© መልካሙ በየነ
ሰኔ 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እንኳን ለጾመ ሐዋርያት በሰላም እና በፍቅር አደረሳችሁ አደረሰን!
ዛሬ ዛሬ ማንነታቸውን ይፋ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ትምህርታቸውንም ከኩሽና ቤት ወደ አደባባይ አውጥተውታል፡፡ በግልጽ ማስተማር መከራከር ጀምረዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን መሳደብ መንቀፍ ጀምረዋል፡፡ መናፍቃኑ!
እነዚህን ልዩ የሚያደርጋቸው በቤተክርስቲያናችን ጥላ ሥር ተጠልለው ከበላነው በልተው ከጠጣነው ጠጥተው እኛ በሠራነው ሥርዓት ተሠርተው ለእኛ በተሾመልን ጳጳስ ደቁነው ቀስሰው ጰጵሰው የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በብዛት ሰፍረው የሚገኙት ደግሞ በጎጃም ጥቂት አካባቢዎች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አስተምህሯቸው በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ ተከታዮቹም የእናት እና የአባቴ እምነት ነው ብለው ክርር ከማለት ባለፈ ምሥጢራትን አያውቁም ነበር፡፡ የየዋሃኑም መከራከሪያ ሆኖ የቆየው የጌታችን የልደት በዓል ቀን በ28 እና በ29 ይከበራል ወይስ ደግሞ በ29 ብቻ ይከበራል የሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ስለነበር ለብዙዎቹ ልዩነት ያለን በ4 ዓመት አንድ ቀን ብቻ ይመስላቸው ነበር፡፡ ስለአጽዋማት የሚያውቁት ደግሞ በጾመ ነቢያት እና በጾመ ሐዋርያት መግቢያ ላይ ብቻ ያለ ልዩነት አድርገው ይቆጥሩት ስለነበር በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚፈጠር የአጿጿም ችግር ይመስላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሊደበቅ የማይችል በምንም በማንም ሊሸፈንና ሊከለል የማይችል አደባባይ ላይ የወጣ ምንፍቅና ቅ--ብ---አ---ት፡፡
ዛሬ ላይ በልደት በዓልና በአጽዋማት መግቢያ ላይ የምንከራከርብት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ አድርጉ ፈጽሙ በተባልንበት ቀን የምናደርጋቸው በተከለከልንባቸው ቀናት ደግሞ የምንቆጠብባቸው የምንታቀብባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ እንድናደርግ ወይም እንዳናደርግ ቤተክርስቲያናችን ስልጣንና ኃላፊነት የሰጠችው አካል አለ እርሱም ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ልደትን በታህሳስ 28 ማክበራችን አያጣላንም ምክንያቱም እንኳን ምሥጢር እያለው ይቅርና መስከረም 1 ወይም ጥቅምት 30 ወይም ደግሞ ሰኔ 24 ወይም ሚያዝያ 7 ወይም ደስ ያላችሁን ቀን መርጣችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ ብንባል ኖሮም እናደርገው ነበር እናከብረውም ነበር፡፡ ጌታችን በየዓመቱ የሚወለድ ሆኖ ነው እንዴ እያከበርነው ያለነው? አይደለም፡፡ የአጽዋማት መግቢያም እንዲሁ ነው፡፡ የነቢያት ጾም በህዳር 15 የሐዋርያት ጾም ደግሞ ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በነጋታው ሰኞ እንድንጀምር ሥርዓት ተሠራልን በዚያ ሥርዓት እንመራለን እንተዳደራለን፡፡ አለቀ ይህ ምንም አያከራክርም ምክንያቱም ቀኖና ስለሆነ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቀደሙ አባቶቻችን እና ከመጽሐፎቻቸው ጋር በማይጣላ መልኩ አድርገው በወሰኑልን ውሳኔ የምንፈጽመው ነው፡፡ እነዚህ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች የሚጠቅሱት ነገር አለ “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ወደ ኋላ ከተመለሰ ጥምቀት ግዝረት ለምን አንድ ቀን ወደኋላ አይመለሱም” የሚል ነው፡፡ የእነርሱ ደጋፊ የሆኑት ጳጳስም “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ቀንሶ በታህሳስ 28 ይከበር የምትሉ እናንተ ልደታችሁን ስታከብሩ አንድ ቀን ቀንሳችሁ ነውን? ታህሳስ 29 የተወለደ ሰው በዘመነ ዮሐንስ ልደቱን ታህሳስ 28 ያከብራልን?” ብለዋል፡፡ መልካም ነው! እኔ ግን ግርም ድንቅ የሚለኝ ነገር አለ፡፡ አሰቀድሜ እንደተናገርኩት ይህ የቀኖና ጉዳይ ነው ይህን መፍታት የሚችል ራሱን የቻለ አካል አለው፡፡ አይደለም ታህሳስ 28 ከ365ቱ ቀናት መካከል አንዱን ቀን መርጠው የጌታችን ልደት በዚህ ቀን ይከበር ብለው ካሉን ግዴታችን ነውና እናከብረዋለን፡፡ ምክንያቱም የጌታችን ስቅለት፤ ትንሣኤ እና ዕርገት በጥንተ ስቅለት፣ በጥንተ ትንሣኤ እና በጥንተ ዕርገት እያከበርናቸው ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የ2008 ዓ.ምን ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት ቀን አስቡት፡፡ ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት 27 ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት 8 ነው እኛ ግን ስቅለቱን ሚያዝያ 21 ትንሣኤውን ሚያዝያ 23 እንዲሁም ዕርገቱን ሰኔ 2 ቀን አከበርን ለምን? ቀኖና ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ በየዓመቱ እነዚህን በዓላት መቼ መቼ እንዳከበርናቸው ተመልከቱ፡፡ በየዓመቱ ይለያያሉ ዕለታቸው አይቀየርም እንጅ ቀናቸው ይቀያየራል፡፡ ታዲያ በአንድ የልደት ቀን አከባበር ላይ ከምንነታረክ ለምን እነዚህንስ አንከራከርባቸውም፡፡ ስለዚህ በልደት በዓል አከባበርና በአጽዋማት መግቢያ ላይ ምንም መከራከሪያ ልናነሣ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም እኛ ታዛዦች እንጅ አዛዦች አይደለንምና አድርጉ በተባልነው ቀን ማድረግ ብቻ ነው ሥራችን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ለቅብአት ምንፍቅና የመደበቂያ ካባዎች እንጅ መሠረታዊ ነጥቦች አይደሉም፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑም ማስተዋል የሚገባው ይህንን ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ጉዳያችን መሆን ያለበት አስተምህሮ ላይ ወይም ዶግማ ላይ ነው፡፡ ዶግማን ማሻሻል የሚችል አካል የለም፡፡ ምክንያቱም ስታምን የምትቆይበት ካላመንክ ደግሞ ተለይተህ የምትወጣበት መሠረተ እምነት ነውና፡፡ ለሲኖዶስ ቀኖናን የማሻሻልም የመለወጥም የመቀየርም ስልጣን አለው ለዶግማ ግን ማንም ቅንጣት ታህል የማሻሻል የመለወጥ የመቀየር ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ነጥቦቻችን መከራከሪያዎቻችን መሆን ያለባቸው አስተምህሮ ላይ ነው፡፡ አስተምህሯቸውን ደግሞ በራሳቸው ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እናገኘዋለን፡፡ ያ አስተምህሮ በእውነት እኛ የተዋሕዶ አማኞች የምንከተለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ወደፊት በዝርዝር የምንመለከተው ስለሚሆን ከላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዮች ላይ እንደመከራከሪያ አድርጋችሁ ጊዜ እንዳታጠፉ እጠይቃለሁ፡፡ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆችም ሳትቸኩሉ በማስተዋል ለስድብ ሳትፈጥኑ ራሳችሁን በመመርመር ስህተቶቻችንን እየተማማርን እንድንቀጥል አሳስባችኋለሁ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment