Tuesday, January 5, 2016

አሻንጉሊት አፍቃሪነታችን ለምን?



© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 26/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በዓላትን ተንተርሰው የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ድሮ ድሮ አባቶቻችን ለዘመን መለወጫ “እንቁ ጣጣሽ” የሚል ስም ያወጡት በዓሉ ብዙ ጣጣ ስለነበረበት ነው ይባላል፡፡ ስለ በዓሉ ክብር ሲባል በጉ፣ ዶሮው፣ ዳቦው፣ጠላው፣ ጠጁ ሁሉም መዘጋጀት ያስፈልገዋል፡፡ ያንን ሁሉ ለማሟላት ደግሞ ገንዘብ ይጠይቃል ስለዚህ ያን ገንዘብ ማግኘት ከባድ ስለሆነ “ጣጣሽ” አሏት፡፡ እኔን የሚቆጨኝ አባቶቻችን ዛሬ ተነሥተው እኛን አለማየታቸው ብቻ ነው፡፡ እኛ በጉ፣ ዶሮው፣ ጠላው፣ ዳቦው፣ ጠጁ ምናችን ነው? ለእኛ እኮ ለዘመናዊዎቹ በዓል ክብር የሚኖረው በዚህ አይደለም በአሻንጉሊቶቹ ነው፡፡ አሻንጉሊቶችን ደርድረን በቀላሉ በዓሉን እንሸውደዋለን እናታልለዋለን የምን ወጭ የምን ጣጣ ነው፡፡ እንደውም አባቶቻችን ለደቂቃ ተነሥተው ቢመለከቱን ባህላችን ባህላቸውን መስሎ ስለማያገኙት “እንቁ ጣጣሽ” ን “እንቁ አሻንጉሊት”፣ “ገና”ንም “አሻንጉሊትና” ፋሲካን ወይም ትንሣኤንም “ኢስተር አሻንጉሊት” ብለው ስም ያወጡልን ነበር፡፡ ለቅጽበት ቢነሡ “በእውነት ልጆቻችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነበርን የቀበሩን?” ማለታቸውም የማይቀር ነው፡፡ ግን ለምን ለአሻንጉሊት ክብርን መስጠት አስፈለገን?
ዛሬ እኮ ሱቆች የተሞሉት ቤቶች ያሸበረቁት በአሻንጉሊቶች ብዛት ነው፡፡ እኔ “ለምን በፍቅረ አሻንጉሊት ተነደፍን” የሚለውን ጥያቄ የምመልስበት የራሴ እይታና አስተሳሰብ አለኝ፡፡ እኔ የምገምተው ለምሳሌ ሕጻናትን የሚመስሉ አሻንጉሊቶችን ታቅፈው የሚያድሩ ሴቶች አሉ ወንዶችም እንዲሁ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ባልና ሚስትም በመካከላቸው እንደ ሕጻን ሕጻናትን ሊተኩ ከሚችሉ አሻንጉሊቶች መርጠው  ሊያስተኙ ይችላሉ፡፡ በዚህ ዘመን ልጅ ለመታቀፍ ልጅ ለማሳደግ ከባድ የሆነባቸው ሰዎች አሻንጉሊት ታቅፈው ኑሮን ይሸውዱታል ያታልሉታል፡፡ ሕጻንን ለማሳደግ ለቁም ነገር ለማብቃት 9 ወር ማርገዝን ከዚያም አምጦ መውለድን ከዚያም ማልበስን መንከባከብን ማብላት ማጠጣትን ይጠይቃል፡፡ አሻንጉሊት ግን ራበኝ አብሉኝ ጠማኝ አጠጡኝ በረደኝ አልብሱኝ ብሎ አያለቅስብንም፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ፍቅረ አሻንጉሊት ያንገበገበን፡፡ እናት አባቶቻችን ስንት ደክመው ስንቱን ወጥተው ስንቱን ወርደው ሳይማሩ አስተምረው ሳይለብሱ አልብሰው ለቁም ነገር ያደረሱን ወልዳችሁ ሳሙ ዘርታችሁ ቃሙ፣ ዓይናችሁን በዓይናችሁ ለማየት ያብቃችሁ  ብለው የመረቁን በስህተት ነበር ለካ፡፡ ምክንያቱም እኛ እየሳምን ያለነው የወለድነውን ልጅ ሳይሆን የገዛነውን አሻንጉሊት ነዋ፡፡ ምክንያቱም እኛ ዓይናችንን በዓይናችን አይተናል የምንለው አሻንጉሊት ታቅፈን ቁም መስታወት ፊት ለፊት ቆመን አምሮብኛል አላማረብኝም እያልን የምንለውን ነዋ፡፡ ውጮቹን ምዕራባውያኑን እንመስላለን ብለን ራሳችንን መሆን አቃተን፡፡ እነርሱ የራሳቸው አስተሳሰብ፣ የራሳቸው አመለካከት፣ የራሳቸው ባህል፣ የራሳቸው የሆነ ነገር አላቸው ከአሻንጉሊቶች ጋርም የተዛመደ ነገር ሊኖራቸው ይችላል እኛ ደግሞ የራሳችን የሆነ ከእነርሱ ጋር የማያዛምደን ዓለምን የሚያስደንቅና የሚያስደምም ባህል አለን፡፡ የእነርሱን አለባበስ የእነርሱን ባህል የእነርሱን አመጋገብ የእነርሱን አነጋገር ወዘተ ሙሉ በሙሉ እኛን በሚመስልና እኛን በሚመጥን መልኩ አለመውሰዳችን ጥፋታችንን ያጎላዋል፡፡
ሌላው የሚገርመኝ ነገር “የገና ዛፍ” የሚባለው አሻንጉሊት ዛፍ ነው፡፡ በመጀመሪያ ይህንን ስም ያወጣለት ሰው ማነው? ምክንያቱም ገና የሚባለውን የምናውቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን፡፡ በእኛ የባህል ታሪክ ውስጥ  በዓላትን የምናከብረው በጉን፣ ዶሮውን፣ እንቁላሉን፣ ጠላውን፣ ጠጁን ወዘተ በማድረግ ራሳችን በሠራነው ራሳችን በጋገርነው ራሳችን ባረድነው ራሳችን በጠመቅነው ራሳችን በደፋነው ነገር ብቻ ነው፡፡ በዓላትን ያለው ለሌለው አካፍሎ በአንድ መሶብ ልጅ አዋቂው ከብቦ እየተመገበ አፈር ስሆን ብሉ አፈር ስሆን ጠጡ በሚሉት እናቶቻችን አጅ ጉርሻም እየተቀበልን ነው ያደግነው፡፡ ታዲያ ዛሬ “የገና ዛፍ” የሚባል አሻንጉሊት አቁመን “መልካም ገና” መባባላችን ትርጉሙ ምንድን ነው? በእውነት ባህል ያለው ሰው ታሪክ ያለው ሰው እምነት ያለው ሰው አፍሪካ ምድር ቅድስቲቱ አገር ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ሰው መሶብን በአሻንጉሊት መለወጡ ምን ያህል ያሳምማል? በእርግጥ አብሉኝ አጠጡኝ ማዳበሪያ ጨምሩልኝ ስለማይለን ሊሆን ይችላል፡፡ ፈረንጆቹ “የገና ዛፍን” የሚጠቀሙበት የራሳቸው የሆነ ምክንያት አላቸው እኛ ግን ምንም ምክንያት የለንም፡፡ እነርሱ በደጉ ዘመን የነበረው አምላካቸው በክፉ ዘመን ድርቅ ሲሆን ሁሉም ዛፎች ሲደርቁ ጽድ ግን በበጋም ስለማይደርቅ አምላካቸው በዚያ ተሸሽጎ ደጉ ዘመን እስኪመጣ ጠብቆ ደጉ ዘመን ሲመጣ ከዚያ ከተሸሸገበት ዛፍ ይወጣል ብለው ያምናሉ፡፡ ለዚያም ባለውለታቸው ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ ለዚህም ነው “የገና ዛፎች” ከጽድ ዛፍ ጋር ተመሳስለው የተሠሩት፡፡ አምላካቸውን ደብቆ ላቆየላቸው ባለውለታቸው ክብር ሰጥተው በመብራቶች አሸብርቀው በዓላትን ያከብሩበታል እንዲያውም ያመልኩበታልም፡፡ እኛ ደግሞ በክፉ ዘመን የሚሸሸግ በደጉ ዘመን እንደ መስቀል ወፍ ብቅ የሚል አምላክ የለንም፡፡ ደግ ዘመን ክፉ ዘመን ሁሉም የሚሆነው በእግዚአብሔር ነው ብለን የምናምን ክርስቲያኖች ነን፡፡ ታዲያ እንዲህ ከሆነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ “የገና ዛፍ” ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል? ምንም ትርጉም የለውም ምናልባት አምልኮ ባዕድ ካልተጠናወተን በስተቀር፡፡ ዛፍ አምላኪነት የተጠናወታቸው ሰዎች ግን በዓላትን ምክንያት ማድረግ አይጠበቅባቸውም፡፡ ሁልጊዜም ሊወድቁለት ሊሰግዱለት ሊገዙለት ያስፈልጋል፡፡ ስለ ገና ዛፍ ምንነትና የት መጣነት ይህንን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ፡፡
www.dw.com/am/የገና-ዛፍ-እና-የገና-አባት-ታሪክ/a-16481554  ወይም ይህንን
lemabesufekad.blogspot.com/2014/12/blog-post_24.html?m=1

ይቅርታ አድርጉልኝ እንጅ አሻንጉሊትን የሚጠቀመው ማኅበረሰብ በብዛት ሰነፍ ነው፡፡ አንድን ሕጻን እና አንድን ዛፍ ከማሳደግ ይልቅ ምንም የማያስቸግሩትን አሻንጉሊቶች መግዛት መታቀፍና ማቆም ይቀናዋል፡፡ ግን ባህላችን አለመሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡ ምን ችግር አለው እኔ የምፈልገው ጌጥነቱን እንጅ አላመልከው ልንል አያስፈልግም፡፡ “ፍቅረ አሻንጉሊት” ለመጨመሩ ብዙ ማሳያዎችን እየተመለከትን ነው፡፡ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የሚገዟቸውን ልብሶች ቅድሚያ የሚለብሱት አሻንጉሊቶች ናቸው፡፡ ልብስ ከሚሸጥባቸው ሱቆች ጎራ በሉና ይህንን አረጋግጡ፡፡ አዳዲስ ዘመናዊ “ፋሽን” የሚባሉ ነገሮችን ቅድሚያ የምናያቸው አሻንጉሊቶች ለብሰዋቸው ነው፡፡ ግን ስለ እውነት እንነጋገር እስኪ አንዱ የለበሰውን ልብስ እንድንለብስ ቢሰጠን እንለብሰዋለን? የእህቶቻችንን የወንድሞቻችንን ልብስ ለመልበስ እንኳ አንፈልግም ምክንያቱም ያ “የማንም ልባሽ” ነዋ፡፡ ታዲያ ላንተ ታዲያ ላንች ከእህትህ ከወንድምህ ከእህትሽ ከወንድምሽ አሻንጉሊት በልጦብህ/ሽ ነው የአሻንጉሊት ልባሽ የምትለብሰው/ የምትለብሽው፡፡ አቤት ጉድ!!!! ፍቅራችንን መተሳሰባችንንም ለካ አሻንጉሊት ተሻምቶብናል፡፡

Monday, January 4, 2016

፯ቱ አጽርሐ መስቀል እና ሐተታቸው


© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 25/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ድኅነት ሲል በፈቃዱ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ የተናገራቸው  ተአምራት ቃላተ ርኅራኄ ሰባት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት የመስቀሉ ላይ የርኅራኄ ቃላት ምን ምን ናቸው የሚለውን ከነሐተታቸው እነሆ፡፡ መልካም ንባብ!!!
1.  አምላኪየ አምላኪየ ነጽረኒ ወለምንት ኀደገኒ፡-  አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ ማለቱ ነው፡፡ “አምላኪየ አምላኪየ ነጽረኒ”  ማለቱ ነጽር ሊተ ተመልከት፡፡ ምዕመናንን ከፍትወታት እኩያት ከኃጣውእ ርኩሳት ጠብቅልኝ በዓይነ ምሕረት እይልኝ ሲል ነው፡፡ ወለምንት ኀደገኒ፡-አቤቱ ምዕመናንን በበደሉት በደል እኔ ከካስሁላቸው በኋላ ምነው ለምን ችላ ትልብኛለህ አውጣልኝ እንጅ ምነው ገሐነመ እሳት አወረድክብኝ ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ሥጋ መልበሱን ሲያስረዳንና እኛን ተገብቶ ሲጸልይልን ነው፡፡
2.  አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ፡- የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለቱ ነው፡፡ መላእክት በቀትር ፈጣሪያቸውን ሊያመሰግኑ ሲመጡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራቁቱን በቀራንዮ አደባባይ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ፊቱ ደም ለብሶ ሲያዩት ደንግጠው እንደ ሻሽ ተነጸፉ እንደ ቅጠል ረገፉ፡፡ ከዚህ በኋላ መልአኩ ሚካኤል ዝም ሲል መልአኩ ገብርኤል ግን በጣም ተበሳጭቶ አይሁድን በሰይፍ ሊያጠፋቸው ሰይፉን አነሣ የዚህን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱን ተዋቸው አታጥፋቸው የሚሠሩትን እና የሚደርጉትን ስለማያውቁ ነው ብሎታል፡፡ ገብርኤል ግን የአንተ ቸርነት አያልቅም ብሎ ተቆጥቶ ሰይፉን ወረወረው ሰይፉም የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ለሁለት ከፍሎ ወደ መሬት ገባ እስካሁንም ድረስ ወደታች ሲሄድ ይኖራል፡፡
3.  ነዋ ወልድኪ ወነያ እምከ ፡- እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ ማለቱ ነው፡፡ ጌታችን የተሰቀለ ዕለት እመቤታችን በከተማው ውላ ነበርና ጌታችን ዮሐንስን ጠርቶ እናቴን ጥራልኝ መከራየን ትመልከት አለው፡፡ ዮሐንስም ሄዶ እመቤታችንን እነሆ ልጅሽን ሰቀሉት ሲላት እርሷም ደንግጣ በሐዘን እያለቀሰች እየወደቀች እየተነሣች ከተሰቀለበት ቦታ ደርሳለች፡፡ በዚያም ራቁቱን ተሰቅሎ ስታይ ምርር ብላ አለቀሰች መልአኩ ጌታን ትወልጃለሽ ብሎ ያበሰረኝ ብሥራት ሞት ሆኖ በገደለኝ ነበር እያለች  አለቀሰች፡፡ ጌታም እናቴ ሆይ ብታለቅሽ ብታለቅሽ አይታክትሽምን እኔ ካልሞትሁላቸው 5500 ዘመን በዲያብሎስ ቁራኝነት የተያዙ ነፍሳት አይድኑም ዛሬ መከራው ሐዘኑ እንደበዛብሽ ነገ ዘመዶችሽ ብርሃን ለብሰው ከሲዖል ሲወጡ ስታዪ ደስታሽ ይበዛልና ተዪ አታልቅሽ አላት፡፡ የታመመ ሰው ልጄን ሚስቴን አደራ እንዲል እንዲሁ ጌታም እናት ትሆነው ዘንድ እርሱም ልጅ ይሆናት ዘንድ ለዮሐንስ አደራ ብሎታል፡፡ ይህን ቃል የተናገረው ለዚሁ ነው፡፡
4.  ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ፡- ትርጉሙ እንደመጀመሪያው አምላኪየ አምላኪየ እንዳለው ያለ ነው፡፡ ነገር ግን “ኤልማስ” ሲል አይሁድ  ኤልያስ ያለ መስሏቸው ኤልያስ መጥቶ ሳያድነው ቶሎ የሚገድለውን ነገር እንስጠው ብለው የዝኆን ሐሞት አጠጥተውታል፡፡
5.  ወአንተ ትቀድሞ ለአዳም በዊአ ውስተ ገነተ፡- አንተ አዳምን ቀድመህ ገነት ትገባለህ ማለቱ ነው፡፡ ከጌታ ጋር 2 ወንበዴ ሽፍቶች አብረው ተሰቅለው ነበር፡፡ አንደኛው በቀኝ ያለው ጥጦስ በሰማይ 3 በምድር 4 ተአምራት ሲደረጉ አይቶ “ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ዳግም ምጽአትከ” እያለ ሲጸልይ ጌታ ወደ የማናይ አንገቱን ዘንበል አድርጎ ግብጽ ስንወርድ የነገርሁህ ሁሉ ደረሰ አለው፡፡ ስለዚህ ከሞቴ በቀር የቀረኝ የለምና አንተ አዳምን ቀድመህ ገነት ትገባለህ ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶት አዳምን ተቀድሞ ገነት ግብቷል፡፡
6.  አባ አማሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ፡-  አቤቱ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ ማለቱ ነው፡፡ በዘመነ ኦሪት ጊዜ የነበሩ ሰዎች ነፍስ ከሥጋቸው እየተለየች ሲዖል ትወርድ ነበር አሁን ጌታ ከተሰቀለ በኋላ ግን ገነት ይገቡ ጀመር፡፡ ስለዚህ ነፍሳችን እንደ ኦሪቱ ሲዖል ብቻ ሳይሆን ገነት መንግሥተ ሰማያትም እንደምትገባ ሲናገር ነው፡፡ አንድም አዳምን ተቀድሞ ጥጦስ ገነትን በደመ ማኅተሙ ከፍቶ ገብቷልና ገነት መግባት መጀመሩን ያሳያል፡፡
7.  ተፈጸመ ኩሉ፡- ሁሉ ነገር ተፈጸመ ሲል ነው፡፡ አምላክ የመጣበት የድኅነት ሥራ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ ሥጋውን በመቁረስ እንደፈጸመው እንደደመደመው ሲናገር ነው፡፡ በመጻሕት የተጻፈው በነቢያት የተነገረው ሁሉ ደረሰ ሁሉ ነገር ተፈጸመ ሲል ነው፡፡
እነዚህን ሰባቱን በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥላጣኑ ለየ፡፡
ምስጋና ይሁን ለአብ ምስጋና ይሁን ለወልድ ምስጋና ይሁን ለመንፈስ ቅዱስ፡፡
አሜን፡፡

Thursday, December 31, 2015

“እመ አምላክ ድንግል ማርያም”

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 21/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ይህ ቃል ለአፍ ስንጠራው ሊቀለን ይችል ይሆናል እንጅ የእምነታችን ትልቁ ምሥጢር የእምነታችን መሠረት የተመሠረተበት እምነታችን የታነጸበት ዋና ቃል ነው፡፡ ስለ ድንግል ማርያም የሚከራከሩን ሰዎች  ይህን ቃል ብትነግሯቸው ቀላል ተራ ቃል ሊመስላቸው ይችላል ከምንም ሳይቆጥሩም ቃሉን ሊጠሩት ይችላሉ ግን አይደለም፡፡ በእውነት ይህንን ቃል እየጠሩ ምን የሚሉት ክህደት ነው? እስኪ ሰው ሆነን እናስበውማ በጣም የረቀቀ ምሥጢርን ያዘለ ቃል እኮ ነው፡፡ በእውነት በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የሚሸፍት ልብ ምን አይነት ልብ ነው? ስለ እናታችን አማላጅነት ለመከራከር እኮ ይህን ቃል ግዴታ መጥራት አለብን፡፡ ይህን ቃል ከጠራነው ደግሞ ትርጉሙን መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ እስኪ በእውነት አስቡትማ ቢያንስ አሁን  ለደቂቃዎች ሰው እንሁንና አስተውለን እንረዳ “እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ” ይህ ቃል ስለእውነት ገብቶን የምንጠራው ስንቶቻችን ነን? የሁለት ተቃራኒ ቃላት ጥምርታ እኮ ነው፡፡ “እመ አምላክ” የአምላክ እናት ማለት ነው “ድንግል ማርያም” ማለት ደግሞ ምንም ወንድ የማታውቅ ሴት ማለት ነው፡፡ “እመ አምላክ ድንግል ማርያም” ስንል ወንድን የማታውቅ በድንግልና በንጽሕና አምላክን ለመውለድ የበቃች አምላክን የወለደች እናት ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እስኪ ሴቶች አስቡት እናት ተብሎ ድንግል ይባላልን? ድንግል ሆኖ ባለልጅ መሆንስ ይቻላልን? አይቻልም፡፡ ምንም ይሁን ምን ድንግል የሆነች ሴት ልጅ ልትወልድ አትችልም፤ በተመሳሳይ ልጅ የወለደች ሴትም ድንግል ልትባል አትችልም፡፡ ድንግል ማርያም ግን ድንግል ወእም ስትባል ለዘለዓለም ትኖራለች፡፡ በእውነት ግን ምን ቃል ይገልጻታል እናታችንን ምን ቃል እንፈጥርላታለን ምን ምሳሌስ እንመስልላታለን፡፡ የማይቻለውን ቻለች የማይወሰነውን ወሰነች ዘመን የማይቆጠርለት መለኮትን ዘመን እንዲቆጠርለት አደረገች፡፡ ሰሎሜ ልታዋልድ ስትቀርብ በቅጽበት እጇ ተቃጠለ ቶማስ የተወጋ ጎኑን እዳስሳለሁ ብሎ እጁን ሲያስጠጋው እጁ እርር ኩምትር አለ እመቤታችን ግን በድንግልና ጸንሳ በድንግላ ስትወልደው እሳተ መለኮቱ አላቃጠላትም ከቶ ለምን ይሆን? እነዚያ ደቂቃ ላልሞላ ጊዜ እጃቸውን ማስጠጋት ያልተቻላቸውን እሷ ግን ታቀፈችው አዘለችው አይገርምም፡፡ አረ ቅዱሳኑም ሊቃውንቱም እመቤታችንን የሚገልጹበት ቃል የላቸውም “በመኑ በአምሳለ መኑ ናስተማስለኪ” ያላት ምስጋና የበዛለት አባ ሕርያቆስ አይደል እንዴ? ታዲያ ምሳሌ ሲያጣላት ቃል ባይገልጽለት ምን ያድርግ? ግርምት ድንግል ማርያም ያልገረመች ማን ይግረም፡፡ በዚያ በኃጢአት ዘመን የቀደመው የአዳም በደል በእናቷና በአባቷ ሳለ እርሷ ግን ያ በደል ሳያገኛት ለድህነታችን የተወለደች የተፈጠረች ንጽሕት ዘር  ናት እናታችን እመብርሃን፡፡ በዚህ እንኳ በሰው ሚዛን በሰው ፍርድ እየነዘንና እየለካን ልንከራከር እንፈልጋለን፡፡ ጥንተ አብሶ አባትና እናቷ ስለነበረባቸው እርሷም አለባት ይላሉ ምስጋና ይግባትና፡፡ በዚህ ዘመን አባትና እናት በሽተኛ ሆነው ልጁም በሽተኛ ሆኖ ይወለዳል ብሎ መከራከር እንዴት ያለ ጭንቅላት ነው?
በእውነት ስሟን ጠርቶ የሚሰለች ማነው? እኔ እኮ እመብርሃንን የማከብራት እመ ብርሃንን የማመሰግናት እመ ብርሃንን የምሰግድላት ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስለማልበልጥ ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስር ሰግዶ ደስታ ይገባሻል ደስ ይበልሽ ብሎ እኮ ነው፡፡ ታዲያ እርሱ እንዲህ ከሰገደላት እንዲህ ካከበራት እኔ ማን ሆኜ ነው እናቴን ላቃልል የስድብ አፍ የምከፍተው? ስሟን መጥራትስ ይቻለኛል እንዴ እንኳን በእናቴ ላይ ስድብን ልሰነዝር የምደፍረው? እናስተውል ወገኖቼ መናፍቃኑ በሚጠሯት አጠራር አንጠራትም እኛ፡፡ ለእኛ እናታችን ናት ለእኛ መድኃኒታችን ናት ለእኛ ተስፋችን ናት ለእኛ ገነት መግቢያችን ናት ለእኛ መመኪያችን ናት ለእኛ ስንቃችን ናት ለእኛ እረፍታችን ናት ለእኛ መሰላላችን ናት ለእኛ የደስታችን መፍሰሻ የደስታችን መፍለቂያ የደስታችን ምንጭ ናት ለእኛ ብርሃናችን ናት ለእኛ አምላክን የወለደችልን ናት ለእኛ አማላጃችን ናት ለእኛ ሁለመናችን ናት ለእኛ በደማችን ውስጥ ያለች በልባችን ውስጥ የታተመች ናት ለእኛ ፍቅሯ በሁለመናችን የመላች እናታችን ናት፡፡ ይህን የምንለው መናፍቃኑን ለመከራከር መናፍቃኑን ለመቃወም አይደለም እናታችን ከዚህም በላይ ስለሆነችልን  ነው፡፡ እኛ ፍቅሯን ቀምሰነዋል እናትነቷን አውቀነዋል መሸሸጊያነቷን አይተነዋል አማላጅነቷን አምነነዋል ሁሉንም እንደሆነችን ተገንዝበናል ለዚህ ሁሉ ክብር ያበቃንም እመ ብርሃንን ለእናትነት የመረጣት ከሴቶች ሁሉ መርጦ ያከበራት አምላካችን ነው፡፡

በእውነት እስኪ አስቡት ማን ነው ኃጢአት መሥራትን የማያውቅ? ከሰው ወገን ሆኖ በገቢር ባይፈጽም በነቢብ፣ በነቢብም ባይፈጽም በሀልዮ ኃጢአትን የማያደርግ ማነው? በእውነት ማነው ይህን ማድረግ የሚቻለው? ንጽሕናን እንደጠበቁ ምንም ኃጢአትን ሳያደርጉ እስከ ዘለዓለም መጽናት ለማን ተሰጠው? ለማንም አልተሰጠውም እኮ መላእክት እንኳ እንደ እርሷ ንጹሕ አይደሉም፡፡ እመቤታችን ግን ምንም አይነት ኃጢአት ርኩሰት የለባትም በሃሳብሽ ድንግል ነሽ በስጋሽም ድንግል ነሽ የምንላት ለምን መሰላችሁ ሃሳቧ ኃጢአትን ለማሳብ ጊዜ የሌለው ስለነበር እኮ ነው፡፡ እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናቴ የማይላት ከቶ ማነው? እርሱ እኮ መዳኑን የማይወድ ተስፋውን የማይሻ መጠጊያውን የማይፈልግ ከለላውን የማያውቅ መከታውን የዘነጋ ምርኩዙን መደገፊያውን የማይወድ ምግብ ስንቁን የሚጠላ ውሉደ አጋንንት ነው፡፡ እንዲያው ሌላውን እንተወውና አምላክን በድንግልና ለመውለድ መመረጧ እንዴት አያስደንቀንም? በድንግልና የሴቶች ልማድ ሳያገኛት በመንፈስ ቅዱስ ጸንሳ መገኘቷ እንዴት አያስደምመንም? ሰው ሆና ሳለች ከኃጢአትና ርኩሰት በሃሳብም በሥጋም ድንግል መሆኗ እንዴት አይገርመንም? መላእክት እንኳ ንጹሕ ባልሆኑበት ዓለም ለብቻዋ ንጽሕት ዘር መሆኗ እንዴት አይደንቀንም? በእውነት ስለእውነት ለስሟ መግለጫ ቃላት እኮ የለንም፡፡ እኛን የሚደንቀን እኮ እንደኛው ሰው ስትሆን እንዲህ ያለውን ንጽሕና ይዛ በመገኘቷ ነው፡፡ እኔ ሰው ነኝ አንተም ሰው ነህ አንችም ሰው ነሽ ማንነታችንን አናውቀውም እንዴ? ለትንሽ ጊዜ እንኳ እስኪ ሰው ሁኑ ያልኳችሁ ለዚህ ነው፡፡ በቅጽበት ውስጥ ምን ያህል ኃጢአትን ነው ስናነሣ ስንጥል የምንውለው? እኛ እንኳን ቆመን ተኝተንስ ኃጢአትን አይደል እንዴ ስንቃዥ የምናድረው እርሷ እንዲህ የሚባል ነገር የለባትም፡፡ ታዲያ እመቤታችን ያልገረመችን ማን ይግረምን? ከመላእክት ወገን ብትሆን እኮ እንዲህም ባልተገረምን ነበር ባልተደነቅንም ነበር ምክንያቱም ባሕርያቸውን ባሕርያችን ስላላደረግን እነርሱ እኮ ከእንደዚህ ባሕርይ ስለተፈጠሩ ነው እንል ነበር እመቤታችን ግን ሰው ናት ለዚያም ነው የደነቀችን የገረመችን፡፡ በእውነት “እመ አምላክ ድንግል ማርያም” የሚለውን ቃል ሳየው ሁልጊዜ አዲስ ነገር አዲስ ትምህርት አዲስ ቃል አዲስ ስብከት ነው ለእኔ፡፡ ዛሬም አዲሴ ነው ነገም እንደዚያው፡፡ ዝም ብሎም እናትና ድንግል ቢል ላይደንቀኝ ይችል ነበር “እመ አምላክ ሲባል ግን እንዴት አይደንቀኝም፡፡ ለሁሉም ነገር ግን አበው ተናግረውት ጽፈውት ያልጨረሱትን የክብሯን ነገር ስጨልፍ ብውል አልጨርሰውምና ዝም ልበል፡፡

“ቀን የወጣላቸው ቃላት”

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዘመን ሲያልፍ ዘመን ሲተካ ያለፈው ዘመን፣ ያለፈው መንግሥት፣ ያለፈው አስተሳሰብ፣ ያለፈው አመለካከት፣ ያለፈው ፍልስፍና፣ ያለፈው ትውልድ ወዘተ የበደላቸው እና አሁን ጊዜ ያን ሁሉ መከራ አልፈው በክብር የተቀመጡ ነገሮች ቀን ወጣላቸው እንላለን፡፡ ያለፈው ዘመን ጨለማቸው ስለነበር አሁን ላይ ብርሃን የሚያዩበት ስለሆነ ቀን ደግሞ ብርሃንን እንጅ ጨለማን ስለማያመጣ ቀን የወጣላቸው ስንል ብርሃን የተገለጠላቸው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በድህነት አለንጋ ሲገረፍ የነበረ ሰው በልጁ በኩል ድህነቱ ሁሉ ተገፍፎ ሃብታም የሚባል ሰው ዝናና ሞገስ የለበሰ ሰው ሲሆን አሁንማ እገሌ ቀን ወጣለት እኮ ይባላል፡፡ አሁን ግን ስለ ሰዎች አይደለም ቀን መውጣቱን የምንነጋገረው ስለ ቃላት ነው፡፡ መንግሥት ሲለወጥ ቃላትም አብረው ይለወጣሉ በሆነ ጊዜ በሆነ ዘመን በሆነ ማኅበረሰብ የተጨቆኑ ቃላት በሌላ ጊዜ በሌላ ማኅበረሰብ ላይ ያልፍላቸዋል ቀን ይወጣላቸዋል፡፡ እንዲያውም እነዚያ ቃላት ከመጠን በላይ ተደጋግመው ስለሚደመጡ ድሮ ግን እነዚህ ቃላት ነበሩን ያሰኛል፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈለፈሉ ቃላት አሉ “ሕዳሴ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ አከርካሪ፣ ከማድረግ አኳያ፣ ከማድረግ አንጻር፣ ሰላማችን ይደፈርሳል፣ የልማት ቡድን ወዘተ” እነዚህ ቃላት እና ብዙዎች አሉ ምንም ስለማይጠቅሙን ነው የተውኳቸው፡፡ እነዚህ ቃላት ድሮ ተጨቁነው የነበሩ ናቸው ማንም የማይጠራቸው ቃላት ነበሩ ወይም የሚጠቀምባቸው ጥቂት ሰው ብቻ ነበር አሁን ግን አልፎላቸዋል እፎይ ብለዋል ቀን ወጥቶላቸዋል ብርሃን ፈንጥቆላቸዋል፡፡ እኔ እነዚህን ያመጣሁላቸችሁ “ቃል ደግሞ ቀን ይወጣለታል እንዴ” እንዳትሉ ያህል ነው እንጅ ጉዳዬ ከእነዚህ ቃላት ጋር አይደለም፡፡
አሁን እኔ የምሄደው ወደ ቤታችን ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ቃላት የፈለጉትን ያህል ቀን ይውጣላቸው በሚዲያ ዐሥር ጊዜ ይነገሩ ይተረቱ ይዘመሩ እንጅ ምኔም አይደሉም እንደማንኛውም ሰው ከመስማት አልዘልም አልደነቅም አልገርምም፡፡ እኔን የሚገርመኝ እና የሚያስጨንቀኝ ብሎም የሚያሳዝነኝና የሚያስለቅሰኝ በቤቴ በመኖሪያዬ በርስቴ የሚነገረው ብቻ ነው፡፡ ዛሬ በእኛ ቤትም አሉ ድሮ ያልተጨቆኑ ዛሬ ግን ድሮ እንደተጨቆኑ አስመስለን ቀን እንዲወጣላቸው ያደረግናቸው ቃላት አሉ፡፡ ባለፈው ልኩን ያለፈ አሜን እና እልልታ በሚል መጻፌን ታስታውሳላችሁ አሁንም እደግመዋለሁ ቀን ያለፈላቸው ቀን የወጣላቸው ቃላት እነዚህና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ በእውነት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ እነዚህ ቃላት ተጨቁነው ኖረዋልን? አረ በፍጹም ቤተክርስቲያናችን ጭቆናን አላስተማረችም አልጨቆነችምም፡፡ ነገር ግን ቦታና ጊዜ ሰርታ ወስና ወጥና ከሽና አዘጋጅታለች እንጅ፡፡ ታዲያ ስብከት የተጀመረው ዛሬ ይመስል እንዲህ ዓይነቱን ያልተገባ ሥርዓት አልባነት ከየት አመጣነው? የዛሬ ሰባኪ አሜን ካላስባለ ካላስጨበጨበ ያስተማረ የማይመስለው የሰበከ የማይመስለው ለምንድን ነው? በእርግጥ የመናፍቃኑ፣ የተሐድሶ መናፍቃን እንዲሁም የሌሎቹ ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እነርሱ በእርግጠኝነት ቀድመውናል በርዘውናል፡፡ እነርሱ ያስተማሩን ትምህርት የነገሩን ቃል ነው በጭንቅላታችን የሚያቃጭለው፡፡ በእውነት እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የሰበኩላት የሞቱላት የተገረፉላት የተገፈፉላት የተራቆቱላት ሃይማኖታችን ተዋሕዶ እንዲህ በመድረኮቿ ላይ ማንም የሚፈነጭባት ለምንድን ነው? ስብከት ሳንሰበክ አሜን በሉ እየተባልን የምንንገላታው አጨብጭቡ እየተባልን ዐሥሬ የምናጨበጭበው ለምኑ ነው? ምንም አልገባኝም ሥርዓት እኮ አለን ያውም የሚያምር የሚማርክ ልክና መጠን ጊዜና ዘመን የተወሠነለት፡፡ እንዴት ከመናፍቃን አዳራሽ ቃላትን አፍልሰን ዛሬ ላይ እንቦርቃለን? አሜን የሚለው ቃል እኮ ይሁንልኝ ይደረግልኝ ለማለት የምንጠቀመው ቃል ነው፡፡ እልልታ የሚገባው እኮ የራሱ የሆነ ክብር ለሚያስፈልገው ነገር ነው፡፡ በብዛት የምንጠቀመው ለደስታ ጊዜ ነው፡፡ የሰማዕታትን ነገር ስንናገር “ቅዱስ ጊዮርጊስን በወፍጮ ፈጩት” ሲባል ድምጽን ከፍ ማድረግ አይፈቀድም ሥርዓትም አይደለም፡፡ መከራ ነውና የምንናገረው ክብራቸው ጸጋቸው ትልቅ ነውና እኛ ለዚያ ጸጋ ክብር ስለማንበቃ ድምጻችንን ዝቅ አድርገን መናገር ያስፈልገናል፡፡ ዛሬ ግን እንዲህ የሚባል ነገር የለም ምክንያቱም ለሰማዕታት ክብር ከማይሰጡት ጋር ነዋ የሚውለው፡፡ ደምጹን ለቅቆ ጮኾ “ቅዱስ ጊዮርጊስ በወፍጮ ተፈጨ ደስ ይበላችሁ” ብሎን ያርፈዋል እኛም እንደለመድነው “እልል እንላለን እናጨበጭባለን አሜን እንላለን” ግን ወዴት እያመራን ነው? ስለእውነት እኔ አሁን አሁን ግራ እየገባኝ ነው ቢያንስ እስኪ እኛ እንዲህ ማለቱን እናቁመው፡፡ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ እንዲህ አሉ “ለመሆኑ እኛ ማን ሆነን ነው እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ጸጋውን ያብዛልህ የምንለው” ልክ ነው ስንት ትልቆች ባሉበት እኛ እንዲህ እንድንደፍር ያደረገን ምንድን ነው? እንዲህ እያለ በአባቶች ፊት የሚሰብክ ሰው ስላለን እኮ ነው፡፡ ከመናፍቃኑ አፍልሰው ወደ እኛ ያመጧቸው ቃላት ናቸው፡፡ መናፍቃኑ ዘንድ ሁሉም እኩል ናቸው ካህን ምእመን ሴት ወንድ ጻድቅ ኀጥእ የሚባል ልዩነት የለም፡፡ ስለዚህም ማንም የፈለገውን መናገር ማስተማር መስበክ መዘመር ይችላል፡፡ ለካህን ለዲያቆን ለጳጳስ ለምእመን ለሴት ለወንድ ለሕጻን ለአዋቂ የሚለው ነገር አይታወቅም ምክንያቱም ማን ከማን ይበልጣል ማንስ ከማን ያንሳል፡፡ ሁሉም መስበክ ይችላል ሁሉም መዘመር ይችላል ሁሉም መፈወስ ይችላል፡፡ ለዛ ነው የእነርሱ ሥርዓት አልባነት ወደኛም መጥቶ እንዲህ የተሸረሸርነው፡፡ በውኑ ጸጋውን ያብዛልህ የምልህ እኔ ማን የሚሉኝ ጳጳስ ማን የሚሉኝ ቅዱስ ነኝ? የማን አባት የማን እናት ሆኜ ነው? የትኛውን ተጋድሎ የትኛውን ሰይፍ አልፌ ነው? በእውነት በጣም ያሳዝነኛል፡፡ አሁን ትውፊታችንና ባህላችንን ክርስቲያናዊ ምግባራችንን የምንፈትሽበት ጊዜ ነው፡፡ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ቀን ያሳለፍንላቸውን ቃላት መመርመር አለብን፡፡ እነዚያ ቃላት እኮ ዛሬ ቀን ያለፈላቸው ቀን የወጣላቸው ድሮ ስለተጨቆኑ አይደለም ድሮ ሥርዓት ያከብሩ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ እኮ መናገር እንጅ አንመርጥም ለምሳሌ ማንም ሰው ካህኑ ማት የሚገባውን “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” እኛ በቅዳሴ ጊዜ ልንለው አንችልም፡፡ ነገ ግን ብንለው ምን ችግር አለው ዜማው በጣም ይመቸኛል ልንል እንችላለን፡፡ የዜማ ምቾት ምን እንደሆነ አላውቅም በእርግጥ ግን ለእኛ አልተገባንም ስለዚህ ለእኛ የሚገቡንን ብቻ ልንመርጥ ይገባናል፡፡
ዛሬ እኮ የእኛ እና የመናፍቃንን ዜማ መለየት እስኪያቅተን ድረስ የደረስን ተው ባይ አጥተን ይመቻል አይመችም እያልን ስንጨቃጨቅ ነው፡፡ በእውነት ሳናውቅ ተበልተናል ተበልጠናልም መንቃት ያሻናል፡፡ ማነው በቤታችን የፈለገውን ነገር የሚናገርበት እኛም እኮ ድርሻ አለን፡፡ ዛሬ ስብከትን መብል መጠጥ ያደረጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ስለሥርዓቱ ስለትውፊቱ አይደንቃቸውም የተሰጣቸውን ጊዜ ብቻ መጠቀማቸውን ነው እነርሱ የሚመለከቱት፡፡ ስለዚህ መንቃት ያስፈልገናል!!!!! ተሐድሶ መናፍቃን በዝተዋል በርትተዋል ማድከም ማዳከም ያስፈልገናል፡፡ ከእኛ ላይ ይውረዱልን በቃ የራሳቸውን ቤተክርስቲያን ይሥሩ በዚያ ላይ የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ያድርጉ እኛ ላይ ግን አንዳች ነገር እንዳያደርጉ መጠበቅ አለብን፡፡ ከዚያ ውጭ ከሆነ ግን የአባቶቻችን አጥንት እሾህ ሆኖ ባይወጋን ምን አለ በሉኝ፡፡

Monday, December 28, 2015

ሲድራቅ----ሚሳቅ----አብደናጎ

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 18/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በዱራ ሜዳ ላይ ናቡከደነፆር አምላኩን አቆመው፣
በስድሳ ክንድ ቁመት በስድት ክንድ ወርድ ከወርቅ አቅልጦ ሠራው፡፡
አምላኩን ሊያስመርቅ ያልተመረቀ አምላክ መርቁልኝ ብሎ፣
መኳንንት፣ ሹማምንት፣ አዛዥ፣ አዛውንቱን፣ መጋቢውን ሁሉ ጠራቸው በቶሎ፡፡
የንጉሥ ትዕዛዝ ነው ከታች ባትን ከላይም አንገትን ሊያስቆርጥ የሚችል፣
ታዲያ ማን ይቀራል? ማንስ ይንቀዋል? ማን ያቃልለዋል?
ሁሉም ለምረቃው ተሰበሰቡና፣
በተሠራው አምላክ ፊት ለፊት ቆሙና፣
ያደንቁት ጀመሩ ንጉሣቸውን አምላክን የሠራ ስለሆነ ጀግና፣
በሚሠራ አምላክ ሁሉም አምኗልና፡፡
ከዚያማ ! አዋጅ ተናጋሪው እየጮኸ መጣ፣
ትእዛዙን ሊናገር ካልፈጸምን ሊቀጣ፡፡
ወገኖችና አህዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ፣
መለከት፣ እንቢልታ፣ መሰንቆ፣ በገና፣ ዋሽንት ክራሩ፣
ዘፈን ግርግሩ፣
እንደተሰማችሁ ንጉሡ ላቆመው ለወርቅ ምስሉ ስግደትን ገብሩ፡፡
ይህን ባታደርጉ በሚነድ እሳት ውስጥ ትጨመራላችሁ፣
ከሰል እስክትሆኑም ትቃጠላላችሁ፡፡
እያለ አስፈራራን እጅግ አስጨነቀን፣
ለጣዖት እንድንሰግድ እያስጠነቀቀን፡፡
ከዚያማ! መለከት፣ እንቢልታ፣ መሰንቆ ክራርን፣
በገና ዘፈንን አዋጅ ተናጋሪው ሁሉንም አሰማን፣
ለጣዖት እንድንሰግድ ፊሽካውን ነፋልን፡፡
ይህን እንደሰሙ አህዛብ በሙሉ፣
በልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪው ሁሉ፣
ተደፍተው ሰገዱ ለወርቅ ምስሉ፡፡
ከዚያ ከለዳውያን አይሁድን ከሰሱ፣
ንጉሥ ሽህ ዓመት ንገሥ እያሉ ወደቁ ተነሡ፡፡
መለከት፣ እቢልታ፣ መሰንቆ እና ክራር፣
በገና እና ዘፈን ስንሰማ ልንሰግድም አልነበር?
ታዲያ እነዚህ ሰዎች በባቢሎን ግዛት ሥራ የሾምካቸው፣
ላንተ ለወርቅ ምሥል አንሰግድም እንቢ ማለታቸው፣
ንጉሥ ሺህ ዓመት ንገሥ ችግሩ ምንድን ነው?
እያሉ ከሰሱን እኛም እንድንሰግድ፣
ለወርቅ ምስሉ እንድናጎበድድ፡፡
ናቡከደነፆር ይህን እንደሰማ እጅግ ተበሳጭቶ፣
መልእክተኛ ልኮ ወሰደን ጎትቶ፡፡
ከዚያማ ጮኸብን እጅግ ተቆጥቶ፣
አምላኬን አለማምለካችሁ፣
ላቆምኩትም ምስል አለመስገዳችሁ፣
ከቶ እውነት ከሆነ ንገሩኝ ፈጥናችሁ አለን ተበሳጭቶ፡፡
አሁንም መለከት፣ እንቢልታ፣ መሰንቆ፣ ክራርን፣
በገና ዋሽንትን ዘፈን እንጉርጉሮን፣
በሰማችሁ ጊዜ ድፍት ብላችሁ ገብሩ ስግደትን፣
ይህን ባታደርጉ ተመልከቱ ያንን፣
በዚያ ተጥላችሁ ትቃጠላላችሁ፣
እያለ ጠቆመን የሚነደውን የእሳት እቶንን፡፡
እኛም ተመለከትን ይነዳል እሳቱ፣
ነገር ግን… ከንቱ እንደሆነ የንጉሥ ትምክህቱ
ማሳየት ማስተማር በመፈለጋችን ዝም አልነው በብርቱ፡፡
እርሱም ጀመረ ገባ ያስፈራራን፣
ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ የለም አለን፣
አምላኩ ወርቅ ሆኖ ለወርቅ ሊያሰግደን፡፡
እኛ ግን! እኛስ አምላክ አለን የሚያድን ከምንም፣
ከእጅህ የሚያስመልጥ የሚበልጥ ከሁሉም፡፡
ምንም ንጉሥ ብትሆን ብናከብርህ ቅሉ፣
አንተ ለሠራኸው ለወርቅ ምስሉ፡፡
አንሰግድም በፍጹም እግዚአብሔር እያለን፣
ሰማይና ምድርን አንተንም እኛንም የፈጠረን አምላክ ከላይ ሆኖ እያየን፡፡
የአምላክ ፈቃድ ሆኖ እንኳ ብንቃጠል፣
አንሰግድም በፍጹም ላንተ ለወርቅ ምስል፡፡
ብለን ስንናገር ፊቱ ተለወጠ ናቡከደነፆር፣
የእርሱ የወርቅ ምስል በልጦበት ከእግዚአብሔር፡፡
ቀድሞ ከሚነደው ሰባት እጥፍ ያህል ይቀጣጠል አለ፣
ነበልባል ሲጨምር ይፈራሉ ብሎ ንጉሥ ተታለለ፡፡
እኛ ግን! ከቶ ምንም ቢሆን ምንም ቢመጣብን፣
አንክድም በፍጹም እግዚአብሔር አምላክን፣
መከራ ስቃዩን ችግሩን ካላለፍን፣
መውረስ እንደማንችል መንግሥተ ሰማይን፣
እኛ እናውቀዋለን ከድሮ ጀምረን፣
ነንና ክርስቲያን፣
ስለዚህ በእቶኑ አቃጥሉን አንድዱን፣
አምላክን ከመካድ ሞት እንመርጣለን አልን፣
የንጉሥ ቃል ሆኖ ሁሉም አሽከሮቹ ተጣድፈው መጡና፣
አርባ ዘጠኝ ክንድ ከፍ ከፍ እስከሚል አቀጣጠሉና፡፡
እጃችንን አስረው በዚያ ላይ ጨመሩን፣
ከሰል እስከምንሆን በእሳት ሊያቃጥሉን፡፡
እኛ እኮ አምላክ አለን አምላክ እንደሌለው፣
አናዝንም አናፍርም ከቶም አንቃጠል እግዚአብሔር ከኛ ነው፡፡
ስቡህኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ እንላለን ገና፣
አምላከ አብርሃም ከኛ ጋር ነው፣
እያልን አጨበጨብን እጃችን ተፈታ፣
ምስጋና ይድረሰው ለፈጠረን ጌታ፡፡
እኛ እሳት ውስጥ ወድቀን ምንም ሳንነካ፣
በዳር የነበሩት እኛን የጣሉን ግን ተቃጥለዋል ለካ፡፡
ናቡከደነፆር አሁንስ ደነቀመው፣
አማካሪዎቹን እንደዚህ አላቸው፡፡
ሦስት ሰው አስረን በእሳቱ ውስጥ ጥለን አልነበረምን?
እጃቸው ተፈትቶ አራት ሰዎች ሆነው የሚመላለሱ ይታዩኛል እኔን፣
ማመን አቅቶኛል ዛሬስ ይህን ዓይኔን፡፡
ይህ እንዴት ይሆናል?
 እንዴት ይደረጋል?
አራተኛው ሰው ግን የአማልክት ልጅን በእጅጉ ይመስላል፡፡
እያለ ሲደነቅ ሲገረም ቆየና፣
የልዑል ባሪያዎች ኑ ውጡ! ወደዚህ ቅዱስ ናችሁና፡፡
እሳት ውኃ ሆኖስ ካላቃጠላችሁ፣
እኔም አመልካለሁ እኔም እሰግዳለሁ፣
ከእቶን እሳት ውስጥ ከእጄም ላዳናችሁ፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሲድራቅ ለሚሳቅ ለአብደናጎ አምላክ፣
እኔም ልወድቅ ልሰግድ ፊቱ ልንበረከክ፣
አምላኬ ጌታዬ ብዬ በእርሱ ብቻ ላመልክ፡፡
ራሴን ሰጠኹኝ እስከመጨረሻ፣
እግዚአብሔር ነውና መነሻ መድረሻ፡፡
ከዛሬ በኋላ በእነዚህ ቅዱሳን ክፉ የሚናገር፣
በአምላካቸውም ላይ የስድብን ነገር ከቶ የሚናገር፡፡
ይቆረጣል  ባቱ፣
ከላይም አንገቱ፡፡
****************************************
እንዲህ ነው እንግዲህ አምላክ የታደገን፣
ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ከመንደድ ያስጣለን፣
በአህዛብ መካከል ከፍ ከፍ ያረገን፡፡
የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

(ትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ ሦስት በሙሉ ያንብቡ)