© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ
26/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አንዳንድ ወገኖች በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ስለሚከናወኑ ጥፋቶች እና የጥፋቱ ፈጻሚዎችን በተመለከተ
በምጽፋቸው ጽሑፎች ላይ በመረጃ ላይ ባልተመሠረተ ድፍን አመለካከት ጭፍን አስተያየት ሲሰነዝሩ ስመለከት በግልጽ ማብራራት
እንደሚያስፈልግ አሰብሁ፡፡ በተለይ በምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት በአቡነ ማርቆስ ላይ በጻፍሁት ትችት ላይ
አንዳንዶች በጥልቀት ሳይመለከቱ አስተያየታቸውን ወርውረዋል፡፡ አስተያየታቸው በዋናነት የሚያተኩረው “ወደ ላይ አትፍሰስ ጳጳስን
ትገስጽ ዘንድ አንተ ማነህ?” የሚል ነው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ይህንን አስተያየት በሰጡበት ጽሑፍ ላይ መልስ ሰጥቸበታለሁ ነገር
ግን ሁሉም ሰው ግልጽ መሆን ስላለበት ደግሜ እጽፈዋለሁ፡፡ እኔ አንድ ተራ ሰው እንደሆንሁ አውቃለሁ፡፡ ብሉያቱን ሐዲሳቱን
ከጉባዔ ቁጭ ብየ አልቀሰምኩም፡፡ ዕውቀቱ የለኝም፡፡ እናንተ በገለጻችሁበት ቋንቋም ልግለጽላችሁ አወ ምንም የማላውቅ ደንቆሮ
ነኝ ነገር ግን ሃይማኖቴን፣ ቤተ ክርስቲያኔን አውቃታለሁ፡፡ እርሷ በምን ላይ እንደተመሠረተች የእምነት መሠረቷ ምን እንደሆነም
ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ አንድ አባትም እንደ አባትነቱ ምን ማድረግ እንዳለበት የእናንተን ያህል ባይሆንም ፍትሐ ነገሥቱን፣
ዲድስቅልያውን አንብቤዋለሁ፡፡ አንድ ልጅም እንደ ልጅነቱ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲሁ አንብቤያለሁ፡፡ “ዲቁና አልሰጥህ
ስላሉ ነው ከእርሳቸው ጋር የተጣላህ” የሚሉም አንዳንድ ሞኞች አሉ፡፡ እኔ አውቄ ተምሬ ከተገኘሁ አምላክም ለዚህ የክህነት
አገልግሎት ከመረጠኝ ዲቁናውን ለማምጣት የግድ ከአቡነ ማርቆስ እግር ሥር መውደቅ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ እኔ ምንም እንኳ
ባልጠቅምበትም ዲቁና ያመጣሁት ጥር17/2000 ዓ.ም ነው ከዛሬ 9 ዓመት በፊት ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ “በሠላሳ ዓመትህ ዲቁና
አልሾምህ” ስላሉ ነው የምትሉ ወገኖች ፋይላችሁን በዚሁ ዘጋሁት፡፡
“ወደ ላይ አትፍሰስ ጳጳስን ትገስጽ ዘንድ አንተ ማነህ?” የሚለውን ፋይል ስከፍተው የማይረባ ብሂል
ሆኖ አገኘሁት፡፡ በዚሁ ልዘጋው አሰብኩና ብዙ የሚጻፍበት እንደሆነ ሳገኘው ፋይሉን በጥልቀት ተመለከትሁት፡፡ ወደ ጥንተ
ፍጥረትም አባቴ ኤጲፋንዮስ እጄን ይዞ አክሲማሮስን ግለጠው አለኝ እኔም መጽሐፉን ተመለከትሁ፡፡ ሳጥናኤል አሐዜ መንጦላእት
አቅራቤ ስብሐት የመላእክት ሁሉ አለቃ ነበረ አለኝ፡፡ ታዲያ የመላእክት ሁሉ አለቃ የሆነው ሳጥናኤል “እኔ ፈጣሪ ነኝ” ብሎ
ራሱን አምላክ ካደረገ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ካልሆነ በቀር ከማን ጋር ትሰለፋለህ አለኝ? እኔም ሰልፌን ከቅዱስ ገብርኤል ጋር
አደርጋለሁ አልኩት፡፡ ማዕርግ ክህደትን ሊደብቅ የሚችል ተራራ ቢሆን ኖሮ የሳጥናኤልን ክህደት ሊቀመላእክትነቱ አቅራቤ
ስብሐትነቱ አሐዜ መንጦላእትነቱ በሸፈነለት ነበር፡፡ በጭፍኑ የምትከራከሩ ሰዎች ልብ በሉ አሁን የነቀፍሁት ሳጥናኤልን እንጅ
ሊቀ መላእክትነትን ወይም አቅራቤ ስብሐትነትን ወይም አሐዜ መንጦላእትነትን አይደለም፡፡
የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ሐዋርያ ተብሎ ስለተመረጠ ሰው ነገረኝ፡፡ ስሙም
ይሁዳ ይባላል አለኝ፡፡ ይሁዳ አባቱን የገደለ እናቱን ሚስት ያደረገ ሰው ነበር አለኝ፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ባይ አምላክ ነውና
ይህንን ኃጢአቱን ትቶ ከእኛ ጋራ ሐዋርያ ብሎ ሾመው መረጠው፡፡ ነገር ግን በሠላሳ ብር ይህንን ይቅር ያለውን፤ ሐዋርያ ብሎ
የመረጠውን ጌታ ለአይሁድ ካህናት አሳልፎ ሰጠው፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ይሁዳ ሐዋርያ የሚለውን ማዕርግ ስለተሸከመ እርሱን ብመስል
እኔን ጴጥሮስን ትቀበለኝ ነበርን አለኝ፡፡ እኔም አንተንስ እውነተኛ ሐዋርያ ነህ ብየ የተቀበልሁህ ይሁዳን ስላልመሰልህ እና “አንተ
ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለህ ስለመሰከርህ ነው አልኩት፡፡ ማዕርግ ክህደትን የሚሸፍን ቢሆን ኖሮ ይሁዳን
የሐዋርያነት ማዕርጉ በደበቀለት ነበር፡፡ ልብ በሉ አሁን የነቀፍሁት ይሁዳን እንጅ ሐዋርያነትን አይደለም፡፡
አሁን ደግሞ በማዕርግ ወደሚመስሏቸው ነገር ግን ስለክህደታቸው ወደተነቀፉ ሰዎች አባቴ ኢትዮጵያዊው
ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ና ብሎ መጽሐፈ ምሥጢርን አንብብ አለኝ፡፡ እኔም መጽሐፉን ገለጥሁ እና በመጀመሪያ አንቀጹ
ስለዘረዘራቸው ጳጳሳት እና ክህደታቸው አነበብሁ፡፡ እንዲህም የሚል ንባብ አገኘሁ፡፡ አቡናርዮስ የሎዶቅያ ጳጳስ ነበረ ነገር
ግን “አብ እና ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ ገጽ ናቸው” በማለት አንድ ገጽ ብሎ አስተማረ፡፡ አርዮስ የሊቢያ ቄስ ነበረ ነገር
ግን “ክርስቶስ ፍጡር ነው” ብሎ ካደ፡፡ ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ነበረ ነገር ግን “ወልድ ከነቢያት እንደ አንዱ
ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በዮርዳኖስ ባደረበት ጊዜ በጸጋ አምላክ ሆነ” በማለት ካደ፡፡ ፎጢኖስ የበሚርና ጳጳስ ነበረ ነገር
ግን “የወልድ ሕልውና ከማርያም ከተወለደ ወዲህ ነው” በማለት ካደ፡፡ ሳዊሮስ የሕንድ ቴዎዶስዮስ ደግሞ የእስክንድርያ ጳጳስ
ነበሩ ነገር ግን “የእግዚአብሔር ልጅ ያለፈቃዱ በግድ ሞተ” ብለው ካዱ፡፡ ልዮን የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “ሥጋ
ከመለኮት ያንሣል” በማለት ካደ፡፡ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ ጳጳሳት ነበሩ ነገር ግን “መለኮት
እና ሥጋ በሁለት መንገድ በሁለት ሥርዓት ናቸው” ብለው ካዱ፡፡ በማለት አስረዳኝ፡፡ አባቴ አባ ጊዮርጊስም ታዲያ በማዕርጋቸው
ተመክተህ ጳጳሳት ናቸው ካህናት ናቸው ብለህ ከአቡናርዮስ፣ ከአርዮስ፣ ከንስጥሮስ፣ ከፎጢኖስ፣ ከሳዊሮስ፣ ከቴዎዶስዮስ፣ ከልዮን
እና ከኬልቄዶን ማኅበርተኞች ጋራ ትሰለፋለህን አለኝ፡፡ እኔም እነርሱስ ከሐድያን ናቸውና አብሬያቸው አልሰለፍም አነርሱንም
አልመስልም አልኩት፡፡ ወገኖቼ! ማዕርግ ክህደትን የሚሸፍን ቢሆን ኖሮ እነአቡናርዮስ፣ እነአርዮስ፣ እነንስጥሮስ፣ እነፎጢኖስ፣
እነሳዊሮስ፣ እነቴዎዶስዮስ፣ እነልዮን እና የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳት እና ፓትርያርኮች ስለነበሩ
ክህደታቸው በተሸፈነላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ልብስ ቢሸፍኑትም በልብስ ላይ ብቅ እንደሚለው ለምጽ ክህደታቸው በአደባባይ
ተጋልጧል፡፡ አሁንም ልብ በሉልኝ እኔ የነቀፍኋቸው እነአቡናርዮስን፣ እነአርዮስን፣ እነንስጥሮስን፣ እነፎጢኖስን፣ እነሳዊሮስን፣
እነቴዎዶስዮስን፣ እነልዮንን እና የኬልቄዶን ማኅበርተኞችን እንጅ ማዕርጋቸውን ጵጵስናቸውን፣ ሊቀጵጵስናቸውን፣ ፕትርክናቸውን
አይደለም፡፡
አቡነ ማርቆስን በተመለከተም የጻፍሁት ይህንኑ ነው፡፡ እኔ አስተያየት ከሰጣችሁኝ ሰዎች ይበልጥ በቅርበት አውቃቸዋለሁ፡፡ ማዕርጋቸው ትልቅ ነው አውቃለሁ፡፡ የተሰጣቸው
አደራ እና ኃላፊነት እጅግ ከባድ ነው አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን አልተጠቀሙበትም አላገለገሉበትም፡፡ እኔም እርሳቸውን የነቀፍሁት
ስም እንጅ ግብር ስለሌላቸው ብቻ ነው፡፡ ልብ በሉልኝ ጵጵስናውን አልነቀፍሁም፤ ሊቀ ጵጵስናውን አልነቀፍሁም እርሳቸውን “አባ
ማርቆስን” ግን እነቅፋለሁ፡፡ እንዲያውም ቅስና ስለሌለኝ ገና ዲቁና ላይ ስለቀረሁ እንጅ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ የማሰር ሥልጣን
አሥራቸው እገዝታቸው አወግዛቸውም ነበረ፡፡ ይህ እኮ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው አባታችን የዲማው ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ አቡነ
ጳውሎስን ያወገዙ ለምን ይመስላችኋል? አቡነ ጳውሎስ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ክብራቸውን አዋርደው ከሮማው ፖፕ መስቀል
ስለተሳለሙ አይደለምን? አቡነ ማርቆስም በሐገረ ስብከቱ ውስጥ እያደረሱት ያለው ጥፋት ቀላል አይደለም፡፡
እኔ ለእርሳቸው ጭፍን የሆነ ጥላቻ ያለኝ የሚመስላችሁ ሰዎች ምንም ዓይነት ጥላቻ የለኝም፡፡ ሹመት ማዕርግ
ሽቼ እርሳቸውን ደጅ እየጠናሁ ያለሁ ሰው አይደለሁም፡፡ የምተዳደረውም ከቤተክርስቲያን ከሚሰጠኝ ገንዘብ ሳይሆን በመንግሥት
መሥሪያ ቤት ተቀጥሬ ከማገኘው ደመወዝ ነው፡፡ ታዲያ በምን ልጠላቸው እችላለሁ? አባትነታቸውን በአግባቡ ስላልተጠቀሙበት ብቻ
ነው የጻፍሁት፡፡ በሐገረ ስብከታችን ምን ጥፋት አደረሱ ካላችሁኝ አንድ በአንድ መጻፍ እችላለሁ፡፡
1. የቅብዓት ሃይማኖት እንዲስፋፋ በመጣር
ላይ መሆናቸው፡፡ ለዚህም “ወልደ አብ” እና “ዝክሪ እና ጳውሊ” የተሰኙ መጻሕፍት በቤተክርስቲያናችን ስም ሲታተም ዝም
ማለታቸው፡፡ መጻሕፍቱ እንዲወገዙልን እና መልስ እንዲሰጥባቸው በደብዳቤ የጠየቅናቸው ሲሆን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ
አለመስጠታቸው ይህንን አስተምህሮ እንደሚደግፉ ማረጋገጫ መሆኑ፡፡
2. ጉንደወይን ከቤተክርስቲያን መድረክ
ላይ ቆመው “ሞኞች ካሌንደር ሲያወጡ ይውላሉ፡፡ ገናን በ28 እናከብራለን ይላሉ፡፡ አያችሁ እነዚህ ካሌንደር የማያውቁ ሰዎች
ጥምቀትን እኮ ጥር 10 አድርገውት አረፉ” በማለት ሕዝቡን ሲያስጨበጭቡ የሚያሳይ መረጃ እጃችን ላይ መሆኑ፡፡
3. ተዓምረ ማርያም ላይ የተገለጹትን
የእመቤታችን 33ቱ በዓላት አታንብቡ ይህ ካሌንደር እኮ ነው በማለት በምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሥር ባሉ በተለይ የከተማ
አብያተ ክርስቲያናት አለመነበባቸው፡፡
4. ገንዘብ ካለህ ደህና ገንዘብ ካቀረብህ
በአቡነ ማርቆስ ዘመን ሹመት ማግኘት ቀላል ነው የሚባልበት ሐገረ ስብከት እንዲሆን ማድረጋቸው፡፡ እዚህ ላይ አንድ መምህር
የተናገረውን መጻፍ እፈልጋለሁ፡፡ መምህሩ ሊቀጠር እርሳቸው ዘንድ በፖስታ አሽጎ ገንዘብ ይዞ ይሄዳል፡፡ ከዚያም ፖስታውን
ክፈተው እስኪ ይሉታል፡፡ እርሱም ይከፍተዋል ስንት ነው ቁጠረው ይባላል 3500 ብር ነው፡፡ “አይ እኔ እኮ ደህና ብር ይዘህ
የመጣህ መስሎኛል” አሉት፡፡ ይህንን የተናገረው ደግሞ ራሱ ሊቀጠር የሄደው መምህር ነው፡፡
5. በየአጥቢያው የሚገኙ አስተዳዳሪዎች
በሙሉ የሥጋ ዘመዶቻቸው ሆነው መገኘታቸው፡፡ ዝምድናቸው የሚያስነቅፍ ባይሆንም እነዚህ የተሾሙት በሙሉ በየአጥቢያው ሕዝቡን
እያስቸገሩ መገኘታቸው፡፡ ለምሳሌ ገዳመ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የመደቡት “መልአከ መንክራት አባ ፍቅረ
ማርያም” በቤተክርስቲያኑ የሰንበት ትምህርት ቤትን በመዝጋቱ ወንድሙን ያለሰበካ ጉባዔው ፈቃድ በመቅጠሩ ከባድ ተቃውሞ
እንደደረሰበት እና አሁን ደግሞ እዚሁ ደብረ ማርቆስ ጌቴሴማኒ ፈረስቤት መድኃኔዓለም ማዛወራቸው፡፡ እዚህ መድኃኔዓለም አዲስ
ሕንጻ ቤተክርስቲያን እየተገነባ ነው ከዚህ ገንዘብ ለመቃረም ሊሆን አንደሚችል አመላካች ነው፡፡
6. በሐገረ ስብከቱ ውስጥ የሙታን
መታሰቢያ በእህል በውኃ መሆኑ ቀርቶ በገንዘብ እየተቀየረ ለቤተክርስቲያን ገቢ እንዲደረግ የሚል አዋጅ ማውጣታቸው፡፡ በዚህም አስተዳዳሪ
ብለው በሾሟቸው ሰዎች በኩል እየተሰበሰበ ገቢ እንዲደረግላቸው ማድረጋቸው፡፡ ልብ በሉ ድሆች የሚመገቡትን እና ሙታንን ነፍስ
ይማር የሚሉበትን እህል ውኃ ነው፡፡ ማርያም እንተ እፍረት በጌታ እግር ላይ ሽቱ እያፈሰሰች በእንባዋ እያጠበች ስታለቅስ ይሁዳ
“ይህን የ300 ብር ሽቱ ከምትደፋው ተሸጦ ለድሆች ቢሆን ይሻል ነበረ” አለ ይሁዳ እንዲህ ያለው ለድሆች አዝኖላቸው አስቦላቸው
አልነበረም፡፡ ወደ ገንዘብ ከተቀየረ ከ10 አንድ ያገኝ ነበረ እና 30 ብር ቀረብኝ ብሎ ነው፡፡ እኒህም ያንኑ ነው
ያደረጉት፡፡
7. ሕዝቡ መምረጥ የሚገባቸውን የሰበካ
ጉባዔ አባላት ቃለ ዐዋዲውን በመጣስ በራሳቸው ፈቃድ በደመወዝ እየቀጠሩ የዚህ አጥቢያ የሰበካ ጉባዔ ሰብሳቢ የዚህ ሰበካ ጉባዔ
ፀሐፊ ወዘተ እያሉ መመደባቸው፡፡
8. የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን
አዳራሾቻቸውን በጥበቆች በማስዘጋት እንዲወጡ መደረጋቸው፡፡ የዐቢይ ጾምን የሌሊት ስግደት ሙሉ በሙሉ ማስቆማቸው፡፡
9. የግቢ ጉባዔ ተማሪዎች በየትኛውም
አጥቢያ ቤተክርስቲያን የኮርስ ትምህርታቸውን እንዳይማሩ መከልከላቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንንም ገንዘብ እንዲሰበስብላቸው ሲፈልጉ
ብቻ እንደሚጠቀሙበት፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እንዲዘጋ ሰበካ ጉባዔያትን ማወያየታቸው፡፡
10. በደብረ ማርቆስ ከተማ ሊገነባ
ለታቀደው ባሕረ ጥምቀት ህዝቡ የመረጣቸው ጠንካራ ኮሚቴዎች ስድስት ወር ባልሞላ የሥራ ዘመን ከ100 ሺህ ብር በላይ
መሰብሰባቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኮሚቴዎች ለእርሳቸው አምስት ሳንቲም ማቅመስ ባለመቻላቸው ባላወቁበት መንገድ
መሻራቸው እና ራሳቸው እንደፈለጉ በሚያዝዟቸው (ገንዘብ ስጡኝ ሲሏቸው የሚሰጡ ማለቴ ነው) መተካታቸው፡፡
11. በአርምሞ እና በጽሙና ሊጾም በሚገባው ዐቢይ ጾም መድረክ ላይ ወጥተው
ሲያስጨበጭቡና እልል ሲያስብሉ መክረማቸው፡፡
12. ያረጁ አብያተ ክርስቲያናትን ለማደስ
በሚጀምሩ ሰበካ ጉባዔዎች ላይ የእድሳት እና የግንባታ ፈቃድ በማለት ከ7000 ብር በላይ መጠየቃቸው፡፡ አዲስ አብያተ
ክርስቲያናትን ለመባረክ ሲጠሩም ከ10ሺህ ብር በላይ መጠየቃቸው፡፡
13. ሕጋዊ ባልሆኑ ደረሰኞች በርካታ
ገንዘብ ማሰብሰባቸው፡፡
14. በሐገረ ስብከታቸው የሚገኙ ገዳማትን
በእኩል ዓይን አለመመልከታቸው፡፡ ዲማ ጊዮርጊስን፣ ደብረ ኤልያስን፣ ሥላሴ ገዳምን (ደብረ ኤልያስ ውስጥ የሚገኝ) ፣ገነተ
ቅዱሳን አዲሱ መድኃኔዓለምን እና የመሳሰሉትን ገዳማት እና አድባራት በማስጠንቀቂያ በማስፈራራት አስተዳዳሪዎችን በማሸማቀቅ ላይ
መሆናቸው፡፡ ሚያዝያ 23/2009 ዓ.ም ይከበር የነበረውን የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ለማደናቀፍ በማሰብ በየአጥቢያው “ዲማ
የምትሄዱ ሰዎች ያለእኔ ፈቃድ እንዳትንቀሳቀሱ” የሚል መልእክት ማስተላለፋቸው፡፡ ቁራሽ ለምነው ለተማሩበት ገዳም ለመርጡለ ማርያም
ገዳም ግን ጥር 21 ለሚከበረው የእመቤታችን የእረፍት በዓል በየአጥቢያው
“ኩንትራት መኪና አዘጋጅተናል ተመዝገቡ” ብለው መቀስቀሳቸው፡፡ ለዚህ መቀስቀሳቸው ለዚያ አትሂዱ ማለታቸው እኩል የሚመለከት
ዓይን እንደሌላቸው ማሳያ ነው፡፡ ጥንታዊቷን ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳምን እየነቀፍሁ ለምን ሄዳችሁ እያልሁ
አይደለም፡፡ ማን ከልካይ አደረገኝና ዓይናቸው እኩል አለመሆኑን ነው የተናገርሁ፡፡
15. ከእኔ ከጳጳሱ ውጭ ማን መጥቶ
ያስተምራችሁ በማለት የዋሐንን የአባቶቻችሁን እምነት ያዙ ዳግመኛ ጥምቀት የለም በማለት ቅብዓትን ለማስፋፋት መጣር ላይ የሚገኙ
መሆናቸው፡፡
16. እርሳቸውን የሚቃወሙ ካህናትን፣
ዲያቆናትን፣ መነኮሳትን ከአገልግሎት በማገድ ደመወዝ በመከልከል በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረጋቸው፡፡
ለዚህም እስከ ክልል ድረስ እርሳቸውን ከስሰው የሚሟገቱ አሉ፡፡
17. ጉባዔ የሰፋላቸውን ተማሪ የበዛላቸውን
የአብነት ትምህርት ቤት መምህራን የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አድርገው በመሾም ጉባዔው እንዲፈታ ተማሪው እንዲሰደድ
ማድረጋቸው፡፡ አብነት ትምህርት ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጦርነት መክፈታቸው፡፡
18. የተሐድሶ መናፍቃንን የሰንበት
ትምህርት ቤት መምሪያ ኃላፊዎች እያደረጉ መመደባቸው፡፡
እኔ ከብዙው በጥቂቱ ይህንን ጻፍሁላችሁ፡፡ ስለዚህም የምነቅፋቸው በዚህ እና በመሳሰለው ግብራቸው እንጅ
አባት መሆናቸውን ጳጳስ መሆናቸውን ዘንግቸው አይደለም፡፡ “አዲስ የሚመረጡትን ትኮንናለህ የተሾሙትንም ትኮንናለህ አንተ
ጵጵስናውን ትይዘው” ያላችሁኝም አላችሁ፡፡ እኔ ጳጳስ ልሁን አላልኩም ጳጳስ ምን ማድረግ እንደሚገባው ግን ተናገርሁ፡፡
ቤተክርስቲያናችን የእውቀት ማዕከል ናት፡፡ ሥርዓት አላት መመሪያ መተዳደሪያ አላት፡፡ ከዚህ ውጭ ልምራ ልመራ ልተዳድር
ላስተዳድር እንደፈለግሁ ልሁን ማለት አይቻልም፡፡ እውነትን እውነት ብለን መናገር መድፈር ካልቻልን “የኢሳይያስ ለምጽ” በእኛ
ላይም እንደሚያድር አትጠራጠሩ፡፡ ዮሐንስ በራዕዩ የሰርዴሱን የቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲገስጽ ከእግዚአብሔር መልእክት መጣለት
ራእ 3÷1 ላይ “…ሥራኽን አውቃለሁ ሕያው እንደመሆንህ ስም አለኽ ሞተኸማል” በል አለኝ ይላል፡፡ አሁንም ልክ እንደዚሁ ነው
እየሆነ ያለው ነገር፡፡ እርሳቸው “ሊቀ ጳጳስ” የሚለውን ሕያው ስም ይዘዋል ነገር ግን በምግባር በሃይማኖት ሞተዋል፡፡ ታዲያ
ዝም እንበላቸው ማለት ምን ማለት ነው? እንደእኔ መምከር የሚገባቸው እርሳቸው ናቸው ባይ ነኝ ነገር ግን ጥፋት ከፈጸሙ እኛም
እንመክራቸው ዘንድ ግዴታችን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ የጻፍኩት ለዚሁ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጥፋት በስም በማዕርግ ደብቆ
ማስቀረት አይቻልም፡፡ በዚያ ቢሆንማ ሳጥናኤል መልአክ በመሆኑ ይሁዳም ሐዋርያ በመሆኑ ንስጥሮስም ፓትርያርክ በመሆኑ ይበልጧቸው
ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ተራ ምእመናን ሁሉ ሳንቀር ስናወግዛቸው እንኖራለን፡፡ ምክንያቱም ስራቸው ነዋ! ታስታውሳላችሁ ያኔ
ስለ እነ በጋሻው ስለ እነምርትነሽ ስለ እነ ዘርፌ ስለ እነትዝታው መናፍቅነት ስንጽፍ መዓት ስድብ ታሸክመኑን እንደነበረ፡፡
ዛሬ ግን ለስድቡ እናንተ ትብሳላችሁ፡፡ አባ ላይም ያለው እንዲሁ ነው አንድ ቀን እውነቱን ስትለዩት ያኔ እናንተ ትብሳላችሁ፡፡
እውነቱን ተናገርሁ ያየሁትን መሰከርሁ የሆነውን ሆነ አልኩ የተደረገውን ተደረገ አልሁ፡፡ ከእርሳቸው ከጳጳሱ በላይ አንተ
አታውቅም ዝም በል ለምትሉኝ ግን የመላእክት አለቃ ከነበረው ሳጥናኤል፤ ሐዋርያ ከነበረው ይሁዳ፣ ፓትርያርክ ከነበረው ንስጥሮስ
የተሻልኩ መሆኔን እገልጻለሁ፡፡ እርሳቸውም በእነዚህ መንገድ እየተጓዙ እስካሉ ድረስ ዝም አልልም፡፡ ጨረስኩ፡፡
No comments:
Post a Comment