Monday, January 22, 2018

ወልዲያን ሳስብ ደብረ ማርቆስ መጣብኝ



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

በዓለ ጥምቀት በዓለ ቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩን የለወጠ ክስተት ነው የተፈጸመው፡፡ ወልዲያ ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት ራሳቸውን ስተው ወድቀዋል ምእመናን ከታቦቱ ፊት ነፍሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ የዚህን ክስተት ሙሉ ኃላፊነት ቤተክርስቲያናችን መውሰድ ይገባታል፡፡ ምክንያቱም የበዓላት ሥነሥርዓት አስከባሪ የቤተክርስቲያኒቱ የሰበካ ጉባዔ እያለ ከሰበካ ጉባዔው ቁጥጥር በላይ የሆነ አንዳች ችግር ሳይፈጠር የመንግሥትን ጸጥታ አስከባሪዎች ወደቦታው መጥራት አስፈላጊ ስላልነበር ነው፡፡ ሕገመንግሥቱ ሃይማኖት እና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው ሃይማኖት በፖለቲካ ፖለቲካም በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ብሎ በደነገገበት ሁኔታ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ከታቦቱ ፊት እንዲገኙ ማድረጋቸው የቤተክርስቲያኒቱን አባቶች ያስተቻል፡፡

ቃለዓዋዲ አንቀጽ ፳፬ ንዑስ አንቀጽ ፬ ላይ “በክብረ በዓል ቀን ከሰበካው መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ ጽ/ቤት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት እንደአስፈላጊነቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የበዓሉን ሥነሥርዓት ያስከብራሉ” ይላል፡፡ ይህ አንቀጽ ስለቤተክርስቲያናችን የህግ አገልግሎት ክፍል የሚናገር ነው፡፡ የህግ አገልግሎቱ የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ብቻ መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ሥነሥርዓቱን ሊያስከብር እንደሚገባ ነው የተገለጠው፡፡ ስለዚህ በበዓላት ጊዜ ለሚጠፋው የንብረት ውድመት የሰው ሞት ሁሉ ኃላፊነት የምትወስደው ቤተክርስቲያናችን መሆን አለባት፡፡ የመንግሥት ወታደሮች በበዓላት ቀን መሣሪያቸውን ይዘው ከህዝቡ መካከል ገብተው በዚህ ግቡ በዚህ ውጡ ከዚህ ራቁ ወደዚህ ተጠጉ ወዘተ እየተባሉ ሲንገላቱ አባቶቻችን ዝም ካሉ ወደው ፈቅደው ያመጧቸው ናቸውና ሰውን ቢገድሉ አካልን ቢጎድሉ ኃላፊነቱን ቤተክርስቲያን ልትወስድ ግድ ይላታል፡፡ የበዓሉን ሥነሥርዓት ያለማንም አጋዥነት በምእመናን እና በካህናት በአግባቡ ማስፈጸም እየተቻለ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎችን መጥራት ለምን አስፈለገ? በዓሉ እኮ ሃይማኖታዊ እንጅ ፖለቲካዊ በዓል አይደለም፡፡ በርግጥ አባቶቻችን “በዓሉ ባህላዊ ነው” እያሉ የሚደሰኩሩ የመንግሥት ተወካዮችን በራሳችን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ሲያሰሙን እና ሲያስደምጡን ነው የሰነበቱት፡፡
ወልዲያ ላይ ወጣቶች ከመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በመጋጨታቸው ህይወታቸው አልፏል አካላቸው ጎድሏል ንብረታቸው ወድሟል፡፡ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ “የተለየ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ወጣቶች ባሥነሱት ግጭት ሰዎች ተገድለዋል” ብሏል፡፡ የፖለቲካ ምሕዳሩን እናስፋ እያለ መንግሥት በፖለቲካ አመለካከታቸው ታሥረው የነበሩ እስረኞችን እየፈታ ባለበት በዚህ ወቅት “የተለየ ፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ወጣቶች ባሥነሱት” በሚል መገለጹ በጣም ያሳዝናል፡፡ የፖለቲካ አመለካት የግለሰቦች ዲሞክራሲያዊ መብት ነው ህገመንግሥቱ እንደጻፈው፡፡ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ስላላቸው ብቻ የሚገደሉ ከሆነማ የታሠሩትን መፍታቱ ምን ዋጋ አለው፡፡
ወጣቶች በበዓሉ ላይ የተገኙት በዓሉን ሊያከብሩ እንጅ የተለየ ብጥብጥ እና ረብሻ ለመፍጠር አስበው አይደለም፡፡ ወታደሮቹን ሲያዩ ባንዲራውን አታውለብልቡ ሲባሉ ለምን በዓሉን በሰላም አናከብርም የሚል ጥያቄ እንዳነሡ ነው በቦታው የነበሩ ሰዎች የሚናገሩት፡፡ በዚህ ሃይማኖታዊ በዓል ላይ የወጣቶች መገደል ቤተክርስቲያናችንን ሊያሳዝናት ይገባል፡፡ ጸሎተ ምሕላም መታወጅ አለበት፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን አስመልክቶ የጸሎተ ምሕላ አዋጅ ማወጅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ በሀገረ ስብከታቸው ላይ ጸሎተ ምሕላ ማወጅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሰው ሳይገደል ተቃውሞን ማስቆም አይቻልም እንዴ? በዚህ የመከራ ጊዜ ህዝቡን ማጽናናት ከአባቶቻችን የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ በሀዘን ላይ ሀዘን በመከራ ላይ መከራ ለሚጨመርበት ለዚህ ምእመን አባቶቻችን ሊደርሱለት እንባውንም ሊያብሱለት ይገባል፡፡ ጌታ በውኃ ተጠምቆ የመሠረተልንን ጥምቀት እኛ በደም ልናከብረው አይገባም፡፡ ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው ብሎ የመጀመሪያውን ተአምር ያሳየበትን ዕለት የቃና ዘገሊላ በዓልን ጋኖችን ደም በመሙላት ልናከብረው አይገባም፡፡
የወልዲያውን የምእመናን ሞት ስመለከት ደብረ ማርቆስ ናት ድቅን ያለችብኝ፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የመንግሥት አካላት እና ምእመናን ቀድመው ነበር ውይይት ያደረጉት፡፡ በዚህ ውይይት ወቅትም በተለይ የሰንበት ትምህርት ቤት እና የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አቡነ ማርቆስ በበዓሉ እንዳይገኙ የግድ እገኛለሁ ካሉ እንኳ እላፊ ነገር እንዳይናገሩ ለመንግሥት አካላት አሳስበው ነበር፡፡ በዚሁ ማሳሰቢያ መሠረትም አቡነ ማርቆስ በቦታው እንዳይገኙ ተደርገዋል፡፡ እርሳቸው ባለመገኘታቸውም በዓሉ በሰላም ተጠናቋል፡፡ ምንም እንኳ በዓሉ ላይ የተገኘው ህዝበ ክርስቲያን እንደድሮው ባይሆንም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በዓሉ ተጠናቋል፡፡ የዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት እንደታሸገ በመሆኑ የመዝሙር ልብሳቸውን ሳይለብሱ ነጠላቸውን መስቀለኛ ለብሰው ታቦቱን በዝማሬ አጅበዋል፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ አቡነ ማርቆስ እንኳንም በበዓሉ አልተገኙ ቢገኙ ኖሮ እላፊ ነገር መናገራቸው አይቀርም ነበር በዚህ የተነሣ ተቃውሞ ሊደርስባቸው ይችል ነበር፡፡ ተቃውሞ ከተነሣ ደግሞ ያው ወልዲያ ላይ እንዳየነው የምእመናን ደም በከንቱ ይፈስ ነበር አካል ይጎድል ንብረት ይወድም ነበር፡፡ ይህንን አስቀድመው የተረዱ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ከምእመናን ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይት በዓሉን በሰላም ለመፈጸም ተችሏል፡፡
በታቦቱ ፊት ደማቸውን ያፈሰሱ ምእመናንን በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ጎን ያቁምልን፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥር ፲፭ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
                                                        ✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment