Friday, June 10, 2016

" ወልድ ሦስት ልደት አለው" ቅብአቶች

©መልካሙ በየነ
ግንቦት 26/2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ

ቅብአቶች ወልድን ሦስት ጊዜ ተወልዷል ብለው ደፍረው ባይናገሩም አሁን ባሳተሙት መጽሐፋቸው ግን የወልድን 3 ልደታት ያሳያሉ። እኛ በተዋሕዶ ከበረ ብለን የምናምን ክርስቲያኖች ወልደ አብ ወልደማርያም ብለን ሁለት ልደታትን እናምናለን። ቅድመዓለም ከአብ እንበለ እም ያለእናት ድኅረ ዓለም ከድንግል እንበለ አብ ካለአባት ከድንግል የተወለደው ማለት ነው።
በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ባይ መናፍቃን ግን አብ ከድንግል ማርያም ማኅጸን በሥጋ ወለደው ብለው እኛ ከምናምናቸው ልደቶች በተጨማሪ ይጠቅሳሉ።
ወልደአብ የተሰኘው የክህደት መጽሐፋቸው ገጽ 216-217 ስናነብ እንዲህ ይላል። " የጌታችን ልደቱ ስንት ነው ቢሉ 2 ነው። እንዴት 2 ነው እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ዳግም ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ 3 አይደለምን እንደምን 2 ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደትና ዛሬ በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ 2 አይባልም። 2 ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ 2 ልደት አይባልም።ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ ያነን በከረጢት ከቶ ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ 2 ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ 2 አይባልም።ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት 2 ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ 2 ዘውድ አይባልም" ይላል።
ሰለእውነት ይህንን ምሳሌ የመሰለልን 2ን ለማስረዳት ነው ወይስ 3ን ለማስረዳት? ልብ በሉ መወለድ ግብር ነው መለበስም ግብር ነው። መወዳደር መነጻጸር የሚችሉት እነዚህ ነገሮች ናቸው። ተለባሹ ከተወላዲው ጋር በሌላ በኩል መነጻጻር መወዳደር ይችላሉ። ነገር ግን ተወላዲውን ከመለበስ ጋር መወለድንም ከተለባሹ(ልብሱ) ጋር ማነጻጸርም ሆነ ማወዳደር ግን አይቻልም። የጸሐፊውን አለመማር የምንረዳው እዚህ ጋር ነው። አስተውሉ ጸሐፊው "መምህር" ገብረመድኅን እንዳለው ያነጻጸረው መለበስን ከተወላዲ ጋር ነው። ልብስን ደግሞ ከመወለድ ጋር ማለት ነው። በእውነት ይህንን ምሳሌ እንኳን ምሥጢርን የተማረ ቀርቶ ያልተማረ ራሱ አማርኛ በመቻሉ ብቻ የሚረዳው ነገር እኮ ነው። መወለዱን ወይም ስንት ጊዜ ተወለደ ለሚለው አቻ የሚሆነው ስንት ጊዜ ተለበሰ የሚለው እንጅ ስንት ልብስ ነው የሚል መሆን የለበትም። ስንት ልብስ ነው ለሚለው አቻ ስንት ልጅ ነው የሚለው መሆን አለበት። ስለዚህ አንዱ ወልድ እምቅድመዓለም ከአብ በመለኮት ተወለደ ካለ በኋላ ዳግመኛ በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ብሎ እነዚህን አንድ ልደት ብሎ ይቆጥራል። የዞረበት ጸሐፊ ነው እንጅ እነዚህ በምን አቆጣጠር ነው አንድ የሚባሉት። በእርግጥ ተወላዲው ራሱ ነው ማለት አንድ ነው የተወለደው ግን ሁለት ጊዜ ነው። የአዲሱ ሸማ ምሳሌ ይህንን በሚገባ ያስረዳናል። ሸማው አንድ ነው ነገር ግን አንድ ጊዜም ከዛም በላይ መልበስ ይቻላል። ታዲያ ልብሱ አንድ ነው ብለን ሽህ ጊዜ የለበስነውን ልብስ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የለበስነው ብለን ብንናገር ሰውስ አይስቅብንም እንዴ? በእውነት የሰው ሳቅ ታየኝ ፍርስ እኮ ነው የሚልብን።
ሁለተኛው ምሳሌ የዘውዱ ጉዳይ ደግሞ በጣም የማይገባ የደናቁርት ምሳሌ ነው። የሚነግሡት ነገሥታት ከተወላዲው  ጋር የሚነጻጸሩ ናቸው።  በዘውዱ 2 ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ስንት ነገሥታት ነገሡ ነው የምንለው? ወይስ ደግሞ ዘውዱ ስላልተቀየረ አንድ ዘውድ ስለሆነ በዚያ ዘውድ የሚነግሡ ነገሥታት ሁሉ አንድ ናቸው ሲባል ሊኖር ነው። አረ ምን ነካህ ገብረመድኅን እንዳለው በእርግጥ መንፈስ ቅዱስ ፊትህን ጸፍቶ ያናገረህ እጅህን ጎትቶ ያጻፈህ ይመስለኛል። ያ ባይሆንማ ሁለቱን አንድ ለማለት ይህንን ምሳሌ ባላደረግኸውም ነበር። የዚህኛው ምሳሌ ደግሞ ተወላዲው የተለያየ እንደሆነ ያስረዳል። ተወላዲው ማለት ነገሥታቱ ማለት ናቸው። ስንት ነገሥታት ናቸው የነገሡበት ለሚለው አቻ የሚሆነው ስንት ልጆች ናቸው የተወለዱበት የሚል ነው። ዘውዱ ደግሞ ከ ልደቱ ጋር አቻ ይሆናል። በአንድ ዘውድ 2 ሦስት እንደነገሡበት ሁሉ በአንዱ ልደት ሁለት ሦስት ልጆች ተወልደውበታል ያሰኛል። ስለዚህ ዘውዱ አንድ ቢሆንም ብዙ ነገሥታት እንዲነግሡበት ሁሉ ልደቱም አንድ ቢባልም ቅሉ ብዙ ልጆች ይወለዱበታል እንደማለት ነው። ስለዚህ ይህ ያስረዳል የተባለው ምሳሌ የሚያስረዳው ነገር ሁለት የሆነውን አንድ እንድንል የማያደርገን ስለሆነ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ባይ መናፍቃን የጌታን ልደት ከ2 ወደ 3 ከፍ ማድረጋቸው ግርምትን ሳይፈጥር አልቀረም። እኛ ግን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ልደቱን ሁለት እንላለን። ቅድመዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደው አንድ ልደት  ድኅረዓለም ያለአባት በተዋሕዶ  ከድንግል  ማርያም የተወለደው ልደት ሁለት ልደት ማለት ነው። እነርሱ ሳይገባቸው  በመቅረቱ የተነሣ የሚጠቅሱት አባጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ምእራፍ 3 ቁጥር 46 ላይ የሚናገረውን የተዋሕዶ ትርጉም ነው። ከተዋሕዶ በኋላ ይህ የመለኮት ነው ይህ ደግሞ የትስብእት ነው ማለት እንዳይገባ መወለዱም በአብ ፈቃድ ብቻ እንዳልሆነ በራሱም  በመንፈስቅዱስም ፈቃድ እንደሆነ ሲያመሰጥር የተናገረውን ለ3ኛ ልደት ምሳሌ ይጠቅሱታል። አባጊዮርጊስ የሚለው ድንግል ማርያም የራሷ በሆነ ሥጋ የራሷ ያልሆነውን መለኮት ወለደችው። አብም የራሱ በሆነ መለኮት የራሱ ያልሆነውን ሥጋ ወለደው ይላል። ይህንን ይዘው ነው እንግዲህ አብም በማኅጸነማርያም በሥጋ ወልዶታል የሚሉት። መወለድ የወልድ የጥንት ግብር ነው ይሁን እንጅ በሥጋ ማርያም ለመገለጥ የሁሉም ፈቃድ ነው። ፍጹም ተዋሕዶን ሲያጠይቅ እኮ ነው በራሱ በሆነ መለኮት የራሱ ያልሆነውን ሥጋ ወለደው ማለቱ። ድንግልም መለኮትና ሥጋን ያዋሐደውን አምላክ ወለደችው ሥግው ቃል ወለደችልን ማለት ነው። መለኮትን ብቻ ያይደለ ሥጋን፤ ሥጋ ብቻ ያይደለ መለኮትን የያዘ ሥግው ቃልን ወለደች ማለት ነው። የአብንም እንዲሁ ነው የሚያስረዳን ከተዋሕዶ በኋላ መለያየት የሌለበትን ወልድ ቅድመዓለም ወለደው ሲል ነው። ይህን ስጽፍ ሞባይል ላይ ስለሆንኩ ብዙም መጻፍ አልቻልኩም እንጅ...

No comments:

Post a Comment