©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አዳም ተስፋ ያደረጋት አምላክ ከ5500 ዘመን በኋላ እናቱ አድርጎ ያለአባት የሚወለድላት እመብርሃን
ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ከእናቷ ሃና እና ከአባቷ ኢየቄም በደብረ ሊባኖስ ተወለደች፡፡ አምላክም ከአንስተ ዓለም መርጦ ማደሪያው
ትሆን ዘንድ ወደዳት፡፡ ዮሴፍን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አክብሮ ከነገረኝ ነገር ውጭ ሌላ አላውቅም ያለችው ድንግል ማርያም በድንግልና
የመጽነሷ ነገር ግሩም ሲባል ይኖራል፡፡ በእውነትም ግሩም ነው ግሩም በሚለው ቃል መግለጽ ከተቻለ አቻ ቃል የለውምና ግሩም አንላለን፡፡
አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወለደችው፡፡ ሰዓሊ ለነ ቅድስት የምንላት እኮ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ፣ ጽንእት ስለሆነች
ነው፡፡ ንጽሕት የምንላት ሌሎች ሴቶች ቢነጹ ከነቢብ፣ ከገቢር ነው የሀልዮ (የማሰብ) ኃጢአት አለባቸው እርሷ ግን ከሀልዮ፣ ከነቢብ፣
ከገቢር ንጽሕት ናት፡፡ ክብርትም የምንላት ሌሎች ሴቶችን የምናከብራቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ መነኮሳትን፣ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣
ዲያቆናትን ወለዱ ብለን ነው እርሷን ግን ወላዲተ አምላክ ብለን ነው፡፡ ልዩም የምንላት ሌሎች ሴቶች ድንግል ከሆኑ እናት እናትም
ከተባሉ ድንግል አይባሉም እርሷ ግን ድንግል ወእም ናት፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች ከእመቤታችን ሌላ ሴት
አትገኝምና ልዩ እንላታለን፡፡ ጽንእትም የምንላት ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው በኋላ ተፈትሆ አለባቸው እርሷ ግን
ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድህረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድህረ ወሊድ ተፈትሆ የለባትም፡፡እንገዲህ አምላክ ትንቢቱን
ባናገረላት ምሳሌውን ባስመሰለላት ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ለመንሣት በእርሷ አደረ፡፡ ለምን ከድንግል
ተወለደ ብንል፡ ትንቢት ስላለ ነው፡፡ “ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ” እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፡፡
ኢሣ7÷14፡፡ ይህ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከድንግል ተወለደ፡፡ ለመወለዱ ምክንያት ግን ክፍል 1 ላይ እንደተመለከትነው የአዳም መሳት
ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍጹም ፍቅር እንረዳ ዘንድ ወደ ምድር መጣ፡፡ ቅዱስ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዳነሣው “ፍቅር ሰሐቦ
ለወልድ ኃያል እመንበሩ” ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው ይላል፡፡ ይህ ፍቅር ግን በቃላት የሚገለጥ ፍቅር አይደለም ከቃላት
ሁሉ በላይ ነው፡፡ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ ወዮ ለዚህ አንክሮ ይገባዋል፡፡ አምላክ በከበረ ዙፋኑ ሆኖ ሳይወለድ፣ ሳይሰደድ፣
ሳይሰቀል፣ ሳይሞት፣ ሳይነሣ፣ ሳያርግ አዳምን ከደብር ቅዱስ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት መመለስ ይቻለው ነበር ነገር ግን ፍቅሩን
ሊገልጥልን መጣ አንድም ትንቢቱን ለመፈጸም መጣ፡፡ አሁን ዘመን የማይቆጠርለት አምላካችን ዘመን ተቆጠረለት፡፡ በ 30 ዓመቱ ተጠመቀ፣
3 ዓመት ከ3 ወር አስተማረ እያልን ዘመኑን እንቆጥርለታለን፡፡ ምንም ምን ሊወስነው የማይችለው አምላክ 3 ክንድ ከስንዝር በሆነ
ቁመት ተወሰነ፡፡ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፡፡ ለዚህ ሁሉ አንክሮ ይገባል፡፡ የአምላክ ወደዚህ መምጣት ከድንግል መወለድ
በግብጽ በረሃ መሰደድ በቀራንዮ መሰቀል፣ በጎልጎታ መቀበር፣ ከመቃብሩ በሥልጣኑ መነሣት፣ በቢታንያ ወደ ሰማይ ማረግ ምን ይረቅ
ምን ይደንቅ፣ ምን ይጠልቅ፡፡
አምላካችን አዳምን የሚያድነው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ነው፡፡
እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የዓለም ትልቁ ስህተት፡፡ ዓለም ለፈጣሪዋ አልተመቸችም፣ ዓለም ሊፈውሳት ሊያድናት የመጣላትን መድኃኒት
አልቀበልም አለች፡፡ ዓለም ድጋፍ የምታደርገው ለኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም ለበርባን ነው፡፡
ይቆየን
No comments:
Post a Comment