Thursday, April 14, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል አራት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 6/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 15 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  16 ኛ ነጥብ፡- ቅዱሳንን በተመለከተ፡፡
·         የድንግል ማርያምን ክብር ለሚያቃልሉ፡- ከመላእክት ወገን የሆነው ስሙ ገብርኤል የተባለው የመላእክት አለቃ ወደ ድንግል ማርያም ቀርቦ በትሕትና ሉቃ 1÷28 ላይ “ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት” ይላል፡፡ ታዲያ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ብሎ አክብሮ ደስ ይበልሽ ብሎ ያመሰገናትን ከሴቶች ሁሉ መካከል ልዩ ክብርት ልእልት የሆነቺውን እመቤት ለምን መናፍቃን ታቃልላላችሁ? ወይስ ደግሞ ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንበልጣለን ለማለት ነው የምትፈልጉት? በሏቸው፡፡
·         ሉቃ 1÷41-44 “ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅጸኗ ውስጥ ዘለለ፡፡ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፡፡ በታላቅ ድምጽም ጮኻ እንዲህ አለች፡- አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል፡፡ እነሆ የሰላምታሽን ድምጽ በዦሮዬ በመጣ ጊዜ ጽንሱ በማኅጸኔ በደስታ ዘሏልና” ይላል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ቅድም መልአኩ የተናገረውን ነገር ኤልሳቤጥም ደገመችው፡፡ በኤልሳቤጥም መንፈስ ብቻ ሳይል መንፈስ ቅዱስ ሞላባት አለ፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ በኤልሳቤጥ የሞላባት መቼ ነው? የእመቤታችንን ሰላምታ በሰማቺ ጊዜ አይደለምን? በጣም የሚገርመው ግን ገና ያልተወለደው በማኅጸን ያለው ዮሐንስ በደስታ ያዘለለው ምሥጢር ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ታዲያ ገና ያልተወለደው ዮሐንስ በማኅጸን ሳለ ሰላምታዋ አስደስቶት በደስታ ከዘለለ ዛሬ ከማኅጸን የወጣን ሰዎች ምኑ ነው ደስታዋ አላዘልለን ያለ በሏቸው፡፡ በዕድሜ የምትበልጣት  አክስቷ ኤልሳቤጥ አክብራ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? ያለቻትን ድንግል ማርያም መናፍቃን ለምን ታቃልላላችሁ በሏቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ብታከብሯት ክብሩ ለራሳችሁ ነው፤ ባታከብሯትም ውርደቱ ለራሳችሁ ነው ምክንያቱም እመቤታችንን ከአንስተ ዓለም መካከል ለእናትነት መርጦ ያከበራት አምላክ ነውና በሏቸው፡፡
·         ቅዱሳን የኢየሱስን ክብር ተሻምተዋል ለሚሉ፡- አልገባቸው ብሎ እንጅ የቅዱሳን ክብር የጸጋ ነው፤ የአምላክ ክብር ደግሞ የባሕርይ ነው፡፡ ቅዱሳንን ስላከበርን አምላክን አናከብርም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የቅዱሳን ክብራቸው ሌላ ነው የአምላክ ክብሩ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ የፀሐይ ክብሯ ከጨረቃ ክብር እንደሚለይ ሁሉ ማለት ነው፡፡ የጨረቃ መኖር ፀሐይን እንድትሸፈን አያደርጋትም፡፡ ምክንያቱም ፀሐይ ሌላ ናት ጨረቃ ደግሞ ሌላ ናት፡፡ የሚያገናኛቸው የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ ነው ያ ማለት ያለፀሐይ የጨረቃን ብርሃን አናይም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳንንም እንዲሁ ነው የምናከብራቸው፡፡ እነርሱን ስናከብር አምላክን አከበርን ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ቅድስናውን የሰጣቸው አምላክ ነውና፡፡ እንዲያውም ባይገርማችሁ ቅዱሳኑን የምናመሰግንበት ጊዜ አጥሮናል በሏቸው፡፡ መጽሐፍ ምን ይላል ዕብ 11÷32 “እንግዲህ ምን እላለሁ ስለጌዴዎንና ስለባርቅ ስለሶምሶንም ስለዮፍታሔም ስለዳዊትና ስለሳሙኤልም ስለነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ የእነዚህን ቅዱሳን ቅድስና ለመተረክ ቅዱስ ጳውሎስ ጊዜ አጠረው እንጅ ጊዜ ባያጥረው ኖሮ ባያችሁ ነበር፡፡ ከዚህ በታች ቅድስናቸውን ይዘረዝራል ቅዱሱ ሰው ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ “እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ ጽድቅን አደረጉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፡፡ የአንበሳዎችን አፍ ዘጉ የእሳትን ኃይል አጠፉ ከሰይፍ ስለት አመለጡ ከድካማቸው በረቱ በጦርነት ኃይለኛዎች ሆኑ የባዕድ ጭፍራዎችን አባረሩ፡፡ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከሞት ድረስ ተደበደቡ፡፡ ሌላዎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ ተፈተኑ በመጋዝ ተሰነጠቁ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ ኹሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፡፡ ዓለም አልተገባቻቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ” ይላል እስከ ቁጥር 38 ድረስ ስናነብብ፡፡ ታዲያ ስለነዚህ ቅዱሳን ሌሊት ከቀን ብንመሰክር ውለታቸውንና ቅድስናቸውን ተናግረን እንጨርሰዋለንን? ብፍጹም አንጨርሰውም፡፡ እኛ ምላጭ ሲቆርጠን ምን ያህል ነው የምንሰቀቀው? እነርሱ ግን በመጋዝ ተሰነጠቁ በእንጨት ላይ ተሰቀሉ እንደ ሽንኩርት ተከተፉ እንደጎመን ተቀረደዱ፡፡ ታዲያ ስለእነርሱ መናገር እንዴት ወንጀል ይሆናል? ስለዚህ ቅዱስ የሆነው አምላክ የቀደሳቸውን ቅዱሳን እስከዘላለም ድረስ ስናከብር እንኖራለን በሏቸው፡፡
·         ቅዱሳንን ለሚንቁ ሰነፎች፡- ሮሜ 8÷33 “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?” ይላል፡፡ ቅዱሳንን የመረጣቸው ደግሞ እግዚአብሔር እንጅ እኛ አይደለንም ስለዚህ ማንም ስለቅድስናቸው ሊከሳቸው አይችልም ከዲያብሎስ በቀር በሏቸው፡፡ ዲያብሎስ ግን የተሰጠውን የመክሰስ ስልጣን ከታች እንመለከተዋለን፡፡
·         ዕብ 13÷7 “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው” ይላል፡፡ የእኛ ዋኖቻችን የእግዚአብሔርንም ቃል የተናገሩን ያስተማሩን በመናገር ብቻ ሳይሆን በተግባር ተርጉመው የኖሩ ቅዱሳን ናቸው በሏቸው፡፡ ስለዚህም በእምነታቸው እንመስላቸው ዘንድ ይገባናል በሏቸው፡፡
·         ራእ13÷5-6 “ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ” ይላል፡፡ ይህ ስልጣን የተሰጠው ለዲያብሎስ ነው፡፡ ስለዚህ እናንተም ቅዱሳንን ስትንቁ የዲያብሎስ ተላላኪዎች መሆናችሁን የሚያሳይ ነው በሏቸው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርንና ማደሪያውን እናቱ ድንግል ማርያምን እንዲሁም ቅዱሳኑን ቤተ ክርስቲያንንም መስቀልንም ጭምር የሚሳደብ ዲያብሎስ ነውና፡፡
·         ከላይ ያሉትን ነጥቦች ካልተቀበሏችሁ መዝ 30÷18 “በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይኹኑ” ይላል በሏቸው፡፡
·         አሁንም ከላይ ያሉትን ሁሉ ካልተቀበሏችሁ 2ኛ ጢሞ 3÷5 “የአምልኮት መልክ አላቸው ኀይሉን ግን ክደዋል ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” ይላልና ቅዱስ ጳውሎስ ከእነዚህ በሃይማኖት ስም ከሚያጭበረብሩ ሰዎች መራቅ ያስፈልገናል፡፡

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment