©መልካሙ በየነ
ግንቦት 30/2008 ዓ.ም
የቅብአት እምነት ከጾም ቀናት መለያየት ውጭ ከተዋሕዶ ጋር ያለው ልዩነት ብዙ መስሎ አይታየንም ነበር አሁን ግን አምላክ የተመሰገነ ይሁን ይኼው "ወልደ አብ" ታትሞልን ምንፍናቸውን አወቅነው።
ተዋሕዶን ሲነቅፉ "ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር በተዋህዶ ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋህዶ ከበረ ቅብአት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል" ይላሉ ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ። ቃል የሚባለው ወልድ አምላክ አይደለምን? ልዩነታችን እዚህ ላይ ይጀምራል። አምላክ ነው ብለን የምናምን ከሆነ የሥጋን ንዴት ራሱ ወልደእግዚአብሔር ማራቅ አይችልምን? ምሥጢረ ሥላሴን ምን ብለው ተምረውት ይሆን። ያለ መንፈስ ቅዱስ ረዳትነት የሥጋ ንዴት አይርቅም ብለው ማመናቸው ወልድን አምላክ አይደለም ከማለታቸው ጋር ምን ይለያያል? ገጽ 230 ላይ ደግሞ ለመለኮት የማይቀጠል ቃል እንዲህ ብለው ቀፀሉ "በዚህም በባሕርይ ልጅነቱ እኛ ብቻ ተጠቅመንበት አልቀረንም እርሱም ተጠቀመበት እንጅ" ይላሉ ሎቱ ስብሐት። አረ ይቅር በለን እንበል ወገኖቼ። ወልድ ምን ተጎድቶ ምን ጎድሎበት ነው በመወለዱ ተጠቀመ የሚባለው? ብዙ ማለት አልቻልኩም እጅግ ዘገነነኝ ውስጤን ሰቀጠጠኝ። በጣም ከባድ ኑፋቄ ተራራ አክሎ ታየኝ። ይባስ ብለው ገጽ 233 ላይ "ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ እንደአስተካከለው..." ብለው አረፉት። በእውነት ወልድ ከባሕርይ አባቱ አብ እና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ያንስ ነበርን? ካላነሰ ታዲያ እንዴት እንዲህ ለማለት ደፈሩ።ሎቱ ስብሐት። አቤቱ ይቅር በለን!!!
No comments:
Post a Comment