Wednesday, May 24, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፰



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 17/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ

፲ኛ አንቀጽ
ለሥላሴ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ እንደሌላቸው ይናገራል፡፡
ጥያቄ:- ለሥላሴ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ አለው ካልተባለ፣ አካለ ጎደሎ ያሰኛል እንጂ፣ በአካል ፍጹማን ያሰኛልን? መልስ:- ልብ ቃል እስትንፋስ በአካል ሕልው ሆኖ ለአካል ሕይወት የሚሆን የባሕርይ ከዊን ነው እንጂ፣ እርሱ እራሱ እንደ ዓይንና እንደ ጀሮ፣ እንደ አፍና እንደ አፍንጫ፣ እንደ እጅና እንደ እግር በቅርጽ የሚለይ አካል አይደለምና አካለ ጎደሎ አያሰኝም:: ይህንም ሌላ ምስክር ሳንፈልግ በራሳችን ሕላዌ እናስረዳለን:: ሰው በሞተ ጊዜ ልቡና ቃሉ እስትንፋሱ ይለዩታል፤ በአካል ያለው ሕይወት ስለተለየው እገሌ ሞተ ይባላል እንጂ አካሉ ጎደለ አይባልም:: አካሉም ከፍጹምነቱ ሳይጎድል በአልጋ ላይ ተኝቶ ይታያል:: ኋላም በመግነዝ ተይዞ ፍጹም አካሉ ወደ መቃብር ይወርዳል:: ኋላም በትንሣኤ ዘጉባኤ ነፍሱ ካለችበት መጥታ ስታድርበት፣ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ያለው ሕያው ሆኖ ይነሣል:: ማስረጃ:- ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው:- ንባብ:- `በቀዳሚ ንፍሐተ ቀርን ይትጋባእ ፀበለ ሥጋ ዘተዘርወ፤ ወበዳግም ንፍሐተ ቀርን ይሰፊያ አዕፅምት ምስለ ሥጋ፤ ወይከውን በድነ ፍጹመ ዘእንበለ አንሰሕስሆ፣ በሣልስ ንፍሐተ ቀርን ይትነሥኡ ሙታን ከመቅጽበተ ዓይን” ትርጉም:- “በመጀመሪያው አዋጅ ተለያቶ ተበትኖ የነበረ አጥንትና ሥጋ ይሰበሰባል፤ በሁለተኛው አዋጅ አጥንት ከሥጋ ጋር ተያይዞ የማይንቀሳቀስ ፍጹም አካል ያለው በድን ይሆናል፤ በሦስተኛው አዋጅ ሙታን እንደ ዓይን ቅጽበት ይነሣሉ” እንዳለ:: (ሐዳፌ ነፍስ) እንዲህ ከሆነ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ በነፍስ አካል ያለ በሥጋ ሕይወት የሚሆን የባሕርይ ከዊን ነው እንጂ፤ እርሱ እራሱ አካል እንዳይደለ ይታወቃል:: “የእርሱስ አካል የነፍስ አካል ነው”  በማለት አንዳንድ ሰዎች የተሳሳቱበትን ምክንያት በሚከተለው መስመር ገልጠን እናሳያለን:: በሥጋ አካል ከደረት በታች ከሆድ በላይ ልብ የተባለ ሥጋዊ አካል አለና፣ በዚህ ምክንያት ልብ አካል ነው ይላሉ፤ ልብ የተባለበትን ምሥጢሩን ግን አልተረዱትም፤ ልብ ማለት የነፍስ ስም ነው:: ማስረጃ ዮሐንስ አፈወርቅ:- ንባብ:- “እስመ ነፍስ ትሰመይ ልበ ወልቡና” ትርጉም:- “ነፍስ ልብ ልቡና ትባላለች” ብሏል:: /ድርሳን ፪ኛ/ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያም አስራ አንደኛ:- ንባብ:- “ወልቡ ለብእሲ መንፈሱ ወውእቱ ፩ ምስለ ነፍሱ እንተ ሃለወት በሥጋሁ::” ትርጉም:- “የሰው ልቡ ነፍሱ ነው ይኸውም በሥጋው ካለች ነፍሱ ጋራ አንድ ነው” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩)  ሃይማኖተ አበው ምዕ ፳፭ ቁ. ፳፮ እንዲህ የተባለች ነፍስ ተዋሕዶ ዕውቀትዋን ስለሣለችበት “በስመ ኅዳሪ ይጸዋዕ ማኅደር” እንደተባለ ማኅደር በኀዳሪው ስም መጠራት ልማድ ነውና፣ በማኅደርነቱ ልብ ተብሏል እንጅ፣ ልብ መባል የራሱ ስም አይደለም:: እርሱስ እንደ ሳንባና ጉበት ያለ አካል ነው:: አንዳንድ ሰዎች የነፍስ የዕውቀቷ ሰሌዳ የሆነ ይህ አካል ልብ በመባሉ ተሳስተው በየራሳቸው ልብ የሚባል አካል ከሌላቸው፣ ሥላሴ በአካል ፍጹማን አይባሉም እያሉ የስህተት ቃል ይናገራሉ፤ ይልቁንም በልብ አስጠግተው ምክንያት የሌላቸውን ቃልንና እስትንፋስን እንደ አካል አድርገው “በየራሳቸው ቃል፣ እስትንፋስ ከሌላቸው አካለ ጎደሎ ያሰኛል” ማለታቸውን አስተዋይ ልቡና ያለው ሰው እውነት ብሎ ሊቀበለው የማይቻል ነው::
፲፩ኛ አንቀጽ
መለኮት ከአካል የማይለይ አንድ ሲሆን፣ ወልድ ሰው ሆነ በተባለ ጊዜ፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ይናገራል፡፡
መለኮት ከአካል የማይለይ አንድ ነው ብለን፣ ወልድ ሰው ሆነ ስንል፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር በምትባል ጥበብ ሆነን፣ የረቀቀውን በማጉላት፣ የጎደለውን ለመሙላት እየመረመርን፣ መላልሰን እናስረዳለን:: ለሥላሴ በግብር የሚጠሩባት ባሕርይ የምትባል አሐቲ ጠባይዕ አለቻቸው፤ ግብሯም ሕይወትነት ነው:: ነገሩን ኋላ በአሥራ ሁለተኛው አንቀጽ እናመጣዋለን:: የዚህችም ጠባይ ጥንታዊና መሠረታዊ የሚሆን ስምዋ ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የማይችል ነው:: አለመቻሉንም ሲአስረዳ ዮሐንስ አፈወርቅ በ፪ኛው ድርሳኑ:- ንባብ:- “እስመ ሶበ ኢረከበ ስመ ዘይኤምር ኀበ ባሕርይሁ ብህለ በዝንቱ አስማት፤ እስመ ኢዕበይ ወኢስብሐት ይኤምሩ ኀበ ውእቱ ስም ዘፈቀደ ይዝክሮ፤ ወባህቱ ስእነ ረኪቦቶ በከመ እቤ ቀዳሚ ከመ ንሕነ ንኄሊ በእንተ ብዙኀ ግብራቲሁ ወንስዕን ፈክሮ ወነጊረ በእንቲአሁ፤ እወ ካዕበ ወኢ ዝስም ዘውእቱ እግዚአብሔር ኢይኤምር እንከ ኀበ ውእቱ ባሕርይ፣ ወፍጹመ ኢይትከሀል ይርከቡ ስሞ ለዝኩ ባሕርይ፤ ኢታንክር ኦ ፍቁር በእንተ ዝንቱ፤ ኅድግሰ ባሕርየ እግዚአብሔር ልዑል፤ ለመልአክኒ ጥቀ ኢይትረከብ ስመ ባሕርይሁ:: ወበእንተ ነፍስኒ ከማሁ ይመስለኒ፤ እስመ ብሂለ ነፍስ ኢይኤምር ኀበ ስመ ባሕርይሃ፤ … ወአልቦ እንከ ስም ዘይትአወቅ ለባሕርይሃ” ትርጉም:- “ባሕርዩን የሚያስረዳ ስም ባያገኝ፣ ዕበይ ስብሐት በማለት የባሕርይ ስሙን ተናገረ:: ዕበይ ስብሐት ማለት ሊናገረው የወደደውን የባሕርይ ስሙን ምንም ባያስረዳ አስቀድሜ እንደተናገርሁ እኛ ብዙውን ሥራውን እንድንመረምር