፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ብጹእ አቡነ ዘካርያስን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወቅታዊ ሁኔታ ከማንም በላይ አሳስቧቸወል፡፡
ብጹእነታቸው አንድ ሊቀ ጳጳስ በሌላው ሀገረ ስብከት ጣልቃ አይገባም የሚለውን ህግ ሳያውቁ እንዳልሆነ ለቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፉት
ደብዳቤ ላይ ገልጠዋል፡፡ ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ የምሥራቅ ጎጃም ጉዳይ እጅጉን ያሳሰባቸው በጎጃም ተወልደው ያደጉ በዚያው
የተማሩ ያስተማሩ በሊቀ ጳጳስነትም ደረጃ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው ብዙ ዲያቆናትን እና ካህናትን ክህነት የሰጡ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን
ጉዳዩ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ ሃይማኖትን ደግሞ አድማስ እንደማይገድበው በመግለጽ ጭምር ነው ለቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ የጻፉ፡፡
ብጹእ አቡነ ዘካርያስ የቅባት እምነት ተከታዮች ያሳተሟቸውን መጻሕፍት በመከታተል እያወገዙ
ይገኛሉ፡፡ “ወልደ አብ” የተባለው የክህደት መጽሐፍ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲወገዝ ከፍተኛውን ድርሻ የወሰዱት እርሳቸው ናቸው፡፡ አሁን
በቀጣይም “መሠረተ ሐይማኖት” እና “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የሚባሉ መጻሕፍትን በቅዱስ ሲኖዶስ ለማስወገዝ
እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከትን በተመለከተ በጥቅምት ወር ስብሰባው ባሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊነት ላይም ግንባር
ቀደም ተሳታፊ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በተለይም የሐገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ውሳኔ በመንቀፍ
አሁንም ድረስ በአቋማቸው እንደጸኑ መገኘታቸው ብጹእነታቸውን በጣም አበሳጭቷል፡፡ “ጎጃም ተጠመቅ ተባልህ”፤ “ዳግም ተጠመቁ የሚሉ
ሰዎች”፣ “ሃይማኖታችን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተወለደ ነው” ወዘተ እያሉ ምእመናንን በማደናገር ላይ ያሉትን የሀገረ ስብከቱን
ሊቀ ጳስ አቡነ ማርቆስን በግልም እንደወንድምነት የመከሯቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን አቡነ ማርቆስ የቅባትን
አስተምህሮ ደግፈው የቆሙ መሆናቸው በሚናገሩት እና በሚያስተላልፉት መልእክት ይታወቃል፡፡ በቆሙበት ዐውደ ምሕረት ሁሉ “ዳግም ጥምቀት” እና “ጎጃም ተጠመቅ ተባለ”
እያሉ የየዋሐንን ቀልብ ለመሳብ ሞክረዋል፡፡ ተጠመቅ የተባለው “ቅባት” እንጅ “ጎጃም” እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባናል፡፡ ቅባት ደግሞ
የጎጃም መገለጫ ሊሆን አይችልም “ጎጃም” የሚለው ስምም “ቅባት” የሚለውን ሃማኖት ተክቶ ሊነገር አይችልም፡፡
በዚህ ልናገባድደው ጥቂት ቀናት በቀሩት ወር ብቻ አቡነ ማርቆስ ከአራት በላይ የፊት ለፊት
ተቃውሞዎች ገጥሟቸዋል፡፡ ታህሳስ ፫ በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን በአንዲት የተዋሕዶ እናት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡
እርሳቸውም “ይችን እብድ ዝም አስብሏት” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ እርሷ ግን በቀጥታ “ቅባት ጳጳስ አያስተዳድረንም በቅባት አንገዛም
እምነታችን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነው” በማለት እውነቱን በቆራጥነት መስክራለች፡፡ ይህን በመናገሯም ለሦስት ቀናት ያህል ለመታሰር
በቅታለች፡፡ ክብር አግኝታለች የዛሬው ሰማእትነት ይኸው ነው፡፡
ታህሳስ ፲፱ የቅዱስ ገብርኤል በዓል በተከበረበት ጊዜ እንደለመዱት “ዳግም ጥምቀት” እና “ጎጃም
ተጠመቅ ተባልህ” እያሉ ሲያስተምሩ “ቅባት አያስተምረንም እስላም አያስተምረንም፡፡ ቅባት የሆነ የግድ ይጠመቃል” በማለት ምእመናን
ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ብዙዎች ተደብድበዋል ክብር ሰማእትነት ነውና በረከታቸው ይድረሰን፡፡
ታህሳስ ፳ ብቸና ማረሚያ ቤት ያለውን ቤተክርቲያን እባርካለሁ ብለው በሄዱበት ወቅት ከብቸና
ልጆች ጠንከር ያለ ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር፡፡ ጽላቱን ወስጀ ደብረ ማርቆስ ባርኬ ልላክላችሁ ያሉት ብጹእነታቸው በምእመናን ዘንድ
ቁጣ አስነስቷል፡፡ ጽላታችንን አንሰጥም ለቅባት አንገዛም ብለው ተቃውሞ አሰምተው ቤተክርስቲያናችንን ጠብቀዋል፡፡ በዚህም የታሰሩ
እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
ታህሳስ ፳፪ ቀን አቡነ ማርቆስ የእድ ውኃ እንደሚሄዱ ተናግረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሸበል
በረንታ ልጆች ከፍተኛ እልህ አስጨራሽ ትግል በቦታው እንዳይገኙ ተደርገዋል፡፡
ታህሳስ ፳፬ በገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃማት ገዳም እንደድሮው ግቢ ጉባዔን ማኅበረ ቅዱሳንን
ሰንበት ትምሀርት ቤትን እየነቀፉ ሲገሩ ከፍተኛ የምእመናን ተቃውሞ ተነሥቶባቸዋል፡፡ “ቅባት አያስተምረንም ቅባት አያስተዳረንም”
የሚሉ ድምጾች ጎልተው ተሰምተዋል፡፡ ብጹእነታቸውም “ካህናት ዝም አላችሁ” በማለት የሚቃወሟቸውን እንዲደበድቡላቸው አዝዘዋል፡፡
በዚህም መሠረት የገዳመ ፀሐፊ በያዘው መቋሚያ ለመደባደብ ሲሞክር ፖሊስ መቋሚያውን ሲነጥቀው ጫማውን አውልቆ በጫማ አንድን ወጣተ
ፈንክቷል፡፡ የተፈነከተው ወጣትም ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ተደርጎለት ምሽት አካባቢ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡ የተደበደቡ በርካታ ወጣቶች
ሲሆኑ ስምንት ያህሉ እስካሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ምሥራቅ ጎጃም እንዲህ ያለ ሀገረ ስብከት ለመሆን በቅቷል፡፡ የተዋሕዶ ልጆች እየታገቱ እየተደበደቡ
መተት እየተደረገባቸው ይገኛሉ፡፡ ለዚህም የደጀኑን መምህር ጌታቸው ተፈሪን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሥራ የታገዱ
ካህናት ብዙዎች ናቸው፡፡ ምእመናንም ከልጅነት እነደተሻሩ የሚገልጹ ደብዳቤወች ከሀገረ ስብከቱ ብዙ ጊዜ ሲወጡ ይታያል፡፡ በነገራችን
ላይ ደብዳቤው አልደረሰኝም እንጅ እኔም ሳልኖርበት አልቀርም፡፡ እኔ ዲቁናየን ቢይዙት ልጅነት የለህም ቢሉኝ አልቀበለውም ምክንያቱም
መጀመሪያ አባቴ መሆን አለባቸው፡፡ እኛ እና እነርሱ እኮ ለየቅል ነን፡፡ እኔ ተዋሕዶ እርሳቸው ደግሞ ሌላ ናቸው፡፡ ታዲ እርሳቸው
ማውገዝ አይችሉም ሊያወግዙኝም ሊያወግዙንም አይችሉም መብቱም ስልጣኑም የላቸውምና፡፡ ዲቁና የተቀበልሁት ደግሞ ከብጹእ አባቴ ከአቡነ
ዘካርያስ ጥር ፲፯/፳፻ ዓ.ም ነው፡፡
ተደብድበው ከተጎዱት ውጭ አሁን ፲፫ ፍርድ ቤት ተከሰው ብይን የሚጠብቁ የተዋሕዶ ልጆች አሉ፡፡
፰ቱ ደግሞ ገና ማረፊያ ክፍል ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ወደ ማረሚያ ቤት ሊዛወሩ እና ክስ ሊመሠረትባቸው እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ጫማ
አውልቀው ሰውን የሚፈነክቱ ጠብደል መነኮሳት ግን ከሳሽ የላቸውም እግዚአብሔር ይፋረዳቸው እንጅ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱ
ዝም ማለቱ ቅዱስ ፓትርያርኩም ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ለቤተክርስቲያናችን ትልቅ ጠባሳ ነው፡፡ ስለዚህ ብጹአን አባቶች ይህንን
ትኩረት ሊያደርጉበት ይገባል፡፡ በቦታው እንዲሰጥ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው የሃይማኖት ትምህርትም ሊጀመር ይገባዋል፡፡ በአንድ
ቤተክርስቲያን ሁለት ሃይማኖት ተጫፍሮ ሊኖር አይችልም፡፡
ብጹእ አቡነ ዘካርያስን እንቅልፍ
የነሣቸው ጉዳይም ይኼው ነው፡፡ ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ ምሥራቅ ጎጃምን በሊቀ ጳጳስነት ያስተዳደሩት ስለሆነ የህዝቡን ጥያቄ
በሚገባ ይረዱታል፡፡ ለዚህም ነው ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት በተለየ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ በማሳሰብ ላይ የሚገኙት፡፡
አጣሪ ኮሚቴው ቤተክርስቲያን የሰጠችውን ትልቅ ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት በገንዘብ ተገዝቶ ሥራውን ሳሠራ በመሄዱ አቡነ ማርቆስ
እንዳሸነፉ አድርገው ካህናትን ሰብስበው የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል፡፡ ያንን የአቋም መግለጫም ለፓትርያርኩ በማሳወቅ ፓትርያርኩም
ማንንም ሳያሳውቁ በሸኝ አድርገው ለምሥራቅ ጎጃም መልሰው መላካቸው ይታወቃል፡፡ ይህንንም በማስመልከት ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ
ቅዱስ ፓትርያርኩ የሠሩት ስህተት እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ ይህን ያህል ተጋድሎ
እያደረጉ ያሉት ምሥራቅ ጎጃሞችን ደስ እንዲለን ብለው አይደለም፡፡ ሃይማኖታቸው አባትነታቸው ስለሚያስገድዳቸው እንጅ፡፡ ብጹእነታቸው የጻፉትን ደብዳቤ ከዚህ ጋር አያይዠላችኋለሁ፡፡ የብጹእነታቸው
በረከት ይድረሰን!!!
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ታህሳስ ፳፮
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment