Tuesday, January 16, 2018

ውግዘት በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ሰስብከት በበርካታ ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ በደል የተሞላ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ በደል ተመልክቶ ዝም ማለት ለተዋሕዶ ልጆች አላስቻላቸውም ነበርና የሚጠበቅባቸውን የልጅነት ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ በርካታዎች ታስረዋል ተደብድበዋል ተንገላተዋል ተጉላልተዋል ተርበዋል ተጠምተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን አያሳስባቸውም ምክንያቱም ትግላቸው ዘላለማዊ ርስትን ስለሚወርሱባት ሃይማኖታቸው ሲሉ ነውና፡፡ ህጋዊውን መንገድ ተከትለው ተስፋ ባለመቁረጥ በልበ ሰፊነት ከሰባት ጊዜ በላይ በግል ወጫቸው አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቤት ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን አጥጋቢ መልስ ማግኘት አልተቻለም፡፡

አጣሪ ኮሚቴ ተብሎ በብጹእ ሥራ አስኪያጁ ተልከው የነበሩት ሦስቱ ልዑካንም የእግዚአብሔርን ነገር ትተው ራሳቸውን በይሁዳ መስመር አገኙት፡፡ ይሁዳ እግዚአብሔርን ለአይሁዳውያን ጠቁሞ ስሞ አሳልፎ ይሰጠው እንደሆነ እንጅ ሐዋርያትን መስሎ ከጎኑ አይቆምም፡፡ የእነዚህ የልዑካኑ ጉዳይም እንዲሁ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡

ከዚህ በፊት እንደገለጽኩላችሁ አጣሪ ኮሚቴው ታማኝነቱን ስላጣ የምሥራቅ ጎጃም የተዋሕዶ ልጆች በሙሉ አጣሪ ኮሚቴውን አልተቀበሉትም ነበር፡፡ ይህ በሆነበት ዕለት አባ ማርቆስ በአበል ከየወረዳው የሰበሰቧቸውን በተለይም የቅባት እምነት ተከታዮችን እና አንዳንድ ጥቅመኛ ካህናትን መርጌቶችን ሰብስበው አሸንፈናል በሚል ስምንት ያህል ነጥብ የያዘ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ይህንንም ይህን ጠቅ አድርጋችሁ ሙሉውን ስሙት፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=iXQoaIzlgkU ይህን የአቋም መግለጫም ለአቡነ ማትያስ በመላክ አሳውቀዋል፡፡ አባ ማትያስም ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና (ያለ ቤተክርስቲያኒቱ እውቅና) “የቤተክርስቲያን ውክልና የሌላቸው ቡድኖች” አባ ማርቆስን መክሰሳቸው ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ለዞኑ አስተዳደር በሸኝ አድርገው አባ ማርቆስ ያረቀቁትን ኮፒ አድርገው መልሰው ልከውታል፡፡ አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ይሏችኋል ይኼው ነው፡፡
ቤተክርስቲያን በነዲዮቅልጥያኖስ በሀገራችንም በነግራኝ በነዮዲት ተፈትና አልፋለች፡፡ ወርቅነቷ በእሳት ተፈትኖ ጠርታ ፈክታ በርታ የታየች ደግሞ ዛሬ ሳይሆን ድሮ ነው፡፡ ጉዳዩ የሃይማኖት ጉዳይ ነው በሞት ድልን የምንቀዳጅበት፡፡ ታዲያ ብንታሰር ብንደበደብ ብንወገር ብንሰቀል ብንራብ ብንጠማ ብንታረዝ ብንንቋሸሽ ብንሰደብ ብንገደል ደማችን ቢፈስ ሃይማኖታችንን አንለውጥም አምላካችንን አንክድም፡፡ ስለዚህ ተጋድሏችን ሃይማኖታዊ እስከሆነ ድረስ ሞት ብቻ ነው የሚለየን፡፡ አሁን በሊቀ ጳጳሱ እየተመራ የሚገኘው ቤተክርስቲያኒቱን ለመበጥበጥ የተነሣው ቡድን ዕድሜ ሰጥቶ ቢያሳየን ራሳቸውን ገንጥለው የሚሄዱ “ቅባቶች” ናቸው በዚህ ምንም አልጠራጠርም፡፡ ይህን እንድል ያደረገኝ ደግሞ አሁን እየሠሩ ያሉትን ሥራ በቅርበት ስለምመለከት ነው፡፡ “ተዋሕዶ ተዋሕዶ” የሚሉ የቅዱሳን አበው በረከት ያደረባቸው የቤተክርስቲያን ልጆች በዚህ ግፈኛ በሆነው የቅባቶች ቡድን እየተወገዘ ይገኛል፡፡ ለዛሬ መረጃው በእጀ ስለገባው ዐራቱ የሉማሜ የተዋሕዶ ልጆች ውግዘት እንመለከታለን፡፡
ወንድሞቻችን፡-
፩. ውለታው አንላይ
፪. ዋስይሁን ሙሉሰው
፫.ምንውየለት ታምሩ
፬. ባለምላይ ባየ የተባሉ የተዋሕዶ ልጆች ተወግዘዋል፡፡ ህዳር ፳፰/፳፻፲ ዓ.ም የተጻፈላቸው ደብዳቤ እንደሚያሳየው እነዚህ ዐራት የተዋሕዶ ልጆች እና መረጃቸው ያልደረሰኝ ተጨማሪ ሁለቱ የተዋሕዶ ልጆች በድምሩ ስድስት ወንድሞቻችን ከአገልግሎት እንደታገዱ ያሳያል፡፡ ለዕገዳው ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው ደግሞ፡
፩.በሉማሜ ማርያም ቤተክርስቲያን ቀሳውስት /ካህናት/ መስቀል አልባረክም
፪.የተቀደሰበትን የቅዳሴ ፀበል አልጠጣም
፫.ተባርኮ የሚታደለውን መክፈልት ለውሻ በመስጠትዎ
፬.ከሰባኪውና ከጥበቃ ሠራተኞች ጋር ረብሻ በመፍጠርዎ የሚል ነው፡፡ የዐራቱም ወንድሞች ተመሳሳይ ደብዳቤ በተመሳሳይ ቁጥር ተጽፎ ሳይጨመር ሳይቀነስ ስማቸውን ብቻ በመቀያየር ነው ተጽፎ የተሰጣቸው፡፡  ይህ የሚያሳየው የውሸት ክስ የሀሰት ውንጀላ መሆኑን ነው፡፡ እስኪ ክሳቸውን አንድ በአንድ እንመልከተው፡፡
፩. “በሉማሜ ማርያም ቤተክርስቲያን ቀሳውስት /ካህናት/ መስቀል አልባረክም” እንደዚህ አላሉም በቅባት ካህን መስቀል አንባረክም ነው ሊሉ የሚችሉት፡፡ ሉማሜ ማርያም ውስጥ የሚገኙት ካህናት በሙሉ ቅባት ናቸው እንዳትሉ እነዚሁ ወንድሞች የንስሐ አባት እንዳላቸው ጠቅሳችኋል፡፡ መስቀሉን የማይባረኩት የንስሐ አባት ደግሞ ሊይዙ አይችሉም አያችሁ ድብልቅልቅ ሲያደርጉት፡፡  በሁሉ ዘንድ የተጠሉ ለማድረግ የተጻፈች የሀሰት ክስ ናት፡፡ “በሉማሜ ማርያም ቤተክርስቲያን ቀሳውስት /ካህናት/ መስቀል አልባረክም” አሉ ሳይሆን “በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የቅባት ካህናት መስቀል አንባረክም” ብለዋል በሚል ቢስተካከል ያምር ነበር፡፡
፪. “የተቀደሰበትን የቅዳሴ ፀበል አልጠጣም” ማለታቸው ሊያስመሰግናቸው እንጅ ሊያስቀጣቸው አይገባም ምክንያቱም ትክክለኛውን ሥርዓት ነውና የተከተሉት፡፡ የቅዳሴ ጸበል (ማይ ቆሪር) የሚሰጠው ለቆረበ ብቻ ነው፡፡ እነርሱም ቆርበው የቅዳሴ ጸበል ተሰጥተው አልጠጣም ብለው ከሆነ ቢጠየቁ ችግር የለውም ግን እንደዚህ እንዳላደረጉ እናውቃለን፡፡ እስኪ በየትኛው የቅዳሴ ሥርዓት ነው የቅዳሴ ጸበል ያልቆረበ እነዲጠጣ የሚያዝዘው እስኪ መጽሐፍ ጥሩልን፡፡ ለነገሩ እናንተማ ከማጠጣትም አልፋችሁ እንደ ፍል ሜዳውን ሁሉ ስትረጩት አይደል የኖራችሁ ምኑ ነውር ይሆንባችኋል፡፡ የቅዳሴን ጸበል ያልቆረበ ሰው መጠጣት እንደሌለት መጽሐፍ አዝዟል መጽሐፍ ያዘዘውን ደግሞ ታላላቅ ሊቀውንት እንደነአለቃ አያሌው ያሉት በሰፊው አስተምረውን አልፈዋል፡፡ ዲማ ብትሄድ ካልቆረብክ አይሰጥም ሥርዓቱ ይኼው ነው፡፡
፫. “ተባርኮ የሚታደለውን መክፈልት ለውሻ በመስጠትዎ” ይህንን በፍጹም አያደርጉትም መቶ ፐርሰንት ውሸት ነው፡፡ ምክንያቱም መክፈልቱን አለመቀበል እየቻሉ እንዴት ተቀብለው ለውሻ ሊሰጡት ይችላሉ? ያለመቀበል መብት እያላቸው ተቀብለው ለውሻ አይሰጡም አያደርጉትምም፡፡
፬. “ከሰባኪውና ከጥበቃ ሠራተኞች ጋር ረብሻ በመፍጠርዎ” ሰባኪው ካጠፋ ጥበቃው ካጠፋስ፡፡ ሰባኪው በተዋሕዶ ማልያ እየተጫወተ ጥበቃውም እንዲሁ እየቀለደ ከሆነ ለምን አይጠየቁም፡፡ ቤተክርስቲያን እኮ የምእመናን መገልገያ እንጅ መሰደቢያ አይደለችም፡፡ ተዋሕዶን የማይሰብክ ሰባኪ ከመድረክ ተጎትቶ ይወርዳል ብጹእ ሥራ አስኪያጁ እንዳስተላለፉት መመሪያ፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ ስድስት ወንድሞቻችን በዚህ መሰል ደብዳቤ ነው ከመንፈሳዊ አገልግሎት መታገዳቸውን ነው አሁን ወደ ጠቅላይ በተክህነት የተዛወሩት የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን አባ እንባቆም ጫኔ የገለጹት፡፡ እነዚህ ወንድሞቻችን በደብዳቤ ስለተገለጸላቸው እንጅ በደብዳቤ ሳይገለጽ በቃለ ጉባዔ ብቻ ተወግዘው የተለዩ የደብረ ማርቆስ የተዋሕዶ ልጆችም አሉ፡፡ አንድ ጊዜ አልበቃ ብሎ ሁለት ጊዜ የተወገዝን እኔን መሰል ልጆችም አለን፡፡ አቡነ እንድርያስ ቢያወግዙኝ ራሴን እፈትሽ ነበር አቡነ ቀውስጦስ ቢያወግዙኝ ራሴን እመለከት አቡነ ኤልሳዕ ቢያወግዙኝ አለቅስ ነበር…ሌሎችም በስም ያልጠቀስኳቸው የተዋሕዶ አባቶች ቢያወግዙኝ ኖሮ ይቅርታ ብየ ራሴን አዋርጀ እቀርብ ነበር፡፡ ግን ያወገዘን በሃይማኖት የማይመስለን ምግባርም ሃይማኖትም የሌለው በስሙ ብቻ የሚነግድ ነጋዴ ስለሆነ አይደንቀኝም፡፡ ቅባት ብሆን ኖሮ አባቴ ምን አጠፋሁ እላቸው ነበር እኔ ደግሞ ተዋሕዶ ነኝ፡፡ ታዲያ ጨለማ ከብርሃን ጋር ምን ኅብረት ኖሮት ነው ጨለማ ቅባት ብርሃን ተዋሕዶን ሊያወግዝ የሚችለው፡፡
ለማንኛውም በምሥራቅ ጎጃም ላይ እየተዘራ ያለው የክህደት መርዝ ተነቅሎ የቤተክርስቲያናችን ትንሣኤ የሚታወጅበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡ ቅባቶች በሊቀ ጳጳሱ መሪነት ራሳቸውን ሊገነጥሉ የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ጎንቻን ሞጣን መርጡለማርያምነ ደብረ ወርቅን ቢቡኝን ለዚህ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ እየተጠቀሙበቸው ይገኘሉም ተበሏል፡፡ ስብሰባዎችን በተከታታይ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በቀጣይ ወደ ቢቡኝ እንደሚያመሩም ተገልጧል፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥር ፰ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment