© በመልካሙ በየነ
ጥር 17/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ሰው ነህና መቼም ፈተና ይገጥምሃል፤ ደካማ ነህና
ደግሞ አምላክህን ታማርራለህ፡፡ የፈጠረህ አምላክ ነገ ላንተ ያዘጋጀልህን ነገር ሳታውቅ በዛሬው ነገር ላይ ብቻ ጭንቅላትህ እስኪፈነዳ
ድረስ ትጨነቃለህ፡፡ ነገር ግን ነገ ሌላ ቀን ነው በእውነት ነገ ሌላ ነው፡፡ ሰው መሆናችን ከሌላው ፍጥረት የሚለየን ነገን ተስፋ
በማድረግ መኖራችን ነው፡፡ እንስሳትን ተመልከት ነገን ተስፋ አያደርጉም ምክንያቱም አእምሮ የላቸውምና ነው፡፡ ዓለም በፈተና የተሞላች
ናት ሰው ደግሞ በዚህች ዓለም ውስጥ ሲኖር የግድ የፈተናው ተቋዳሽ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ አንተ የምትጨነቀው ብታገኘው ስለሚጎዳህ
ነገር ሁሉ ነው፡፡ ፈጣሪ ደግሞ የለመንከውን ሁሉ የማይሰጥህ እንዳትጠፋበት፣ እንዳትሞትበት፣ እንዳትጎዳበት ነው፡፡ ወደፊት የሚመጣውን
የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው ነገን ማን ያውቃል? አንተ ነቢይ አይደለህም፤ ያለፈውንና የሚመጣውን አትመለከትም፤ ታዲያ ዛሬ ላይ ሆነህ
ስለዛሬ ብቻ ስለምን ትጨነቃለህ? ስለምንስ ፈጣሪህን ታማርራለህ? በእውነት አምላካችን እኮ እኛ ስለእኛ ከምንጨነቅበት የበለጠ ያስብልናል፡፡
የምንተነፍሰው አየር የማን ነው? የምንጠጣው ውኃ የማን ነው? የምንሞቀው ጸሐይ የማን ነው? የምናይበት ዓይናችን፣ የምንሔድበት
እግራችን፣ የምንዳስስበት እጃችን፣ የምንሰማበት ጆሯችን፣ የምናሸትበት አፍንጫችን …የማን ነው? እስኪ አስቡት እኛ ለእኛነታችን
ምን አስተዋጽኦ አበርክተናል? ምንም!
አንተ የበላይህን እያየህ የበታችህን ሳትመለከት
የቤትህን መጉደል እየተመለከትህ ትጨነቃለህ፡፡ አንተ በኪራይ ቤት ስለምትኖር ሌሎች የራሳቸውን ቤት ስለሠሩ እኔስ መቼ ይሆን ቤት
የምሠራው? እያልክ ራስህን ትጠይቃለህ፡፡ ግን መልስ የለህም ምክንያም የጠየቅኸው ጥያቄ መልስ የሚያገኘው በፈጣሪ ስለሆነ፡፡ ከአንተ
በታች የሚከራዩበት ገንዘብ አጥተው ሜዳ ላይ የቀን ጸሐይ የሌሊት ቁር የሚፈራረቅባቸውን ወገኖችህን አላስታወስክም፡፡ አንተ የበላይህን
እየተመለከትህ በቀን 3 እና 4 ጊዜ የተለያየ ይዘት ያለውን ምግብ እንዴት እና መቼ መቼ ልመገብ እያልክ ትጨነቃለህ፡፡ ነገር ግን
በቀን አንድ ጊዜ እንኳ የሚመገቡት አጥተው መንገድ ዳር የወደቁ ወገኖችህን ረስተሃል፡፡ አንተ የቱን “ፋሽን” ልብስ ልልበስ የቱ
ያምርብኛል እያልክ ትጨነቃለህ ነገር ግን ወገኖችህ የሚቀይሩት ልብስ አጥተው የተባይ መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ሰው መሆን ማለት እንዲህ
ለሌሎች አለማሰብ ከሆነ ከሆነ ሰው አለመሆን መቶ እጥፍ ይሻላል፡፡ የሚገርመው ነገር አንድ ቀን እኩል እንሆናታለን እኮ፡፡ በላህ፣
ጠጣህ፣ ለበስክ፣ አጌጥህ፣ አማረብህ፣ ወፈርህ፣ ቀላህ … ከዚያስ? ወገኖቻችን ደግሞ ተራቡ፣ ተጠሙ፣ ታረዙ፣ አዳፋ ሆኑ፣ ለእይታ
አላምር አሉ፣ ከሱ፣ ቀጨጩ፣ ጠቆሩ፣ ሥጋቸው ከአጥንታቸው ጋር ተጣበቀ… ከዚያስ?
ከዚያማ እነሱም በችግር ይኖራሉ
እኛም በድሎት በምቾት በቅንጦት እንኖራለን፡፡ ነገር ግን እኛ በደም ብዛት እንሰቃያለን እነሱ ጤና! እኛ በስኳር ህመም ሺህ ሆስፒታል
እንንከራተታለን እነርሱ ጤና ! እኛ በልብ በሽታ በብርድ ህመም እንሰቃያለን እነርሱ ጤና! እኛ በኩላሊት በጨጓራ በሽታ እንቃጠላለን
እነርሱ ጤና! ታዲያ መጨነቃችን ምን ለውጥ አመጣልን? ምንም!!!! “ዋናው አድሮ መገኘቱ ነው” የምላት አባባሌ ደስ ትለኛለች፡፡
ስትራብ የጠገቡትን አታስብ፣ ስትታረዝ የለበሱትን አታስብ፣ ስትጠማ የረኩትን የጠጡትን አታስብ፣ ስትታመም ጤነኞችን አታስብ ምክንያቱም
ጥቅም የለውም፡፡ ምናልባት ተስፋ የምናደርገውን ነገር ለመጠበቅ ካልሆነ በቀር ምንም አይረባንም፡፡ ነገር ግን ይህንን እያሰብን
ተስፋ ይኖረናል ብየ አልገምትም ምኞት ግን ሊኖረን ይችል ይሆናል፡፡ እኔ እኮ እገሌን ብሆን? እንዲህ አደርግ ነበር እያልን በምኞት
ባሕር ልንሰጥም እንችል ይሆናል፡፡ ምኞት ደግሞ ተስፋ አይደለምና አይጠቅመንም፡፡ እሱ በላ እኔ ተራብኩ ግን እኩል አድረን ተገኘን፤
እሱ ጠጣ እኔ ተጠማሁ ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ እሱ ለበሰ እኔ ታረዝኩ ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ እኔ ጠቆርሁ ገረጣሁ እሱ
ቀላ ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ እኔ ጎዳና ወድቄ አደርሁ እሱ በሚያምር አልጋ ላይ ተኝቶ አደረ ግን እኩል አድረን ተገኘን፣ እኔ
ገንዘብ የለኝም እሱ ደግሞ ሁሉ ሞልቶታል ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ እኔ ከውሻ ጋር ተሻምቼ ተመገብኩ እሱ ደግሞ በጠረንጴዛ ዙሪያ
በክብር ተቀምጦ ተመገበ ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ እኔ ባሪያ ሆኘ እየተንገላታሁ እሱ ደግሞ ጌታ ሆኖ እያንገላታ ኖርን ግን እኩል
አድረን ተገኘን፤ እኔ በስደት እጨነቃለሁ እሱ ግን ከቪላ ቤቱ ሰገነት ላይ ይንፈላሰሳል ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ እኔ በልመና
የሰው ፊት ይገርፈኛል እሱ ግን ገንዘብን ይጫወትበታል ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ እኔ ደመወዜ ከወር እስከ ወር አላደርስ ብሎኝ እጨነቃለሁ እሱ ግን ለ50
ዓመቱ የሚያቅድበት ገንዘብ አለው ግን እኩል አድረን ተገኘን፤ በቃ በሥጋ ደረጃ እኩል ነን፡፡ ዓላማችን ተስፋ የምናደርጋትን ነገ
አድሮ በመገኘት ማየት ነው፡፡ ፈጣሪህን ለማመስገን ምክንያት አትሻ፡፡ ዛሬ ሳይኖርህም አመስግነው ነገ ሲኖርህም አመስግነው፡፡ ዛሬ
ታመህም አመስግነው ነገ ስትድንም አመስግነው፡፡ ዛሬ ተርበህም አመስግነው ነገ ስትጠግብም አመስግነው፡፡ ዛሬ ስትታረዝም አመስግነው
ነገ ስትለብስም አመስግነው፡፡ ዛሬ መንገድ ዳር ወድቀህም አመስግነው ነገም ቤት ስትሠራም አመስግነው፡፡ ዛሬ ታስረህም አመስግነው
ነገ ስትፈታም አመስግነው፡፡ ስለሁሉ ነገር ስላደረገልህም ስላላደረገልህም ስለሚያደርግልህም ሁሉ አመስግነው፡፡ ምስጋና ገንዘቡ የሆነ
አምላክ አንተን እንዲረዳህ አመስግነው፡፡
በሥጋዊ አረዳድ ትልቁ ነገር አድሮ
መገኘቱ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ብዙ ዘመንን በችግር ከማሳለፍ አንድ ቀን ደስ ብሎኝ በልቼ ጠጥቼ ገንዘብ አግኝቼ ብሞት ይሻለኛል ይላሉ፡፡
እኔ ግን አልስማማበትም ምክንያቱም አምላክ ለሁሉ ነገር ጊዜ አለው፡፡ ዛሬ እኔ ድሃ እንድሆን ያደረገበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡
እኔ እንድራብ እንድጠማ ያደረገበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ምናልባት ገንዘቡን ቢሰጠኝና ብጠፋበትስ? ምናልባትስ ምግብ ሰጥቶኝ
እስክጠግብ በልቼ አምላኬን ረስቼ ብጠፋበትስ? የራሱ ጊዜ አለው በቃ ያንን ጊዜ በትእግስት መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ በ3
ብር ሎተሪ ሚሊየነር ያደርግሃል ምን ይሳነዋል፡፡ ነገር ግን ቁም ነገራችን ይህ ገንዘብ መሰብሰቡ አይደለም በሕይወት መኖሩ በቃለ
እግዚአብሔር መመራቱ ነው፡፡ ሁላችንም አድረን እንገኛለን ነገር ግን ለተለያዩ ዓላማዎች ነው አድረን የተገኘነው፡፡ ሰአታቱን ለመቆም፣
ኪዳኑን ለማድረስ፣ ቅዳሴውን ለማስቀደስ፣ ለመቁረብ ለማስቆረብ፣ ለጽድቅ ሥራ አድሮ የሚገኝ አለ ለኃጢአት ሥራውም አድሮ የሚገኝ
አለ፡፡ ስለዚህ ስለገንዘቡ ስለምግቡ ሳይሆን ስለንስሐው ስለጽድቁ ነገር ዋናው ነገር አድሮ መገኘቱ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment