Monday, April 18, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል ስድስት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 8/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 17 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  18 ነጥብ፡- ካህናትን በተመለከተ፡፡
·         ካህናት የሚሠሩት ኃጢአት ፕሮቴስታንት እንድሆን አደረገኝ ለሚሉ፡- የካህናትን ሰማያዊ ሥልጣን ንስሐን በተመለከተ ስንማር ዓይተናል፡፡ መናፍቃኑ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሲጠየቁእኔ ድሮ ኦርቶዶክስ ነበርሁ ነገር ግን ካህናት ሲቀድሱ ሲያስተምሩ ውለው አልባሌ ከሆነ ቦታ አገኛቸዋለሁ ጠንቋይ ቤት ሳይቀር ሲሄዱ አያለሁ፡፡ ከዚያ እነሱ አስተማሪዎች እንዲህ እያደረጉ ለምን ኦርቶዶክስ እሆናለሁ ብዬ ፕሮቴስታንት ሆንኩይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ፕሮቴስታንት መሆናቸው በራሱ ያሳፈራቸው አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ወደምንፍቅና የሄዱበት ዋናው ምክንያት የካህናቱ ችግር አይደለም ነገር ግን ቢያንስ እንዲህ ልበል ብለው ራሳቸውን ማጽናናት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው፡፡አያ ጅቦ ሳታመኸኝ ብላኝአለ አሉ፡፡ ፕሮቴስታንት የሆንኩ ጾሙ ከብዶኝ፣ መዝፈን አምሮኝ መጨፈር አስደስቶኝ ነው በሉን ዝም ብላችሁ እየተዋወቅን። ከዚህ ባለፈ ግን ስም በማጥፋት ላይ አትሰማሩ፡፡ ግን እንጅ ካህናት ጠንቋይ ላይ ሄዱ እራሳቸውም ጠንቋይ ሆኑ እንበል አልባሌ ቦታም እስከመስከር ድረስ ደርሰው ዓየናቸው እንበል... እና ቢሆንስ ምን ይመለከተናል፡፡ ያንን ሥራ የሚሠሩት ሰዎች እኮ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሚባል እምነት አይደሉም ሰዎች ናቸው እንጅ፡፡ ሰዎች ስህተት በሠሩ እምነቱ የሚወቀስበትና የሚናቅበት ነገር የለም፡፡ ከመላእክት መካከል ዲያብሎስ ካደ በዲያብሎስ መካድ የተነሣ ግን ቅዱሳን መላእክትን አማልዱን ማለታችንን አናቆምም፡፡ ምክንያቱም ዲያብሎስ ሌላ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ ሌላ ናቸውና በሏቸው፡፡ ከሐዋርያት መካከልም ይሁዳ አምላኩን ሸጦታል ነገር ግን በይሁዳ መሳት የተነሣ ቅዱስ ጴጥሮስን እና የቀሩትን ሐዋርያት አንንቃቸውም አናቃልላቸውም በሏቸው፡፡ በመጀመሪያ እንዲህ አድርገዋል የምንላቸው ካህናት ለምን ዓላማ ክህነቱን እንደተቀበሉም ማዎቅ አለብን፡፡ ካህኑ ስላጠፋ ደግሞ እምነትን ለመለወጥ መሮጥ አያስፈልግም ምክንያቱም የካህኑ ነፍስ ለራሱ ነው የእኛ ነፍስ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ እሱ በሥራው እኛም በሥራችን ነው የምንጠየቀው በሏቸው፡፡ በፍርድ ቀን ምን ሥራህ የት ነበርህ እንጅ ካህን እገሌ የት ነበረ ምን ሠራ ተብለን አንጠየቅም። እኛ የራሳችን ኃጢአት ይበቃናል በሰው ኃጢአት ምንም አይመለከተንም። በተጨማሪም የሚከተሉትን እንመልከት፡፡
·          ማቴ 7÷1-2 ላይእንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መሰፈሪያ ይሰፈርባችኋልይላል፡፡ ስለዚህ እናንተ እንደምትሉት ካህኑ ጠንቋይ ይሁንም ይስከር ይጨፍርም እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ ተብሏልና ልንፈርድ አይገባንም በሏቸው እኛ እነማን ሆነን ነው የሰውን ኃጢአት እየመዘገብን የምንወቅስ። እኛ ስንሠራው ኃጢአት የማይሆነው ነገር ሁሉ ካህናት ላይ ስናየው ኃጢአተኛ ናቸው እያልን እንድንወቅስ ማነው ሥልጣኑን የሰጠን? ራሳችንን በውል የማናውቅ ሰዎች ሆነን ካልሆነ በቀር ካህናት ላይ ዘለን ፊጥ ማለታችን ምን የሚሉት ቅዠት ነው፡፡ ይህንንም የማይቀበሉ ከሆነ፤
·         ማቴ 7÷3 ላይበወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ በዐይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትምይላል፡፡ ስለዚህ ከካህናት ዐይን ያለውን ጉድፍ አጥርታችሁ ከምትመለከቱ ይልቅ ከራሳችሁ ዐይን ላይ ያለውን ምሰሶ ተመልከቱ በሏቸው፡፡ እስከ ቁጥር 5 ስንመለከት እንዲህ ይላልወይም ወንድምህን ከዐይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ እነሆም በዐይንህ ምሰሶ አለ፡፡ አንተ ግብዝ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዐይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህይላል በግልጽ፡፡ ምናልባት ሌላ ምክንያት ካላችሁ እንጅ የካህናት ሥነምግባር እምነታችሁን እንድትለውጡ ሊያደርጋችሁ በፍጹም አይችልም በሏቸው፡፡ 
·         በዚህ ምክንያት ነው ብለው ከሞገቷችሁ ግን ስንቱ ዋልጌ ፓስተር ወደሚቆምርበት አዳራሽ የሚያስሄድ ጥፋት ካህናት ላይ አለ ብለን አናምንም በሏቸው።ፓስተር ዳዊትና ፓስተር ዘማሪ ተከስተየሰው ሚስት ሲያማግጡ ምነው ወደ እኛ አልተመለሳችሁም ነበር በሏቸው፡፡ ወይስ ደግሞ እስልምናን እንሞክረው ብላችሁ ወደዚያ ገባችሁ በሏቸው። የሚገርመው ነገር የእኛ ካህናት እንዲህ ሲያደርጉ ቢገኙ ተወግዘው ይለያሉ የእነርሱ ፓስተሮች ግን ዛሬም ድረስ ያው ፓስተር እየተባሉ የሰው ሚስት ሲያማግጡ ነው የሚገኙት፡፡ እንዲህ ዓይነት አንድን ሴት ለጋራ ለመጠቀም አስበው ሴቶችም ይህንኑ ሽተው የሄዱ ከሆነ ግን በርቱ በሏቸው ሌላ ምን ይባላል መቼስ፡፡ አንድ ቀን አምላክ እውነቱን ሲገልጥላቸው ማሰብ ይጀምሩ ይሆናል ማን ያውቃል የአምላክን ሥራ።
·         መናፍቃን ራሳቸውን እንደ ትለቅ ጻድቅ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ እነርሱ የሚሠሩት ሁሉ መልካም እና ጽድቅ ነው ሌላው ከእነርሱ እምነት ውጭ ያለ ሰው የሚሠራው ሁሉ ደግሞ መጥፎ እና ኃጢአት ነው፡፡ የእኛን አባቶች በገዳም ቢጫ ጋቢያቸውን ለብሰው አስኬማቸውን ደፍተው ዓለም አልገባቸው ብላ ለጸሎት በዱር በገደል ሲመለከቷቸው ይንቋቸዋልጽድቅ እንዲህ በመንከራተት የሚገኝ መስሏቸውእያሉ ይዘብታሉ ያፌዛሉ፡፡ በዚያ ጎን ካህኑ ኃጢአት ሲሠራ ዓይተን ፕሮቴስታንት ሆንን ይላሉ በዚህ ጎን ደግሞ በዱር በበረሃ በባዶ እግራቸው ለጸሎት ለስግደት የሚተጉ ባሕታውያንንና መነኮሳትን ሲንቁ ሲያንቋስሽሹ እንሰማለን፡፡ ታዲያ እናንተን ለመምሰል የግድ በየአዳራሹ በዝሙት አልጋ ላይ እንተኛላችሁ ወይስ ደግሞ እንጨፍርላችሁ በሏቸው፡፡ ማቴ 11÷18-19 ላይዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ እርሱም ጋኔን አለበት አሉት፡፡ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ እርሱም እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጪ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታልአለ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ የሰው ልጅ ምንም ብታደርግለት ሐሜቱን አያቆምም ሳይበላ የመጣውን ዮሐንስ ጋኔን አለበት አለ እየበላ የመጣውን ኢየሱስ ደግሞ በላተኛ ነው አሉት፡፡ አንድ ደስ የሚል አባባል አንብቤያለሁሰዎች በውኃ ላይ ስትራመድ ቢያዩህ ዋና ስለማይችል ነው ይሉሃልየሚል አባባል ነው፡፡ በጣም ትልቅ አባባል ነው፡፡ሰው ምንም ያህል ጻድቅ ቢሆን ከመታማት አያመልጥም። ካህናት ምንም ንጹሕ ቢሆኑ ከመታማት አይጠሩም ግድ ነው፡፡ ኢየሱስ አጋንንት ያደረባቸውን ሰዎች ከአጋንንት ቁራኝነት ሲያላቅቅ፣ ለምጻሞችን ሲያነጻ፣ ሽባዎችን ሲተረትር፣ ዕውራንን ሲያበራ፣ የሰላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛ መጻጉእን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ሲል፣ አልዓዛር አልዓዛር ከመቃብር ውጣ ብሎ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ሲያነሣ የእጁን ተአምራት የተመለከቱ ፈሪሳውያን ማቴ 12÷24 “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣምያሉት እውነታቸውን ነበርን በሏቸው፡፡ በእውነት ኢየሱስ ያንን ሁሉ ድንቅ ሥራ የሠራው በአጋንንት አለቃ በሆነው ብብዔል ዜቡል ነበርን? በሏቸው። ስለዚህ ሰው የፈለገውን ሊሠራ ይችላል እምነትን እንድንለውጥ ሊያደርግ የሚችል ምክንያት ግን የለውም ምክንያቱም እኛ የምናምነው አምላክን እንጅ ሰውን አይደለምና፡፡ በአገራችን በፖለቲካው ዓለም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ የሥልጣን ደረጃ አለው። እሱ ህገ መንግሥቱን ሲጥስ ብትመለከቱ ከዛሬ ጀምሬ ተቃዋሚ ድርጅት ላይ አባል እሆናለሁ የሚል ሰው አለን? የአፈጻጸም ችግር ነው ብለህ እንደምትቀመጥ ይታወቃል እኮ። ይህም የእናንተ ከንቱ ሃሳብ ከዚህ የዘለለ አይደለም በሏቸው።

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

ተጨማሪ ትምህርቶችን ለማግኘት http://melkamubeyene.blogspot.com ን ይጎብኙ፡፡

No comments:

Post a Comment