Wednesday, August 5, 2015

“አንድን የማያውቀው ዘጠና ዘጠኝ”

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ዛሬ ትንሽ መዝናናት ፈልግሁ መሰለኝ በመዝናናቴ ቀረጥ ወደሚከፈልበት ሆቴል ጎራ አልኩ፡፡ ከአንድ  የሆቴሉ ክፍል ቁጭ አልኩና በስም እንኳ የማላውቃቸውን ምግቦችና መጠጦች ዝርዝር የያዘውን ወረቀት ተመለከትሁ፡፡ ሁሉንም አነበብሁት ከጎኑ ለእያንዳንዳቸው የተቀመጠላቸውንም የዋጋ ተመን እንዲሁ ራሴን እየነቀነቅሁ በማድነቅ ይሁን በመገረም ባላውቅም ብቻ ራሴን አወዛውዛለሁ፡፡ ትንሽ አረፍ ካልሁ በኋላ አጨበጨብኩ፡፡ አስተናጋጇ መጣችና “ምን ልታዘዝ አለችኝ” የኪሴን መጠን የማውቀው እኔው ራሴ አይደለሁ ለዛውም የዋጋውን ዝርዝር ቀድሜ አውቄው አይደል፡፡ ነቄ እንዳትልብኝ ዝርዝሩን ያላየሁት ለመምሰል “ ምግብ ምን ምን አለ” አልኳት “የፍስክ… ቋንጣ ፍርፍር፣ ጥብስ፣ ቀይ ወጥ፣ እንቁላል ፍርፍር፣ ዱለት ወዘተ የጾም ደግሞ በየአይነት፣ ተጋቢሮ፣ ሽሮ ፈሰስ፣ ፓስታ፣ እንጀራ ፍርፍር ወዘተ አለ ምን ላርግልክ?” ብላ አፋጠጠችኝ፡፡ እርሷ የምትጠራቸውን ምግቦች ሁሉ አንድ በአንድ ከነዋጋቸው አውቃቸዋለሁ፡፡ ከእርሷ ቀድሜ እንደ ጎበዝ ሸምድቻቸዋለሁ፡፡ ወሬየን ለማራዘም ያህል “የሚጠጣስ?” አልኳት፡፡ “ኦኬ! መጠጥ ነው ያልከው? ቢራ፣ ለስላሳ፣ ትኩስም ሻይ፣ ቡና፣ ለውዝ፣ ማኪያቶ ብዙ አለ ታዲያ ምን ላርግልክ?” አለችኝ፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ  ሲያፋጥጡኝ አልወድም፡፡ “እባክሽ ለስላሳ አድርጊልኝ” አልኳት፡፡ “ኦኬ! ባይ ዘ ዌይ ለስላሳም እኮ የሚመረጥ አለው፡፡ ሚሪንዳ፣ ፔፕሲ፣ ፋንታ፣ ሰቨን አፕ ወዘተ የሚመችህን እዘዝ” አለችኝ፡፡ እኔ በቀላሉ የተገላገልኩ መስሎኝ ነበር ለካ ለስላሳም ምርጫ አለው “ባክሽ ፔፕሲ አርጊው” አልኳት፡፡ “ኦኬ ይመጣልዎታል” አለችኝና ሄደች፡፡ “ግን አንድ ፔፕሲ ለማዘዝና ለመታዘዝ ይህን ያህል ማስቀባጠርንና መቀባጠርን ምን አመጣው? አልኩ በውስጤ፡፡” ከጥቂት ቆይታ በኋላ ፔፕሲውን ከነመክፈቻው አመጣችና ከተቀመጥኩበት ፊት ያለውን ጠረንጴዛ ጠርጋ ከፊቴ አስቀመጠችው፡፡ በመክፈቻው ከፈተችልኝና ሄደች፡፡ እኔም በድህነቴ ምክንያት የታዘዘብኝን ለስላሳ እየተጎነጨሁ መዝናናት የሚመስለውን መዝናናት ተያያዝኩት፡፡ “ለምን እዚህ ቦታ መጣሁ? እን እገሌ መናፈሻ ቤት በቅናሽ ዋጋ መጠጣት የምችለውን ለስላሳ ይህን ያህል ገንዘብ የምከሰክስበት ለምንድን ነው? አንድ አይነት መጠጥ የተለያየ ዋጋ አንድ አይነት ምግብ የተለያየ ዋጋ ቆይ እንጅ ግን ለምን?” እያልሁ ከውስጤ ጋር መሟገት ጀመርሁ፡፡ ከሙግቴ ብዛትም የተነሣ ለስላሳውን እንዴት እንደጨረስኩት አላወቅሁም ነበር፡፡ አጨበጨብኩና “ሂሳብ” አልኩ የሚሰማኝ አጣሁ ደግሜ አጨበጨብኩ አስተናጋጇ ቀና አለች “ሂሳብ ውሰጂ” አልኳት፡፡ መጣች፡፡ “ሂሳብ ስንት ነው?” አልኳት የማላውቅ ለመምሰል ያህል፡፡ እርሷም “ደረሰኙ ይኸው” አለችኝ፡፡ “ደረሰኝ ሳይቀበሉ አይክፈሉ” የሚለውን ጽሁፍ ግድግዳ ላይ ከመለጠፍ ባለፈ ተግባራዊ እንዳደረጉት ተረዳሁ፡፡ ደረሰኙን ተቀበልኩና ተመለከትኩት 10.99 ብር ይላል፡፡ አንድ ለስላሳ 7.00 ብር የሚጠጣበት ቦታ ሞልቶ ምን ሲያክለፈልፍ እዚህ እንዳመጣኝ ከራሴ ጋር መዋቀስ አበዛሁ፡፡ “እሽ ቆይ ለምንድን ነው ዋጋው እንዲህ የተሰቀለው?” አልኳት፡፡ “ለዚህ ሆቴል አዲስ እንደሆኑ ያሳውቃሉ እዚህ ሆቴል እኮ “vat” የሚባል ነገር አለ እርሱ በዋናው ዋጋ ላይ ይጨመርበታል፡፡ 10.99 እኮ ጠቅላላ ዋጋው ነው” አለችኝ፡፡ ቫት የሚባለው ነገር የማይከፈለው ለምንተነፍሰው አየር ብቻ እንደሆነ የሆነ መጽሐፍ ሳነብ አግኝቸዋለሁ፡፡ ግን ይህን ያህል ይጋነናል የሚል ሃሳብ የለኝም ነበር፡፡ “ቆይ እንጅ መንግሥት ለምን ጠጣችሁ ብሎ ነው የሚያስከፍለን፡፡ ቆይ አንጅ በነጻ መዝናናት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ለሃብታሞችስ ይሁን እሽ ለእኛ ለድሆችስ ስለድህነታችን 15% ቅናሽ አይደረግልንም እንዴ? እዚህ ሃገር በዋጋ ላይ ዋጋ መጨመር እንጅ መቀነስ የሚባል ነገር የለም ልበል? ቆይ ዋጋ እያረጋጋን ነው እያለ ሌት ከቀን የሚለፈልፈው ሚዲያ ውሸት ነው እንዴ? አየሁት እኮ ዛሬማ እይውልሽ መንግሥት ራሱ በዋጋው ላይ ጨመረበት እኮ፡፡ ጉድ ነው መቼም! ጊዜ ይስጠን እንጅ ገና ብዙ ነገር እናያለን” አልኩ፡፡ ክትክት ብላ ሳቀችብኝ “ኤኒ ዌይ ሂሳብ አልከፈሉኝም” አለችኝ፡፡ “አውቃለሁ እንቺ ያዢ” አልኩና 11 ብር ሰጠኋትና መልሴን እስክትመልስልኝ ድረስ ተቀመጥሁ፡፡ የቫቱ ነገር ውስጤን እያሳረረው አንዱን ሃሳብ ካንዱ ጋር እያፋጨሁ በጣም ብዙ ጊዜ ቁጭ አልኩ፡፡ በጣም ብዙ ሰዓታትን ቁጭ አልኩ መልስ ግን ልታመጣልኝ አልቻለችም፡፡ እንደረሳችውና እንደማታመጣልኝ ስረዳ አጨበጨብኩ ወዲያውኑ ተመልሳ መጣች “ምን ልጨምርዎ?” አለችኝ፡፡ “ምን ትጨምሪኛለሽ ደግሞ! መልሴን ብቻ ነው የምፈልግ” አልኳት በብስጭት አይነት ንግግር፡፡ “የምን መልስ ነው የሚያወሩት ጌታዬ?” አለችኝ፡፡ “በትክክል ረስተዋለች ማለት ነው፡፡ ዋጋው 10.99 ብር ነበር የሰጠኋት ደግሞ 11.00 ብር ነው፡፡ ታዲያ አንድ ሳንቲም መልስ የለኝም እንዴ?” አልኩ በውስጤ ለእርሷ ባልነግራትም፡፡ “እንዴ 1 ሳንቲም አለኝ እኮ” አልኳት፡፡ ክትክት ብላ ሳቀችብኝ “እንዴ ምን አይነት ሰው ነህ ባክህ? ስንቱ ወንድ ቲፕ እያለ 10 ብር 50 ብር ከዛም በላይ ትቶልን ይሄዳል አንተ በ 1 ሳንቲም ይህን ያህል ሰዓት ትቀመጣለህ? በጣም ታሳዝናለህ ቆይ እንጅ የት ቦታ ነው 1 ሳንቲም መልስ የሚመለሰው?” አለችኝ በጣም እየሳቀች፡፡ “አትሳቂ እንጅ እመቤቴ መልስ አለኝ ማለት ይህን ያህል ያስቃል እንዴ? ሌሎች ቦታዎች እኮ 1 ሳንቲም የማይመልሱት 99 የሚባል ዋጋ ስለሌላቸው ነው፡፡ ታዲያ “እሽ 11 ብር የምትቀበሉ ከሆነ ለምን 10.99 ዋጋ እንደሆነ ደረሰኝ ቆረጣችሁ?” አልኳት፡፡ የእኛን ጭቅጭቅ የሰሙ ሰዎች ወደ እኛ ተጠግተው “ምን ያጨቃጭቃችኋል?” አሉን፡፡ የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገርኳቸው፡፡ አንዳንዶች “ እንዴት በዚህ ይጨቃጨቃል?” እያሉ እርስ በርሳቸው ይንሾካሾካሉ፡፡ አንዱ እንዲያውም “ ፍሬንድ ምነው ባትረብሸን? ሰላማችንን እንፈልገዋለን እኮ፡፡ ለምን ዝም ብለህ ጊዜ ታጠፋለህ፡፡ 1 ሳንቲም መልስ ብለህ እዚህ በተቀመጥክበት 1000 ብር ትሠራ ነበር እኮ አለኝ፡፡ “የእኔ ጉዳይ ከአስተናጋጇ እንጅ ከእናንተ ጋር አይደለም” አልኳቸው፡፡ ጥቂቶቹ የያዙትን እንደያዙ ቦታ ቀይረው እኔን ከማይሰሙበት ቦታ ተቀመጡ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በተመስጦ ያዳምጡኛል፤ ጆሯቸውን ለእኔ እንዳደረጉም ተረድቻለሁ፡፡ እኔንም ሊተባበሩኝ እንደሚችሉና 1ዴን ሳንቲም እንደሚያስመልሱልኝ ተገነዘብሁ፡፡ “አሁን የምፈልገው 1 ሳንቲም መልስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ፈጠን ብለሽ እንድታመጭልኝ በትህትና እማጸንሻለሁ አይሆንም ካልሽ ግን ያው ፖሊስ መጥራቴ አይቀርም” አልኳት፡፡ “ለ አንድ ሳንቲም ብለህ ፖሊስ ስትጠራ እናያለን” ብላ ከት ብላ ሳቀችብኝ፡፡ የእኔ ጉዳይ እኮ 1ዷሳንቲም ተመልሳልኝ ፎቅ ልሰራባት አይደለም፤ የመጨቃጨቅ አባዜ ተጠናውቶኝም አይደለም፡፡ 1 ሳንቲም የማይመለስ ከሆነ ለምን 99 ሳንቲም የሚል ዋጋ ይተመናል ከሚለው ላይ ነው፡፡ ደግሞም እኮ 99 የሚባለው 1 ተብሎ ከተጀመረ ብቻ ነው፡፡ 1 የማይመሠርተው 99 አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ እኔ ደግሞ ጥሩ የሂሳብ አስተማሪ እንደሆንኩ አውቃለሁ፡፡ መቀነስ ሳስተምርም 100-1 ስንት ነው? ብየ ስጠይቃቸው 99 ብለው ካልመለሱ አላርምም፡፡ ዛሬ ግን እንዳርም እየተገደድሁ ነው፡፡ 11-10.99 እኩል ይሆናል 1 በእኔ ሂሳብ ቀመር ሲሰላ እኩል ይሆናል 11.00 በአስተናጋጇ የሂሳብ ቀመር ሲሰላ ታዲያ ማነው ትክክል? ለነገሩ ዛሬ የዚህን ፍርድ የሚሰጥ እውነት ተናጋሪ ላይኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም እውነትን መድፈር እንደ ወንጀል እየታየ ባለበት ሁኔታ ትንሽ ከበድ ይል ይሆናል፡፡ ለነገሩ ለ1 ቦታ የሚሰጥ ዳኛም ላይኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ቅድሚያ ለብዙኃኑ አይደል የሚባለው፡፡ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር እነዚያ ብዙ የሚባሉት ነጠላዎች ተደምረው እንደሆነ መረዳት አለመቻላቸው ነው፡፡ በዚህች ሃገር እኮ 1 ብለን ከመነሣት ይልቅ 99 ብለን ለ100 መቅረብ ነው የሚቀናን፡፡ ታሪካችንን ተመልከቱት እስኪ ስንት በወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ ዓለም የሚመሰክርለት በዓለም የሚያበራ ያሸበረቀ ታሪክ እያለን ዘለን ፊጥ የምንለው 1980 ቹ ላይ ነው፡፡ በእውነት ለኢትዮጵያውያን የሃገሩን ታሪክ ዓለም ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ማዎቅ ነው ወይስ የዛሬውን ብቻ ማወቅ ነው የሚጠቅመው? በእርግጥ የዛሬ ታሪክ አዋቂዎች እንደ አስተናጋጇ በ99 ላይ 1ን አይመለከቱም፡፡ ምክንያቱም መልስ የላቸውማ! አስተናጋጇ እኮ እንዲህ የምትሞግተኝ መልስ ስለሌላት እንጅ 1 ሳንቲም ወስዳ ቤት ልትሠራበት አይደለም፡፡ እኛም የሚቀናን 1 ከማለት ይልቅ 99 ማለት ነው፡፡ ዘጠና ዘጠኝም ዘጠና ዘጠኝ መሆኑን እንጅ ከአንድ መነሣቱን አያውቅም፡፡ ከመካከላቸው 1 ብትጎድል የዘጠና ዘጠኙ ህልውና ማክተሙ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ይህንን እንኳ ማወቅ የተሳነውን ዘጠና ዘጠኝ ነው የምናጠራቅመው፡፡ ለሃገር የሚጠቅማት አንድ ብሎ የተጀመረ ዘጠና ዘጠኝ እንጅ ዝም ብሎ ዘጠና ዘጠኝ ላይ ፊጥ ያለ ድርጅት ወይም ማኅበር አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment