Friday, August 25, 2017

አክሊሌን ተንጠልጥሎ አየሁት



© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 19/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================
ወይ የእኔ ነገር በጣም እገርማለሁ በጣም ሲበዛ! “መካን ይቄድሶ  ለሰብእ፤ ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” ሲሉ አባቶቸን እሰማቸዋለሁ ግን ብዙም አላስተዋልሁትም ነበር፡፡ አሁን ግን በራሴ ሕይወት ተረዳሁት ከልክም በላይ ተገነዘብኩት፡፡ “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” የተባለላቸው ግሩማን መካናት አሉ፡፡ ታላቁ ጻድቅ ሐዲስ ሐዋርያ ተብለው የሚታወቁት አባታችን ተክለ ሃይማኖት የተጋደሉበት ደብረ ሊባኖስን መጥቀስ እንችላለን፡፡ አባታችን አቡነ ሐብተ ማርያምም እንዲሁ የተጋደሉበትን ገዳማቸውን መመልከት እንችላለን፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን  ጸብአ አጋንንቱን ድምጸ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን በመታገስ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው በቅዱሱ ተጋድሎ ራሳቸውን ለአምላካቸው በመስጠት ቃልኪዳን የተቀበሉባቸውን ቦታዎች መመልከት እንችላለን፡፡ ሚዳ አቡነ መልከጼዴቅ ገዳምን ስንመለከትም ተመሳሳይ ታሪክ ነው ያለው፡፡ ይህ ቦታ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ መልካሙን ተጋድሎ የተጋደሉበት ቦታ በመሆኑ እርሳቸው ይህን ቦታ ቀድሰውታል ልዩ አድርገውታልም፡፡ በዚህ ቦታ የተቀበረ ሰው አጽሙ አይበሰብስም አይፈራርስም ስለዚህም “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” ቢሉ የቀና ንግግር ነው፡፡ ይህንን አነጋገራችንን ምናልባትም ሊቃወመን የሚችል ቢኖር ዲያብሎስ እና ተከታዮቹ እነ መናፍቃን እነ ተሐድሶ ናቸው፡፡ እኛ ግን ብዙ ተአምራትን እና ድንቆችን ተመልክተንባቸዋል፡፡

“መካን ይቄድሶ ለሰብእ” ይህ አነጋገር ደግሞ ለላይኛው ተቃራኒ የመሰለ የቀና ንግግር ነው፡፡ ቦታ ሰውን ያከብራል የሚል ትርጉም ያለው ነው፡፡ የላይኛው ግን ሰው ቦታን ያከብራል ይቀድሳል የሚል ትርጉም የያዘ ነበር፡፡ የአሁኑ አነጋገርም ቢሆን የቀና እና ለሁሉ በጎላ የተረዳ ቀጥተኛ ንግግር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ አነጋገር መሠረት እኛን ወደ ክብር ወደ በረከት ሊያሸጋግሩን የሚችሉ መካናት ወይም ቅዱሳን ቦታዎች አሉ ማለት ነው፡፡ ቤትህ ውስጥ መጸለይ እና ከቤተክርስቲያን ሂደህ መጸለይ በጸሎትህ ተመስጦ ውስጥ ተመሳሳይ ቦታ የላቸውም፡፡ ከአብያተ ክርስቲያናትም ልዩ የሆነ የቅዱሳን ቃል ኪዳን የተሰጠባቸው ፈጣሪ አብዝቶ የባረካቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እንደ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለው በአቡነ ተከስተ ብርሃን በአቡነ ተክለ አልፋ እና በሌሎችም እልፍ በሚሆኑ ቅዱሳን ጸሎት እና ተጋድሎ የተባረከው ቦታ እኛን ሊቀድስ የተሰጠን ቦታ ነው፡፡ እንደ ጣና ቂርቆስ የመሣሰሉት እንደ አክሱም ጽዮን እንደ ግሸን ደብረ ከርቤ እንደ ደብረ ሊባኖስ እንደ ደብረ ዳሞ እንደ ዝቋላ እንደ ዋልድባ ያሉ ቅዱሳን በሰፊው የተጋደሉባቸው ቦታዎች እኛን ይቀድሳሉ ያከብራሉ ከቃል ኪዳናቸው በረከት ያሳትፉናል፡፡ በአንድ አቡነ ዘበሰማያት የኃጢአታችን ክምር የሚናድባቸው የቃል ኪዳን ቦታዎች አሉ፡፡ ስለዚህም “መካን ይቄድሶ ለሰብእ ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” ማለት የተገባ ንግግር መሆኑን ተረዳሁት፡፡
 
በዚህም መሠረት በያለንበት አካባቢ ሁሉ ሰው ያከበራቸውም ቦታዎች ቦታ ያከበራቸውንም ሰዎች ልንመለከት እንችላለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በሰው ምክንያት የተረገሙ ቦታዎች አሉ፡፡ በቦታዎች ምክንያትም የተረገሙ ሰዎች አሉ፡፡ ቦታ የረገማቸው ሰዎች እምነታቸውን እንኳ በይፋ እስካለመረዳት ድረስ በጣዖት አምልኮ ውስጥ የተደበቁ ናቸው፡፡ በሰው ምክንያት የተረገሙ ቦታዎችም እንደሰዶም እና እንደ ገሞራ ይጠፋሉ፡፡ ሰው ለቦታ ቦታም ለሰው መልማትም ሆነ መጥፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዳችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን አምነን ተቀብለናል፡፡ በርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነንም ቢሆን ቦታው ይለያያል፡፡ እስልምና አለ ፕሮቴስታንት አለ ካቶሊክ አለ ሌላም ሌላም እምነት እንዲሁ አለ በቀደመው መናገር ነው እንጅ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ አሜሪካ ተወልደህ ቢሆን አረብ ተወልደህ ቢሆን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን አታገኛትም ነበር ብታገኛት እንኳ የአብርሃምን ፈጣሪን የመመርመር ልዩ ጥበብ ሲሰጥህ ብቻ ነው፡፡ እኔ ግን እላለሁ አምላኬ ሆይ ተመስገን ከአገራት ሁሉ መርጠህ በኢትዮጵያ እንደፈጠር ስለፈቀድክልኝ፡፡

ዛሬ በጣም አዝናለሁ፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶነታችንን የሚፈታተን ተግባር ሳይ እበሳጫለሁ፡፡ መቼ ይሆን በሰላም በተመስጦ ጸልየን ተገቢ ምላሽ አግኝተን እንዳንተ ፈቃድ የምንመላለስ እላለሁ፡፡ አስቀድሰን የማንቆርበበት ቦታ ንስሐ የምንገባበት ደግ ካህን ማግኘት ተቸግረናል፡፡ እኔ የማወራችሁ ስለራሴ ብቻ ነው ስለደብረማርቆስ ከተማ ማለቴ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሆነህ በቀደመው የዋሕነት ምንም ሳትሰማ በንጹሕ ኅሊና ካለህ  ብቻ ነው በረከት የሚሰጥህ፡፡ ይህንን የኅሊና ንጽሕና ግን እንዴት ማምጣት እችላለሁ የሚለው ጥያቄ መልስ የለውም ለእኔ፡፡ ባላውቀው ጥሩ ባልሰማው መልካም ነበር ግን ሰምቸዋለሁ አውቄዋለሁም ታዲያ ኅሊናየን እንዴት ላነጻው እችላለሁ፡፡ ንስሐ አባት የምይዘው ደግ ካህን ባገኝ እንኳ እርሳቸው በሚቀድሱበት ቦታ ቢያንስ አንድ ቅባት አብሯቸው ይቀድሳል፡፡ ታዲያ በማን እጅ ነው ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የምቀበለው፡፡ ይኼ አሳብ በኅሊናዬ ውስጥ እየተመላለሰ በድፍረት ወደ ሥጋ ወደሙ መቅረብ ደግሞ ቅስፈት ነው ታዲያ ምን ይሻላል ብየ ራሴን ስጠይቅ መልስ አጣለትና እጨነቃለሁ፡፡ ከላይ ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ከታች ያሉት የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች እና ቀዳሾች በዚህ እምነት ውስጥ ካሉ በማን እንጅ እንቆርባለን፡፡ ጊዜ ያላቸው የከተማው ነዋሪዎች ብዙ ኪሎሜትሮችን አቆራርጠው ንስሐ ይገባሉ ሥጋውን ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ክርስትና የሚያስነሡት እንዲሁ በስንት ውጣ ውረድ ከሚያገኙት ቦታ ነው፡፡  ጊዜ የሌላቸው ታዲያ ምን ይዋጣቸው፡፡ ድሮ በንጹሕ ኅሊናየ ሳለሁ ቅባት ተዋሕዶ የሚለው ምሥጢር ሳይገባኝ በነበርሁበት ወቅት አብማ ማርያምን ሳልሳለም ከዋልሁ ይጨንቀኝ ነበር፡፡ ከዚህች ቦታ የማገኘው የልብ ደስታ ቀኑን ሙሉ በብሩኅ ገጽ እንድውል ያደርገኝ ነበረ፡፡ ዛሬ ግን ኅሊናየ ውስጥ የታጨቀው የሁለቱ እምነቶች ልዩነት ኅሊናየን እያረሰው በረከትን ማግኘት አላስቻለኝም፡፡ ጸሎቴን በቤቴ አድርጌ በበዓላት ቀናት እንኳ የምወዳቸውን ቤተክርስቲያናት ሳልሳለማቸው ስውል እስከመቼ በሚለው ጥያቄ ጽኑእ የኅሊና ክርክር ውስጥ እወድቃለሁ፡፡ ነጭ ነጠላውን አጣፍቶ መብሩቁን ለብሶ በጠዋቱ ተነሥቶ ቤተክርስቲያን ገብቶ ጸሎትን ጨርሶ ኪዳን አስደርሶ ቅዳሴውን አስቀድሶ ቆርቦ መመለስ ምንኛ ውብ ነገር ነበር፡፡ ግን ምን ይሆናል አይ አለመታደል! ሁል ጊዜ የበረከት አክሊሌ ተንጠልጥላ ትታየኛለች፡፡ ይችን አክሊል እንዳልቀዳጃት በቦታው የለውም ስለዚህም ይች አክሊል ለሌላው ትደረብለታለች ትጨመርለታለች፡፡ ይህ ሀገረ ስብከት መቼ ይሆን ከዚህ ሁሉ ነገር ነጻ ወጥቶ በአባቶቻችን እየተባረክን በጸሎታችሁ አስቡን እያልን የምንባረከው፡፡

እግር መንገዴን አንዳንድ መረጃዎችን ልስጣችሁ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ይህንን ቦታ እንዲለቁት እና ደግ አባት እንዲመደብልን በሚል ህዝበ ክርስቲያኑ ይህን ዓመት ሙሉውን በመጠየቅ ላይ ነው፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስም የድምጽም የምስልም የጽሑፍም ማስረጃዎችን አድርሰዋል፡፡ ሲኖዶሱም ለኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ቅድሚያ በመስጠት ጉዳዩ ከመያዙ ውጭ መፍትሔ አላመጣም ነበር፡፡ ይህንን ዝምታ የተመለከቱ የከተማው ነዋሪዎች በድጋሜ በመሄድ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ ወቅት የተሰጣቸው ምላሽ “ይቅርታ በመዘግየታችን በሥራዎች ስለተወጠርን ነው፡፡ አሁን ግን አጣሪ ኮሚቴ ወደ ቦታው እንልካለን፡፡ የዝውውር ጉዳይ ግን አሁን አንመለከትም ምክንያቱም በቅርቡ ሰርተናልና፡፡ በጥቅምት ሲኖዶስ ግን ጥያቄያችሁን እንመለከታለን፡፡ ዝውውሩንም እንሰራለን” በማለት ነበር መልስ የሰጡ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁኔታው ያላማራቸው ክርስቲያኖች “ከዚህ በኋላ ወደዚያ ቦታ ብትልኳቸው ክፉ ነገር ይፈጠራል” በማለት በጥብቅ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳ ሊቀጳጳሱ ከመንበራቸው ላይ ባይገኙም ነሐሴ 16 በእመቤታችን ዕርገት ቀን ህዝበ ክርስቲያኑ “አባታችን እንዳይመጡብን” በሚል ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማሰማታቸው ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ስንመለከተው በጥቅምቱ ሲኖዶስ እንደሚነሡ ግልጽ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን ሀገረ ስብከት ማን ይቀመጥበት ይሆን የሚለው እና አባታችንስ የት ይሄዱ ይሆን የሚለው ከባድ ጥያቄ መልስ አላገኘም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት የእኛ ጥያቄ መሆን ያለበት ከምሥራቅ ጎጃም ተወላጅ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ላይ አይመደብብን የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ከምሥራቅ ጎጃም ለጵጵስና የተመረጡትን ስትመለከቱ አብዛኞቹ በእምነት ዙሪያ ህጸጽ አለባቸው “ቅብአት” ናቸውና፡፡ አዲስ ከተሾሙት እንኳ በግልጽ የምናውቃቸው አሉበት፡፡ ስለዚህ ለዚህ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ የምናገኝበትን ዘመን ልንናፍቅ ያስፈልጋል፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑ ግን ከምንጊዜውም በላይ ስለሃይማኖቱ ግንባር ቀደም በመሆን ለሚደርገው ክርስቲያናዊ ተጋድሎ አድናቆቴን መቸር እሻለሁ፡፡

ይህን የደግ ዘመን መቼ እናገኘው ይሆን? ለእኛ የመጣውን አክሊል ራሳችን የምንቀበለውስ መቼ ይሆን? የእኔ የሁልጊዜ ጥያቄዬ በስማችን ለምን ይነገድብናል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ራሱን ለይቶ በይፋ ለሕዝቡ አሳውቆ የራሱን መሠረተ እምነት ማራመድ ህገ መንግሥታዊ መብቱ መሆኑን እያወቀ በእኛው ቤት ውስጥ ተደብቆ እንዴት ምንፍቅናውን ሊዘራ ይችላል? የመጨረሻ አማራጭ የምናደርገው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለፍርድ ማብቃት ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ መንግሥትም ዝም የሚለው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ አንድ እስላም እኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቶ የራሱን ሥርዓት ላስፈጽም ቢል አይችልም መንግሥትም ለፍርድ እንደሚያበቃው አልጠራጠርም እኛም እንዲሁ ወደ መስጊድ ገብተን የእኛን ሥርዓት ብንከውን ለፍርድ መቆማችን ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ያልተፈቀደልንን ድንበር ጥሰን ገብተናልና ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ የቅባት መናፍቃንስ በእኛ ቤት ገብተው በማያገባቸው ሲፈተፍቱ ዝም ሊባሉ ይገባል ወይ?

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment