Friday, June 10, 2016

“ለቅድስና ያልታደለ ኅሊና ለኃጢአት ያጎበድዳል”

© መልካሙ በየነ
ግንቦት 9/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ፣

ዘመናችን ዘመነ መከራ ዘመናችን ዘመነ ሰቆቃ ነው፡፡ ለመዳን መሰናክሉ የበዛበት ለመጥፋት ደግሞ ሰፊ ጥርጊያ የተዘጋጀበት ዘመን፡፡ ተኩላዎች ከበጎች ጋር መስለው እና ተመሳስለው ስለሚኖሩ በጎች የተኩላዎችን ተኩላዎችም የበጎችን ቋንቋ የሚናገሩበት፣ አለባበስ የሚለብሱበት፣ አነጋገር የሚናገሩበት፣ አረማመድ የሚራመዱበት ዘመን፡፡ ይህ ዘመን ከሌላው ዘመን ሁሉ የሚያስጨንቅ ዘመን ነው ምክንያቱም በጎ ኅሊናችንን ጠላታችን ሰውሮብን መጥፎ ኅሊናችንን አጉልቶብናልና፡፡ ለቅድስና ከመጣር ይልቅ ለኃጢአት መሮጥን እንመርጣለን፡፡ ወንጌልን ከመማር ከማስተማር ይልቅ ተረት ተረት ስናወራ ስንሰማ እንውላለን፡፡ ትንንሽ ባቢሎኖችን በየቤታችን መሥርተናል፡፡ እነዚህ ባቢሎኖች የሚመሠረቱት ደግሞ በቤት አባወራዎች እና እመወራዎች ብቻ አይደለም ስልጣነ ክህነትን በተቀበሉት ለቤተክርስቲያን ጠባቂ ሆነው በተሸሙት ጭምር ነው እንጅ፡፡ ሁላችንም በተለይ ደግሞ መምህራን እኔ ልመክራችሁ የምችል ባልሆንም ተገድጀም ቢሆን እናገራለሁ መንፈሳዊውን ትምህርት ለመቅሰም ጉባኤ ለጉባኤ የተንከራተታችሁት፣ ዶክተር ማስተር ዲግሪ ዲፕሎማ ወዘተ ለመባል በየመንፈሳዊ ኮሌጆች ደጅ የጠናችሁት፣ ህዝቡን ለማስተማር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ለመመለስ ወንጌልን ያነገባችሁት፣ “ሑሩ ወመሀሩ” ተብላችሁ ዞራችሁ ታስተምሩ ዘንድ አደራ የተቀበላችሁት ለማን እንደሆነ ለምን እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋችኋል፡፡ ምክንያቱም አምላክ በእኛ ላይ አድሮ የሚሠራውን ሥራ እኛ ማዎቅ አንችልምና፡፡

የሁልጊዜ ጸሎታችን ሊሆን የሚገባው “አምላክ ሆይ ሳጥናኤል ከመላእክት ወገን ተቆጥሮ ነበር እንዲያውም አሐዜ መንጦላእት አቅራቤ ስብሐት ሊቀ መላእክት ነበረ ነገር ግን ወደቀ፤ አምላክ ሆይ ይሁዳ ከ12ቱ ደቀመዛሙርትህ ቁጥር ገብቶ ነበር ነገር ግን አንተን በ30 ብር ሸጠህ፣ አምላክ ሆይ አርዮስ ከሊቃውንት ቁጥር ገብቶ ተቆጥሮ ነበር ነገር ግን አንተን ፍጡር እናትህንም ወላዲተ ሰብእ ብሎ ካደ ስለዚህ ጅማሬን ሳይሆን ፍጻሜን ስጠኝ፡፡ ከምእመናን ጋር እቆጠር ዘንድ፣ ከዲያቆናት ጋር እቆጠር ዘንድ፣ ከቀሳውስት ጋር እቆጠር ዘንድ፤ ከመምህራን ጋር እቆጠር ዘንድ.፤ ከሊቃውን ጋር እቆጠር ዘንድ፣ ከጳጳሳት ጋር እቆጠር ዘንድ አንተ እንደረዳኸኝ ሁሉ ከዚህ ከተቆጠርኹበት ምድቤ አትለየኝ” ልንል ይገባናል፡፡ ምክንያቱም አሁን ዛሬ ላይ ምእመን፣ ዲያቆን፣ ቄስ፣ ጳጳስ፣ መምህር፣ ሊቅ ብሆን ነገ ግን ይህንን ስለመሆኔ ምንም ዋስትና የለኝምና፡፡

አሁን እየተቸገርን ያለነው በዚህ ጉዳይ ነው፡፡ የኔ ቢጤው ለስሙ ዲቁና ያመጣና በቤተመቅደስ ብጥብጥ ይጀምራል፡፡ “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይቀርም” እንዲሉ ቄስ ለመባል መስቀሉን ለመጨበጥ ይፈጥንና መስቀሉን ይጨብጣ ስሙን ይቀበላል ከዚያ በኋላ ማሰር መገዘት ብቻ እንጅ መፍታት የማይችል ይሆናል፡፡ የሚሰጠው ስልጣን ማሰርም መፍታትም እንዲችል ነበር ነገር ግን ዓላማው ሰውን ማሰር መገዘት ብቻ ስለነበር መፍታትን ይዘነጋል፡፡ በምንኩስናው ዓለምም እንዲሁ መስሎ ለማደር ብቻ ከእኔ በላይ ማን አለ እኔ የምላችሁን ብቻ አድርጉ ብሎ ለማስፈራራት እስከ ጵጵስና ማዕረግ ድረስ ወንበሩን መረከብ ይሻሉ፡፡ በጣም ከባድ አስጨናቂ ዘመን ማለት ዓላዊ ንጉሥ ከሐዲ ጳጳስ አንድ ዘመን ሲገናኙ ነው፡፡ ንጉሡ ብቻ ዓላዊ ቢሆን ጳጳሱ ምእመኑን በትምህርት ያበረታል ለሰማእትነት ያበቃል፡፡ ጳጳሱም ከሐዲ ከሆነ ግን በትምህርት የሚጸና በእምነት የሚቆም ለሰማእትነት የሚበቃ ክርስቲያን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ዛሬ በሀሜት ተላልቀናል፡፡ ጳጳሱ እንዲህ ናቸው አሉ ካህኑ እንዲህ ናቸው አሉ ዲያቆኑ እንዲህ ነው አሉ እየተባባልን ነው፡፡ በእርግጥ ከሀሜት ያለፈ በተግባር የተረጋገጠ በንግግራቸው የተመሰከረ ማስረጃ ያለባቸውም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በጎ ኅሊና ስለሌላቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የአስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የእምነት ድሆችም ናቸው፡፡

በእርግጥ እኛም ላይ ችግር አለ፡፡ አባቶች በተለይ ደግሞ አንዳንድ ጳጳሳት የሚያስተምሩት የሚናገሩት ሁሉ ትክክል የሚመስላቸው አሉ፡፡ “አቡነ እገሌ እንዲህ አደረጉ” ተብሎ መረጃው ሲቀርብላቸው አባቶች ምንም ቢያጠፉ እንዲህ አደረጉ መባል የለባቸውም ብለን እንሞግታለን፡፡ በዚያ ቢሆንማ ይሁዳ አይቀድማቸውም ነበር በዚያ ቢሆንማ አርዮስ አይቀድማቸውም ነበር በዚያ ቢሆንማ ሳጥናኤል አይልቃቸውም ነበር እንዴ፡፡ እኛ የምንነጋገረው ስለእምነታችን ከሆነ በእምነታችን መቀለድ አይገባንም፡፡ እምነታችንን የተመሠረተችው ደግሞ በክርስቶስ ደም ነው፡፡ ስለዚህ ይች ቤተክርስቲን ቅድስት ክብርት ንጽሕት ናት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የወንበዴዎች ዋሻ ስትሆን እየተመለከትን ዝም ማለት ያለብን አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ አምላክ ዝም ያለውን እኛ ምን አገባን የምንልም የዋሐን አለን፡፡ አምላክ የእኛን ጽናትና ብርታት ይመዝናል ይለካል በመጀመሪያ አምላክ ዝም እንዳይላቸው እኛ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ለጆሮ የሚቀፍ ንግሮችን ዐውደምሕረቱ ላይ ሲነገሩ እንሰማለን፣ ጳጳሱ ቆመው እኔ ካልኩት ውጭ አታድርጉ እያሉ ከሥርዓ ውጭ እንድንሆን ያስገድዱናል፡፡ እኔ በጣም የሚገርመኝ አቡነ ማርቆስ የተናገሩት አንድ ንግግር ነው፡፡ በእርግጠኝነት ይህንን እሳቸው ተናግረውታል ብላችሁ ላታምኑ ትችላላችሁ፡፡ የሚያውቃቸው ሰው ግን አንተ ይች እንዴት ትገርምሃለች እንደሚል አልጠራጠርም፡፡ በታላቁ ዲማ ገዳም የቅዳሴ ጸበል የሚጠጣው የቆረበ ሰው ብቻ ነው፡፡ ማንም ሰው ካልቆረበ የቅዳሴ ጸበል አይሰጠውም፡፡ የቅዳሴ ጸበል ክብር አለው ትንሽም ጠብ አትደረግም፡፡ ይህንን ግን አይፈልጉም አባ ማርቆስ ከዚያ ምን አደረጉ የቅዳሴውን ጸበል መድረኩ ላይ ቆመው ህዝቡን ይረጩት ጀመሩ፡፡ ዲማ እንኳ ጸበል እንዲህ መሬት ላይ ሊረጭ ቀርቶ እንደነገርኳችሁ ያልቆረበ ሰው አይቀምሰውም፡፡ ከዚያ ለምን የቅዳሴ ጸበል ትረጩናላችሁ ብለው አንዳንዶች ይጠይቃሉ፡፡ አባ ምን አሉ “ታዲያ አረቂ ልርጫችሁ ወይ”፡፡ በእውነት ይህ ለዚያ ምእመን መልስ ነው ዐወደ ምሕረት ላይ የሚነገር ንግግር ነው አይደለም፡፡ በእርግጥ ይህን ከተናገሩት ከርመዋል፡፡ ብቻ ኅሊናችን በጎ ማሰብ ቅድስና ማሰብ ካቆመ ነቅአ ኃጢአት እንደሚሆን ማስተዋል ያስፈልገናል፡፡

አንድ ደቀመዝሙር ነበር መምህሩ ራሳቸው በሕይወት ሳሉ “ይህ እኮ ይሁዳ ነው” ይሉት የነበረ፡፡ ከዚያም እንደማንኛውም ደቀመዝሙር አስተማሩት ለቁም ነገር አበቁት፡፡ መምህሩ አረፍተ ዘመን ገደባቸው እና እንደአባቶቻችን እሳቸውም አንቀላፉ ከዚያም በወንበራቸው እሳቸውን ይተካል ተብሎ በመምህሩ ወንበር ላይ ይህን ደቀመዝሙር በመምህርነት አስቀመጡት፡፡ በመንበራቸው ሲቀመጥ “አይገባኝም ብሎ እያለቀሰ ነበር” ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ነገር ተገልብጦ ታሪክ ተቀይሮ የመምህሩን ሚስት ተኛት፡፡ በዚህ የተነሣ ዲማ ላይ ታላቅ ማዕበል ተፈጠረ፡፡ ይህን የሚያደርገው ሰው የዲማ አካባቢ ተወላጅ ከመሆኑ የተነሣ የእርሱ ወገን የሆኑት ብጥብጥ አስነሡ፡፡ ነገር ግን ከላይ እስከታች ያሉት በሙሉ ከመንበሩ እንዲነሣ ፈረዱና ተነሥቶ ሌላ ከተማ  በአቡነ ማርቆስ ረዳትነት ሥራ ተሰጠው፡፡ የዲማ ሰው የዲማ ሊቃውንት አብረውት የተማሩት ሊቃውንት ያ ሰው ዲማ እንዳይደርስ አወገዙት፡፡ እዚያ ከሄደ ግን ሊፈጠር የሚችለው ብጥብጥ ከባድ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል ነገር ግን ዛሬ የዲማን ብጥብጥ የሚሹት አቡነ ማርቆስ ደብዳቤ ጽፈው ዲማ መምህር እንዲሆን ሾመውት አረፉ፡፡ ምክንያቱም “ለቅድስና ያልታደለ ኅሊና ለኃጢአት ያጎበድዳል” እና የኃጢአት ልምምድ መጀመራቸውን እያሳዩን ነው፡፡ ግነ ነገ ዲማ ላይ ምን ይፈጠር ይሆን??
አምላክ ሆይ ለቤተክርስቲያናችን ፍቅርን አንድነትን አድል፡፡

No comments:

Post a Comment