Wednesday, May 3, 2017

ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን በመብላትሽ ደስ አለኝ

© መልካሙ በየነ

ሚያዝያ 25/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ሔዋን ሆይ በገነት መካከል ሦስት ዛፎች እንደነበሩ ከእኔ ይልቅ አንች ታውቂያለሽ፡፡ አዳም ግን ከአንች ቀድሞ ይህንን ሁሉ ያውቅ ነበርና ስለዕፅዋት ሁሉ አስቀድሞ ነግሮሻል፡፡ ይህንን ብሉ ተብለናል እንበለዋለን አለሽ፡፡ ይህንን ግን አትብሉ የበላችሁት ጊዜ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ብሎ አዝዞናል እና እንጠብቀዋለን እንጅ አንበላውም አለሽ፡፡ ስለሦስተኛው ዕፅ ግን ብሉም አትብሉም አልተባልንም ብሎ ነበር የነገረሽ፡፡ በምክረ ከይሲ ተታልለሽ አንች ግን የበላሽው የተከለከላችሁትን ነበር፡፡ ብሉም አትብሉም ብሎ ያላዘዛችሁን ዕፅስ በልታችሁ ቢሆን ኖሮ የሕይወት ዕፅ ነበርና ከገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ያሸጋግራችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን አትብሉ የበላችሁት ጊዜ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ያለሽን ዕፅ ዕፀ በለስን በመብላትሽ ወደ ምድር ተሸጋገርሽ፡፡ ከተድላ ቦታሽ ከገነት ወጣሽ፡፡
ሔዋን ሆይ! አንችን ይበልጥ ያስተዋልሁሽ ይበልጥም የተረዳሁሽ በበዓለ ደብረ ዘይት ነው፡፡ ቅዳሴውን ላስቀድስ እነሆ ከቤተ ክርስቲያን ቆምሁ፡፡ ካህኑም የአትናቴዎስን ቅዳሴ ሲያነብልን ሰማሁ፡፡ ሊቁን ወደ አንች እና ወደ አዳም ምሥጢር ስቦ አስገባው፡፡ እርሱም እንዲል አለ፡፡ “አዳም ሆይ የሞት ፍርድን ያመጣህብን ምን አደረግንህ፡፡ አዳም ሆይ ደስታ ባለበት በገነት ጌታ ማደሪያ ደስ ይለን ዘንድ ያልተውኸን ምን አደረግንህ” ብሎ አዳምን ወቀሴታ በመሰለ ቃል አነሣው፡፡ ከዚያም ወዳንች ተመለሰ እንዲህም አለሽ “ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ እነሆ በኃጢአት ብዛት ሥጋችን ጠቆረ በሰማያውያን አምሳል በኖርነ ነበረ፡፡ ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ እነሆ ልጆችሽ በጭንቅና በሕማም በወለዱ ጊዜ ያለቅሳሉ አንች ያቺን በገነት ያለችውን እንጨት እንዳደማሻት ይደማሉ” ብሎ የወቀሴታ በመሰለ ቃል ተናገረሽ፡፡ ከዚያም ማንም የማይለያችሁ አንድ አካል አንድ ሥጋ ሆናችኋልና በጋራ እንዲህ አላችሁ “አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተን እንነቅፍ ዘንድ የሚቻል አይደለም እኮ! አንደበትን እየተናገሩበት ሊሰድቡበትና ሊነቅፉበት እንዳይቻል እንደዚህም እናንተ እኛን ናችሁ እኛም እናንተን ነን” አለ፡፡ እውነት ነው ሊቁ ጨርሶታል፡፡  እናንተን እንነቅፍ ዘንድ እኛ ከየት ተገኘን? እኛ ከእናንተ ባሕርይ የተገኘን ነንና እናንተን የምንነቅፍበት አንደበት ከቶ የለንም፡፡ ቀጥሎም እንዲህ አለ “አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ ይቅር ባይ በሆነ ጌታ ተግሣፅ ንስሐ ገብታችኋል፡፡ አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ በውነት ድናችኋል በተበጃችሁ በጌታ ደም ያለመከልከል ወደ ቀደመ ርስታችሁ ገብታችኋል፡፡ በተበጃችሁ በጌታ የማያምኑ ዐላውያን ሁሉ ልጆቻችሁ አይደሉም፡፡ አርአያችሁ ምሳሌያችሁ ናቸው እንጅ፡፡ በአንድ ልጃችሁ ያመን እኛ ግን በእውነት ከወገባችሁ የወጣን አርአያችሁ ምሳሌያችሁ ነን፡፡ እነሆ እኛን ልጆቻችሁን ኃጢአት እንደ እሳት በላችን፡፡ ፍትወትም አቃጠለችን፡፡ የነፍስ ፍትወት አይደለም የሥጋ ፍትወት ነው እንጅ፡፡ ይኸውም ነፍስን የሚያጠፋት ነው” አለ፡፡ እኔም እንዲህ እላችኋለሁ “አዳምና ሔዋን ሆይ እኛማ ከእናንተ ባሕርይ የተገኘን አይደለንምን? አርአያችሁ ምሳሌያችሁስ አይደለንምን? ታዲያ እናንተን እንነቅፍ ዘንድ ምን ያበረታናል፡፡ እናንተስ ስለ በደላችሁት በደል ተጸጽታችሁ ንስሐ ገብታችኋል፡፡ እናንተስ ከልጅ ልጃችሁ በተወለደ ጌታ ድናችኋል፡፡ እናንተስ ተድላ ገነትን ዳግም አግኝታችኋል፡፡ የእናንተን ክብር ያላገኙትን አርአያና ምሳሌያችሁ ብቻ የሆኑትን ከአብራካችሁ ያልተገኙትን ዐላውያን እንነቅፋቸዋለን እንጅ፡፡ እናንተስ የምትነቀፉ የምተውቀሱ አይደላችሁም እኮን”
ሔዋን ሆይ እኔም አመሰግንሻለሁ፡፡ እኔ ግን የማመሰግንሽ ዕፀ በለስን በመብላትሽ ነው፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ ገነት መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባኝን ርኅርኅተ ልብ ድንግል ማርያምን ባላገኘኋት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ የአምላኬን ፍቅር ባልተረዳሁት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ እንካችሁ ሥጋየ ብሉት እንካችሁ ደሜ ጠጡት ያለንን አምላክ ባላየነውም ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ አፍሽ በዕፀ በለሱ ባይረክስ ኖሮ ቀድሶ ገነት መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባንን የክርስቶስ ሥጋውን ባልበላንበት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ አፍሽ በዕፀ በለሱ ባይረክስ ኖሮ ቀድሶ ገነት መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባንን የክርስቶስ ደሙን ባልጠጣንበት ነበር፡፡ ሔዋን ሆይ ዕፀ በለስን ባትበይ ኖሮ ከሽህ ዘመን በኋላ ዕፀ ሕይወትን በልተሽ ታድሰሽ ከነልጆችሽ መንግሥተ ሰማያት በገባሽ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀድመሽ ዕፀ በለስን በላሽ ምክንያተ ስህተት እያሉም ወንዶች ተሳለቁብሽ፡፡ ድንግል ማርያም ከአንች ባሕርይ ስትወለድ ግን ምክንያተ ድኅነት ብለው ተመኩብሽ፡፡ ሔዋን ሆይ እኔስ አልወቅስሽም አልነቅፍሽምም፡፡ ሔዋን ሆይ ባሕርይሽ ባሕርየ ነውና ደካማነቴን አውቀዋለሁ፡፡ ሔዋን ሆይ ባሕርየ ከአንች ባሕርይ ጋራ አንድ ስለሆነ ዕፀ በለስን ለምን በላሽ አልልሽም? ሔዋን ሆይ በአንች ምክንያት ገነት ተዘግቶብን በፍዳ ብንያዝም ከአንቺው በተወለደች ልጅሽ ፍዳችንን መርገማችንን አራግፈን ገነትን ወረስናት፡፡ ዕፀ በለስን በመብላትሽ የተነሣ ድንግል ማርያምን የምታህል አምላክን ለመውለድ በቅታ የተገኘች እናትን አግኝቻለሁና የጌታየንም ልዩ ፍቅር ተመልክቻለሁና ሔዋን ሆይ! ስለዚህ ነገር ዕፀ በለስን በመብላትሽ ደስ አለኝ፡፡ 

No comments:

Post a Comment