Thursday, May 11, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል ፪



© መልካሙ በየነ

ግንቦት 4/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተጽሕፈ እም አሐዱ ሊቅ ኢትዮጵያዊ ኅሩይ ወመፈክራዊ
ጌታው አለቃ ኅሩይ


መቅድም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሕዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ::
ንባብ :- ንጽሕፍ መቅድመ አሠሩ ወፍኖቱ ለእግዚአብሔር በረድኤት አምላካዊት ከሃሊተ ኩሉ፣ ክሂሎታኒ አኮ ባሕቲቱ በአበው ለባውያን ወማእምራን፣ አላ ዓዲ በሕፃናትኒ የዋሃን፣ በከመ ቃሉ ለእግዚእነ “አእኩተከ አባ እግዚአ ሰማይ ወምድር፣ እስመ ኀባእኮ ለዝንቱ እማእምራን ወእምጠቢባን፣ ወከሠትኮ ለሕፃናት እስመ ከማሁ ኮነ ሥምረትከ በቅድሜከ”
ትርጉም :- ከአምላክ በምትገኝ፣ ሁሉን ማድረግ በሚቻላት ረድኤት የእግዚአብሔርን የጎዳናውንና የፍለጋውን መቅድም እንጽፋለን:: ችሎታዋም በዐዋቆችና በልበኞች ብቻ አድራ አይደለም፣ አላዋቆች በሆኑ ሕፃናትም አድራ ነው እንጂ:: ጌታችን እንዲህ ብሎ እንደተናገረ “አመሰግንሃለሁ አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ፣ ይህን ከዐዋቆችና ከልበኞች ሰውረህ ለሕፃናት ገልጠኸዋልና፣ እንዲህ በፊትህ ፈቃድህ ስለሆነ” ማቴ ፲፩÷፳፭-፳፮
ንባብ :- በእንተ ዝንቱ ፈቀድነ ንጽሐፍ ኀዳጠ እምነ ብዙኅ፣ በእንተ እማሬሃ ለይእቲ ፍኖት ሠናይት:: ፍኖትሂ ሠናይት ሃይማኖት ይእቲ ብሂለ አሐዱ መለኮት ወሠለስቱ አካላት፣ ባቲ ያጽንዐነ እግዚአብሔር ሎቱ ስብሐት እስከ እስትንፋስ ደሃሪት ለዓለመ ዓለም አሜን::

ትርጓሜ:- ለሕፃናተ አእምሮ ምሥጢርን የሚገልጽ ስለሆነ የዚችን ቅን ጎዳና ነገር ለማስረዳት፣ ከብዙ በጥቂቱ ልንጽፍ ወደድነ:: መልካም ጎዳና የተባለችም ሃይማኖት ናት:: ይህችውም በአንድ መለኮት፣ ሦስት አካላት ብሎ ማመን ናት:: እስከ ጊዜ ሞት ድረስ በርስዋ ያጽናን እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና ለዘለዓለም አሜን:: ከጌታችን ከኢየሱስ የተገኘች ሃይማኖት አንዲት ነበረች:: ለዚኸውም ማስረጃ ሐዋርያው ዻውሎስ “ሃይማኖት አንዲት ናት” ብሎ ተናግሮአል:: ኤፌሶን ፬÷፭ ነገር ግን የሰው ጥንተ ጠላቱ ሰይጣን በአንዳንድ ሰዎች እያደረ በዓላማው ስሕተት የሃይማኖት መለያየት መጣ:: ማስረጃ ጌታችን በወንጌል
ንባብ :- “ወእንዘ ይነውሙ ሰብኡ መጽአ ጸላኢ ወዘርዐ ክርዳደ ማዕከለ ሥርናይ ወኀለፈ”
ትርጉም :- “ሰዎች በተኙ ጊዜ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶበት ሄደ” እንዳለ ማቴ ፲፫÷፳፭
ንባብ :- “ፀጋሰ ኢትትወሀብ ዘእንበለ ለትሑታን ወፈድፋደሰ ለምኑናን ወለየዋሃን”
ትርጉም:- “የዕውቀት ሀብት ለተዋረዱ፣ ይልቁንም ለተናቁና፣ ቅንነት ላላቸው ነው እንጂ፣ ለትዕቢተኞች አትሰጥም” ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 3 ያለውን በመዘንጋቱ በፍቅርና በትሕትና ፀንቶ ወንድም ከወንድም ጋራ ሐሳብ ለሐሳብ እየተግባባ፣ በስምምነት ሃይማኖትን ወደጥንተ ቦታዋ፣ ወደ አንድነት በመመለስ ፈንታ፣ እኔ ያልሁት ይሁን ማለትን ስለወደደና፣ መለያየት ስለተስፋፋ፣ መነቃቀፍ ያመጣው የወገን ስም መለያየት ተፈጠረ:: ይልቁንም ወላዲ መለኮት ተወላዲ መለኮት ሠራፂ መለኮት የማለትና፣ መለኮትንም መንግሥትንም በአካል ሦስት የማለት እንግዳ ትምህርት ስለመጣ፣ ይህንም አንዳንድ ሰዎች አክብረው ስለተቀበሉት፣ አንዲት የኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከብዙ ከፋፈላት:: የመጣበትም ምክንያት እንዲህ ነው የኢትዮጵያ ሊቃውንት ወንጌላዊ “ቃል ሥጋ ኮነ” ዮሐንስ ፩÷፲፬ ያለውን ንባብ ከምሥጢር ተመልክተው፣ መለኮትና ትስብእት ተዋሕደው አንድ አካልና አንድ ባሕርይ በመሆናቸው፣ ክርስቶስ የአምላክነትንም የሰውነትንም ሥራ በአንድ ፈቃድ ይሠራል ብለው፣ እምነታቸውን ስለገለጡና ስላስተማሩ፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች:- “ባሕርይ ተዋሐደ ከተባለ፣ ባሕርየ ሥላሴ አንድ ነውና፣ ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ” ያሰኛል ብለው ሲከራከሩ፣ ምሥጢሩን ያላስተዋሉ ሰዎች “መለኮት በአካል ሦስት” በማለትና “ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሰራጺ መለኮት” በማለት፣ የሐዲስ ትምህርት መንገድን አውጥተዋል:: ነገር ግን ይህ የሐዲስ ትምህርት መንገድ ዮሐንስ ተዐቃቢ የሔደበት ያልቀና መንገድ ነው:: ስለዚህ አስተዋዮች በቅን አስተያየት ተመልክተው በዚህ ባልቀና መንገድ ከመሄድ እንዲጠበቁበትና፣ “አንድ መለኮት በሦስት አካላት አለ” ወደ ማለት  ቅን ጎዳና እግረ ልቦናቸውን እንዲያቃኑበት ይችን ትንሽ መጽሐፍ እንጽፋለን:: የዚችም መጽሐፍ ጥርጊያ ጎዳና “በአካል ሦስት በመለኮት አንድ አሰኝቶ፣ መለኮት አንድ ከሆነ፣ ሦስቱ ሰው ሆኑ ያሰኛል ብሎ ከመፍራት ጠብቆ “ከሦስት አካላት አንድ አካል ወልድ ብቻ ሰው ሆነ” ወደ ማለት ያለችግር በቀጥታ የሚያደርስ ስለሆነ ስሟ “ፍኖተ
እግዚአብሔር” ተባለ::
አሠረ ፍኖት
ንባብ :- “ኩሉ ማዕመቅ የምላዕ፣ ወኩሉ ደብር ወአውግር ይተሐት ወይኩን መብዕስ መጽያህተ ርቱዐ፣ ወይዕሪ ፍኖት መብዕስ፣ ወይርአይ ኲሉ ዘነፍስ አድኅኖቶ ለእግዚአብሔር”
ትርጓሜ :- “ዝቅ ያለው ሁሉ ከፍ ይበል፣ ተራራው ኮረብታው ሁሉ ዝቅ ይበል:: ጠማማውም ይቅና:: አቀበቱም ሜዳ ይሁን:: ሥጋን የለበሰ ሁሉም የእግዚአብሔርን ትድግናውን ይይ” ኢሳ ፵÷፴፭ “ማዕምቅ እንደ ሰባልዮስ አንድ ገጽ የሚል አንድ ገጽ ማለቱን ትቶ ባሕርየ መለኮት
አንድ በሚያደርጋቸው በሦስቱ አካላትና በሦስቱ ገጻት ይመን”
ማስረጃ :- ዮሐንስ ዘአንጾኪያ “ንትአመን በሠለስቱ አካላት ወበሠለስቱ ገጻት፣ እንተ አሐዱ ባሕርየ መለኮት” ፍቹ “በሦስት አካላት በሦስት ገጾች አንድ ባሕርይ መለኮት ባለው እንታመናለን” ማለት ነው፡፡ ብሏልና::
ደብር (ተራራ)
እንደ ዮሐንስ ተዐቃቢ ዘጠኝ መለኮት ወይም ሦስት አማልክት ዘጠኝ አካላት ከማለት የሚያደርስ መለኮትና መንግሥት በአካል ሦስት የማለት እምነትን የያዘ ይህን አርቆ ሥላሴ በአካል ሦስት በመለኮት አንድ፣ መንግሥታቸውም በአካል ከሦስት የማትከፈል አንዲት ብቻ እንደሆነች ይመን::
ማስረጃ:- የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ዲዮናስዮስ “ወኢንበውእ ውስተ ከፊለ መለኮት ወመንግሥት አላ ንብል አሐዱ መለኮት ወአሐዱ መንግሥት ይትወሐዱ በመለኮት ወይሤለሱ በአካላት” መለኮትን ወደ መክፈል አንገባም:: መንግሥትንም አንከፍልም አንድ መለኮት አንድ መንግሥት እንላለን እንጅ በመለኮት አንድ ናቸው በአካል ሦስት ናቸው ማለት ነው::(ሃይማኖተ አበው) እንዳለ::
ሠለስቱ ምዕትም:- “ሥሉስ ፍጹም በአሐዱ መለኮት እስከ ለዓለም አሐዱ እግዚእ ወአሐቲ መንግሥት እንተ ኢትትከፈል ወኢትትፋለስ” “ፍጹም ሦስትነትን በአንድ መለኮት፣ እስከ ዘለዓለም አንድ ጌታ፣ አንዲት መንግሥት የማትከፈል እና የማትፋለስ  ማለት ነው። (ሃይማኖተ አበው)  ብለዋል::
ፍኖት መብዕስ (ያልቀና መንገድ)
ወላዲ መለኮት ተወላዲ መለኮት ሠራጺ መለኮት የማለት ትምህርትም አንድ መለኮት በሦስት አካላት ሕልው ሆኖ ሦስቱን አካላት ያገናዝባል በማለት የቀና ይሁን የተካከለም::
ማስረጃ ንባብ :- ዮሐንስ ዘአንጾኪያ “ወበሠለስቲሆሙ ሀሎ ፩ መለኮት” በሦስቱ አንድ መለኮት አለ ማለት ነው::(ሃይማኖተ አበው) ብሎአል:: “ይርአይ ኩሉ ዘነፍስ” በነፍስ ዕውቀት ዐዋቂ ሆኖ የሚኖር ሁሉ ወንጌላዊት ሃይማኖትን ለመግለጽ እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት በሊቃውንት በየአንቀጹ ያናገረው የአካላትን ሦስትነት፣ የመለኮትንና የመንግሥትንም አንድነት የሚያስረዳውን ኃይለ ቃል “ፍኖተ እግዚአብሔር” በተባለች በዚች ትንሽ መጽሐፍ ለተመልካች በቅርብ እንዲገኝለት በመደረጉ፣ በቅን ኅሊና የሚመለከታት ከብዙ ስሕተት መዳኑን ይወቅ:: ተመልካችዋም ቃሏን ተመልክቶ ተቀብሎ ከስሕተት የሚድንበትንና የዘለዓለም ድኅነት የሚያገኝበት ጊዜ እነሆ ከሞት በፊት ዛሬ ነው::
ማስረጃ :- ቅዱስ ዻውሎስ “በዕለት ኅሪት ሰማዕኩከ ወበዕለተ መድኀኒት ረዳዕኩከ” በተመረጠች ቃል ሰማሁህ በዕለተ ድኅነት እረዳሁህ ማለት ነው:: ያለውን የኢሳይያስን ትንቢት ከጠቀሰበት:: ኢሳ ፵፱÷፰ ንባብ :- “ወናሁ ይእዜ ዕለት ኅሪት፣ ወናሁ ዮም ዕለተ አድኅኖት” ትርጓሜ :- “የተመረጠች ቀን ድኅነት የሚገኝባትም ጊዜ ዛሬ ናት'' እንዳለ:: ፪ኛ ቆሮ ፯÷፪ የዘለዓለም ድኅነት የተባለችም፣ ዕሪናቸው በአካል፣ መመሳሰላቸው በኅብረ መልክዕ፣ ህልውናቸው በእኩልነት፣ ተዋሕዶዋቸው በመለኮት የሚነገር ሥላሴ፣ በአብ ልብነት ለባውያን፣ በወልድ ቃልነት ነባብያን፣ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሕያዋን መሆናቸውን አውቆ ተረድቶ አንድ የባሕርይ አምለክ ብሎ ማመን ናት::
ማስረጃ :- ባለቤቱ ጌታችን ንባብ :- “አባ በጽሐ ጊዜሁ ከመ ትሰብሆ ለወልድከ፣ ወከመ ወልድከኒ ይሰብሕከ፣ በከመ አኮነንኮ ላዕለ ኩሉ ዘሥጋ ወነፍስ ከመ የሀቦሙ ሕይወተ ዘለዓለም ለኩሎሙ እለ ወሀብካሁ ወዛቲ ይእቲ ሕይወት ዘለዓለም ከመ ያእምሩከ ለከ ለአሐዱ ዘበአማን አምላክ ወለዘፈነውኮ ኢየሱስ ክርስቶስ” ብሎአል:: ትርጓሜ :- “አባት ሆይ ልጅህን ትገልጸው ዘንድ፣ ልጅህም አንተን ይገልጽህ ዘንድ፣ የምትገልጽበት ጊዜውም ደረሰ፣ ለሰጠኸው ሁሉ ዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸው ዘንድ፣ በሥጋዊና በነፍሳዊ ሁሉ ላይ እንዳሠለጠንኸው መጠን፣ የዘለዓለም ሕይወት ይች ናት:: ያውቁህ ዘንድ አንተ ብቻህ /እውነተኛ/ የባሕርይ አምላክ እንደሆንህ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን'' ብሏልና:: ዮሐ ፲፯÷፩-፫ የባሕርይ አምላክ እንደሆነም የሚያውቁበትን ዕውቀት የሚገልጽ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስረዳ:- ንባብ:- “ጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ ዘይፌኑ አብ በስምየ፣ ውእቱ ይሜረክሙ ኩሎ፣ ወያዜክረክሙ ኩሎ ዘነገርኩክሙ አነ” ትርጓሜ:- “አብ በእኔ ስም የሚሰድላችሁ የሚያፀና መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ያስተምራችኋል ይገልጽላችኋል/ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል'' ብሏል:: ዮሐ ፲፬÷፮ በማቴዎስ ወንጌልም:- ንባብ:- “እስመ ኢኮንክሙ አንትሙ እለ ትትናገሩ አላ መንፈሱ ለአቡክሙ ውእቱ ይትናገር በላዕሌክሙ” ትርጓሜ:- “እናንተ የምትናገሩ አይደላችሁም ያባታችሁ መንፈስ በእናንተ አድሮ ይናገራል እንጂ'' ብሏል:: ማቴ ፲÷፳ ጳውሎስም:- ንባብ ፦ “ወአልቦ ዘይክል ብሂለ እግዚእ ኢየሱስ ዘእንበለ ዘመንፈስ ቅዱስ ላዕሌሁ” ትርጓሜ:- “መንፈስ ቅዱስ ካደረበት ሰው በቀር ኢየሱስ የባሕርይ አምላክ ነው የሚል የለም” ብሏል:: ፩ኛ ቆሮ ፲፪÷፫ ነገር ግን የበጎ ሃይማኖት የምሥጢሩን ፍለጋ ለሚከታተል ሰው በቅዱሳት መጻሕፍትና በሊቃውንት የተጻፈውን በጎ ትምህርት ይዞ ምሥጢሩን እንዲገልጽለት የአምላክ መሆን ይገባዋል እንጂ የመጻሕፍት ንባባቸውንና ምሥጢራቸውን አፍርሶ ስህተትን ሲያንጽ፣ አስተዋይ ልቦና ለሌላቸው ሰዎች የቀና መስሎ ወደሚታይ ክፉ ጠማማ ሃይማኖት በመሳብ መንፈስ ቅዱስን ማሳዘን አይገባም:: ማስረጃ:- ሐዋርያው ጳውሎስ:- ንባብ፦ “ወኢታምዕዎ ለመንፈስ ቅዱስ ዘቦቱ ዐተቡክሙ አመ ድኅንክሙ'' ትርጓሜ:- “ከክህደት በዳናችሁ ጊዜ የታተማችሁበትን መንፈስ ቅዱስን አታሳዝኑት” እንዳለ:: ኤፌ ፬÷፴ የሰው ኅሊናው ወደ በጎ ሃይማኖት ሳያስብ የሃይማኖት ምሥጢርን በመግለጽ የእግዚአብሔር ፀጋ ሰውን አትረዳውምና:: ማስረጃ:- ፊልክስዩስ “እምቅድመ ትጽንን ኅሊናሁ ለስብእ ለኂሩት ወለእከይ፣ ኢትረድኦ ወኢትርሕቅ እምኔሁ'' እንዳለ:: /ክፍል ፪ ተስእሎ ፲፬/ ትርጉም:- “ወደ በጎና ወደ ክፉ ሳይጸን በመካከል ሳለ /ፈዞ ማለት ነው/ አትረዳውም አትርቀውም” ብሎአል:: ስለዚህ አምላካዊ የሆነ የሃይማኖትን ምሥጢር ለመረዳት አምላካችን ወደ በጎ ሃይማኖት የሚሳብ በጎ ኅሊናን ይስጠን አሜን::
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

