Friday, January 22, 2016

ፍቅረ ሰብእ/ ሰውን መውደድ/



© በመልካሙ በየነ
ጥር 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በኦሪት ሕግ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” /ዘሌ19÷18/ በማለት ሰውን መውደድ ጥሩ ክርስቲያዊ ሥነምግባር ከመሆኑም ባለፈ የሌሎች ሕግጋት ሁሉ ጉልላት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አንተ ራስህን በምትወደው መውደድ እንዲሁ ባልንጀራህን ውደድ፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም ምን ብትሠራ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አትችልም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” /1ኛ ጴጥ4÷8/ በማለት ባልንጀራን መውደድ ከሁሉ ሕግጋት መቅደም እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይህን መዋደድ ልንቀናበት እንደሚገባ ሲያስረዳ “… ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ሥጦታ በብርቱ ፈለጉ” ይላል፡፡ ከሌሎች የጸጋ ሥጦታዎች የሚበልጠው የጸጋ ሥጦታ ፍቅር ነው፡፡ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ከመናገር፣ ድሆችን ከመመገብ፣ ሥጋችንን ለእሳት መቃጠል አሳልፈን ከመስጠት ሁሉ የሚበልጠው ጸጋ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ካለ አነዚህን ሁሉ ለመሥራት እንችላለን ነገር ግን እነዚህ ጸጋዎች ፍቅርን ማምጣት አይችሉም፡፡ ፍቅር በቃል የሚገለጽ ጸጋ አይደለም በተግባር እንጅ፡፡ አንተም ፍቅርን በተግባር እንጅ በሽንገላ ቃላት አትግለጽ፡፡ ነቢዩ ዳዊት እንዲህ ይላል “በአፋቸው ይባርካሉ በልባቸው ይረግማሉ” /መዝ61÷4/ እነዚህን ሰዎች በግብር አትምሰላቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በፍቅር ቃላት በአፋቸው ይባርካሉ ነገር ግን በልባቸው የሚረግሙ ናቸው፡፡ ፍቅራቸው ግብዝነት የተሞላበት የሽንገላ ነው፡፡ እነዚህ በአፋቸው የሚባርኩት ሰዎች ፍቅራቸው ጊዜያዊ፣ ወረተኛ፣ የሚሻር፣ የሚለወጥ ነው፡፡ ገንዘብ ስታገኝ ያንዣብብልሃል ስታጣ ደግሞ ነፋስ እንደተመለከተ ደመና ተገፎ ይሄዳል፡፡ አንተ ግን ሰውን ስትወድድ ያለምንም ነገር ውደደው፡፡ ሰውን ለመውደድ ምክንያት የምታደርገው  ቁሳዊ ወይም ሌላ ነገር አትሻ፡፡ ሰውን ሰው በመሆኑ የእግዚአብሔር ክቡር ፍጥረት መሆኑን ብቻ አስበህ ከወደድከው ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆንህ ትልቅ ምስክር አገኘህ ማለት ነው፡፡ ፍጹም ፍቅር ጠላትን ይወድዳል፡፡ ምክንያቱም  ወንጌል “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላታችሁን ውደዱ”/ማቴ5÷44-45/ ይለናልና፡፡ የሰው ልጅ የመጨረሻ ተስፋው ርስት መንግሥተ ሰማያትን ወርሶ ከመላእክት ጋር “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያለ ለዘላለም ማመስገን ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ለሰማይ አባታችን ልጆች መሆን ያስፈልገናል፡፡ ልጆች ለመሆን ደግሞ ጠላትን መውደድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህ ፍጹም ፍቅር ቀዳሜ ሰማእት ቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ አንዲህ በተግባር ተተረጎመ፡፡ “… እስጢፋኖስም ፡- ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮም ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ” /የሐዋ7÷60/ የፍቅር ባለቤት የእግዚአብሔር ቅዱስ ሰማእት የሆነው ሊቀ ዲያቆን  እስጢፋኖስ ድንጋይ አንሥተው ለወገሩትና ለሞት አሳልፈው ለሰጡት ሰዎች ኃጢአታቸውን እንዳይቆጥርባቸው አምላኩን ለመነላቸው፡፡ እውነተኛ ፍጹም ፍቅር እግዚአብሔርንም በዙፋኑ ቁጭ እንዳለ የሚያሳይ ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ፍቅር ነው፡፡ እናትና አባቶቻችንን ስለወለዱን ብሎም ስላሳደጉን፣ ጓደኞቻችን ውለታ ስለዋሉልን ወይም የልባችንን መነጋገር ስለምንችል እንወዳቸዋለን ነገር ግን ሊወግሩን ድንጋይ በእጃቸው የያዙትን ሰዎች እንወዳቸዋለንን? የዚህ መልስ አዎ መሆን ከቻለ ፍጹም ፍቅር ማለት እርሱ ነው፡፡ ከዜሮ ወይም ከምንም ተነሥተን መውደድ ከቻልን ለመውደዳችንም ምንም ምን ምክንያት የሌለን ከሆነ እውነተኛ ፍቅር ያንጊዜ አለን እንላለን፡፡ ይህ ፍቅር እግዚአብሔርን የሚያሳይ ነው፡፡ /የሐዋ7÷56/ ሰውን መውደድ ስትጀምር አንተን ሌሎች እንዲወዱህ እግዚአብሔር ጸጋውን ያድልሃል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚገኘው በፍቅር መካከል ነውና፡፡ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ሲሆን ሰዎች ከትቢያ አንሥተው ከከበረ ዙፋን ላይ ያስቀምጡሃል፡፡  በግብጽ በግዞት ውስጥ የነበረው ዮሴፍ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ በማግኘቱ በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ፈርዖን ሹመት ሰጠው፡፡ ፈርዖን ቀለበቱን ከእጁ አውጥቶ በዮሴፍ እጅ ላይ አደረገው ነጭ የተልባ እግር ልብስም አለበሰው፣ በአንገቱም የወርቅ ዝርግፍ አደረገለት፤ በቤቱ ላይም ሁሉ አሰለጠነው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እንዲታዘዝለት አዋጅ አስነገረ፡፡ /ዘፍ 41÷37-45/ እግዚአብሔር  አብሮህ ሲሆን የጨካኞችን ልብ ያራራልህና የመወደድ ካባ አልብሶ ለሹመት ይመርጥሃል፡፡ ፍቅር በቃላት ከምንገልጸው በላይ ትልቅ ኃይል ነው፡፡ ፍቅር ዛሬ በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚደረገው ድራማ መሰል ጨዋታ አይደለም፡፡ አንዱ አንዲቷን በአለባበሷ፣ በሃብቷ፣ በውበቷ ወይም በሌላ ነገር ደልሎ ሥጋዊ ፈቃዱን የሚፈጽምበትን ድለላ አይደለም፡፡ ይህ አይነቱ ፍቅር ሶምሶን የከፈለውን ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ ኃያሉ ሶምሶን በደሊላ ፍቅር በመውደቁ ኃይሉ በምን ሊደክም እንደሚችል ትልቁን ምሥጢር አሳልፎ ሰጣት፡፡ በዚህም የተነሣ ፍልስጥኤማውያን ጸጉሩን ላጭተው፣ ኃይሉን አድክመው አይኑን አወጡት፣ በሰንሰለትም አሰሩት፣ በግዞትም ውስጥ እህል ያስፈጩት ነበር፡፡ /መሳ16÷1-31/ አንተ ግን ከእንደዚህ አይነቱ ፍቅር ልትርቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ አይነቱ ፍቅር የልብ ሳይሆን የአፍ መውደድ ነው፡፡ ፍቅር ራስህን አሳልፈህ የምትሰጥበት እንጂ ሌሎችን የምታጠምድበት ወጥመድ አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment