Sunday, August 27, 2017

እኔ ለመነጋገሪያ አጀንዳ የበቃሁ አይደለሁም




© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 21/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================

ዛሬ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ቀን በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ላስቀደሱ ምእመናን ነሐሴ 19/2009 ዓ.ም የለጠፍሁትን ጽሑፍ ፕሪንት አድርገው መድረክ ላይ እያነበቡ ለምእመናን ግንዛቤ ሲፈጥሩ ውለዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ ዋና መልእክቱ መድረክ ላይ ተጣሞ እንደተላለፈው ያለ አይደለም፡፡ እኔ የጻፍሁት ስለራሴ ብቻ የራሴን ሃሳብ ይዠ ነው፡፡ የራሴን ሃሳብ ይዠ ይሁን እንጅ እናት ቤተክርስቲያን እንድትሰደብ እና እውነተኛ ካህናት እንዲጠሉ አላደረግሁም ወደፊትም አላደርግም፡፡ “አክሊሌን ተንጠልጥሎ አየሁት” የሚለው ጽሑፌ ላይ በዋናነት ማንሣት የፈለግሁት ኅሊናየ ውስጥ የሚመላለሰውን ጥያቄየን ነው፡፡ ማሰቀደስ እፈልጋለሁ ግን የእምነት ልዩነት ያላቸው ካህናት አብረው እንደሚቀድሱ ሳስብ ኅሊናየ እረፍት ያጣል ታዲያ እንዴት ላስቀድስ የሚል ነው፡፡ ታዲያ ለዚህ እኮ ተገቢ መልስ እንደአባትነታችሁ ልትሰጡኝ ይገባ ነበር እንጅ እንዲህ መድረክ ላይ አጀንዳ አድርጋችሁ ልታነሡኝ አይገባም ነበር፡፡ ሊቃውንቱ ተሰብስበው ሊፈቱት የሚገባውን ጥያቄ ለምን አጣማችሁ መድረክ ላይ እንዳመጣችሁት ባላውቅም እኔ ግን ኅሊናየን የሚያሳርፍልኝ መልስ እሻለሁ፡፡
ልብ በሉልኝ! እኔ በደፈናው አልወቅስም፡፡ ሁሉም የእምነት ህጸጽ አለባቸው አላልኩም አልልምም ምክንያቱም ጊዜ አልመቻች ብሎኝ እንጅ ቁጭ ብየ ብማር የምመኛቸው ሊቃውንት እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ “መልካሙ በየነ የሚባል ሰው እዚህ ደብረ ማርቆስ የሚኖር ሰው ቤተክርስቲያንን ሰድቧል አባቶቻችንንም የሃይማኖት ሕጸጽ አለባቸው ብሏል” ተብሎ ወንጌል ከሚሰበክበት መድረክ ላይ ይህን መስማት በጣም ያሣዝናል፡፡ እኔ ለዚህ አጀንዳ የምበቃ ሰው አይደለሁም፡፡ እኔ ለማለት የፈለግሁት እና እናንተ መድረክ ላይ ያስተላለፋችሁት መልእክት በጭራሽ ስለማይስማማ ጥሩ ተርጓሜ ያሻዋል፡፡ እኔን ክርስቲያን እንድባል በ40 ቀኔ ሀብተ ወልድን ያገኘሁባትን ቤተክርስቲያኔን የምሳደበው በእውነት እኔ አረማዊ ነኝን ? ያልተደረገውን ተደረገ ብላችሁ ቅዱሱ መድረክ ላይ አንድን ተራ ግለሰብ አንሥታችሁ መነጋገሪያ ስታደርጉ መስማት ያሳዝናል፡፡ በ19/12/2009 ዓ.ም የጻፍሁትን ጽሑፍ ሁላችሁም አንብቡትና የሚያስቀይማችሁ ምንባብ ካገኛችሁ አስተያየት ስጡ ስህተት ከሆነ አርመዋለሁ፡፡ መድረክ ላይ ያስተላለፉትን መልእክት ይዛችሁ እኔ የጻፍሁትን ሳታነቡ ወደ ፍርድ እንዳትሄዱ አደራ፡፡
እኔ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኔን ስሰማ የእኔን ገጽ የማይከታተል ካህን የለም ማለት ነው እንዴ አልኩኝ፡፡ ይህን ያህል ትልቅ አጀንዳ የምሆን ሰው አይደለሁም እኮ፡፡ የሚከታተለኝም ሰው ይህን ያህል ብዙ የሚባል ስላልሆነ ስጋታችሁ ልሆን እንደማልችል ይገባኛል፡፡ ስለዚህ ወደ መፍትሔው ብናተኩር መልካም ይመስለኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን እኔን ወደ በረከት እንደምትመሩኝ አልጠራጠርም፡፡ ሰማእትነትም አለና፡፡ እዚሁ በመካከላችሁ ስላለሁኝ የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ምክንያቱም ከውስጤ ፍቄ የማላወጣው ተዋሕዶ እምነቴ ያስገድደኛልና፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment