Wednesday, May 24, 2017

እኛ እና እነርሱ--እግር ኳሱ ተጀመረ!!!



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 9/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
09/09/09 ታሪካዊ ቀን!!!
አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእነታቸው በሰማእቱ ሐዋርያ በቅዱስ ማርቆስ የእረፍት በዓል ሚያዝያ 30/2009 ዓ.ም ከመንበረ ጵጵስናቸው ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው “እግር ኳሱ ተጀምሯል፡፡ ማን እንደሚያሸንፍ እንተያያለን” በማለት ይቃወሟቸው የነበሩትን ሁሉ ዝተውባቸው ነበር፡፡ ምሥራቅ ጎጃም አትድረሱብኝ እያለ እየተናገረ በሃይማኖቱ ደረሱበት፡፡ ጎጃሜው በሃይማኖቱ የዋዛ አይደለምና ሥርዓት ይከበር ትምህርተ ሃይማኖት አይበረዝ ብሎ ሆ ብሎ ተነሣ ሆ ብሎ!!! ትናንትና ግንቦት 8/2009 ዓ.ም በሌሊት ተነሥቶ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አደረገ፡፡ 299 ኪ.ሜን አቆራርጦ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ግቢ ፈሰሰ፡፡ ቅዱስነታቸው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሥራ አስኪያጁ አቡነ ዲዎስቆሮስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ አቡነ ሳዊሮስ የምሥራቅ ጎጃምን ሕዝብ አነጋገሩ፡፡ እንደ አባትነት እና እንደ ልጅነት ፍቅር ቁጭ አድርገው ጸጉራቸውን እያሻሹ ልጆቻችን ችግራችሁን ተረድተናል፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ምን እንደሚሠራ ተገንዝበናል፡፡ አይዟችሁ ይህንን የምንላችሁ ግን እናንተን ደስ እንዲላችሁ ብቻ አይደለም ስለእናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስንል ነው እንጅ፡፡ አሏቸው፡፡

አቡነ ማርቆስ ተጀምሯል ያሉት እግር ኳስ ዛሬ ዳኛ ተበጀለት፡፡ ሲኖዶስ ዳኛ ሆነ ያውም ሦስት ዳኛ ይኼው ፓትርያርኩ አሉ ጸሐፊው አሉ ሥራ አስኪያጁም አሉ፡፡ ደብረ ማርቆስ ከተማ ያለቀስነውን እንባ አዲስ አበባ በደስታ አለቀስነው፡፡ አባ ማርቆስ ፈቅደው ያሳተሟቸው ሁለቱ የቅባት መጻሕፍት በእጃቸው ገቡ፡፡ ታዲያ ይህንን የሰሙት በየቦታው አለቃ እያደረጉ የሾሟቸው 48ቱ የሥጋ ዘመዶቻቸው የእኛን ልጆች እግር እየተከተሉ ውስጣቸው እየተቃጠለ ይባስ ብሎ በዐባይ በረሃ እየነደዱ አዲስ አበባ ከች አሉ፡፡ የሚያናግራቸው የለም በጣም ዘግይተዋላ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካይ የሌለበት ንጹሕ የሥጋ ወይም የገንዘብ ዘመዶቻቸው ሆነው አረፉት፡፡ መጋቤ ሐዲስ ሳሙኤል አያልነህን አገኟቸው፡፡ ደስታ ሞቱ በደስታ ፈነጠዙ፡፡ “ምንድን ናችሁ አሏቸው” መጋቤ ሐዲስ፡፡ “ከዚያ በፊት ግን የቤተ ክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ቪዲዮ ቀራጭ ይምጣልን” አሉ ቀልደኞች ናቸው፡፡ “ማንም አይመጣም ማንም አይቀርጽም ችግር ካለባችሁ ችግራችሁን ተናገሩ” አሏቸው፡፡  “ማኅበረ ቅዱሳን ተሰብስቦ አባታችንን ሊከስ መጥቷል ተብለን ነው፡፡ ጎጃምን ያህል ትልቅ አገር እንዴት ሁለተኛ ተጠመቁ ይባላል” አለ አንደኛው፡፡ መጋቤ ሐዲስ የምሥራቅ ጎጃምን ነገር ከሥር መሠረቱ ያውቁ ስለነበር አንድ በአንድ ገቧቸው፡፡ “እናንተ እኮ ሲጀመር የሥጋ ዘመዶቻቸው ናችሁ፡፡ አባ እንባቆም እርስዎስ በጥንቆላ አይታሙምን፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ተአምረ ማርያም አታንብቡ አልተባለምን፡፡ ሁለት የቅባት መጻሕፍትስ አላሳተማችሁምን፡፡ ዲማ እና መርጡለ ማርያም እያላችሁ ቦታዎችን አልከፋፈላችሁምን፡፡ ዲማ የምትሄድ ወዮልህ እያላችሁ መድረክ ላይ ቆማችሁ አልተናገራችሁምን፡፡ ግቢ ጉባዔ እንዲዘጋ ማኅበረ ቅዱሳን ሥራ እንዳይሠራ አላደረጋችሁምን፡፡ አቡነ ማርቆስስ ቢሆን የመልሰከ ብርሃን አድማሱ አተላ አልለቅ ብሏችኋል አላሉምን፡፡ አሁን እዚህ ማንም አይቀበላችሁም ወደ መጣችሁበት ተመለሱ…” አሏቸው ያዝ አንግዲህ ቻለው፡፡  አንድ ቲዎሎጅ የተማረ ሰው አብሮ ነበር ለካ “አንተ ቲዎሎጅ ስትማር ተቀብዐ ተብለህ ነው የተማርህን” ተባሉ “መምህር እንደዛ አልተማርኩም” አለ፡፡ መጋቢ ሐዲስም “ታዲያ የት የተማርከውን ነው በዐውደ ምሕረት ላይ ተቀብዐ እያልክ የምታስተምር” አሏቸው፡፡ ዐይኑ ቁልጭ ቁልጭ እርግብ እርግብ ማለት ጀመረ እንባ አቀረረ ማን ይጠርግልሃል ዛሬማ አልቅስ  በደንብ እንጅ፡፡ የእግር ኳስ ጀማሪዎች በፎርፌ ተዘረሩላችሁ፡፡ በመጡበት መኪና ተጭነው ተመልሰው ሌሊቱን ሲጓዙ አድረዋል እንደ ጤፍ ነጋዴ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ደብረ ማርቆስ ገብተዋል፡፡

አቡነ ማርቆስ አበዱ ያው በሚታወቀው የስድብ ለዛቸው ስድቡን አወረዱት፡፡ ዛሬስ ችግር የለውም ተበሳጭተዋል “50 ቢወለድ 50 ነው ጉዱ” ሆነባቸዋ፡፡ በየደብሩ የሾሟቸው ዘመዶቻቸው እኮ 50 ሊሞሉ 2 ብቻ ነው የቀራቸው ድፍን 48 ናቸው፡፡ እናማ እየውላችሁ! ዛሬም በታሪካዊው ቀን በ09/09/09 በጠዋት ጀምረው በአቡነ ማርቆስ እየተመሩ ቢሮ ለቢሮ ሲዞሩ አረፈዱ፡፡ ማን ወይ ይበላቸው እዚህ እኮ አዲስ አበባ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው ደብረ ማርቆስ አይደለም፡፡ ዛሬ ከአቡነ ማርቆስ ጋር ሆነው ይንቀሳቀሱ የነበሩት፡
1.  ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን
2.  የበዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ
3.  የገዳመ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ አዲሱ
4.  አባ ፍቅረ ማርያም የፈረስ ቤት መድኃኔዓለም አስተዳዳሪ ከሚካኤል የተባረረው
ከ48 ዘመዶች 4ብቻ ቀርተዋል ሊቀ ሊቃውንትም ዘመድ አይደሉም ይባል ነበር ለነገሩ፡፡ ምን እግር ጣላችው እባካችሁ፡፡ በመጨረሻም እግራቸው ቁርጥ ሲል ውሎ አባ ማትያስን “አንዴ እናናግርዎ ይፍቀዱልን” ብለው አቁመው ከሰላምታ ያልዘለለ ነገር ተነጋግረው ተለያይተዋል፡፡ ዛሬ በአስተዳድር ጉዳይ በተደረገው ስብሰባ የደብረ ማርቆስ ሕዝብ ይህን ያህል አምርሮ ለምን መጣ በሚለው ጉዳይ ላይ እና የሐገረ ስብከቱ የመምሪያ ኃላፊዎች ሥራቸውን ትተው ከሐገረ ስብከቱ ገንዘብ ወጭ አድርገው እንዴት እዚህ ድረስ ይመጣሉ ብለው ተወያይተዋል፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሠረት የእኛ እግር ኳስ ቡድን በብዙ ጎሎች እየመራ ይገኛል፡፡ አረ ሳልነግራችሁ ረስቼው! አቡነ ማርቆስን ደግፈው የሄዱት ዘመዶቻቸው ማርቆስ ሲደርሱ ምን አሉ መሰላችሁ “እኛማ በፍጥነት አሳክተነው መጣን ከሳሾቻቸው ግን አልሳካላቸው ብሎ እስካሁን አልተመለሱም” ብለው ሞኞችን ፈገግ ሲያሰኙ አረፈዱ አሉ፡፡ የእኛ ልጆች ለምን አረፈዱ መሰላችሁ!
1.  የቅባት መጻሕፍቱ ወልደ አብ እና ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ በሊቃውንቱ እንዲታዩ መጻሕፍቱ በአካል ይቅረቡ ስለተባለ ዛሬ መጻሕፍቱን ገቢ ለማድረግ ነበር ተሳክቷል ገብተዋል፡፡
2.  ኮንትራት የያዙት መኪና ትናንት ተመልሶ ስለነበር ዛሬ አሁን አዲስ አበባ ሄዶላቸው ቸር መንገድ አድርግልን ብለው ጉዞ ጀምረዋል፡፡
እኛና እነሱ እግር ኳሱ ላይ ያለን አሰላለፍ እና አጨዋወት ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡ ያልተሳካለት የአቡነ ማርቆስ ቡድን እንጅ እኛማ ድንግልን ይዘን እንዴት አይሳካልንም!!!
ቸር ወሬ ያሰማን!!

No comments:

Post a Comment