© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ
24/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በመጽሐፈ ኪዳን በነግህ ምስጋና
ላይ “ወዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ ዘእምፈቃዱ፤ ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ ወዶ የሚሰጠን” የሚል ድንቅ ምስጋና አለ፡፡
ሁልጊዜ በነግህ ምስጋናችን ላይ ይህንን ቃል መስማት እና ማሰማት ምንኛ መታደል ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንም እያንዳንዳችን
የምንሻውን አውቆ ሳንለምነው ብዙ ነገር ሰጥቶናል፡፡ ወንጌል “ለምኑ ይሰጣችኋል” ይለናል ኪዳኑ ደግሞ “ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ
ወዶ የሚሰጠን” ይላል፡፡ በሁለቱ ዘንድ ተቃርኖ ያለ ይመስላል ግን የለም ሁሉም ይታረቃል፡፡ እኛ የምንሻውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር
ያውቃል፤ የምንለምነውም ይህንኑ የምንሻውን ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሁላችንንም ምሥጢር ያውቃል፡፡ “ለምኑ ይሰጣችኋል” የሚለን
ከእግዚአብሔር መራቅ እንደማይገባን፣ ሁል ጊዜ ወደ አምላካችን በጸሎት መቅረብ እንዳለብን ሲያስረዳን ነው፡፡ ራሳችንን በትህትና
ዝቅ አድርገን የጎደለንን ለይተን “አምላኬ ሆይ ይህ ጎደሎ አለብኝ እና አንተ በቸርነትህ ጎደሎየን ሙላልኝ ችግሬን አስወግድልኝ
አምነቴን አጽናልኝ ምግባሬን አሳምርልኝ” ብለን በእርሱ ፊት መቆማችንን ከእርሱ አለመራቃችንን ወደ እርሱ ዕለት ዕለት መቅረባችንን
እንደ ልመና ይቆጥርልናል፡፡ ይህ ሃሳብ በውስጣችን በልባችን መሻት የተረጋገጠ ነውና፡፡ በውስጣችን በልባችን “መቼ ይሆን ሥጋህን
የምበላው ደምህንም የምጠጣው” ብለን ብንሻ እርሱ ይህንን የልባችንን መሻት አውቆ ወዶ ይፈጽምልናል፡፡
ለዚህ ትልቁ የነግህ ምስጋችን
ማረጋገጫ ጥንተ ፍጥረት አዳምን መውሰድ እንችላለን፡፡ አዳም የተፈጠረው ሰማይ እና ምድር ብርሃናት እና እንስሳት ሁሉም ሥነ ፍጥረታት
ከተፈጠሩ በኋላ በመጨረሻው ቀን ዐርብ ዕለት ነው፡፡ አዳም የሚበላው የሚጠጣው የሚለብሰው ነገርን ይፈልጋል፡፡ ልብሱስ ከጸጋው ከተገፈፈ
በኋላ ነው እንጅ ከዚያ በፊትስ የጸጋ ልብሱን ተጎናጽፎ ይኖር ነበር፡፡ ስለዚህ አዳም ሳይፈጠር አዳም የሚሻውን ነገር አውቆ እግዚአብሔር
ሥነ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጠረለት፡፡ ከዚህም በኋላ አዳም ረዳትን ፍጠርልኝ ብሎ እግዚአብሔርን ሳይለምነው አዳም የሚያስፈልገውን የሚሻውን
ነገር አውቆ እግዚአብሔር አምላክ “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና ረዳት የምትሆነውን እንፍጠርለት” ብሎ ከግራ ጎኑ
ሄዋንን ፈጠረለት፡፡ አባታችን አዳም ረዳቱ ሄዋን እንድትፈጠርለት ሲለምን በመጽሐፍ አልተጻፈልንም እግዚአብሔር ግን አዳም የሚሻውን
አውቆ ሰጠው እንጅ፡፡ በእኛ ሕይወት ዘንድም ያለው ይኸው ነው፡፡
ሁላችንንም ወደ ማስተዋል
ጎዳና ይመልሰንና እግዚአብሔር አምላክ እኛ ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ የሰጠን ስንቱን ነገር ነው? በእውነት ራቁታችንን ወደዚች
ዓለም የተቀላቀልን እኛ የአዳም ዘሮች የመጀመሪያውን ልብሳችንን ፈጣሪያችን ያለበሰን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ ሰጠን?
በእውነት እጅ እግራችንን፤ ዓይን ጆሯችንን ሌሎችንም የአካል ክፍሎቻችንን ጤናማ አድርጎ የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን
አውቆ? በዐርባ በሰማንያ ቀናችን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ ልደት መወለድን የሰጠን ለእርሱ ልጆቹ እንድንሆን
የመረጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ዕድሜን ለንስሐ ዘመንን ለፍስሐ እየሰጠ እስካሁን ድረስ በቸርነቱ ጠብቆ ያቆየን
ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ከህጻንነት ለጋ አስተሳሰብ ወደ ጉልምስና ጠንካራ አስተሳሰብ እና አዋቂነት ጠብቆ ያደረሰን
ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ አደረገልን? በመንፈሳዊው እውቀት
አጎልምሶ ከአላዋቂነት ወደ አዋቂነት፤ ከተማሪነት ወደ መምህርነት፤ ከምእመንነት ወደ ካህንነት ማዕረግ ከፍ ከፍ ያደረገን ለምነነው
ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ አደረገልን? በዓለማዊው እውቀትም እንዲሁ በአእምሮ አጎልምሶ ከተማሪነት ወደ ተመራማሪነት ከአንደኛ
ክፍል ወደ ሁለተኛ ከዚያም ወደ ኮሌጅ ከዚያም ወደ ዩኒቨርሲቲ ያደረሰን ዲፕሎማ፤ ዲግሪ እንድናገኝ የረዳን ለምነነው ነው ወይስ
የምንሻውን አውቆ ሰጠን? የዘላለም ርስት መንግሥተ ሰማያትን የምንወርስበትን ሥጋውን እና ደሙን እንኩ ብሉ እንኩ ጠጡ ብሎ የሰጠን
ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ከኃጢአት ከርኲሰት ጠብቆ በቅድስና እንድንኖር የረዳን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ
ሰጠን? የምንበላውን የምንጠጣውን የምንለብሰውን ይህን ሁሉ ነገር የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? እኛ ከማናየው
እርሱ ከሚያየው፤ እኛ ከማናውቀው እርሱ ከሚያውቀው መከራ ሁሉ በቸርነቱ የጠበቀን እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ለሞት
ከሚያበቃ ከባድ በሽታ ታድጎ በጤንነት የጠበቀን እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? የትዳር ጓደኛችንን (ለሴቶች ባልን
ለወንዶች ሚስትን) የሰጠን እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? የተባረከ ትዳርን ሰጥቶ በልጆች መወለድ ፍቅራችንን ያጠነከረልን
እኛ ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? እሳትን በጉያችን ታቅፈን ከፍትወታት እኲያት ጠብቆ በንጽሕና በድንግልና እንድናገለግለው
ጽናቱን የሠጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? ግርማ ሌሊቱን ድምጸ አራዊቱን ጸብአ አጋንንቱን ሳንፈራ ጤዛ ልሰን ድንጋይ
ተንተርሰን በበረሃ ወድቀን በዋሻ በዓት ዘግተን እንድንኖር ጽናቱን የሰጠን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? በኃጢአት ተዘፍቀን
የጽድቅን ፀሐይ እንዳንመለከት አንገታችንን ከደፋንበት እና ካቀረቀርንበት ቦታ ፈልጎ ሸክማችሁ የከበዳችሁ ኑ ወደ እኔ ብሎ በንስሐ
ያራገፈልን ለምነነው ነው የምንሻውን አውቆ? ከመቅሰፍት ጠብቆ እስካሁን ድረስ ያቆየን ለምነነው ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ? “በምድር
ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ ነው፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይም የተፈታ ነው” የሚለውን የማሰር እና የመፍታት ስልጣን የሰጠን ለምነነው
ነው ወይስ የምንሻውን አውቆ?
No comments:
Post a Comment