Monday, April 11, 2016

መናፍቃንን እንደ ገባዖን ፀሐይ--ክፍል ሁለት


© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 3/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ መናፍቃንን እንደገባዖን ፀሐይ የሚያቆሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎች ርእሶችን እንመለከታለን። መልካም ንባብ!!!
v  6ኛ ነጥብ፡- መስቀልን በተመለከተ።
·         መስቀልን አባት እንደተገደለበት ሽጉጥ ለሚቆጥሩ፡- 1ኛ ቆሮ 1፥18 ላይ "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው" ይላልና ለእኛስ ሽጉጥ ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃይል ነው በሏቸው። ይህንን የሚሉ ሰዎችም ለሚጠፉት ሞኝነት ነው የተባለላቸው ሰዎች ናቸው።
·         መስቀል አያስፈልግም ለሚሉ፡- ገላ6፥14 ላይ "ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ይላልሳ በሏቸው። በማቴ 16፥24 ላይ "እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ" ያለው ማነው በሏቸው። ይህን የተናገረ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና መስቀል ካላስፈለገ ለምን ይህን ተናገረ በሏቸው።
v  7ኛ ነጥብ፡- እጣንን በተመለከተ።
·         እጣን መጠቀምን ለሚነቅፉ:- ራእ 8፥3 ላይ "ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ እጣን ተሰጠው። የእጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ" ይልባችኋልሳ በሏቸው። ዳግመኛም በማቴ 3፥11 ላይ "ወደ ቤትም ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት ወድቀውም ሰገዱለት ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና እጣን ከርቤም አቀረቡለት" ይላል ታዲያ እጣን አስፈላጊ ካልሆነ የጥበብ ሰዎች ያቀረቡለትን የእጣን እጅ መንሻ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተቀበላቸው በሏቸው።
v  8ኛ ነጥብ፡- ንስሐ መግባትን በተመለከተ።
·         ንስሐ ቀጥታ በአምላክ ፊት የሚገባ እንጅ ለካህናት በመንገር አይደለም ለሚሉ:- ማቴ 8፥4፤ ማር 1፥44 ላይ "ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መብዐ አቅርብ አለው" ንስሐ በቀጥታ ለእርሱ የሚነገር ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ለምን ወደ ካህናት ላካቸው በሏቸው። እንዲሁም ሉቃ 17፥14 ላይስ "ሂዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው" ይላል ለምን እንዲህ አላቸው በሏቸው። ካህናት አላስፈላጊ ቢሆኑ ኖሮ ዮሐ 21፥15-18 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ግልገሎቸን አሰማራ ብሎ ልጆችን ሕጻናትን፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ ብሎ ወጣቶችን፣ በጎቼን አሰማራ ብሎ ሽማግሌዎችን እብዲጠብቅ በእረኝነት ለምን አሰማራው በሏቸው። 
v  9ኛ ነጥብ፡- ጸበልን በተመለከተ።
·         ጸበል አያድንም ለሚሉ። ዘፍ 1፥2 ላይ "የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር " ይላልሳ በሏቸው። ዮሐ5፥4 ላይ "ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር" ይልባችኋልሳ በሏቸው።
v  10ኛ ነጥብ፡- ጽላትን በተመለከተ።
·         ጽላትን ጣዖት ነው ለሚሉ፡- ዘጸ 31፥18 ላይ "እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው" ይላል ታዲያ ታቦት እንደ ጣዖት ከተቆጠረ እግዚአብሔር ለሙሴ እንዴት ጣዖት ሊሰጠው ይችላል በሏቸው። ነገር ግን አሁንም አይቆሙም እግዚአብሔር የሰጠው ጽላትማ በዘፍ 32፥19 ላይ ተሰብሮ ቀርቷል እኮ ይሏችኋል ነገር ግን ይህም የመጨረሻ መልስ አለው። ወደ ዘፍ 34፥1 ላይ ወርዳችሁ " ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ በሰበርኸቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ" ብሎት እንደገና ዘፍ 37፥1 ላይ አሰርቶታል በሏቸው።
v  11ኛ ነጥብ፡- ትርጉምን በተመለከተ፡፡
·         የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደወረደ እንጅ ትርጉም አያስፈልገውም ለሚሉ፡- ይህን ርእስ የደገምሁት የምጨምረው ነገር ባገኝ ጊዜ ነው። ገላ 6፥14 ላይ "ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ይላል። ጳውሎስ ይህን መልእክት ከመጻፉ በፊት ወይም ሲጽፍ በጌታችን መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነበር ማለት ነውን በሏቸው።
·         ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ 21፥15-18 ላይ ጴጥሮስን ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና በጎቼን አሰማራ ያለው የበግ እረኛ እያደረገው ነውን በሏቸው። ግልገል፣ ጠቦት እና በግ ያላቸው እነማንን ነው ብላችሁ አቁሟቸው። 
·         ማቴ 16፥23 ላይ ኢየሱስ ዞር ብሎ ጴጥሮስን "ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጅ የእግዚአብሔርን አታስብምና እንቅፋት ሆነህብኛል አለው" ይላል። ታዲያ ትርጉም ካላስፈለገ ቅዱስ ጴጥሮስን ከሰውነት አውጥተን ሰይጣን ነው ልንል ነውን በሏቸው። ጴጥሮስማ ሰው ነው እንጅ ሰይጣን አይደለም ካሉ ደግሞ ታዲያ ኢየሱስ ለምን እንዲህ አለ ወይስ ደግሞ ኢየሱስን ይዋሻል ልትሉን ነው በሏቸው፡፡
v  12ኛ ነጥብ፡- እምነትን በተመለከተ።
·         እምነት የእናት የአባቴ አይባልም ለሚሉ:- ሲጀመር የፕሮቴስታንት እምነት ከአያት ከቅድመ አያቶቻችን የዘለለ እድሜ ስለሌለው የእናት የአባቴ እምነት ወይም እናቶቻችን እና አባቶቻችን እያልን ስንናገር ይነዳቸዋል ይበሳጫሉ። እኛ ግን የቀደመች እምነት ተዋሕዶ እንደሆነች አውቀን በዚች መንገድ ብቻ ድኅነት እንደምናገኝ አምነናል አውቀናልም። ስለዚህ ከዚህች ጠባብ የድኅነት መንገድ ወጥተን ወደ ሰፊው የጥፋት መንገድ አንገባም በሏቸው። ከዚያም ሃይማኖት ስንት ነው ብላችሁ ጠይቋቸው። ኤፌ 4፥4 ላይ "አንድ ሃይማኖት" ናት ይሏችኋል። ከዚህ የተለየ መልስ ከመለሱላችሁ ይህን ጥቅስ አንብቡላቸው። ይህን አንቀበልም ካሉም ሃይማኖት ከአንድ በላይ ነው የሚል ጥቅስ ተቀበሏቸው። ሃይማኖት አንድ መሆኑን ከተማመናችሁ ግን ታዲያ ያ አንድ ሃይማኖት ማነው? በሏቸው። እናንተ ግን የግድ ወደ ሃይማኖት የምስረታ ዘመን ማለፍ አለባችሁ። ከተዋሕዶ ሃይማኖት በፊት የነበረ ሃይማኖት ንገሩን በሏቸው። ምክንያቱም የእኛ እምነት የተመሠረተው የፕሮቴስታንትን እምነት ከመሠረተው ሉተር መፈጠር በፊት በፊት ሽህ ዘመናትን ቀድሞ ነውና። የእኛ እምነት የተጀመረው ገና የሥነ ፍጥረት መጀመሪያ በሆነችው ዕለት ነውና እንቀድማቸዋለን። 

·         ለእምነት ዕድሜ ምንም አይሰራም ለሚሉ፡- ኤር 6÷16 ላይ "በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ" ይላልና የትኛውም አይነት መንገድ ላይ ቆማችሁ ቢሆንም እንኳ የቀደመችውን የድኅነት መንገድ ማወቅ ያስፈልጋል። ማወቅ ብቻም ሳይሆን በዚያች መንገድ ልትጓዙባትም ግዴታ ነው በሏቸው። ይህን ማድረግ ግዴታ የሚሆነው ግን ለነፍስ ዕረፍት ለማግኘት ነው ለነፍሱ ዕረፍትን የማይፈልግ ሰው አይገደድም በሏቸው። ያች የቀደመችው መንገድ ተዋሕዶ ናት። ምክንያቱም ዛሬ እንደ አሸን ከፈላው የእምነት ድርጅት በፊት የእኛ እምነት ነበረችና የቀደመች መንገድ እንላታለን።

ሎሎችን በርካታ ነገሮችን ማንሣት ይቻላል ለዛሬ ግን ለዚህ ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽም በቀጣይ ክፍል ሌሎችን በርካታ ነገሮችን በዚሁ አይነት አቀራረብ እንመለከታለን። 
ይቀጥላል...


No comments:

Post a Comment