Monday, April 18, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል ስድስት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 8/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 17 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  18ኛ ነጥብ፡- ካህናትን በተመለከተ፡፡
·         ካህናት የሚሠሩት ኃጢአት ፕሮቴስታንት እንድሆን አደረገኝ ለሚሉ፡- የካህናትን ሰማያዊ ሥልጣን ንስሐን በተመለከተ ስንማር ዓይተናል፡፡ መናፍቃኑ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሲጠየቁ “እኔ ድሮ ኦርቶዶክስ ነበርሁ ነገር ግን ካህናት ሲቀድሱ ሲያስተምሩ ውለው አልባሌ ከሆነ ቦታ አገኛቸዋለሁ ጠንቋይ ቤት ሳይቀር ሲሄዱ አያለሁ፡፡ ከዚያ እነሱ አስተማሪዎች እንዲህ እያደረጉ ለምን ኦርቶዶክስ እሆናለሁ ብዬ ፕሮቴስታንት ሆንኩ” ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ፕሮቴስታንት መሆናቸው በራሱ ያሳፈራቸው አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ወደምንፍቅና የሄዱበት ዋናው ምክንያት የካህናቱ ችግር አይደለም ነገር ግን ቢያንስ እንዲህ ልበል ብለው ራሳቸውን ማጽናናት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው፡፡ “አያ ጅቦ ሳታመኸኝ ብላኝ” አለ አሉ፡፡ ፕሮቴስታንት የሆንኩ ጾሙ ከብዶኝ፣ መዝፈን አምሮኝ መጨፈር አስደስቶኝ ነው በሉን ዝም ብላችሁ እየተዋወቅን። ከዚህ ባለፈ ግን ስም በማጥፋት ላይ አትሰማሩ፡፡ ግን እንጅ ካህናት ጠንቋይ ላይ ሄዱ እራሳቸውም ጠንቋይ ሆኑ እንበል አልባሌ ቦታም እስከመስከር ድረስ ደርሰው ዓየናቸው እንበል... እና ቢሆንስ ምን ይመለከተናል፡፡ ያንን ሥራ የሚሠሩት ሰዎች እኮ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሚባል እምነት አይደሉም ሰዎች ናቸው እንጅ፡፡ ሰዎች ስህተት በሠሩ እምነቱ የሚወቀስበትና የሚናቅበት ነገር የለም፡፡ ከመላእክት መካከል ዲያብሎስ ካደ በዲያብሎስ መካድ የተነሣ ግን ቅዱሳን መላእክትን አማልዱን ማለታችንን አናቆምም፡፡ ምክንያቱም ዲያብሎስ ሌላ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ ሌላ ናቸውና በሏቸው፡፡ ከሐዋርያት መካከልም ይሁዳ አምላኩን ሸጦታል ነገር ግን በይሁዳ መሳት የተነሣ ቅዱስ ጴጥሮስን እና የቀሩትን ሐዋርያት አንንቃቸውም አናቃልላቸውም በሏቸው፡፡ በመጀመሪያ እንዲህ አድርገዋል የምንላቸው ካህናት ለምን ዓላማ ክህነቱን እንደተቀበሉም ማዎቅ አለብን፡፡ ካህኑ ስላጠፋ ደግሞ እምነትን ለመለወጥ መሮጥ አያስፈልግም ምክንያቱም የካህኑ ነፍስ ለራሱ ነው የእኛ ነፍስ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ እሱ በሥራው እኛም በሥራችን ነው የምንጠየቀው በሏቸው፡፡ በፍርድ ቀን ምን ሥራህ የት ነበርህ እንጅ ካህን እገሌ የት ነበረ ምን ሠራ ተብለን አንጠየቅም። እኛ የራሳችን ኃጢአት ይበቃናል በሰው ኃጢአት ምንም አይመለከተንም። በተጨማሪም የሚከተሉትን እንመልከት፡፡
·          ማቴ 7÷1-2 ላይ “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መሰፈሪያ ይሰፈርባችኋል” ይላል፡፡ ስለዚህ እናንተ እንደምትሉት ካህኑ ጠንቋይ ይሁንም ይስከር ይጨፍርም እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ ተብሏልና ልንፈርድ አይገባንም በሏቸው እኛ እነማን ሆነን ነው የሰውን ኃጢአት እየመዘገብን የምንወቅስ። እኛ ስንሠራው ኃጢአት የማይሆነው ነገር ሁሉ ካህናት ላይ ስናየው ኃጢአተኛ ናቸው እያልን እንድንወቅስ ማነው ሥልጣኑን የሰጠን? ራሳችንን በውል የማናውቅ ሰዎች ሆነን ካልሆነ በቀር ካህናት ላይ ዘለን ፊጥ ማለታችን ምን የሚሉት ቅዠት ነው፡፡ ይህንንም የማይቀበሉ ከሆነ፤
·         ማቴ 7÷3 ላይ “በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ በዐይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም” ይላል፡፡ ስለዚህ ከካህናት ዐይን ያለውን ጉድፍ አጥርታችሁ ከምትመለከቱ ይልቅ ከራሳችሁ ዐይን ላይ ያለውን ምሰሶ ተመልከቱ በሏቸው፡፡ እስከ ቁጥር 5 ስንመለከት እንዲህ ይላል “ወይም ወንድምህን ከዐይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ እነሆም በዐይንህ ምሰሶ አለ፡፡ አንተ ግብዝ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዐይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ” ይላል በግልጽ፡፡ ምናልባት ሌላ ምክንያት ካላችሁ እንጅ የካህናት ሥነምግባር እምነታችሁን እንድትለውጡ ሊያደርጋችሁ በፍጹም አይችልም በሏቸው፡፡ 
·         በዚህ ምክንያት ነው ብለው ከሞገቷችሁ ግን ስንቱ ዋልጌ ፓስተር ወደሚቆምርበት አዳራሽ የሚያስሄድ ጥፋት ካህናት ላይ አለ ብለን አናምንም በሏቸው። “ፓስተር ዳዊትና ፓስተር ዘማሪ ተከስተ” የሰው ሚስት ሲያማግጡ ምነው ወደ እኛ አልተመለሳችሁም ነበር በሏቸው፡፡ ወይስ ደግሞ እስልምናን እንሞክረው ብላችሁ ወደዚያ ገባችሁ በሏቸው። የሚገርመው ነገር የእኛ ካህናት እንዲህ ሲያደርጉ ቢገኙ ተወግዘው ይለያሉ የእነርሱ ፓስተሮች ግን ዛሬም ድረስ ያው ፓስተር እየተባሉ የሰው ሚስት ሲያማግጡ ነው የሚገኙት፡፡ እንዲህ ዓይነት አንድን ሴት ለጋራ ለመጠቀም አስበው ሴቶችም ይህንኑ ሽተው የሄዱ ከሆነ ግን በርቱ በሏቸው ሌላ ምን ይባላል መቼስ፡፡ አንድ ቀን አምላክ እውነቱን ሲገልጥላቸው ማሰብ ይጀምሩ ይሆናል ማን ያውቃል የአምላክን ሥራ።
·         መናፍቃን ራሳቸውን እንደ ትለቅ ጻድቅ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ እነርሱ የሚሠሩት ሁሉ መልካም እና ጽድቅ ነው ሌላው ከእነርሱ እምነት ውጭ ያለ ሰው የሚሠራው ሁሉ ደግሞ መጥፎ እና ኃጢአት ነው፡፡ የእኛን አባቶች በገዳም ቢጫ ጋቢያቸውን ለብሰው አስኬማቸውን ደፍተው ዓለም አልገባቸው ብላ ለጸሎት በዱር በገደል ሲመለከቷቸው ይንቋቸዋል “ጽድቅ እንዲህ በመንከራተት የሚገኝ መስሏቸው” እያሉ ይዘብታሉ ያፌዛሉ፡፡ በዚያ ጎን ካህኑ ኃጢአት ሲሠራ ዓይተን ፕሮቴስታንት ሆንን ይላሉ በዚህ ጎን ደግሞ በዱር በበረሃ በባዶ እግራቸው ለጸሎት ለስግደት የሚተጉ ባሕታውያንንና መነኮሳትን ሲንቁ ሲያንቋስሽሹ እንሰማለን፡፡ ታዲያ እናንተን ለመምሰል የግድ በየአዳራሹ በዝሙት አልጋ ላይ እንተኛላችሁ ወይስ ደግሞ እንጨፍርላችሁ በሏቸው፡፡ ማቴ 11÷18-19 ላይ “ ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ እርሱም ጋኔን አለበት አሉት፡፡ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ እርሱም እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጪ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል” አለ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ የሰው ልጅ ምንም ብታደርግለት ሐሜቱን አያቆምም ሳይበላ የመጣውን ዮሐንስ ጋኔን አለበት አለ እየበላ የመጣውን ኢየሱስ ደግሞ በላተኛ ነው አሉት፡፡ አንድ ደስ የሚል አባባል አንብቤያለሁ “ሰዎች በውኃ ላይ ስትራመድ ቢያዩህ ዋና ስለማይችል ነው ይሉሃል” የሚል አባባል ነው፡፡ በጣም ትልቅ አባባል ነው፡፡ሰው ምንም ያህል ጻድቅ ቢሆን ከመታማት አያመልጥም። ካህናት ምንም ንጹሕ ቢሆኑ ከመታማት አይጠሩም ግድ ነው፡፡ ኢየሱስ አጋንንት ያደረባቸውን ሰዎች ከአጋንንት ቁራኝነት ሲያላቅቅ፣ ለምጻሞችን ሲያነጻ፣ ሽባዎችን ሲተረትር፣ ዕውራንን ሲያበራ፣ የሰላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛ መጻጉእን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ሲል፣ አልዓዛር አልዓዛር ከመቃብር ውጣ ብሎ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ሲያነሣ የእጁን ተአምራት የተመለከቱ ፈሪሳውያን ማቴ 12÷24 “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” ያሉት እውነታቸውን ነበርን በሏቸው፡፡ በእውነት ኢየሱስ ያንን ሁሉ ድንቅ ሥራ የሠራው በአጋንንት አለቃ በሆነው ብብዔል ዜቡል ነበርን? በሏቸው። ስለዚህ ሰው የፈለገውን ሊሠራ ይችላል እምነትን እንድንለውጥ ሊያደርግ የሚችል ምክንያት ግን የለውም ምክንያቱም እኛ የምናምነው አምላክን እንጅ ሰውን አይደለምና፡፡ በአገራችን በፖለቲካው ዓለም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ የሥልጣን ደረጃ አለው። እሱ ህገ መንግሥቱን ሲጥስ ብትመለከቱ ከዛሬ ጀምሬ ተቃዋሚ ድርጅት ላይ አባል እሆናለሁ የሚል ሰው አለን? የአፈጻጸም ችግር ነው ብለህ እንደምትቀመጥ ይታወቃል እኮ። ይህም የእናንተ ከንቱ ሃሳብ ከዚህ የዘለለ አይደለም በሏቸው።

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

ተጨማሪ ትምህርቶችን ለማግኘት http://melkamubeyene.blogspot.com ን ይጎብኙ፡፡

Friday, April 15, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል አምስት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 7/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 16 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  17ኛ ነጥብ፡- ሥርዓትን በተመለከተ፡፡
·         ሥርዓት ማለት ደንብ አሰራር ማለት ነው:: ለማንኛውም ሥራ ሥርዓት ሊኖረው ያስፈልጋል:: እምነት ውስጥ ያለው መታመን በዘፈቀደ ሳይሆን በሥርዓት መሆን አለበት:: አንድ እምነት ሥርዓት ካለው ብቻ ነው እምነት ሊባል የሚችለው:: ሥርዓት አያስፈልግም ብለው የሚከራከሩን መናፍቃን እኮ እነርሱ እንደፈለጉ ለመሆን ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 10÷23  “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” ብሏል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ እንደፈለገው ለመሆን የሚፈልግ ሰው “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ብቻ የምትለውን ጥቅስ እንዳነበበ መጽሐፉን ይዘጋዋል፡፡ ቀጥሎ ግን ምን ይል ነበር  “ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” ስለዚህ ሁሉ ቢፈቀድልንም ሁሉ የሚጠቅመን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሥርዓትንም እየነገረን ነው ያለው፡፡ የተፈቀደውን ሁሉ አትሥሩ የሚጠቅመውን መርምሩ እያለን እኮ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ሁሉ ቢፈቀድልንም መብላት፣ መጠጣት፣ መስከር፣ መጨፈር፣ አምላክን መካድ ከዚህም ሌላውን ሁሉ ነገር ማድረግ የራሳችን ነጻ ፈቃድ ቢሆንም ይህ ሁሉ ግን አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ በሥርዓት ተመርተን የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው መለየትና የሚጠቅመውን ብቻ መምረጥና መያዝ ይገባናል በሏቸው፡፡
·         ሥርዓትን ለሚንቁ (የቤተ ክርስቲያንን)፡- ሥርዓትን የሚንቁ ሰዎች በሰፊው የጥፋት መንገድ መሄድ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ጠባቡ የድኅነት መንገድ ሥርዓት አለው ሰፊው የጥፋት መንገድ ግን ሥርዓት የለውም፡፡ ማቴ 7÷13-14 ላይ “በጠበበው ደጅ ግቡ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና ወደርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ይላል፡፡ ሰፊው ደጅ ብዙዎች የሚገቡበት ሥርዓት የሌለውና ሥርዓትን የሚንቁ ሰዎች የሚጓዙበት መንገድ የሚገቡበት በር ነው፡፡ በዚህ በር መግባት የሚሹ ሰዎች ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት አይፈልጉም፡፡ መብላት፣ መጠጣት፣ መዳራት የሚፈልጉ ሰዎች በዚህ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ ሰፊዋ በር ኦሪት ናት በኦሪት ጥርስ ላወለቀ ጥርሱ እንዲወልቅ ዓይን ላጠፋ ዓይኑ እንዲጠፋ ታዝዛለችና፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ መጓዝ የሚሹ ሰዎች ትሕትናን ገንዘብ ያላደረጉ፣ በትዕቢት የተነፉ፣ በጉልበታቸው የሚመኩ ናቸው፡፡ አንድም ሰፊው መንገድ ፈቃደ ሥጋ ነው፡፡ ፈቃደ ሥጋን ለመፈጸም የሚፈልጉ ሰዎች እምነትን መከታ አድርገው አንድ ጥቅስ ብቻ ይዘው ሃሌ ሉያ እያሉ መጮኽን ገንዘባቸው አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሥጋቸው ብቻ የሚሮጡ ናቸውና ሥርዓትን አይወዱም እንደፈለጉ መሆንን ይፈልጋሉ፡፡ ጠባቡ መንገድ ግን ወንጌልና ፈቃደ ነፍስ ነው፡፡ ወንጌል ድሃን ጹም ባለጸጋንም መጽውት የምትል ግራህን ለሚመታህ ቀኝህን ስጥ የምትል አንድ ምእራፍ ሂድ ብሎ ለሚያስገድድህ ሁለት ምእራፍ ሂድለት የምትል ጠባብ ደጅ ጠባብ መንገድ ናት፡፡ ስትጾም እንዲህ ጹም ስትጸልይ እንዲህ ጸልይ ብላ ሥርዓት የምታስተምር ናትና ጠባብ ደጅ ናት፡፡ ፈቃደ ነፍስም እንዲሁ ልብላ ሳይሆን ልጹም፣ ልስረቅ ሳይሆን ልመጽውት የምትል ናትና ጠባብ ደጅ ናት፡፡ ስለዚህ ወደ ጥፋት በሚወስደው የምንፍቅና ሰፊ መንገድ አንሄድም በሏቸው፡፡ ሥርዓት የከበደው ሰው መጀመሪያም ከእኛ ያልሆነ ሰው ስሙን ብቻ የያዘ “ክርስቲያን ነኝ” ብቻ በማለት ወደ ሰፊው መንገድ ሊያስገባን ይሻልና አትስሙት፡፡ በሰፊው መንገድ ብዙዎች መጓዝ ይሻሉ እንደ ሥጋውያን ስናስበው ከመጾም መብላት ይሻላል፤ ከመስጠትም መቀበል ይበልጣል፡፡ እንደ ሥጋውያን ስናስብ ቆሞ ከማስቀደስ አልጋ ላይ ተኝቶ ሙዚቃ መስማት ይበልጣል፤ ቆሞ ውዳሴ ማርያምን ከመጸለይ ይልቅ ተጋድሞ ማርፈድ ይበልጣል፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊ ዓይን ስንመለከተው ይህ ሁሉ አላፊ ጠፊ ነው ሁሉም ያልፋልና ለነፍስ ማሰብን እንመርጣለን፡፡ ለዚህም የምንበላው ነገር እያለን አንበላም ብለን እጾማለን፣ ገንዘብን ለራሳችን ችግር መፍቻ ማዋል ስንችል የራሳችንን ትተን ለድሃ እንመጸውታለን ጠባብ በር ማለት ይህ ነው፡፡ በዚህ ጠባብ በር እንገባለን በዚህም ጠባብ መንገድ እንጓዛለን ምክንያቱም ጥቂቶች ብቻ የሚጓዙበትን መንገድ መርጠናልና በሏቸው፡፡
·         1ኛ ቆሮ 14÷40 “ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሥርዓት የሌለበት እምነት እኮ አንዱ ሲጸልይ ሌላው የሚዘምርበት ነው፡፡ አንዱ ሲዘምር ደግሞ ሌላው የሚስቅበት ነው፡፡ አንዱ ሲያስቀድስ ሌላው የሚዘፍንበት ነው፡፡ ታዲያ አጥር የሆነ ሥርዓት አያስፈልግምን በሏቸው፡፡ ምክንያቱም ሁሉ ነገር በአገባብና በሥርዓት ይሁን ብሎናልና ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ዝም ብሎ መንፈስ ተገለጠልኝ እያሉ መንፈራገጥ እና ልሳን ነው እያሉ ዝም ብሎ ማንም የማይሰማውን ቋንቋ መቀባጠር አይደለም ይህ ሁሉ በአገባብና በሥርዓት መሆን አለበትና በሏቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሲጥልና ሲያንፈራግጥ ዓይተንም አንብበንም ሰምተንም አናውቅም ሰይጣን ግን ሲጥል ሲያንፈራግጥ አረፋ ሲያስደፍቅ አይተናል አንብበናልም፡፡ ስለዚህም ከሥርዓታችን ወዴትም አንሄድም በሏቸው፡፡

