፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

ጥር ፳፩ እረፍታ ለቅድስት ወለንጽሕት ድንግል በክልኤ ማርያም
ማርያም ማለት ፍስሐ ወሐሴት፣ ተለአኪተ ሰብእ ወእግዚአብሔር፣ መርኅ ለመንግሥተ ሰማያት፣ ፍጽምት፣
ክብርት፣ ቅድስት ማለት ነው:: አንድም ማርን ከምድር ጣፋጭ ምግብ ያምን ከገነት ጣፋጭ ምግብ ሁለቱን ቢገጥሙት ማርያም የሚለው
ይገኛል:: አንድም
ማ-ማኅደረ መለኮት
ር-ርግብየ ይቤላ
ያ-ያንቀአዱ ኀቤኪ ኩሉ ፍጥረት
ም-ምሥሐል ወምስጋድ ማለት ነው::

ኃጢአት ሳይሠሩ መኖር እንኳን ለሰው ለመላእክትም እንኳ አልተቻላቸውም ነበር ከሰው ወገን ከሆነች ከድንግል ማርያም በቀር:: ድንግል ሲሆኑ እናት ደንግል ወእም መባል ለማንኛዪቱም ሴት አልተቻላትም ለእመ ብርሃን ለወላዲተ አምላክ ለንጽሕተ ንጹሐን ለቅድስተ ቅዱሳን ለአምላክ እናት ለድንግል ማርያም ብቻ ተቻለ እንጅ:: አምላክን መሸከም ለማንም አይቻለውም ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ግን እሳተ መለኮቱ ሳያቃጥላት በማህጸኗ ፱ ወር ከ ፭ ቀን ተሸከመችው:: ወለደችውም ጡቶቿንም አጠባችው ዳሰሰችው ሳመችውም፡፡ እሳትን ታቅፎ አለመቃጠል እሳትን ስሞ አለመንደድ ግሩም ነው፡፡ ምን ዓይነት ልዩ ቅድስና እና ፍጹምነት ነው አምላክን እንበለ ዘርእ ፀንሶ እስከመውለድ የሚያደርስ? ነቢያቱ ትንቢት የተናገሩላት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም የድኅነታችን መጀመሪያ የንጽህናችንም መሠረት ናት:: ያለድንግል ማርያም ድኅነት ለዓለም አልተሠጠም:: ያ ቅዱስ ሥጋ የተቆረሰው ያ ክቡር ደም የፈሰሰው ከድንግል ማርያም የነሳው እንደሆነ አንጠራጠርም:: እውራን ያዩባት ድኩማን የጠነከሩባት ጎባጣዎች የቀኑባት ያረጁት የታደሱባት ድንግል ማርያም ለእኔስ መግለጫ ቃላትም የለኝ:: አባ ኤፍሬምስ የገናንነቷን ነገር መናገር አይቻልምና ዝም እንበል ማለቱ ለዚህ አይደል:: የሀናና የኢያቄም የማኅጸን ፍሬ ድንግል ማርያም በጥር ፳፩ ቀን በ፷፬ ዓመቷ አረፈች:: አይሁዳውያን ለምቀኝነት አያርፉምና ሥጋዋን እናቃጥል ቢሉ መብረቅ ፈጃቸው ሥጋዋም በጌቴሴማኒ በአትክልት ቦታ ተሰወረ:: በነሐሴም ሐዋርያቱ ሥጋዋን አግኝተው ቀበሯት እረፍት በጥር በነሐሴ መቃብር መባሉ ለዚህ ነው:: የአምላክ እናት ስትሆን እንደ ልጇ ሞተች ተቀበረች ተነሣች ዐረገች:: “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ይላል ታላቁ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፡፡ አወ ሞት ለሟች ሁሉ የተገባ ነው ሞት ይገባልና፡፡ አምላክን በማኅጸኗ የተሸከመች አምላክን የወለከደች አምላክን ጡት ያጠባች ዘመናት የማይሽሩት ዘመናትን አሳልፎ የሚኖር ጌታ እናቱ የሆነች ድንግል ማርያም ስትሞት ግን በጣም ይገርማል በጣምም ይደንቃል፡፡ የአምላክ እናት ሞተች ከመባል በላይ ምን ድንቅ ነገር አለ ብሎ እንዲህ አለ፡፡ ኤልያስን፣ ሄኖክን ሳይሞቱ ወደ ብሔረ ሕያዋን የነጠቀ አምላክ እናቱን ግን በ፷፬ ዓመት እንድታርፍ ማድረጉ ድንቅ ነው፡፡



በእውነት እስኪ አስቡት ማን ነው ኃጢአት መሥራትን የማያውቅ? ከሰው ወገን ሆኖ በገቢር ባይፈጽም
በነቢብ፣ በነቢብም ባይፈጽም በሀልዮ ኃጢአትን የማያደርግ ማነው? በእውነት ማነው ይህን ማድረግ የሚቻለው? ንጽሕናን እንደጠበቁ
ምንም ኃጢአትን ሳያደርጉ እስከ ዘለዓለም መጽናት ለማን ተሰጠው? ለማንም አልተሰጠውም እኮ መላእክት እንኳ እንደ እርሷ ንጹሐን
አይደሉም፡፡ እመቤታችን ግን ምንም አይነት ኃጢአት ርኩሰት የለባትም በሃሳብሽ ድንግል ነሽ በስጋሽም ድንግል ነሽ የምንላት ለምን
መሰላችሁ ሃሳቧ ኃጢአትን ለማሰብ ጊዜ የሌለው ስለነበር እኮ ነው፡፡ እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናቴ የማይላት
ከቶ ማነው? እርሱ እኮ መዳኑን የማይወድ ተስፋውን የማይሻ መጠጊያውን የማይፈልግ ከለላውን የማያውቅ መከታውን የዘነጋ ምርኩዙን
መደገፊያውን የማይወድ ምግብ ስንቁን የሚጠላ ውሉደ አጋንንት ነው፡፡ እንዲያው ሌላውን እንተወውና አምላክን በድንግልና ለመውለድ
መመረጧ እንዴት አያስደንቀንም? በድንግልና የሴቶች ልማድ ሳያገኛት በመንፈስ ቅዱስ ጸንሳ መገኘቷ እንዴት አያስደምመንም? ሰው ሆና
ሳለች ከኃጢአትና ርኩሰት በሃሳብም በሥጋም ድንግል መሆኗ እንዴት አይገርመንም? መላእክት እንኳ ንጹሕ ባልሆኑበት ዓለም ለብቻዋ
ንጽሕት ዘር መሆኗ እንዴት አይደንቀንም? በእውነት ስለእውነት ለስሟ መግለጫ ቃላት እኮ የለንም፡፡ እኛን የሚደንቀን እኮ እንደኛው
ሰው ስትሆን እንዲህ ያለውን ንጽሕና ይዛ በመገኘቷ ነው፡፡ እኔ ሰው ነኝ አንተም ሰው ነህ አንችም ሰው ነሽ ማንነታችንን አናውቀውም
እንዴ? ለትንሽ ጊዜ እንኳ እስኪ ሰው ሁኑ ያልኳችሁ ለዚህ ነው፡፡ በቅጽበት ውስጥ ምን ያህል ኃጢአትን ነው ስናነሣ ስንጥል የምንውለው?
እኛ እንኳን ቆመን ተኝተንስ ኃጢአትን አይደል እንዴ ስንቃዥ የምናድረው እርሷ እንዲህ የሚባል ነገር የለባትም፡፡ ታዲያ እመቤታችን
ያልገረመችን ማን ይግረምን? ከመላእክት ወገን ብትሆን እኮ እንዲህም ባልተገረምን ነበር ባልተደነቅንም ነበር ምክንያቱም ባሕርያቸውን
ባሕርያችን ስላላደረግን እነርሱ እኮ ከእንደዚህ ባሕርይ ስለተፈጠሩ ነው እንል ነበር እመቤታችን ግን ሰው ናት ለዚያም ነው የደነቀችን
የገረመችን፡፡ በእውነት “እመ አምላክ ድንግል ማርያም” የሚለውን ቃል ሳየው ሁልጊዜ አዲስ ነገር አዲስ ትምህርት አዲስ ቃል አዲስ
ስብከት ነው ለእኔ፡፡ ዛሬም አዲሴ ነው ነገም እንደዚያው፡፡ ዝም ብሎም እናትና ድንግል ቢል ላይደንቀኝ ይችል ነበር “እመ አምላክ
ሲባል ግን እንዴት አይደንቀኝም፡፡ ለሁሉም ነገር ግን አበው ተናግረውት ጽፈውት ያልጨረሱትን የክብሯን ነገር ስጨልፍ ብውል አልጨርሰውምና
ዝም ልበል፡፡
በቀጣይ ሰንበት ትምህርት ቤት እና ገዳማትን በተመለከተ ቃለዓዋዲው ምን እንደሚል እጽፋለሁ፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት ብቻ አንድን ደብር ገዳም ነው ብሎ መናገርስ ይቻላልን? ይጠብቁን፡፡
ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከት ያሳትፈን አሜን፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥር ፳፩
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment