© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 25/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ድኅነት ሲል በፈቃዱ
በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ የተናገራቸው ተአምራት ቃላተ ርኅራኄ
ሰባት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት የመስቀሉ ላይ የርኅራኄ ቃላት ምን ምን ናቸው የሚለውን ከነሐተታቸው እነሆ፡፡ መልካም ንባብ!!!
1.
አምላኪየ አምላኪየ ነጽረኒ ወለምንት
ኀደገኒ፡- አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ ማለቱ ነው፡፡ “አምላኪየ አምላኪየ ነጽረኒ” ማለቱ ነጽር ሊተ ተመልከት፡፡ ምዕመናንን ከፍትወታት እኩያት ከኃጣውእ ርኩሳት
ጠብቅልኝ በዓይነ ምሕረት እይልኝ ሲል ነው፡፡ ወለምንት ኀደገኒ፡-አቤቱ ምዕመናንን በበደሉት በደል እኔ ከካስሁላቸው በኋላ ምነው
ለምን ችላ ትልብኛለህ አውጣልኝ እንጅ ምነው ገሐነመ እሳት አወረድክብኝ ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ሥጋ መልበሱን ሲያስረዳንና
እኛን ተገብቶ ሲጸልይልን ነው፡፡
2.
አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ፡- የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር
በላቸው ማለቱ ነው፡፡ መላእክት በቀትር ፈጣሪያቸውን ሊያመሰግኑ ሲመጡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራቁቱን በቀራንዮ አደባባይ በእንጨት ላይ
ተሰቅሎ ፊቱ ደም ለብሶ ሲያዩት ደንግጠው እንደ ሻሽ ተነጸፉ እንደ ቅጠል ረገፉ፡፡ ከዚህ በኋላ መልአኩ ሚካኤል ዝም ሲል መልአኩ
ገብርኤል ግን በጣም ተበሳጭቶ አይሁድን በሰይፍ ሊያጠፋቸው ሰይፉን አነሣ የዚህን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱን ተዋቸው አታጥፋቸው
የሚሠሩትን እና የሚደርጉትን ስለማያውቁ ነው ብሎታል፡፡ ገብርኤል ግን የአንተ ቸርነት አያልቅም ብሎ ተቆጥቶ ሰይፉን ወረወረው ሰይፉም
የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ለሁለት ከፍሎ ወደ መሬት ገባ እስካሁንም ድረስ ወደታች ሲሄድ ይኖራል፡፡
3.
ነዋ ወልድኪ ወነያ እምከ
፡- እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ ማለቱ ነው፡፡ ጌታችን የተሰቀለ ዕለት እመቤታችን በከተማው ውላ ነበርና ጌታችን ዮሐንስን ጠርቶ
እናቴን ጥራልኝ መከራየን ትመልከት አለው፡፡ ዮሐንስም ሄዶ እመቤታችንን እነሆ ልጅሽን ሰቀሉት ሲላት እርሷም ደንግጣ በሐዘን እያለቀሰች
እየወደቀች እየተነሣች ከተሰቀለበት ቦታ ደርሳለች፡፡ በዚያም ራቁቱን ተሰቅሎ ስታይ ምርር ብላ አለቀሰች መልአኩ ጌታን ትወልጃለሽ
ብሎ ያበሰረኝ ብሥራት ሞት ሆኖ በገደለኝ ነበር እያለች አለቀሰች፡፡
ጌታም እናቴ ሆይ ብታለቅሽ ብታለቅሽ አይታክትሽምን እኔ ካልሞትሁላቸው 5500 ዘመን በዲያብሎስ ቁራኝነት የተያዙ ነፍሳት አይድኑም
ዛሬ መከራው ሐዘኑ እንደበዛብሽ ነገ ዘመዶችሽ ብርሃን ለብሰው ከሲዖል ሲወጡ ስታዪ ደስታሽ ይበዛልና ተዪ አታልቅሽ አላት፡፡ የታመመ
ሰው ልጄን ሚስቴን አደራ እንዲል እንዲሁ ጌታም እናት ትሆነው ዘንድ እርሱም ልጅ ይሆናት ዘንድ ለዮሐንስ አደራ ብሎታል፡፡ ይህን
ቃል የተናገረው ለዚሁ ነው፡፡
4.
ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ፡- ትርጉሙ እንደመጀመሪያው
አምላኪየ አምላኪየ እንዳለው ያለ ነው፡፡ ነገር ግን “ኤልማስ” ሲል አይሁድ
ኤልያስ ያለ መስሏቸው ኤልያስ መጥቶ ሳያድነው ቶሎ የሚገድለውን ነገር እንስጠው ብለው የዝኆን ሐሞት አጠጥተውታል፡፡
5.
ወአንተ ትቀድሞ ለአዳም በዊአ ውስተ ገነተ፡- አንተ አዳምን ቀድመህ ገነት ትገባለህ ማለቱ ነው፡፡ ከጌታ ጋር 2 ወንበዴ ሽፍቶች አብረው
ተሰቅለው ነበር፡፡ አንደኛው በቀኝ ያለው ጥጦስ በሰማይ 3 በምድር 4 ተአምራት ሲደረጉ አይቶ “ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ
ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ዳግም ምጽአትከ” እያለ ሲጸልይ ጌታ ወደ የማናይ አንገቱን ዘንበል አድርጎ ግብጽ ስንወርድ የነገርሁህ ሁሉ
ደረሰ አለው፡፡ ስለዚህ ከሞቴ በቀር የቀረኝ የለምና አንተ አዳምን ቀድመህ ገነት ትገባለህ ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶት አዳምን ተቀድሞ
ገነት ግብቷል፡፡
6.
አባ አማሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ፡- አቤቱ
ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ ማለቱ ነው፡፡ በዘመነ ኦሪት ጊዜ የነበሩ ሰዎች ነፍስ ከሥጋቸው እየተለየች ሲዖል ትወርድ ነበር
አሁን ጌታ ከተሰቀለ በኋላ ግን ገነት ይገቡ ጀመር፡፡ ስለዚህ ነፍሳችን እንደ ኦሪቱ ሲዖል ብቻ ሳይሆን ገነት መንግሥተ ሰማያትም
እንደምትገባ ሲናገር ነው፡፡ አንድም አዳምን ተቀድሞ ጥጦስ ገነትን በደመ ማኅተሙ ከፍቶ ገብቷልና ገነት መግባት መጀመሩን ያሳያል፡፡
7.
ተፈጸመ ኩሉ፡- ሁሉ ነገር ተፈጸመ ሲል ነው፡፡ አምላክ የመጣበት የድኅነት ሥራ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ
ሥጋውን በመቁረስ እንደፈጸመው እንደደመደመው ሲናገር ነው፡፡ በመጻሕት የተጻፈው በነቢያት የተነገረው ሁሉ ደረሰ ሁሉ ነገር ተፈጸመ
ሲል ነው፡፡
እነዚህን
ሰባቱን በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥላጣኑ ለየ፡፡
ምስጋና
ይሁን ለአብ ምስጋና ይሁን ለወልድ ምስጋና ይሁን ለመንፈስ ቅዱስ፡፡
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment