© መልካሙ በየነ
ግንቦት 16/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ
ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ
፯ኛ አንቀጽ
እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት አንድ ሲሆን፣ ልዩነት እንዳለበት ይናገራል::
እግዚአብሔር ማለትና መለኮት
ማለት አንድ ሲሆን፣ ልዩነት አለበት፤ ልዩነት እንዳለበት የሚያስረዳ ነገር እናሳያለን:: መለኮት ማለት እንዲህ ነው ተብሎ በማይነገርና
በማይታወቅ ጠባይ የሚጠራበት ስም ነው:: እግዚአብሔር ማለት ግን፤ አካል በአካልነቱ ግብር ሳይሆን፣ በባሕርይ ግብሩ የሚጠራበት
የግብር ስም ነው:: እግዚአብሔር የማለትም ትርጓሜው:- በአንድነትና በሦስትነት ፈጥሮ የሚገዛ፣ ቅድመ ዓለም ያለ ጥንት የነበረ፣
ድኅረ ዓለም ያለ ፍጻሜ የሚኖር ዘላለማዊ አምላክ ማለት ነው:: ሊቃውንትም እግዚአብሔር ማለትም አንቀጽ ተቀባይ ባለቤት፤ መለኮትን
ማድረጊያ እያደረጉ “በ” የሚባል አገባብ እየጫኑ ይነግሩናል:: “እግዚአብሔር አሐዱ በመለኮት” እግዚአብሔር በመለኮት አንድ ነው
ይላል እንጅ፤ “መለኮት አሐዱ በእግዚአብሔር” መለኮት በእግዚአብሔር አንድ ነው አይባልም (አይልም)፤ ይሤለሱ በአካላት ብሎ ይትወሐዱ
በመለኮት በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ይሆናሉ ይላል እንጂ፣ “ይትወሐዱ በእግዚአብሔር” በእግዚአብሔር አንድ ይሆናሉ::
የሚል አይገኝም:: ይኸውም እግዚአብሔርና መለኮት የማለት ስም አንድ ሲሆን፣ ልዩነትን ያስረዳል:: እንዲህ ከሆነ መጻሕፍት ማዋሐጃ
አድርገው የተናገሩትን መለኮት፣ መለኮትን አንቀጽ ተቀባይ ባለቤት አድርጎ፣ መለኮት በአካል ሦስት ማለት ስህተት እንደሆነ አስተዋይ
ልቡና ሳይረዳው አይቀርም::
፰ኛ አንቀጽ
የሥላሴ መንግሥት በአካል ከሦስት የማይከፈል አንድ መሆኑን ይናገራል፡፡
ጥያቄ:- የሥላሴ መንግሥት በአካል ሦስት ነው ማለት ስሕተት ይሆናልን? መልስ:- አዎን ስሕተት ነው፤
መንግሥት በአካል የሚከፈል ሦስት ነው ማለት፣ ሦስት መንግሥት አስገኝቶ ዘጠኝ አካላት ማለትን ያስከትላልና፣ እንዲህም ከሆነ ሊቃውንት
በየአንቀጹ አሐቲ መንግሥት አንዲት መንግሥት እያሉ የተናገሩት ቃል ሐሰት ሆነ ማለት ነው:: ማስረጃ:- አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ፯ኛ ንባብ:- “ሥላሴ ዕሪት ዘእንበለ ፍልጠት በ፫ አካላት ወበ፩ መለኮት፣
አሐቲ መንግሥት፣ ወአሐቲ ምልክና፣ ወአሐቲ ሥምረት፣ ወአሐቲ ኃይል፣ ወአሐቲ ስብሐት::” ትርጉም:- “ሥላሴ ያለመለያየት በመለኮት አንዲት ትክክል ናት:: ያለመለወጥም በአካላት ሦስት ናት፤ በመንግሥት
አንዲት፣ በአገዛዝም አንዲት፣ በፈቃድም አንዲት፣ በኃይልም አንዲት፣ በጌትነትም አንዲት ናት” ብሏል:: (ሃይ. አበው ክፍል ፩
)ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፩ ÷፭-፮ ሠለስቱ ምዕትም ፲፫:- ንባብ:-
“ሥሉስ ፍጹም በ፩ መለኮት እስከ ለዓለም ፩ እግዚአብሔር፣ ወአሐቲ መንግሥት እንተ ኢትትከፈል ወኢትትፋለስ” ትርጉም:- “በገጽ
በአካል ፍጹማን የሚሆኑ ሦስቱ አካላት፣ እስከዘለዓለም ድረስ በመለኮት አንድ ናቸው:: አንድ ጌታ ከሦስት የማትከፈል ከአንድ ወደ
አንዱ የማታልፍ አንዲት መንግሥት ናቸው” ብለዋል ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፱ ÷ ፬-፮ ክፍል ፩ኛ ዲዮናስዮስም:- ንባብ:- “ኢንበውዕ
ውስተ ከፊለ መንግሥት፤ አላ ንበል አሐቲ መንግሥት” ብሏል:: ፲፫ አንቀጽ እይ:: አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው:- ንባብ፦ “መለኮትሰ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ፣ አሐቲ መንግሥት፣ ወአሐቲ ሥልጣን፣ ወአሐቲ ምኩናን” ትርጉም:- “መለኮትስ አንድ አምላክ፣
አንዲት መንግሥት፣ አንዲት ሥልጣን፣ አንዲት አገዛዝ የሚሆን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው” ብሏል:: ይህን የመሰለ የተናገሩ
ሊቃውንት ብዙ ናቸውና፣ ማስረጃ ሳይዙ መንግሥት በአካል ሦስት ከማለት ተጠብቆ እንዴት እንደሆነች መጻሕፍት በየአንቀጹ የመሰከርዋት
/የመሰከሩላት/ የሥላሴ መንግሥት በአካል ከሦስት የማትከፈል አንዲት መሆኗን አምኖ፣ “ትምጻእ መንግሥትከ” መንግሥትህ ትምጣ እያሉ
የዚችን አንዲት መንግሥት በአለበት እግዚአብሔርን ደጅ መጥናት ይገባል:: ዳግመኛ መንግሥት ሦስት ከሆነ ዙፋን የሌለው መንግሥት
የለምና ሦስት መንበር አለ ማለት የግድ ነው:: እንዲህ ከሆነ ሕዝቅኤል በፈለገ ኮቦር፣ /ሕዝ ፩÷ ፲፱ - ፳፫/ ዮሐንስ በደሴተ
ፍጥሞ /ራዕ ፬ ÷ ፪- ፫/ አራቱ ኪሩቤል ተሸክመውት ያዩት መንበር ከሦስቱ ነገሥታት የማናቸው ንጉሥ ነው ይባላል? ሦስቱ ገጻት
በአንድ መንበር ላይ መታየታቸው ሦስቱ አካላት የአንድ ሕላዌ መለኮት በምትሆን በአንዲት መንግሥት አንድ መሆናቸውን ሲያስረዳ አይደለምን?
መንበር ያለውም መንግሥት እንደሆነ የሚያስረዳ ነገር ነቢዩ ዳዊት ንባብ:- “መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም::” ትርጉም:- “አቤቱ
ዙፋንህ ለዘላለም ነው” ያለውን መዝ ፵፭÷፯ ሲተረጉም ዮሐንስ አፈወርቅ፦ ንባብ:- “ወዝንቱ ያሌቡ እንበይነ መንግሥቱ” ትርጉም:-
“ዙፋንህ ለዘላለም ነው” ያለውን “መንግሥቱ ዘለዓለም መሆኑን ያስረዳል” ብሏል:: /ድርሳን ፫/ በተረፈ ቄርሎስም ሳዊሮስ ዘገብሎን:-
ንባብ:- “መንበረሰ ሶበ ሰማዕከ ለብዎ ለመንበር ከመ ድልወተ መለኮት ዘውእቱ መንግሥት ወሥልጣን ወእግዚእና” ትርጉም:- “መንበር
ሲል በሰማህ ጊዜ መንበር ያለው ለመለኮት የሚገባ መንግሥትና ሥልጣን ጌትነትም እንደሆነ እወቅ” ብሎ ተርጉሞታል:: መንግሥትማ በአካል የሚከፈል ሦስት ከሆነ፣ ሦስቱ ገጻት በየራሳቸው በሦስት
መንበር ተቀምጠው ባልታዩም ነበርን? እንኪያስ ሦስቱ ገጻት በአንድ መንበር ተቀምጠው ከታዩ፣ ነቢዩም መንበር ያለውን ዮሐንስ አፈወርቅና
ሳዊሮስ መንግሥት ብለው ከተረጎሙት፣ መንግሥት በአካል የማይከፈል አንድ እንደሆነ፣ ታወቀ ተረዳም:: ኢሳይያስም:- ንባብ:- “ርኢክዎ
ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ልዑል ወነዋኅ” ትርጉም:- “እግዚአብሔርን ከፍ ባለ በረጅም ዙፋን ተቀምጦ አየሁት” ብሎ
አንድ መንበርን አንድ እግዚእን ከተናገረ በኋላ፦ ንባብ:- “ወሱራፌል ይቀውሙ አውዶ ይጸርሁ ወይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር
ጸባዖት መልዐ ኩሎ ምድረ ስብሐቲከ” ትርጉም:- “ሱራፌል በዙሪያው ቁመው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ ምሥጋናህ
በምድር መላ እያሉ ይጮሁ ነበር” ብሏል:: ኢሳ ፮ ÷ ፩-፫ ሦስት ጊዜ መላልሶ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ማለት አካላት ሦስት መሆናቸውን፣
ምስጋናው አንድ ቅዱስ መሆኑንና መንበሩም አንድ መሆኑን፣ ሦስቱ በአንድ መንግሥት፣ አንድ እግዚእ (ጌታ) መሆናቸውን ያስረዳል::
እንዲህም መንግሥት በአካል የሚከፈል ሦስት ነው ማለት ስህተት እንደሆነ አስተውል:: አስተዋይ ልቦና ያለው ሰውም እንዲረዳው የታመነ
ነው::
፱ኛ አንቀጽ
አብ ማለትና ወላዲ ማለት፣ ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት፣ መንፈስ ቅዱስ ማለትና ሰራጺ ማለት ልዩ
ልዩ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣
ሰራጺ መለኮት ማለትን ነቅፈን አብ መለኮት ወልድ መለኮት መንፈስ ቅዱስ መለኮት ማለት አያስነቅፍም ስላልነ፣ አብ ማለትና ወላዲ
ማለት፣ ወልድ ማለትና ተወላዲ ማለት፣ መንፈስ ቅዱስ ማለትና ሰራጺ ማለት አንድ አይደለምን? ምን ይለየዋል የሚል ሰው ቢኖር:-
መልሱ:- ይህን ለይተን በተናገርንበት በአራተኛው አንቀጽ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት የአካል ስም፣ ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ማለት
ግን የግብር ስም እንደሆነ፣ በዚህም ልዩነት እንዳለበት ያሳየነውን ምሥጢር ቢመረምር ልዩነቱን ይረዳዋል:: አሁንም እየደጋገመነ
በሚከተለው መስመር እናስጠነቅቀዋለን:: ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ማለት በአካል ቅሉ የማይገናዘብ ልዩ ነው:: አብ ወልድ መንፈሰ ቅዱስ
ማለት ግን በሕላዌ መለኮት ባለች በባሕርይ ከዊንና በሕልውና የሚገናዘብና የሚዋሐድ ነው:: መገናዘቡንም የሚያስረዳ:- ባስልዮስ
ዘቂሳርያ: ንባብ:- “ለወልድሰ ቦቱ ኩሉ ዘተናገርነ በእንተ ሕላዌ አብ ዘበድልዎት፤ ዝንቱ ውእቱ ዘተወልደ እም አብ፤ እስመ ወልድ
ዋሕድ ውእቱ፣ ወቦቱ ኩሉ ኮነ ወአልቦ ዘይትከፈል ምንትኒ ማዕክሌሁ ወማእከለ አቡሁ፤ ወዝንቱ ስም ዘውእቱ ወልድ ያጤይቅ ሕብረተ
ሕላዌሆሙ፣ እስመ ወልዱ ውእቱ ዘተወልደ እምኔሁ::” ትርጉም:- “ስለ አብ ባሕርይ ጌትነት በሚገባ የተናገርው ሁሉ በወልድ ያለ
ነው:: ይኸውም ከአብ የተወለደው ነው፤ በመለኮት አንድ ባሕርይ የሚሆን አንድ ልጅ ነውና፣ በመለኮት አንድ ሕልውና የሚሆን በአባቱ
ያለ ሁሉ በእርሱ አለና፣ ሁሉ የተፈጠረበት አንድ ልጅ ስለሆነ፣ በእርሱና በአባቱ መካከል ምንም ምን መለየት የለም፤ ይኸም ስም
ይኸውም ወልድ መባል የባሕርያቸውን አንድነት ያስረዳል፤ ከእርሱ የተወለደ የባሕርይ ልጅ ስለሆነ” ብሏል:: (ሃ. አበው ክፍል ፩)
ሃይ.አበው ክፍል ፬ ፤ ምዕ ፴፫ ÷ ፴-፴፪ አንባቢ ሆይ በአካል ስም ወልድ ብሎ በመለኮት አንድ ባሕርይ ያለውንና “ይህን ስም
ይኸውም ወልድ መባል ነው” ብሎ “የባሕርያቸውን አንድነት ያስረዳል” ያለውን ጠንቅቀህ አስተውል:: በእርሱና በአባቱ መካከል ምን
ምን መለየት የለም በማለቱ በሁለቱ አካላት ያለ መለኮት ተከፍሎ የሌለበት አንድ መሆኑን ያስረዳልና:: ማስረጃ:- ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ:-
ንባብ:- “ንነግረከ ወናሌብወከ ዘንተ ስመ ዘውእቱ ወልድ ከመ ውእቱ ፩ ሕላዌ ምስለ አብ::” ትርጉም:- “ይህንን ስም ይኸውም
ወልድ ማለት ነው ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ መሆኑን እንዲያስረዳ እንናገራለን፤” ብሏል:: (ሃ. አበው ክፍል ፩) ሃይ.አበው ምዕ ፶፫ ÷ ፲፩ ይኸውም የባስልዮስን ቃል የመሰለ ነው:: እንዲህ
ባለ ምሥጢር የአካል ስም ከግብር ስም፣ የግብር ስም ከአካል ስም ልዩ ነውና፣ በስህተት ባሕር እንዳትጠልቅ በክህደት ገደል እንዳትወድቅ
ተጠንቀቅ::
ይቀጥላል፡፡
ይቆየን፡፡
No comments:
Post a Comment