“እገሌ ባዘጋጀው ልዩ የስብከት መርኀ ግብር ይህን ያህል ሽህ
ብር ለቤተክርስቲያን ገቢ አደረገ፡፡ ስለዚህ እገሌ ተሐድሶ ሊባል እንዴት ይችላል በእኔ በኩል ግን ተሐድሶ መናፍቅ መባሉን አልደግፍም”
የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች “ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል”
የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር የዘነጉ ናቸው፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ለቤተክርስቲያን የሰጠው ገንዘብ እንጅ ጥሩ ምእመን አይደለም እኮ
፡፡ ቤተክርስቲያን የምትፈልገው ደግሞ በሽህ የሚቆጠር ጥሩ ምእመንን ነው፡፡ ስለዚህ ገንዘብ መስጠት ብቻውን የተዋሕዶ ልጅ የሚያሰኝ
ባለመሆኑ ትምህርቱን፣ ሥርዓት አጠባበቁን መመልከት ተገቢ ነው፡፡
የሚያስለቅስህ ፈልግ
ተሐድሶ መናፍቃን ስብከቶቻቸው በቀልድ በሳቅ የታጀቡ በመሆናቸው ለመሳቅ የሚከተላቸው እጅግ ብዙ ነው፡፡ አንድ ወጣት
“እገሌ ሲሰብክ እየቀለደና እያሳቀ በጣም እያዝናና ስለሆነ ሁልጊዜ
ከእርሱ ጋር ብውል ባድር እንዴት ደስ ይለኝ ነበር” እያለ ለአባቱ ይነግራቸዋል፡፡ አባቱም “ልጄ ከዛሬ ጀምረህ ኃጢአትህን እየነገረ ስለኃጢአትህ በንስሓ የሚያስለቅስህ
ሰባኪ ፈልግ” አሉት፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገው ኃጢአታችንን እያሰብን ወደ ንስሓ የሚመራን ስብከት እንጅ የሚያስቅ የሚያዝናና
አይደለም፡፡ ሳቅ ጨዋታማ በዓለምስ ሞልቶ ተርፎ የለም እንዴ? ቤተክርስቲያን መሄድ ያስፈለገው ለንስሓ ነው እንጅ፡፡
አገልግሎት ስብከት ብቻ
አንድ የተሐድሶ መናፍቅ ሰባኪ አርብና ረቡዕን በሌሊት ሲመገብ ቅር አይለውም፡፡ ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? ሲሉትም
እኔ አገልጋይ ስለሆንኩ እንዳይደክመኝ ነው ይላል፡፡ በእውነት አገልግሎት ስብከት ብቻ ነው? ጹሙ ለማለትስ መጾም አያስፈልግም?
ያለ ምግብ ቃለ እግዚአብሔርን ማስተማርስ አይቻልም? እንዲህ አይነቱ የሰባኪነትን ክብር ማቃለል የሚፈልግ የዲያብሎስ የግብር ልጅ
ነው፡፡ ሐዋርያት ሳንበላ ሳንጠጣ ወንጌልን አንናገርም ብለው ነበር እንዴ? ቅዱስ ጳውሎስ ዕለት ዕለት የሚያሳስበኝ የሚከብድብኝ
የአብያተ ክርስቲያናት ነገር ነው ያለው ከሆዱ መሙላት በኋላ መሰላችሁ እንዴ? አይደለም ብዙ መከራ እንደደረሰበት ዘርዝሮ ያንን
ሁሉ ከምንም ሳልቆጥር የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ያሳስበኛል ነው እኮ ያለው፡፡
የሚደግፈው እንዳያጣ ነው
ብዙዎች “እገሌ በስብከቱ ውስጥ ድንግል ማርያምን የማይሰብከው
ለምንድን ነው?” ይላሉ፡፡ ድንግል ማርያምን የማይሰብከውማ ድንግልን አምባ መጠጊያ እያደረገ በእናትነት ጥላዋ ሥር እየተጠለለ
የሚኖር ትውልድ እንዳይፈጠር ነው፡፡ ትውልዱ ድንግል ማርያምን ከተጠጋ እርሱን የሚደግፈው ደጋፊ እንዳያጣ ስለሚሰጋ እርሱን ብቻ
እንዲከተሉት ለማድረግ ሌሊት ከቀን የራሱን የማይጠቅም ታሪክ ሲዘረዝር ይኖራል፡፡ በተጨማሪም እመብርሃንን የካዱ ለሆዳቸው ያደሩ
ስለሆኑ የእመቤታችንን ሥም ማንሣት አይፈልጉም፡፡
እውነትን ለማስጠላት
መናፍቃን ሻሽ ጠምጥመው መስቀል ጨብጠው ሰክረው ለመውደቅ ይንገዳገዳሉ፡፡ የምንኩስና ቆብ ገዝተው ይለብሱና ከሴት
ጋር ተቃቅፈው መንገድ ለመንገድ ይዞራሉ፡፡ የሰውን ኅሊና ለመስረቅም ጀርባቸውን በብረት እየገረፉ እግዚአብሔር የላከን ነን እያሉ
በየቦታው ይልከሰከሳሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት በርካታ ሕዝብ በሚገኙባቸው ቦታዎች መሆኑ አውነተኛ ካህናትን፣ መነኮሳትን ባሕታውያንን
ለማስጠላት ነው፡፡ ወይ የዘመኑ ቄስ! ወይ የዘመኑ መነኩሴ! ወይ የዘመኑ ባሕታዊ! እያለ ያያቸው የተመለከታቸው ሁሉ አውነተኞቹን
ይሰድባል፡፡ ቤተክርስቲያንም እንድትጠላ ጃንጥላ ዘቅዝቀው ሰሌን ዘርግተው ቅዱሳት ሥዕላትን አንግበው
መስቀል ይዘው የቅዱሳንን ሥም እየጠሩ የዚህ ቤተክርስቲያን ማሰሪያ እጃችሁን ዘርጉ እያሉ የየዋሃንን ገንዘብ መስከሪያ የሚያደርጉ
እየተበራከቱ ነውና ወገኔ መንቂያ ሰዓትህ አሁን ነው እንቅልፍ ይብቃህ፡፡
ድፍረት
የተሐድሶ መናፍቃን ዋና መርኅ ድፍረት ነው፡፡ በትምህርታቸውና በመዝሙራቸው ውስጥ ይህን ድፍረታቸውን ለትውልዱ ሁሉ በማለማመድ ላይ ይገኛሉ፡፡ “ዓለምን ተኝቶ የሚገዛ ፈጣሪ ነው የምናመልከው” ይላሉ፡፡ ይህን የድፍረት ቃል ማነው ያስተማራቸው? ከየትስ ነው ያነበቡት? በእውነት ዓለም የምትተዳደረው በሚያንቀላፋ አምላክ ነውን? እስራኤልን የሚጠብቅ አያንቀላፋም ሲባል ነው ከመምህራን የሰማነው ከመጻሕፍት ያነበብነው የዛሬ ደፋሮች ግን እግዚአብሔርን የሚያንቀላፋ እንቅልፍ የሚያሸንፈው አድርገው ያስተምራሉ፡፡“የሳሎኑ ጽጌረዳ” በማለት ክርስቶስን ከሰው ሠራሹ የፕላስቲክ አበባ ጋር የሚደምሩም ድፍረትን በጥሩ ሁኔታ የለመዱ ደፋሮች አሉ፡፡ “ዕድሜ ብቻ! ማቱሳላ ያን ያህል ዘመን ቢኖር ምን ሠራ” እያሉ ማቱሳላን የሚንቁ ሽማግሌዎችንም የሚሳደቡ ድፍረት ገንዘባቸው የሆኑ አፈ ጮሌዎችም አሉ፡፡ እነርሱ በተጠቀሙት ቃል እኛም ብንገልጸው ለጆሮ የሚያሳክክ ከባድ ኑፋቄ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ከድፍረት ኃጢአት ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡
No comments:
Post a Comment