© በመልካሙ በየነ
ጥር 18/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ዛሬስ ደግሞ ምኖች መጡና አረፉታ! እነ “ብጹእ
ወቅዱስ አቡነ” መልከጼዴቅ እነ “ቀሲስ” መላኩ ተረፈ ፍቅረ ኦርጋን አንገበገባቸው አንሰፈሰፋቸውሳ፡፡ አንድ ሞኝ የተከለውን ሃምሳ
ሊቃውንት አይነቅሉትም አለ የአገሬ ሰው፡፡ እናንተ ሰነፎች! እናንተ ጅሎች! እናንተ ሞኞች! ዛሬ ለመትከል የምትሯሯጡትን ምንፍቅና
ሀምሳ ሊቃውንት ለመንቀል በሚያስቸግራቸው ሁኔታ ልታደርጉት ነው የተነሣችሁ፡፡ እየቀላቀላችሁ ትውልዱን ልትነጥቁት የበግ ለምድ የለበሳችሁ
ተኩላዎች እባካችሁ ታገሱ ወደ ልባችሁ ተመለሱ፡፡ እንዴ! ምን ሆናችሁ? ምን ነካችሁ? የክርስቶስን ጥምቀት ልብ በሉት እንጅ፡፡
ጌታ ነው ወይስ ባሪያው ዮሐንስ ነው ወደ መጠመቂያ ቦታው የሄደው? መጠመቅ የፈለገው ነው ወይስ ማጥመቅ የፈለገው ነው ወደ መጠመቂያው
የወረደው? ረስታችሁታል መሰለኝ፡፡ አቡኑም ቀሲሱም ረሳችሁት? እሽ ልመልስላችሁ ጌታ መጠመቅ ፈለገ ወደሚያጠምቀው ባሪያው ወደ ዮሐንስ
ሔደ፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው መጠመቅ የሚፈልግ ሰው ነው ወደ መጠመቂያ ቦታው መሔድ ያለበት አይደል፡፡ ስለዚህ እንደዚያ ከሆነ ፍቅረ
ኦርጋን ያቃጠለው ሰው ኦርጋን ወደሚገኝበት ቦታ መሄድ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን እርሱ ፍቅረ ኦርጋን ስላደረበት ሌሎችንም ፍቅረ
ኦርጋን እንዲያድርባቸው ማስገደድ አይችልም፡፡ መብቱም አይደለም፡፡
በ1970ዎቹ አካባቢ የወጡ የመዝሙር ካሴቶች
ለምሳሌ ሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብ ወ/ቂርቆስ ቁጥር1 እና 2 እንዲሁም ሌሎች ኦርጋንን ተጠቅመው መዝሙር አሳትመዋል፡፡ አሁን እነዚህ
ፍቅረ ኦርጋን ያንገበገባቸው ሰዎች እንደማሳመኛ የሚጠቀሙት ይህንን የሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብን እንደቸርነትህ የሚለውን በኦርጋን
የተሠራውን መዝሙር ነው፡፡ በሆነ ዘመን የሆነ ጅል የተከለውና ሊቃውንት ለመንቀል አልመቻቸው ብሎ የቆየው በኋላ ግን ጊዜው ሲደርስ
የነቀሉት አረም ነው ኦርጋን፡፡ ታዲያ የዚያን ዘመን የነበሩትን ጳጳሳት እንደማስረጃ ልንጠቀምባቸውና የአሁኑን ሥርዓተ ቤተ-ክርስቲያን
ልንጥስበት አንችልም፡፡ ያ ዘመን በቃ ከነችግሩ ከነኃጢአቱ ከነቆሻሻው ተጥሏል፡፡ አዲስ አዋጅ አዲስ ሥርዓት ተሠርቷል፡፡ ኦርጋንን
መጠቀም አይቻልም ተብሎ የእኛ የሆኑት መሰንቆ፣ በገና፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ፣ እንቢልታ፣ ከበሮ ተለይተው ልንጠቀምባቸው ሥርዓት ተሠራልን፡፡
ይህ የሆነው እኮ የዛሬ ስንት እና ስንት ዓመት ነው፡፡ ታዲያ እስከዛሬ የት ነበርን? ዳንስ ያማራችሁ ጭፈራ ያማራችሁ ዛሬ ነው
እንዴ? ወይስ ደግሞ ብቻችንን ከምንጨፍር ብቻችንን ከምንደንስ ልጆቻችንን ይዘናቸው እንጥፋ ነው?
ሌላው በጣም የሚገርመኝ ነገር አርጋኖንን እና
ኦርጋንን በማቀላቀል በሕዝቡ ዘንድ ብዥታን ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ “ሊበሏት ያሏትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል”
ነው የሚባለው አይደል፡፡ አርጋኖን ማለት እኮ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ብቻ የምንጠቀምባቸው ከብረት ከእንጨት ወይም ከነሐስ የተሠሩ
መሣሪያዎችን እንደ ጸናጽል እንደ እንዚራ ያሉትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በሌላ በኩል አርጋኖን ማለት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እመቤታችንን
ያመሰገነበት የምስጋና መጽሐፍ ነው መጽሐፈ አርጋኖን እንዲል፡፡ ሌላም አርጋኖን ማለት የበገና ሰላምታ የበገና ድርድር ማለት ነው፡፡
ነገር ግን እነ “አቡነ” መልከጼዴቅ እና እነ “ቀሲስ” መላኩ ተረፈ ፍቅረ ኦርጋናቸውን በአርጋኖን ስም ለውጠው ብቅ ብለዋል፡፡
“አቡኑ” ወይም “ቀሲሱ” በነካ እጃችሁ በተናገረ አፋችሁ እዛው ጨርሱት መቼም አንዴ ከስራችኋል አርጋኖን አትበሉ ኦርጋን በሉ፡፡
አርጋኖኑን እኛው እናመስግንበት ኦርጋኑን ግን እናንተው እንደጀመራችሁ ጠቅልላችሁ ውሰዱልን አንፈልገውም፡፡ እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም የተረፈ ምርጥ ምርጥ ልብን የሚመስጡ ንዋያት አሏት፡፡ እኛ መሰንቆው ይበቃናል፣ እኛ ጸናጽሉ
ይበቃናል፣ እኛ ከበሮው ይበቃናን፣ እኛ በገናው ይበቃናል፣ እኛ መቋሚያው ይበቃናል፣ እኛ እንዚራው እንቢልታው ይበቃናል፣ እኛ የእኛ
የሆነው ብቻ ይበቃናል ይህ አልበቃው ያለ ሰው ግን እዛው ከለመደው ባዶ አዳራሽ ገብቶ ይደንስ ይጨፍር መቼስ ምን እናደርገዋለን፡፡
ያላወቀውን እናሳውቃለን አዋቂ ነኝ ያለውን ግን ምን እናደርገዋለን፡፡ ሰው በስተርጅና ዳንስ ጭፈራ እንዴት ይመኛል? ያውም ጳጳሱ
አቡነ አቡነ የምንላቸው ያውም ቀሲሱ ይፍቱኝ ይባርኩኝ የምንላቸው፡፡
ለዚህ ትቅልድ ግን መልእክቴ አርጋኖን ስንል
የሙዚቃ መሣሪያ የሚለው የእነ አቡኑ እና የእነ ቀሲሱ አመለካከት እንዳይሸረሽራችሁ ነው፡፡ እነርሱ ኦርጋን ለማለት ፈልገው ነው
ሳያውቁት አርጋኖን ያሉት፡፡ አርጋኖንን የእመቤታችን ፍቅሯ ጣዕሟ ውዳሴዋ የሚበልጥበት ክርስቲያን ገዝቶ የሚጸልየው መጽሐፍ ነው፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን እናመሰግነዋለን መጽሐፈ አርጋኖንን እንጸልይበት ዘንድ ከእናታችን ከእመብርሃን ረድኤትን በረከትን እናገኝ
ዘንድ ስለረዳን፡፡ ዛሬ ፍቅረ ኦርጋን ያደረባቸው ሰዎች አርጋኖን እያሉ ስሙን ለመቀላቀል ቢፈልጉም እኛ ግን አባቶቻችን መምህራን
አባቶቻችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን እነዳሳዩን እንጓዛለን እንመራለን፡፡