:- “እኁዛን እሙንቱ በጽምረተ ፩ መለኮት ወበዝንቱ ፩ መለኮት ይሰመዩ እግዚአብሔር” ትርጉም:- “በአንድ መለኮት አንድ አድራጊነት የተገናዘቡ ናቸው፤ በዚህ በአንድ መለኮት እግዚአብሔር ይባላሉ” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩ ፵፩ ኛ )ሃይ. አበው ምዕ ፺፩ ÷ ፲-፲፩ ማስረጃ ከባስልዮስ ዘአንጾኪያ:- ንባብ:- “አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር፤ እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እስመ ፩ ውእቱ መለኮተ ሥላሴ፤ ወሠለስቲሆሙ ፩ እሙንቱ በመለኮት” ትርጉም:- “እኔ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ እግዚአብሔር ማለትን ስለአብ፣ ስለ ወልድ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ፤ የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና፤ ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና” ብሏል:: (አንቀጽ ፩ እይ) ሃ.አበው ዘባስልዮስ ምዕ ፺፮ ÷ ፮ እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት አንድ ከሆነ አፈወርቅም “እግዚአብሔር ማለት የባሕርይ ስሙን አያስረዳም” ካለ ፣ መለኮት ማለት ስሙ ለማይታወቅ ባሕርይ መጠሪያ ሊሆን የሚነገር ስሙ እንጂ፣ የጠባይ ስሙ እንዳይደለ በዚህ እንረዳለን:: መጻሕፍትም “መለኮት አምላክ ሰው ሆነ” ማለታቸው የጠባይ ስሙን ባያገኙት በግብር ስሙ ጠርተውት ነው:: ዳግመኛም "ወልድ ቃል ሰው ሆነ" ብለው አምላክ መለኮት ባይሉት፣ “ፍጡር” የሚሉ እነ አርዮስ፣ “ከመ፩ እም ነቢያት” የሚሉ እነ ንስጥሮስ፣ “ዝርው” የሚሉ እነ መርቅያን፣ ባልተረቱም ነበርና፤ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ አንድ በሚያደርገው፤ ሦስቱን በሚያገናዝባቸው ስም ጠርተውታል እንጂ፤ መለኮት በሦስት ይከፈላል ማለታቸው እንዳይደለ ጠንቅቆ ማስተዋል ነው::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፯



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 16/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

፯ኛ አንቀጽ
እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት አንድ ሲሆን፣ ልዩነት እንዳለበት ይናገራል::
እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት አንድ ሲሆን፣ ልዩነት አለበት፤ ልዩነት እንዳለበት የሚያስረዳ ነገር እናሳያለን:: መለኮት ማለት እንዲህ ነው ተብሎ በማይነገርና በማይታወቅ ጠባይ የሚጠራበት ስም ነው:: እግዚአብሔር ማለት ግን፤ አካል በአካልነቱ ግብር ሳይሆን፣ በባሕርይ ግብሩ የሚጠራበት የግብር ስም ነው:: እግዚአብሔር የማለትም ትርጓሜው:- በአንድነትና በሦስትነት ፈጥሮ የሚገዛ፣ ቅድመ ዓለም ያለ ጥንት የነበረ፣ ድኅረ ዓለም ያለ ፍጻሜ የሚኖር ዘላለማዊ አምላክ ማለት ነው:: ሊቃውንትም እግዚአብሔር ማለትም አንቀጽ ተቀባይ ባለቤት፤ መለኮትን ማድረጊያ እያደረጉ “በ” የሚባል አገባብ እየጫኑ ይነግሩናል:: “እግዚአብሔር አሐዱ በመለኮት” እግዚአብሔር በመለኮት አንድ ነው ይላል እንጅ፤ “መለኮት አሐዱ በእግዚአብሔር” መለኮት በእግዚአብሔር አንድ ነው አይባልም (አይልም)፤ ይሤለሱ በአካላት ብሎ ይትወሐዱ በመለኮት በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ይሆናሉ ይላል እንጂ፣ “ይትወሐዱ በእግዚአብሔር” በእግዚአብሔር አንድ ይሆናሉ:: የሚል አይገኝም:: ይኸውም እግዚአብሔርና መለኮት የማለት ስም አንድ ሲሆን፣ ልዩነትን ያስረዳል:: እንዲህ ከሆነ መጻሕፍት ማዋሐጃ አድርገው የተናገሩትን መለኮት፣ መለኮትን አንቀጽ ተቀባይ ባለቤት አድርጎ፣ መለኮት በአካል ሦስት ማለት ስህተት እንደሆነ አስተዋይ ልቡና ሳይረዳው አይቀርም::
፰ኛ አንቀጽ
የሥላሴ መንግሥት በአካል ከሦስት የማይከፈል አንድ መሆኑን ይናገራል፡፡
ጥያቄ:- የሥላሴ መንግሥት በአካል ሦስት ነው ማለት ስሕተት ይሆናልን? መልስ:- አዎን ስሕተት ነው፤ መንግሥት በአካል የሚከፈል ሦስት ነው ማለት፣ ሦስት መንግሥት አስገኝቶ ዘጠኝ አካላት ማለትን ያስከትላልና፣ እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት በየአንቀጹ አሐቲ መንግሥት አንዲት መንግሥት እያሉ የተናገሩት ቃል ሐሰት ሆነ ማለት ነው:: ማስረጃ:- አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ፯ኛ ንባብ:- “ሥላሴ ዕሪት ዘእንበለ ፍልጠት በ፫ አካላት ወበ፩ መለኮት፣ አሐቲ መንግሥት፣ ወአሐቲ ምልክና፣ ወአሐቲ ሥምረት፣ ወአሐቲ ኃይል፣ ወአሐቲ ስብሐት::” ትርጉም:- “ሥላሴ ያለመለያየት በመለኮት አንዲት ትክክል ናት:: ያለመለወጥም በአካላት ሦስት ናት፤ በመንግሥት አንዲት፣ በአገዛዝም አንዲት፣ በፈቃድም አንዲት፣ በኃይልም አንዲት፣ በጌትነትም አንዲት ናት” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩ )ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፩ ÷፭-፮ ሠለስቱ ምዕትም ፲፫:- ንባብ:- “ሥሉስ ፍጹም በ፩ መለኮት እስከ ለዓለም ፩ እግዚአብሔር፣ ወአሐቲ መንግሥት እንተ ኢትትከፈል ወኢትትፋለስ” ትርጉም:- “በገጽ በአካል ፍጹማን የሚሆኑ ሦስቱ አካላት፣ እስከዘለዓለም ድረስ በመለኮት አንድ ናቸው:: አንድ ጌታ ከሦስት የማትከፈል ከአንድ ወደ አንዱ የማታልፍ አንዲት መንግሥት ናቸው” ብለዋል ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፱ ÷ ፬-፮ ክፍል ፩ኛ ዲዮናስዮስም:- ንባብ:- “ኢንበውዕ ውስተ ከፊለ መንግሥት፤ አላ ንበል አሐቲ መንግሥት” ብሏል:: ፲፫ አንቀጽ እይ:: አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው:- ንባብ፦ “መለኮትሰ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ፣ አሐቲ መንግሥት፣ ወአሐቲ ሥልጣን፣ ወአሐቲ ምኩናን” ትርጉም:- “መለኮትስ አንድ አምላክ፣ አንዲት መንግሥት፣ አንዲት ሥልጣን፣ አንዲት አገዛዝ የሚሆን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው” ብሏል:: ይህን የመሰለ የተናገሩ ሊቃውንት ብዙ ናቸውና፣ ማስረጃ ሳይዙ መንግሥት በአካል ሦስት ከማለት ተጠብቆ እንዴት እንደሆነች መጻሕፍት በየአንቀጹ የመሰከርዋት /የመሰከሩላት/ የሥላሴ መንግሥት በአካል ከሦስት የማትከፈል አንዲት መሆኗን አምኖ፣ “ትምጻእ መንግሥትከ” መንግሥትህ ትምጣ እያሉ የዚችን አንዲት መንግሥት በአለበት እግዚአብሔርን ደጅ መጥናት ይገባል:: ዳግመኛ መንግሥት ሦስት ከሆነ ዙፋን የሌለው መንግሥት የለምና ሦስት መንበር አለ ማለት የግድ ነው:: እንዲህ ከሆነ ሕዝቅኤል በፈለገ ኮቦር፣ /ሕዝ ፩÷ ፲፱ - ፳፫/ ዮሐንስ በደሴተ ፍጥሞ /ራዕ ፬ ÷ ፪- ፫/ አራቱ ኪሩቤል ተሸክመውት ያዩት መንበር ከሦስቱ ነገሥታት የማናቸው ንጉሥ ነው ይባላል? ሦስቱ ገጻት በአንድ መንበር ላይ መታየታቸው ሦስቱ አካላት የአንድ ሕላዌ መለኮት በምትሆን በአንዲት መንግሥት አንድ መሆናቸውን ሲያስረዳ አይደለምን? መንበር ያለውም መንግሥት እንደሆነ የሚያስረዳ ነገር ነቢዩ ዳዊት ንባብ:- “መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም::” ትርጉም:- “አቤቱ ዙፋንህ ለዘላለም ነው” ያለውን መዝ ፵፭÷፯ ሲተረጉም ዮሐንስ አፈወርቅ፦ ንባብ:- “ወዝንቱ ያሌቡ እንበይነ መንግሥቱ” ትርጉም:- “ዙፋንህ ለዘላለም ነው” ያለውን “መንግሥቱ ዘለዓለም መሆኑን ያስረዳል” ብሏል:: /ድርሳን ፫/ በተረፈ ቄርሎስም ሳዊሮስ ዘገብሎን:- ንባብ:- “መንበረሰ ሶበ ሰማዕከ ለብዎ ለመንበር ከመ ድልወተ መለኮት ዘውእቱ መንግሥት ወሥልጣን ወእግዚእና” ትርጉም:- “መንበር ሲል በሰማህ ጊዜ መንበር ያለው ለመለኮት የሚገባ መንግሥትና ሥልጣን ጌትነትም እንደሆነ እወቅ” ብሎ ተርጉሞታል::  መንግሥትማ በአካል የሚከፈል ሦስት ከሆነ፣ ሦስቱ ገጻት በየራሳቸው በሦስት መንበር ተቀምጠው ባልታዩም ነበርን? እንኪያስ ሦስቱ ገጻት በአንድ መንበር ተቀምጠው ከታዩ፣ ነቢዩም መንበር ያለውን ዮሐንስ አፈወርቅና ሳዊሮስ መንግሥት ብለው ከተረጎሙት፣ መንግሥት በአካል የማይከፈል አንድ እንደሆነ፣ ታወቀ ተረዳም:: ኢሳይያስም:- ንባብ:- “ርኢክዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ልዑል ወነዋኅ” ትርጉም:- “እግዚአብሔርን ከፍ ባለ በረጅም ዙፋን ተቀምጦ አየሁት” ብሎ አንድ መንበርን አንድ እግዚእን ከተናገረ በኋላ፦ ንባብ:- “ወሱራፌል ይቀውሙ አውዶ ይጸርሁ ወይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት መልዐ ኩሎ ምድረ ስብሐቲከ” ትርጉም:- “ሱራፌል በዙሪያው ቁመው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ ምሥጋናህ በምድር መላ እያሉ ይጮሁ ነበር” ብሏል:: ኢሳ ፮ ÷ ፩-፫ ሦስት ጊዜ መላልሶ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ማለት አካላት ሦስት መሆናቸውን፣ ምስጋናው አንድ ቅዱስ መሆኑንና መንበሩም አንድ መሆኑን፣ ሦስቱ በአንድ መንግሥት፣ አንድ እግዚእ (ጌታ) መሆናቸውን ያስረዳል:: እንዲህም መንግሥት በአካል የሚከፈል ሦስት ነው ማለት ስህተት እንደሆነ አስተውል:: አስተዋይ ልቦና ያለው ሰውም እንዲረዳው የታመነ ነው::
፱ኛ አንቀጽ
አብ ማለትና ወላዲ ማለት፣ ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት፣ መንፈስ ቅዱስ ማለትና ሰራጺ ማለት ልዩ ልዩ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሰራጺ መለኮት ማለትን ነቅፈን አብ መለኮት ወልድ መለኮት መንፈስ ቅዱስ መለኮት ማለት አያስነቅፍም ስላልነ፣ አብ ማለትና ወላዲ ማለት፣ ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት፣ መንፈስ ቅዱስ ማለትና ሰራጺ ማለት አንድ አይደለምን? ምን ይለየዋል የሚል ሰው ቢኖር:- መልሱ:- ይህን ለይተን በተናገርንበት በአራተኛው አንቀጽ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት የአካል ስም፣ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ማለት ግን የግብር ስም እንደሆነ፣ በዚህም ልዩነት እንዳለበት ያሳየነውን ምሥጢር ቢመረምር ልዩነቱን ይረዳዋል:: አሁንም እየደጋገመነ በሚከተለው መስመር እናስጠነቅቀዋለን:: ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ማለት በአካል ቅሉ የማይገናዘብ ልዩ ነው:: አብ ወልድ መንፈሰ ቅዱስ ማለት ግን በሕላዌ መለኮት ባለች በባሕርይ ከዊንና በሕልውና የሚገናዘብና የሚዋሐድ ነው:: መገናዘቡንም የሚያስረዳ:- ባስልዮስ ዘቂሳርያ: ንባብ:- “ለወልድሰ ቦቱ ኩሉ ዘተናገርነ በእንተ ሕላዌ አብ ዘበድልዎት፤ ዝንቱ ውእቱ ዘተወልደ እም አብ፤ እስመ ወልድ ዋሕድ ውእቱ፣ ወቦቱ ኩሉ ኮነ ወአልቦ ዘይትከፈል ምንትኒ ማዕክሌሁ ወማእከለ አቡሁ፤ ወዝንቱ ስም ዘውእቱ ወልድ ያጤይቅ ሕብረተ ሕላዌሆሙ፣ እስመ ወልዱ ውእቱ ዘተወልደ እምኔሁ::” ትርጉም:- “ስለ አብ ባሕርይ ጌትነት በሚገባ የተናገርው ሁሉ በወልድ ያለ ነው:: ይኸውም ከአብ የተወለደው ነው፤ በመለኮት አንድ ባሕርይ የሚሆን አንድ ልጅ ነውና፣ በመለኮት አንድ ሕልውና የሚሆን በአባቱ ያለ ሁሉ በእርሱ አለና፣ ሁሉ የተፈጠረበት አንድ ልጅ ስለሆነ፣ በእርሱና በአባቱ መካከል ምንም ምን መለየት የለም፤ ይኸም ስም ይኸውም ወልድ መባል የባሕርያቸውን አንድነት ያስረዳል፤ ከእርሱ የተወለደ የባሕርይ ልጅ ስለሆነ” ብሏል:: (ሃ. አበው ክፍል ፩) ሃይ.አበው ክፍል ፬ ፤ ምዕ ፴፫ ÷ ፴-፴፪ አንባቢ ሆይ በአካል ስም ወልድ ብሎ በመለኮት አንድ ባሕርይ ያለውንና “ይህን ስም ይኸውም ወልድ መባል ነው” ብሎ “የባሕርያቸውን አንድነት ያስረዳል” ያለውን ጠንቅቀህ አስተውል:: በእርሱና በአባቱ መካከል ምን ምን መለየት የለም በማለቱ በሁለቱ አካላት ያለ መለኮት ተከፍሎ የሌለበት አንድ መሆኑን ያስረዳልና:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ:- ንባብ:- “ንነግረከ ወናሌብወከ ዘንተ ስመ ዘውእቱ ወልድ ከመ ውእቱ ፩ ሕላዌ ምስለ አብ::” ትርጉም:- “ይህንን ስም ይኸውም ወልድ ማለት ነው ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ መሆኑን እንዲያስረዳ እንናገራለን፤” ብሏል:: (ሃ. አበው ክፍል ፩)  ሃይ.አበው ምዕ ፶፫ ÷ ፲፩ ይኸውም የባስልዮስን ቃል የመሰለ ነው:: እንዲህ ባለ ምሥጢር የአካል ስም ከግብር ስም፣ የግብር ስም ከአካል ስም ልዩ ነውና፣ በስህተት ባሕር እንዳትጠልቅ በክህደት ገደል እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡

እኛ እና እነርሱ--እግር ኳሱ ተጀመረ!!!



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 9/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
09/09/09 ታሪካዊ ቀን!!!
አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእነታቸው በሰማእቱ ሐዋርያ በቅዱስ ማርቆስ የእረፍት በዓል ሚያዝያ 30/2009 ዓ.ም ከመንበረ ጵጵስናቸው ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው “እግር ኳሱ ተጀምሯል፡፡ ማን እንደሚያሸንፍ እንተያያለን” በማለት ይቃወሟቸው የነበሩትን ሁሉ ዝተውባቸው ነበር፡፡ ምሥራቅ ጎጃም አትድረሱብኝ እያለ እየተናገረ በሃይማኖቱ ደረሱበት፡፡ ጎጃሜው በሃይማኖቱ የዋዛ አይደለምና ሥርዓት ይከበር ትምህርተ ሃይማኖት አይበረዝ ብሎ ሆ ብሎ ተነሣ ሆ ብሎ!!! ትናንትና ግንቦት 8/2009 ዓ.ም በሌሊት ተነሥቶ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አደረገ፡፡ 299 ኪ.ሜን አቆራርጦ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ግቢ ፈሰሰ፡፡ ቅዱስነታቸው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሥራ አስኪያጁ አቡነ ዲዎስቆሮስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ አቡነ ሳዊሮስ የምሥራቅ ጎጃምን ሕዝብ አነጋገሩ፡፡ እንደ አባትነት እና እንደ ልጅነት ፍቅር ቁጭ አድርገው ጸጉራቸውን እያሻሹ ልጆቻችን ችግራችሁን ተረድተናል፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ምን እንደሚሠራ ተገንዝበናል፡፡ አይዟችሁ ይህንን የምንላችሁ ግን እናንተን ደስ እንዲላችሁ ብቻ አይደለም ስለእናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስንል ነው እንጅ፡፡ አሏቸው፡፡

አቡነ ማርቆስ ተጀምሯል ያሉት እግር ኳስ ዛሬ ዳኛ ተበጀለት፡፡ ሲኖዶስ ዳኛ ሆነ ያውም ሦስት ዳኛ ይኼው ፓትርያርኩ አሉ ጸሐፊው አሉ ሥራ አስኪያጁም አሉ፡፡ ደብረ ማርቆስ ከተማ ያለቀስነውን እንባ አዲስ አበባ በደስታ አለቀስነው፡፡ አባ ማርቆስ ፈቅደው ያሳተሟቸው ሁለቱ የቅባት መጻሕፍት በእጃቸው ገቡ፡፡ ታዲያ ይህንን የሰሙት በየቦታው አለቃ እያደረጉ የሾሟቸው 48ቱ የሥጋ ዘመዶቻቸው የእኛን ልጆች እግር እየተከተሉ ውስጣቸው እየተቃጠለ ይባስ ብሎ በዐባይ በረሃ እየነደዱ አዲስ አበባ ከች አሉ፡፡ የሚያናግራቸው የለም በጣም ዘግይተዋላ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካይ የሌለበት ንጹሕ የሥጋ ወይም የገንዘብ ዘመዶቻቸው ሆነው አረፉት፡፡ መጋቤ ሐዲስ ሳሙኤል አያልነህን አገኟቸው፡፡ ደስታ ሞቱ በደስታ ፈነጠዙ፡፡ “ምንድን ናችሁ አሏቸው” መጋቤ ሐዲስ፡፡ “ከዚያ በፊት ግን የቤተ ክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ቪዲዮ ቀራጭ ይምጣልን” አሉ ቀልደኞች ናቸው፡፡ “ማንም አይመጣም ማንም አይቀርጽም ችግር ካለባችሁ ችግራችሁን ተናገሩ” አሏቸው፡፡  “ማኅበረ ቅዱሳን ተሰብስቦ አባታችንን ሊከስ መጥቷል ተብለን ነው፡፡ ጎጃምን ያህል ትልቅ አገር እንዴት ሁለተኛ ተጠመቁ ይባላል” አለ አንደኛው፡፡ መጋቤ ሐዲስ የምሥራቅ ጎጃምን ነገር ከሥር መሠረቱ ያውቁ ስለነበር አንድ በአንድ ገቧቸው፡፡ “እናንተ እኮ ሲጀመር የሥጋ ዘመዶቻቸው ናችሁ፡፡ አባ እንባቆም እርስዎስ በጥንቆላ አይታሙምን፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ተአምረ ማርያም አታንብቡ አልተባለምን፡፡ ሁለት የቅባት መጻሕፍትስ አላሳተማችሁምን፡፡ ዲማ እና መርጡለ ማርያም እያላችሁ ቦታዎችን አልከፋፈላችሁምን፡፡ ዲማ የምትሄድ ወዮልህ እያላችሁ መድረክ ላይ ቆማችሁ አልተናገራችሁምን፡፡ ግቢ ጉባዔ እንዲዘጋ ማኅበረ ቅዱሳን ሥራ እንዳይሠራ አላደረጋችሁምን፡፡ አቡነ ማርቆስስ ቢሆን የመልሰከ ብርሃን አድማሱ አተላ አልለቅ ብሏችኋል አላሉምን፡፡ አሁን እዚህ ማንም አይቀበላችሁም ወደ መጣችሁበት ተመለሱ…” አሏቸው ያዝ አንግዲህ ቻለው፡፡  አንድ ቲዎሎጅ የተማረ ሰው አብሮ ነበር ለካ “አንተ ቲዎሎጅ ስትማር ተቀብዐ ተብለህ ነው የተማርህን” ተባሉ “መምህር እንደዛ አልተማርኩም” አለ፡፡ መጋቢ ሐዲስም “ታዲያ የት የተማርከውን ነው በዐውደ ምሕረት ላይ ተቀብዐ እያልክ የምታስተምር” አሏቸው፡፡ ዐይኑ ቁልጭ ቁልጭ እርግብ እርግብ ማለት ጀመረ እንባ አቀረረ ማን ይጠርግልሃል ዛሬማ አልቅስ  በደንብ እንጅ፡፡ የእግር ኳስ ጀማሪዎች በፎርፌ ተዘረሩላችሁ፡፡ በመጡበት መኪና ተጭነው ተመልሰው ሌሊቱን ሲጓዙ አድረዋል እንደ ጤፍ ነጋዴ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ደብረ ማርቆስ ገብተዋል፡፡

አቡነ ማርቆስ አበዱ ያው በሚታወቀው የስድብ ለዛቸው ስድቡን አወረዱት፡፡ ዛሬስ ችግር የለውም ተበሳጭተዋል “50 ቢወለድ 50 ነው ጉዱ” ሆነባቸዋ፡፡ በየደብሩ የሾሟቸው ዘመዶቻቸው እኮ 50 ሊሞሉ 2 ብቻ ነው የቀራቸው ድፍን 48 ናቸው፡፡ እናማ እየውላችሁ! ዛሬም በታሪካዊው ቀን በ09/09/09 በጠዋት ጀምረው በአቡነ ማርቆስ እየተመሩ ቢሮ ለቢሮ ሲዞሩ አረፈዱ፡፡ ማን ወይ ይበላቸው እዚህ እኮ አዲስ አበባ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው ደብረ ማርቆስ አይደለም፡፡ ዛሬ ከአቡነ ማርቆስ ጋር ሆነው ይንቀሳቀሱ የነበሩት፡
1.  ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን
2.  የበዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ
3.  የገዳመ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ አዲሱ
4.  አባ ፍቅረ ማርያም የፈረስ ቤት መድኃኔዓለም አስተዳዳሪ ከሚካኤል የተባረረው
ከ48 ዘመዶች 4ብቻ ቀርተዋል ሊቀ ሊቃውንትም ዘመድ አይደሉም ይባል ነበር ለነገሩ፡፡ ምን እግር ጣላችው እባካችሁ፡፡ በመጨረሻም እግራቸው ቁርጥ ሲል ውሎ አባ ማትያስን “አንዴ እናናግርዎ ይፍቀዱልን” ብለው አቁመው ከሰላምታ ያልዘለለ ነገር ተነጋግረው ተለያይተዋል፡፡ ዛሬ በአስተዳድር ጉዳይ በተደረገው ስብሰባ የደብረ ማርቆስ ሕዝብ ይህን ያህል አምርሮ ለምን መጣ በሚለው ጉዳይ ላይ እና የሐገረ ስብከቱ የመምሪያ ኃላፊዎች ሥራቸውን ትተው ከሐገረ ስብከቱ ገንዘብ ወጭ አድርገው እንዴት እዚህ ድረስ ይመጣሉ ብለው ተወያይተዋል፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሠረት የእኛ እግር ኳስ ቡድን በብዙ ጎሎች እየመራ ይገኛል፡፡ አረ ሳልነግራችሁ ረስቼው! አቡነ ማርቆስን ደግፈው የሄዱት ዘመዶቻቸው ማርቆስ ሲደርሱ ምን አሉ መሰላችሁ “እኛማ በፍጥነት አሳክተነው መጣን ከሳሾቻቸው ግን አልሳካላቸው ብሎ እስካሁን አልተመለሱም” ብለው ሞኞችን ፈገግ ሲያሰኙ አረፈዱ አሉ፡፡ የእኛ ልጆች ለምን አረፈዱ መሰላችሁ!
1.  የቅባት መጻሕፍቱ ወልደ አብ እና ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ በሊቃውንቱ እንዲታዩ መጻሕፍቱ በአካል ይቅረቡ ስለተባለ ዛሬ መጻሕፍቱን ገቢ ለማድረግ ነበር ተሳክቷል ገብተዋል፡፡
2.  ኮንትራት የያዙት መኪና ትናንት ተመልሶ ስለነበር ዛሬ አሁን አዲስ አበባ ሄዶላቸው ቸር መንገድ አድርግልን ብለው ጉዞ ጀምረዋል፡፡
እኛና እነሱ እግር ኳሱ ላይ ያለን አሰላለፍ እና አጨዋወት ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡ ያልተሳካለት የአቡነ ማርቆስ ቡድን እንጅ እኛማ ድንግልን ይዘን እንዴት አይሳካልንም!!!
ቸር ወሬ ያሰማን!!

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፮

© መልካሙ በየነ

ግንቦት 9/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
09/09/09 ታሪካዊ ቀን!!!
፭ኛ አንቀጽ
ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ ያለ የከዊን ስም ነው፡፡
የከዊን ስም “ልብ” አብ ለራሱ ለባዊ አዋቂው (አዋቂ) ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልቡና (ዕውቀት) መሆኑን የ ሚያመለክት ስም ነው:: ቃልም የወልድ የከዊን ስም ነው:: ለራሱ ነባቢ (ተናጋሪ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ መሆኑ የሚገለጽበት የከዊን (ቃል የመሆን) ስሙ ነው:: እስትንፋስ የመንፈስ ቅዱስ የከዊን ስሙ ነው:: መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት እንደሆነ የምና ውቅበት የከዊን (ሕይወተ አብ ወወልድ) የመሆን ስሙ ነው:: ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ተከፍሎ በሌለባት በአንዲት ባሕርይ ያለ የከዊን ስም ነው፡፡ ይኸውም ልዩነት ሳለበት አንድነት አንድነትም ሳለበት ልዩነት አለበት:: ልዩነቱ በከዊን ነው አንድነቱ ግን በሕልውና መገናዘብ ነው:: ወልድ ሰው ሆነ በተባለ ጊዜ አካል ተዋሐደ እንጂ ባሕርይ አልተዋሐደም እንዳይባል ወንጌላዊ ቃል ሥጋ ኮነ አለ እንጂ ወልድ ሥጋ ኮነ አላለም:: ባሕርይም ከተዋሐደ የሥላሴ ባሕርይ አንድ ነውና:: ፫ቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ከልብና ከእስትንፋስ ለይቶ “ቃል ሥጋ ኮነ” አለ:: ቃልም ማለት በአካለ አብና በአካለ መንፈስ ቅዱስ በኮዊን የምትለይ በሕልውና የምትገናዘብ እንደሆነች “ነገር በምሳሌ መዝሙር በሃሌ እንደተባለው አስቀድመን ምሳሌውን መርምረን በሁለተኛው አንቀጽ በነፋስና በፀሐይ በእሳትና በቀላይ መስለን ተናግረናልና በማስተዋል ይመለከቷል:: መለኮት እንደ አካላት ከ፫ ይከፈላል የሚል ሰው ይህን ነገር ከራሱ አንቅቶ በልብ-ወለድ ቃል ተናግሮታል እንጂ መጻሕፍት ከተናገሩት ኃይለ ቃልና ከመሰሉት ምሳሌ ምስክር አምጥቶ ለማስረዳት አይችልም:: የሥላሴን ባሕርይና አካል እንደ ሰው ባሕርይና አካል አድረጎ አካል የሌለው ባሕርይ፣ ባሕርይም የሌለው አካል የለምና ባሕርይ፣ አካልን ተከትሎ ከሦስት ይከፈላል ይላል:: መልስ:- ባያስተውለው ነው እንጂ ይህ ነገር ከሰማይና ከምድር ይልቅ የተራራቀ ነው:: የሰው ባሕርይ በአካል ቢከፈል በየራሱ ልብ፣ በየራሱ ቃል፣ በየራሱ እስትንፋስ ያለው ሆኖ በየራሱ ልዩ ልዩ ሥራውን ይሠራል:: አንዳንድ ቅዱሳንም በፀጋ ቢተዋወቁና አንዳንድ ሥራ ቢሠሩ ያደረባቸው መንፈስ ቅዱስ በሀብት አገናኝቷቸው ነው እንጂ የባሕርይና የሕልውና አንድነት ኖሯቸው አይደለም::ሥላሴ ግን አካላቸው የተለየ ሲሆን ባሕርያቸው ተከፍሎ የሌለበት አንድ ለመሆኑ ማስረጃው የሦስቱ ልብ አንድ አብ ሆኖ አንድ ዕውቀትን ያውቃሉ:: የሦስቱ ቃል አንድ ወልድ ሆኖ አንድ ነገርን ይናገራሉ:: የሦስቱ እስትንፋስ አንድ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ አንድ የሕይወትን ሥራ ይሠራሉ:: እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት “ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት” ያሉትን ተመልክቶ ይልቁንም “አጤን ይበልጡ ቃለ አጤ'' እንዲሉ እርሱ ባለቤቱ “አነ ወአብ ፩ ንሕነ፤ እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ ፲÷፴:: “አነ በአብ ወአብ ብየ'' "እኔ በአብ ሕልው ነኝ አብም በእኔ ሕልው ነው” ዮሐ ፲፯፤፲:: ያለውን ተረድቶ ባሕርየ መለኮት በአካል ከሦስት የማይከፈል መሆኑን ማመን ይገባል:: ከዚህ ግን ወጥቶ መለኮት እንደ አካላት ከሦስት ይከፈላል ማለት ግን አብን ልብ ወልድን ቃል መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ማለትን ትቶ፣ ለሦስቱ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ አላቸው ብሎ፣ ሦስት አማልክት በማለት የዮሐንስ ተዐቃቢን ሃይማኖት መመስከር ነው:: ይወልደዋል አይቀድመውም ማለት ቅሉ አካል በተከፍሎ ሲለይ፣ አንድ ባሕርየ መለኮት ተከፍሎ ሳይኖርበት፣ ሦስቱን አካላት በማገናዘብ /ማዋሐድ/ በቅድምና የነበረ ስለሆነ ነው:: ይህንም ለመረዳት:- ባስልዮስ ዘቂሣርያ የተናገረውን ይመልከቱ:: ፲፪ኛ ንባብ:- “ይደልወነ ናእምር ኀበ ኅብረተ ተዋሕዶተ መለኮት ዘ ፫ አካላት፣ ወናስተዋሕድ በአኀብሮ ዘዚአሆሙ ፩ መለኮት:: ንእመን በሃይማኖት ከመ ይትወሐድ መለኮት በአብ:: እስመ እምኀበ አብ ተወልደ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስሂ ወፅአ እምኔሁ:: እንዘ ኢይቀድም ፩ እምካልኡ፣ ወካልኡ እምሣልሱ፣ ወበልደተ ወልድ ወበጸአተ መንፈስ ቅዱስ እምአብ፣ ይትወሐድ መለኮተ ሥላሴሁ ለአምላክነ” ትርጉም:- “በአንድ መለኮት ተዋሕዶ የሦስቱን አካላት መገናዘብ ልናውቅ ይገባል:: በአንድ መለኮት በማገናዘብም ልዩ ልዩ የሆነ አካላትን እናዋሕድ:: መለኮት አንድ እንደሆነ በማመን፣ በአብ ያለ መለኮት ወልድን መንፈስ ቅዱስን እንዲዋሐድ እንመን:: አብ ከወልድ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ሳይቀድም፣ ወልድ ከአብ ተወልድዋልና፣ መንፈስ ቅዱስም ከርሱ ሠርፆአል፣ ከአብ ወልድ በመወለዱ፣ መንፈስ ቅዱስም በመሥረፁ፣ የአምላካችን የሦስትነቱን አካል መለኮት ይዋሐዳል” ብሏልና:: (ክፍል ፪ ) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፴፪ ÷ ክፍል ፪ ቁ. ፬-፮ አሁን በዚህ መስመር ያነበብውን የባስልስዮስን ቃል አስተውሎ የሚመለከት ሰው:- መለኮትን በአካል ሦስት ማለት ከሚያመጣው ፫ ልብ፣ ቃል፣ ፫ እስትንፋስ ከማለት ተጠብቆ በአብ ልብነት ለባውያን፣ በወልድ ቃልነት ነባብያን፣ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሕያዋን ብሎ በአካል ፫ በመለኮት አንድ በምታሰኝ ሃይማኖት ይፀናል:: መለኮት እንደ አካላት ከሦስት ይከፈላል የሚል ሰው ግን ወልድ ከአብ የሚወለደው ልደት ሰው ሁሉ ከአባቱ እንደሚወለደው ልደት ነው ማለቱ እንደሆነ ጠንቅቆ ማስተዋል ያሸዋል:: ማናቸውም ልጅ ከአባቱ ሲወለድ ባሕርዩ በአካል የሚከፈልና የሚለይ ስለሆነ አባት ከልጁ ይቀድማል ይበልጣልም:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ ፳ኛ:- ንባብ:- “ወእመሰ ኮነ ብእሲ አበ፣ ክሡት ነገሩ ከመ የዐቢ አብ እምወልድ:: ወስሞሂ ያጤይቅ ከመ ውእቱ እምቅድመ ወልዱ::'' ትርጉም:- “ሰው አባት ሲባል ከልጁ እንዲበልጥ ነገሩ የታወቀ ነው:: አባት መባሉም ከልጁ አስቀድሞ እንደነበረ ያስረዳል'' እንዳለ:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ÷ ክፍል ፩ ቁ. ፰ ወልድ ግን ከአብ ሲወለድ አካሉ በተከፍሎ ቢለይም ሕላዌ መለኮት በተከፍሎ መለየት የለበትም:: አወላለዱም ብርሃነ ፀሐይ ተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት ከክበብ እንዲገኝ በሕላዌ መለኮት ከአብ ተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት ነውና፣ መቅደም መቀዳደም መብለጥ መበላለጥ የለበትም:: አሁን ማስረጃ አድርገን የጠራነው ቴዎዶጦስ:- ንባብ:- “ወለነሰሂ ይደልወነ ነሐሊ ዘንተ በሕላዌ መለኮት:: አላ ነአምን በወልድ ዋሕድ ከመ ውእቱ ቀዳማዊ ምስለ አብ በኩሉ ዘመን፣ ወወልደ አብ ዋሕድ ይሰመይ ብርሃነ፣ እስመ ብርሃን ዘተወልደ እምብርሃን፣ ኢይትበሀል ተወልደ እምድኀረ ብርሃን አላ በጊዜ ዘኮነ ቦቱ ውእቱ ብርሃን፣ ይትረከብ ብርሃን ዘተወልደ እምኔሁ፣ ወወትረ ሕልው ምስሌሁ:: ብርሃንኒ ያጤይቀከ አምሳሊሁ ለወልድ ዘውእቱ ሕልው ምስለ አብ በኩሉ ጊዜ እምቅድመ ኩሉ ዓለም::'' ትርጉም:- “በመለኮት ባሕርይ ይህን ማሰብ ለእኛ አይገባንም፣ ወልድ ዋሕድ በዘመን ሁሉ ከአብ ጋር የነበረ ቀዳማዊ እንደሆነ እናምናለን እንጂ፣ ከአብ የተወለደ ዋሕድ ቃልም ብርሃን ይባላል:: ከክበብ የተገኘ ብርሃን ከክበብ በኋላ ተገኘ አይባልምና:: ብርሃን ክበብ በተገኘበት ጊዜ ተገኝቶ ከክበብ ሳይለይ አብሮ ይኖራል እንጂ፣ ብርሃንም የወልድ ምሳሌነቱን ያስረዳሃል ይኸውም ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ከአብ ጋራ ሁልጊዜ የነበረ ነው'' እንዳለ:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ክፍል ፩ ቁ. ፱ ይህን ምሳሌ ጠንቅቀን ብንመለከት አማናዊውን አጉልቶ ያሳየናል:: የሰውም ቃል በተወለደ ጊዜ አወላለዱ አሁን በተናገርነው በብርሃንና በክበብ አምሳል ነው:: ቃል ከልብ በተከፍሎ መለየት ሳይኖርበት፣ በአካል ከዊን ይወለዳል፣ በአካል ከዊን ተለይቶ መወለዱንም የሚያስረዳ ነገር፣ ከብራና ላይ በቀለም በተጻፈ ጊዜ አካል ገዝቶ ይታያል ይነበባልም:: ባሕርዩ ግን በተከፍሎ መለየት የለበትምና በልብ ውስጥ ሕልው ሆኖ ሲታሰብ ይኖራል:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ ፳፭ኛ:- ንባብ:- “ወለከሂ ቃልከ ዘይትወለድ እምልብከ ይሄሉ ውስቴትክ ተወሊዶ እምልብከ::''  ትርጉም:- “ያንተስ ስንኳ ከልብህ የሚገኝ ቃልህ፣ ከልብህ ተገኝቶ፣ በልብህ ውስጥ ሕልው ሆኖ ይኖራል'' እንዳለ:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩)  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፶፫ ክፍል ፩ ቁ. ፲፯ ንባብ:- ዳግመኛም “ወህየንተ ልብ ዘዝየ ነአምሮ ለአብ ህየ፣ ወህየንተ ቃል ዘዝየ ነአምሮ ለቃል ዘእግዚአብሔር ከመ ቦቱ ሕላዌ ወቦቱ አካል በፍጹም ገጽ ወመልክዕ፣ ዘከመ ገጸ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ እስመ ውእቱ ወልዱ ለአብ::'' ትርጉም:- “በኛ ባለ በልብ አምሳል አብን እናውቀዋለን:: እንደ አብና እንደ መንፈስ ቅዱስ ባለ በፍጹም ገጽ በፍጹም መልክዕ አካልና ባሕርይ እንዳለው፣ በእኛ ባለ በቃል አምሳል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን እናውቃለን፣ አብን አህሎ መስሎ የተወለደ የአብ ልጅ ነውና” ብሎ የአብ ልብነት በልብ፣ የወልድ ቃልነት በቃል፣ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በእስትንፋስ መመሰላቸውን ያስረዳል:: (ሃይማኖተ አበው ክፍል ፩) ዝኒ ከማሁ ቁ ፳ ልጅ ከአባቱ ባሕርይ በአካል ተለይቶ የሚከፈል ስለሆነ አባትና ልጅ አንድ ልብ አንድ ቃል አንድ እስትንፋስ በመሆን አይገኙም:: ወልድ ግን ከአብ ሲወለድ፣ ባሕርይ እንደ አካሉ የማይከፈል አንድ ስለሆነ፣ ሦስት አካላት በአንድ ልብ በአንድ ቃል በአንድ እስትንፋስ ተገናዝበው ይኖራሉ:: ይህንም ለመረዳት በየአንቀጹ የተነገረውን መመልከት ነው::
፮ኛ አንቀጽ
ወልድ ማለት የተረክቦ ስሙ እንደሆነ ይናገራል (ተረክቦ ማለት መገኘት ማለት ነው) ወልድ ማለት አካሉ በቃልነቱ ከዊን ተድኀሮ  ሳይኖርበት (ወደ ኋላ ሳይቀር) አብን አህሎ መስሎ ከአብ አካል በመገኘቱ የሚጠራበት የተረክቦ ስሙ ነው:: ተረክቦውም ተፈልጦ ሳይኖርበት በሕልውና እያለ ነው:: የነፍስ ቃሏ ከልብነቷ ተገኝቶ ሳይለይ አካሏ ሕልው ሆኖ እንደሚኖር ማነጻጸር ነው:: ማስረጃ:- ቄርሎስ በእስተጉቡእ: ንባብ:- “ወልድ ዋሕድ በሕላዌሁ ዘእምኀበ እግዚአብሔር አብ ይሰመይ ቃለ፣ እስመ ፩ ውእቱ ተወለደ እም ፩ አብ::''ትርጉም:- “ወልድ ዋሕድ ከእግዚአብሔር አብ ተወልዶ በአብ ሕልው ሆኖ በሚኖርበት ባሕርዩ ቃል ይባላል:: “አንዱ እርሱ ከአንድ አብ ተወልዷልና” ብሏል:: ተወላዲ ማለት ግን በተከፍሎ የሚጠራበት የግብር ስሙ ነው:: ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት በግሥ አንቀጽ መልክ ፊደሉ አንድ ሲመስል፣ የምሥጢር ልዩነት እንዳለው አሁን የተናገርነውን የተረክቦንና የተከፍሎን ምሥጢር ጠንቅቆ ማስተዋል ነው:: ተረክቦ ያልነውም የአካሉ ሕላዌ ከአብ አካል የተለየ ሆኖ በፍጹም ገጽና በፍጹም መልክ መታወቁ ነው እንጂ፤ እግዚአበሔር የተገኘበት ጊዜ አይደለም:: ማስረጃ:- ሱኑትዩስ:- ንባብ:- “ወኢይትረከብ ሀልዎቱ እምኃበ ወኢምንትኒ”ትርጉም:- “አኗኗሩ ከምንም ከምን አይገኝም” እንዳለ:: “ከምንም ተገኘ አይባልም” ሃይማኖተ አ በው ምዕ ፻፲ ክፍል ፪ ቁ. ፬ ሠለስቱ ምዕትም በቅዳሴ:- ንባብ:- “ኢይክል መኑሂ ይባዕ ማዕከለ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ያዕምር ዘከመ እፎ ህላዌሁ፣ ወለዶ አብ ለወልዱ ኢይትበሀል ዘጊዜ ወበዘከመዝ መዋዕል ወለዶ፤ ኢይትአመር ልደቱ እም አብ እስመ ዕፁብ ውእቱ፣ ወኢይትአወቅ ህላዌሁ እስመ ስውር ውእቱ” ትርጉም:- “ማንም ማን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መካከል ሊገባ አይችልም:: አኗኗሩ እንደምንም እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፣ አብ ልጁን ወልዶታል:: ነገር ግን አብ ልጁን በዚህ ጊዜ እንዲህም ባለ ዘመን ወለደው አይባልም፤ ከአብ መወለዱ አይመረመርም፣ የሚያስጨንቅ ነውና፤ አኗኗሩ አይታወቅም የተሰወረ ነውና፤” እንዲሉ:: ተከፍሎም በመለየት እንደሆነ የሚያስረዳ ሊቃውንት በብዙ አንቀጽ ገልጸዋል:: ንባብ:- “ተጋብኦ በተከፍሎ ወተከፍሎ በተጋብኦ” ትርጉም:- "አንድነት በመለየት መለየትም በአንድነት አለ” ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፮÷ ፫ ፵፱ኛ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ ፶፪ኛ ሱኑትዩስ ዘእስክንድርያ ፶፬ኛ ክርስቶዶሉ ዘእስክንድርያ እመልዕክተ ሲኖዲቆን አንቀጽ ሁለተኛ እይ ፩. ፪. ፫. ንባብ፦ “ኀቡራን እንበለ ተሌልዮ ወሊሉያን እንበለ ትድምርት” ትርጉም:- “ባለመለያየት አንድ ናቸውና አንድ ባለመሆንም ልዩ ናቸው” እያሉ ይናገራሉና:: (ቆዝሞስ ዘእስክንድርያ ክፍል ፩ኛ ሃይ.አበው ፵፪ኛ)ሃይማኖተ አበው ምዕ ፺፭ ÷ ፫ ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት፣ በምሥጢር ልዩነት እንዳለበት በዚህ ማስተዋል ነው::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