© በመልካሙ በየነ
ሰኔ 06/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ጾመ ሐዋርያት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ይህ ጾም ሐዋርያት መንፈስቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለትምህርት ወደ ዓለም ከመሄዳቸው አስቀድመው ለሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገው የጾሙት ነው። ይህንን ሲገልጽ ፍትሐነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 586 ላይ "ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን" ይላል። በበዓለ ሃምሳ ጾምና ስግደት የለም ይኼውም ማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 9 ቁጥር 15 ላይ እንደተጻፈው ነው። ፍትሐ ነገሥቱም ይህንን ቃል ወስዶ አንቀጽ 15 ቁጥር 579 ላይ እንዲህ ብሏል። ጌታ ስለ ራሱ እንዲህ አለ “ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው በወሰዱት ጊዜ ያንጊዜ ይጾማሉ”። በዚህም መሠረት ጾም መጾም ተገቢ እንደሆነ እነሆ ተነገረ። የጾምን አስፈላጊነት አበው እንዲህ ይገልጹታል ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 564 ላይ "ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ" በተጨማሪም ቁጥር 573 "ጾምስ የሥጋ ግብር ነው ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ጸሎትን ያሻው ፈቃድ ለልብ የቁጣ ኃይል እንድትታዘዝ እንደሆነ" ቁጥር 574 ላይም "ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያንን እንመስላለን ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በፅኑዕ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለአጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው"ይላል። በዚህም መሠረት ለክርስቲያኖች 7 አጽዋማት ታዘዙ። ከእነዚህ መካካል አንዱ ጾመ ሐዋርያት ወይም የሰኔ ጾም ብለን የምንጠራው ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 569 ላይ "ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ 5 ቀን ነው" ተብሏል። አባቶቻችን እንደሰሩልን ሥርዓት መሠረት የዚህ ጾም መጀመሪያ በዓለሃምሳ እንደተፈጸመ የመጀመሪያው ሰኞ ነው። ይህም ማለት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ከጰራቅሊጦስ በዓል ቀጥሎ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይጀመራል ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ለመብላት ካላቸው ልዩ ፍቅር የተነሣ የፍትሐ ነገሥቱን ትእዛዝ በሙሉ ሳያነቡ ለራሳቸው እንደሚገባ አድርገው ተርጉመው ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሌላ 7 ቀናትን ይበላሉ። ይህንንስ ከየት አግኝተውት ነው ቢሉ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 580 ላይ "በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ጹሙ" የሚለውን ይዘው ነው። ነገር ግን በዓልን በማድረግ የሚጾሙ አጽዋማት አሉና በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ለዚህም ሲያስረዳ ቁጥር 581ላይ "እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው የተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ሊበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር" ይላል። ረቡዕ እና አርብን ከዓመት እስከዓመት ጹሙ ነገር ግን ጥምቀት፣ በዓለ ልደት እና በዓለሃምሳ ካልዋሉባቸው በቀር ብሎ ተናግሮ ነበርና። ቁጥር 566 ላይ "ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው" ብሎ አዘዘ። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ብሉበት ቢል ኖሮ ግን በዚህ ቁጥር ላይ "በዓለ ሃምሳ እና ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባሉት ሰባት ቀን" ባለ ነበር። በመጾም በዓል ማድረግ እንደሚገባ እዚሁ አንቀጽ ላይ ቁጥር 582 ላይ "ዳግመኛም እንዳንጾምባቸው እንዳንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም፡፡ ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር፡፡ በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና" ይላል። እንደዚሁም ቁጥር 583 ላይ "ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ፡፡ በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጅ ሊበሉበት አይደለም፡፡ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ 3 ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ3 ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም" በማለት እንድንጾም ያስረዳል። ነገርግን ለመብል ራሳቸውን የሰጡ ወገኖች ይህንን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለውን 7 ቀን ይበሉበት ዘንድ በዓል አድርጉ ተብለናል ይላሉ። ከላይ እንደተመለከትነው በዓል የሚደረገው በመብል በመጠጥ ብቻ አይደለም በጾምም ጭምር ነው እንጅ። የሚበላበት ቢሆን ኖሮ ቁጥር 588 ላይ "አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም፡፡ ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጅ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል" ብለው ባላዘዙም ነበር። ነገር ግን መጾም እንዲገባ ጹሙ ብለው አዘዙ እንጅ። አባቶቻችን ይህን ያዘዙን እነርሱ ሳይጾሙ አይደለም ጾመው ነው እንጅ ለዚህም ቁጥር 585 ላይ "ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው" ብለዋል። ሰለዚህ ከአባቶቻችን አንበልጥምና በእነርሱ መንገድ እንጓዝ ዘንድ ይገባል። ይህን ሁሉ ብለው አልሰማ ላላቸው ግን ሁሉን ሊጠቀልል የሚችል ትእዛዝ እነሆ ሰጡን። ቁጥር 584 ላይ "ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል" ብለው አዘዙን። በጾም ወቅት ክርክር ከተፈጠረ ጹሙ ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ። ስለዚህ የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት ነው እንጅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ሌላ አንድ ሳምንት ከበላን በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት አይደለም።
No comments:
Post a Comment