© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 21/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ

በእውነት ስሟን ጠርቶ የሚሰለች ማነው? እኔ
እኮ እመብርሃንን የማከብራት እመ ብርሃንን የማመሰግናት እመ ብርሃንን የምሰግድላት ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስለማልበልጥ ነው፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስር ሰግዶ ደስታ ይገባሻል ደስ ይበልሽ ብሎ እኮ ነው፡፡ ታዲያ እርሱ እንዲህ ከሰገደላት
እንዲህ ካከበራት እኔ ማን ሆኜ ነው እናቴን ላቃልል የስድብ አፍ የምከፍተው? ስሟን መጥራትስ ይቻለኛል እንዴ እንኳን በእናቴ ላይ
ስድብን ልሰነዝር የምደፍረው? እናስተውል ወገኖቼ መናፍቃኑ በሚጠሯት አጠራር አንጠራትም እኛ፡፡ ለእኛ እናታችን ናት ለእኛ መድኃኒታችን
ናት ለእኛ ተስፋችን ናት ለእኛ ገነት መግቢያችን ናት ለእኛ መመኪያችን ናት ለእኛ ስንቃችን ናት ለእኛ እረፍታችን ናት ለእኛ መሰላላችን
ናት ለእኛ የደስታችን መፍሰሻ የደስታችን መፍለቂያ የደስታችን ምንጭ ናት ለእኛ ብርሃናችን ናት ለእኛ አምላክን የወለደችልን ናት
ለእኛ አማላጃችን ናት ለእኛ ሁለመናችን ናት ለእኛ በደማችን ውስጥ ያለች በልባችን ውስጥ የታተመች ናት ለእኛ ፍቅሯ በሁለመናችን
የመላች እናታችን ናት፡፡ ይህን የምንለው መናፍቃኑን ለመከራከር መናፍቃኑን ለመቃወም አይደለም እናታችን ከዚህም በላይ ስለሆነችልን
ነው፡፡ እኛ ፍቅሯን ቀምሰነዋል እናትነቷን አውቀነዋል መሸሸጊያነቷን
አይተነዋል አማላጅነቷን አምነነዋል ሁሉንም እንደሆነችን ተገንዝበናል ለዚህ ሁሉ ክብር ያበቃንም እመ ብርሃንን ለእናትነት የመረጣት
ከሴቶች ሁሉ መርጦ ያከበራት አምላካችን ነው፡፡
በእውነት እስኪ አስቡት ማን ነው ኃጢአት መሥራትን
የማያውቅ? ከሰው ወገን ሆኖ በገቢር ባይፈጽም በነቢብ፣ በነቢብም ባይፈጽም በሀልዮ ኃጢአትን የማያደርግ ማነው? በእውነት ማነው
ይህን ማድረግ የሚቻለው? ንጽሕናን እንደጠበቁ ምንም ኃጢአትን ሳያደርጉ እስከ ዘለዓለም መጽናት ለማን ተሰጠው? ለማንም አልተሰጠውም
እኮ መላእክት እንኳ እንደ እርሷ ንጹሕ አይደሉም፡፡ እመቤታችን ግን ምንም አይነት ኃጢአት ርኩሰት የለባትም በሃሳብሽ ድንግል ነሽ
በስጋሽም ድንግል ነሽ የምንላት ለምን መሰላችሁ ሃሳቧ ኃጢአትን ለማሳብ ጊዜ የሌለው ስለነበር እኮ ነው፡፡ እናታችን እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያምን እናቴ የማይላት ከቶ ማነው? እርሱ እኮ መዳኑን የማይወድ ተስፋውን የማይሻ መጠጊያውን የማይፈልግ ከለላውን
የማያውቅ መከታውን የዘነጋ ምርኩዙን መደገፊያውን የማይወድ ምግብ ስንቁን የሚጠላ ውሉደ አጋንንት ነው፡፡ እንዲያው ሌላውን እንተወውና
አምላክን በድንግልና ለመውለድ መመረጧ እንዴት አያስደንቀንም? በድንግልና የሴቶች ልማድ ሳያገኛት በመንፈስ ቅዱስ ጸንሳ መገኘቷ
እንዴት አያስደምመንም? ሰው ሆና ሳለች ከኃጢአትና ርኩሰት በሃሳብም በሥጋም ድንግል መሆኗ እንዴት አይገርመንም? መላእክት እንኳ
ንጹሕ ባልሆኑበት ዓለም ለብቻዋ ንጽሕት ዘር መሆኗ እንዴት አይደንቀንም? በእውነት ስለእውነት ለስሟ መግለጫ ቃላት እኮ የለንም፡፡
እኛን የሚደንቀን እኮ እንደኛው ሰው ስትሆን እንዲህ ያለውን ንጽሕና ይዛ በመገኘቷ ነው፡፡ እኔ ሰው ነኝ አንተም ሰው ነህ አንችም
ሰው ነሽ ማንነታችንን አናውቀውም እንዴ? ለትንሽ ጊዜ እንኳ እስኪ ሰው ሁኑ ያልኳችሁ ለዚህ ነው፡፡ በቅጽበት ውስጥ ምን ያህል
ኃጢአትን ነው ስናነሣ ስንጥል የምንውለው? እኛ እንኳን ቆመን ተኝተንስ ኃጢአትን አይደል እንዴ ስንቃዥ የምናድረው እርሷ እንዲህ
የሚባል ነገር የለባትም፡፡ ታዲያ እመቤታችን ያልገረመችን ማን ይግረምን? ከመላእክት ወገን ብትሆን እኮ እንዲህም ባልተገረምን ነበር
ባልተደነቅንም ነበር ምክንያቱም ባሕርያቸውን ባሕርያችን ስላላደረግን እነርሱ እኮ ከእንደዚህ ባሕርይ ስለተፈጠሩ ነው እንል ነበር
እመቤታችን ግን ሰው ናት ለዚያም ነው የደነቀችን የገረመችን፡፡ በእውነት “እመ አምላክ ድንግል ማርያም” የሚለውን ቃል ሳየው ሁልጊዜ
አዲስ ነገር አዲስ ትምህርት አዲስ ቃል አዲስ ስብከት ነው ለእኔ፡፡ ዛሬም አዲሴ ነው ነገም እንደዚያው፡፡ ዝም ብሎም እናትና ድንግል
ቢል ላይደንቀኝ ይችል ነበር “እመ አምላክ ሲባል ግን እንዴት አይደንቀኝም፡፡ ለሁሉም ነገር ግን አበው ተናግረውት ጽፈውት ያልጨረሱትን
የክብሯን ነገር ስጨልፍ ብውል አልጨርሰውምና ዝም ልበል፡፡
No comments:
Post a Comment