ትምህርት በምሳሌያዊ አነጋገር
“ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ፤ ብዙ ቢተቹ ይሰለቹ” እንዲሉ ኢትዮጵያውያን በጥቂት
የቃላት ጥምርታ ብዙ ቁም ነገሮችን በማስተላለፍ የታወቁ ናቸው፡፡ ከንባብ መብዛት ይልቅ ለምሥጢር መብዛት ትኩረት የሚሰጡ ለመሆናቸው
በርካታ አባባሎች ምስክርነታቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል፡፡ እነዚህ አባባሎች በቀጥታው ካለው ትምህርታቸው በተጨማሪ በብዙ አቅጣጫ አስተማሪ
የሆኑ ድብቅ ምሥጢሮችን የያዙ ናቸው፡፡ ከበርካታ አባባሎች ጥቂቶችን በጥቂት በጥቂቱ እንመልከት፡፡
ለልጅ ከሳቁለት…
ሰይጣን በነገሠበት በዚህ ዓለም ለምንኖር በሰይጣን የተሰረቀ ልቡናችንን የምንመልስበት ልቡናችን እናዳይሰረቅም የምንጠነቀቅበት
ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡ ሥነ ቃሉ “ለልጅ ከሳቁለት ለውሻ ከሮጡለት” የሚል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ የተገለጹ ልጅና ውሻ ከሚስማሟቸው
ባሕርያት ጋር ነው፡፡ ልጅ ከሳቁለት ሽንቴን ልሽናብህ፣ ሰገራዬን ልጸዳዳብህ፣ ንፍጤን ልነፈጥብህ፣ በዱላ ልደብድብህ ፣ ጭቃ ልቀባህ
ወዘተ… በማለት የብልግና ሥራ ሊሠራብን ይወዳል፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙ ጊዜ የሳቃችሁለት ከሆነ እነዚህን የብልግና ሥራዎች እንዳይሠራ
ብትቆጡት ያለቅሳል፡፡ ውሻም ምንም ያህል እንኳ ፈሪ ቢሆን ከሮጣችሁለት ተከትሎ ማባረሩ አይቀርም፡፡ ጎንበስ ስትሉ ያየ እንደሆነ
ግን ከተከተለበት በበለጠ ፍጥነት ወደ ኋላው ይሸሻል፡፡ ሰይጣን እንዲሁ ልጅ ሲስቁለት የብልግና ሥራ እንደሚሠራ ሁሉ ወድደውት ለሚስቁለት
የሥጋ ሥራን አሠርቶ በኃጢአት ሊያቆሽሽ ይወዳል፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ ሲስቁለት ኖረው በጾም፣ በጸሎት ፣ በስግደት ፣ በንስሓ ቢቆጡት
እንደ ሕጻን አልቅሶ የሥጋ ሥራን ከማሠራት መታገሱ አይቀሬ ነው፡፡ ዳግመኛም ሰይጣን እንደ ውሻ ሲሮጡለት ከቤተክርስቲያን ፣ ከጸሎት
፣ ከጾም፣ ከስግደት ፣ ከበጎ ሥራ ወዘተ… ፈሪነቱን ደብቆ ደፋር መስሎ እየተከተለ ያባርራል፡፡ ይሁን እንጅ በእምነት፣ በጸሎት፣
በጾም፣ በትሕትና ወዘተ… ጎንበስ ሲሉ ያየ እንደሆነ ከተከተለበት
በበለጠ ፍጥነት አፍሮ ወደኋላው ይመለሳል፡፡ ስለዚህ ሰይጣንን እንደ ልጅ በመሳቅ እንደ ውሻ በመሮጥ ልንገዛለት አይገባም፡፡ ሰይጣን
ማለት የተዋረደ፣ የወደቀ፣ ወራዳ፣ ውዳቂ፣ የከረፋ ማለት ስለሆነ ለተዋረደ፣ ለወደቀና ለከረፋ ደግሞ እጅ መስጠት በክርስትና ሕይወት
ልማድ አይደለም፡፡ ሰይጣን
ጸሎት እንዳትጸልዩ፣ ጾም እንዳትጾሙ፣ ስግደት እንዳትሰግዱ፣ በጎ ሥራ እንዳትሠሩ ወዘተ… በሰንሰለት ቢያስራችሁ ሰንሰለቱን ሊፈቱ
ወደሚችሉት ካህናት መሄድ እንጅ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ወዳልተሰጠው ሰይጣን መገስገስ አይገባም፡፡
የራሷ እያረረባት…
ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ሁለት
ጠቃሚ ትምህርቶች በውስጡ የያዘ ስለሆነ ባለሁለት ስለት ቢላዋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሥነ ቃሉ “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” የሚል ነው፡፡ ከዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር የምናገኘው የመጀመሪያው ትምህርት
ማቴ 7÷3 “በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ
በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ አትመለከትም” የሚለውን
አምላካዊ ቃል የሚገልጽ ነው፡፡ ሰዎች በባሕርያችን ከእኛ ይልቅ በሌሎች ያለውን ለማየት እንፈጥናለን፡፡ ከእግዚአብሔር ርቀን፣ በኃጢአት
ተዘፍቀን፣ የጽድቅ ፀሐይ ጨልሞብን በሥጋ ሥራ ተጨማልቀን ሳለ ስለሌሎች በኃጢአት መዘፈቅ፣ ከእግዚአብሔር መራቅ ስናወራ በርካታ ጊዜያትን እናቃጥላለን፡፡ የራሳችን ሕይወት በኃጢአት እያረረ መሆኑን
ሳንመለከት የሌሎችን ኃጢአት እናማስላለን፡፡ እኛ የምናማስለው የሌሎች ኃጢአት በንስሓ ጠፍቶ ይሁን አይሁን ምን ማረጋገጫ ኖሮን
ነው በሌሎች ዓይን ያለውን ጉድፍ ስንመለከት ዓይናችን የሚፈዘው? የራስ የሆነውን አሳርሮ የሌሎችን ማማሰል ከንቱነት ነው፡፡ የሌሎችን
ከማማሰል በፊት የራስን በአግባቡ ማማሰል ይቀድማል፡፡ ስለዚህ የሌሎችን ትንሽ ኃጢአት ከምናማስል የራሳችንን ትልቅ ኃጢአት በንስሓ
አስወግደን በኃጢአት እሳት ለማረር የቀረበ ሕይወታችንን ልንታደግ ይገባናል፡፡
ሁለተኛው ትምህርት ከዚህ በተለየ
መልኩ የጻድቃንን ደግነት የሚያሳይ ነው፡፡ ጻድቃን የዚችን ዓለም ጣዕም ንቀው፣በበረሐ ወድቀው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ
ልሰው፣ ዳባ ለብሰው፣ ፀብአ አጋንንትን ድምጸ አራዊትን ታግሰው፣ ተድላ ሥጋቸውን ጠልተው፣ ተድላ ነፍሳቸውን ፈልገው ከሰው ርቀው ፣ ንጽሕ ጠብቀው ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ለሥጋ
በማይመች ኑሮ እየኖሩ በተድላ ሥጋ ለሚኖረው ዓለም ይጸልያሉ፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ያስቀድማሉና
ነው፡፡ እነርሱ ነድደው ለሌሎች ብርሃን ይሆናሉ፡፡ ራሳቸውን ጎድተው ሌሎችን ይጠቅማሉ ፡፡ የራሳቸው ተድላ ሥጋ አርሮ ሳለ ለሌሎች
ተድላ ሥጋ ይጸልያሉ፡፡ ስለዚህ የጻድቃንን ደግነት የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች ብለን ልንገጸው እንችላለን ማለት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment