© በመልካሙ በየነ
ጥር 06/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ይህ ሰላም በውሸት የሚገኝ ምናባዊ ሰላም ነው፡፡ሰላም
አለመኖሩ እየታወቀ “ሰላም አለ” እየተባለ የሚነገርለት ነው፡፡ “ሰላም ሳይኖር ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና” /ሕዝ13÷10/
ሐሰተኛነት ባሪያ ያደረጋቸው ሰዎች ሰላም በሌለበት መካከል “ሰላም አለ” እያሉ ሕዝቡን ያታልላሉ፡፡ ይህ እነርሱ አለ የሚሉት ሰላም
የውሸትነው፡፡ እነዚህ ሰዎችን ነቢዩ ኤርምያስ “ሰላም ሳይሆን ሰላም ሰላም ይላሉ” /ኤር 6÷14/ በማለት ይገልጻል፡፡ እንዲህ
አይነቱ ሰላም ምናባዊ ነው፤ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ አይደለም፡፡
መዳብን ወርቅ በስሱ ቀብተው ያብረቀርቁታል በወርቅ ዋጋም ይሸጡታል፤ ገዥዎች ለጊዜው ወርቅ የገዙ ይመስላቸዋል፡፡ የተወሰነ ጊዜ
ከተጠቀሙበት በኋላ ማንነቱን ይገልጥላቸዋል፡፡ የወርቁና የመዳቡ ጓደኝነት ጊዜያዊ ነው፡፡ የዚያን ጊዜ ወርቅ ሳይሆን መዳብ እንደገዙ
ይረዳሉ፤ እጅግም ያዝናሉ ይተክማል፡፡ ይህ ውሸተኛ ሰላም እንዲህ ያለ ነው፡፡ ለጊዜው ሰላም ይመስለናል እንጨብጠዋለን ከጨበጥነው
በኋላ ግን መርዝ ያለበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰው ኃጢአትን የሚሠራው ሰላም አገኝበት መስሎት ነው፡፡ በኋላ ግን ኅሊናው መሸከም
የማይችለውን ዕዳ ያሸክመውና ሰላሙን ያጣል፡፡ እንቁላል ላይ ላዩን ሲያዩት ጠንካራ ወድቆ የማይሰበር ይመስላል፡፡ ነገር ግን ያ
ጠንካራ የመሰለው ቅርፊት በውስጡ ፈሳሽ የያዘ ነው፡፡ ውሸተኛ ሰላም እንዲህ አይነት ነው፡፡ ንጉሥ አክዓብና ኤልዛቤል የናቡቴን
ርስት ለመውረስ ናቡቴን መግደል በቂ ሰላም የሚፈጥርላቸው መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ናቡቴን በመግደላቸው ሰላማቸውን አጡ፡፡/1ኛነገ20÷1-17/ ይህ አይነቱ ሰላም በማር የተለወሰ መርዝ ነው፡፡ ስትበላው ማር ስለሆነ ሊጣፍጥህ ቢችልም መርዝ
ስላለበት ደግሞ በስተጀርባው ሞት ያመጣል፡፡ ከሰዎች እና ከዓለም የምታገኘው ሰላም እንዲህ ያለ ሰላም ነው፡፡ ቃየን መልከ መልካሟን
ሉድ ለማግባትና በሰላም ለመኖር ነበር ወንድሙ አቤልን የገደለው፡፡ ነገር ግን በፊት ያሰበውን ሰላም ማግኘት አልቻለም፡፡ በአንጻሩ
በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ሆነ፡፡ ሰው የሰውን ልጅ ሲገድል ማንም ሳያውቅበት በሰላም ለመኖር አስቦ ነው፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር
የሚሠወር ነገር የለምና ያንን ኃጢአት መፈጸሙ ታውቆ ወደ ወኅኒ ቤት ሲወርድ ሰላሙ ይደፈርሳል፡፡ ያፈሰሰው ደም ኅሊናውን ያስጨንቀዋል፤
በእግዚአብሔር ፊትም ይከስሰዋል፡፡ በፊት ያሰበውን ሰላም ሳይሆን ጭንቀትን ይለብሳል፡፡ በዘመኑ የነበረው ንጉስ ሔሮድስ የወንድሙ
ፊሊጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ለአንተ አልተፈቀደችም ይለው የነበረውን መጥምቁ ዮሐንስን ወደ እስር ቤት አወረደው፡፡ ሄሮድያዳና ሔሮድስ
ተጋብተዋል፤ በዚህም መካከል የሚመጣባቸውን ነገር አይቀበሉም፡፡ በንጉሡ የልደት በዓል የሄሮድያዳ ልጅ ዘፈነችለት ሽልማትም እንደሚሰጣት
ቃል ገባላት፡፡ ለእናቷ አማከረቻት እናቷም ሰላም የነሣኝ ዮሐንስ የሚሉት ነቢይ ነውና አንገቱን ቆርጦ ይስጥሽ አለቻት፡፡ ለጊዜው
ቢያዝንም ቃል ገብቶላታልና በወኅኒ ቤት ውስጥ የዮሐንስን አንገት አስቆረጠው፡፡ /ማቴ13÷1-12/ የዮሐንስን አንገት መቁረጥ ሰላም
የሚፈጥርላቸው መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የዮሐንስ አንገት ክንፍ አውጥታ እየበረረች ለ 15 ዓመታት ያህል ያንኑ የቀደመውን
ትምህርቷን ማስተማር ቀጠለች፡፡ ሄሮድያዳና ሔሮድስ የጠበቁትን ሰላም ማግኘት አልቻሉም ውሸተኛ ሰላም ነበርና፡፡ሰላም ስለፈለግናት ብቻ የምትመጣልን አይደለችም፡፡ ሰላምበከበረ ዕንቁ በብዙ ዋጋ በሚከፈል ገንዘብ ልትገዛት
አትችልም፡፡ምናልባትለዛሬ ብቻ ደስታ የምትፈጥርልህን ሰላም ትገዛ
ይሆናል ለነገ የሚተርፍህ ሰላም ግን አታገኝም፡፡ ሰላምን ያይደለ ሰላም የመመስል ነገር ታጠራቅም ይሆናል እንጅ በሽብርና
በጭንቀት መካከል የመ፣ያስፈራህን የዕረፍት ሰላም አታገኝም፡፡ ዲያብሎስ በእጁ ሲያስገባህ የሰላምን ትርጉም ያሳጣሃል፡፡ በወንጌል
የተጻፈልን የጠፋው ልጅ ታሪክ ይህንን ያሳያል፡፡ ታናሹ ልጅ በምቾት፣ በሰላምና በደስታ ይኖርበት ከነበረው ከአባቱ ቤት መውጣት
ፈለገ፡፡ አባቱም ለልጁ የሚደርሰውን ገንዘብ ሰጠው፡፡ በአባቱ ቤት የነበረው ሰላም ለጊዜው ተሠውሮበታልና ሰላም በዓለም የሚገኝ ስለመሰለው ገንዘቡን ተካፍሎ ወደ ሩቅ አገር ኮበለለ፡፡
ዓለም በብልጭልጭ ጊዜያዊ ሰላሟ አቅፋ ተቀበለችው፡፡ ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከደቡብ ወደ ሰሜን፤ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ፣ ከምዕራብ
ወደ ምሥራቅ ዞረ ተንከራተተ በእጁ የነበረውን ገንዘብ አባከነ በእጁ ምንም ምን አልተረፈውም ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ መካከል
ሰላምን ማግኘት አልተቻለውም፡፡ እንዲያውም ገንዘቡ ባለቀበት ጊዜ አገሪቱ ውስጥ ጽኑ ረሃብ በመነሣቱ እጅግ አብዝቶ ይጨነቅ ነበር፡፡
በአባቱ ቤት ሳለ ከምንም ያልቆጠረው ሰላም ከጥሩ የአባትነት ፍቅርና እንክብካቤ ጋር ትዝ ሲለው ይባስ ያለቅስ ነበር፡፡ ረሃብ ሲጸናበት
በዚያች አገር ካለ ከአንድ ሰው ጋር ተዳበለ፡፡ የሚበላው በማጣቱ እጅግ ተራበ እሪያዎች ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ተመኘ ነገር ግን
ያንን የእሪያዎች ትራፊ እንኳ የሚሰጠው አልነበረም፡፡ ረሃቡ እጅግ ከመጠን በላይ ሲያስጨንቀው የአባቱ ቤት ታወሰው፡፡ /ሉቃ 15÷11-24/
ገንዘብ ስላለን ብቻ ሰላምን መግዛት እንደማንችል ታሪኩ ያስረዳናል፡፡ ዓለምም ሰላም የምትሰጠን ገንዘባችን እስከሚያልቅ ድረስ ብቻ
ነው፡፡ ገንዘባችንን ከጨረሰች በኋላ ግን እንደማይጠቅም ነገር ከውጭ ጥላ መሳቂያ ታደርገናለች፡፡ ዲያብሎስ ዓይንህን ሲያጨልምብህ ሰላ ምን እንደሆነ አትረዳውም፡፡ ለባልንጀራህ
“ሰላም ነው?” በሚል ጥያቄ ሰላምታ ታቀርባለህ እርሱም “ሰላም ነው” ብሎ ይመልስልሃል ነገር ግን አንተ የጠየቅኸው እርሱም የመለሰልህ
ሰላም እውነተኛ ሰላም አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ዳዊት “ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር
አትጣለኝ” /መዝ 27÷3/ በማለት የገለጸው፡፡ በልብህ ውስጥ ሰላም ሳይኖር አንተ ግን በአፍህ ብቻ “ሰላም ነው” እንድትል ትገደዳለህ፡፡
ፈጣሪህን እንዳታመሰግን ሰላምህን ያሳጣህ ጠላት “ሰላም ነው” በሚል ጥያቄና መልስ ሰላምታ እንድታቀርብ ያስገድድሃል፡፡ ሰላም ስትኖረው
የምታገኘው ስትቀምሰው የምታውቀው እንጅ ስለተናገርከው “ሰላም ነው” ስላልህ ብቻ የምትጎናጸፈውና የምትደርበው ካባ አይደለም፡፡
ቁጥሩ ከ12ቱ ነቢያት መካከል አንዱ የነበረው ይሁዳ “ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ አምላን ስሞ አሳልፎ ሲሰጥ በውስጡ ሰላም የለም
ነበር፡፡ /ማቴ 26÷49/ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተያዘ በኋላ በመጀመሪያ እንዳሰበው ሊሆንለት ባለመቻሉ በውስጡ ሳይኖር በአፉ ብቻ
“ሰላም” ይል የነበረው የውሸት ሰላም አእምሮውን ነሣው፡፡ ንጹሕ ደም አሳልፎ በመስጠቱም መበደሉን ተረድቶ ገንዘቡን በቤተመቅደስ
ጥሎ ታንቆ ሞተ፡፡ /ማቴ 27÷3-5/ ነገሮች ሁሉ ይሁዳ መጀመሪያ እንዳሰባቸው ሊሆኑለት አልቻሉምና የመጨረሻ ዕጣ ፈንታው የዘላለም
ሞት ሆነበት፡፡ ስለዚህ አምላክህን ያችን ገንዘብ የማይገዛትን የከበረች እውነተኛ ሰላም ይሰጥህ ዘንድ ተማጸነው፡፡
No comments:
Post a Comment