ውሻ በቀደደው…
ሥነ ቃሉ “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ተብሎ ይሟላል፡፡ ውሻ የጌታውን አጥር ከቀደደው
በዚያ ጅብ ገብቶ በበረት ያሉ እንስሳትን ይጎዳል፡፡ ጅብ እንስሳቱን ለመጉዳት አጥሩን ጥሶ መግባት ስለማይችል የሚገባበትን ትንሽ
ቀዳዳ ይፈልጋልና ትንሽ ቀዳዳ በውሻ ከተከፈተችለት ያችን ቀዳዳ አስፍቶ ለመግባት ስለማይቸገር “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ይባላል፡፡ ሰይጣን እንዲህ ያለ የጅብ ባሕርይ አለው፡፡ ሰይጣን ትንሽ ቀዳዳ ካገኘ
ያችን ተጠቅሞ በሰው ልቡና ለማደር አይቸገርም፡፡ ትልቅ መርከብ የመርፌ ቀዳዳ በምታክል ቀዳዳ በሚገባ ውኃ እንዲሰጥም የሰው ልጅም
እንዲሁ ነው፡፡ አጥራችንን በሚገባ አጥረን ትንሽ ቀዳዳ ከተውን ያችን የማስፋት ልምድ ያለው ሁሉ ሊያጠቃን ይችላል፡፡ ሁሉንም ትዕዛዛት
ጠብቀን አንዷን ከጣስን ስለተጣሰችዋ ትዕዛዝ ይፈረድብናል፡፡ አሥር መስኮቶች ያሉትን ቤት ዘጠኙን ዘግተን አንዷን ብንተዋት በዚያች
የገባ ሌባ ቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ ለመዝረፍ እንደማይቸገር ሁሉ ብዙ የጽድቅ ሥራ እየሠራን አንዲት ኃጢአት ብንሠራ ስለዚያች
ኃጢአት የጽድቃችን ሥራ ዋጋ ያጣል፡፡ ሠይጣን ምቹ ጊዜና ሁኔታን ካገኘ በልቡናችን አድሮ እግዚአብሔርን ለማስካድ ፣ለጣዖት ለማሰገድና
ኃጢአት ለማሠራት ዝግጁ ነው፡፡ ሰይጣን የምንወድደውን ኃጢአት እንደቀዳዳ ተጠቅሞ ወደ ሌሎች ኃጢአቶች አስፋፍቶ ወደ ሲዖል ይጥለናል፡፡
ለምሳሌ ፡- የመጠጥ ሱስ ያለበትን ሰው ከአንድ ወደ ሁለት ፣ ከሁለት ወደ ሦስት ፣ ከዚያም ወደ አራት እንዲህ ትንሿን ካሰፋ በኋላ
እስክንሰክር እንድንጠጣ ያደርግና ሰካራም በሚለው ሥም እንድንጠራ ያደርጋል፡፡ ስካርንም አስፍቶ አሳድጎ በዝሙት እንድንወድቅ ያደርገናል፡፡
ተመልከቱ ሰይጣን በዝሙት ለመጣል የተጠቀመው ትንሽ ቀዳዳ አንድ መጠጣትን ነው፡፡ ሰይጣን ከዜሮ ተነስቶ አያጠቃም፤ መነሻ የሚያደርገው
ጥቂት ቀዳዳን ይፈልጋል እንጅ፡፡ ስለዚህ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ነውና አውቀን በቀደድነው የማናውቀው እንዳይገባ የልቡና አጥራችንን
በሚገባ ልናጥር ይገባናል፡፡
አባት ያበጀው…
ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ዕብ13÷6 “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን
አስቡ፡፡ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ይደግፋል፡፡ ሥነ ቃሉ “አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” የሚል ነው፡፡ የሥጋም ሆኑ የመንፈስ አባቶቻችን ለእኛ ለልጆቻቸው ያሳዩን በርካታ
መንገዶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መንገዶች መካከል ለእኛ የሚበጁንም የማይበጁንም አሉ፡፡ ለእኛ ለክርስቲያኖች የሚበጁን አባቶቻችን የነገሩን
የእግዚአብሔር ቃል ፣ የኑሯቸው ፍሬ፣ እምነታቸው ፣ የሠሩልን ሥርዓት ፣ ዜማው፣ ቅኔው፣ ጸሎቱ፣ ጾሙ፣ ስግደቱ ወዘተ… ነው፡፡
አባቶቻችን ጤዛ ልሰው፣ ዳዋ ጥሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ በዱር በበረሐ በገደል ተንከራትተው ቅዱሳት መጻሕፍቱን ፣ጽላቱን ደብቀው
ባያቆዩን፣ ያሬድም መጻሕፍትን በዜማ ባይደርስልን፣ አብያተ ክርስቲያናትን ባያንጹልን፣ የጥምቀት ፣ የቁርባን፣የተክሊል፣የቅዳሴ፣
የንስሓ ወዘተ… ሥርዓት ባይሠሩልን እኛ ልጆቻቸው ምን ይበጀን ነበር? አባቶቻችን ባበጁልን ሥርዓት የማንጓዝ ከሆነ አባት ያበጀው
ለልጅ ይበጀው እንዲሉ ራሳችንን ፈትሸን ዋኖቻችንን ልናስባቸው በእምነት ልንመስላቸው ይገባናል፡፡
በሌላ መልኩ የሥጋ አባቶቻችን
ጣዖት በማምለክ ፣ ጾም በመግደፍ ፣ ሐሰት በመናገር፣ በመስከር፣ በመስረቅ ወዘተ… ያሳዩን መንገድ ካለ ይህ ለእኛ የሚበጅ መንገድ
አይደለምና ልንጓዝበት አይገባም፡፡ እንዲህ አይነቱን “አባት ያበጀው
ለልጅ አይበጀው” ብንለው ይቀናል፡፡ ምክንያቱም እያሳዩን ያለ የኃጢአት መንገድ ብቻ ስለሆነ፡፡
ስለዚህ “አባት ያበጀው
ለልጅ ይበጀው” የሚለው በቃለ እግዚአብሔር የጸኑት፣ የኑሯቸው ፍሬ አስተማሪ የሆኑት፣ በእምነታቸው የጸኑት፣ በትምህርታቸው
መናፍቃንን የረቱት ፣ በጸሎታቸው የሚጠብቁት አባቶች ያበጁት ሥርዓት በእነርሱ እግር ለተተካን ልጆቻቸው ይበጁናልና የቀደሙ አባቶች
በሠሩልን ሥርዓት በከፈቱልን መንገድ ልንጓዝ ይገባናል፡፡
No comments:
Post a Comment