ሥራውን ተረድተን መናገርም እንዳይቻለን የባሕርይ ስሙን ማግኘት ባይቻለው ይህን ተናገረ እንጅ:: ዳግመኛም ይህ ስም ይኸውም እግዚአብሔር ማለት የማይመረመር ባሕርይውን እንዳያስረዳ እውነት ነው፤ የዚያን ባሕርይ ስሙን ማወቅ ፍጹም አይቻልም:: ወዳጅ ሆይ ስለዚህ ነገር አታድንቅ የልዑል እግዚአብሔርስ የባሕርይ ስሙ ይቅርና የመላእክስ እንኳ የባሕርይ ስሙ አይታወቅም፤ የነፍስም ነገር እንደዚሁ ይመስለኛል፤ ነፍስ መባል የባሕርይ ስሟን አያስረዳምና፤ እንግዲያስ ለባሕርይዋ የሚታወቅ ስም የለም” ብሏል:: ይህችም ጠባይ በልብነቷ ከዊን ከወላዲ አካል ስትኖር መቅደም፣ መከተል፣ ጥንት፣ ፍጻሜ ሳይኖርባት፣ በቃልነቷ ከዊን በተወላዲ አካል፣ በእስትንፋስነቷ ከዊን በሰራጺ አካል የነበረች ያለች የምትኖር ናት:: ማስረጃ:- ከአረጋዊ መንፈሳዊ ንባብ:- “አብሰ ጠባይዕ ውእቱ፤ ወልድኒ ወመንፈስ ቅዱስ ኃይላቲሁ፤ አልቦኬ ዘይኄሊ በእንተ አካላት ስቡሓት ከመ ፩ዱ ይቀድም እምነ ፩ዱ እስመ ጠባይዒሆሙ ሀሎ ዕሩየ እንበለ ጥንት” ትርጉም:- “አብ የእውቀትና የሕይወት መገኛ ልብ ነው፤ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ግን ኃይሉን የሚገልጥባቸው አእምሮና ሕይወት ናቸው፤ ከሚመሰገኑ አካላትም አንዱ ከአንዱ እንዲቀድም፣ የሚያስብ አይኑር፤ መገኛቸው አብ ሳይቀድም ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ዕሩይ ሆኖ ነበርና (ኑሯልና)” ብሏል:: ይህ ዕሪና የዘመን ነው:: /ድርሳን ፳፪ኛ/ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ኬራኮስም ፴፫ኛ: ንባብ:- “ወ፫ቱ አካላት ዕሩያን በኩሉ ግብር፤ እስመ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እምኔሁ ለአብ፣ ወጥንተ ቅድምና እሙንቱ ዘከመ አብ፣ ወአሐቲ ቅድምናሆሙ ለሥላሴ” ትርጉም:- “ሦስቱ አካላት በሥራው ሁሉ አንድ ናቸው፤ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተገኝተዋልና፣ እንደ አብ ቅድምና ያላቸው ጥንት ናቸውና፣ የሦስቱም ቅድምና አንዲት ናት” ብሏል:: (ሃይ.አበው ክፍል ፩) በሦስቱ አካላት አለች ማለታችንም በራስዋ መከፈል፤ በከዊንዋ መለየት ሳይኖርባት፤ በሕልውና ነው፤ ሕልውናውም ሦስቱን አካላት ማገነዘብ ነው:: ሃይማኖተ አበው ዘኪራኮስ ምዕ ፺፩ ቁ.፭ ማስረጃ ከዮሐንስ አፈወርቅ ንባብ:- “እስመ አርአያ ባሕርይ ካልዕ ውእቱ እምቀዳሚ ሥርው፤ ወባህቱ ኢፍሉጥ ውእቱ ክዋኔሁ በግዕዘ ጠባይዕ ወስምረት፣ ዘእንበለ በአካል ባህቲቱ” ትርጉም:- “አብን የሚመስል ወልድ፤ በቅድምና ከተገኘበት ከአብ ልዩ ነው፤ ነገር ግን ልዩነቱ በአካል ብቻ ነው እንጂ፤ በባሕርይ ሥራና በፈቃድ አይደለም” እንዳለ:: /ድርሳን ፪/ ማስረጃ ከአረጋዊ መንፈሳዊ ንባብ:- “ወአልቦ ጊዜ አመ ነበረ እንበለ አእምሮ ወሕይወት::” ትርጉም:- “ያለ እውቀትና ያለ ሕይወት የኖረበት ጊዜ የለም” ብሏል:: /ድርሳን ፳፪ኛ/ ዳግመኛም ንባብ:- ዳግመኛም “ነጽርኬ ዘተብህለ በእንተ አበ ኩሉ ከመ መሰልዎ በዛቲ ባሕር እንተ ትትገሠሥ፤ ለወልድኒ ዘይሴባህ በኀበ ኩሉ መሰልዎ በርጥበተ ማይ፤ ወለመንፈስ ቅዱስኒ ዘይሴባህ በሁከተ ማይ በውስተ ባሕር፤ ለመኑ ይትከሀሎ ከመ ይፍልጥ ኃይለ ባሕር እምነ ጠባይዒሁ፤ ይተከሀሎኑ ከመ የሀሉ ባሕር እንበለ ርጥበት፤ ወዘእንበለ ተሀውኮ:: ወለመኑ ይተከሀሎ ይፍልጥ ሁከተ እምነ ማይ ወባሕር ወያቅማ በባህቲታ፤ ለማይኒ ወለርጥበት በበባህቲቶሙ:: አው መኑ ዘርእየ አሐደ እምኔሆሙ እንዘ ይቀውም በባህቲቱ፣ ዘእንበለ በትሥልስቱ፤ እስመ ፩ እሙንቱ እንዘ ፫ቱ:: ወእንዘ ፫ አሐዱ ይትበሀሉ:: ወሶበሂ ይትኔጸር ወይትሌለይ በ፫ አካላት፣ ይትሔለይ ምስለ ኃይላቲሁ፤ ወኢይትሌለዩ ኃይላቲሁ እምጠባይዒሁ፤ ወጠባይዒሁ እምኃይላቲሁ፤ ወከመዝ እሔሊ በእንተ ጠባይዓት ስቡሐት::” ትርጉም:- “የሁሉ መገኛ አብን ነፋስ በሚያማታት ባሕር ባለች በውሃ እንደ መሰሉት እወቅ፤ በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን ወልድንም በውሃ እርጥበት እንደመሰሉት፤ በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን መንፈስ ቅዱስንም፣ በባሕር ባለ በውሃ ሁከት ይመሰላል (ይመስላል):: የባሕርን ኃይል ከጠባዩ መለየት ለማን ይቻለዋል? ባሕር ያለ እርጥበትና ያለ መታወክ ሊኖር ይቻላልን? ሁከትን ከእርጥበትና ከስፋት ለይቶ ለብቻዋ ማቆም ለማን ይቻለዋል? ስፋትንና እርጥበትንስ ከሁከት ለይቶ ለብቻቸው ማቆም ለማን ይቻለዋል? ከእነዚህስ አንዱን ብቻውን ቁሞ ያየው ማን ነው? በሦስትነቱ ነው እንጂ:: ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸውና፣ ሦስት ሲሆኑም አንድ ይባላሉና፣ ሦስት ኲነታት እንዳለ ቢታይ ቢታሰብም፣ ስፍሐት ኃይሉን የሚገልጥባቸው እርጥበትና ሁከትም ከስፍሐት አይለዩም:: ስፍሐትም ከርጥበቱና ከሁከቱ:: ስለተመሰገኑ ጠባያትም እንዲሁ እናገራለሁ” ብሏል:: /ድርሳን ፴፯ኛ/ በዚህ ጊዜ ጠባይዓት የተባሉት ኩነታት እንደሆኑ፤ አንዲት ጠባይም ሦስትነት ባለው ከዊን፣ በሦስት አካላት እንዳለች ያስተውሏል:: እንዲህም ሲሆን፣ ተወላዲ ቃለ እግዚአብሔር በተወላዲነት ፀንቶ ቢኖር አካሉ ባለች የጠባይ ከዊን ሰው ሆነ እንላለን ጠባይ የሌለው አካል የለምና:: ይህንም የሚያስረዳ ኪራኮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያ:- ንባብ:- “ኢይደሉ ይኩን ሕላዌ ዘእንበለ አካል፤ ወኢይደሉ ይትረከብ አካል ዘእንበለ አምሳሉ፤ ዘውእቱ አርአያሁ::” ትርጉም:- “ባሕርይ ያለ አካል ሊኖር አይችልም፤ አካልም አካልን ከሚመስለው ከጠባይ ጋር ነው እንጂ፣ ብቻውን ሊገኝ አይችልም፤ ይኸውም መታወቂያው ነው” ብሏል:: (ክፍል ፩ ሃ. አበው) ሃይማኖተ አበው ዚኪራኮስ ምዕ ፺፩ ÷ ፳፰ ክፍል ፩ እንዲህም ባልን ጊዜ ጠባይ ተከፍሎ ባይኖርባት፣ በከዊን በሦስቱ አካላት ትገኛለች ብሏልና፣ ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ማስተዋል ነው:: መለኮት፣ አምላክ ማለት፣ የጠባይ ስማቸው አይደለም:: በአንድነት ፈጥረው ስለገዙ መለኮት ስለተመለኩም አምላክ የሚያሰኛቸው በአንድነት የሚጠሩበት የባሕርይ ግብር ስማቸው ነው እንጅ:: እንዲህም ከሆነ ዘንድ ዮሐንስ አፈውርቅ:- “የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ አይገኝም” ብሎ ነግሮናልና፣ ልዩነት እንዳለበት በሰባተኛው አንቀጽ ለይተን ካሳየነው ምክንያት በቀር፤ እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት ምስጢሩ አንድ ነው:: ይህንም የሚያስረዳ ዮሐንስ ዘእስክንድርያ:- ንባብ:- “እኁዛን እሙንቱ በጽምረተ ፩ መለኮት ወበዝንቱ ፩ መለኮት ይሰመዩ እግዚአብሔር” ትርጉም:- “በአንድ መለኮት አንድ አድራጊነት የተገናዘቡ ናቸው፤ በዚህ በአንድ መለኮት እግዚአብሔር ይባላሉ” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩ ፵፩ ኛ )ሃይ. አበው ምዕ ፺፩ ÷ ፲-፲፩ ማስረጃ ከባስልዮስ ዘአንጾኪያ:- ንባብ:- “አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር፤ እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እስመ ፩ ውእቱ መለኮተ ሥላሴ፤ ወሠለስቲሆሙ ፩ እሙንቱ በመለኮት” ትርጉም:- “እኔ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ እግዚአብሔር ማለትን ስለአብ፣ ስለ ወልድ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ፤ የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና፤ ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና” ብሏል:: (አንቀጽ ፩ እይ) ሃ.አበው ዘባስልዮስ ምዕ ፺፮ ÷ ፮ እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት አንድ ከሆነ አፈወርቅም “እግዚአብሔር ማለት የባሕርይ ስሙን አያስረዳም” ካለ ፣ መለኮት ማለት ስሙ ለማይታወቅ ባሕርይ መጠሪያ ሊሆን የሚነገር ስሙ እንጂ፣ የጠባይ ስሙ እንዳይደለ በዚህ እንረዳለን:: መጻሕፍትም “መለኮት አምላክ ሰው ሆነ” ማለታቸው የጠባይ ስሙን ባያገኙት በግብር ስሙ ጠርተውት ነው:: ዳግመኛም "ወልድ ቃል ሰው ሆነ" ብለው አምላክ መለኮት ባይሉት፣ “ፍጡር” የሚሉ እነ አርዮስ፣ “ከመ፩ እም ነቢያት” የሚሉ እነ ንስጥሮስ፣ “ዝርው” የሚሉ እነ መርቅያን፣ ባልተረቱም ነበርና፤ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ አንድ በሚያደርገው፤ ሦስቱን በሚያገናዝባቸው ስም ጠርተውታል እንጂ፤ መለኮት በሦስት ይከፈላል ማለታቸው እንዳይደለ ጠንቅቆ ማስተዋል ነው::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡

No comments:

Post a Comment