©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በኃጢአት የረከሰችውን ዓለም በደሙ ለመቀደስ ወደዚህ ምድር የመጣው አምላካችን የሕጻናትን ልማድ
ሳያፋልስ በጥቂት በጥቂቱ አደገ “በበህቅ ልህቀ” እንዲል፡፡ አምላክ ነኝና መዳህን አልፌ ልቁም ሳይል፣ አምላክ ነንና ቶሎ ወጣት
ልሁን ሳይል ከኃጢአት በቀር እንደኛ ሰው ሆነ፡፡ በሰላሳ ዓመቱ በማየ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ከዚያም ሳይውል ሳያድር
ወደ ገዳመ ቆርንቶስ ሄዶ በዚያ ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋ ሳያጥፍ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ ጸለየ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ሊፈትነው
ወደደ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ያልተረዳው ወራዳው ዲያሎስ በሦስት ትላልቅ ኃጣውእ ፈትኖታል፡፡ ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ
ንዋይ ናቸው፡፡ ማቴ4ን ይመልከቱ እነዚህን ፈተናዎች እንደአመጣጣቸው በሚገባ አድርጎ ሰይጣንን አሳፍሮ አሸንፎታል፡፡ ከዚህ ከ40
ቀንና ሌሊት ጾም በኋላ በተለያዩ ቦታዎች እየዞረ አስተምሯል፡፡
እንግዲህ ዓለም 5 እንጀራና ሁለት አሣ ማበርከቱን አይታ አምስት ገበያ ሆና ትከተለዋለች፡፡
ከበረከቱ በልታ ፍርፋሪውን ታነሣለች፡፡ ድውያንን ሲፈውስ ሙታንን ሲያነሣ ተመልክታ ከድውይነቷ ለመፈወስ ትከተለዋለች ስትድን ዞራ
አታየውም፡፡ ዓለም ሲርባትና ስትታመም ብቻ የምትከተለው ሆነች፡፡ እንዲያውም ሙት ማንሣቱ ድውይ መፈወሱ አበርክቶ መመገቡ ነውር
ነቀፋ ሆነበት፡፡ ዓለም ስትበላና ስትፈወስ እንጅ ስትራብና ስትታመም የነበረባትን መከራ ማሰብ ተሳናት፡፡ በዚህም የተነሣ የአይሁድ
ካህናት ለግርፋት ለስቅላት ብሎም ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት አግኝተንበታል ብለው ተነሣሱ ለንጉሣቸውም ከሰሱት፡፡ ከበላው የበላ
ከጠጣው የጠጣ ካደረበት ያደረ ከዋለበት የዋለ አንድ 30 ብር እና ብልጠት ያታለለው ይሁዳ ለካህናት አሳልፎ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ይሁዳ
30 ብር ዓይኑን ሰወረው ስሞ አሳልፎ ሰጠው፡፡ንጉሣቸው ሁሉንም ነገር መረመረው ከአፉ ሀሰት አጣበት እንዲህ ዓይነቱን ይሾሙታል
ይሸልሙታል እንጅ እንዴት ይፈርዱበታል ብሎ ሰጣቸው፡፡ እርሱ ግን ይሙት በቃ እንዲፈረድበት አብዝተው ጮሁ፡፡ አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በጲላጦስ አደባባይ ነው ምንም ወንጀል ሳይኖርበት
እንደወንጀለኛ ለፍርድ ቆመ፡፡ የ38 ዓመት በሽተኛ ማዳኑ ቤተመቅደሱን አፍርሱት በ3ኛው ቀን አነሠዋለሁ ማለቱ ለሞት እንደሚያበቁት
ሃናና ቀያፋ አሰምተው ተናገሩ፡፡ ይሰቀል ይሰቀል ይሰቀል በሞት አስወግድልን የሚሉ ድምጾች አስተጋቡ፡፡ ዓለም ያበላትን፣ ያጠጣትን፣
የፈወሳትን ፈጣሪዋን ልትሰቅል ተቻኮለች፡፡
እንደ እስር ቤቱ ዘበኞች አቆጣጠር አራት ወንበዴዎች ተይዘዋል፡፡ እንደ አይሁድ ካህናት እና
እንደእኔ አቆጣጠር ግን 3ናቸው ሦስትነታችን ግን ለየቅል ነው አይገናኝም አይስማምም፡፡ ወንበዴዎቹም ለዘበኞቹ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ፣
ጥጦስ፣ ዳክርስና በርባን እንደ አይሁድ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ጥጦስና ዳክርስ እንደእኔ ደግሞ ጥጦስ፣ ዳክርስና በርባን ናቸው፡፡
እንግዲህ ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ ያሉት በሙሉ ወንበዴዎች፣ ቀማኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የእነርሱ ተቃራኒ
ነው፡፡ የሞቱትን የሚያሥነሳ፣ የታመሙትን የሚፈውስ፣ ለምጻሞችን የሚያነጻ ነው፡፡ ነገር ግን እኩል ታስረዋል፡፡ እንደልማዳቸው ለበዓል
ከታሰሩ አራት እስረኞች መካከል አንዱን ይፈታሉ ሦስቱን ደግሞ ይሰቅላሉ፡፡ ኢየሱስን ልፍታላችሁ ሌሎችን ግን ስቀሉ አላቸው ፈራጁ፡፡
ነገር ግን ዓለም ለበርባን የተስማማች ናትና ነፍሰገዳዩ በርባን፣ ቀማኛው በርባን፣ ወንበዴው በርባን (እንዲያውም የወንበዴዎች አለቃ
ነው) እንዲፈታላት ኢየሱስ ግን እንዲሰቀልላት ጮኸች፡፡ በእርግጥ ነው ኢየሱስ ካልተሰቀለላት ዓለም ከታመመችበት የኃጢአት በሽታ
እንደማትድን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እርሷ መድኃኒቷን አታውቅም፡፡
በርባን የይሁዳ የሚስቱ ወንድም ነው፡፡ ይሁዳ 30 ብር የተመዘነለት ኢየሱስን አሳልፎ ሊሰጥና
የሚስቱ ወንድም በርባን እንዲፈታለት ነው፡፡ በርባን ድጋፍ አለው፣ በርባን ቀማኛነቱን እንደያዘ አይሁድ ደግፈውታል፡፡ ዓለም ለቀማኞች
ናት፣ ዓለም ለወንበዴዎች ናት፣ ዓለም ለዘራፊዎች ናት ለዚያም ነው መድኃኒቷን ይሙት በቃ ፈርዳ ለበርባን የምታጨበጭብ፡፡ ኢየሱስ
ለመስቀል ሞት ተላልፎ ተሰጠ ሁለቱ ማለትም ጥጦስና ዳክርስም እንዲሁ አብረውት ወደ ቀራንዮ ወጡ ዓለም ያጨበጨበችለት በርባን ግን
በነጻ ተለቀቀ፡፡ ዓለም የምትፈልገው ትእግስተኛን አይደለም፣ ዓለም የምትፈልገው ትህትና የተላበሰን አይደልመ፣ ዓለም የምትሻው የሚሰጥን
አይደለም፣ ዓለም የምትፈልገው መድኃኒት አይደለም፣ ዓለም የምትፈልገው መልካም ትምህርት አይደለም፣ ዓለም የምትሻው የኢየሱስ ክርስቶስን
ማዳንና ፈውስ እንደሁም የእርሱን መድኃኒትነት አይደለም የበርባንን ውንብድና ብቻ ነው፡፡ ለበርባን እጃቸው እሰኪዝል አጨበጨቡለት
ኢየሱስን ደግሞ እጃቸው እስኪዝል ድረስ ደበደቡት፡፡ ሥጋውን ያበላው ደሙንም ያጠጣው ይሁዳ እንኳ ሳይቀር ለበርባን አጨበጨበ፡፡
የበላበትን ጣት ነከሰ ሰላሳ እንጅ ገነትን የሚመለከትበት ዓይኑ ታወረ፣ በርባንን እንጅ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያስብበት ኅሊናው
ተገፈፈ፡፡
አሁን በቤተክርስቲያናችን እየተፈጠረ ያለው የአይሁዳውያኑ (የተሐድሶ መናፍቃን) ጫጫታ በርባን ይፈታልን ኢየሱስን ስቀልልን የሚል ይመስላል፡፡ እገሊት እገሌ
ካጠመደባት ወጥመድ ነጻ ሆነች፣እገሌ እንዲህ የሚባለው ማኅበር አስደበደበው ሃብት ንብረቱን ዘረፈው እያለች ደጋፊዋን ትለቃቅማለች፡፡
ይቆየን
No comments:
Post a Comment