©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ክፍል አራት
ቅዱሳን ሥዕላት የሚሣሉበት
ቦታእና ክብራቸው
ስለቅዱሳን ሥዕላት ክብርና
ቅድስና ባለፉት ክፍሎች ተመልክተናል፡፡ በመሆኑም ስለክብራቸውና ስለ ቅድስናቸው ለአገልግሎትም ጠቀሜታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በቤተክርስቲያን
ይሣላሉ፡፡ ይሁን እንጅ ምዕመናንም ቅዱሳን ሥዕላትን ለተለያዩ አገልግሎቶች ስለሚጠቀሙባቸው እያሣሉ በቤታቸው ይገለገሉባቸዋል፡፡
እዚህ ላይ ግን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ቅዱሳን ሥዕላት ለግድግዳ ጌጥነት የምንጠቀምባቸው አይደሉም፡፡ በክብር በተለየ ቦታ
በመጋረጃ ተጋርደው ለጸሎት በምንጠቀምበት ልዩ ቦታ ላይ ሊደረጉ ይገባል፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ አባቶች መንገድ ሲጓዙ ለጸሎት የሚጠቀሙበት
የገበታ ሥዕል በመባል የሚታወቅ አለ፡፡ በአጠቃላይ ሥዕላት በቤተክርስቲያን ውስጥ በጣሪያና በግድግዳ ላይ እንዲሁም በበሮችና በመስኮቶች
ላይ ይሣላሉ፡፡ በተጨማም ከላይ እንደተመለከትነው በገበታ እና በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ሊሣሉ ይችላሉ፡፡
1. በግድግዳ፡- በቤተክርስቲያን ውስጥ በተለይ በቤተመቅደስ ግድግዳዎች ዙሪያ
ቅዱሳን ሥዕላት ይሣላሉ፡፡ በብዛት ክብ ቤተክርስቲያን በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ የመቅደሱ ግድግዳ ከታች እስከ ላይ ድረስ በቅዱሳን
ሥዕላት የተሸፈነ ነው፡፡ እዚህ ላይ የአሣሣሉም የራሱ የሆነ አቅጣጫ አለው፡፡
ሀ.
በምዕራብ፡- ቅድስት ሥላሴ፣ የጌታችንን መከራ የሚያሳዩ ሥዕላት፣ ጸሎተ ሐሙስ፣ ሥርዓተ ቁርባን እነዚህን የሚያሳዩ ሥዕላት
ይሣላሉ፡፡
ለ.
በደቡብ፡- የእመቤታችንን ታሪክ ማለትም ልደቷን፣ ወደ ቤተመቅደስ መግባቷን፣ ስደቷን፣ እረፍቷን ወዘተ የሚያሳዩ ሥዕላት
ይሣላሉ፡፡
ሐ.
በምሥራቅ፡- ከጽንሰት እስከ ዳግም ምጽአት ያለው የጌታችን ታሪክ ይሣላል፡፡
መ.
በሰሜን፡- የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት ተጋድሎ
የሚያሳዩ ሥዕሎች ይሣላሉ፡፡
2. በጣሪያ፡- የፊት መልክ ብቻ የሚሣልላቸው ሠራዊተ መላእክት በብዛት
ይሣላሉ፡፡ ምሳሌያዊ ሥዕላት እንደ በግ፣ ወይን፣ ዓሣና ባህር፣ መርከብ በተጨማሪም ሐረጋት ይሣላሉ፡፡
3. በበር፡- ቅዱሳን መላእክት ልዩ ከሆነው ተአምራቸው ጋርበሙሉ ቁመታቸው
ይሣላሉ፡፡
4. ገበታ፡- ገበታ ከእንጨት ተፈልፍሎ የሚሠራ ሊከፈት እና ሊዘጋ የሚችል
እንደመጽሐፍ ያለ ነው፡፡ ገበታ በቀላሉ ለሰዎች ምቹ በሆነ መልኩ ስለሚዘጋጅ በዚያው መጠን ሥዕል ይሣልበታል ወይም ይለጠፍበታል፡፡
በብዛት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ትሣልበታለች ነገር ግን እንደ ሰው ፍላጎት የተለያዩ ሥዕላት ሊሣሉበት ይችላሉ፡፡
5. በቅዱሳት መጻሕፍት፡- በመጽሐፍ የተገለጠን ታሪክ መሠረት አድርገው አባቶች ከመጽሐፉ
ውስጥ ይሥላሉ፡፡ ይህ በብዛት በብራና መጻሕፍት ላይ ይዘወተራል፡፡
የቅዱሳን
ሥዕላት ክብር
ቅዱሳን ሥዕላት የከበሩ
ናቸው፡፡ በመሆኑም አስፈላጊ ባልሆነ መንገድ መጠቀም ጉዳት እንጅ ጥቅም የለውም፡፡ አሁን በብዛት የምናስተውለው ለቅዱሳን ሥዕላቱ
የምንሰጠው ክብር በጣም የቀነሰ መሆኑን ነው፡፡ ስዕላትን ለጌጥ፣ለማስታወቂያ፣ እነዲሁም በኮፊያ እና በተለያዩ ልብሶች ላይ መጠቀም
ተገቢ አይደለም፡፡
1. ለጌጥነት አለመጠቀም፡- ለቤት ማስጌጣነት፣ ለመኝታ ቤት ማስጌጫነት፣ለቤትና ለመኪና
ቁልፍ መያዣነት መጠቀም፣ ለመኪና መስኮቶች ጌጥነት ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ መኪና ውስጥ ስትመለከቱ ሲጋራ ይጨስባቸዋል፣
ይቀደዳሉ፣ ጫት ይቃምባቸዋል ወዘተ ስለዚህ የተከለከለ ነው፡፡
2. ልብስ ላይ አለማድረግ፡- ኮፊያ፣ ከነቴራ ላይ መሣል ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ልብሱ
ይቆሽሻል ያ ማለት ሥዕሉንም እናበላሸዋለን ማለት ነው፡፡ ሲቆሽሽ ታሽቶ ይታጠባል በዚህም የተነሣ ሥዕሉ ይላላጣል፡፡ ስለዚህ በተለይ
ለክብረ በዓላት ቅዱሳን ሥዕላትን የምናሳትም ወገኖች ጥንቃቄ ብናደርግ ጥሩ ነው፡፡ ለበረከት ስንል ለመቅሰፍት እንዳይሆንብን፡፡
3. ሥዕላትን ለማስታወቂያ አለመጠቀም፡- አንዳንድ ነጋዴዎችና ድርጅቶች በሚያመርቱት ምርት ላይ ቅዱሳን
ሥዕላትን ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ላይ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ሰው ይሰክራል፣
ሥዕሉን ከጠርሙሱ ልጦ ይጥለዋል፣ ሥዕሉ ተገቢ ባልሆነ ቦታ ይወድቃል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ለቅዱሳን ሥዕላት ክብርን የሚቀንሱ
ነገሮችን ከመጠቀም ልንታቀብ ተገቢ ነው፡፡
ተፈጸመ
ምንጭ፡-
የተለያዩ መጻሕፍት እና በራሪ ጽሑፎች
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ReplyDelete