Wednesday, May 10, 2017

“ጳጳስ እያስተማረ አሁን እናንተ በስመ አብን ሳትሉ እምነት እናስተምር ይባላል”-- አቡነ ማርቆስ


 © መልካሙ በየነ
ግንቦት 2/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ብጹእ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የቤተክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ሥርጭት ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እነዚህን ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ያገኙት ደግሞ በተሐድሶ መናፍቃኑ ከፍተኛ እገዛ እና ጥረት እንደሆነ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ ሚያዝያ 30/2009 ዓ.ም የሐዋርያው የቅዱስ ማርቆስ የእረፍት መታሰቢያ በዓል ይከበራል፡፡ በእድሳት ምክንያት የዓመታት አገልግሎት ተቋርጦበት የነበረው መንበረ ጵጵስናቸው ደብረ ፀሐይ መልእልተ አድባር ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ምረቃ በ ሚያዝያ 28/2009 ዓ.ም ተፈጸመ፡፡ እርሳቸው ግን ህዝቡን በስፋት የሚያገኙበት ነውና ጉባዔውን ተጠቅመውበት አልፈዋል፡፡ በሚያዝያ 30/2009 ዓ.ም በሐዋርያው የእረፍት በዓል ላይ ካስተላለፉት መልእክት የተወሰነውን በቪዲዮ አስደግፌ እጽፍላችኋለሁ፡፡ ቪዲዮውን ግን ሁላችሁ ተመልከቱት፡፡
አቡኑ ብዙ ነገር ሲዝቱ ውለዋል ብዙ ነገር ሲያስፈራሩ ውለዋል እኔ ግን ከመኸል ቀንጭቤ የወሰድኳትን ልጻፍላችሁ፡፡
“ኦርቶዶክስ ነን እያሉ መናፍቃን እዚያ ገብተዋል” አሉ፡፡ ብጹእነታቸው ይህን የተናገሩት ስለ ተሐድሶ መናፍቃን አይደለም፡፡ ስለፕሮቴስታንቶችም አይደለም፡፡ ስለቅባት እና ፀጋዎችም አይደለም፡፡ ስለግቢ ጉባዔ ተማሪዎች እና ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ እርሳቸው መናፍቃን ያሏቸው ተሐድሶዎችን ቢሆን ኖሮማ በሥራቸው ደመወዝ እየከፈሉ ባላስቀመጧቸውም ነበር፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ በተሐድሶ መናፍቃን ሥልጠና ወስደው ቤተክርስቲያናችንን ለማፈራረስ የተነሡ በርካታ መናፍቃንን ደመወዝ እየከፈሉ በስራቸው ሸጉጠው አስቀምጠዋቸዋል፡፡
ቀጠሉና “እየው ተጠንቀቁ መናፍቃን ማለት እንዴ እኒህ ጎጃም ምን እንደው ታሪክ የሌለበት ጎጃም ሲያጠምቅ አዲስ አበባን ማን ያስተምረው እኮ አዲስ አበባ የየት አገር ሊቃውንት ነው ያሉ፡፡ በኢትዮጵያ የየት አገር እና በጣም በእውነት ሞራላቸው የወደቁ ልጆች አሉ” አሉን፡፡ ጎጃምንማ ቢያውቁት የእነ አቡነ ቴዎፍሎስ፤ የእነመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፤ የእነ አለቃ አያሌው ታምሩ አገር ነበር፡፡ ጊዜው ጅል ሆነና ስንት ሊቃውንትን እንዳላፈራ ስንት ቅዱሳንን እንዳላሳየ እርስዎን በመድረክ ላይ ተመለከትንበት እንጅ፡፡ ወንጌል በሚነገርበት መድረክ ላይ ቆመው ልጆችዎ ነን ብለው ከትቢያ ላይ ተቀምጠው የሚማሩትን ልጆች መናፍቃን ብለው ዘለፏቸው፡፡ “ሞራላቸው የወደቁ” ብለው የዘለፏቸው የግቢ ጉባዔ ተማሪዎች እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ነገ ታሪክ እንደሚሠሩ የሚያጡት አይመስለኝም፡፡ “በሰፈሩት ቁና…” እንዳይሆን ነገሩ በጊዜው ይቅርታ ማለት በተገባዎት ነበር፡፡
አሁንም ቀጠሉ “ካስፈለገም በጊዜው መዝግበናቸዋል፡፡ አዎ በእውነት ከዚያ ፊት ግን ይጎዳሉ ነው ይጎዳሉ፡፡ እንዴ ጎጃም ምን ሆኖ ነው እንዲህ እንዲህ ሞራሉን እንዲህ የማይከተበው አገር ተጠመቅ፡፡ ልጀ ይማራል ብሎ ዩኒቨርሲቲ ሰዶ… ያ ደሃ እኮ ልጁ እንዲማር ነው ጎጃም ሃይማኖት ብሎ ዩኒቨርሲቲ ይልካል እንዴ ልጁን አይልክም፡፡ አዎ ጥሩ ትምህርት መሐንዲስ ሆኖ ኑሮው እንዲያልፍለት ነው” አሉ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው “ያለበት አብላላበት” የሚባለው ነገር ነው፡፡ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በፌዴራል ደረጃ የሚታወቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚማርበት ተቋም እንጅ የጎጃም ልጆች ብቻ የሚማሩበት ተቋም አይደለም፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲነቱ ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በተሰጠው መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባዔን ያቋቁማል፡፡ በዚህ መሠረትም ትምህርተ ሃይማኖትን እያስተማረ ወደ ተዋሕዶ እምነታችን የሚመለሱትን ሁሉ እንዲጠመቁ ለካህናት ይመራል፡፡ ልብ በሉ! ለካህናት ይመራል ማለት ከሚያጠምቁ ካህናት ጋር አገናኝቶ የልጅነት ጥምቀትን እንዲጠመቁ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ይላል ወንጌል፡፡ አባታችን ግን ለምን ተጠመቁ ትላላችሁ እያሉ ሲያስተምሩ ምን ለማለት ፈልገው ይመስላቸኋል፡፡ አባታችን “ጎጃምን ያህል የሊቃውንት አገር” እያሉ የሚናገሩ ጎጃም አትጠመቁ ብሎ ስለሚያስተምር ይሆን፡፡ አይመስለኝም ዩኒቨርሲቲውንም በጎጃም ተማሪዎች ብቻ የወከሉት እና ጎጃሞች ተጠመቁ ተባሉ እያሉን ያለው የ“ቅብዓት” እምነትን የሚከተሉ ተማሪዎችን ወክለው ነው፡፡ እርሳቸው ለቅብዓት እምነት ዘብ መቆማቸው የተረጋገጠ ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም “ወልደ አብ” እና “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተባሉ መጻሕፍት በዘመነ ጵጵስናቸው መታተማቸው አማላካች ነው፡፡ እነዚህ በቅብዓት እምነት የሚኖሩ የጎጃም ተማሪዎች (ቅብዓት ከጎጃም ውጭ ስለማይታወቅ ማለቴ ነው) መሠረታዊ የሆነውን የተዋሕዶ እምነት ከተማሩ እና ከተቀበሉ በኋላ እንደማንኛውም ሁሉ የልጅነት ጥምቀትን ይጠመቃሉ፡፡ ይህ እኮ ማንም የሚፈርደው ለማንም የታወቀ እውነት ነው፡፡ ተጠመቅ የተባለ ማነው ብለን እንጠይቃቸው እስኪ፡፡ ጎጃም ትልቅ አገር ቢባል እነመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን እነ አለቃ አያሌው ታምሩን እነ አቡነ ቴዎፍሎስን እነ በላይ ዘለቀን እነ ሐዲስ አለማየሁን የመሣሠሉትን የእውቀት እና የአስተሳሰብ የእምነት እና የነጻነት ጀግኖች ስላስገኘ እንጅ በገዳማት ውስጥ ተደብቀው ምንፍቅናቸውን ስለጻፉ መሰልዎት እንዴ፡፡ “ስማቸውን መዝግበናቸዋል… ግን ይጎዳሉ” ብለው ያሏቸው የተዋሕዶ ልጆች ከእርስዎ በሚሰነዘር ቀስት እንደማይጎዱ እተማመናለሁ፡፡ ምክንያቱም ከእርስዎ ጋር ካለው ይልቅ ከእነርሱ ጋር ያለው ይበልጣልና፡፡ አንድ አባት በመድረክ ላይ ወጥቶ እንዲህ ያለ የረከሰ ንግግር ማድረግን ግን አልጠብቅምና አፈርሁብዎት፡፡ ዩኒቨርሲቲ የሚሠጠው ትምህርት ምህንድስና ብቻ መሰልዎት እንዴ፡፡ ዩኒቨርሲቲ የገባው ሁሉ መሐንዲስ ሆኖ የሚወጣ መስሎዎት የማይገባ ንግግርን ተናገሩ፡፡ ለነገሩ … ይተውት በቃ፡፡ እኔም ተውኩት፡፡
ቀጥለው “በዩኒቨርሲቲም ያላችሁ መምህራን እንዴ ዩኒቨርሲቲውን ዩኒቨርሲቲ አድርጉት እንጅ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ማለት ገበያ ነው፡፡… ስእለት መቀበያ እየተባለ በዶርም ተለጥፎ ስእለት… እዶርም ስእለት ማነው ታቦቱ እ እኮ ግዛቸው ነው ይበልጣል… እዶርም ስእለት መረጃ ይዘናል” አሉ፡፡ በዚህ ንግግርዎ እንዴት እንዳፈርኩብዎ ቢያውቁልኝ ኖሮ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የትኛው ሃይማኖት ነው እየተራመደ ያለው፡፡ አባታችን! ተማሪዎች እኮ ቁርሳቸውን ትተው ምሳቸውን ከፍለው ዳቦ ሰብስበው ያንን ሸጠው ያገኙት ገንዘብ ነው፡፡ እርር ክስል ቢሉ እርስዎ ኪስ አምስት ሳንቲም ጠብ የማትል የግል ገንዘባቸው ናት፡፡ ዓይንዎን ከዚች ሳንቲም ያንሡ! እርስዎ እዛው ለመባረኪያ እና ለእድሳት ፈቃድ እያሉ በ10 ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ይሰብስቡ እንጅ ከግቢ ጉባዔውስ አምስት አያገኙም፡፡ አረ እንዲያውም አንድ መረጃ ወጥቷል እውነት መሆኑን እስኪ እራስዎ ይመስክሩልን፡፡ የገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ደብረ ማርቆስ የሚገኘውን ማለቴ ነው ግንቦት 12/2009 ዓ.ም ይህን አዲስ ቤተክርስቲያን ለመባረክ 40 ሺህ ብር ጠይቀዋል ብለው ብዙዎች መረጃውን አሰራጭተዋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የግዛቸው እና የይበልጣልን ስም አንስተው ታቦት ናቸው ወይ ማለትዎ ነው፡፡ ታቦትማ የሆኑ እርስዎ ነበሩ አላወቁበትም እንጅ፡፡ ግዛቸው ማለት የማኅበረ ቅዱሳን የደብረ ማርቆስ ማእከል ጸሐፊ እንደሆነ ይበልጣልም ሰብሳቢ እንደሆነ ነበር የምናውቅ እርስዎ ግን ታቦት አደረጋችኋቸው እና አረፉ፡፡ እስኪ የትኛው ዶርም ነው ስእለት የሚሰበሰብበት ዛሬማ እውነትም አፍረዋል ምን ማፈር ብቻ እርር ብለዋል እንጅ፡፡ እናስታውሳለን ሁሉንም እናውቃለን፡፡ ግቢ ጉባዔ ተማሪዎች ገንዘባቸውን ለእኛ ይስጡን ብላችሁ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ድረስ መጥታችሁ የተቋሙን ፕሬዝዳንት ሳይቀር እንዳናገራችሁ መረጃው አለን፡፡ ፕሬዝዳንቱን ግን በጣም እናደንቀዋለን “ተማሪዎች ቁርሳቸውን ትተው ዳቧቸውን ሸጠው የሰበሰቡትን ገንዘብ የትስ ቢያደርሱት ምን አገባችሁ” ብሎ አሳፍሮ ሰዷችኋል፡፡ ፍንድት ብትሏት ብትቋምጡ የግቢ ጉባዔውን አምስት ሳንቲም አታገኟትም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ምን እንደሆነ ምን እንደሚካሄድበት ከእርስዎ ይልቅ እየሰደቡት ያለው ተማሪ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
በመጨረሻም “ጳጳስ እያስተማረ አሁን እናንተ በስመ አብን ሳትሉ እምነት እናስተምር ይባላል” አሉ፡፡ አባቴ! ጵጵስና እውቀት አይደለም፤ ጵጵስና መዓርግ ነው፡፡ ጳጳስ ሁሉ አዋቂ አማኝ ነው ማለት አይቻልም ያውም ዘንድሮ አይይይ… አይሆንም፡፡ አቡናርዮስ የሎዶቅያ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “አብ እና ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ ገጽ ናቸው” በማለት አንድ ገጽ ብሎ አስተማረ፡፡ ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ነበረ ነገር ግን “ወልድ ከነቢያት እንደ አንዱ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በዮርዳኖስ ባደረበት ጊዜ በጸጋ አምላክ ሆነ” በማለት ካደ፡፡ ፎጢኖስ የበሚርና ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “የወልድ ሕልውና ከማርያም ከተወለደ ወዲህ ነው” በማለት ካደ፡፡ ሳዊሮስ የሕንድ ቴዎዶስዮስ ደግሞ የእስክንድርያ ጳጳስ ነበሩ ነገር ግን “የእግዚአብሔር ልጅ ያለፈቃዱ በግድ ሞተ” ብለው ካዱ፡፡ ልዮን የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “ሥጋ ከመለኮት ያንሣል” በማለት ካደ፡፡ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ ጳጳሳት ነበሩ ነገር ግን “መለኮት እና ሥጋ በሁለት መንገድ በሁለት ሥርዓት ናቸው” ብለው ካዱ፡፡ ስለዚህ ጳጳስ ስለሆኑ ብቻ አዋቂ ነዎት እምነት አለዎት ብለን አንናገርም፡፡ ስሙን ግን ለግል ዓላማዎ እየተጠቀሙበት እና እየነገዱበት እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ እርስዎም ስልጣነ ጵጵስናውን ስለያዙ አባታችን እያልን ብናከብርዎ ደንቆሮ መሆናችን አይደለም፡፡ የቀደሙ አባቶቻችንን በተመለከትንበት ዓይናችን ስለተመለከትንዎ ብቻ ነው፡፡ የእውቀት መለኪያው ስልጣን መጨበጥ ብቻ ከሆነ ስንት የክብር ዶክትሬት ያላቸው ሰዎች አሉ መሰልዎት፡፡ ጵጵስናም የክብር እየተባለ መሰጠት ተጀመረ አይሉኝም መቸም፡፡ እውነቴን ነው አሁንስ! የክብር ጵጵስና ነው የእርስዎስ፡፡ ታዲያ ወንጌል ጠፋብዎት እንዴ ዩኒቨርሲቲ ዶርም የገቡ፡፡ የምን ጓዳ ለጓዳ መልከስከስ ነው ወጣ ብለው ወንጌልን ይስበኩ እንጅ፡፡ ቆይ በእርስዎ ዘመነ ጵጵስና የቱን መናፍቅ ነው አስተምረው የመለሱ፡፡ እንዲህ በቅዱሱ መድረክ ላይ ቆመው ሲሰድቡ ሲዘልፉ እየዋሉ በስመ አብን ከማን እንማር፡፡ ተያይዘን ደነቆርን እንጅ፡፡
ወገን አስተውል ብጹእ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የቤተክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ሥርጭት ሰብሳቢ ናቸው ብለናል ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎችን ከያዘ አባት ይህን ንግግር ትጠብቃላችሁ፡፡ ተወያዩበት፡፡ ተጨማሪ የቪዲዮም ሆነ የድምጽ መረጃ ያላችሁ ሁሉ በውስጥ መስመር ላኩልኝ፡፡

Thursday, May 4, 2017

ክህደት በማዕርግ አይደበቅም


© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 26/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

አንዳንድ ወገኖች በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ስለሚከናወኑ ጥፋቶች እና የጥፋቱ ፈጻሚዎችን በተመለከተ በምጽፋቸው ጽሑፎች ላይ በመረጃ ላይ ባልተመሠረተ ድፍን አመለካከት ጭፍን አስተያየት ሲሰነዝሩ ስመለከት በግልጽ ማብራራት እንደሚያስፈልግ አሰብሁ፡፡ በተለይ በምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት በአቡነ ማርቆስ ላይ በጻፍሁት ትችት ላይ አንዳንዶች በጥልቀት ሳይመለከቱ አስተያየታቸውን ወርውረዋል፡፡ አስተያየታቸው በዋናነት የሚያተኩረው “ወደ ላይ አትፍሰስ ጳጳስን ትገስጽ ዘንድ አንተ ማነህ?” የሚል ነው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ይህንን አስተያየት በሰጡበት ጽሑፍ ላይ መልስ ሰጥቸበታለሁ ነገር ግን ሁሉም ሰው ግልጽ መሆን ስላለበት ደግሜ እጽፈዋለሁ፡፡ እኔ አንድ ተራ ሰው እንደሆንሁ አውቃለሁ፡፡ ብሉያቱን ሐዲሳቱን ከጉባዔ ቁጭ ብየ አልቀሰምኩም፡፡ ዕውቀቱ የለኝም፡፡ እናንተ በገለጻችሁበት ቋንቋም ልግለጽላችሁ አወ ምንም የማላውቅ ደንቆሮ ነኝ ነገር ግን ሃይማኖቴን፣ ቤተ ክርስቲያኔን አውቃታለሁ፡፡ እርሷ በምን ላይ እንደተመሠረተች የእምነት መሠረቷ ምን እንደሆነም ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ አንድ አባትም እንደ አባትነቱ ምን ማድረግ እንዳለበት የእናንተን ያህል ባይሆንም ፍትሐ ነገሥቱን፣ ዲድስቅልያውን አንብቤዋለሁ፡፡ አንድ ልጅም እንደ ልጅነቱ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲሁ አንብቤያለሁ፡፡ “ዲቁና አልሰጥህ ስላሉ ነው ከእርሳቸው ጋር የተጣላህ” የሚሉም አንዳንድ ሞኞች አሉ፡፡ እኔ አውቄ ተምሬ ከተገኘሁ አምላክም ለዚህ የክህነት አገልግሎት ከመረጠኝ ዲቁናውን ለማምጣት የግድ ከአቡነ ማርቆስ እግር ሥር መውደቅ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ እኔ ምንም እንኳ ባልጠቅምበትም ዲቁና ያመጣሁት ጥር17/2000 ዓ.ም ነው ከዛሬ 9 ዓመት በፊት ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ “በሠላሳ ዓመትህ ዲቁና አልሾምህ” ስላሉ ነው የምትሉ ወገኖች ፋይላችሁን በዚሁ ዘጋሁት፡፡
“ወደ ላይ አትፍሰስ ጳጳስን ትገስጽ ዘንድ አንተ ማነህ?” የሚለውን ፋይል ስከፍተው የማይረባ ብሂል ሆኖ አገኘሁት፡፡ በዚሁ ልዘጋው አሰብኩና ብዙ የሚጻፍበት እንደሆነ ሳገኘው ፋይሉን በጥልቀት ተመለከትሁት፡፡ ወደ ጥንተ ፍጥረትም አባቴ ኤጲፋንዮስ እጄን ይዞ አክሲማሮስን ግለጠው አለኝ እኔም መጽሐፉን ተመለከትሁ፡፡ ሳጥናኤል አሐዜ መንጦላእት አቅራቤ ስብሐት የመላእክት ሁሉ አለቃ ነበረ አለኝ፡፡ ታዲያ የመላእክት ሁሉ አለቃ የሆነው ሳጥናኤል “እኔ ፈጣሪ ነኝ” ብሎ ራሱን አምላክ ካደረገ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ካልሆነ በቀር ከማን ጋር ትሰለፋለህ አለኝ? እኔም ሰልፌን ከቅዱስ ገብርኤል ጋር አደርጋለሁ አልኩት፡፡ ማዕርግ ክህደትን ሊደብቅ የሚችል ተራራ ቢሆን ኖሮ የሳጥናኤልን ክህደት ሊቀመላእክትነቱ አቅራቤ ስብሐትነቱ አሐዜ መንጦላእትነቱ በሸፈነለት ነበር፡፡ በጭፍኑ የምትከራከሩ ሰዎች ልብ በሉ አሁን የነቀፍሁት ሳጥናኤልን እንጅ ሊቀ መላእክትነትን ወይም አቅራቤ ስብሐትነትን ወይም አሐዜ መንጦላእትነትን አይደለም፡፡
የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ሐዋርያ ተብሎ ስለተመረጠ ሰው ነገረኝ፡፡ ስሙም ይሁዳ ይባላል አለኝ፡፡ ይሁዳ አባቱን የገደለ እናቱን ሚስት ያደረገ ሰው ነበር አለኝ፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ባይ አምላክ ነውና ይህንን ኃጢአቱን ትቶ ከእኛ ጋራ ሐዋርያ ብሎ ሾመው መረጠው፡፡ ነገር ግን በሠላሳ ብር ይህንን ይቅር ያለውን፤ ሐዋርያ ብሎ የመረጠውን ጌታ ለአይሁድ ካህናት አሳልፎ ሰጠው፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ይሁዳ ሐዋርያ የሚለውን ማዕርግ ስለተሸከመ እርሱን ብመስል እኔን ጴጥሮስን ትቀበለኝ ነበርን አለኝ፡፡ እኔም አንተንስ እውነተኛ ሐዋርያ ነህ ብየ የተቀበልሁህ ይሁዳን ስላልመሰልህ እና “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለህ ስለመሰከርህ ነው አልኩት፡፡ ማዕርግ ክህደትን የሚሸፍን ቢሆን ኖሮ ይሁዳን የሐዋርያነት ማዕርጉ በደበቀለት ነበር፡፡ ልብ በሉ አሁን የነቀፍሁት ይሁዳን እንጅ ሐዋርያነትን አይደለም፡፡
አሁን ደግሞ በማዕርግ ወደሚመስሏቸው ነገር ግን ስለክህደታቸው ወደተነቀፉ ሰዎች አባቴ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ና ብሎ መጽሐፈ ምሥጢርን አንብብ አለኝ፡፡ እኔም መጽሐፉን ገለጥሁ እና በመጀመሪያ አንቀጹ ስለዘረዘራቸው ጳጳሳት እና ክህደታቸው አነበብሁ፡፡ እንዲህም የሚል ንባብ አገኘሁ፡፡ አቡናርዮስ የሎዶቅያ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “አብ እና ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ ገጽ ናቸው” በማለት አንድ ገጽ ብሎ አስተማረ፡፡ አርዮስ የሊቢያ ቄስ ነበረ ነገር ግን “ክርስቶስ ፍጡር ነው” ብሎ ካደ፡፡ ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ነበረ ነገር ግን “ወልድ ከነቢያት እንደ አንዱ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በዮርዳኖስ ባደረበት ጊዜ በጸጋ አምላክ ሆነ” በማለት ካደ፡፡ ፎጢኖስ የበሚርና ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “የወልድ ሕልውና ከማርያም ከተወለደ ወዲህ ነው” በማለት ካደ፡፡ ሳዊሮስ የሕንድ ቴዎዶስዮስ ደግሞ የእስክንድርያ ጳጳስ ነበሩ ነገር ግን “የእግዚአብሔር ልጅ ያለፈቃዱ በግድ ሞተ” ብለው ካዱ፡፡ ልዮን የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “ሥጋ ከመለኮት ያንሣል” በማለት ካደ፡፡ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ ጳጳሳት ነበሩ ነገር ግን “መለኮት እና ሥጋ በሁለት መንገድ በሁለት ሥርዓት ናቸው” ብለው ካዱ፡፡ በማለት አስረዳኝ፡፡ አባቴ አባ ጊዮርጊስም ታዲያ በማዕርጋቸው ተመክተህ ጳጳሳት ናቸው ካህናት ናቸው ብለህ ከአቡናርዮስ፣ ከአርዮስ፣ ከንስጥሮስ፣ ከፎጢኖስ፣ ከሳዊሮስ፣ ከቴዎዶስዮስ፣ ከልዮን እና ከኬልቄዶን ማኅበርተኞች ጋራ ትሰለፋለህን አለኝ፡፡ እኔም እነርሱስ ከሐድያን ናቸውና አብሬያቸው አልሰለፍም አነርሱንም አልመስልም አልኩት፡፡ ወገኖቼ! ማዕርግ ክህደትን የሚሸፍን ቢሆን ኖሮ እነአቡናርዮስ፣ እነአርዮስ፣ እነንስጥሮስ፣ እነፎጢኖስ፣ እነሳዊሮስ፣ እነቴዎዶስዮስ፣ እነልዮን እና የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳት እና ፓትርያርኮች ስለነበሩ ክህደታቸው በተሸፈነላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ልብስ ቢሸፍኑትም በልብስ ላይ ብቅ እንደሚለው ለምጽ ክህደታቸው በአደባባይ ተጋልጧል፡፡ አሁንም ልብ በሉልኝ እኔ የነቀፍኋቸው እነአቡናርዮስን፣ እነአርዮስን፣ እነንስጥሮስን፣ እነፎጢኖስን፣ እነሳዊሮስን፣ እነቴዎዶስዮስን፣ እነልዮንን እና የኬልቄዶን ማኅበርተኞችን እንጅ ማዕርጋቸውን ጵጵስናቸውን፣ ሊቀጵጵስናቸውን፣ ፕትርክናቸውን አይደለም፡፡
አቡነ ማርቆስን በተመለከተም የጻፍሁት ይህንኑ ነው፡፡ እኔ አስተያየት ከሰጣችሁኝ ሰዎች ይበልጥ  በቅርበት አውቃቸዋለሁ፡፡ ማዕርጋቸው ትልቅ ነው አውቃለሁ፡፡ የተሰጣቸው አደራ እና ኃላፊነት እጅግ ከባድ ነው አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን አልተጠቀሙበትም አላገለገሉበትም፡፡ እኔም እርሳቸውን የነቀፍሁት ስም እንጅ ግብር ስለሌላቸው ብቻ ነው፡፡ ልብ በሉልኝ ጵጵስናውን አልነቀፍሁም፤ ሊቀ ጵጵስናውን አልነቀፍሁም እርሳቸውን “አባ ማርቆስን” ግን እነቅፋለሁ፡፡ እንዲያውም ቅስና ስለሌለኝ ገና ዲቁና ላይ ስለቀረሁ እንጅ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ የማሰር ሥልጣን አሥራቸው እገዝታቸው አወግዛቸውም ነበረ፡፡ ይህ እኮ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው አባታችን የዲማው ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ አቡነ ጳውሎስን ያወገዙ ለምን ይመስላችኋል? አቡነ ጳውሎስ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ክብራቸውን አዋርደው ከሮማው ፖፕ መስቀል ስለተሳለሙ አይደለምን? አቡነ ማርቆስም በሐገረ ስብከቱ ውስጥ እያደረሱት ያለው ጥፋት ቀላል አይደለም፡፡
እኔ ለእርሳቸው ጭፍን የሆነ ጥላቻ ያለኝ የሚመስላችሁ ሰዎች ምንም ዓይነት ጥላቻ የለኝም፡፡ ሹመት ማዕርግ ሽቼ እርሳቸውን ደጅ እየጠናሁ ያለሁ ሰው አይደለሁም፡፡ የምተዳደረውም ከቤተክርስቲያን ከሚሰጠኝ ገንዘብ ሳይሆን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥሬ ከማገኘው ደመወዝ ነው፡፡ ታዲያ በምን ልጠላቸው እችላለሁ? አባትነታቸውን በአግባቡ ስላልተጠቀሙበት ብቻ ነው የጻፍሁት፡፡ በሐገረ ስብከታችን ምን ጥፋት አደረሱ ካላችሁኝ አንድ በአንድ መጻፍ እችላለሁ፡፡
1.  የቅብዓት ሃይማኖት እንዲስፋፋ በመጣር ላይ መሆናቸው፡፡ ለዚህም “ወልደ አብ” እና “ዝክሪ እና ጳውሊ” የተሰኙ መጻሕፍት በቤተክርስቲያናችን ስም ሲታተም ዝም ማለታቸው፡፡ መጻሕፍቱ እንዲወገዙልን እና መልስ እንዲሰጥባቸው በደብዳቤ የጠየቅናቸው ሲሆን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ አለመስጠታቸው ይህንን አስተምህሮ እንደሚደግፉ ማረጋገጫ መሆኑ፡፡
2.  ጉንደወይን ከቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ቆመው “ሞኞች ካሌንደር ሲያወጡ ይውላሉ፡፡ ገናን በ28 እናከብራለን ይላሉ፡፡ አያችሁ እነዚህ ካሌንደር የማያውቁ ሰዎች ጥምቀትን እኮ ጥር 10 አድርገውት አረፉ” በማለት ሕዝቡን ሲያስጨበጭቡ የሚያሳይ መረጃ እጃችን ላይ መሆኑ፡፡
3.  ተዓምረ ማርያም ላይ የተገለጹትን የእመቤታችን 33ቱ በዓላት አታንብቡ ይህ ካሌንደር እኮ ነው በማለት በምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሥር ባሉ በተለይ የከተማ አብያተ ክርስቲያናት አለመነበባቸው፡፡
4.  ገንዘብ ካለህ ደህና ገንዘብ ካቀረብህ በአቡነ ማርቆስ ዘመን ሹመት ማግኘት ቀላል ነው የሚባልበት ሐገረ ስብከት እንዲሆን ማድረጋቸው፡፡ እዚህ ላይ አንድ መምህር የተናገረውን መጻፍ እፈልጋለሁ፡፡ መምህሩ ሊቀጠር እርሳቸው ዘንድ በፖስታ አሽጎ ገንዘብ ይዞ ይሄዳል፡፡ ከዚያም ፖስታውን ክፈተው እስኪ ይሉታል፡፡ እርሱም ይከፍተዋል ስንት ነው ቁጠረው ይባላል 3500 ብር ነው፡፡ “አይ እኔ እኮ ደህና ብር ይዘህ የመጣህ መስሎኛል” አሉት፡፡ ይህንን የተናገረው ደግሞ ራሱ ሊቀጠር የሄደው መምህር ነው፡፡
5.  በየአጥቢያው የሚገኙ አስተዳዳሪዎች በሙሉ የሥጋ ዘመዶቻቸው ሆነው መገኘታቸው፡፡ ዝምድናቸው የሚያስነቅፍ ባይሆንም እነዚህ የተሾሙት በሙሉ በየአጥቢያው ሕዝቡን እያስቸገሩ መገኘታቸው፡፡ ለምሳሌ ገዳመ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የመደቡት “መልአከ መንክራት አባ ፍቅረ ማርያም” በቤተክርስቲያኑ የሰንበት ትምህርት ቤትን በመዝጋቱ ወንድሙን ያለሰበካ ጉባዔው ፈቃድ በመቅጠሩ ከባድ ተቃውሞ እንደደረሰበት እና አሁን ደግሞ እዚሁ ደብረ ማርቆስ ጌቴሴማኒ ፈረስቤት መድኃኔዓለም ማዛወራቸው፡፡ እዚህ መድኃኔዓለም አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እየተገነባ ነው ከዚህ ገንዘብ ለመቃረም ሊሆን አንደሚችል አመላካች ነው፡፡
6.  በሐገረ ስብከቱ ውስጥ የሙታን መታሰቢያ በእህል በውኃ መሆኑ ቀርቶ በገንዘብ እየተቀየረ ለቤተክርስቲያን ገቢ እንዲደረግ የሚል አዋጅ ማውጣታቸው፡፡ በዚህም አስተዳዳሪ ብለው በሾሟቸው ሰዎች በኩል እየተሰበሰበ ገቢ እንዲደረግላቸው ማድረጋቸው፡፡ ልብ በሉ ድሆች የሚመገቡትን እና ሙታንን ነፍስ ይማር የሚሉበትን እህል ውኃ ነው፡፡ ማርያም እንተ እፍረት በጌታ እግር ላይ ሽቱ እያፈሰሰች በእንባዋ እያጠበች ስታለቅስ ይሁዳ “ይህን የ300 ብር ሽቱ ከምትደፋው ተሸጦ ለድሆች ቢሆን ይሻል ነበረ” አለ ይሁዳ እንዲህ ያለው ለድሆች አዝኖላቸው አስቦላቸው አልነበረም፡፡ ወደ ገንዘብ ከተቀየረ ከ10 አንድ ያገኝ ነበረ እና 30 ብር ቀረብኝ ብሎ ነው፡፡ እኒህም ያንኑ ነው ያደረጉት፡፡
7.  ሕዝቡ መምረጥ የሚገባቸውን የሰበካ ጉባዔ አባላት ቃለ ዐዋዲውን በመጣስ በራሳቸው ፈቃድ በደመወዝ እየቀጠሩ የዚህ አጥቢያ የሰበካ ጉባዔ ሰብሳቢ የዚህ ሰበካ ጉባዔ ፀሐፊ ወዘተ እያሉ መመደባቸው፡፡
8.  የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አዳራሾቻቸውን በጥበቆች በማስዘጋት እንዲወጡ መደረጋቸው፡፡ የዐቢይ ጾምን የሌሊት ስግደት ሙሉ በሙሉ ማስቆማቸው፡፡
9.  የግቢ ጉባዔ ተማሪዎች በየትኛውም አጥቢያ ቤተክርስቲያን የኮርስ ትምህርታቸውን እንዳይማሩ መከልከላቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንንም ገንዘብ እንዲሰበስብላቸው ሲፈልጉ ብቻ እንደሚጠቀሙበት፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እንዲዘጋ ሰበካ ጉባዔያትን ማወያየታቸው፡፡
10.  በደብረ ማርቆስ ከተማ ሊገነባ ለታቀደው ባሕረ ጥምቀት ህዝቡ የመረጣቸው ጠንካራ ኮሚቴዎች ስድስት ወር ባልሞላ የሥራ ዘመን ከ100 ሺህ ብር በላይ መሰብሰባቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኮሚቴዎች ለእርሳቸው አምስት ሳንቲም ማቅመስ ባለመቻላቸው ባላወቁበት መንገድ መሻራቸው እና ራሳቸው እንደፈለጉ በሚያዝዟቸው (ገንዘብ ስጡኝ ሲሏቸው የሚሰጡ ማለቴ ነው) መተካታቸው፡፡
11.  በአርምሞ እና በጽሙና ሊጾም በሚገባው ዐቢይ ጾም መድረክ ላይ ወጥተው ሲያስጨበጭቡና እልል ሲያስብሉ መክረማቸው፡፡
12. ያረጁ አብያተ ክርስቲያናትን ለማደስ በሚጀምሩ ሰበካ ጉባዔዎች ላይ የእድሳት እና የግንባታ ፈቃድ በማለት ከ7000 ብር በላይ መጠየቃቸው፡፡ አዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለመባረክ ሲጠሩም ከ10ሺህ ብር በላይ መጠየቃቸው፡፡
13. ሕጋዊ ባልሆኑ ደረሰኞች በርካታ ገንዘብ ማሰብሰባቸው፡፡
14. በሐገረ ስብከታቸው የሚገኙ ገዳማትን በእኩል ዓይን አለመመልከታቸው፡፡ ዲማ ጊዮርጊስን፣ ደብረ ኤልያስን፣ ሥላሴ ገዳምን (ደብረ ኤልያስ ውስጥ የሚገኝ) ፣ገነተ ቅዱሳን አዲሱ መድኃኔዓለምን እና የመሳሰሉትን ገዳማት እና አድባራት በማስጠንቀቂያ በማስፈራራት አስተዳዳሪዎችን በማሸማቀቅ ላይ መሆናቸው፡፡ ሚያዝያ 23/2009 ዓ.ም ይከበር የነበረውን የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ለማደናቀፍ በማሰብ በየአጥቢያው “ዲማ የምትሄዱ ሰዎች ያለእኔ ፈቃድ እንዳትንቀሳቀሱ” የሚል መልእክት ማስተላለፋቸው፡፡ ቁራሽ ለምነው ለተማሩበት ገዳም ለመርጡለ ማርያም ገዳም ግን  ጥር 21 ለሚከበረው የእመቤታችን የእረፍት በዓል በየአጥቢያው “ኩንትራት መኪና አዘጋጅተናል ተመዝገቡ” ብለው መቀስቀሳቸው፡፡ ለዚህ መቀስቀሳቸው ለዚያ አትሂዱ ማለታቸው እኩል የሚመለከት ዓይን እንደሌላቸው ማሳያ ነው፡፡ ጥንታዊቷን ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳምን እየነቀፍሁ ለምን ሄዳችሁ እያልሁ አይደለም፡፡ ማን ከልካይ አደረገኝና ዓይናቸው እኩል አለመሆኑን ነው የተናገርሁ፡፡
15. ከእኔ ከጳጳሱ ውጭ ማን መጥቶ ያስተምራችሁ በማለት የዋሐንን የአባቶቻችሁን እምነት ያዙ ዳግመኛ ጥምቀት የለም በማለት ቅብዓትን ለማስፋፋት መጣር ላይ የሚገኙ መሆናቸው፡፡
16. እርሳቸውን የሚቃወሙ ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ መነኮሳትን ከአገልግሎት በማገድ ደመወዝ በመከልከል በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረጋቸው፡፡ ለዚህም እስከ ክልል ድረስ እርሳቸውን ከስሰው የሚሟገቱ አሉ፡፡
17. ጉባዔ የሰፋላቸውን ተማሪ የበዛላቸውን የአብነት ትምህርት ቤት መምህራን የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አድርገው በመሾም ጉባዔው እንዲፈታ ተማሪው እንዲሰደድ ማድረጋቸው፡፡ አብነት ትምህርት ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጦርነት መክፈታቸው፡፡
18. የተሐድሶ መናፍቃንን የሰንበት ትምህርት ቤት መምሪያ ኃላፊዎች እያደረጉ መመደባቸው፡፡
እኔ ከብዙው በጥቂቱ ይህንን ጻፍሁላችሁ፡፡ ስለዚህም የምነቅፋቸው በዚህ እና በመሳሰለው ግብራቸው እንጅ አባት መሆናቸውን ጳጳስ መሆናቸውን ዘንግቸው አይደለም፡፡ “አዲስ የሚመረጡትን ትኮንናለህ የተሾሙትንም ትኮንናለህ አንተ ጵጵስናውን ትይዘው” ያላችሁኝም አላችሁ፡፡ እኔ ጳጳስ ልሁን አላልኩም ጳጳስ ምን ማድረግ እንደሚገባው ግን ተናገርሁ፡፡ ቤተክርስቲያናችን የእውቀት ማዕከል ናት፡፡ ሥርዓት አላት መመሪያ መተዳደሪያ አላት፡፡ ከዚህ ውጭ ልምራ ልመራ ልተዳድር ላስተዳድር እንደፈለግሁ ልሁን ማለት አይቻልም፡፡ እውነትን እውነት ብለን መናገር መድፈር ካልቻልን “የኢሳይያስ ለምጽ” በእኛ ላይም እንደሚያድር አትጠራጠሩ፡፡ ዮሐንስ በራዕዩ የሰርዴሱን የቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲገስጽ ከእግዚአብሔር መልእክት መጣለት ራእ 3÷1 ላይ “…ሥራኽን አውቃለሁ ሕያው እንደመሆንህ ስም አለኽ ሞተኸማል” በል አለኝ ይላል፡፡ አሁንም ልክ እንደዚሁ ነው እየሆነ ያለው ነገር፡፡ እርሳቸው “ሊቀ ጳጳስ” የሚለውን ሕያው ስም ይዘዋል ነገር ግን በምግባር በሃይማኖት ሞተዋል፡፡ ታዲያ ዝም እንበላቸው ማለት ምን ማለት ነው? እንደእኔ መምከር የሚገባቸው እርሳቸው ናቸው ባይ ነኝ ነገር ግን ጥፋት ከፈጸሙ እኛም እንመክራቸው ዘንድ ግዴታችን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ የጻፍኩት ለዚሁ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጥፋት በስም በማዕርግ ደብቆ ማስቀረት አይቻልም፡፡ በዚያ ቢሆንማ ሳጥናኤል መልአክ በመሆኑ ይሁዳም ሐዋርያ በመሆኑ ንስጥሮስም ፓትርያርክ በመሆኑ ይበልጧቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ተራ ምእመናን ሁሉ ሳንቀር ስናወግዛቸው እንኖራለን፡፡ ምክንያቱም ስራቸው ነዋ! ታስታውሳላችሁ ያኔ ስለ እነ በጋሻው ስለ እነምርትነሽ ስለ እነ ዘርፌ ስለ እነትዝታው መናፍቅነት ስንጽፍ መዓት ስድብ ታሸክመኑን እንደነበረ፡፡ ዛሬ ግን ለስድቡ እናንተ ትብሳላችሁ፡፡ አባ ላይም ያለው እንዲሁ ነው አንድ ቀን እውነቱን ስትለዩት ያኔ እናንተ ትብሳላችሁ፡፡ እውነቱን ተናገርሁ ያየሁትን መሰከርሁ የሆነውን ሆነ አልኩ የተደረገውን ተደረገ አልሁ፡፡ ከእርሳቸው ከጳጳሱ በላይ አንተ አታውቅም ዝም በል ለምትሉኝ ግን የመላእክት አለቃ ከነበረው ሳጥናኤል፤ ሐዋርያ ከነበረው ይሁዳ፣ ፓትርያርክ ከነበረው ንስጥሮስ የተሻልኩ መሆኔን እገልጻለሁ፡፡ እርሳቸውም በእነዚህ መንገድ እየተጓዙ እስካሉ ድረስ ዝም አልልም፡፡ ጨረስኩ፡፡

Wednesday, May 3, 2017

ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን በመብላትሽ ደስ አለኝ

© መልካሙ በየነ

ሚያዝያ 25/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ሔዋን ሆይ በገነት መካከል ሦስት ዛፎች እንደነበሩ ከእኔ ይልቅ አንች ታውቂያለሽ፡፡ አዳም ግን ከአንች ቀድሞ ይህንን ሁሉ ያውቅ ነበርና ስለዕፅዋት ሁሉ አስቀድሞ ነግሮሻል፡፡ ይህንን ብሉ ተብለናል እንበለዋለን አለሽ፡፡ ይህንን ግን አትብሉ የበላችሁት ጊዜ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ብሎ አዝዞናል እና እንጠብቀዋለን እንጅ አንበላውም አለሽ፡፡ ስለሦስተኛው ዕፅ ግን ብሉም አትብሉም አልተባልንም ብሎ ነበር የነገረሽ፡፡ በምክረ ከይሲ ተታልለሽ አንች ግን የበላሽው የተከለከላችሁትን ነበር፡፡ ብሉም አትብሉም ብሎ ያላዘዛችሁን ዕፅስ በልታችሁ ቢሆን ኖሮ የሕይወት ዕፅ ነበርና ከገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ያሸጋግራችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን አትብሉ የበላችሁት ጊዜ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ያለሽን ዕፅ ዕፀ በለስን በመብላትሽ ወደ ምድር ተሸጋገርሽ፡፡ ከተድላ ቦታሽ ከገነት ወጣሽ፡፡
ሔዋን ሆይ! አንችን ይበልጥ ያስተዋልሁሽ ይበልጥም የተረዳሁሽ በበዓለ ደብረ ዘይት ነው፡፡ ቅዳሴውን ላስቀድስ እነሆ ከቤተ ክርስቲያን ቆምሁ፡፡ ካህኑም የአትናቴዎስን ቅዳሴ ሲያነብልን ሰማሁ፡፡ ሊቁን ወደ አንች እና ወደ አዳም ምሥጢር ስቦ አስገባው፡፡ እርሱም እንዲል አለ፡፡ “አዳም ሆይ የሞት ፍርድን ያመጣህብን ምን አደረግንህ፡፡ አዳም ሆይ ደስታ ባለበት በገነት ጌታ ማደሪያ ደስ ይለን ዘንድ ያልተውኸን ምን አደረግንህ” ብሎ አዳምን ወቀሴታ በመሰለ ቃል አነሣው፡፡ ከዚያም ወዳንች ተመለሰ እንዲህም አለሽ “ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ እነሆ በኃጢአት ብዛት ሥጋችን ጠቆረ በሰማያውያን አምሳል በኖርነ ነበረ፡፡ ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ እነሆ ልጆችሽ በጭንቅና በሕማም በወለዱ ጊዜ ያለቅሳሉ አንች ያቺን በገነት ያለችውን እንጨት እንዳደማሻት ይደማሉ” ብሎ የወቀሴታ በመሰለ ቃል ተናገረሽ፡፡ ከዚያም ማንም የማይለያችሁ አንድ አካል አንድ ሥጋ ሆናችኋልና በጋራ እንዲህ አላችሁ “አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተን እንነቅፍ ዘንድ የሚቻል አይደለም እኮ! አንደበትን እየተናገሩበት ሊሰድቡበትና ሊነቅፉበት እንዳይቻል እንደዚህም እናንተ እኛን ናችሁ እኛም እናንተን ነን” አለ፡፡ እውነት ነው ሊቁ ጨርሶታል፡፡  እናንተን እንነቅፍ ዘንድ እኛ ከየት ተገኘን? እኛ ከእናንተ ባሕርይ የተገኘን ነንና እናንተን የምንነቅፍበት አንደበት ከቶ የለንም፡፡ ቀጥሎም እንዲህ አለ “አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ ይቅር ባይ በሆነ ጌታ ተግሣፅ ንስሐ ገብታችኋል፡፡ አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ በውነት ድናችኋል በተበጃችሁ በጌታ ደም ያለመከልከል ወደ ቀደመ ርስታችሁ ገብታችኋል፡፡ በተበጃችሁ በጌታ የማያምኑ ዐላውያን ሁሉ ልጆቻችሁ አይደሉም፡፡ አርአያችሁ ምሳሌያችሁ ናቸው እንጅ፡፡ በአንድ ልጃችሁ ያመን እኛ ግን በእውነት ከወገባችሁ የወጣን አርአያችሁ ምሳሌያችሁ ነን፡፡ እነሆ እኛን ልጆቻችሁን ኃጢአት እንደ እሳት በላችን፡፡ ፍትወትም አቃጠለችን፡፡ የነፍስ ፍትወት አይደለም የሥጋ ፍትወት ነው እንጅ፡፡ ይኸውም ነፍስን የሚያጠፋት ነው” አለ፡፡ እኔም እንዲህ እላችኋለሁ “አዳምና ሔዋን ሆይ እኛማ ከእናንተ ባሕርይ የተገኘን አይደለንምን? አርአያችሁ ምሳሌያችሁስ አይደለንምን? ታዲያ እናንተን እንነቅፍ ዘንድ ምን ያበረታናል፡፡ እናንተስ ስለ በደላችሁት በደል ተጸጽታችሁ ንስሐ ገብታችኋል፡፡ እናንተስ ከልጅ ልጃችሁ በተወለደ ጌታ ድናችኋል፡፡ እናንተስ ተድላ ገነትን ዳግም አግኝታችኋል፡፡ የእናንተን ክብር ያላገኙትን አርአያና ምሳሌያችሁ ብቻ የሆኑትን ከአብራካችሁ ያልተገኙትን ዐላውያን እንነቅፋቸዋለን እንጅ፡፡ እናንተስ የምትነቀፉ የምተውቀሱ አይደላችሁም እኮን”
ሔዋን ሆይ እኔም አመሰግንሻለሁ፡፡ እኔ ግን የማመሰግንሽ ዕፀ በለስን በመብላትሽ ነው፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ ገነት መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባኝን ርኅርኅተ ልብ ድንግል ማርያምን ባላገኘኋት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ የአምላኬን ፍቅር ባልተረዳሁት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ እንካችሁ ሥጋየ ብሉት እንካችሁ ደሜ ጠጡት ያለንን አምላክ ባላየነውም ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ አፍሽ በዕፀ በለሱ ባይረክስ ኖሮ ቀድሶ ገነት መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባንን የክርስቶስ ሥጋውን ባልበላንበት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ አፍሽ በዕፀ በለሱ ባይረክስ ኖሮ ቀድሶ ገነት መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባንን የክርስቶስ ደሙን ባልጠጣንበት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ ከሽህ ዘመን በኋላ ዕፀ ሕይወትን በልተሽ ታድሰሽ ከነልጆችሽ መንግሥተ ሰማያት በገባሽ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀድመሽ ዕፀ በለስን በላሽ ምክንያተ ስህተት እያሉም ወንዶች ተሳለቁብሽ፡፡ ድንግል ማርያም ከአንች ባሕርይ ስትወለድ ግን ምክንያተ ድኅነት ብለው ተመኩብሽ፡፡ ሔዋን ሆይ እኔስ አልወቅስሽም አልነቅፍሽምም፡፡ ሔዋን ሆይ ባሕርይሽ ባሕርየ ነውና ደካማነቴን አውቀዋለሁ፡፡ ሔዋን ሆይ ባሕርየ ከአንች ባሕርይ ጋራ አንድ ስለሆነ ዕፀ በለስን ለምን በላሽ አልልሽም? ሔዋን ሆይ በአንች ምክንያት ገነት ተዘግቶብን በፍዳ ብንያዝም ከአንቺው በተወለደች ልጅሽ ፍዳችንን መርገማችንን አራግፈን ገነትን ወረስናት፡፡ ዕፀ በለስን በመብላትሽ የተነሣ ድንግል ማርያምን የምታህል አምላክን ለመውለድ በቅታ የተገኘች እናትን አግኝቻለሁና የጌታየንም ልዩ ፍቅር ተመልክቻለሁና ሔዋን ሆይ! ስለዚህ ነገር ዕፀ በለስን በመብላትሽ ደስ አለኝ፡፡ 

Tuesday, May 2, 2017

“ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ የሚሰጠን” ኪዳን ዘነግህ

© መልካሙ በየነ

ሚያዝያ 24/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በመጽሐፈ ኪዳን በነግህ ምስጋና ላይ “ወዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ ዘእምፈቃዱ፤ ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ ወዶ የሚሰጠን” የሚል ድንቅ ምስጋና አለ፡፡ ሁልጊዜ በነግህ ምስጋናችን ላይ ይህንን ቃል መስማት እና ማሰማት ምንኛ መታደል ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንም እያንዳንዳችን የምንሻውን አውቆ ሳንለምነው ብዙ ነገር ሰጥቶናል፡፡ ወንጌል “ለምኑ ይሰጣችኋል” ይለናል ኪዳኑ ደግሞ “ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ ወዶ የሚሰጠን” ይላል፡፡ በሁለቱ ዘንድ ተቃርኖ ያለ ይመስላል ግን የለም ሁሉም ይታረቃል፡፡ እኛ የምንሻውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያውቃል፤ የምንለምነውም ይህንኑ የምንሻውን ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሁላችንንም ምሥጢር ያውቃል፡፡ “ለምኑ ይሰጣችኋል” የሚለን ከእግዚአብሔር መራቅ እንደማይገባን፣ ሁል ጊዜ ወደ አምላካችን በጸሎት መቅረብ እንዳለብን ሲያስረዳን ነው፡፡ ራሳችንን በትህትና ዝቅ አድርገን የጎደለንን ለይተን “አምላኬ ሆይ ይህ ጎደሎ አለብኝ እና አንተ በቸርነትህ ጎደሎየን ሙላልኝ ችግሬን አስወግድልኝ አምነቴን አጽናልኝ ምግባሬን አሳምርልኝ” ብለን በእርሱ ፊት መቆማችንን ከእርሱ አለመራቃችንን ወደ እርሱ ዕለት ዕለት መቅረባችንን እንደ ልመና ይቆጥርልናል፡፡ ይህ ሃሳብ በውስጣችን በልባችን መሻት የተረጋገጠ ነውና፡፡ በውስጣችን በልባችን “መቼ ይሆን ሥጋህን የምበላው ደምህንም የምጠጣው” ብለን ብንሻ እርሱ ይህንን የልባችንን መሻት አውቆ ወዶ ይፈጽምልናል፡፡
ለዚህ ትልቁ የነግህ ምስጋችን ማረጋገጫ ጥንተ ፍጥረት አዳምን መውሰድ እንችላለን፡፡ አዳም የተፈጠረው ሰማይ እና ምድር ብርሃናት እና እንስሳት ሁሉም ሥነ ፍጥረታት ከተፈጠሩ በኋላ በመጨረሻው ቀን ዐርብ ዕለት ነው፡፡ አዳም የሚበላው የሚጠጣው የሚለብሰው ነገርን ይፈልጋል፡፡ ልብሱስ ከጸጋው ከተገፈፈ በኋላ ነው እንጅ ከዚያ በፊትስ የጸጋ ልብሱን ተጎናጽፎ ይኖር ነበር፡፡ ስለዚህ አዳም ሳይፈጠር አዳም የሚሻውን ነገር አውቆ እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጠረለት፡፡ ከዚህም በኋላ አዳም ረዳትን ፍጠርልኝ ብሎ እግዚአብሔርን ሳይለምነው አዳም የሚያስፈልገውን የሚሻውን ነገር አውቆ እግዚአብሔር አምላክ “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና ረዳት የምትሆነውን እንፍጠርለት” ብሎ ከግራ ጎኑ ሄዋንን ፈጠረለት፡፡ አባታችን አዳም ረዳቱ ሄዋን እንድትፈጠርለት ሲለምን በመጽሐፍ አልተጻፈልንም እግዚአብሔር ግን አዳም የሚሻውን አውቆ ሰጠው እንጅ፡፡ በእኛ ሕይወት ዘንድም ያለው ይኸው ነው፡፡
ሁላችንንም ወደ ማስተዋል ጎዳና ይመልሰንና እግዚአብሔር አምላክ እኛ ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ የሰጠን ስንቱን ነገር ነው? በእውነት ራቁታችንን ወደዚች ዓለም የተቀላቀልን እኛ የአዳም ዘሮች የመጀመሪያውን ልብሳችንን ፈጣሪያችን ያለበሰን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ ሰጠን? በእውነት እጅ እግራችንን፤ ዓይን ጆሯችንን ሌሎችንም የአካል ክፍሎቻችንን ጤናማ አድርጎ የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? በዐርባ በሰማንያ ቀናችን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ ልደት መወለድን የሰጠን ለእርሱ ልጆቹ እንድንሆን የመረጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ዕድሜን ለንስሐ ዘመንን ለፍስሐ እየሰጠ እስካሁን ድረስ በቸርነቱ ጠብቆ ያቆየን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ከህጻንነት ለጋ አስተሳሰብ ወደ ጉልምስና ጠንካራ አስተሳሰብ እና አዋቂነት ጠብቆ ያደረሰን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን  አውቆ አደረገልን? በመንፈሳዊው እውቀት አጎልምሶ ከአላዋቂነት ወደ አዋቂነት፤ ከተማሪነት ወደ መምህርነት፤ ከምእመንነት ወደ ካህንነት ማዕረግ ከፍ ከፍ ያደረገን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ አደረገልን? በዓለማዊው እውቀትም እንዲሁ በአእምሮ አጎልምሶ ከተማሪነት ወደ ተመራማሪነት ከአንደኛ ክፍል ወደ ሁለተኛ ከዚያም ወደ ኮሌጅ ከዚያም ወደ ዩኒቨርሲቲ ያደረሰን ዲፕሎማ፤ ዲግሪ እንድናገኝ የረዳን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ ሰጠን? የዘላለም ርስት መንግሥተ ሰማያትን የምንወርስበትን ሥጋውን እና ደሙን እንኩ ብሉ እንኩ ጠጡ ብሎ የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ከኃጢአት ከርኲሰት ጠብቆ በቅድስና እንድንኖር የረዳን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ ሰጠን? የምንበላውን የምንጠጣውን የምንለብሰውን ይህን ሁሉ ነገር የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? እኛ ከማናየው እርሱ ከሚያየው፤ እኛ ከማናውቀው እርሱ ከሚያውቀው መከራ ሁሉ በቸርነቱ የጠበቀን እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ለሞት ከሚያበቃ ከባድ በሽታ ታድጎ በጤንነት የጠበቀን እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? የትዳር ጓደኛችንን (ለሴቶች ባልን ለወንዶች ሚስትን) የሰጠን እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? የተባረከ ትዳርን ሰጥቶ በልጆች መወለድ ፍቅራችንን ያጠነከረልን እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? እሳትን በጉያችን ታቅፈን ከፍትወታት እኲያት ጠብቆ በንጽሕና በድንግልና እንድናገለግለው ጽናቱን የሠጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ግርማ ሌሊቱን ድምጸ አራዊቱን ጸብአ አጋንንቱን ሳንፈራ ጤዛ ልሰን ድንጋይ ተንተርሰን በበረሃ ወድቀን በዋሻ በዓት ዘግተን እንድንኖር ጽናቱን የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? በኃጢአት ተዘፍቀን የጽድቅን ፀሐይ እንዳንመለከት አንገታችንን ከደፋንበት እና ካቀረቀርንበት ቦታ ፈልጎ ሸክማችሁ የከበዳችሁ ኑ ወደ እኔ ብሎ በንስሐ ያራገፈልን ለምነነው ነው የምንሻውን አውቆ? ከመቅሰፍት ጠብቆ እስካሁን ድረስ ያቆየን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? “በምድር ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ ነው፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይም የተፈታ ነው” የሚለውን የማሰር እና የመፍታት ስልጣን የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ?