ታህሳስ 26/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
በዓላትን ተንተርሰው የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ድሮ ድሮ አባቶቻችን ለዘመን መለወጫ “እንቁ ጣጣሽ” የሚል ስም ያወጡት
በዓሉ ብዙ ጣጣ ስለነበረበት ነው ይባላል፡፡ ስለ በዓሉ ክብር ሲባል በጉ፣ ዶሮው፣ ዳቦው፣ጠላው፣ ጠጁ ሁሉም መዘጋጀት ያስፈልገዋል፡፡
ያንን ሁሉ ለማሟላት ደግሞ ገንዘብ ይጠይቃል ስለዚህ ያን ገንዘብ ማግኘት ከባድ ስለሆነ “ጣጣሽ” አሏት፡፡ እኔን የሚቆጨኝ አባቶቻችን
ዛሬ ተነሥተው እኛን አለማየታቸው ብቻ ነው፡፡ እኛ በጉ፣ ዶሮው፣ ጠላው፣ ዳቦው፣ ጠጁ ምናችን ነው? ለእኛ እኮ ለዘመናዊዎቹ በዓል ክብር የሚኖረው በዚህ አይደለም በአሻንጉሊቶቹ ነው፡፡ አሻንጉሊቶችን
ደርድረን በቀላሉ በዓሉን እንሸውደዋለን እናታልለዋለን የምን ወጭ የምን ጣጣ ነው፡፡ እንደውም አባቶቻችን ለደቂቃ ተነሥተው ቢመለከቱን
ባህላችን ባህላቸውን መስሎ ስለማያገኙት “እንቁ ጣጣሽ” ን “እንቁ አሻንጉሊት”፣ “ገና”ንም “አሻንጉሊትና” ፋሲካን ወይም ትንሣኤንም
“ኢስተር አሻንጉሊት” ብለው ስም ያወጡልን ነበር፡፡ ለቅጽበት ቢነሡ “በእውነት ልጆቻችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነበርን የቀበሩን?” ማለታቸውም
የማይቀር ነው፡፡ ግን ለምን ለአሻንጉሊት ክብርን መስጠት አስፈለገን?
ዛሬ እኮ ሱቆች የተሞሉት ቤቶች ያሸበረቁት በአሻንጉሊቶች
ብዛት ነው፡፡ እኔ “ለምን በፍቅረ አሻንጉሊት ተነደፍን” የሚለውን ጥያቄ የምመልስበት የራሴ እይታና አስተሳሰብ አለኝ፡፡ እኔ የምገምተው
ለምሳሌ ሕጻናትን የሚመስሉ አሻንጉሊቶችን ታቅፈው የሚያድሩ ሴቶች አሉ ወንዶችም እንዲሁ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ባልና ሚስትም በመካከላቸው
እንደ ሕጻን ሕጻናትን ሊተኩ ከሚችሉ አሻንጉሊቶች መርጠው ሊያስተኙ
ይችላሉ፡፡ በዚህ ዘመን ልጅ ለመታቀፍ ልጅ ለማሳደግ ከባድ የሆነባቸው ሰዎች አሻንጉሊት ታቅፈው ኑሮን ይሸውዱታል ያታልሉታል፡፡
ሕጻንን ለማሳደግ ለቁም ነገር ለማብቃት 9 ወር ማርገዝን ከዚያም አምጦ መውለድን ከዚያም ማልበስን መንከባከብን ማብላት ማጠጣትን
ይጠይቃል፡፡ አሻንጉሊት ግን ራበኝ አብሉኝ ጠማኝ አጠጡኝ በረደኝ አልብሱኝ ብሎ አያለቅስብንም፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ፍቅረ አሻንጉሊት ያንገበገበን፡፡ እናት አባቶቻችን ስንት ደክመው ስንቱን ወጥተው ስንቱን ወርደው ሳይማሩ
አስተምረው ሳይለብሱ አልብሰው ለቁም ነገር ያደረሱን ወልዳችሁ ሳሙ ዘርታችሁ ቃሙ፣ ዓይናችሁን በዓይናችሁ ለማየት ያብቃችሁ ብለው የመረቁን በስህተት ነበር ለካ፡፡ ምክንያቱም እኛ እየሳምን ያለነው
የወለድነውን ልጅ ሳይሆን የገዛነውን አሻንጉሊት ነዋ፡፡ ምክንያቱም እኛ ዓይናችንን በዓይናችን አይተናል የምንለው አሻንጉሊት ታቅፈን
ቁም መስታወት ፊት ለፊት ቆመን አምሮብኛል አላማረብኝም እያልን የምንለውን
ነዋ፡፡ ውጮቹን ምዕራባውያኑን እንመስላለን ብለን ራሳችንን መሆን አቃተን፡፡ እነርሱ የራሳቸው አስተሳሰብ፣ የራሳቸው አመለካከት፣
የራሳቸው ባህል፣ የራሳቸው የሆነ ነገር አላቸው ከአሻንጉሊቶች ጋርም የተዛመደ ነገር ሊኖራቸው ይችላል እኛ ደግሞ የራሳችን የሆነ
ከእነርሱ ጋር የማያዛምደን ዓለምን የሚያስደንቅና የሚያስደምም ባህል አለን፡፡ የእነርሱን አለባበስ የእነርሱን ባህል የእነርሱን
አመጋገብ የእነርሱን አነጋገር ወዘተ ሙሉ በሙሉ እኛን በሚመስልና እኛን በሚመጥን መልኩ አለመውሰዳችን ጥፋታችንን ያጎላዋል፡፡
ሌላው የሚገርመኝ ነገር “የገና ዛፍ” የሚባለው
አሻንጉሊት ዛፍ ነው፡፡ በመጀመሪያ ይህንን ስም ያወጣለት ሰው ማነው? ምክንያቱም ገና የሚባለውን የምናውቀው እኛ ኢትዮጵያውያን
ብቻ ነን፡፡ በእኛ የባህል ታሪክ ውስጥ በዓላትን የምናከብረው በጉን፣
ዶሮውን፣ እንቁላሉን፣ ጠላውን፣ ጠጁን ወዘተ በማድረግ ራሳችን በሠራነው ራሳችን በጋገርነው ራሳችን ባረድነው ራሳችን በጠመቅነው
ራሳችን በደፋነው ነገር ብቻ ነው፡፡ በዓላትን ያለው ለሌለው አካፍሎ በአንድ መሶብ ልጅ አዋቂው ከብቦ እየተመገበ አፈር ስሆን ብሉ
አፈር ስሆን ጠጡ በሚሉት እናቶቻችን አጅ ጉርሻም እየተቀበልን ነው ያደግነው፡፡ ታዲያ ዛሬ “የገና ዛፍ” የሚባል አሻንጉሊት አቁመን
“መልካም ገና” መባባላችን ትርጉሙ ምንድን ነው? በእውነት ባህል ያለው ሰው ታሪክ ያለው ሰው እምነት ያለው ሰው አፍሪካ ምድር
ቅድስቲቱ አገር ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ሰው መሶብን በአሻንጉሊት መለወጡ ምን ያህል ያሳምማል? በእርግጥ አብሉኝ አጠጡኝ ማዳበሪያ
ጨምሩልኝ ስለማይለን ሊሆን ይችላል፡፡ ፈረንጆቹ “የገና ዛፍን” የሚጠቀሙበት የራሳቸው የሆነ ምክንያት አላቸው እኛ ግን ምንም ምክንያት
የለንም፡፡ እነርሱ በደጉ ዘመን የነበረው አምላካቸው በክፉ ዘመን ድርቅ ሲሆን ሁሉም ዛፎች ሲደርቁ ጽድ ግን በበጋም ስለማይደርቅ
አምላካቸው በዚያ ተሸሽጎ ደጉ ዘመን እስኪመጣ ጠብቆ ደጉ ዘመን ሲመጣ ከዚያ ከተሸሸገበት ዛፍ ይወጣል ብለው ያምናሉ፡፡ ለዚያም
ባለውለታቸው ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ ለዚህም ነው “የገና ዛፎች” ከጽድ ዛፍ ጋር ተመሳስለው የተሠሩት፡፡ አምላካቸውን ደብቆ ላቆየላቸው
ባለውለታቸው ክብር ሰጥተው በመብራቶች አሸብርቀው በዓላትን ያከብሩበታል እንዲያውም ያመልኩበታልም፡፡ እኛ ደግሞ በክፉ ዘመን የሚሸሸግ
በደጉ ዘመን እንደ መስቀል ወፍ ብቅ የሚል አምላክ የለንም፡፡ ደግ ዘመን ክፉ ዘመን ሁሉም የሚሆነው በእግዚአብሔር ነው ብለን የምናምን
ክርስቲያኖች ነን፡፡ ታዲያ እንዲህ ከሆነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ “የገና ዛፍ” ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል? ምንም ትርጉም የለውም
ምናልባት አምልኮ ባዕድ ካልተጠናወተን በስተቀር፡፡ ዛፍ አምላኪነት የተጠናወታቸው ሰዎች ግን በዓላትን ምክንያት ማድረግ አይጠበቅባቸውም፡፡
ሁልጊዜም ሊወድቁለት ሊሰግዱለት ሊገዙለት ያስፈልጋል፡፡ ስለ ገና ዛፍ ምንነትና የት መጣነት ይህንን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ፡፡
www.dw.com/am/የገና-ዛፍ-እና-የገና-አባት-ታሪክ/a-16481554 ወይም ይህንን
lemabesufekad.blogspot.com/2014/12/blog-post_24.html?m=1
www.dw.com/am/የገና-ዛፍ-እና-የገና-አባት-ታሪክ/a-16481554 ወይም ይህንን
lemabesufekad.blogspot.com/2014/12/blog-post_24.html?m=1
ይቅርታ አድርጉልኝ እንጅ አሻንጉሊትን የሚጠቀመው
ማኅበረሰብ በብዛት ሰነፍ ነው፡፡ አንድን ሕጻን እና አንድን ዛፍ ከማሳደግ ይልቅ ምንም የማያስቸግሩትን አሻንጉሊቶች መግዛት መታቀፍና
ማቆም ይቀናዋል፡፡ ግን ባህላችን አለመሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡ ምን ችግር አለው እኔ የምፈልገው ጌጥነቱን እንጅ አላመልከው
ልንል አያስፈልግም፡፡ “ፍቅረ አሻንጉሊት” ለመጨመሩ ብዙ ማሳያዎችን እየተመለከትን ነው፡፡ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የሚገዟቸውን ልብሶች
ቅድሚያ የሚለብሱት አሻንጉሊቶች ናቸው፡፡ ልብስ ከሚሸጥባቸው ሱቆች ጎራ በሉና ይህንን አረጋግጡ፡፡ አዳዲስ ዘመናዊ “ፋሽን” የሚባሉ
ነገሮችን ቅድሚያ የምናያቸው አሻንጉሊቶች ለብሰዋቸው ነው፡፡ ግን ስለ እውነት እንነጋገር እስኪ አንዱ የለበሰውን ልብስ እንድንለብስ
ቢሰጠን እንለብሰዋለን? የእህቶቻችንን የወንድሞቻችንን ልብስ ለመልበስ እንኳ አንፈልግም ምክንያቱም ያ “የማንም ልባሽ” ነዋ፡፡
ታዲያ ላንተ ታዲያ ላንች ከእህትህ ከወንድምህ ከእህትሽ ከወንድምሽ አሻንጉሊት በልጦብህ/ሽ ነው የአሻንጉሊት ልባሽ የምትለብሰው/
የምትለብሽው፡፡ አቤት ጉድ!!!! ፍቅራችንን መተሳሰባችንንም ለካ አሻንጉሊት ተሻምቶብናል፡፡
No comments:
Post a Comment