Monday, April 11, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል አንድ

© መልካሙ በየነ
መጋቢት 30/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

መናፍቃን የተዋሕዶ ልጆችን ለማሳትና በልባቸውም ጥርጥርን ፈጥረው ኑፋቄያቸውን ለመርጨት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እስከአሁን ድረስ የተነሡትን መናፍቃን አባቶቻችን በትምህርታቸው ረትተው እምነታችንን ጠብቀው አቆይተውናል፡፡ በመጽሐፍ የመጡትን በመጽሐፍ በቃል የመጡትንም በቃል ተከራክረው በማሸነፍ በእምነታችን እንድንጸና ብሎም እንድንኮራ አድርገው ለዚህ ደረጃ አብቅተውናል፡፡ አሁን ላሉትና ወደፊትም ለሚፈጠሩት መናፍቃን እጅግ ብዙ መልሶችን ሰንቀውልን አልፈዋል፡፡ ስለዚህ እኛም የእነርሱን አብነት ተከትለን በየጊዜው እንደአሸን የሚፈሉብንን መናፍቃን መርታት ይኖርብናል፡፡

ኢያሱ በገባዖን ላይ ፀሐይን በኤሎንም ሸለቆ ላይ ጨረቃን ያቆመበትን ጥበብ ዛሬ መናፍቃንን ለማቆም ተጠቀምበት /ኢያ10÷13/፡፡ ኢያሱን መሆን ካልቻልክ ጠላቶችህን ለማጥፋት በምታደርገው ጦርነት መካከል መምሸቱና ፀሐይ መጥለቋ በዚህም የተነሣ ጨለማ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ጨለማ መካከል ደግሞ ጠላት ሊመታህ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንተም ሆነ ጠላትህ በጨለማ ውስጥ ናችሁና፡፡ ስለዚህ ብርሃንን ለማቆየት ፀሐይን ባለችበት ማቆም ያስፈልግሃል፡፡ ይችን ፀሐይ ለማቆም ደግሞ ኢያሱን መሆን አልያም ከኢያሱ ጎን መቆም ግድ ይላል፡፡ አሁን እኔም ለመጻፍ የተገደድሁት መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ እንደኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ ለማቆም የሚያስችሉ ነጥቦችን ለማንሣት ነው፡፡ መናፍቃን መሠረት አልባዎች፣ ላይ ላዩን ብቻ የሚጋልቡ ናቸው፡፡ ይህን የምለው ዝም ብየ ከምድር ተነሥቼ ወይም ጥላቻ ስላለኝ አይደለም፡፡ እኔ ብዙ መናፍቃን የፌስቡክ ጓደኞች አሉኝ እነርሱ ብዙ አሳውቀውኛል፡፡ የስህተታቸው መነሻ ምን እንደሆነ ፍንትው አድርገው አሳይተውኛል፡፡ ስለዚህ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ስንከራከራቸው እንደገባዖኗ ፀሐይ አቁሞ ለማስቀረት የሚያስችል ነገር ማወቅ አለብን፡፡ እነዚህ ነጥቦች የሚገኙት እነርሱ በያዙት 66 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡
·         1ኛ ነጥብ፡- የሰው ዘርን በተመለከተ፡፡
·         መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ላይ እግዚአብሔር አዳምን በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረው ይናገራል፡፡ ከዚያም ከግራ ጎኑ ደግሞ ሔዋንን እንደፈጠረለት ይናገራል፡፡ ከዚያ በኋላ አዳም ሔዋንን አወቃትና ቃየን ተወለደ፡፡ በመቀጠልም አቤል ተወለደ፡፡ ከዚያም ቃየን አቤልን ገደለው አዳምም ሔዋንን አወቃትና ሴት ተወለደ፡፡ ከዚያ በኋላ ሴት ሄኖስ የተባለ ልጅን ወለደ፡፡ ሄኖስ የአዳም የልጅልጅ የሴት ልጅ ነው፡፡ ነገር ግን ሴት ሄኖስን ማን ከምትባል ሚስቱ ነው የወለደው?
·         2ኛ ነጥብ፡- አማላጅነትን በተመለከተ፡፡
·         ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ አያማልዱም ለሚሉ፡- 2ኛ ነገ13÷21 “ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ” ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ በቃልኪዳናቸው የማይጠብቁ ከሆነ የኤልሳዕ አጥንት እንዴት ሙት ሊያስነሣ ቻለ?
·         ኢየሱስን አማልጅ ነው ለሚሉ፡-  ሮሜ8÷26  ላይእንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናልይላል:: ኤር7÷25  ላይ ደግሞ “አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበርይላል:: ታዲያ ኢየሱስ ብቻ ለምን አማላጅ ይባላል በሏቸው፡፡
·         ኢየሱስ አይፈርድም ለሚሉ፡- ሮሜ 14÷10 ላይ  “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና” ይላልሳ በሏቸው፡፡
·         3ኛ ነጥብ፡- ድንግል ማርያምን በተመለከተ፡፡
·         አልተነሣችም አላረገችም ብለው ለሚከራከሩ ሰዎች፡- ድንግል ማርያም እንደዐረፈች ይናገራሉ ነገር ግን አልተነሣችም አላረገችም ብለው ይሞግታሉ፡፡ ተነሥታለች ዐርጋለች ስትሏቸው ደግሞ ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካላሳያችሁን እንሞታለን ይላሉ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች አጭሩ መልስ ድንግል ማርያም ዐርፋለች ካላችሁን ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱሳችሁ ውስጥ ጥቅስ አሳዩን የሚል ነው፡፡ እነርሱ ዐርፋለች የሚል ጥቅስ ሲያሳዩን እኛ ደግሞ በዚህን ቀን ተነሥታለች በዚህን ቀን ዐርጋለች እንላቸዋለን፡፡ ግን ማረፏን የሚያሳይ ጥቅስ ከየትም ማምጣት አይችሉም፡፡
·         ድንግል አታማልድም ለሚሉ ሰዎች፡- ዮሐ 2 ላይ በቃና ዘገሊላው ሰርግ ቤት ውኃውን ወይን ያስደረገችው በምን ምክንያት ነው በሏቸው?
·         ላለማዊ ድንግልናዋን ለሚጠራጠሩ፡- እነዚህ ሰዎች የሚጠቅሱት የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም /ማቴ1÷25/ የሚለውን ጥቅስ ነው፡፡ የበኩር ልጇን ከወለደች በኋላ ዮሴፍ በግብር አውቋታል ብለው ለመሞገት ማለት ነው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች “…ሜልኮል እስከሞተችበት ቀን ድረስ  ልጅ አልወለደችም” 2ኛ ሳሙ6÷23 ይላል፡፡ ታዲያ ሜልኮል ከሞተች በኋላ ልጅ ወልዳለችን በሏቸው፡፡ በተጨማሪም “ማዎቅ” የሚለው ቃል በግብር መተዋወቅ ብቻ ነው ተብሎ ከተተረጎመ “ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ስለነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደሆነ አላወቀም” ዮሐ5÷14 ይላል፡፡ታዲያ አወቃው ቢል ኖሮ መጻጉዕ ኢየሱስን በግብር አወቀው ልትሉን ነውን በሏቸው፡፡
·         4ኛ ነጥብ፡- ትውፊትን በተመለከተ፡፡
·         ትውፊት አያስፈልግም ለሚሉ፡- ትውፊት ማለት በቃል አንዱ ለአንዱ በቃል እያስተማረው በቅብብሎሽ የመጣ መንፈሳዊ ትምህርት ነው፡፡ ይህ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም ስለዚህም አንቀበለውም ብለው ሲሞግቷችሁ፡፡ 2ኛ ዮሐ 1፥12 ላይ “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላል፡፡ እንዲሁም በ 3ኛ ዮሐ1÷13 ላይም “ልጽፈው የምፈልገው ብዙ ነገር ነበር ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፈው አልወድም” ይላል:: ዮሐ 21፥25 ላይ እንዲህ ይላል “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ ኹሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ይላል፡፡ ታዲያ ዮሐንስ በቃል ያስተማረውን ትምህርት መቀበል አይገባምን በሏቸው፡፡ በተጨማሪም “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ” እያለ ዮሐንስ ተአምረ ኢየሱስ ስንል ለምን አትቀበሉንም በሏቸው፡፡
·         5ኛ ነጥብ፡- ትርጉምን በተመለከተ፡፡
·         የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደወረደ እንጅ ትርጉም አያስፈልገውም ለሚሉ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትርጉም ካላስፈለገው፡፡ የጌታ ስቅለት የተከናወነው በስንት ሰዓት እንደሆነ ጠይቋቸው፡፡ በስድስት ሰዓት ነው ከሏችሁ ማርቆስ ወንጌል 15÷25 ላይ በሦስት ሰዓት ተሰቀለ ይላልሳ በሏቸው፡፡ በሦስት ሰዓት ተሰቀለ ካሏችሁ ደግሞ ማቴዎስ ወንጌል 26÷45 ላይ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ ይላልሳ በሏቸው፡፡ እነዚህን እንዴት ታስታርቋቸዋላችሁ በሏቸው፡፡
·         ሮሜ 10፥15 “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው” ይላል ታዲያ ትርጉም ካላስፈለገው እግራቸው ያወራል ይናገራል ልንል ነውን በሏቸው፡፡
መናፍቃንን በእነዚህ እና በሌሎችም በርካታ ጥቅሶች ኢያሱ እንዳቆማት የገባዖን ፀሐይ እንድታቆሟቸው እያልኩ ለአሁኑ እሰናበታችኋለሁ፡፡ በሌሎች የቤተክርስቲያናችን ጉዳዮች ዙሪያ ለሚያነሷቸው ሌሎች ጥያቄዎች በቀጣይ ክፍል በዚሁ መልኩ እመለሳለሁ፡፡
ይቀጥላል…

1 comment:

  1. qall hiwot yasmalen bnfs bsiga ytebkelen amenn!!!!

    ReplyDelete