Monday, June 20, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 1

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እንኳን ለጾመ ሐዋርያት በሰላም እና በፍቅር አደረሳችሁ አደረሰን!

ዛሬ ዛሬ ማንነታቸውን ይፋ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ትምህርታቸውንም ከኩሽና ቤት ወደ አደባባይ አውጥተውታል፡፡ በግልጽ ማስተማር መከራከር ጀምረዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን መሳደብ መንቀፍ ጀምረዋል፡፡ መናፍቃኑ!
እነዚህን ልዩ የሚያደርጋቸው በቤተክርስቲያናችን ጥላ ሥር ተጠልለው ከበላነው በልተው ከጠጣነው ጠጥተው እኛ በሠራነው ሥርዓት ተሠርተው ለእኛ በተሾመልን ጳጳስ ደቁነው ቀስሰው ጰጵሰው የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በብዛት ሰፍረው የሚገኙት ደግሞ በጎጃም ጥቂት አካባቢዎች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አስተምህሯቸው በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ ተከታዮቹም የእናት እና የአባቴ እምነት ነው ብለው ክርር ከማለት ባለፈ ምሥጢራትን አያውቁም ነበር፡፡ የየዋሃኑም መከራከሪያ ሆኖ የቆየው የጌታችን የልደት በዓል ቀን በ28 እና በ29 ይከበራል ወይስ ደግሞ በ29 ብቻ ይከበራል የሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ስለነበር ለብዙዎቹ ልዩነት ያለን በ4 ዓመት አንድ ቀን ብቻ ይመስላቸው ነበር፡፡ ስለአጽዋማት የሚያውቁት ደግሞ በጾመ ነቢያት እና በጾመ ሐዋርያት መግቢያ ላይ ብቻ ያለ ልዩነት  አድርገው ይቆጥሩት ስለነበር በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚፈጠር የአጿጿም ችግር ይመስላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሊደበቅ የማይችል በምንም በማንም ሊሸፈንና ሊከለል የማይችል አደባባይ ላይ የወጣ ምንፍቅና  ቅ--ብ---አ---ት፡፡
ዛሬ ላይ በልደት በዓልና በአጽዋማት መግቢያ ላይ የምንከራከርብት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ አድርጉ ፈጽሙ በተባልንበት ቀን የምናደርጋቸው በተከለከልንባቸው ቀናት ደግሞ የምንቆጠብባቸው የምንታቀብባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ እንድናደርግ ወይም እንዳናደርግ ቤተክርስቲያናችን ስልጣንና ኃላፊነት የሰጠችው አካል አለ እርሱም ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ልደትን በታህሳስ 28 ማክበራችን አያጣላንም ምክንያቱም እንኳን ምሥጢር እያለው ይቅርና መስከረም 1 ወይም ጥቅምት 30 ወይም ደግሞ ሰኔ 24 ወይም ሚያዝያ 7 ወይም ደስ ያላችሁን ቀን መርጣችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ ብንባል ኖሮም እናደርገው ነበር እናከብረውም ነበር፡፡ ጌታችን በየዓመቱ የሚወለድ ሆኖ ነው እንዴ እያከበርነው ያለነው? አይደለም፡፡ የአጽዋማት መግቢያም እንዲሁ ነው፡፡ የነቢያት ጾም በህዳር 15 የሐዋርያት ጾም ደግሞ ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በነጋታው ሰኞ እንድንጀምር ሥርዓት ተሠራልን በዚያ ሥርዓት እንመራለን እንተዳደራለን፡፡ አለቀ ይህ ምንም አያከራክርም ምክንያቱም ቀኖና ስለሆነ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቀደሙ አባቶቻችን እና ከመጽሐፎቻቸው ጋር በማይጣላ መልኩ አድርገው በወሰኑልን ውሳኔ የምንፈጽመው ነው፡፡ እነዚህ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች የሚጠቅሱት ነገር አለ “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ወደ ኋላ ከተመለሰ ጥምቀት ግዝረት ለምን አንድ ቀን ወደኋላ አይመለሱም” የሚል ነው፡፡ የእነርሱ ደጋፊ የሆኑት ጳጳስም “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ቀንሶ በታህሳስ 28  ይከበር የምትሉ እናንተ ልደታችሁን ስታከብሩ አንድ ቀን ቀንሳችሁ ነውን? ታህሳስ 29 የተወለደ ሰው በዘመነ ዮሐንስ ልደቱን ታህሳስ 28 ያከብራልን?” ብለዋል፡፡ መልካም ነው! እኔ ግን ግርም ድንቅ የሚለኝ ነገር አለ፡፡ አሰቀድሜ እንደተናገርኩት ይህ የቀኖና ጉዳይ ነው ይህን መፍታት የሚችል ራሱን የቻለ አካል አለው፡፡ አይደለም ታህሳስ 28 ከ365ቱ ቀናት መካከል አንዱን ቀን መርጠው የጌታችን ልደት በዚህ ቀን ይከበር ብለው ካሉን ግዴታችን ነውና እናከብረዋለን፡፡ ምክንያቱም የጌታችን ስቅለት፤ ትንሣኤ እና ዕርገት  በጥንተ ስቅለት፣ በጥንተ ትንሣኤ እና በጥንተ ዕርገት እያከበርናቸው ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የ2008 ዓ.ምን ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት ቀን አስቡት፡፡ ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት 27 ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት 8 ነው እኛ ግን ስቅለቱን ሚያዝያ 21 ትንሣኤውን ሚያዝያ 23 እንዲሁም ዕርገቱን ሰኔ 2 ቀን አከበርን ለምን? ቀኖና ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ በየዓመቱ እነዚህን በዓላት መቼ መቼ እንዳከበርናቸው ተመልከቱ፡፡ በየዓመቱ ይለያያሉ ዕለታቸው አይቀየርም እንጅ ቀናቸው ይቀያየራል፡፡ ታዲያ በአንድ የልደት ቀን አከባበር ላይ ከምንነታረክ ለምን እነዚህንስ አንከራከርባቸውም፡፡ ስለዚህ በልደት በዓል አከባበርና በአጽዋማት መግቢያ ላይ ምንም መከራከሪያ ልናነሣ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም እኛ ታዛዦች እንጅ አዛዦች አይደለንምና አድርጉ በተባልነው ቀን ማድረግ ብቻ ነው ሥራችን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ለቅብአት ምንፍቅና የመደበቂያ ካባዎች እንጅ መሠረታዊ ነጥቦች አይደሉም፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑም ማስተዋል የሚገባው ይህንን ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ጉዳያችን መሆን ያለበት አስተምህሮ ላይ ወይም ዶግማ ላይ ነው፡፡ ዶግማን ማሻሻል የሚችል አካል የለም፡፡ ምክንያቱም ስታምን የምትቆይበት ካላመንክ ደግሞ ተለይተህ የምትወጣበት መሠረተ እምነት ነውና፡፡ ለሲኖዶስ ቀኖናን የማሻሻልም የመለወጥም የመቀየርም ስልጣን አለው ለዶግማ ግን ማንም ቅንጣት ታህል የማሻሻል የመለወጥ የመቀየር ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ነጥቦቻችን መከራከሪያዎቻችን መሆን ያለባቸው አስተምህሮ ላይ ነው፡፡ አስተምህሯቸውን ደግሞ በራሳቸው ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እናገኘዋለን፡፡ ያ አስተምህሮ በእውነት እኛ የተዋሕዶ አማኞች የምንከተለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ወደፊት በዝርዝር የምንመለከተው ስለሚሆን ከላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዮች ላይ እንደመከራከሪያ አድርጋችሁ ጊዜ እንዳታጠፉ እጠይቃለሁ፡፡ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆችም ሳትቸኩሉ በማስተዋል ለስድብ ሳትፈጥኑ ራሳችሁን በመመርመር ስህተቶቻችንን እየተማማርን እንድንቀጥል አሳስባችኋለሁ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል…

Monday, June 13, 2016

ጾመ ሐዋርያት

© በመልካሙ በየነ
ሰኔ 06/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ጾመ ሐዋርያት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ይህ ጾም ሐዋርያት መንፈስቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለትምህርት ወደ ዓለም ከመሄዳቸው አስቀድመው ለሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገው የጾሙት ነው። ይህንን ሲገልጽ ፍትሐነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 586 ላይ "ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን" ይላል። በበዓለ ሃምሳ ጾምና ስግደት የለም ይኼውም ማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 9 ቁጥር 15 ላይ እንደተጻፈው ነው።  ፍትሐ ነገሥቱም ይህንን ቃል ወስዶ አንቀጽ 15 ቁጥር 579 ላይ እንዲህ ብሏል። ጌታ ስለ ራሱ እንዲህ አለ “ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው በወሰዱት ጊዜ ያንጊዜ ይጾማሉ”። በዚህም መሠረት ጾም መጾም ተገቢ እንደሆነ እነሆ ተነገረ። የጾምን አስፈላጊነት አበው እንዲህ ይገልጹታል ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 564 ላይ "ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ" በተጨማሪም ቁጥር 573 "ጾምስ የሥጋ ግብር ነው ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ጸሎትን ያሻው ፈቃድ ለልብ የቁጣ ኃይል እንድትታዘዝ እንደሆነ" ቁጥር 574 ላይም "ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያንን እንመስላለን ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በፅኑዕ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለአጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው"ይላል። በዚህም መሠረት ለክርስቲያኖች 7 አጽዋማት ታዘዙ። ከእነዚህ መካካል አንዱ ጾመ ሐዋርያት ወይም የሰኔ ጾም ብለን የምንጠራው ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 569 ላይ "ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ 5 ቀን ነው" ተብሏል። አባቶቻችን እንደሰሩልን ሥርዓት መሠረት የዚህ ጾም መጀመሪያ በዓለሃምሳ እንደተፈጸመ የመጀመሪያው ሰኞ ነው። ይህም ማለት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ከጰራቅሊጦስ በዓል ቀጥሎ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይጀመራል ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ለመብላት ካላቸው ልዩ ፍቅር የተነሣ የፍትሐ ነገሥቱን ትእዛዝ በሙሉ ሳያነቡ ለራሳቸው እንደሚገባ አድርገው ተርጉመው ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሌላ 7 ቀናትን ይበላሉ። ይህንንስ ከየት አግኝተውት ነው ቢሉ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 580 ላይ "በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ጹሙ" የሚለውን ይዘው ነው። ነገር ግን በዓልን በማድረግ የሚጾሙ አጽዋማት አሉና በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ለዚህም ሲያስረዳ ቁጥር 581ላይ  "እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው የተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ሊበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር" ይላል። ረቡዕ እና አርብን ከዓመት እስከዓመት ጹሙ ነገር ግን ጥምቀት፣ በዓለ ልደት እና በዓለሃምሳ ካልዋሉባቸው በቀር ብሎ ተናግሮ ነበርና። ቁጥር 566 ላይ "ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው" ብሎ አዘዘ። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ብሉበት ቢል ኖሮ ግን በዚህ ቁጥር ላይ "በዓለ ሃምሳ እና ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባሉት ሰባት ቀን" ባለ ነበር። በመጾም በዓል ማድረግ እንደሚገባ እዚሁ አንቀጽ ላይ  ቁጥር 582 ላይ "ዳግመኛም እንዳንጾምባቸው እንዳንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም፡፡ ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር፡፡ በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና" ይላል። እንደዚሁም ቁጥር 583 ላይ "ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ፡፡ በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጅ ሊበሉበት አይደለም፡፡ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ 3 ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ3 ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም"  በማለት እንድንጾም ያስረዳል። ነገርግን ለመብል ራሳቸውን የሰጡ ወገኖች ይህንን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለውን 7 ቀን ይበሉበት ዘንድ በዓል አድርጉ ተብለናል ይላሉ። ከላይ እንደተመለከትነው በዓል የሚደረገው በመብል በመጠጥ ብቻ አይደለም በጾምም ጭምር ነው እንጅ። የሚበላበት ቢሆን ኖሮ  ቁጥር 588 ላይ "አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም፡፡ ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጅ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል" ብለው ባላዘዙም ነበር። ነገር ግን መጾም እንዲገባ ጹሙ ብለው አዘዙ እንጅ። አባቶቻችን ይህን ያዘዙን እነርሱ ሳይጾሙ አይደለም ጾመው ነው እንጅ ለዚህም  ቁጥር 585 ላይ "ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው" ብለዋል። ሰለዚህ ከአባቶቻችን አንበልጥምና በእነርሱ መንገድ እንጓዝ ዘንድ ይገባል። ይህን ሁሉ ብለው አልሰማ ላላቸው ግን ሁሉን ሊጠቀልል የሚችል ትእዛዝ እነሆ ሰጡን። ቁጥር 584 ላይ "ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል" ብለው አዘዙን። በጾም ወቅት ክርክር ከተፈጠረ ጹሙ ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ። ስለዚህ የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት ነው እንጅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ሌላ አንድ ሳምንት ከበላን በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት አይደለም።

Friday, June 10, 2016

ሎቱ ስብሐት !

©መልካሙ በየነ
ግንቦት 30/2008 ዓ.ም

የቅብአት እምነት ከጾም ቀናት መለያየት ውጭ ከተዋሕዶ ጋር ያለው ልዩነት ብዙ መስሎ አይታየንም ነበር አሁን ግን አምላክ የተመሰገነ ይሁን ይኼው "ወልደ አብ" ታትሞልን ምንፍናቸውን አወቅነው።
ተዋሕዶን ሲነቅፉ "ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር በተዋህዶ ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋህዶ ከበረ ቅብአት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል" ይላሉ ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ። ቃል የሚባለው ወልድ አምላክ አይደለምን? ልዩነታችን እዚህ ላይ ይጀምራል። አምላክ ነው ብለን የምናምን ከሆነ የሥጋን ንዴት ራሱ ወልደእግዚአብሔር ማራቅ አይችልምን? ምሥጢረ ሥላሴን ምን ብለው ተምረውት ይሆን። ያለ መንፈስ ቅዱስ ረዳትነት የሥጋ ንዴት አይርቅም ብለው ማመናቸው ወልድን አምላክ አይደለም ከማለታቸው ጋር ምን ይለያያል?  ገጽ 230 ላይ ደግሞ ለመለኮት የማይቀጠል ቃል እንዲህ ብለው ቀፀሉ "በዚህም በባሕርይ ልጅነቱ እኛ ብቻ ተጠቅመንበት አልቀረንም እርሱም ተጠቀመበት እንጅ" ይላሉ ሎቱ ስብሐት። አረ ይቅር በለን እንበል ወገኖቼ። ወልድ ምን ተጎድቶ ምን ጎድሎበት ነው በመወለዱ ተጠቀመ የሚባለው? ብዙ ማለት አልቻልኩም እጅግ ዘገነነኝ ውስጤን ሰቀጠጠኝ።  በጣም ከባድ ኑፋቄ ተራራ አክሎ ታየኝ። ይባስ ብለው ገጽ 233 ላይ "ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ እንደአስተካከለው..." ብለው አረፉት። በእውነት ወልድ ከባሕርይ አባቱ አብ እና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ያንስ ነበርን? ካላነሰ ታዲያ እንዴት እንዲህ ለማለት ደፈሩ።ሎቱ ስብሐት። አቤቱ ይቅር በለን!!!

" ወልድ ሦስት ልደት አለው" ቅብአቶች

©መልካሙ በየነ
ግንቦት 26/2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ

ቅብአቶች ወልድን ሦስት ጊዜ ተወልዷል ብለው ደፍረው ባይናገሩም አሁን ባሳተሙት መጽሐፋቸው ግን የወልድን 3 ልደታት ያሳያሉ። እኛ በተዋሕዶ ከበረ ብለን የምናምን ክርስቲያኖች ወልደ አብ ወልደማርያም ብለን ሁለት ልደታትን እናምናለን። ቅድመዓለም ከአብ እንበለ እም ያለእናት ድኅረ ዓለም ከድንግል እንበለ አብ ካለአባት ከድንግል የተወለደው ማለት ነው።
በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ባይ መናፍቃን ግን አብ ከድንግል ማርያም ማኅጸን በሥጋ ወለደው ብለው እኛ ከምናምናቸው ልደቶች በተጨማሪ ይጠቅሳሉ።
ወልደአብ የተሰኘው የክህደት መጽሐፋቸው ገጽ 216-217 ስናነብ እንዲህ ይላል። " የጌታችን ልደቱ ስንት ነው ቢሉ 2 ነው። እንዴት 2 ነው እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ዳግም ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ 3 አይደለምን እንደምን 2 ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደትና ዛሬ በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ 2 አይባልም። 2 ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ 2 ልደት አይባልም።ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ ያነን በከረጢት ከቶ ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ 2 ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ 2 አይባልም።ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት 2 ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ 2 ዘውድ አይባልም" ይላል።
ሰለእውነት ይህንን ምሳሌ የመሰለልን 2ን ለማስረዳት ነው ወይስ 3ን ለማስረዳት? ልብ በሉ መወለድ ግብር ነው መለበስም ግብር ነው። መወዳደር መነጻጸር የሚችሉት እነዚህ ነገሮች ናቸው። ተለባሹ ከተወላዲው ጋር በሌላ በኩል መነጻጻር መወዳደር ይችላሉ። ነገር ግን ተወላዲውን ከመለበስ ጋር መወለድንም ከተለባሹ(ልብሱ) ጋር ማነጻጸርም ሆነ ማወዳደር ግን አይቻልም። የጸሐፊውን አለመማር የምንረዳው እዚህ ጋር ነው። አስተውሉ ጸሐፊው "መምህር" ገብረመድኅን እንዳለው ያነጻጸረው መለበስን ከተወላዲ ጋር ነው። ልብስን ደግሞ ከመወለድ ጋር ማለት ነው። በእውነት ይህንን ምሳሌ እንኳን ምሥጢርን የተማረ ቀርቶ ያልተማረ ራሱ አማርኛ በመቻሉ ብቻ የሚረዳው ነገር እኮ ነው። መወለዱን ወይም ስንት ጊዜ ተወለደ ለሚለው አቻ የሚሆነው ስንት ጊዜ ተለበሰ የሚለው እንጅ ስንት ልብስ ነው የሚል መሆን የለበትም። ስንት ልብስ ነው ለሚለው አቻ ስንት ልጅ ነው የሚለው መሆን አለበት። ስለዚህ አንዱ ወልድ እምቅድመዓለም ከአብ በመለኮት ተወለደ ካለ በኋላ ዳግመኛ በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ብሎ እነዚህን አንድ ልደት ብሎ ይቆጥራል። የዞረበት ጸሐፊ ነው እንጅ እነዚህ በምን አቆጣጠር ነው አንድ የሚባሉት። በእርግጥ ተወላዲው ራሱ ነው ማለት አንድ ነው የተወለደው ግን ሁለት ጊዜ ነው። የአዲሱ ሸማ ምሳሌ ይህንን በሚገባ ያስረዳናል። ሸማው አንድ ነው ነገር ግን አንድ ጊዜም ከዛም በላይ መልበስ ይቻላል። ታዲያ ልብሱ አንድ ነው ብለን ሽህ ጊዜ የለበስነውን ልብስ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የለበስነው ብለን ብንናገር ሰውስ አይስቅብንም እንዴ? በእውነት የሰው ሳቅ ታየኝ ፍርስ እኮ ነው የሚልብን።
ሁለተኛው ምሳሌ የዘውዱ ጉዳይ ደግሞ በጣም የማይገባ የደናቁርት ምሳሌ ነው። የሚነግሡት ነገሥታት ከተወላዲው  ጋር የሚነጻጸሩ ናቸው።  በዘውዱ 2 ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ስንት ነገሥታት ነገሡ ነው የምንለው? ወይስ ደግሞ ዘውዱ ስላልተቀየረ አንድ ዘውድ ስለሆነ በዚያ ዘውድ የሚነግሡ ነገሥታት ሁሉ አንድ ናቸው ሲባል ሊኖር ነው። አረ ምን ነካህ ገብረመድኅን እንዳለው በእርግጥ መንፈስ ቅዱስ ፊትህን ጸፍቶ ያናገረህ እጅህን ጎትቶ ያጻፈህ ይመስለኛል። ያ ባይሆንማ ሁለቱን አንድ ለማለት ይህንን ምሳሌ ባላደረግኸውም ነበር። የዚህኛው ምሳሌ ደግሞ ተወላዲው የተለያየ እንደሆነ ያስረዳል። ተወላዲው ማለት ነገሥታቱ ማለት ናቸው። ስንት ነገሥታት ናቸው የነገሡበት ለሚለው አቻ የሚሆነው ስንት ልጆች ናቸው የተወለዱበት የሚል ነው። ዘውዱ ደግሞ ከ ልደቱ ጋር አቻ ይሆናል። በአንድ ዘውድ 2 ሦስት እንደነገሡበት ሁሉ በአንዱ ልደት ሁለት ሦስት ልጆች ተወልደውበታል ያሰኛል። ስለዚህ ዘውዱ አንድ ቢሆንም ብዙ ነገሥታት እንዲነግሡበት ሁሉ ልደቱም አንድ ቢባልም ቅሉ ብዙ ልጆች ይወለዱበታል እንደማለት ነው። ስለዚህ ይህ ያስረዳል የተባለው ምሳሌ የሚያስረዳው ነገር ሁለት የሆነውን አንድ እንድንል የማያደርገን ስለሆነ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ባይ መናፍቃን የጌታን ልደት ከ2 ወደ 3 ከፍ ማድረጋቸው ግርምትን ሳይፈጥር አልቀረም። እኛ ግን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ልደቱን ሁለት እንላለን። ቅድመዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደው አንድ ልደት  ድኅረዓለም ያለአባት በተዋሕዶ  ከድንግል  ማርያም የተወለደው ልደት ሁለት ልደት ማለት ነው። እነርሱ ሳይገባቸው  በመቅረቱ የተነሣ የሚጠቅሱት አባጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ምእራፍ 3 ቁጥር 46 ላይ የሚናገረውን የተዋሕዶ ትርጉም ነው። ከተዋሕዶ በኋላ ይህ የመለኮት ነው ይህ ደግሞ የትስብእት ነው ማለት እንዳይገባ መወለዱም በአብ ፈቃድ ብቻ እንዳልሆነ በራሱም  በመንፈስቅዱስም ፈቃድ እንደሆነ ሲያመሰጥር የተናገረውን ለ3ኛ ልደት ምሳሌ ይጠቅሱታል። አባጊዮርጊስ የሚለው ድንግል ማርያም የራሷ በሆነ ሥጋ የራሷ ያልሆነውን መለኮት ወለደችው። አብም የራሱ በሆነ መለኮት የራሱ ያልሆነውን ሥጋ ወለደው ይላል። ይህንን ይዘው ነው እንግዲህ አብም በማኅጸነማርያም በሥጋ ወልዶታል የሚሉት። መወለድ የወልድ የጥንት ግብር ነው ይሁን እንጅ በሥጋ ማርያም ለመገለጥ የሁሉም ፈቃድ ነው። ፍጹም ተዋሕዶን ሲያጠይቅ እኮ ነው በራሱ በሆነ መለኮት የራሱ ያልሆነውን ሥጋ ወለደው ማለቱ። ድንግልም መለኮትና ሥጋን ያዋሐደውን አምላክ ወለደችው ሥግው ቃል ወለደችልን ማለት ነው። መለኮትን ብቻ ያይደለ ሥጋን፤ ሥጋ ብቻ ያይደለ መለኮትን የያዘ ሥግው ቃልን ወለደች ማለት ነው። የአብንም እንዲሁ ነው የሚያስረዳን ከተዋሕዶ በኋላ መለያየት የሌለበትን ወልድ ቅድመዓለም ወለደው ሲል ነው። ይህን ስጽፍ ሞባይል ላይ ስለሆንኩ ብዙም መጻፍ አልቻልኩም እንጅ...

“ለቅድስና ያልታደለ ኅሊና ለኃጢአት ያጎበድዳል”

© መልካሙ በየነ
ግንቦት 9/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ፣

ዘመናችን ዘመነ መከራ ዘመናችን ዘመነ ሰቆቃ ነው፡፡ ለመዳን መሰናክሉ የበዛበት ለመጥፋት ደግሞ ሰፊ ጥርጊያ የተዘጋጀበት ዘመን፡፡ ተኩላዎች ከበጎች ጋር መስለው እና ተመሳስለው ስለሚኖሩ በጎች የተኩላዎችን ተኩላዎችም የበጎችን ቋንቋ የሚናገሩበት፣ አለባበስ የሚለብሱበት፣ አነጋገር የሚናገሩበት፣ አረማመድ የሚራመዱበት ዘመን፡፡ ይህ ዘመን ከሌላው ዘመን ሁሉ የሚያስጨንቅ ዘመን ነው ምክንያቱም በጎ ኅሊናችንን ጠላታችን ሰውሮብን መጥፎ ኅሊናችንን አጉልቶብናልና፡፡ ለቅድስና ከመጣር ይልቅ ለኃጢአት መሮጥን እንመርጣለን፡፡ ወንጌልን ከመማር ከማስተማር ይልቅ ተረት ተረት ስናወራ ስንሰማ እንውላለን፡፡ ትንንሽ ባቢሎኖችን በየቤታችን መሥርተናል፡፡ እነዚህ ባቢሎኖች የሚመሠረቱት ደግሞ በቤት አባወራዎች እና እመወራዎች ብቻ አይደለም ስልጣነ ክህነትን በተቀበሉት ለቤተክርስቲያን ጠባቂ ሆነው በተሸሙት ጭምር ነው እንጅ፡፡ ሁላችንም በተለይ ደግሞ መምህራን እኔ ልመክራችሁ የምችል ባልሆንም ተገድጀም ቢሆን እናገራለሁ መንፈሳዊውን ትምህርት ለመቅሰም ጉባኤ ለጉባኤ የተንከራተታችሁት፣ ዶክተር ማስተር ዲግሪ ዲፕሎማ ወዘተ ለመባል በየመንፈሳዊ ኮሌጆች ደጅ የጠናችሁት፣ ህዝቡን ለማስተማር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ለመመለስ ወንጌልን ያነገባችሁት፣ “ሑሩ ወመሀሩ” ተብላችሁ ዞራችሁ ታስተምሩ ዘንድ አደራ የተቀበላችሁት ለማን እንደሆነ ለምን እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋችኋል፡፡ ምክንያቱም አምላክ በእኛ ላይ አድሮ የሚሠራውን ሥራ እኛ ማዎቅ አንችልምና፡፡

የሁልጊዜ ጸሎታችን ሊሆን የሚገባው “አምላክ ሆይ ሳጥናኤል ከመላእክት ወገን ተቆጥሮ ነበር እንዲያውም አሐዜ መንጦላእት አቅራቤ ስብሐት ሊቀ መላእክት ነበረ ነገር ግን ወደቀ፤ አምላክ ሆይ ይሁዳ ከ12ቱ ደቀመዛሙርትህ ቁጥር ገብቶ ነበር ነገር ግን አንተን በ30 ብር ሸጠህ፣ አምላክ ሆይ አርዮስ ከሊቃውንት ቁጥር ገብቶ ተቆጥሮ ነበር ነገር ግን አንተን ፍጡር እናትህንም ወላዲተ ሰብእ ብሎ ካደ ስለዚህ ጅማሬን ሳይሆን ፍጻሜን ስጠኝ፡፡ ከምእመናን ጋር እቆጠር ዘንድ፣ ከዲያቆናት ጋር እቆጠር ዘንድ፣ ከቀሳውስት ጋር እቆጠር ዘንድ፤ ከመምህራን ጋር እቆጠር ዘንድ.፤ ከሊቃውን ጋር እቆጠር ዘንድ፣ ከጳጳሳት ጋር እቆጠር ዘንድ አንተ እንደረዳኸኝ ሁሉ ከዚህ ከተቆጠርኹበት ምድቤ አትለየኝ” ልንል ይገባናል፡፡ ምክንያቱም አሁን ዛሬ ላይ ምእመን፣ ዲያቆን፣ ቄስ፣ ጳጳስ፣ መምህር፣ ሊቅ ብሆን ነገ ግን ይህንን ስለመሆኔ ምንም ዋስትና የለኝምና፡፡

አሁን እየተቸገርን ያለነው በዚህ ጉዳይ ነው፡፡ የኔ ቢጤው ለስሙ ዲቁና ያመጣና በቤተመቅደስ ብጥብጥ ይጀምራል፡፡ “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይቀርም” እንዲሉ ቄስ ለመባል መስቀሉን ለመጨበጥ ይፈጥንና መስቀሉን ይጨብጣ ስሙን ይቀበላል ከዚያ በኋላ ማሰር መገዘት ብቻ እንጅ መፍታት የማይችል ይሆናል፡፡ የሚሰጠው ስልጣን ማሰርም መፍታትም እንዲችል ነበር ነገር ግን ዓላማው ሰውን ማሰር መገዘት ብቻ ስለነበር መፍታትን ይዘነጋል፡፡ በምንኩስናው ዓለምም እንዲሁ መስሎ ለማደር ብቻ ከእኔ በላይ ማን አለ እኔ የምላችሁን ብቻ አድርጉ ብሎ ለማስፈራራት እስከ ጵጵስና ማዕረግ ድረስ ወንበሩን መረከብ ይሻሉ፡፡ በጣም ከባድ አስጨናቂ ዘመን ማለት ዓላዊ ንጉሥ ከሐዲ ጳጳስ አንድ ዘመን ሲገናኙ ነው፡፡ ንጉሡ ብቻ ዓላዊ ቢሆን ጳጳሱ ምእመኑን በትምህርት ያበረታል ለሰማእትነት ያበቃል፡፡ ጳጳሱም ከሐዲ ከሆነ ግን በትምህርት የሚጸና በእምነት የሚቆም ለሰማእትነት የሚበቃ ክርስቲያን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ዛሬ በሀሜት ተላልቀናል፡፡ ጳጳሱ እንዲህ ናቸው አሉ ካህኑ እንዲህ ናቸው አሉ ዲያቆኑ እንዲህ ነው አሉ እየተባባልን ነው፡፡ በእርግጥ ከሀሜት ያለፈ በተግባር የተረጋገጠ በንግግራቸው የተመሰከረ ማስረጃ ያለባቸውም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በጎ ኅሊና ስለሌላቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የአስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የእምነት ድሆችም ናቸው፡፡

በእርግጥ እኛም ላይ ችግር አለ፡፡ አባቶች በተለይ ደግሞ አንዳንድ ጳጳሳት የሚያስተምሩት የሚናገሩት ሁሉ ትክክል የሚመስላቸው አሉ፡፡ “አቡነ እገሌ እንዲህ አደረጉ” ተብሎ መረጃው ሲቀርብላቸው አባቶች ምንም ቢያጠፉ እንዲህ አደረጉ መባል የለባቸውም ብለን እንሞግታለን፡፡ በዚያ ቢሆንማ ይሁዳ አይቀድማቸውም ነበር በዚያ ቢሆንማ አርዮስ አይቀድማቸውም ነበር በዚያ ቢሆንማ ሳጥናኤል አይልቃቸውም ነበር እንዴ፡፡ እኛ የምንነጋገረው ስለእምነታችን ከሆነ በእምነታችን መቀለድ አይገባንም፡፡ እምነታችንን የተመሠረተችው ደግሞ በክርስቶስ ደም ነው፡፡ ስለዚህ ይች ቤተክርስቲን ቅድስት ክብርት ንጽሕት ናት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የወንበዴዎች ዋሻ ስትሆን እየተመለከትን ዝም ማለት ያለብን አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ አምላክ ዝም ያለውን እኛ ምን አገባን የምንልም የዋሐን አለን፡፡ አምላክ የእኛን ጽናትና ብርታት ይመዝናል ይለካል በመጀመሪያ አምላክ ዝም እንዳይላቸው እኛ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ለጆሮ የሚቀፍ ንግሮችን ዐውደምሕረቱ ላይ ሲነገሩ እንሰማለን፣ ጳጳሱ ቆመው እኔ ካልኩት ውጭ አታድርጉ እያሉ ከሥርዓ ውጭ እንድንሆን ያስገድዱናል፡፡ እኔ በጣም የሚገርመኝ አቡነ ማርቆስ የተናገሩት አንድ ንግግር ነው፡፡ በእርግጠኝነት ይህንን እሳቸው ተናግረውታል ብላችሁ ላታምኑ ትችላላችሁ፡፡ የሚያውቃቸው ሰው ግን አንተ ይች እንዴት ትገርምሃለች እንደሚል አልጠራጠርም፡፡ በታላቁ ዲማ ገዳም የቅዳሴ ጸበል የሚጠጣው የቆረበ ሰው ብቻ ነው፡፡ ማንም ሰው ካልቆረበ የቅዳሴ ጸበል አይሰጠውም፡፡ የቅዳሴ ጸበል ክብር አለው ትንሽም ጠብ አትደረግም፡፡ ይህንን ግን አይፈልጉም አባ ማርቆስ ከዚያ ምን አደረጉ የቅዳሴውን ጸበል መድረኩ ላይ ቆመው ህዝቡን ይረጩት ጀመሩ፡፡ ዲማ እንኳ ጸበል እንዲህ መሬት ላይ ሊረጭ ቀርቶ እንደነገርኳችሁ ያልቆረበ ሰው አይቀምሰውም፡፡ ከዚያ ለምን የቅዳሴ ጸበል ትረጩናላችሁ ብለው አንዳንዶች ይጠይቃሉ፡፡ አባ ምን አሉ “ታዲያ አረቂ ልርጫችሁ ወይ”፡፡ በእውነት ይህ ለዚያ ምእመን መልስ ነው ዐወደ ምሕረት ላይ የሚነገር ንግግር ነው አይደለም፡፡ በእርግጥ ይህን ከተናገሩት ከርመዋል፡፡ ብቻ ኅሊናችን በጎ ማሰብ ቅድስና ማሰብ ካቆመ ነቅአ ኃጢአት እንደሚሆን ማስተዋል ያስፈልገናል፡፡

አንድ ደቀመዝሙር ነበር መምህሩ ራሳቸው በሕይወት ሳሉ “ይህ እኮ ይሁዳ ነው” ይሉት የነበረ፡፡ ከዚያም እንደማንኛውም ደቀመዝሙር አስተማሩት ለቁም ነገር አበቁት፡፡ መምህሩ አረፍተ ዘመን ገደባቸው እና እንደአባቶቻችን እሳቸውም አንቀላፉ ከዚያም በወንበራቸው እሳቸውን ይተካል ተብሎ በመምህሩ ወንበር ላይ ይህን ደቀመዝሙር በመምህርነት አስቀመጡት፡፡ በመንበራቸው ሲቀመጥ “አይገባኝም ብሎ እያለቀሰ ነበር” ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ነገር ተገልብጦ ታሪክ ተቀይሮ የመምህሩን ሚስት ተኛት፡፡ በዚህ የተነሣ ዲማ ላይ ታላቅ ማዕበል ተፈጠረ፡፡ ይህን የሚያደርገው ሰው የዲማ አካባቢ ተወላጅ ከመሆኑ የተነሣ የእርሱ ወገን የሆኑት ብጥብጥ አስነሡ፡፡ ነገር ግን ከላይ እስከታች ያሉት በሙሉ ከመንበሩ እንዲነሣ ፈረዱና ተነሥቶ ሌላ ከተማ  በአቡነ ማርቆስ ረዳትነት ሥራ ተሰጠው፡፡ የዲማ ሰው የዲማ ሊቃውንት አብረውት የተማሩት ሊቃውንት ያ ሰው ዲማ እንዳይደርስ አወገዙት፡፡ እዚያ ከሄደ ግን ሊፈጠር የሚችለው ብጥብጥ ከባድ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል ነገር ግን ዛሬ የዲማን ብጥብጥ የሚሹት አቡነ ማርቆስ ደብዳቤ ጽፈው ዲማ መምህር እንዲሆን ሾመውት አረፉ፡፡ ምክንያቱም “ለቅድስና ያልታደለ ኅሊና ለኃጢአት ያጎበድዳል” እና የኃጢአት ልምምድ መጀመራቸውን እያሳዩን ነው፡፡ ግነ ነገ ዲማ ላይ ምን ይፈጠር ይሆን??
አምላክ ሆይ ለቤተክርስቲያናችን ፍቅርን አንድነትን አድል፡፡

Monday, May 9, 2016

“የቅዱስ ማርቆስ እረፍት በዓል በአቡነ ማርቆስ ስብከት”


© መልካሙ በየነ
ግንቦት 1/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ዕለቱ ዳግማይ ትንሣኤ የሚከበርበት ዕለተ ሰንበት የወሩ መጨረሻ ሚያዝያ 30 በምሥራቅ ጎጃም ብቸኛ በሆነው የቅዱስ ማርቆስ ታቦት ከሚገኝበት ከመልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሱ በረከትን ለመካፈል በዚያ ተሰባስበናል፡፡ ግቢው ከወትሮው በተለየ ከቅርብም ከሩቅም ሳይቀር በኮንትራት አውቶቡስ በመጡ ብዛት ባላቸው ሕዝበ ክርስቲያኖች ተሞልቷል፤ ክህነት የሚቀበሉ የቆሎ ተማሪዎችም ግቢውን አድምቀውታል፡፡ የቅዱስ ማርቆስ ታቦት ማደሪያ የነበረው ቤተክርስቲያን በመታደስ ላይ ስለሆነ የተቀደሰው እዚያው ግቢ ካለው ከቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ነበር፡፡ ቅዳሴውን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ማርቆስ ቀደሱትና 1፡30 አካባቢ ተፈጸመ፡፡ ከዚያም የሚገርመው ስብከት ተሰጠ፡፡

ዕለቱ ዕለተሰንበት እንደመሆኑ መጠን የእመቤታችን ተአምር በየአጥቢያው ይነበባል እዚህ ግን አቡኑ ራሳቸው አንባቢ ስለነበሩ “እሰግድ ለኪ” የሚለው ከተአምሩ ክፍል ተነበበና እመቤታችን የአደረገችው ተአምር እና የእመቤታችንን 33 በዓላት የሚገልጸው የምንባቡ ክፍል ሳይነበብ “አባታችን ሆይ” ብለው አሰሩት፡፡ በእርግጥ አባታችን ከዚህ በፊት ነግረውናል “የእመቤታችንን 33 በዓላት ማነብነብ ካሌንደር መናገር ነው፡፡ ዝም ብላችሁ እለፉት” ብለውን ነበር አላስችል ብሎን እንጅ፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ መነኩሴ ተነሡና ይቅርታ ስማቸውን ስለማላውቃቸው ነው “ከተማችን ደብረ ማርቆስ፣ ጳጳሳችን አቡነ ማርቆስ፣ የምናከብረው በዓል የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ነው” ብለው አባታችንን በብዙ ነገር ገለጹላቸው፡፡ “አባታችን የወንጌል አባት የትምህርት አባት” እንደሆኑ በብዙ ነገር ተናገሩላቸው፡፡ ግን የተነገረው ሁሉ አባታችንን የሚገልጻቸው አልመሰለኝም ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ያስተማሩት ትምህርት ከተባለው በታች እጅጉን የወረደ ስለነበር፡፡ መድረኩን ለአቡነ ማርቆስ ለቀቁላቸው፡፡ ከዚያም “አስተማሩን” ያስተማሩንን ግን አብረን እንየው፡፡

አቡኑ ማይኩን እንደያዙ “ቁጭ በሉ” አሉን፡፡ “ጭቃ ምናምን አይባልም ዛሬ የመጣችሁት የቅዱሱን ሐዋርያ ዜና እረፍት ልትማሩ ነው” ይህ ንግግራቸው እንዴት ያለ ማር ንግግር ነበር መሰላችሁ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የተቀበለውን መከራ ጭቃ ላይ ከመቀመጥ አሳንሰን ልንመለከተው ስለማይገባ፡፡ ግን ከዚህ በኋላ ያለው ትምህርት እውቀት ያልታከለበት ፍጹም ከጨዋም የማይጠበቅ የማይረባ ነገር ነበር፡፡ ሰውን እንዴት እስከ 3 ሰዓት ድረስ ላቆየው የሚል ብቻ ነበር፡፡ “መርሐ ግብራችን እስከ 3 ሰዓት ይቆያል፡፡ ዛሬ ስለሐዋርያው በስፋት እንማማራለን፡፡ ትምህርቱን ሳትጨርሱ እንዳትነቃነቁ ባላችሁበት አረፍ አረፍ በሉ” አሉና ስንክሳሩን ማንበብ ጀመሩ “ወበዛቲ ዕለት አእረፈ ቅዱስ ማርቆስ…” ብለው የቅዱሱን እረፍት ጀመሩና ወደግብረ ሐዋርያት ምእራፍ 12 ተሸጋገሩ በእርግጥ የትምህርታቸውም መነሻ ይኼው ግብረ ሐዋርያት ላይ ያለው ቃል ነበር፡፡ ስንክሳሩን ጨርሰው ማስተማር ወይም ማንበብ አልቻሉም መሰል ወደ ሌላ ርእስ ገቡ፡፡ የቅዱስ ማርቆስን እረፍት ለመማር የተቀመጠው ሰው የቅዱሱን እረፍት ሳይማር ዝም ብሎ ተቀምጦ ያልገባው ሲስቅ የገባው ደግሞ ሲቃጠል ቆየ፡፡ ትምህርቱ ወደ መባእ ተለወጠ እና “አንች ጥላ ይዘሽ የምትዞሪዪት በእውነት እግዚአብሔር ጥላ ቸገረውን እግዚአብሔር የቸገረው ሰው ነው፡፡ እናንተን ነው የሚፈልግ” አሉ በጣም መልካም ንግግር ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን ፍለጋ ነው የተሰቀለው የሞተው የተነሣው ነገር ግን መባዕ ማስገባት ካልተቻለ ለምን መባእ ተቀባዮችን ምንጣፍ አንጥፈው እንዲሰበሰቡ ፈቀዱላቸው ብየ ውስጤ ተቃጠለ፡፡ እዚያው ውስጥ መባእ ተቀባዮች አሉ እኮ ጥላውም የሚሸጠው ከእነሱው ነው፡፡ “ጥላ ይዛችሁ ዙሩ የሚል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈ ነገር አለን” ብለው ጠየቁ፡፡ “ታዲያ ያልተጻፈ ነገር ከየት አመጣችሁ እናቶች የምላችሁን ስሙ፡፡ እኮ ከእኔ ከጳጳሱ በላይ ማን ይንገራችሁ” አሉ፡፡ እኛ እኮ ተዋሕዶዎች ነን አይደል እንዴ፡፡ ትውፊት የምንቀበል ነን፡፡ በእምነታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ጥቅስ ይገኝላቸዋል ብሎ መገመት ያዳግታል፡፡ ያንንማ የሚሉት መናፍቃኑ ናቸው እኮ፡፡ ታዲያ ጥላ ይዛችሁ ዙሩ የሚል ጥቅስ አሳዩን የሚሉን ከሆነማ እያስተማሩን የነበረው የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ሚያዝያ 30 መሆኑን ጥቅስ ማሳየት ነበረባቸው ማለት እኮ ነው፡፡ በአንዴ ረሱት መሰለኝ እንጅ እኮ ስንክሳሩን ከማንበባቸው በፊት እንዲህ ብለውን ነበር “መጽሐፍ ቅዱስ ማንዋል ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ መፍቻ ስንክሳር ገድል እና ተአምር ነው”፡፡ አሁን ጥላው ላይ ግን ጥቅስ አምጡ ሲሉን ገረመን፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ለሁሉ ነገር ግልጽ ናት፡፡ ወይ በግልጽ ጥላ አታስገቡ ብሎ ማስተማር ነው የሚሻለው፡፡ ከዚህ በኋላ የቅዱስ ማርቆስ እረፍት እንዴት እንደሆነ ሳንማር ወደ ሌላ ርእስ ገቡ፡፡ የጥምቀት ጉዳይ ተነሣ፡፡ “አንዴ ተጠምቃችኋል ዳግመኛ ጥምቀት የለም፡፡ ጥምቀት አንዲት ናት ልብ ብላችሁ ስሙኝ ዋናው መልእክት እዚህ ላይ ነው፡፡ ዳግመኛ ተጠመቁ ቢባል ኖሮ እኛ እንነግራችሁ ነበር እኮ ከእኛ ከጳጳሳትና ከካህናት ውጭ ማን ይንገራችሁ እንግዲህ፡፡ እኮ  አንድ ዲማ ብቻ ነው እንዴ ደብር ያለ፡፡ ዲማ እኮ አንድ ተራ እንደማንኛውም ሁሉ ደብር ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለይ እናንተ የመጣችሁ ልትማሩ ነው እሱን ተምራችሁ ሂዱ፡፡ መጠመቅ ምናምን የሚባል ነገር የለም፡፡ ወላጆችም ልጆቻችሁን እኔ በ40 በ80 አስጠምቄሃለሁ አስጠምቄሻለሁ ዳግም ጥምቀት አያስፈልግም በሏቸው፡፡ በዲማ በዚህም በአብማ በኩል እናጠምቃለን እያሉ የሚልከሰከሱ አሉ አሉ፡፡ ደግሞ እኮ የሚገርማችሁ በስመ አብን ያልተማሩ ናቸው” ብለው ምንታዌነትን ደግፈው አስተማሩ፡፡ ሰው በብዛት አልገባውም የገባው ግን ልቡ በንዴት ጨሷል፡፡ ሰው የተረዳቸው እነዚህ አጥማቂ ነን ባዮችን የገሰጹ አድርጎ ነው፡፡ ግልጽ ነው ምሥራቅ ጎጃም ላይ ቅብአት የሚባል እምነት አለ፡፡ እሱ እምነት በእኛው በተዋሕዶ እምነት ሥር ተደብቆ ራሱን ይፋ ሳያደርግ የሚኖር ነው፡፡ ተአምረ ማርያምን በ28 ጌታን የወለደችበት ነው በ29ም መድኃኒታችንን የወለደችበት ነው ይላል፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ገና በ28 ይከበራል በቅብአት እምነት ዘንድ ግን ሁልጊዜም በ29 ይከበራል፡፡ ይህንን በ28 መከበሩን እሳቸው አይቀበሉትም ለዚያም እኮ ነው ተአምረ ማርያም ሁለቱን ቀን ስለሚጠቅስ “ካሌንደር ነው” ለማለት የደፈሩ፡፡ ዲማ ጊዮርጊስ ሳይሆን አብማ ላይ ይልከሰከሳሉ የተባሉት ግለሰቦችም ብቻ ሳይሆኑ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በፍትሐ ነገሥቷ ላይ አንቀጽ 3 ቁጥር 24 ላይ “ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም” ይላል፡፡ ስለዚህ ጥምቀት አንዲት ናት አትከለስም አትደገምም ግን ቅብአት ያጠመቀው ሰው ክርስቲያን ሊባል ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ አባታችን በእርግጥ “ኦርቶዶክስ አንዲት ጥምቀት ብላ ታምናለች ዳግም መጠመቅ የለባችሁም” ያሉት ተዋሕዶ የሆኑትን አይደለም ቅብአት የሆኑትን ነው፡፡ በዚያው እምነታችሁ ጽኑ ብለው በግልጽ ነው የተናገሩት፡፡ “በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እዚህ የመጣችሁ እምነታችሁን ልትለውጡ አይደለምና ዳግም መጠመቅ የለባችሁም፡፡ ዳግም ተጠመቁ የሚላችሁ ሰው ካለም ስም ዝርዝሩን በሊስት አቅርቡልኝ” ነው ያሉት ይህ ደግሞ ግልጽና ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ ከዚህ በፊት በሥውር ያስተምሩ የነበሩ የቅብአት አስተማሪዎችም አሁን በግልጽና በድፍረት ማስተማሩን ተያይዘውታል፡፡ ከዚህም አልፈው በአንድ ገዳም ስም “ወልደ አብ” የሚል መጽሐፍ አሳትመው እየሸጡ ናቸው፡፡ ይህ የተደረገው ደግሞ አሁን አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃም ላይ ከመጡ በኋላ ነው፡፡ ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና ፍትሐ ነገሥቱ “ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም” ይላል፡፡ አማኒ ካልሆነ ደግሞ ያ ከእነርሱ የተቀበለው ጥምቀት አንድ ተብሎ አይቆጠርም ዜሮ ተብሎ ይቆጠራል እንጅ፡፡ የቅብአት ካህናት መናፍቃን ናቸውን የሚል ጥያቄ ከተነሣ እኔ በበኩሌ መልሴ አዎ መናፍቃን ብቻ ሳይሆኑ መንፈስ ቅዱስን በማጭበርበር የተቀበሉ የመሰላቸው ስልጣኑ ያላደረባቸው ናቸው ብየ አምናለሁ፡፡ ይህን የምለው ክህነት የሚሰጡት ጳጳሳት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ናቸው ቅብአት የራሱ ጳጳስ የለውም ስለዚህ ክህነቱን ለመቀበል የግድ ለአንድ ቀን ራሱን ተዋሕዶ ነኝ ማለት አለበት፡፡ ተዋሕዶ ነኝ ብሎ በተዋሕዶ ስም ክህነት ይቀበላል ክህነቱን ከተቀበለ በኋላ ግን ቅብአት ነኝ ይላል፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ካህን ነውን እንግዲህ ራሳችሁ ፍረዱት፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሰው ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ዳግመኛ ይጠመቃል ምክንያም የመጀመሪያው ጥምቀት አማኒ ሊያደረገን የሚችል ስላልሆነ፡፡ ይህንን የሚለው ደግሞ መጽሐፋችን እንጅ አቡኑ የጠቃቀሷቸው አድባራትና ገዳማት ወይም ግለሰቦች አይደሉም፡፡ ስለዚህ ቅብአትና ተዋሕዶን ተምሮ የምስጢራቸውን ልዩነት የተረዳ ማንኛውም ሰው ዳግም ይጠመቃል አራት ነጥብ፡፡ እሳቸው ሰውን ለማደናገር “ክዶ የተመለሰ ሰው እንኳ ዳግም ተጠመቅ አይባልም እንኳን መጀመሪያ የተጠመቀና ሳይክድ እዚሁ የቆየ ሰው” አሉ፡፡ ይህማ እኮ ልክ ነው መጀመሪያ በትክክል ተጠምቆ ልጅነትን ያገኘ ሰው ከመናፍቅ ስላልተጠመቀ አማኒ ነው፡፡ ነገር ግን ሥጋ ፈትኖት ካደ በኋላም ተመለሰ፡፡ መጀመሪያ ተጠምቆ ስለነበር ክህደቱ ኃጢአት ስለሆነ የቄድር ጥምቀት ይጠመቃል ቅብአት የሆነ ሰው ግን ከዚያ ይለያል ምክንያቱም በመጀመሪያም አማኒ ስላልነበር ተጠመቀ ተብሎ አይቆጠርምና፡፡ በእውነት የማዝነው በዙሪያቸው ላሉት ሊቃውንት ነው፡፡ ደፍረው ማስተማር አይችሉም “እምነታችን ተዋሕዶ ናት” ማለት አይችሉም ምክንያቱም የሚመጣባቸውን ፈተና ያውቃሉና ስለዚህ በድፍኑ “ኦርቶዶክስ” ብለው ያልፉታል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የስድብ ገፈት ተቋዳሽ የነበሩት በበዓላት ላይ ለታቦቱ ክብር ድካማቸውን ያራቁ ወጣቶች ነበሩ፡፡ “እውነት አሁን አስፋልት ላይ ጨፌ መነስነስ ምን የሚሉት ነገር ነው፡፡ እኔ ደጋግሜ ተናገርኩ የሚሰማኝ ግን አጣሁ፡፡ የእኔ ሥራ መናገር ብቻ ነው የሚሠማ ካለ ይስማኝ” አሉ፡፡ በእውነት ዳዊት ራቁቱን እስኪሆን ድረስ በፊቱ የዘመረለትን ታቦት፤ በሆሣዕና ዕለት ልብሳቸውንና ዘንባባቸውን እያነጠፉ የተቀበሉትን አምላክ ወጣቱ በቻለው ነገር ቢያደርግ ምኑ ነው ክፋቱ፡፡ ህዝቡን ለመሳብ ግን በድርቁ አሳብበው ገቡት “ስንት ወንድሞቻችን እየተራቡ እየተጠሙ አስፋልት ላይ ሳር መነስነስ ምንድን ነው፡፡ ብራብ አላበላችሁኝም እንጅ ሳር አልነሰነሳችሁልኝም ብሎ አይጠይቀንም፡፡ ሳር የሚነሰነሰው እናቶቻችን ቡና ሲያፈሉ ነው” ብለው አስተማሩን፡፡ በእውነት የሳሩ ገንዘብ ነው በድርቅ የተጎዱ ወገኖቻችንን የሚመግባቸው፡፡ በእውነት መቼ ነው በድርቅ ለተጎዱት ልጆቻችን ብለው ጸሎተ ምሕላ ያስያዙን፡፡ እንጃ ግን የመልእክቱ ዓላማው ሌላ ነው፡፡

በእውነት እኛን ያሰባሰበን የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ነበር ግን አልታደልንምና ስንወናበድ ስንሰደብ ዋልን፡፡ ከዚያ በኋላ 3 ሰዓት አካባቢ ሆነ “ማሳሰቢያ ነገር አለችኝ ሰዓቱም ጥሩ ላይ ነው የጨረስኩ” አሉ፡፡ ማሳሰቢው እንዳለቀ ታቦቱ ይወጣል ዑደት ይካሄዳል ብለን ነበር ግን ማሳሰቢያቸው በጣም ረዘመብን፡፡ “በዚያ በቢቡኝ በኩል” ብለው ጀመሩና ስለአቻ ጋብቻ አስተማሩን፡፡ “ሴት ስትደርስ ምልክት ታሳያለች” ብለው በድንችና በበቆሎ እየመሰሉ አስተማሩን፡፡ እኛም ሴት የምትደርስበትን ጊዜ በሚገባ አወቅን፡፡ የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ግን ተረሣ፡፡

ከዚህ በኋላ ግን መታገስ አልቻልኩምና ወደ ወንድሜ ዲ.ን ሰሎሞን ስልኬን ደወልኩ ‹‹የት ነህ አልኩት›› ‹‹እኔ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስቀድሼ አሁን ዶርሜ ነኝ›› አለኝ፡፡ ‹‹በቃ መጣሁ›› አልኩና ስልኬን ዘግቼ ወስጤ እተቃጠለ የታቦቱን ዑደት ሳላከብር ሳላይ ወደ ዶርሜ አቀናሁ፡፡ አምላክ ዘመናችንን ይባርክልን መናፍቃንን ያስታግስልን፡፡

አሜን፡፡