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

Thursday, April 14, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል አራት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 6/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 15 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  16 ኛ ነጥብ፡- ቅዱሳንን በተመለከተ፡፡
·         የድንግል ማርያምን ክብር ለሚያቃልሉ፡- ከመላእክት ወገን የሆነው ስሙ ገብርኤል የተባለው የመላእክት አለቃ ወደ ድንግል ማርያም ቀርቦ በትሕትና ሉቃ 1÷28 ላይ “ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት” ይላል፡፡ ታዲያ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ብሎ አክብሮ ደስ ይበልሽ ብሎ ያመሰገናትን ከሴቶች ሁሉ መካከል ልዩ ክብርት ልእልት የሆነቺውን እመቤት ለምን መናፍቃን ታቃልላላችሁ? ወይስ ደግሞ ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንበልጣለን ለማለት ነው የምትፈልጉት? በሏቸው፡፡
·         ሉቃ 1÷41-44 “ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅጸኗ ውስጥ ዘለለ፡፡ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፡፡ በታላቅ ድምጽም ጮኻ እንዲህ አለች፡- አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል፡፡ እነሆ የሰላምታሽን ድምጽ በዦሮዬ በመጣ ጊዜ ጽንሱ በማኅጸኔ በደስታ ዘሏልና” ይላል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ቅድም መልአኩ የተናገረውን ነገር ኤልሳቤጥም ደገመችው፡፡ በኤልሳቤጥም መንፈስ ብቻ ሳይል መንፈስ ቅዱስ ሞላባት አለ፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ በኤልሳቤጥ የሞላባት መቼ ነው? የእመቤታችንን ሰላምታ በሰማቺ ጊዜ አይደለምን? በጣም የሚገርመው ግን ገና ያልተወለደው በማኅጸን ያለው ዮሐንስ በደስታ ያዘለለው ምሥጢር ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ታዲያ ገና ያልተወለደው ዮሐንስ በማኅጸን ሳለ ሰላምታዋ አስደስቶት በደስታ ከዘለለ ዛሬ ከማኅጸን የወጣን ሰዎች ምኑ ነው ደስታዋ አላዘልለን ያለ በሏቸው፡፡ በዕድሜ የምትበልጣት  አክስቷ ኤልሳቤጥ አክብራ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? ያለቻትን ድንግል ማርያም መናፍቃን ለምን ታቃልላላችሁ በሏቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ብታከብሯት ክብሩ ለራሳችሁ ነው፤ ባታከብሯትም ውርደቱ ለራሳችሁ ነው ምክንያቱም እመቤታችንን ከአንስተ ዓለም መካከል ለእናትነት መርጦ ያከበራት አምላክ ነውና በሏቸው፡፡
·         ቅዱሳን የኢየሱስን ክብር ተሻምተዋል ለሚሉ፡- አልገባቸው ብሎ እንጅ የቅዱሳን ክብር የጸጋ ነው፤ የአምላክ ክብር ደግሞ የባሕርይ ነው፡፡ ቅዱሳንን ስላከበርን አምላክን አናከብርም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የቅዱሳን ክብራቸው ሌላ ነው የአምላክ ክብሩ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ የፀሐይ ክብሯ ከጨረቃ ክብር እንደሚለይ ሁሉ ማለት ነው፡፡ የጨረቃ መኖር ፀሐይን እንድትሸፈን አያደርጋትም፡፡ ምክንያቱም ፀሐይ ሌላ ናት ጨረቃ ደግሞ ሌላ ናት፡፡ የሚያገናኛቸው የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ ነው ያ ማለት ያለፀሐይ የጨረቃን ብርሃን አናይም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳንንም እንዲሁ ነው የምናከብራቸው፡፡ እነርሱን ስናከብር አምላክን አከበርን ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ቅድስናውን የሰጣቸው አምላክ ነውና፡፡ እንዲያውም ባይገርማችሁ ቅዱሳኑን የምናመሰግንበት ጊዜ አጥሮናል በሏቸው፡፡ መጽሐፍ ምን ይላል ዕብ 11÷32 “እንግዲህ ምን እላለሁ ስለጌዴዎንና ስለባርቅ ስለሶምሶንም ስለዮፍታሔም ስለዳዊትና ስለሳሙኤልም ስለነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ የእነዚህን ቅዱሳን ቅድስና ለመተረክ ቅዱስ ጳውሎስ ጊዜ አጠረው እንጅ ጊዜ ባያጥረው ኖሮ ባያችሁ ነበር፡፡ ከዚህ በታች ቅድስናቸውን ይዘረዝራል ቅዱሱ ሰው ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ “እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ ጽድቅን አደረጉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፡፡ የአንበሳዎችን አፍ ዘጉ የእሳትን ኃይል አጠፉ ከሰይፍ ስለት አመለጡ ከድካማቸው በረቱ በጦርነት ኃይለኛዎች ሆኑ የባዕድ ጭፍራዎችን አባረሩ፡፡ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከሞት ድረስ ተደበደቡ፡፡ ሌላዎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ ተፈተኑ በመጋዝ ተሰነጠቁ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ ኹሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፡፡ ዓለም አልተገባቻቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ” ይላል እስከ ቁጥር 38 ድረስ ስናነብብ፡፡ ታዲያ ስለነዚህ ቅዱሳን ሌሊት ከቀን ብንመሰክር ውለታቸውንና ቅድስናቸውን ተናግረን እንጨርሰዋለንን? ብፍጹም አንጨርሰውም፡፡ እኛ ምላጭ ሲቆርጠን ምን ያህል ነው የምንሰቀቀው? እነርሱ ግን በመጋዝ ተሰነጠቁ በእንጨት ላይ ተሰቀሉ እንደ ሽንኩርት ተከተፉ እንደጎመን ተቀረደዱ፡፡ ታዲያ ስለእነርሱ መናገር እንዴት ወንጀል ይሆናል? ስለዚህ ቅዱስ የሆነው አምላክ የቀደሳቸውን ቅዱሳን እስከዘላለም ድረስ ስናከብር እንኖራለን በሏቸው፡፡
·         ቅዱሳንን ለሚንቁ ሰነፎች፡- ሮሜ 8÷33 “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?” ይላል፡፡ ቅዱሳንን የመረጣቸው ደግሞ እግዚአብሔር እንጅ እኛ አይደለንም ስለዚህ ማንም ስለቅድስናቸው ሊከሳቸው አይችልም ከዲያብሎስ በቀር በሏቸው፡፡ ዲያብሎስ ግን የተሰጠውን የመክሰስ ስልጣን ከታች እንመለከተዋለን፡፡
·         ዕብ 13÷7 “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው” ይላል፡፡ የእኛ ዋኖቻችን የእግዚአብሔርንም ቃል የተናገሩን ያስተማሩን በመናገር ብቻ ሳይሆን በተግባር ተርጉመው የኖሩ ቅዱሳን ናቸው በሏቸው፡፡ ስለዚህም በእምነታቸው እንመስላቸው ዘንድ ይገባናል በሏቸው፡፡
·         ራእ13÷5-6 “ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ” ይላል፡፡ ይህ ስልጣን የተሰጠው ለዲያብሎስ ነው፡፡ ስለዚህ እናንተም ቅዱሳንን ስትንቁ የዲያብሎስ ተላላኪዎች መሆናችሁን የሚያሳይ ነው በሏቸው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርንና ማደሪያውን እናቱ ድንግል ማርያምን እንዲሁም ቅዱሳኑን ቤተ ክርስቲያንንም መስቀልንም ጭምር የሚሳደብ ዲያብሎስ ነውና፡፡
·         ከላይ ያሉትን ነጥቦች ካልተቀበሏችሁ መዝ 30÷18 “በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይኹኑ” ይላል በሏቸው፡፡
·         አሁንም ከላይ ያሉትን ሁሉ ካልተቀበሏችሁ 2ኛ ጢሞ 3÷5 “የአምልኮት መልክ አላቸው ኀይሉን ግን ክደዋል ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” ይላልና ቅዱስ ጳውሎስ ከእነዚህ በሃይማኖት ስም ከሚያጭበረብሩ ሰዎች መራቅ ያስፈልገናል፡፡

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

Wednesday, April 13, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል ሦስት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 5/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 12 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  13ኛ ነጥብ፡- ጾምን በተመለከተ፡፡
·         ጾም አያስፈልግም (አይጠቅምም) ለሚሉ፡- ኢዩ 2÷12 “አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ይላልሳ ጾም ካላስፈለገ ታዲያ እግዚአብሔር ለምን እንዲህ ሊለን ቻለ በሏቸው፡፡
·         በክፉ በሽታ የሚሰቃይ አንድን ህጻን ወደ ደቀመዛሙርቱ አመጡ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም፡፡ ከዛም ኢየሱስ ወደ እኔ አምጡት አላቸውና እርሱ ገሰጸው ጋኔኑም ከብላቴናው ላይ ወጣ፡፡ ከዚያን ሰዓት ጀምሮ ብላቴናው ተፈወሰ ይላል፡፡ ከዚያም ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ተጠግተው እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለምን ነው? ብለው ጠየቁት ኢየሱስም ስለእምነታችሁ ማነስ ነው እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ (ፍጹም እምነት ቢኖራችሁ ማለት ነው) ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል የሚሳናችሁ ነገር የለም ካላቸው በኋላ የጸሎትንና የጾምን ጥቅም ሲያስረዳ በማቴ 17÷21 ላይ “ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጾም በቀር አይወጣም አላቸው” ይላል፡፡ ታዲያ ጾም የማይጠቅም ቢሆን ኖሮ  ለምን እንዲህ ሊላቸው ይችላል በሏቸው፡፡ ይህን ሁሉ የማይሰሙ ከሆኑ ግን በቅዱስ ጳውሎስ ጥቅስ እንገስጻቸውና እንሰነባበታቸው፡፡
·          ጥቅሱ ይህ ነው ፊሊ 3÷19-20 “መጨረሻቸው ጥፋት ነው ሆዳቸው አምላካቸው ነው ክብራቸውም በነውራቸው ነው ዐሳባቸውም ምድራዊ ነው እኛ አገራችን በሰማይ ነውና…” እንበላቸው፡፡
·         ኢየሱስ ጾሞልኛል ለሚሉ፡- በማቴ 26÷20 “በመሸ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር በማዕድ ተቀመጠ” ይላልና ኢየሱስ ስለበላልኝ አልበላም ማለት አለባችሁ በሏቸው፡፡
·         ጾም በአዋጅ መሆን የለበትም ለሚሉ፡- በመጀመሪያ ይህንን ጥያቄ ለማቅረብ መጾም ያስፈልጋል፡፡ የማይጾም ሰው በአዋጅ ሆነም፤ ሰው በተመቸው ጊዜ ሆነም ጾም አይመለከተውምና ምንም ጥያቄ ሊያነሣ አይችልም፡፡ ግን ምን ይላሉ መሰላችሁ “እኛም እኮ እንጾማለን! ግን በአዋጅ ከዚህ እስከዚህ ጾም ነው በዚህን ቀን ደግሞ አይጾምም ተብሎ ጾም መታወጅ የለበትም!” ይላሉ፡፡ እሽ ኢዩ 2÷15 ላይ “በጸዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ ጉባኤውንም ዐውጁ” ይላልሳ በሏቸው፡፡
v  14ኛ ነጥብ፡- ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ፡፡
·         ኢየሱስ አልተሰበከም ለሚሉ፡- ኢየሱስ ማን እንደሆነ ጠንቅቃ የምታስተምር በኢትዮጵያ ብቸኛዋ ቤተክርስቲያን  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴዋ፣ በማኅሌቷ፣ በሰዓታቷ፣ በምልክእ፣በድርሳኗ፣ በተአምራት መጻሕፍቷ በአጠቃላይ ከጉልላቷ እስከ ታች መሠረቷ ድረስ ኢየሱስን ስትሰብክ የኖረች እየሰበከች ያለች ወደፊትም የምትሰብክ እመቤት ናት፡፡ ተሐድሶ መናፍቃኑም እዚህ ላይ ያነሣሉ “በቤተ ክርስቲያን ኢየሱስን መስበክ መናፍቅ ያስብላል” ይላሉ፡፡ ይህን የሚያስብለው “ኢየሱስ አማላጅ ነው” ብሎ የሰበከ ሰው ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ብርጭቆ በተሰበረብን ቁጥር “በኢየሱስ ሥም!” ብሎ መጮኽ ኢየሱስን መስበክ ከመሰላቸው እኛ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥም” ነው የምንል ልጅ ኢየሱስን ስንጠራ አባቱ አብን እና ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስንም ጨምረን ነው በሏቸው፡፡ እውነተኛውን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስበክ አንደኛዋ፤ የመጀመሪያዋ፤ ግንባር ቀደሟ ቤተ ክርስቲያን የእኛዋ ናት፡፡ ተአምረ ኢየሱስ፤ መልክአ ኢየሱስ፣ መልክአ መድኃኔ ዓለም ስንል የማይቀበሉን ሰዎች ናቸው እኮ ኢየሱስ አልተሰበከም ብለው የሚጮኹት አይገርምም!!!!! መልክአ መድኃኔ ዓለም መጨረሻው ላይ “የቅዱስ አብ አካላዊ ቃል ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ኢየሱስ ሆይ ለአንተ ክብር ምስጋና ይገባል ለዘላለሙ አሜን” ይላል፡፡ እኛስ ጸሎታችንም ስብከታችንም ትምህርታችንም መሠረታችንም ጉልላታችንም ኢየሱስ ነው በሏቸው፡፡
v  15ኛ ነጥብ፡- ስግደትን በተመለከተ፡፡
·         ለእመቤታችን ስግደት አይገባም ለሚሉ፡- እመቤታችን መልእልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ናት፡፡ እመቤታችን አምላክን በድንግልና ጸንሶ በድንግልና የመውለድ ለማንም ያልተደረገ ልዩ ጸጋ የተሰጣት ናትና የጸጋ ስግደት እንሰግድላታለን፡፡ የምንሰግድላት ግን አምላካችን ብለን ሳይሆን የአምላክ እናት እናታችን ብለን ነው፡፡ መዝ 131÷7 ላይ “ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን” ይላል ዳዊት፡፡ እመቤታችን ደግሞ እግሮቹ ከቆሙበት ሥፍራ በላይ በማኅጸኗ ተሸክማዋለችና እንሰግድላታለን በሏቸው፡፡
·         ለመላእክት ስግደት አይገባም ለሚሉ፡- ለቅዱሳን መላእክት የሚሰገደው ስግደት የአክብሮት ስግደት ነው፡፡ ዘፍ 19÷1 ላይ “ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር፡፡ ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ” ይላል ታዲያ እናንተ ከሎጥ ትበልጣላችሁን በሏቸው፡፡
·         ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ለሚሉ፡- ለቅዱሳን የሚሰገደው ስግደት የአክብሮት ስግደት ነው፡፡ ዳን 2÷46 ላይ “የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነጾር በግንባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት” ይላል፡፡ ታዲያ ለቅዱሳን ስግደት ባይገባ ኖሮ ያውም ትእቢተኛ የነበረው ንጉሥ ናቡከደነጾር ለነቢዩ ዳንኤል እንዴት ሊሰግድለት ቻለ በሏቸው፡፡
ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

Monday, April 11, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል ሁለት


© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 3/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  6ኛ ነጥብ፡- መስቀልን በተመለከተ።
·         መስቀልን አባት እንደተገደለበት ሽጉጥ ለሚቆጥሩ፡- 1ኛ ቆሮ 1፥18 ላይ "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው" ይላልና ለእኛስ ሽጉጥ ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃይል ነው በሏቸው። ይህንን የሚሉ ሰዎችም ለሚጠፉት ሞኝነት ነው የተባለላቸው ሰዎች ናቸው።
·         መስቀል አያስፈልግም ለሚሉ፡- ገላ6፥14 ላይ "ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ይላልሳ በሏቸው። በማቴ 16፥24 ላይ "እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ" ያለው ማነው በሏቸው። ይህን የተናገረ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና መስቀል ካላስፈለገ ለምን ይህን ተናገረ በሏቸው።
v  7ኛ ነጥብ፡- እጣንን በተመለከተ።
·         እጣን መጠቀምን ለሚነቅፉ:- ራእ 8፥3 ላይ "ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ እጣን ተሰጠው። የእጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ" ይልባችኋልሳ በሏቸው። ዳግመኛም በማቴ 3፥11 ላይ "ወደ ቤትም ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት ወድቀውም ሰገዱለት ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና እጣን ከርቤም አቀረቡለት" ይላል ታዲያ እጣን አስፈላጊ ካልሆነ የጥበብ ሰዎች ያቀረቡለትን የእጣን እጅ መንሻ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተቀበላቸው በሏቸው።
v  8ኛ ነጥብ፡- ንስሐ መግባትን በተመለከተ።
·         ንስሐ ቀጥታ በአምላክ ፊት የሚገባ እንጅ ለካህናት በመንገር አይደለም ለሚሉ:- ማቴ 8፥4፤ ማር 1፥44 ላይ "ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መብዐ አቅርብ አለው" ንስሐ በቀጥታ ለእርሱ የሚነገር ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ለምን ወደ ካህናት ላካቸው በሏቸው። እንዲሁም ሉቃ 17፥14 ላይስ "ሂዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው" ይላል ለምን እንዲህ አላቸው በሏቸው። ካህናት አላስፈላጊ ቢሆኑ ኖሮ ዮሐ 21፥15-18 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ግልገሎቸን አሰማራ ብሎ ልጆችን ሕጻናትን፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ ብሎ ወጣቶችን፣ በጎቼን አሰማራ ብሎ ሽማግሌዎችን እብዲጠብቅ በእረኝነት ለምን አሰማራው በሏቸው። 
v  9ኛ ነጥብ፡- ጸበልን በተመለከተ።
·         ጸበል አያድንም ለሚሉ። ዘፍ 1፥2 ላይ "የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር " ይላልሳ በሏቸው። ዮሐ5፥4 ላይ "ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር" ይልባችኋልሳ በሏቸው።
v  10ኛ ነጥብ፡- ጽላትን በተመለከተ።
·         ጽላትን ጣዖት ነው ለሚሉ፡- ዘጸ 31፥18 ላይ "እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው" ይላል ታዲያ ታቦት እንደ ጣዖት ከተቆጠረ እግዚአብሔር ለሙሴ እንዴት ጣዖት ሊሰጠው ይችላል በሏቸው። ነገር ግን አሁንም አይቆሙም እግዚአብሔር የሰጠው ጽላትማ በዘፍ 32፥19 ላይ ተሰብሮ ቀርቷል እኮ ይሏችኋል ነገር ግን ይህም የመጨረሻ መልስ አለው። ወደ ዘፍ 34፥1 ላይ ወርዳችሁ " ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ በሰበርኸቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ" ብሎት እንደገና ዘፍ 37፥1 ላይ አሰርቶታል በሏቸው።
v  11ኛ ነጥብ፡- ትርጉምን በተመለከተ፡፡
·         የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደወረደ እንጅ ትርጉም አያስፈልገውም ለሚሉ፡- ይህን ርእስ የደገምሁት የምጨምረው ነገር ባገኝ ጊዜ ነው። ገላ 6፥14 ላይ "ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ይላል። ጳውሎስ ይህን መልእክት ከመጻፉ በፊት ወይም ሲጽፍ በጌታችን መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነበር ማለት ነውን በሏቸው።
·         ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ 21፥15-18 ላይ ጴጥሮስን ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና በጎቼን አሰማራ ያለው የበግ እረኛ እያደረገው ነውን በሏቸው። ግልገል፣ ጠቦት እና በግ ያላቸው እነማንን ነው ብላችሁ አቁሟቸው። 
·         ማቴ 16፥23 ላይ ኢየሱስ ዞር ብሎ ጴጥሮስን "ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጅ የእግዚአብሔርን አታስብምና እንቅፋት ሆነህብኛል አለው" ይላል። ታዲያ ትርጉም ካላስፈለገ ቅዱስ ጴጥሮስን ከሰውነት አውጥተን ሰይጣን ነው ልንል ነውን በሏቸው። ጴጥሮስማ ሰው ነው እንጅ ሰይጣን አይደለም ካሉ ደግሞ ታዲያ ኢየሱስ ለምን እንዲህ አለ ወይስ ደግሞ ኢየሱስን ይዋሻል ልትሉን ነው በሏቸው፡፡
v  12ኛ ነጥብ፡- እምነትን በተመለከተ።
·         እምነት የእናት የአባቴ አይባልም ለሚሉ:- ሲጀመር የፕሮቴስታንት እምነት ከአያት ከቅድመ አያቶቻችን የዘለለ እድሜ ስለሌለው የእናት የአባቴ እምነት ወይም እናቶቻችን እና አባቶቻችን እያልን ስንናገር ይነዳቸዋል ይበሳጫሉ። እኛ ግን የቀደመች እምነት ተዋሕዶ እንደሆነች አውቀን በዚች መንገድ ብቻ ድኅነት እንደምናገኝ አምነናል አውቀናልም። ስለዚህ ከዚህች ጠባብ የድኅነት መንገድ ወጥተን ወደ ሰፊው የጥፋት መንገድ አንገባም በሏቸው። ከዚያም ሃይማኖት ስንት ነው ብላችሁ ጠይቋቸው። ኤፌ 4፥4 ላይ "አንድ ሃይማኖት" ናት ይሏችኋል። ከዚህ የተለየ መልስ ከመለሱላችሁ ይህን ጥቅስ አንብቡላቸው። ይህን አንቀበልም ካሉም ሃይማኖት ከአንድ በላይ ነው የሚል ጥቅስ ተቀበሏቸው። ሃይማኖት አንድ መሆኑን ከተማመናችሁ ግን ታዲያ ያ አንድ ሃይማኖት ማነው? በሏቸው። እናንተ ግን የግድ ወደ ሃይማኖት የምስረታ ዘመን ማለፍ አለባችሁ። ከተዋሕዶ ሃይማኖት በፊት የነበረ ሃይማኖት ንገሩን በሏቸው። ምክንያቱም የእኛ እምነት የተመሠረተው የፕሮቴስታንትን እምነት ከመሠረተው ሉተር መፈጠር በፊት በፊት ሽህ ዘመናትን ቀድሞ ነውና። የእኛ እምነት የተጀመረው ገና የሥነ ፍጥረት መጀመሪያ በሆነችው ዕለት ነውና እንቀድማቸዋለን። 

·         ለእምነት ዕድሜ ምንም አይሰራም ለሚሉ፡- ኤር 6÷16 ላይ "በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ" ይላልና የትኛውም አይነት መንገድ ላይ ቆማችሁ ቢሆንም እንኳ የቀደመችውን የድኅነት መንገድ ማወቅ ያስፈልጋል። ማወቅ ብቻም ሳይሆን በዚያች መንገድ ልትጓዙባትም ግዴታ ነው በሏቸው። ይህን ማድረግ ግዴታ የሚሆነው ግን ለነፍስ ዕረፍት ለማግኘት ነው ለነፍሱ ዕረፍትን የማይፈልግ ሰው አይገደድም በሏቸው። ያች የቀደመችው መንገድ ተዋሕዶ ናት። ምክንያቱም ዛሬ እንደ አሸን ከፈላው የእምነት ድርጅት በፊት የእኛ እምነት ነበረችና የቀደመች መንገድ እንላታለን።

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻላል ለዛሬ ግን ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ እንመለከታለን። 
ይቀጥላል...


መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል አንድ

© መልካሙ በየነ
መጋቢት 30/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

መናፍቃን የተዋሕዶ ልጆችን ለማሳትና በልባቸውም ጥርጥርን ፈጥረው ኑፋቄያቸውን ለመርጨት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እስከአሁን ድረስ የተነሡትን መናፍቃን አባቶቻችን በትምህርታቸው ረትተው እምነታችንን ጠብቀው አቆይተውናል፡፡ በመጽሐፍ የመጡትን በመጽሐፍ በቃል የመጡትንም በቃል ተከራክረው በማሸነፍ በእምነታችን እንድንጸና ብሎም እንድንኮራ አድርገው ለዚህ ደረጃ አብቅተውናል፡፡ አሁን ላሉትና ወደፊትም ለሚፈጠሩት መናፍቃን እጅግ ብዙ መልሶችን ሰንቀውልን አልፈዋል፡፡ ስለዚህ እኛም የእነርሱን አብነት ተከትለን በየጊዜው እንደአሸን የሚፈሉብንን መናፍቃን መርታት ይኖርብናል፡፡

ኢያሱ በገባዖን ላይ ፀሐይን በኤሎንም ሸለቆ ላይ ጨረቃን ያቆመበትን ጥበብ ዛሬ መናፍቃንን ለማቆም ተጠቀምበት /ኢያ10÷13/፡፡ ኢያሱን መሆን ካልቻልክ ጠላቶችህን ለማጥፋት በምታደርገው ጦርነት መካከል መምሸቱና ፀሐይ መጥለቋ በዚህም የተነሣ ጨለማ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ጨለማ መካከል ደግሞ ጠላት ሊመታህ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንተም ሆነ ጠላትህ በጨለማ ውስጥ ናችሁና፡፡ ስለዚህ ብርሃንን ለማቆየት ፀሐይን ባለችበት ማቆም ያስፈልግሃል፡፡ ይችን ፀሐይ ለማቆም ደግሞ ኢያሱን መሆን አልያም ከኢያሱ ጎን መቆም ግድ ይላል፡፡ አሁን እኔም ለመጻፍ የተገደድሁት መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ እንደኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ ለማቆም የሚያስችሉ ነጥቦችን ለማንሣት ነው፡፡ መናፍቃን መሠረት አልባዎች፣ ላይ ላዩን ብቻ የሚጋልቡ ናቸው፡፡ ይህን የምለው ዝም ብየ ከምድር ተነሥቼ ወይም ጥላቻ ስላለኝ አይደለም፡፡ እኔ ብዙ መናፍቃን የፌስቡክ ጓደኞች አሉኝ እነርሱ ብዙ አሳውቀውኛል፡፡ የስህተታቸው መነሻ ምን እንደሆነ ፍንትው አድርገው አሳይተውኛል፡፡ ስለዚህ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ስንከራከራቸው እንደገባዖኗ ፀሐይ አቁሞ ለማስቀረት የሚያስችል ነገር ማወቅ አለብን፡፡ እነዚህ ነጥቦች የሚገኙት እነርሱ በያዙት 66 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡
·         1ኛ ነጥብ፡- የሰው ዘርን በተመለከተ፡፡
·         መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ላይ እግዚአብሔር አዳምን በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረው ይናገራል፡፡ ከዚያም ከግራ ጎኑ ደግሞ ሔዋንን እንደፈጠረለት ይናገራል፡፡ ከዚያ በኋላ አዳም ሔዋንን አወቃትና ቃየን ተወለደ፡፡ በመቀጠልም አቤል ተወለደ፡፡ ከዚያም ቃየን አቤልን ገደለው አዳምም ሔዋንን አወቃትና ሴት ተወለደ፡፡ ከዚያ በኋላ ሴት ሄኖስ የተባለ ልጅን ወለደ፡፡ ሄኖስ የአዳም የልጅልጅ የሴት ልጅ ነው፡፡ ነገር ግን ሴት ሄኖስን ማን ከምትባል ሚስቱ ነው የወለደው?
·         2ኛ ነጥብ፡- አማላጅነትን በተመለከተ፡፡
·         ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ አያማልዱም ለሚሉ፡- 2ኛ ነገ13÷21 “ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ” ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ በቃልኪዳናቸው የማይጠብቁ ከሆነ የኤልሳዕ አጥንት እንዴት ሙት ሊያስነሣ ቻለ?
·         ኢየሱስን አማልጅ ነው ለሚሉ፡-  ሮሜ8÷26  ላይ “እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል” ይላል:: ኤር7÷25  ላይ ደግሞ “አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር” ይላል:: ታዲያ ኢየሱስ ብቻ ለምን አማላጅ ይባላል በሏቸው፡፡
·         ኢየሱስ አይፈርድም ለሚሉ፡- ሮሜ 14÷10 ላይ  “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና” ይላልሳ በሏቸው፡፡
·         3ኛ ነጥብ፡- ድንግል ማርያምን በተመለከተ፡፡
·         አልተነሣችም አላረገችም ብለው ለሚከራከሩ ሰዎች፡- ድንግል ማርያም እንደዐረፈች ይናገራሉ ነገር ግን አልተነሣችም አላረገችም ብለው ይሞግታሉ፡፡ ተነሥታለች ዐርጋለች ስትሏቸው ደግሞ ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካላሳያችሁን እንሞታለን ይላሉ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች አጭሩ መልስ ድንግል ማርያም ዐርፋለች ካላችሁን ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱሳችሁ ውስጥ ጥቅስ አሳዩን የሚል ነው፡፡ እነርሱ ዐርፋለች የሚል ጥቅስ ሲያሳዩን እኛ ደግሞ በዚህን ቀን ተነሥታለች በዚህን ቀን ዐርጋለች እንላቸዋለን፡፡ ግን ማረፏን የሚያሳይ ጥቅስ ከየትም ማምጣት አይችሉም፡፡
·         ድንግል አታማልድም ለሚሉ ሰዎች፡- ዮሐ 2 ላይ በቃና ዘገሊላው ሰርግ ቤት ውኃውን ወይን ያስደረገችው በምን ምክንያት ነው በሏቸው?
·         ዘላለማዊ ድንግልናዋን ለሚጠራጠሩ፡- እነዚህ ሰዎች የሚጠቅሱት የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም /ማቴ1÷25/ የሚለውን ጥቅስ ነው፡፡ የበኩር ልጇን ከወለደች በኋላ ዮሴፍ በግብር አውቋታል ብለው ለመሞገት ማለት ነው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች “…ሜልኮል እስከሞተችበት ቀን ድረስ  ልጅ አልወለደችም” 2ኛ ሳሙ6÷23 ይላል፡፡ ታዲያ ሜልኮል ከሞተች በኋላ ልጅ ወልዳለችን በሏቸው፡፡ በተጨማሪም “ማዎቅ” የሚለው ቃል በግብር መተዋወቅ ብቻ ነው ተብሎ ከተተረጎመ “ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ስለነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደሆነ አላወቀም” ዮሐ5÷14 ይላል፡፡ታዲያ አወቃው ቢል ኖሮ መጻጉዕ ኢየሱስን በግብር አወቀው ልትሉን ነውን በሏቸው፡፡
·         4ኛ ነጥብ፡- ትውፊትን በተመለከተ፡፡
·         ትውፊት አያስፈልግም ለሚሉ፡- ትውፊት ማለት በቃል አንዱ ለአንዱ በቃል እያስተማረው በቅብብሎሽ የመጣ መንፈሳዊ ትምህርት ነው፡፡ ይህ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም ስለዚህም አንቀበለውም ብለው ሲሞግቷችሁ፡፡ 2ኛ ዮሐ 1፥12 ላይ “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላል፡፡ እንዲሁም በ 3ኛ ዮሐ1÷13 ላይም “ልጽፈው የምፈልገው ብዙ ነገር ነበር ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፈው አልወድም” ይላል:: ዮሐ 21፥25 ላይ እንዲህ ይላል “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ ኹሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ይላል፡፡ ታዲያ ዮሐንስ በቃል ያስተማረውን ትምህርት መቀበል አይገባምን በሏቸው፡፡ በተጨማሪም “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ” እያለ ዮሐንስ ተአምረ ኢየሱስ ስንል ለምን አትቀበሉንም በሏቸው፡፡
·         5ኛ ነጥብ፡- ትርጉምን በተመለከተ፡፡
·         የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደወረደ እንጅ ትርጉም አያስፈልገውም ለሚሉ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትርጉም ካላስፈለገው፡፡ የጌታ ስቅለት የተከናወነው በስንት ሰዓት እንደሆነ ጠይቋቸው፡፡ በስድስት ሰዓት ነው ከሏችሁ ማርቆስ ወንጌል 15÷25 ላይ በሦስት ሰዓት ተሰቀለ ይላልሳ በሏቸው፡፡ በሦስት ሰዓት ተሰቀለ ካሏችሁ ደግሞ ማቴዎስ ወንጌል 26÷45 ላይ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ ይላልሳ በሏቸው፡፡ እነዚህን እንዴት ታስታርቋቸዋላችሁ በሏቸው፡፡
·         ሮሜ 10፥15 “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው” ይላል ታዲያ ትርጉም ካላስፈለገው እግራቸው ያወራል ይናገራል ልንል ነውን በሏቸው፡፡
መናፍቃንን በእነዚህ እና በሌሎችም በርካታ ጥቅሶች ኢያሱ እንዳቆማት የገባዖን ፀሐይ እንድታቆሟቸው እያልኩ ለአሁኑ እሰናበታችኋለሁ፡፡ በሌሎች የቤተክርስቲያናችን ጉዳዮች ዙሪያ ለሚያነሷቸው ሌሎች ጥያቄዎች በቀጣይ ክፍል በዚሁ መልኩ እመለሳለሁ፡፡
ይቀጥላል…