© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ዘመን ሲያልፍ ዘመን ሲተካ ያለፈው ዘመን፣ ያለፈው
መንግሥት፣ ያለፈው አስተሳሰብ፣ ያለፈው አመለካከት፣ ያለፈው ፍልስፍና፣ ያለፈው ትውልድ ወዘተ የበደላቸው እና አሁን ጊዜ ያን ሁሉ
መከራ አልፈው በክብር የተቀመጡ ነገሮች ቀን ወጣላቸው እንላለን፡፡ ያለፈው ዘመን ጨለማቸው ስለነበር አሁን ላይ ብርሃን የሚያዩበት
ስለሆነ ቀን ደግሞ ብርሃንን እንጅ ጨለማን ስለማያመጣ ቀን የወጣላቸው ስንል ብርሃን የተገለጠላቸው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በድህነት
አለንጋ ሲገረፍ የነበረ ሰው በልጁ በኩል ድህነቱ ሁሉ ተገፍፎ ሃብታም የሚባል ሰው ዝናና ሞገስ የለበሰ ሰው ሲሆን አሁንማ እገሌ
ቀን ወጣለት እኮ ይባላል፡፡ አሁን ግን ስለ ሰዎች አይደለም ቀን መውጣቱን የምንነጋገረው ስለ ቃላት ነው፡፡ መንግሥት ሲለወጥ ቃላትም
አብረው ይለወጣሉ በሆነ ጊዜ በሆነ ዘመን በሆነ ማኅበረሰብ የተጨቆኑ ቃላት በሌላ ጊዜ በሌላ ማኅበረሰብ ላይ ያልፍላቸዋል ቀን ይወጣላቸዋል፡፡
እንዲያውም እነዚያ ቃላት ከመጠን በላይ ተደጋግመው ስለሚደመጡ ድሮ ግን እነዚህ ቃላት ነበሩን ያሰኛል፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ
የተፈለፈሉ ቃላት አሉ “ሕዳሴ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ አከርካሪ፣ ከማድረግ አኳያ፣ ከማድረግ አንጻር፣ ሰላማችን ይደፈርሳል፣ የልማት ቡድን
ወዘተ” እነዚህ ቃላት እና ብዙዎች አሉ ምንም ስለማይጠቅሙን ነው የተውኳቸው፡፡ እነዚህ ቃላት ድሮ ተጨቁነው የነበሩ ናቸው ማንም
የማይጠራቸው ቃላት ነበሩ ወይም የሚጠቀምባቸው ጥቂት ሰው ብቻ ነበር አሁን ግን አልፎላቸዋል እፎይ ብለዋል ቀን ወጥቶላቸዋል ብርሃን
ፈንጥቆላቸዋል፡፡ እኔ እነዚህን ያመጣሁላቸችሁ “ቃል ደግሞ ቀን ይወጣለታል እንዴ” እንዳትሉ ያህል ነው እንጅ ጉዳዬ ከእነዚህ ቃላት
ጋር አይደለም፡፡
አሁን እኔ የምሄደው ወደ ቤታችን ውስጥ ነው፡፡
እነዚህ ቃላት የፈለጉትን ያህል ቀን ይውጣላቸው በሚዲያ ዐሥር ጊዜ ይነገሩ ይተረቱ ይዘመሩ እንጅ ምኔም አይደሉም እንደማንኛውም
ሰው ከመስማት አልዘልም አልደነቅም አልገርምም፡፡ እኔን የሚገርመኝ እና የሚያስጨንቀኝ ብሎም የሚያሳዝነኝና የሚያስለቅሰኝ በቤቴ
በመኖሪያዬ በርስቴ የሚነገረው ብቻ ነው፡፡ ዛሬ በእኛ ቤትም አሉ ድሮ ያልተጨቆኑ ዛሬ ግን ድሮ እንደተጨቆኑ አስመስለን ቀን እንዲወጣላቸው
ያደረግናቸው ቃላት አሉ፡፡ ባለፈው ልኩን ያለፈ አሜን እና እልልታ በሚል መጻፌን ታስታውሳላችሁ አሁንም እደግመዋለሁ ቀን ያለፈላቸው
ቀን የወጣላቸው ቃላት እነዚህና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ በእውነት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ እነዚህ ቃላት ተጨቁነው ኖረዋልን? አረ
በፍጹም ቤተክርስቲያናችን ጭቆናን አላስተማረችም አልጨቆነችምም፡፡ ነገር ግን ቦታና ጊዜ ሰርታ ወስና ወጥና ከሽና አዘጋጅታለች እንጅ፡፡
ታዲያ ስብከት የተጀመረው ዛሬ ይመስል እንዲህ ዓይነቱን ያልተገባ ሥርዓት አልባነት ከየት አመጣነው? የዛሬ ሰባኪ አሜን ካላስባለ
ካላስጨበጨበ ያስተማረ የማይመስለው የሰበከ የማይመስለው ለምንድን ነው? በእርግጥ የመናፍቃኑ፣ የተሐድሶ መናፍቃን እንዲሁም የሌሎቹ
ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እነርሱ በእርግጠኝነት ቀድመውናል በርዘውናል፡፡ እነርሱ ያስተማሩን ትምህርት የነገሩን ቃል ነው
በጭንቅላታችን የሚያቃጭለው፡፡ በእውነት እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የሰበኩላት
የሞቱላት የተገረፉላት የተገፈፉላት የተራቆቱላት ሃይማኖታችን ተዋሕዶ እንዲህ በመድረኮቿ ላይ ማንም የሚፈነጭባት ለምንድን ነው?
ስብከት ሳንሰበክ አሜን በሉ እየተባልን የምንንገላታው አጨብጭቡ እየተባልን ዐሥሬ የምናጨበጭበው ለምኑ ነው? ምንም አልገባኝም ሥርዓት
እኮ አለን ያውም የሚያምር የሚማርክ ልክና መጠን ጊዜና ዘመን የተወሠነለት፡፡ እንዴት ከመናፍቃን አዳራሽ ቃላትን አፍልሰን ዛሬ
ላይ እንቦርቃለን? አሜን የሚለው ቃል እኮ ይሁንልኝ ይደረግልኝ ለማለት የምንጠቀመው ቃል ነው፡፡ እልልታ የሚገባው እኮ የራሱ የሆነ
ክብር ለሚያስፈልገው ነገር ነው፡፡ በብዛት የምንጠቀመው ለደስታ ጊዜ ነው፡፡ የሰማዕታትን ነገር ስንናገር “ቅዱስ ጊዮርጊስን በወፍጮ
ፈጩት” ሲባል ድምጽን ከፍ ማድረግ አይፈቀድም ሥርዓትም አይደለም፡፡ መከራ ነውና የምንናገረው ክብራቸው ጸጋቸው ትልቅ ነውና እኛ
ለዚያ ጸጋ ክብር ስለማንበቃ ድምጻችንን ዝቅ አድርገን መናገር ያስፈልገናል፡፡ ዛሬ ግን እንዲህ የሚባል ነገር የለም ምክንያቱም
ለሰማዕታት ክብር ከማይሰጡት ጋር ነዋ የሚውለው፡፡ ደምጹን ለቅቆ ጮኾ “ቅዱስ ጊዮርጊስ በወፍጮ ተፈጨ ደስ ይበላችሁ” ብሎን ያርፈዋል
እኛም እንደለመድነው “እልል እንላለን እናጨበጭባለን አሜን እንላለን” ግን ወዴት እያመራን ነው? ስለእውነት እኔ አሁን አሁን ግራ
እየገባኝ ነው ቢያንስ እስኪ እኛ እንዲህ ማለቱን እናቁመው፡፡ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ እንዲህ አሉ “ለመሆኑ እኛ ማን ሆነን
ነው እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ጸጋውን ያብዛልህ የምንለው” ልክ ነው ስንት ትልቆች ባሉበት እኛ እንዲህ እንድንደፍር ያደረገን ምንድን
ነው? እንዲህ እያለ በአባቶች ፊት የሚሰብክ ሰው ስላለን እኮ ነው፡፡ ከመናፍቃኑ አፍልሰው ወደ እኛ ያመጧቸው ቃላት ናቸው፡፡ መናፍቃኑ
ዘንድ ሁሉም እኩል ናቸው ካህን ምእመን ሴት ወንድ ጻድቅ ኀጥእ የሚባል ልዩነት የለም፡፡ ስለዚህም ማንም የፈለገውን መናገር ማስተማር
መስበክ መዘመር ይችላል፡፡ ለካህን ለዲያቆን ለጳጳስ ለምእመን ለሴት ለወንድ ለሕጻን ለአዋቂ የሚለው ነገር አይታወቅም ምክንያቱም
ማን ከማን ይበልጣል ማንስ ከማን ያንሳል፡፡ ሁሉም መስበክ ይችላል ሁሉም መዘመር ይችላል ሁሉም መፈወስ ይችላል፡፡ ለዛ ነው የእነርሱ
ሥርዓት አልባነት ወደኛም መጥቶ እንዲህ የተሸረሸርነው፡፡ በውኑ ጸጋውን ያብዛልህ የምልህ እኔ ማን የሚሉኝ ጳጳስ ማን የሚሉኝ ቅዱስ
ነኝ? የማን አባት የማን እናት ሆኜ ነው? የትኛውን ተጋድሎ የትኛውን ሰይፍ አልፌ ነው? በእውነት በጣም ያሳዝነኛል፡፡ አሁን ትውፊታችንና
ባህላችንን ክርስቲያናዊ ምግባራችንን የምንፈትሽበት ጊዜ ነው፡፡ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ቀን ያሳለፍንላቸውን ቃላት መመርመር አለብን፡፡
እነዚያ ቃላት እኮ ዛሬ ቀን ያለፈላቸው ቀን የወጣላቸው ድሮ ስለተጨቆኑ አይደለም ድሮ ሥርዓት ያከብሩ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ እኮ
መናገር እንጅ አንመርጥም ለምሳሌ ማንም ሰው ካህኑ ማት የሚገባውን “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ
ቅዱስ” እኛ በቅዳሴ ጊዜ ልንለው አንችልም፡፡ ነገ ግን ብንለው ምን ችግር አለው ዜማው በጣም ይመቸኛል ልንል እንችላለን፡፡ የዜማ
ምቾት ምን እንደሆነ አላውቅም በእርግጥ ግን ለእኛ አልተገባንም ስለዚህ ለእኛ የሚገቡንን ብቻ ልንመርጥ ይገባናል፡፡
ዛሬ እኮ የእኛ እና የመናፍቃንን ዜማ መለየት
እስኪያቅተን ድረስ የደረስን ተው ባይ አጥተን ይመቻል አይመችም እያልን ስንጨቃጨቅ ነው፡፡ በእውነት ሳናውቅ ተበልተናል ተበልጠናልም
መንቃት ያሻናል፡፡ ማነው በቤታችን የፈለገውን ነገር የሚናገርበት እኛም እኮ ድርሻ አለን፡፡ ዛሬ ስብከትን መብል መጠጥ ያደረጉ
ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ስለሥርዓቱ ስለትውፊቱ አይደንቃቸውም የተሰጣቸውን ጊዜ ብቻ መጠቀማቸውን ነው እነርሱ የሚመለከቱት፡፡ ስለዚህ
መንቃት ያስፈልገናል!!!!! ተሐድሶ መናፍቃን በዝተዋል በርትተዋል ማድከም ማዳከም ያስፈልገናል፡፡ ከእኛ ላይ ይውረዱልን በቃ የራሳቸውን
ቤተክርስቲያን ይሥሩ በዚያ ላይ የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ያድርጉ እኛ ላይ ግን አንዳች ነገር እንዳያደርጉ መጠበቅ አለብን፡፡ ከዚያ
ውጭ ከሆነ ግን የአባቶቻችን አጥንት እሾህ ሆኖ ባይወጋን ምን አለ በሉኝ፡፡
No comments:
Post a Comment