Friday, April 15, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል አምስት

© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 7/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ 16 ያህል የሚሆኑ ነጥቦችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ጋር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  17ኛ ነጥብ፡- ሥርዓትን በተመለከተ፡፡
·         ሥርዓት ማለት ደንብ አሰራር ማለት ነው:: ለማንኛውም ሥራ ሥርዓት ሊኖረው ያስፈልጋል:: እምነት ውስጥ ያለው መታመን በዘፈቀደ ሳይሆን በሥርዓት መሆን አለበት:: አንድ እምነት ሥርዓት ካለው ብቻ ነው እምነት ሊባል የሚችለው:: ሥርዓት አያስፈልግም ብለው የሚከራከሩን መናፍቃን እኮ እነርሱ እንደፈለጉ ለመሆን ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 10÷23  “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” ብሏል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ እንደፈለገው ለመሆን የሚፈልግ ሰው “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ብቻ የምትለውን ጥቅስ እንዳነበበ መጽሐፉን ይዘጋዋል፡፡ ቀጥሎ ግን ምን ይል ነበር  “ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” ስለዚህ ሁሉ ቢፈቀድልንም ሁሉ የሚጠቅመን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሥርዓትንም እየነገረን ነው ያለው፡፡ የተፈቀደውን ሁሉ አትሥሩ የሚጠቅመውን መርምሩ እያለን እኮ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ሁሉ ቢፈቀድልንም መብላት፣ መጠጣት፣ መስከር፣ መጨፈር፣ አምላክን መካድ ከዚህም ሌላውን ሁሉ ነገር ማድረግ የራሳችን ነጻ ፈቃድ ቢሆንም ይህ ሁሉ ግን አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ በሥርዓት ተመርተን የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው መለየትና የሚጠቅመውን ብቻ መምረጥና መያዝ ይገባናል በሏቸው፡፡
·         ሥርዓትን ለሚንቁ (የቤተ ክርስቲያንን)፡- ሥርዓትን የሚንቁ ሰዎች በሰፊው የጥፋት መንገድ መሄድ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ጠባቡ የድኅነት መንገድ ሥርዓት አለው ሰፊው የጥፋት መንገድ ግን ሥርዓት የለውም፡፡ ማቴ 7÷13-14 ላይ “በጠበበው ደጅ ግቡ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና ወደርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ይላል፡፡ ሰፊው ደጅ ብዙዎች የሚገቡበት ሥርዓት የሌለውና ሥርዓትን የሚንቁ ሰዎች የሚጓዙበት መንገድ የሚገቡበት በር ነው፡፡ በዚህ በር መግባት የሚሹ ሰዎች ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት አይፈልጉም፡፡ መብላት፣ መጠጣት፣ መዳራት የሚፈልጉ ሰዎች በዚህ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ ሰፊዋ በር ኦሪት ናት በኦሪት ጥርስ ላወለቀ ጥርሱ እንዲወልቅ ዓይን ላጠፋ ዓይኑ እንዲጠፋ ታዝዛለችና፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ መጓዝ የሚሹ ሰዎች ትሕትናን ገንዘብ ያላደረጉ፣ በትዕቢት የተነፉ፣ በጉልበታቸው የሚመኩ ናቸው፡፡ አንድም ሰፊው መንገድ ፈቃደ ሥጋ ነው፡፡ ፈቃደ ሥጋን ለመፈጸም የሚፈልጉ ሰዎች እምነትን መከታ አድርገው አንድ ጥቅስ ብቻ ይዘው ሃሌ ሉያ እያሉ መጮኽን ገንዘባቸው አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሥጋቸው ብቻ የሚሮጡ ናቸውና ሥርዓትን አይወዱም እንደፈለጉ መሆንን ይፈልጋሉ፡፡ ጠባቡ መንገድ ግን ወንጌልና ፈቃደ ነፍስ ነው፡፡ ወንጌል ድሃን ጹም ባለጸጋንም መጽውት የምትል ግራህን ለሚመታህ ቀኝህን ስጥ የምትል አንድ ምእራፍ ሂድ ብሎ ለሚያስገድድህ ሁለት ምእራፍ ሂድለት የምትል ጠባብ ደጅ ጠባብ መንገድ ናት፡፡ ስትጾም እንዲህ ጹም ስትጸልይ እንዲህ ጸልይ ብላ ሥርዓት የምታስተምር ናትና ጠባብ ደጅ ናት፡፡ ፈቃደ ነፍስም እንዲሁ ልብላ ሳይሆን ልጹም፣ ልስረቅ ሳይሆን ልመጽውት የምትል ናትና ጠባብ ደጅ ናት፡፡ ስለዚህ ወደ ጥፋት በሚወስደው የምንፍቅና ሰፊ መንገድ አንሄድም በሏቸው፡፡ ሥርዓት የከበደው ሰው መጀመሪያም ከእኛ ያልሆነ ሰው ስሙን ብቻ የያዘ “ክርስቲያን ነኝ” ብቻ በማለት ወደ ሰፊው መንገድ ሊያስገባን ይሻልና አትስሙት፡፡ በሰፊው መንገድ ብዙዎች መጓዝ ይሻሉ እንደ ሥጋውያን ስናስበው ከመጾም መብላት ይሻላል፤ ከመስጠትም መቀበል ይበልጣል፡፡ እንደ ሥጋውያን ስናስብ ቆሞ ከማስቀደስ አልጋ ላይ ተኝቶ ሙዚቃ መስማት ይበልጣል፤ ቆሞ ውዳሴ ማርያምን ከመጸለይ ይልቅ ተጋድሞ ማርፈድ ይበልጣል፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊ ዓይን ስንመለከተው ይህ ሁሉ አላፊ ጠፊ ነው ሁሉም ያልፋልና ለነፍስ ማሰብን እንመርጣለን፡፡ ለዚህም የምንበላው ነገር እያለን አንበላም ብለን እጾማለን፣ ገንዘብን ለራሳችን ችግር መፍቻ ማዋል ስንችል የራሳችንን ትተን ለድሃ እንመጸውታለን ጠባብ በር ማለት ይህ ነው፡፡ በዚህ ጠባብ በር እንገባለን በዚህም ጠባብ መንገድ እንጓዛለን ምክንያቱም ጥቂቶች ብቻ የሚጓዙበትን መንገድ መርጠናልና በሏቸው፡፡
·         1ኛ ቆሮ 14÷40 “ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሥርዓት የሌለበት እምነት እኮ አንዱ ሲጸልይ ሌላው የሚዘምርበት ነው፡፡ አንዱ ሲዘምር ደግሞ ሌላው የሚስቅበት ነው፡፡ አንዱ ሲያስቀድስ ሌላው የሚዘፍንበት ነው፡፡ ታዲያ አጥር የሆነ ሥርዓት አያስፈልግምን በሏቸው፡፡ ምክንያቱም ሁሉ ነገር በአገባብና በሥርዓት ይሁን ብሎናልና ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ዝም ብሎ መንፈስ ተገለጠልኝ እያሉ መንፈራገጥ እና ልሳን ነው እያሉ ዝም ብሎ ማንም የማይሰማውን ቋንቋ መቀባጠር አይደለም ይህ ሁሉ በአገባብና በሥርዓት መሆን አለበትና በሏቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሲጥልና ሲያንፈራግጥ ዓይተንም አንብበንም ሰምተንም አናውቅም ሰይጣን ግን ሲጥል ሲያንፈራግጥ አረፋ ሲያስደፍቅ አይተናል አንብበናልም፡፡ ስለዚህም ከሥርዓታችን ወዴትም አንሄድም በሏቸው፡፡

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻል ነበር ነገር ግን ለዛሬው ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ ይዤላችሁ እመጣለሁ። አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ “ወልደ ማርያም” ነኝ፡፡
ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment