፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠


ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና በጉባያ አካባቢ ከሚገኙ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል
አንዱ ደብረ ምሕረት የረቦ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በየወሩ በቅዱስ ገብርኤል በዓል ላይ ቦታውን ተሳልሞ ቅዳሴውን አስቀድሶ የሚሄደው
ሰው ቦታውን የትልቅ ከተማ ቤተክርስቲያን ማስመሰሉ ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ ትናንት በተከበረው ክብረ በዓል ላይ በዚህ ቦታ የተገኘው
የምእመን ቁጥር በጣም በርካታ ነበር፡፡ ልብ በሉ! እንደካህናት ድካም (አለማስተማር አለመምከር አለመገሰጽ) ይህን አድርጉ ይህን
አታድርጉ ብሎ የሚያስተምር ሰው እንደመጥፋቱ መጠን በራሱ ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከብረ በዓል ላይ ተገኝቼ በረከቱን እሳተፋለሁ
ብሎ የተገኘው ሰው ቁጥር እጅጉን ያስገርማል፡፡

ይህ ቦታ አሁን አዲስ ህንጻ ቤተክርስቲያን በሚያምር ዲዛይን በማሠራት ላይ ይገኛል፡፡ የህንጻውን
ዲዛይን የተመለከተ ሁሉ “የየት ከተማ ቤተክርስቲያን ነው” ብሎ መጠየቁ ብዙዎችን ያስገርማቸዋል፡፡ ቦታው ገጠር ቢሆንም አሁን በመሠራት
ላይ ያለው ህንጻ ቤተክርስቲያን ግን የአንድ ትልቅ ከተማ ካቴድራል የሚመስል በመሆኑ ለደጀን ከተማ ጌጥ ሆኗል፡፡ የህብረተሰቡ ትጋት
ይህን ህንጻ ለመሥራት ያለው ቁርጠኝነት ጉልበቱን ገንዘቡን እውቀቱን ሳይሰስት መለገሱ ሲታይ ለደጀን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም
አርአያ የሚሆን ተግባር ነው፡፡ ህንጻው ከተጀመረ ሁለት ዓመት አልሞላውም ሆኖም ግን የህንጻው ግማሽ ክፍል ያህል የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡
በባለሙያዎች ምልከታ መሠረት ከዐርባ በመቶ በላይ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ ትናንትና ለዚህ ህንጻ ማሰሪያ በተደረገው ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ
ከአስራ ዘጠኝ ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ገጠር ቤተክርስቲያን ላይ በአንድ ሰዓት ቅስቀሳ ይህን ያህል ገንዘብ ሲሰበሰብ ለእኔ
የመጀመሪያ ጊዜየ ነው፡፡
ይህ ቦታ ገጠር መሆኑን እና ብዙ ገቢ እንደማያገኝ በዚያ ላይ አዲስ ህንጻ ቤተክርስቲያን እያሠራ
መሆኑን የዘነጉት የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ግን ከአሥር ሺህ ብር በላይ እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል፡፡
ይህን አዲስ ጅምር ህንጻ ቤተክርስቲያን ሠርቶ ለማጠናቀቅ የሁሉም ክርስቲያኖች ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡
በጸሎት፣ በጉልበት፣ በገንዘብ፣ በእውቀት ሁሉም ሊረዳ ይገባዋል፡፡ ከመልአኩ በረከት ለመሳተፍ የሚፈልግ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲባርከው
የሚፈልግ ሁሉ ሊሳተፍ ይገባዋል፡፡ በተለይ ደግሞ #የደጀን_ተወላጆች ይህ ጉዳይ ይመለከታችኋል፡፡ ከደጀንም በተለይ #የጉባያ_ልጆች
የግድ ይመለከታችኋል፡፡ ጉባያ በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው በኩል ብዙ ሊቃውንት አሏት ስለዚህ የዚህ ህንጻ ጉዳይ ይመለከታችኋል፡፡
ቦታው ላይ ከህንጻ ቤተክርስቲያኑ በተጨማሪ በርካታ ሥራዎችን መሥራት የሚገባን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ስለዚህ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችንም
መሥራት ስለሚኖርብን ድምጻችሁን ልታሰሙ ይገባል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ይህ ህንጻ ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅ እንኳ ሥርዓተ
ማኅሌቱ በዚሁ ቦታ እንዲደረግ በርካታ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ታህሳስ ፳
/ ፳፻፲ ዓ.ም
የረቦ ደጀን፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment