Monday, August 17, 2015

ሽታ አልባው አበባ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እኔ ነኝ ያውም እኔው ራሴ አበባ ነኝ ያውም ሽታ አልባው፡፡ አበባነት ደረጃ ላይ ለመድረስ እግዚአብሔር ብዙ ነገርን ሰጥቶኛል፤ መስጠት ብቻም አይደለም ብዙ ነገርን አድርጎልኛል፡፡ ከማብቀል ጀምሮ ግንድና ቅርንጫፎቼን እስከማጠንከር ድረስ የአምላኬ ድርሻ ነው፡፡ “እስመ አንተ አውጻእከኒ እምከርሥ ወተወከልኩከ እንዘ ሀለውኩ ውስተ አጥባተ እምየ፡፡ ላዕሌየ ተገደፍኩ እማኅጸን፤ እምከርሠ እምየ አንተ አምላኪየ” ከማኅጸን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ፡፡ መዝ 21÷10 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት እኔንም እንዲሁ ነው ከእናቴ ሆድ ጀምረህ የጠበቅኸኝ፡፡ ዳግመኛም “እስመ አንተ ተስፋየ እግዚኦ እግዚእየ ተሰፈውኩከ እምንእስየ ወብከ ጸናእኩ በውስተ ከርሰ እምየ ወበውስተ ማኅጸን አንተ ከደንከኒ”  አቤቱ አንተ ተስፋየ ነህና እግዚአብሔር ሆይ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛየ ነህና ከማኅጸንም ጀምሮ ባንተ ተደገፍኩ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያየ ነህ” መዝ 70÷5-6 አለ ቅዱስ ዳዊት፡፡ በእናቴ ሆድ 9 ወር ከ5 ቀን ጠበቅኸኝ ከዚያም ወደዚህ ዓለም እንድመጣ ፈቀድህ፡፡ ምንም እንኳ በኃጢአት የተጸነስኩ ይሁን አይሁን ባላውቀም እንደ ዳዊት “እስመ ናሁ በኃጢአት ተጸሰነስኩ ወበአመጻ ወለደተኒ እምየ” እነሆ በአመጻ ተጸነስኩ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ፡፡ መዝ 50÷5 በኃጢአትም ይሁን በጽድቅ ለኃጢአትም ይሁን ለጽድቅ አምላክ እርሱ ባወቀ ተወለድሁ፡፡ ከመወለድ ጀምሮ ማደግን አምላክ በማያልቅ ቸርነቱ አደለኝ፡፡ ከልጅነት እስከ አዋቂነት፣ ከኩተት እስከ ሽበት በሚዘልቀው የዘመናት ቅብብሎሽ ሁሉ አምላኬ አልተለየኝም፡፡ አሁን የወጣትነት ዘመን ላይ ወይም የጉልምስና ዘመን ላይ ልሆን እንደምችል እገምታለሁ፡፡ ከማኅጸን ጀምሮ የጠበቀኝን አምላክ በመወለዴ እንዳመሰገንሁት ለዚህ ጊዜም ያደረሰኝ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፡፡ የዛሬም ጸሎቴ እንዲሁ ያው የቅዱስ ዳዊት መዝሙር ነው፡፡ “ኢትሰደኒ በመንፈቀ ዓመትየ” በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ መዝ101÷24 እያልኩ እማጸነዋለሁ፡፡ የሰው ልጅ ዕድሜው 70 ዓመት ነው ቢበዛም 80 ዓመት እንደሆነ ዳዊት ይናገራል፡፡ እንግዲህ በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ እያልኩ የምጸልየው በ35 አልያም በ 40 ዓመቴ አትውሰደኝ ለማለት አይደለም፡፡ የዘመኔ እኩሌታ ፍሬ አልባ የሆነው ዘመኔ ነው፡፡ በዚያ ፍሬ በሌለበት ቅጠል ብቻ በሆንኩበት ዕድሜየ ቢበዛም ፍሬ ለማፍራት በማይችለው እንቡጥ አበባ በሆንኩበት በለጋ ዕድሜየ አትውሰደኝ አትቅሰፈኝ ማለቴ ነው፡፡ ህይወቴ ወተትን ብቻ እመገብ ከነበረበት ሕጻንነቴ እስከ አሁን አጥንትን ሳይቀር መቆርጠም እስከምችልበት ጎልማሳነቴ ድረስ ለዘር ለፍሬ የበቃ ምግባር እንደሌለኝ የማውቀው እኔው ራሴ ነኝ፡፡ የራሴን ህይወት የምመለከተው በራሴ መነጸር ብቻ አይደለም በእግዚአብሔር ቃልና ስለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ደማቸውን ባፈሰሱት ሰማእታት እንዲሁም በጾም በጸሎት በኖሩት በቅዱሳኑ ተጋድሎ ውስጥ ጭምር ነው፡፡ አሁን አበባ ነኝ ያውም ዘር የማያፈራ ለምልክት ብቻ የተቀመጥኩ ለጌጥ ከምግብ ጠረንጴዛ ላይ የኖርሁ አበባ ነኝ ያውም የማልሸት አበባ…
ተራሮችን በአበቦች የሚያስጌጥ አምላክ አኔንም አበባ አደረገኝ፡፡ እንዲያውም ሰው የሆኑ ሰዎችን ለማስተማር ጌታችን ተጠቅሞብኛል፡፡ “ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ማቴ 6÷28-29፡፡ ዛሬ እኔ አበባ ነኝ ለጌጥነት ማንም ሊጠቀምብኝ የሚችል፡፡ በጌጥነቴ እና ውብ በመሆኔ ግን የምማርከው ንቦችን እና ቢራቢሮዎችን ብቻ አይደለም፤ ማንም ተራ የሚባለውንም ሰው ብቻ አይደለም እኔ የምማርከው ንጉሡንም ጭምር ነው፡፡ ሰሎሞን ንጉሥ ነው ነገር ግን እኔ ባጌጥኩበት መጠን አላጌጠም እኔም በከበርኩበት መክበር አልከበረም፡፡ ለዛም ነው ሁሉንም ወደ እኔ የመሳብ ችሎታ ያለኝ፡፡ ነገር ግን አበባ መሆኔ ብቻ አይደለም ለዚህ ክብር ያበቃኝ መልኬ ደም ግባቴ እና ሽታየ ጭምር ነው እንጅ፡፡ ብዙ አበቦች አሉ በተለያየ ኅብረ መልክ የሚታዩ፤ ብዙ አበቦች አሉ በተለያየ መልኩ ለአፍንጫ የሚሸቱ፡፡ ታዲያ እንደ መልካችንና ሽታችን እንለያያለን፡፡ ሰው የሚመለከተን አበባ መሆናችንን ብቻ ሊሆን ይችላል ግን የማንሸት አበቦችም እንዳለን ልብ ልትሉ ያስፈልጋል፡፡
“በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ፡፡ በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርሷ መጣ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትም” ማቴ21÷ 18-19 ይች ዛፍ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ታሪክ አላት፡፡ እርሷ ለእይታ በጣም ማራኪ ናት ለተራበ ሰው ደግሞ እጅግ በጣም ሲበዛ  ማራኪ ናት፡፡ ነገር ግን ለጥላነት ካለሆነ በቀር ለምግብነት የሚሆን ነገር የላትም፡፡ በሩቅ ለሚመለከታት ቀርቦ ላልፈተሸት ግን ፍሬ ያላት ለርኁባን ጥጋብን የምታድል ትመስላለች፡፡ እኔም ብሆን አበባ መሆኔ እንጅ እንደ እርሷ ነኝ፡፡ ሰው ዛፏን የሚቀርባት የሚበላ ነገር ለመፈለግ ነው እኔን ግን የሚጠጋኝ በመልኬ አልያም በሽታየ ተማርኮ ነው፡፡ ነገር ግን አልሸትም አለመሽተቴ የሚታወቀው ግን ለቀረበኝ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን አስመርቄያለሁ፣ ብዙ ሰዎችን አጋብቻለሁ፣ የብዙዎችን ቤት አጊጫለሁ ነገር ግን አልሸትም፡፡ ሰዎች ለምረቃ ገዝተው ለስጦታነት ያበረክቱኛል፣ ለቤታቸው ጌጥነት ይጠቀሙብኛል፣ በጋብቻቸው መካከል የፍቅር ማሞቂያነት ይጠቀሙብኛ፡፡ ነገር ግን ለራሴ አበባ አይደለሁም ለሰዎች ግን ስላላስተዋሉኝ አበባ ነኝ፡፡ አበባ ለመባል ቀለሜ ብቻውን በቂ አልነበረም ሽታየም ተገቢ ነበር ግን ሰዎች አላስተዋሉም፡፡
የእኔ ህይወትም እንደዚህ አበባ ነው ሽታ የሌለው አበባ፡፡ ሰዎች እንደ ትልቅ ሰው የሚቆጥሩኝ፣ የበለሷን ዛፍ የመሰልኩ አለባበሴ ከሩቅ የሚማርክ፣ አነጋገሬ በቅርብ የሚያሳምን፣ ለእይታ ማራኪ፣ ለሚዳስሰኝ እጅግ በጣም ለስላሳ ቅጠል ያለኝ ነገር ግን ፍሬ አልባ ዛፍ፡፡ ነገር ግን ሽታ አልባ አበባ፡፡ አበባው እኔ ነኝ ሽታው ደግሞ ምግባሬ ነው፡፡ ከጌጥነት ከቁጥር የዘለለ ጥቅም የማልሰጥ ከንቱ ሽታ አልባ አበባ፡፡ በተፈጥሮ ከሚገኘው መልክና ሽታው ማራኪ ከሆነው አበባ ጋር ተመሳስየ በሰው እጅ በፋብሪካ የተሰራሁና የተመረትሁ አበባ፡፡ በቃ እኔ ሰው ሰራሽ ሽታ አልባ አበባ ነኝ፡፡

No comments:

Post a Comment