Wednesday, August 26, 2015

ዓለም ለበርባን ናት /ክፍል አራት/

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተሐድሶ መናፍቃኑ ያሰባሰቧቸው የአፍ ደጋፊዎች በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛዎች እገሊት እገሌ ካጠመደባት ወጥመድ ነጻ ሆነች፣ እገሌን እንዲህ የሚባለው ማኅበር አስደበደበው ሃብት ብረቱን ዘረፈው እያለች ደጋፊዋን ትለቃቅማለች፡፡ እውነት በቤተክርስቲያን ያደገ ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንጅ ከበርባን ምን ሊማር ይችላል? በርባን እህቱን ሰጥቶ ከእስር ቤት ሊወጣ ይጥራል ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ከኃጢአት ነጻ ሊያወጣ ከመስቀል ላይ ይሰቀላል፡፡ ምንም ኅብረት የላቸውም፡፡ የደጋፊ ብዛትና ቁጥር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ካልሆነ በቀር ሃይማኖት ውስጥ ምን ቦታ አለው? ዘረኝነት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው ይችላል? በእውነት በተዋሕዶ እምነት ውስጥ ያለ ግለሰብ ወይም ማኅበር በግለሰቦች ላይ ወይም በማኅበራት ላይ ወጥመድ የሚያጠምደው ለምንድን ነው? ማንንስ ለማጥመድ ይሞክራል? የሚጠመደውስ ለምን እንደሚጠመድ ያውቃልን? መጠማመድ እዚህ ውስጥ ምን አገባው? መጥመድ መጠመድ ያለው በእርሻ ሥራ ላይ ብቻ ነው በእርግጥ እሱም ትራክተር እየተካው ስለሆነ መጥመድና መጠመድ አየቀረ ነው፡፡ ታዲያ እርሻ ላይ የቀረው መጠማመድ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ብሎ ሊመጣ ቻለ? አንዳንዴ እንቆቅልሽ ነገር ይመስላል፡፡
በእርግጥ ዓለም ለበርባን ናት፡፡ በርባንን ትደግፈዋለች፣ ታሞግሰዋለች፣ ትሸልመዋለች፣ ታከብረዋለች፣ ታጨበጭበለታለች ግን ለምን? መልሱን መመለስ አትችልም፡፡ በርባን የወንበዴዎች አለቃ ነው ብለናል፡፡ ታዲያ አጨብጫቢዎችስ ምን ሊባሉ ይችላሉ? የወንበዴዎች አለቃ መሆኑን አምነው የሚያጨበጭቡ አሉ፣ወንበዴ መሆኑን ሳያውቁ ሰዎች ስላጨበጨቡለት ብቻ አብሮ አለ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ማጨብጨብ ደስ ስለሚላቸው ብቻ የሚያጨበጭቡለት ናቸው፡፡ የወንበዴነቱን አለቅነት አውቀው የሚያጨበጭቡ ሰዎች ሳያውቁ የሚያጨበጭቡለትን ሰዎች ቁጥር ለማብዛት ይጥራሉ፡፡ አሁን እያየን ያለው ነገር እርሱን ነው፡፡ ሃገር ውስጥ አልበቃ ብሏቸው እስከ ሃገር ውጭ ድረስ መስመራቸውን ዘርግተዋል፡፡ የማኅበራዊ ድረገጾች እና መገናኛዎችም እንደ ታንቡር ይደልቃሉ እንደ ደወልም ያቃጭላሉ፡፡ የዋሃንን ለማታለል ብዙ የበርባን ደጋፊዎች ብዙ ነገር ይጥራሉ ብዙ ሥራን ይሠራሉ፡፡
ጹሙ፣ ጸልዩ፣ ንስሐ ግቡ ብሎ ደፍሮ የማያስተምርና ደፍሮ የማይዘምር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት የማይናገር ስለ ድንግል ዘላለማዊ ድንግልናና ክብር የማይናገር ምሥጢራትን ጠንቅቆ የማያስተምር መምህር እና ዘማሪ ለተዋሕዶ አይረባትም አይጠቅማትምም፡፡ መናፍቃን የሚናገሩትንና የሚያስተምትን የሚዘምሩትንና የሚናገሩትን ገልብጠው በቤታችን መጥተው ከመድረኮቿ ላይ ቆመው በነጭ ልብስ ተጎናጽፈው የሚለፈልፉ ተሐድሶ መናፍቃን በርባንን ፍቱልን የሚሉ ናቸው፡፡ ታዲያ ለእነዚህ ማጨብጨብ ማለት ምን ማለት ነው? ምንም ሊገባኝ አይችልም፡፡ አምላክ ልብ እንዲሰጣቸው ጸልዩ በማለት ፋንታ ማጨብጨብን ምን አመጣው? ቆም ብለን ልናስተውል ይገባል፡፡ ስለ እውነት ግን የትኛው መዝሙራቸውና ትምህርታቸው ነው የቤተክርስቲያናችን ጣዕምና ለዛ ያለው? ነገር ግን ዓለም ለበርባን ናትና ዛሬም ድረስ አጨብጫቢዋን ትፈልጋለች፡፡
ተፈጸመ

ዓለም ለበርባን ናት /ክፍል ሦስት/

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በኃጢአት የረከሰችውን ዓለም በደሙ ለመቀደስ ወደዚህ ምድር የመጣው አምላካችን የሕጻናትን ልማድ ሳያፋልስ በጥቂት በጥቂቱ አደገ “በበህቅ ልህቀ” እንዲል፡፡ አምላክ ነኝና መዳህን አልፌ ልቁም ሳይል፣ አምላክ ነንና ቶሎ ወጣት ልሁን ሳይል ከኃጢአት በቀር እንደኛ ሰው ሆነ፡፡ በሰላሳ ዓመቱ በማየ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ከዚያም ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆርንቶስ ሄዶ በዚያ ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋ ሳያጥፍ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ ጸለየ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ሊፈትነው ወደደ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ያልተረዳው ወራዳው ዲያሎስ በሦስት ትላልቅ ኃጣውእ ፈትኖታል፡፡ ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ ማቴ4ን ይመልከቱ እነዚህን ፈተናዎች እንደአመጣጣቸው በሚገባ አድርጎ ሰይጣንን አሳፍሮ አሸንፎታል፡፡ ከዚህ ከ40 ቀንና ሌሊት ጾም በኋላ በተለያዩ ቦታዎች እየዞረ አስተምሯል፡፡
እንግዲህ ዓለም 5 እንጀራና ሁለት አሣ ማበርከቱን አይታ አምስት ገበያ ሆና ትከተለዋለች፡፡ ከበረከቱ በልታ ፍርፋሪውን ታነሣለች፡፡ ድውያንን ሲፈውስ ሙታንን ሲያነሣ ተመልክታ ከድውይነቷ ለመፈወስ ትከተለዋለች ስትድን ዞራ አታየውም፡፡ ዓለም ሲርባትና ስትታመም ብቻ የምትከተለው ሆነች፡፡ እንዲያውም ሙት ማንሣቱ ድውይ መፈወሱ አበርክቶ መመገቡ ነውር ነቀፋ ሆነበት፡፡ ዓለም ስትበላና ስትፈወስ እንጅ ስትራብና ስትታመም የነበረባትን መከራ ማሰብ ተሳናት፡፡ በዚህም የተነሣ የአይሁድ ካህናት ለግርፋት ለስቅላት ብሎም ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት አግኝተንበታል ብለው ተነሣሱ ለንጉሣቸውም ከሰሱት፡፡ ከበላው የበላ ከጠጣው የጠጣ ካደረበት ያደረ ከዋለበት የዋለ አንድ 30 ብር እና ብልጠት ያታለለው ይሁዳ ለካህናት አሳልፎ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ይሁዳ 30 ብር ዓይኑን ሰወረው ስሞ አሳልፎ ሰጠው፡፡ንጉሣቸው ሁሉንም ነገር መረመረው ከአፉ ሀሰት አጣበት እንዲህ ዓይነቱን ይሾሙታል ይሸልሙታል እንጅ እንዴት ይፈርዱበታል ብሎ ሰጣቸው፡፡ እርሱ ግን ይሙት በቃ እንዲፈረድበት አብዝተው ጮሁ፡፡  አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በጲላጦስ አደባባይ ነው ምንም ወንጀል ሳይኖርበት እንደወንጀለኛ ለፍርድ ቆመ፡፡ የ38 ዓመት በሽተኛ ማዳኑ ቤተመቅደሱን አፍርሱት በ3ኛው ቀን አነሠዋለሁ ማለቱ ለሞት እንደሚያበቁት ሃናና ቀያፋ አሰምተው ተናገሩ፡፡ ይሰቀል ይሰቀል ይሰቀል በሞት አስወግድልን የሚሉ ድምጾች አስተጋቡ፡፡ ዓለም ያበላትን፣ ያጠጣትን፣ የፈወሳትን ፈጣሪዋን ልትሰቅል ተቻኮለች፡፡
እንደ እስር ቤቱ ዘበኞች አቆጣጠር አራት ወንበዴዎች ተይዘዋል፡፡ እንደ አይሁድ ካህናት እና እንደእኔ አቆጣጠር ግን 3ናቸው ሦስትነታችን ግን ለየቅል ነው አይገናኝም አይስማምም፡፡ ወንበዴዎቹም ለዘበኞቹ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ጥጦስ፣ ዳክርስና በርባን እንደ አይሁድ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ጥጦስና ዳክርስ እንደእኔ ደግሞ ጥጦስ፣ ዳክርስና በርባን ናቸው፡፡ እንግዲህ ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ ያሉት በሙሉ ወንበዴዎች፣ ቀማኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የእነርሱ ተቃራኒ ነው፡፡ የሞቱትን የሚያሥነሳ፣ የታመሙትን የሚፈውስ፣ ለምጻሞችን የሚያነጻ ነው፡፡ ነገር ግን እኩል ታስረዋል፡፡ እንደልማዳቸው ለበዓል ከታሰሩ አራት እስረኞች መካከል አንዱን ይፈታሉ ሦስቱን ደግሞ ይሰቅላሉ፡፡ ኢየሱስን ልፍታላችሁ ሌሎችን ግን ስቀሉ አላቸው ፈራጁ፡፡ ነገር ግን ዓለም ለበርባን የተስማማች ናትና ነፍሰገዳዩ በርባን፣ ቀማኛው በርባን፣ ወንበዴው በርባን (እንዲያውም የወንበዴዎች አለቃ ነው) እንዲፈታላት ኢየሱስ ግን እንዲሰቀልላት ጮኸች፡፡ በእርግጥ ነው ኢየሱስ ካልተሰቀለላት ዓለም ከታመመችበት የኃጢአት በሽታ እንደማትድን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እርሷ መድኃኒቷን አታውቅም፡፡
በርባን የይሁዳ የሚስቱ ወንድም ነው፡፡ ይሁዳ 30 ብር የተመዘነለት ኢየሱስን አሳልፎ ሊሰጥና የሚስቱ ወንድም በርባን እንዲፈታለት ነው፡፡ በርባን ድጋፍ አለው፣ በርባን ቀማኛነቱን እንደያዘ አይሁድ ደግፈውታል፡፡ ዓለም ለቀማኞች ናት፣ ዓለም ለወንበዴዎች ናት፣ ዓለም ለዘራፊዎች ናት ለዚያም ነው መድኃኒቷን ይሙት በቃ ፈርዳ ለበርባን የምታጨበጭብ፡፡ ኢየሱስ ለመስቀል ሞት ተላልፎ ተሰጠ ሁለቱ ማለትም ጥጦስና ዳክርስም እንዲሁ አብረውት ወደ ቀራንዮ ወጡ ዓለም ያጨበጨበችለት በርባን ግን በነጻ ተለቀቀ፡፡ ዓለም የምትፈልገው ትእግስተኛን አይደለም፣ ዓለም የምትፈልገው ትህትና የተላበሰን አይደልመ፣ ዓለም የምትሻው የሚሰጥን አይደለም፣ ዓለም የምትፈልገው መድኃኒት አይደለም፣ ዓለም የምትፈልገው መልካም ትምህርት አይደለም፣ ዓለም የምትሻው የኢየሱስ ክርስቶስን ማዳንና ፈውስ እንደሁም የእርሱን መድኃኒትነት አይደለም የበርባንን ውንብድና ብቻ ነው፡፡ ለበርባን እጃቸው እሰኪዝል አጨበጨቡለት ኢየሱስን ደግሞ እጃቸው እስኪዝል ድረስ ደበደቡት፡፡ ሥጋውን ያበላው ደሙንም ያጠጣው ይሁዳ እንኳ ሳይቀር ለበርባን አጨበጨበ፡፡ የበላበትን ጣት ነከሰ ሰላሳ እንጅ ገነትን የሚመለከትበት ዓይኑ ታወረ፣ በርባንን እንጅ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያስብበት ኅሊናው ተገፈፈ፡፡
አሁን በቤተክርስቲያናችን እየተፈጠረ ያለው የአይሁዳውያኑ (የተሐድሶ መናፍቃን)  ጫጫታ በርባን ይፈታልን ኢየሱስን ስቀልልን የሚል ይመስላል፡፡ እገሊት እገሌ ካጠመደባት ወጥመድ ነጻ ሆነች፣እገሌ እንዲህ የሚባለው ማኅበር አስደበደበው ሃብት ንብረቱን ዘረፈው እያለች ደጋፊዋን ትለቃቅማለች፡፡

ይቆየን

Friday, August 21, 2015

ዓለም ለበርባን ናት /ክፍል ሁለት/

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አዳም ተስፋ ያደረጋት አምላክ ከ5500 ዘመን በኋላ እናቱ አድርጎ ያለአባት የሚወለድላት እመብርሃን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ከእናቷ ሃና እና ከአባቷ ኢየቄም በደብረ ሊባኖስ ተወለደች፡፡ አምላክም ከአንስተ ዓለም መርጦ ማደሪያው ትሆን ዘንድ ወደዳት፡፡ ዮሴፍን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አክብሮ ከነገረኝ ነገር ውጭ ሌላ አላውቅም ያለችው ድንግል ማርያም በድንግልና የመጽነሷ ነገር ግሩም ሲባል ይኖራል፡፡ በእውነትም ግሩም ነው ግሩም በሚለው ቃል መግለጽ ከተቻለ አቻ ቃል የለውምና ግሩም አንላለን፡፡ አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወለደችው፡፡ ሰዓሊ ለነ ቅድስት የምንላት እኮ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ፣ ጽንእት ስለሆነች ነው፡፡ ንጽሕት የምንላት ሌሎች ሴቶች ቢነጹ ከነቢብ፣ ከገቢር ነው የሀልዮ (የማሰብ) ኃጢአት አለባቸው እርሷ ግን ከሀልዮ፣ ከነቢብ፣ ከገቢር ንጽሕት ናት፡፡ ክብርትም የምንላት ሌሎች ሴቶችን የምናከብራቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ መነኮሳትን፣ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ዲያቆናትን ወለዱ ብለን ነው እርሷን ግን ወላዲተ አምላክ ብለን ነው፡፡ ልዩም የምንላት ሌሎች ሴቶች ድንግል ከሆኑ እናት እናትም ከተባሉ ድንግል አይባሉም እርሷ ግን ድንግል ወእም ናት፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች ከእመቤታችን ሌላ ሴት አትገኝምና ልዩ እንላታለን፡፡ ጽንእትም የምንላት ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው በኋላ ተፈትሆ አለባቸው እርሷ ግን ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድህረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድህረ ወሊድ ተፈትሆ የለባትም፡፡እንገዲህ አምላክ ትንቢቱን ባናገረላት ምሳሌውን ባስመሰለላት ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ለመንሣት በእርሷ አደረ፡፡ ለምን ከድንግል ተወለደ ብንል፡ ትንቢት ስላለ ነው፡፡ “ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ” እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፡፡ ኢሣ7÷14፡፡ ይህ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከድንግል ተወለደ፡፡ ለመወለዱ ምክንያት ግን ክፍል 1 ላይ እንደተመለከትነው የአዳም መሳት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍጹም ፍቅር እንረዳ ዘንድ ወደ ምድር መጣ፡፡ ቅዱስ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዳነሣው “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ” ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው ይላል፡፡ ይህ ፍቅር ግን በቃላት የሚገለጥ ፍቅር አይደለም ከቃላት ሁሉ በላይ ነው፡፡ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ ወዮ ለዚህ አንክሮ ይገባዋል፡፡ አምላክ በከበረ ዙፋኑ ሆኖ ሳይወለድ፣ ሳይሰደድ፣ ሳይሰቀል፣ ሳይሞት፣ ሳይነሣ፣ ሳያርግ አዳምን ከደብር ቅዱስ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት መመለስ ይቻለው ነበር ነገር ግን ፍቅሩን ሊገልጥልን መጣ አንድም ትንቢቱን ለመፈጸም መጣ፡፡ አሁን ዘመን የማይቆጠርለት አምላካችን ዘመን ተቆጠረለት፡፡ በ 30 ዓመቱ ተጠመቀ፣ 3 ዓመት ከ3 ወር አስተማረ እያልን ዘመኑን እንቆጥርለታለን፡፡ ምንም ምን ሊወስነው የማይችለው አምላክ 3 ክንድ ከስንዝር በሆነ ቁመት ተወሰነ፡፡ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፡፡ ለዚህ ሁሉ አንክሮ ይገባል፡፡ የአምላክ ወደዚህ መምጣት ከድንግል መወለድ በግብጽ በረሃ መሰደድ በቀራንዮ መሰቀል፣ በጎልጎታ መቀበር፣ ከመቃብሩ በሥልጣኑ መነሣት፣ በቢታንያ ወደ ሰማይ ማረግ ምን ይረቅ ምን ይደንቅ፣ ምን ይጠልቅ፡፡
አምላካችን አዳምን የሚያድነው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የዓለም ትልቁ ስህተት፡፡ ዓለም ለፈጣሪዋ አልተመቸችም፣ ዓለም ሊፈውሳት ሊያድናት የመጣላትን መድኃኒት አልቀበልም አለች፡፡ ዓለም ድጋፍ የምታደርገው ለኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም ለበርባን ነው፡፡

ይቆየን

Thursday, August 20, 2015

ዓለም ለበርባን ናት /ክፍል አንድ/

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዓለም የምላችሁ ይችን እኛ የምንኖርባትን ምድር ነው፡፡ ብዙ ዓለማት ስላሉ ነው እንዲህ ያልኳችሁ፡፡ የፍጡራን ሁሉ ተቀዳሚ የሆነው አዳም በተድላ ሊኖርባት ከተፈጠረችለት ገነት በዕለተ ዓርብ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ” ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር ዘፍ1÷26 ብሎ እግዚአብሔር ፈጠረው፡፡ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም እንዳልሆነ የሚያውቅ ፈጣሪ ረዳት አጋዥ የምትሆነውን ከግራ ጎኑ አንዲትን አጥንት ነሥቶ ሴትን (ሄዋንን) ፈጠረለት፡፡ ዘፍ2÷23 ለሰባት ዓመታት ያህል በተድላ በደስታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የሰባውን እያረዱ ያሸተውን እየተመገቡ ኖሩ፡፡ አዳም የእንስሳትን ሁሉ ስም እያወጣ እየባረከ ይሰዳቸው ስለነበር ስም እንዲወጣለት እንደ ላም አራት እግር የነበረው እባብም ወደ አዳም ይጓዝ በነበረበት ጊዜ ዲያብሎስ ራሱን ሰውሮ ከአዳም ዘንድ ከገነት ገባ፡፡ አዳም ከመላእክት እንደተማረው ጸሎት ያደርግ ነበር ሄዋን ግን እግሯን ዘርግታ ነበር የተገኘችው፡፡ ሰይጣን “ሰላም ለከ ኦ አዳም ንጉሠ ሰማያት ወምድር” አለው አልተቀበለውም ወደ ሄዋን ሄደ “ሰላም ለኪ ኦ ሄዋን ንግሥተ ሰማያት ወምድር” አላት ተቀበለችው፡፡ ሄዋን ፈጣሪ የሰጣትን ትእዛዝና ምሥጢር ለጠላቷ አሳልፋ ሰጠች፡፡ በገነት ሶስት ዕጽዋት አሉ፡- ብሉ የተባሉት፣ አትብሉ የተባሉት (ዕጸ በለስ)፣ ብሉም አትብሉም ያልተባሉት (ዕጸ ሕይወት) ናቸው፡፡ ሄዋን ለዲያብሎስ የነገረችው ክፉና ደጉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ፍሬ አትብሉ ብሎናል ከእርሷም የበላችሁ እንደሆነ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ብሎናል ብላ ነገረችው፡፡ ዲያብሎስ ግን አትሞቱም ምስጢር ይገለጥላችኋል እንደ እርሱም አምላክ ትሆናላችሁ አላት፡፡ አዳም አልተቀበለውምና ለዚያ ለባልሽም ንገሪና አብዪው አንቺ ብቻ አምላክ እንዳትሆኚ ሁላችሁም አምላክ እንድትሆኑ ብሎ አሳመናት፡፡ እርሷም ቆረጠች በላች ለአዳምም አበላች ሁለቱም ከክብር ተዋረዱ፡፡ ቀድማ በልታው ቢሆን ኖሮ አዳም ከክብር ስትራቆት ሲያያት አልበላም ባለ ነበርና አዳም ቀድሞ በልቶ ቢሆን ኖሮም ሄዋን የአዳምን መራቆት አይታ አልበላም ባለች ነበርና ነው አንድ ላይ እንዲበሉ ያደረጋቸው፡፡ /ዘፍ3 በሙሉ/
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አዳምና ሄዋንን ከገነት አባረራቸው ወደ ሕይወት ዘፍም የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በገነት ምሥራቅ አስቀመጠ፡፡ ዘፍ 3÷24 ከላይ ያየነው አንዱ ዕጽ ብላም አትብላም ያላለው ነው ይህ ዕጽ ዕጸ ሕይወት ይባላል፡፡ አዳምና ሄዋን ትእዛዙን ጠብቀው ቢሆን ኖሮ ከ 1000 ዘመን በኋላ እርሱን በልተው ታድሰው መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ነበር፡፡ ለዛ ነው ገነት ገብተው ያችን የሕይወት ዛፍ እንዳይበሉ ገነትን በኪሩቤል ያስጠበቃት፡፡ ገነት አሁን ያለች ቅዱሳን የሚገቡባት መንግሥተ ሰማያት ደግሞ ከምጽአት በኋላ የምትከፈት በገነት የነበሩ ቅዱሳን ለዘላልም የሚገቡባት ናት፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አዳምና ሄዋን ከገነት ከተባረሩ በኋላ በገነት አንጻር ወዳለች ደብር ቅዱስ ተቀመጡ፡፡ እግዚአብሔር አዳምና ሄዋንን ከደብር ቅዱስ ማስቀመጡ ገነትን ፊት ለፊት እያዩ ወደ ቀደመ ቦታችን ወደ ቀደመ ክብራችን ይመልሰን ይሆን እያሉ ተስፋ እንዳይቆርጡ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ከዕለታት አንድ ቀን አዳም “እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ ባንቺ ምክንያት አጣሁ” ብሎ ሄዋንን ተቆጣት፡፡ እርሷም ደንግጣ ሮጠች ርቃም ሄደች፡፡ አዳም መላእክት እንዳስተማሩት ጸሎት ሲያደርስ መልአኩ መጥቶ ምን ዋጋ አለው የመስተቀይምን ጸሎት እግዚአብሔር አይሰማ አለው፡፡ በእርሷ ምክንያት ገነትን ያህል ቦታ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ አጥቻለሁና እንዴት አልቀየም አለ፡፡ በእርሷ ምክንያት ያጣኸውን ቦታ በእርሷው ምክንያት ታገኘዋለህ ብሎ ነገረው፡፡ እንግዳስ አምጣልኝ አለው መልአኩም አንተው ሄደህ አምጣት ብሎታል ምንም ተርታ ሴት ብትሆን ወንድ ማልዶ ያመጣታል እንጅ ሴት አትማልድም ይህ ከአዳም የመጣ አብነት ነው፡፡ አዳም ሄዶ ሄዋንን ያመጣታል ከዚህ በኋላ አንድ ቀን ሲጨዋወቱ እግዚአብሔር ይቅር አይለንምን? ብላ አዳምን ትጠይቀዋለች፡፡ ምን ይሆናል አንቺ አለሽ እንጅ እርሱስ ይቅር ይለን ነበር ይላታል፡፡ ሁለቱም የ40 ቀን ሱባኤ ይገባሉ በ 35ኛው ቀን ሰይጣን መልአከ ብርሃን መስሎ መጥቶ አስወጥቷታል አዳምም መልአኩ አትራቃት ብሎት ነበርና ሱባኤውም አቋርጦ ይወጣል፡፡ ሰይጣንም አዳምና ሔዋንን እየመራ ከእግረ ገነት አደረሳቸው ከዚያም ቦታ ሲደርሱ አርአያውን ቀይሮ በድንጋይ ይፈነክተዋል፡፡ ከዚያ ላይ ሶስት ቀን ያህል ወድቆ ይሰነብታል ኅሊናው ሲመለስለት ተነሥቶ የፈሰሰ ደሙን አእዋፋት በሚያመጡለት ፍሬ ለውሶ መሥዋእት ያቀርባል፡፡ አርሱም ተስፋውን ይቀበላል፡፡ መልአኩ በርሷ እንደ ወደቅህ በእርሷ ትነሣለህ በእርሷ እንደወጣህ በእርሷ ትገባለህ ያለው ሊፈጸምለት ነው፡፡ “በኃሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ” ከ5 ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ አለሁ፡፡ ልጅ ልጁ የተባለች አመብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ አባ ሕርያቆስ “አንቲ ውእቱ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት” አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተሳፋው አንቺ ነሽ ብሎ በቅዳሴው ያመሰግናታል፡፡ እንግዲህ የአዳም ተስፋ ማለት ይህ ነው፡፡ 5 ቀን ተኩል ማለት 5500 ዘመን ማለት ይህንን ዘመን በተስፋ መኖር ነበረበት፡፡ ልጆች ተወለዱለት የልጅልጆችም እንዲሁ ትውል ያልፋል ትውልድ ይተካል እንዲህ እያለ 5500 ዘመን ሲፈጸም ቃል ከእምቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ይዋሃዳል፡፡ ይወለዳል የአዳም ተስፋ ይፈጸም ዘንድ በጽኑ ቀጠሮው ከሰዓቷ ሰዓትን ከደቂቃዋ ደቂቃን ከሰከንዷ ሰከንድን ሳያፋልስ ይወለዳል፡፡

ይቆየን 

Monday, August 17, 2015

ሽታ አልባው አበባ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እኔ ነኝ ያውም እኔው ራሴ አበባ ነኝ ያውም ሽታ አልባው፡፡ አበባነት ደረጃ ላይ ለመድረስ እግዚአብሔር ብዙ ነገርን ሰጥቶኛል፤ መስጠት ብቻም አይደለም ብዙ ነገርን አድርጎልኛል፡፡ ከማብቀል ጀምሮ ግንድና ቅርንጫፎቼን እስከማጠንከር ድረስ የአምላኬ ድርሻ ነው፡፡ “እስመ አንተ አውጻእከኒ እምከርሥ ወተወከልኩከ እንዘ ሀለውኩ ውስተ አጥባተ እምየ፡፡ ላዕሌየ ተገደፍኩ እማኅጸን፤ እምከርሠ እምየ አንተ አምላኪየ” ከማኅጸን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ፡፡ መዝ 21÷10 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት እኔንም እንዲሁ ነው ከእናቴ ሆድ ጀምረህ የጠበቅኸኝ፡፡ ዳግመኛም “እስመ አንተ ተስፋየ እግዚኦ እግዚእየ ተሰፈውኩከ እምንእስየ ወብከ ጸናእኩ በውስተ ከርሰ እምየ ወበውስተ ማኅጸን አንተ ከደንከኒ”  አቤቱ አንተ ተስፋየ ነህና እግዚአብሔር ሆይ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛየ ነህና ከማኅጸንም ጀምሮ ባንተ ተደገፍኩ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያየ ነህ” መዝ 70÷5-6 አለ ቅዱስ ዳዊት፡፡ በእናቴ ሆድ 9 ወር ከ5 ቀን ጠበቅኸኝ ከዚያም ወደዚህ ዓለም እንድመጣ ፈቀድህ፡፡ ምንም እንኳ በኃጢአት የተጸነስኩ ይሁን አይሁን ባላውቀም እንደ ዳዊት “እስመ ናሁ በኃጢአት ተጸሰነስኩ ወበአመጻ ወለደተኒ እምየ” እነሆ በአመጻ ተጸነስኩ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ፡፡ መዝ 50÷5 በኃጢአትም ይሁን በጽድቅ ለኃጢአትም ይሁን ለጽድቅ አምላክ እርሱ ባወቀ ተወለድሁ፡፡ ከመወለድ ጀምሮ ማደግን አምላክ በማያልቅ ቸርነቱ አደለኝ፡፡ ከልጅነት እስከ አዋቂነት፣ ከኩተት እስከ ሽበት በሚዘልቀው የዘመናት ቅብብሎሽ ሁሉ አምላኬ አልተለየኝም፡፡ አሁን የወጣትነት ዘመን ላይ ወይም የጉልምስና ዘመን ላይ ልሆን እንደምችል እገምታለሁ፡፡ ከማኅጸን ጀምሮ የጠበቀኝን አምላክ በመወለዴ እንዳመሰገንሁት ለዚህ ጊዜም ያደረሰኝ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፡፡ የዛሬም ጸሎቴ እንዲሁ ያው የቅዱስ ዳዊት መዝሙር ነው፡፡ “ኢትሰደኒ በመንፈቀ ዓመትየ” በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ መዝ101÷24 እያልኩ እማጸነዋለሁ፡፡ የሰው ልጅ ዕድሜው 70 ዓመት ነው ቢበዛም 80 ዓመት እንደሆነ ዳዊት ይናገራል፡፡ እንግዲህ በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ እያልኩ የምጸልየው በ35 አልያም በ 40 ዓመቴ አትውሰደኝ ለማለት አይደለም፡፡ የዘመኔ እኩሌታ ፍሬ አልባ የሆነው ዘመኔ ነው፡፡ በዚያ ፍሬ በሌለበት ቅጠል ብቻ በሆንኩበት ዕድሜየ ቢበዛም ፍሬ ለማፍራት በማይችለው እንቡጥ አበባ በሆንኩበት በለጋ ዕድሜየ አትውሰደኝ አትቅሰፈኝ ማለቴ ነው፡፡ ህይወቴ ወተትን ብቻ እመገብ ከነበረበት ሕጻንነቴ እስከ አሁን አጥንትን ሳይቀር መቆርጠም እስከምችልበት ጎልማሳነቴ ድረስ ለዘር ለፍሬ የበቃ ምግባር እንደሌለኝ የማውቀው እኔው ራሴ ነኝ፡፡ የራሴን ህይወት የምመለከተው በራሴ መነጸር ብቻ አይደለም በእግዚአብሔር ቃልና ስለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ደማቸውን ባፈሰሱት ሰማእታት እንዲሁም በጾም በጸሎት በኖሩት በቅዱሳኑ ተጋድሎ ውስጥ ጭምር ነው፡፡ አሁን አበባ ነኝ ያውም ዘር የማያፈራ ለምልክት ብቻ የተቀመጥኩ ለጌጥ ከምግብ ጠረንጴዛ ላይ የኖርሁ አበባ ነኝ ያውም የማልሸት አበባ…
ተራሮችን በአበቦች የሚያስጌጥ አምላክ አኔንም አበባ አደረገኝ፡፡ እንዲያውም ሰው የሆኑ ሰዎችን ለማስተማር ጌታችን ተጠቅሞብኛል፡፡ “ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ማቴ 6÷28-29፡፡ ዛሬ እኔ አበባ ነኝ ለጌጥነት ማንም ሊጠቀምብኝ የሚችል፡፡ በጌጥነቴ እና ውብ በመሆኔ ግን የምማርከው ንቦችን እና ቢራቢሮዎችን ብቻ አይደለም፤ ማንም ተራ የሚባለውንም ሰው ብቻ አይደለም እኔ የምማርከው ንጉሡንም ጭምር ነው፡፡ ሰሎሞን ንጉሥ ነው ነገር ግን እኔ ባጌጥኩበት መጠን አላጌጠም እኔም በከበርኩበት መክበር አልከበረም፡፡ ለዛም ነው ሁሉንም ወደ እኔ የመሳብ ችሎታ ያለኝ፡፡ ነገር ግን አበባ መሆኔ ብቻ አይደለም ለዚህ ክብር ያበቃኝ መልኬ ደም ግባቴ እና ሽታየ ጭምር ነው እንጅ፡፡ ብዙ አበቦች አሉ በተለያየ ኅብረ መልክ የሚታዩ፤ ብዙ አበቦች አሉ በተለያየ መልኩ ለአፍንጫ የሚሸቱ፡፡ ታዲያ እንደ መልካችንና ሽታችን እንለያያለን፡፡ ሰው የሚመለከተን አበባ መሆናችንን ብቻ ሊሆን ይችላል ግን የማንሸት አበቦችም እንዳለን ልብ ልትሉ ያስፈልጋል፡፡
“በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ፡፡ በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርሷ መጣ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትም” ማቴ21÷ 18-19 ይች ዛፍ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ታሪክ አላት፡፡ እርሷ ለእይታ በጣም ማራኪ ናት ለተራበ ሰው ደግሞ እጅግ በጣም ሲበዛ  ማራኪ ናት፡፡ ነገር ግን ለጥላነት ካለሆነ በቀር ለምግብነት የሚሆን ነገር የላትም፡፡ በሩቅ ለሚመለከታት ቀርቦ ላልፈተሸት ግን ፍሬ ያላት ለርኁባን ጥጋብን የምታድል ትመስላለች፡፡ እኔም ብሆን አበባ መሆኔ እንጅ እንደ እርሷ ነኝ፡፡ ሰው ዛፏን የሚቀርባት የሚበላ ነገር ለመፈለግ ነው እኔን ግን የሚጠጋኝ በመልኬ አልያም በሽታየ ተማርኮ ነው፡፡ ነገር ግን አልሸትም አለመሽተቴ የሚታወቀው ግን ለቀረበኝ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን አስመርቄያለሁ፣ ብዙ ሰዎችን አጋብቻለሁ፣ የብዙዎችን ቤት አጊጫለሁ ነገር ግን አልሸትም፡፡ ሰዎች ለምረቃ ገዝተው ለስጦታነት ያበረክቱኛል፣ ለቤታቸው ጌጥነት ይጠቀሙብኛል፣ በጋብቻቸው መካከል የፍቅር ማሞቂያነት ይጠቀሙብኛ፡፡ ነገር ግን ለራሴ አበባ አይደለሁም ለሰዎች ግን ስላላስተዋሉኝ አበባ ነኝ፡፡ አበባ ለመባል ቀለሜ ብቻውን በቂ አልነበረም ሽታየም ተገቢ ነበር ግን ሰዎች አላስተዋሉም፡፡
የእኔ ህይወትም እንደዚህ አበባ ነው ሽታ የሌለው አበባ፡፡ ሰዎች እንደ ትልቅ ሰው የሚቆጥሩኝ፣ የበለሷን ዛፍ የመሰልኩ አለባበሴ ከሩቅ የሚማርክ፣ አነጋገሬ በቅርብ የሚያሳምን፣ ለእይታ ማራኪ፣ ለሚዳስሰኝ እጅግ በጣም ለስላሳ ቅጠል ያለኝ ነገር ግን ፍሬ አልባ ዛፍ፡፡ ነገር ግን ሽታ አልባ አበባ፡፡ አበባው እኔ ነኝ ሽታው ደግሞ ምግባሬ ነው፡፡ ከጌጥነት ከቁጥር የዘለለ ጥቅም የማልሰጥ ከንቱ ሽታ አልባ አበባ፡፡ በተፈጥሮ ከሚገኘው መልክና ሽታው ማራኪ ከሆነው አበባ ጋር ተመሳስየ በሰው እጅ በፋብሪካ የተሰራሁና የተመረትሁ አበባ፡፡ በቃ እኔ ሰው ሰራሽ ሽታ አልባ አበባ ነኝ፡፡

Tuesday, August 11, 2015

ፍርድማ ይች ናት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ፍርድ ከአንድ አካል ውሳኔ በላይ ነው፡፡ ፍርድ ለመፍረድ የሚፈረድበት ነገር ያስፈልጋል፡፡ ሳይጀመር ሲጠቀለል ፍርድ የፈራጅ፣ የአስፈራጅና የተፈራጅ መስተጋብር ነው፡፡ ፍርድ ካለ ፈራጅ አለ ፈራጅ ካለ ተፈራጅ አለ ተፈራጅ ካለ አስፈራጅ አለ ማለት ነው፡፡ ፈራጅ በተፈራጅ ለመፍረድ አስፈራጅም በተፈራጁ ለማስፈረድ ግን ህግ፣ ድንበር መኖር አለበት፡፡ ድንበር ሲጥስ፣ ህግ ሲያፈርስ የሚበደል አካል እንዳለ ሁሉ የሚበድልም አለ፡፡ የተበደለ አካል የበደለውን አካል ይጠይቃል ወይም ይከስሳል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ዳኛ ወይም ፈራጅ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ዳኛውም በተቀመጠለት ህግ መሰረት ለተበደለ ያስክሳል ለተቀማ ያስመልሳል፡፡ ዳኝነት ፊት አይቶ የማያደላ፣ ጉቦ የማይወድ፣ አድልዎ የሚጠላ፣ ከህግ በላይ የማይሆን፣ ሕግ የሚገዛው፣ በህግ የሚዳኝ(ዳ ይላላል)  እና የሚዳኝ(ዳ ይጠብቃል) መሆን አለበት፡፡
ነገር ግን አሁን በተግባር የምናየው ነገር ምናልባትም የዳኝነትን ሥራ እንድንኮንን ይዳርገን ይሆናል፡፡ በዳኞች ላይም የስድብ ውርጅብኝ እናወርድ ይሆናል፡፡ ተበድለን የበደለንን ጠይቀን ፍርድ አላገኝ ብለን አንጀታችን ቆስሎ ይሆናል፡፡ ነገር ግን መረዳት የሚገባን ነገር አለ፡፡ ዳኝነት ወይም ፍርድ መስጠት ማለት ህግ ባስቀመጠው መልኩ መወሰን ማለት እንጅ ከሳሽ ሁልጊዜ ያሸንፋል ማለት አይደለም፡፡ ደግሞም እኮ ሰው ፊት አይቶ ያደላል ይህ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ከሳሽ መክሰሱ አንድ ነገር ቢሆንም ተከሳሽ በዚያ ጉዳይ ላይ ምን እውነታ እንዳለው ከተጠየቀ በኋላ ማመኑ ሲረጋገጥ አልያም ሦስት ምስክሮች ቀርበው ሲያረጋግጡ ብቻ ነው ውሳኔ ሊተላለፍ የሚችለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ህግ አስፈጻሚዎችም የተቀመጠላቸውን ህግ ሊሸርፉ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የአስፈጻሚዎች ከህግ በላይ መሆን ነው፡፡ ለአንተ የሚሰራው ህግ ለሌላው አይሰራም፣ ላንተ የማይሰራው ደግሞ ለሌላው ይሰራል፡፡ አንተ የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት 6 ወር በቀበሌው ውስጥ መኖር ግዴታህ ሊሆን ይችላል ምክንያም ህግ ስለሆነ፡፡ ከአንተ በኋላ የመጣ ሰው ግን የቀበሌ መታወቂያውን አውጥቶ እቁልልጭ ከኋላህ መጥቼ ላፍ አደረኩት ይልህ ይሆናል፡፡ ለዚህ ሰው የሰራው ህግ ላንተ ግን አይሰራም፡፡ ሂደህ ብታናግራቸው የዚያን ጊዜማ አድርገናል አሁን ግን ቆሟል ይሉሃል ታዲያ ምን ታመጣለህ በቃ አዝነህ መመለስ ነው፡፡ በእርግጥ አንተም አኮ ያልተረዳኸው ነገር አለ መሰለኝ፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ከመሄድህ በፊት ስለህጉ እና ስለአካሄዱ ከምትጠይቅ ይልቅ እዚያ መስሪያ ቤት ማን እንዳለ ማዎቅ መረዳት ይበልጥሃል፡፡ ህጉ ህግ ሆኖ የሚሠራው ለእኔና ለአንተ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ማን ሞኝ አለ ህግ ለማዎቅ በጣርክበት የመሥሪያ ቤቱን ኃላፊ በእጅ በእግሩ ገብተህ ጉዳይህን ማስፈጸም ነው እንጅ፡፡ አንተ ስትሆን ኃላፊ ይምራው፣ ምክትሉ ይምራው፣ መዝገብ ቤቱ ይሰረው ወዘተ እየተባልክ የ1 ሰዓቱን ጉዳይ ዓመት ትፈጅበታለህ፡፡ ግን የምታዝነው ከኋላህ መጥቶ ተመሳሳይ ችግር አቅርቦ ቀድሞህ ጉዳዩ ሲፈጸምለት ስታይ ነው፡፡ እርሱ እኮ እንዲህ ስለሆነ ነው፣ እርሷ እኮ እንዲህ ስላለባት ነው፣ እነርሱ እኮ የዚህ ድርጅት አባል ስለሆኑ ነው፣ እነዚያ እኮ ከባድ ስራ ትተው ስለመጡ ነው ወዘተ የሚሉ ተልካሻ ምክንያቶች ይደረደራሉ፡፡ አንተ ተሰለፍ ተብለህ በመስኮት በኩል ታንጋጥጣለህ ስምህ እስኪጠራ ድረስ በጉጉት ስምህን ትናፍቃለህ፡፡ ከአንተ ኋላ የመጣ ሌላ ሰው ግን በበር በኩል ገብቶ ካንተ ቀድሞ ይስተናገዳል፡፡ በቃ ፍርዱ የፈራጁ ነዋ ምን ታመጣለህ፡፡
ፍርድስ ይች ናት፡፡ ያውም የፈጣሪ ፍርድ፡፡ ቅልጥፍ ያለች፤ ቁርጥ ያለች፡፡ ለማንም የማታዳላ፡፡ የአምላክ ፍርድ እንደ ሰው ፍርድ ፊት አይቶ የሚያዳላ አይደለም፡፡ ከመጀመሪያው ከባድ ፍርድ ጀምሩ ከአዳምና ሄዋን ማለቴ ነው፡፡ ዕጸ በለስን አትብሉ የሚል ህግ ተሰጣቸው ህጉን ጣሱ ያውም በምክንያት፡፡ ሄዋን በእባብ፣ አዳምም በሄዋን ምክንያት በሉ፡፡ በቃ እዚያው ላይ ተፈረደባቸው 5500 ዘመን በጨለማ ኖሩ በባርነት ኖሩ ጽድቃቸው የመርገም ጨርቅ ሆነ፡፡ ቀና ብለው የሚያዩት የቅድስና ሥራ ጠፋ፡፡ በቃ ቁርጥ ያለ ፍርድ ማለት ይህ ነው፡፡ 80 ዓመት በገዳም በብሕትውና ዓለምን ንቀህ ኖረህ በቅጽበት ማለት ከደቂቃ ባነሰች እድሜ ዓለምን ለመቀላቀል በዓለም ምኞት ባህር ለመዋኘት ብትወስን ወዲያውኑ ውሳኔው ይደርስሃል፡፡ ምክንያቱም ሶስት ምስክር አይሻማ እርሱ፡፡ የ80 ዓመትህ ቅድስና በቅጽበት ስለሰራሃት ኃጢአት ትሻራለች፡፡ በቃ እውነተኛ ፍርድ ነዋ ምንም አስተያየት የሚባል ይግባኝ የሚባል ነገር የሌለበት፡፡ 80 ዓመት ኃጢአት ስትሰራ ኖረህ በቅጽበት ውስጥ ተጸጽተህ ንስሐ ልትገባ ስትሄድ ገና ኃጢአትህ ተፍቆ ለገነት ትታጫለህ፡፡ ፍርድ እንዲህ ነው በቃ፡፡ ላንተም ለእኔም እኩል የሚሰራ ፍርድ፡፡ ሞትን ተመልከታት ማንንም አትመርጥም እኩል ነው የምትፈርደው፡፡ እንኳን እኛ ፈጣሪስ ሞቶ የለምን? እናቱ እመብርሃንስ ሞትን ቀምሳ የለምን? አስብ እንግዲህ 5 ዓመት ተምረህ ነገ የምረቃ ቀንህ ነው እንበል ዛሬ ማታ ግን ልትሞት ትችላለህ በቃ እንድትኖር የተወሰነልህ እስከዚህ ብቻ ነዋ ምን ማድረግ ትችላለህ፡፡ የእኛ ዳኞች ቢሆኑ ኖሮ ሞትን ለተወሰነ ጊዜ ማረፊያ ክፍል ያግቱት ነበር፡፡ ምክንያም 5 ዓመት ሙሉ ተምረህ ሳትቀጠር፣ ለአገር የሚጠቅም ሥራ ሳትሰራ፣ በዚያ ላይ እኮ ደግሞ የወጭ መጋራትህን ሳትከፍል እንዴት ሆኖ አስተያየት ይደረግልህ ነበር፡፡ ነገ የሚጋቡ እጮኛሞች ዛሬ ማታ ላይ ከሁለት አንዱ አልያም ሁለቱም ሞተው ሊያድሩ ይችላሉ የአምላክ ፍርድ ነዋ በቃ፡፡ ለሰርጋቸው የተደገሰው ለቀብራቸው ይሆናል ምንም ማድረግ አንችልም በቃ፡፡ እኛ ብንሆን ኖሮ ተጋብተው ልጅ ወልደው ሃብት አፍርተው ቤት ሰርተው ከዚያ በኋላ ይሁን እንል ነበር ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍርድ ነው፡፡ ይግባኝ የሌለው!!!

በእግዚአብሔር ዘንድ ለእኔ የሚሠራው ሕግ ላንተም፣ ላንቺም ለሁላችንም እኩል የሚሠራ ነው፡፡ በሰዎች ዘንድ ያለው ዳኝነትና ፍርድ ግን በፈራጆች መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለዚህም ላንተ ሲሰራ ለእኛ አይሰራም፣ ለእኛ ሲሰራ ደግሞ ላንተ አይሰራም፡፡ እንዲህ አይነት ፍርድ ቢገጥምህ አትዘን ምክንያቱም ሰው ስለሆንክ እነርሱም ሰው ስለሆኑ፡፡

Wednesday, August 5, 2015

“አንድን የማያውቀው ዘጠና ዘጠኝ”

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ዛሬ ትንሽ መዝናናት ፈልግሁ መሰለኝ በመዝናናቴ ቀረጥ ወደሚከፈልበት ሆቴል ጎራ አልኩ፡፡ ከአንድ  የሆቴሉ ክፍል ቁጭ አልኩና በስም እንኳ የማላውቃቸውን ምግቦችና መጠጦች ዝርዝር የያዘውን ወረቀት ተመለከትሁ፡፡ ሁሉንም አነበብሁት ከጎኑ ለእያንዳንዳቸው የተቀመጠላቸውንም የዋጋ ተመን እንዲሁ ራሴን እየነቀነቅሁ በማድነቅ ይሁን በመገረም ባላውቅም ብቻ ራሴን አወዛውዛለሁ፡፡ ትንሽ አረፍ ካልሁ በኋላ አጨበጨብኩ፡፡ አስተናጋጇ መጣችና “ምን ልታዘዝ አለችኝ” የኪሴን መጠን የማውቀው እኔው ራሴ አይደለሁ ለዛውም የዋጋውን ዝርዝር ቀድሜ አውቄው አይደል፡፡ ነቄ እንዳትልብኝ ዝርዝሩን ያላየሁት ለመምሰል “ ምግብ ምን ምን አለ” አልኳት “የፍስክ… ቋንጣ ፍርፍር፣ ጥብስ፣ ቀይ ወጥ፣ እንቁላል ፍርፍር፣ ዱለት ወዘተ የጾም ደግሞ በየአይነት፣ ተጋቢሮ፣ ሽሮ ፈሰስ፣ ፓስታ፣ እንጀራ ፍርፍር ወዘተ አለ ምን ላርግልክ?” ብላ አፋጠጠችኝ፡፡ እርሷ የምትጠራቸውን ምግቦች ሁሉ አንድ በአንድ ከነዋጋቸው አውቃቸዋለሁ፡፡ ከእርሷ ቀድሜ እንደ ጎበዝ ሸምድቻቸዋለሁ፡፡ ወሬየን ለማራዘም ያህል “የሚጠጣስ?” አልኳት፡፡ “ኦኬ! መጠጥ ነው ያልከው? ቢራ፣ ለስላሳ፣ ትኩስም ሻይ፣ ቡና፣ ለውዝ፣ ማኪያቶ ብዙ አለ ታዲያ ምን ላርግልክ?” አለችኝ፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ  ሲያፋጥጡኝ አልወድም፡፡ “እባክሽ ለስላሳ አድርጊልኝ” አልኳት፡፡ “ኦኬ! ባይ ዘ ዌይ ለስላሳም እኮ የሚመረጥ አለው፡፡ ሚሪንዳ፣ ፔፕሲ፣ ፋንታ፣ ሰቨን አፕ ወዘተ የሚመችህን እዘዝ” አለችኝ፡፡ እኔ በቀላሉ የተገላገልኩ መስሎኝ ነበር ለካ ለስላሳም ምርጫ አለው “ባክሽ ፔፕሲ አርጊው” አልኳት፡፡ “ኦኬ ይመጣልዎታል” አለችኝና ሄደች፡፡ “ግን አንድ ፔፕሲ ለማዘዝና ለመታዘዝ ይህን ያህል ማስቀባጠርንና መቀባጠርን ምን አመጣው? አልኩ በውስጤ፡፡” ከጥቂት ቆይታ በኋላ ፔፕሲውን ከነመክፈቻው አመጣችና ከተቀመጥኩበት ፊት ያለውን ጠረንጴዛ ጠርጋ ከፊቴ አስቀመጠችው፡፡ በመክፈቻው ከፈተችልኝና ሄደች፡፡ እኔም በድህነቴ ምክንያት የታዘዘብኝን ለስላሳ እየተጎነጨሁ መዝናናት የሚመስለውን መዝናናት ተያያዝኩት፡፡ “ለምን እዚህ ቦታ መጣሁ? እን እገሌ መናፈሻ ቤት በቅናሽ ዋጋ መጠጣት የምችለውን ለስላሳ ይህን ያህል ገንዘብ የምከሰክስበት ለምንድን ነው? አንድ አይነት መጠጥ የተለያየ ዋጋ አንድ አይነት ምግብ የተለያየ ዋጋ ቆይ እንጅ ግን ለምን?” እያልሁ ከውስጤ ጋር መሟገት ጀመርሁ፡፡ ከሙግቴ ብዛትም የተነሣ ለስላሳውን እንዴት እንደጨረስኩት አላወቅሁም ነበር፡፡ አጨበጨብኩና “ሂሳብ” አልኩ የሚሰማኝ አጣሁ ደግሜ አጨበጨብኩ አስተናጋጇ ቀና አለች “ሂሳብ ውሰጂ” አልኳት፡፡ መጣች፡፡ “ሂሳብ ስንት ነው?” አልኳት የማላውቅ ለመምሰል ያህል፡፡ እርሷም “ደረሰኙ ይኸው” አለችኝ፡፡ “ደረሰኝ ሳይቀበሉ አይክፈሉ” የሚለውን ጽሁፍ ግድግዳ ላይ ከመለጠፍ ባለፈ ተግባራዊ እንዳደረጉት ተረዳሁ፡፡ ደረሰኙን ተቀበልኩና ተመለከትኩት 10.99 ብር ይላል፡፡ አንድ ለስላሳ 7.00 ብር የሚጠጣበት ቦታ ሞልቶ ምን ሲያክለፈልፍ እዚህ እንዳመጣኝ ከራሴ ጋር መዋቀስ አበዛሁ፡፡ “እሽ ቆይ ለምንድን ነው ዋጋው እንዲህ የተሰቀለው?” አልኳት፡፡ “ለዚህ ሆቴል አዲስ እንደሆኑ ያሳውቃሉ እዚህ ሆቴል እኮ “vat” የሚባል ነገር አለ እርሱ በዋናው ዋጋ ላይ ይጨመርበታል፡፡ 10.99 እኮ ጠቅላላ ዋጋው ነው” አለችኝ፡፡ ቫት የሚባለው ነገር የማይከፈለው ለምንተነፍሰው አየር ብቻ እንደሆነ የሆነ መጽሐፍ ሳነብ አግኝቸዋለሁ፡፡ ግን ይህን ያህል ይጋነናል የሚል ሃሳብ የለኝም ነበር፡፡ “ቆይ እንጅ መንግሥት ለምን ጠጣችሁ ብሎ ነው የሚያስከፍለን፡፡ ቆይ አንጅ በነጻ መዝናናት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ለሃብታሞችስ ይሁን እሽ ለእኛ ለድሆችስ ስለድህነታችን 15% ቅናሽ አይደረግልንም እንዴ? እዚህ ሃገር በዋጋ ላይ ዋጋ መጨመር እንጅ መቀነስ የሚባል ነገር የለም ልበል? ቆይ ዋጋ እያረጋጋን ነው እያለ ሌት ከቀን የሚለፈልፈው ሚዲያ ውሸት ነው እንዴ? አየሁት እኮ ዛሬማ እይውልሽ መንግሥት ራሱ በዋጋው ላይ ጨመረበት እኮ፡፡ ጉድ ነው መቼም! ጊዜ ይስጠን እንጅ ገና ብዙ ነገር እናያለን” አልኩ፡፡ ክትክት ብላ ሳቀችብኝ “ኤኒ ዌይ ሂሳብ አልከፈሉኝም” አለችኝ፡፡ “አውቃለሁ እንቺ ያዢ” አልኩና 11 ብር ሰጠኋትና መልሴን እስክትመልስልኝ ድረስ ተቀመጥሁ፡፡ የቫቱ ነገር ውስጤን እያሳረረው አንዱን ሃሳብ ካንዱ ጋር እያፋጨሁ በጣም ብዙ ጊዜ ቁጭ አልኩ፡፡ በጣም ብዙ ሰዓታትን ቁጭ አልኩ መልስ ግን ልታመጣልኝ አልቻለችም፡፡ እንደረሳችውና እንደማታመጣልኝ ስረዳ አጨበጨብኩ ወዲያውኑ ተመልሳ መጣች “ምን ልጨምርዎ?” አለችኝ፡፡ “ምን ትጨምሪኛለሽ ደግሞ! መልሴን ብቻ ነው የምፈልግ” አልኳት በብስጭት አይነት ንግግር፡፡ “የምን መልስ ነው የሚያወሩት ጌታዬ?” አለችኝ፡፡ “በትክክል ረስተዋለች ማለት ነው፡፡ ዋጋው 10.99 ብር ነበር የሰጠኋት ደግሞ 11.00 ብር ነው፡፡ ታዲያ አንድ ሳንቲም መልስ የለኝም እንዴ?” አልኩ በውስጤ ለእርሷ ባልነግራትም፡፡ “እንዴ 1 ሳንቲም አለኝ እኮ” አልኳት፡፡ ክትክት ብላ ሳቀችብኝ “እንዴ ምን አይነት ሰው ነህ ባክህ? ስንቱ ወንድ ቲፕ እያለ 10 ብር 50 ብር ከዛም በላይ ትቶልን ይሄዳል አንተ በ 1 ሳንቲም ይህን ያህል ሰዓት ትቀመጣለህ? በጣም ታሳዝናለህ ቆይ እንጅ የት ቦታ ነው 1 ሳንቲም መልስ የሚመለሰው?” አለችኝ በጣም እየሳቀች፡፡ “አትሳቂ እንጅ እመቤቴ መልስ አለኝ ማለት ይህን ያህል ያስቃል እንዴ? ሌሎች ቦታዎች እኮ 1 ሳንቲም የማይመልሱት 99 የሚባል ዋጋ ስለሌላቸው ነው፡፡ ታዲያ “እሽ 11 ብር የምትቀበሉ ከሆነ ለምን 10.99 ዋጋ እንደሆነ ደረሰኝ ቆረጣችሁ?” አልኳት፡፡ የእኛን ጭቅጭቅ የሰሙ ሰዎች ወደ እኛ ተጠግተው “ምን ያጨቃጭቃችኋል?” አሉን፡፡ የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገርኳቸው፡፡ አንዳንዶች “ እንዴት በዚህ ይጨቃጨቃል?” እያሉ እርስ በርሳቸው ይንሾካሾካሉ፡፡ አንዱ እንዲያውም “ ፍሬንድ ምነው ባትረብሸን? ሰላማችንን እንፈልገዋለን እኮ፡፡ ለምን ዝም ብለህ ጊዜ ታጠፋለህ፡፡ 1 ሳንቲም መልስ ብለህ እዚህ በተቀመጥክበት 1000 ብር ትሠራ ነበር እኮ አለኝ፡፡ “የእኔ ጉዳይ ከአስተናጋጇ እንጅ ከእናንተ ጋር አይደለም” አልኳቸው፡፡ ጥቂቶቹ የያዙትን እንደያዙ ቦታ ቀይረው እኔን ከማይሰሙበት ቦታ ተቀመጡ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በተመስጦ ያዳምጡኛል፤ ጆሯቸውን ለእኔ እንዳደረጉም ተረድቻለሁ፡፡ እኔንም ሊተባበሩኝ እንደሚችሉና 1ዴን ሳንቲም እንደሚያስመልሱልኝ ተገነዘብሁ፡፡ “አሁን የምፈልገው 1 ሳንቲም መልስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ፈጠን ብለሽ እንድታመጭልኝ በትህትና እማጸንሻለሁ አይሆንም ካልሽ ግን ያው ፖሊስ መጥራቴ አይቀርም” አልኳት፡፡ “ለ አንድ ሳንቲም ብለህ ፖሊስ ስትጠራ እናያለን” ብላ ከት ብላ ሳቀችብኝ፡፡ የእኔ ጉዳይ እኮ 1ዷሳንቲም ተመልሳልኝ ፎቅ ልሰራባት አይደለም፤ የመጨቃጨቅ አባዜ ተጠናውቶኝም አይደለም፡፡ 1 ሳንቲም የማይመለስ ከሆነ ለምን 99 ሳንቲም የሚል ዋጋ ይተመናል ከሚለው ላይ ነው፡፡ ደግሞም እኮ 99 የሚባለው 1 ተብሎ ከተጀመረ ብቻ ነው፡፡ 1 የማይመሠርተው 99 አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ እኔ ደግሞ ጥሩ የሂሳብ አስተማሪ እንደሆንኩ አውቃለሁ፡፡ መቀነስ ሳስተምርም 100-1 ስንት ነው? ብየ ስጠይቃቸው 99 ብለው ካልመለሱ አላርምም፡፡ ዛሬ ግን እንዳርም እየተገደድሁ ነው፡፡ 11-10.99 እኩል ይሆናል 1 በእኔ ሂሳብ ቀመር ሲሰላ እኩል ይሆናል 11.00 በአስተናጋጇ የሂሳብ ቀመር ሲሰላ ታዲያ ማነው ትክክል? ለነገሩ ዛሬ የዚህን ፍርድ የሚሰጥ እውነት ተናጋሪ ላይኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም እውነትን መድፈር እንደ ወንጀል እየታየ ባለበት ሁኔታ ትንሽ ከበድ ይል ይሆናል፡፡ ለነገሩ ለ1 ቦታ የሚሰጥ ዳኛም ላይኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ቅድሚያ ለብዙኃኑ አይደል የሚባለው፡፡ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር እነዚያ ብዙ የሚባሉት ነጠላዎች ተደምረው እንደሆነ መረዳት አለመቻላቸው ነው፡፡ በዚህች ሃገር እኮ 1 ብለን ከመነሣት ይልቅ 99 ብለን ለ100 መቅረብ ነው የሚቀናን፡፡ ታሪካችንን ተመልከቱት እስኪ ስንት በወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ ዓለም የሚመሰክርለት በዓለም የሚያበራ ያሸበረቀ ታሪክ እያለን ዘለን ፊጥ የምንለው 1980 ቹ ላይ ነው፡፡ በእውነት ለኢትዮጵያውያን የሃገሩን ታሪክ ዓለም ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ማዎቅ ነው ወይስ የዛሬውን ብቻ ማወቅ ነው የሚጠቅመው? በእርግጥ የዛሬ ታሪክ አዋቂዎች እንደ አስተናጋጇ በ99 ላይ 1ን አይመለከቱም፡፡ ምክንያቱም መልስ የላቸውማ! አስተናጋጇ እኮ እንዲህ የምትሞግተኝ መልስ ስለሌላት እንጅ 1 ሳንቲም ወስዳ ቤት ልትሠራበት አይደለም፡፡ እኛም የሚቀናን 1 ከማለት ይልቅ 99 ማለት ነው፡፡ ዘጠና ዘጠኝም ዘጠና ዘጠኝ መሆኑን እንጅ ከአንድ መነሣቱን አያውቅም፡፡ ከመካከላቸው 1 ብትጎድል የዘጠና ዘጠኙ ህልውና ማክተሙ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ይህንን እንኳ ማወቅ የተሳነውን ዘጠና ዘጠኝ ነው የምናጠራቅመው፡፡ ለሃገር የሚጠቅማት አንድ ብሎ የተጀመረ ዘጠና ዘጠኝ እንጅ ዝም ብሎ ዘጠና ዘጠኝ ላይ ፊጥ ያለ ድርጅት ወይም ማኅበር አይደለም፡፡

Monday, August 3, 2015

ቅዱሳን ስዕላት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ክፍል አራት
ቅዱሳን ሥዕላት የሚሣሉበት ቦታእና ክብራቸው
ስለቅዱሳን ሥዕላት ክብርና ቅድስና ባለፉት ክፍሎች ተመልክተናል፡፡ በመሆኑም ስለክብራቸውና ስለ ቅድስናቸው ለአገልግሎትም ጠቀሜታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በቤተክርስቲያን ይሣላሉ፡፡ ይሁን እንጅ ምዕመናንም ቅዱሳን ሥዕላትን ለተለያዩ አገልግሎቶች ስለሚጠቀሙባቸው እያሣሉ በቤታቸው ይገለገሉባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ቅዱሳን ሥዕላት ለግድግዳ ጌጥነት የምንጠቀምባቸው አይደሉም፡፡ በክብር በተለየ ቦታ በመጋረጃ ተጋርደው ለጸሎት በምንጠቀምበት ልዩ ቦታ ላይ ሊደረጉ ይገባል፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ አባቶች መንገድ ሲጓዙ ለጸሎት የሚጠቀሙበት የገበታ ሥዕል በመባል የሚታወቅ አለ፡፡ በአጠቃላይ ሥዕላት በቤተክርስቲያን ውስጥ በጣሪያና በግድግዳ ላይ እንዲሁም በበሮችና በመስኮቶች ላይ ይሣላሉ፡፡ በተጨማም ከላይ እንደተመለከትነው በገበታ እና በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ሊሣሉ ይችላሉ፡፡
1.   በግድግዳ፡- በቤተክርስቲያን ውስጥ በተለይ በቤተመቅደስ ግድግዳዎች ዙሪያ ቅዱሳን ሥዕላት ይሣላሉ፡፡ በብዛት ክብ ቤተክርስቲያን በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ የመቅደሱ ግድግዳ ከታች እስከ ላይ ድረስ በቅዱሳን ሥዕላት የተሸፈነ ነው፡፡ እዚህ ላይ የአሣሣሉም የራሱ የሆነ አቅጣጫ አለው፡፡
ሀ. በምዕራብ፡- ቅድስት ሥላሴ፣ የጌታችንን መከራ የሚያሳዩ ሥዕላት፣ ጸሎተ ሐሙስ፣ ሥርዓተ ቁርባን እነዚህን የሚያሳዩ ሥዕላት ይሣላሉ፡፡
ለ. በደቡብ፡- የእመቤታችንን ታሪክ ማለትም ልደቷን፣ ወደ ቤተመቅደስ መግባቷን፣ ስደቷን፣ እረፍቷን ወዘተ የሚያሳዩ ሥዕላት ይሣላሉ፡፡
ሐ. በምሥራቅ፡- ከጽንሰት እስከ ዳግም ምጽአት ያለው የጌታችን ታሪክ ይሣላል፡፡
መ. በሰሜን፡-  የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት ተጋድሎ የሚያሳዩ ሥዕሎች ይሣላሉ፡፡
2.   በጣሪያ፡- የፊት መልክ ብቻ የሚሣልላቸው ሠራዊተ መላእክት በብዛት ይሣላሉ፡፡ ምሳሌያዊ ሥዕላት እንደ በግ፣ ወይን፣ ዓሣና ባህር፣ መርከብ በተጨማሪም ሐረጋት ይሣላሉ፡፡
3.   በበር፡- ቅዱሳን መላእክት ልዩ ከሆነው ተአምራቸው ጋርበሙሉ ቁመታቸው ይሣላሉ፡፡
4.   ገበታ፡- ገበታ ከእንጨት ተፈልፍሎ የሚሠራ ሊከፈት እና ሊዘጋ የሚችል እንደመጽሐፍ ያለ ነው፡፡ ገበታ በቀላሉ ለሰዎች ምቹ በሆነ መልኩ ስለሚዘጋጅ በዚያው መጠን ሥዕል ይሣልበታል ወይም ይለጠፍበታል፡፡ በብዛት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ትሣልበታለች ነገር ግን እንደ ሰው ፍላጎት የተለያዩ ሥዕላት ሊሣሉበት ይችላሉ፡፡
5.   በቅዱሳት መጻሕፍት፡- በመጽሐፍ የተገለጠን ታሪክ መሠረት አድርገው አባቶች ከመጽሐፉ ውስጥ ይሥላሉ፡፡ ይህ በብዛት በብራና መጻሕፍት ላይ ይዘወተራል፡፡

የቅዱሳን ሥዕላት ክብር
ቅዱሳን ሥዕላት የከበሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም አስፈላጊ ባልሆነ መንገድ መጠቀም ጉዳት እንጅ ጥቅም የለውም፡፡ አሁን በብዛት የምናስተውለው ለቅዱሳን ሥዕላቱ የምንሰጠው ክብር በጣም የቀነሰ መሆኑን ነው፡፡ ስዕላትን ለጌጥ፣ለማስታወቂያ፣ እነዲሁም በኮፊያ እና በተለያዩ ልብሶች ላይ መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡
1.   ለጌጥነት አለመጠቀም፡- ለቤት ማስጌጣነት፣ ለመኝታ ቤት ማስጌጫነት፣ለቤትና ለመኪና ቁልፍ መያዣነት መጠቀም፣ ለመኪና መስኮቶች ጌጥነት ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ መኪና ውስጥ ስትመለከቱ ሲጋራ ይጨስባቸዋል፣ ይቀደዳሉ፣ ጫት ይቃምባቸዋል ወዘተ ስለዚህ የተከለከለ ነው፡፡
2.   ልብስ ላይ አለማድረግ፡- ኮፊያ፣ ከነቴራ ላይ መሣል ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ልብሱ ይቆሽሻል ያ ማለት ሥዕሉንም እናበላሸዋለን ማለት ነው፡፡ ሲቆሽሽ ታሽቶ ይታጠባል በዚህም የተነሣ ሥዕሉ ይላላጣል፡፡ ስለዚህ በተለይ ለክብረ በዓላት ቅዱሳን ሥዕላትን የምናሳትም ወገኖች ጥንቃቄ ብናደርግ ጥሩ ነው፡፡ ለበረከት ስንል ለመቅሰፍት እንዳይሆንብን፡፡
3.   ሥዕላትን ለማስታወቂያ አለመጠቀም፡- አንዳንድ ነጋዴዎችና ድርጅቶች በሚያመርቱት ምርት ላይ ቅዱሳን ሥዕላትን ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ላይ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ሰው ይሰክራል፣ ሥዕሉን ከጠርሙሱ ልጦ ይጥለዋል፣ ሥዕሉ ተገቢ ባልሆነ ቦታ ይወድቃል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ለቅዱሳን ሥዕላት ክብርን የሚቀንሱ ነገሮችን ከመጠቀም ልንታቀብ ተገቢ ነው፡፡
ተፈጸመ

ምንጭ፡- የተለያዩ መጻሕፍት እና በራሪ ጽሑፎች