© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 5/2009
ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት (
facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================
**************************************************************************************
ይህን ልጥፍ ከዚህ በፊት በራሴ ገጽ ላይ አቅርቤዋለሁ፡፡ ዛሬ
በድጋሜ እንድለጥፍ ያነሣሣኝ “የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” ርእሰ አንቀጽ ሰጥቶ ቃለመጠይቅ አድርጎ በቋንቋችን አጠቃቀም
ዙሪያ ዘገባ ሠርቷል፡፡ ይህን ዘገባውንም በነሐሴ 2/2009 ዓ.ም በምሽት 2 ሰዓት ዜናው ላይ ለህዝቡ አስደምጧል አሳይቷልም፡፡
ይህንንም ዘገባ ለማዳመጥ እና ለመመልከት ከዚህ ጽሑፍ ጋራ የተያያዘውን ቪዲዮ መክፈት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ ያለውን ዘገባ
ለመዘገብ ራሳችንም ከቋንቋ አጠቃቀማችን ጋራ በተያያዘ ችግር ሊኖርብን አይገባውም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ቋንቋችን መግለጽ የማይችል
በሚያስመስል መልኩ ራሱ የዘገባው ጣቢያችን ስሙ “የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” የሚል መሆኑ ግርምትን ይፈጥራል፡፡ በእውነት
በየትኛው የአማርኛ ቃላት መዝገብ ውስጥ ነው “ብሮድካስቲንግ” “ኮርፖሬሽን” የሚሉ ቃላትን የምናገኘው? ለማንኛውም ከዚህ በፊት
የለጠፍሁትን በድጋሜ የተወሰነውን በማሻሻል እነሆ ብያለሁ!!!
****************************************************************************************
ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ ከመግባቢያነቱ ባለፈ ቋንቋ የራሱ የሆነ
የአነጋገርና የአጻጻፍ ሥርዓት አለው፡፡ አንድ ቋንቋ በራሱ ለተናጋሪው ምሉዕ (የተሟላ) እንዲሆን ዘመኑን የሚዋጁ (ዘመኑ
የሚወልዳቸው) ቃላት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እኔ ምንም እንኳ የቋንቋ ተመራማሪ ባልሆንም አንድ ቋንቋ ምን ማሟላት እንዳለበት ግን እረዳለሁ፡፡
የሰው ልጅ በበርካታ ነገሮች ሊግባባ ይችላል፡፡ የሚግባባበት ሁሉ ግን ቋንቋ አይደለም፡፡ ወፎችም፣ እንስሳትም ሁሉም ይግባባሉ
(የራሳቸው የሆነ መግባቢያ አላቸው) ነገር ግን ቋንቋ የላቸውም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ሥልጣኔ ውስጥ አብራ የሰለጠነች በዘመናት
መካከልም አብራ የዘመነች ብቻ ሳትሆን የስልጣኔ መጀመሪያ የዘመናዊነት መመንጫ የሰው ዘር መገኛ ገነትን ከሚያጠጧት ወንዞች መካከል
አንዱ የሆነው ግዮን መገኛ ድንቅ አገር እንደሆነች በርካታ ማስረጃዎችን ማንሣት እንችላለን፡፡ አኲሱም ሐውልትን የመሰለ ልዩ ምህንድስና
ያለበት፣ ላሊበላን የመሰለ ልዩ ጥበብ የፈለቀበት፣ ልዩ የሆነውን 13 ወራት የሚይዘው የቀን አቆጣጠር ሃብታችን፣ የራሳችን የሆነው
የፊደል ገበታችን፤ በክብር የተጻፉ ቁጥሮቻችን ስልጣኔያችን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር በቂ ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡ በርካታ
አገራት ፊደላትን ከሌሎች እየተዋሱ ሲጠቀሙ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለውን የራሷ የሆነውን ብርቅየ ቋንቋ ከነፊደሉ
ማዘጋጀቷ ትልቅ እና የጥበብ መፍለቂያ አገር እንደነበረች ያስረዳናል፡፡
የግዕዝ ፊደላት አማርኛ ቋንቋ ውስጥ የምንጠቀምባቸው ብቸኛ ፊደላት
ናቸው፡፡ ቃላት እንደዘመናት መፈራረቅ ሁሉ ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ የቃላት ዑደት በማንኛውም ቋንቋ ዘንድ
እንደሚኖር አልጠራጠርም፤ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ግን አለ፡፡ አሁን አሁን ግን እየተወለዱ ያሉት ቃላት አማርኛ አማርኛ የማይሸቱ
እየሆኑ በመምጣታቸው ለአማርኛ ቋንቋችን ከፍተኛ ተጽእኖን እያሳደሩ ናቸው፡፡ በቋንቋችን አፍረን ለሌላ ቋንቋ ልባችንን ከፍተን የማንነታችን
መታወቂያ የሆነውን ቋንቋ በርዘነዋል፡፡ የተወሰነውን የቋንቋ ባህርይ ለሌላው በማውረስም ቃላትን የምንፈጥር አለን፡፡ ለምሳሌ እንመልከት፡-
“ኮምፒዩተር” የሚለው ቃል እንግሊዝኛ ነው እኛ እንደአማርኛ ኮምፒዩተሮች እያልን አናረባዋለን፡፡ “እገሌ የኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክስ
መሸጫ መደብር” ብለንም ማስታወቂያ እንሰራለን፡፡ የእንግሊዝኛ ቃላትን ከአማርኛ ቃላት ጋር በማጣመርም ቃል የፈጠርን የሚመስላቸው
ሞኞች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡ “እገሌ ባርና ሬስቶራንት፣ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ፣ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ፣
ሬጅስትራር ጽ/ቤት፣ አርቲስት እገሌ፣ ኢንጅነር እገሌ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የፋይናንስ አስተዳደር፣
የኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር” አረ ስንቱ፡፡ በአማርኛ
ፊደል መጻፉ ብቻ አማርኛ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ይኼ ደግሞ በፍጹም
ኢትዮጵያዊነት ባህርይ የጎደለው ግድየለሽነት ነው፡፡ በዚህ የምንቀጥል ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ምናልባትም ፊደላችን ብቻ ሊቀር
እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እንግሊዝኛን ከአማርኛ ጋር ቀላቅሎ መናገር
ትልቅነት የሚመስላቸው በርካታዎች ናቸው፡፡ እንግሊዝኛ ማለት እንደ አማርኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣልያንኛ ወዘተ ሁሉ አንድ
መግባቢያ ቋንቋ ነው፡፡ በሚገባ ማግባባት ካስቻለን የእኛው አማርኛ ምኑ ላይ ነው ድክመት ያለበት? የተለያዩ ቋንቋዎችን መቻል በጣም
ጥሩ ነው ደስም ይላል፡፡ ምክንያቱም ብዙ እውቀት ልናገኝበት የምንችልበትን እድል ስለሚከፍት፡፡ ነገር ግን አንዱን ከአንዱ ጋር
እየቀላቀሉ መናገርም ሆነ መጻፍ ግን አላዋቂነት ነው፡፡
በተለያዩ ቦታዎች የተጻፉ ማስታወቂያዎችን ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? አንድ
ከተማ ውስጥ ግቡ እና ማስታወቂያዎችን ተመልከቱ ሙሉ አማርኛ አታገኙም፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ ጥቂቶችን ልግለጽላችሁ፡፡ “እገሌ
ሆቴል፣ ኤፍ. ኤም ኢንተርናሽናል
ሆቴል፣ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ፣ ፎቶ ስታር፣ ፓራዳይዝ ሕንጻ፣
እገሌ የኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር፣እገሌ
ጁስ ቤት፣ እገሌ ኢት ፍሩት መሸጫ መደብር” ወዘተ
ዘርዝሬ መግለጽ አልችልም በእርግጥ “እገሌ” እያልኩ የገለጽኋቸው ተደጋጋሚ እና በርካታ ስሞች ስለሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ
ቤቶችም የዚህ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- “ፋይናንስና ግዥ አስተዳደር፣ የታክስና ኦዲት ባለስልጣን፣ የፌዴራል
ኦዲተር፣ የዩኒቨርሲቲ
ፕሬዝዳንት፣ ዳይሬክተር፣
ዲፓርትመንት ሄድ፣ ምርጫ ቦርድ፣
የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር” ወዘተ
… እነዚህ ሁሉ በአማርኛ የተጻፉ በአማርኛ የቃላት እርባታ እንደአስፈላጊነቱ እየረቡ ያሉ ናቸው፡፡ ለነገው ትውልድ ምንድን ነው
የምናወርሰው? ይህን የተበረዘ አማርኛችንን ነው? የመንግሥት ተቋማትስ ምን እየሠሩ ነው? የአማርኛ ትምህርት ክፍልስ ምን አይነት
መምህራንና ተማሪዎችን እያፈራ ነው? መቼ ይሆን በራሳችን ፊደል የራሳችንን ቋንቋ ብቻ የምንጽፍበት? ሁኔታው አሳሳቢ ነው፡፡ አንድ ደብዳቤ ምን ያህል የእንግሊዝኛ ቃላትን
በአማርኛ ፊደላት እንደተጠቀመ በየአጋጣሚው የሚጻፉ ደብዳቤዎችን ተመልከቱ፡፡
በውኑ የአማርኛ ቋንቋ መግለጽ የማይችለው ነገር አለን? ካለስ የአማርኛ ቋንቋ ምሁራን ሰብሰብ ብለው ለዚያ ነገር አዲስ የአማርኛ
ቃልን መውለድ (መፍጠር) እንዴት ተሳናቸው? በዚህ ችግር እስከመቼ እንቆይ ይሆን?
ታዲያ መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ በመጀመሪያ
መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ተናጋሪው አካል በራሱ ትክክለኛውን አማርኛ መናገር እና መጻፍ አለበት፡፡ ሁለተኛም የአማርኛ ቋንቋ ምሁራን
ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ አሁን ቋንቋችን ያለበት ሁኔታ ከፍተኛ ትኩረትን በሚሻበት መልኩ ነውና፡፡ በመጨረሻም መንግሥት
ከፍተኛ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል፡፡ ከራሱ መሥሪያ ቤቶች ስያሜ በመጀመር፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ይህንን የአገራችንን
ቋንቋ ሊጠብቅ የሚችል አዳዲስ ቃላትን ሊወልድ ወይም ሊፈጥር የሚችል አካል ሊመሠርት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በትምህርት ሥርዓታችን
ውስጥ ትክክለኛውን አማርኛ በትምህርት ቤቶች ውስጥ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት ይሰጥ እንደነበረው ሁሉ በሀገር አቀፍ ፈተናዎች
ውስጥም እየተካተተ በተማሪዎች ዘንድ ትኩረትን ሊገኝ ይገባዋል፡፡ አማርኛን 12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ላይ ማስቀረታችን
ከምን አኳያ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ሆኖም ግን በመካነ አእምሮ ውስጥ ሲገቡ አማርኛ ቋንቋን እንደ አንድ ትምህርት ክፍል ተምረው
የሚመረቁ ተማሪዎች ይኖራሉ፡፡ ታዲያ 12ኛ ክፍል ላይ ያልተፈተኑትን ቋንቋ እንዴት ተመርቀውበት ሊወጡ ይችላሉ? ይህ በእውነት ትልቅ
ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን የወሰነ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃኑን ስያሜ (EBC) ማለቱ በጣም ቅር የሚያሰኝ
ነው፡፡ ኢብኮ- የኢትዮጵያ “ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” ብሮድካስቲንግ”
እና “ኮርፖሬሽን” የትኛው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ ነው እነዚህ ቃላት የሚገኙት?
ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ሊወስድ ይገባዋል፡፡ ማደግ የምንችለው በራሳችን ሃብት መጠቀም ስንችል ብቻ ነው፡፡ ቋንቋችን ደግሞ ትልቁ ሃብታችን ነው፡፡ ቻይና ለማደጓ ምሥጢሩ የራሷን ቋንቋን
መጠቀሟ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እኛም ማደግ የምንችለው በራሳችን ቋንቋ መጠቀም ስንችል ብቻ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
አማርኛን ከእንግሊዝኛ ጋር ቀላቅሎ መጠቀሙ እና ሙሉ በሙሉ በሚባል
መልኩ የተወሰደው እንግሊዘዝኛ ምናልባትም እንግሊዝኛ ቋንቋ ዓለም አቀፋዊ ስለሆነ ነው ልንል እንችል ይሆናል፡፡ ዓለምአቀፋዊ የምናደርገው
አገራዊም የምናደርገው ክልላዊም የምናደርገው ሰፈራዊም የምናደርገው እኛው ራሳችን ነን፡፡ መቸም ወፍ እና እንስሳቱ በዚህ ቋንቋ
አይግባቡበትም እኛ ሰዎች እንጅ፡፡ ታዲያ እኛ ንቀን የተውነውን አማርኛ አሜሪካ፣ አውሮፓ እንዲናገርልን እንሻለን እንዴ በመጀመሪያ
እኮ ቋንቋችን ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን የምንሻ ከሆነ የራሳችንን ቋንቋ ክብር ልንሰጠው ያስፈልጋል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ፊደሎቻችን
ቦታ ቆጣቢዎች መሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝኛው “ABEBE” ብለን ስንጽፍ 5 ፊደላትን እንጠቀማለን “አበበ” ስንል ግን
ሦስት ፊደላትን ብቻ እንጠቀማለን፡፡ የእኛ ፊደል ሁልጊዜ አንድ ሆሄ አንድ ድምጽ አለው እንግሊዝኛ ላይ ግን በአብዛኛው ብዙ ሆሄዎች
ተባብረውበት ነው አንድ ድምጽ የሚፈጠረው፡፡ በቁጥሮቻችንም በኩል እንደዚሁ ነው፡፡ ቁጥሮቻችንን ሳስብ በጣም የሚገርመኝ ነገር የአጻጻፍ
ክብራቸው ነው፡፡ ከላይም ከታችም በሚያምር ክብር በሚሰጥ ክብር በሚደርብ መስመር የተዋቡ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እስከ መቶ
ድረስ ላሉት የዐሥር ብዜት ቁጥሮች ራሳቸውን የቻሉ ውክሎች አሏቸው፡፡ ፩ አንድ፣ ፪ ኹለት፣ ፫ ሦስት፣ ፬ ዐራት፣ ፭ አምስት፣
፮ ሰድስት፣ ፯ ሰባት፣ ፰ ስምንት፣ ፱ ዘጠኝ፣ ፲ ዐሥር፣ ፳ ሃያ፣ ፴ ሠላሳ፣ ፵ ዐርባ፣ ፶ ሐምሳ፣ ፷ ስድሳ፣ ፸ ሰባ፣ ፹ ሰማንያ፣ ፺ ዘጠና፣ ፻ መቶ፣ ፼ እልፍ
(ዐሥር ሺህ) አጻጻፋቸው በዚህ መልኩ ነው፡፡ እነዚህ ቁጥሮች የአጻጻፍ ኪነጥበባቸው ማራኪ ነው፡፡ ከላይ እና ከታች ክብራቸውን
የሚጨምር መስመር አላቸው፡፡ ዝም ብለው መለል ብለው እርቃናቸውን የሚጻፉ ቁጥሮች የሉንም፡፡
ስለዚህ ራሳችንን በመሆን የራሳችንን በመጠቀም ወደራሳችን ኢትዮጵያዊነት
ኅሊና ልንመለስ ያስፈልገናል፡፡ በርካታ ቋንቋዎች በራሳችን አገር ውስጥ ተቀምጠው የሌላውን ቋንቋ ባሕር ተሻግሮ መኮረጅ እና የራስን
በዚያ ስልት መበረዝ ከባርነት ያልተናነሰ ተግባር ነው፡፡ ይህ ባርነት ግን ተገደን ሳይሆን ወደን ፈቅደን ያመጣነው መሆኑን ልብ
ይሏል፡፡ መጀመሪያ የአገራችንን ቋንቋዎች አጥርተን እንወቃቸው እስኪ ከዚያ በኋላ ለልዩ ልዩ ጥናቶች የሌላውን እንደሁኔታው እናስከትለዋለን፡፡
የጥንት ሥልጣኔዎች ተጽፈው ያሉት በአገራችን ነው፡፡ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው አገራችን ናት፡፡ ገነትን ከሚያጠጡት ዐራት አፍላጋት
አንዱ የእኛው የራሳችን ግዮን ነው፡፡ የመድኃኒት ቅመማዎች እና ጥንታዊ ፍልስፍናዎች ተመዝግበው የሚገኙት እዚሁ አገራችን ውስጥ
ነው፡፡ ታዲያ የሌለው ይፈልግ እንጅ እኛማ ሁሉ እያለን እንዴት በማንም እንበረዛለን፡፡ የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗን ማረጋገጥ
የሚፈልግ ሰው አማርኛን ተምሮ ይምጣ እንጅ እርሱን ለማስረዳት ብለን አማርኛችንን በዚያ ሰው ቋንቋ ልንበርዘው አይገባንም፡፡
ከዚህ በፊት ጽፌው የነበረውን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት የምትችሉ
ይሆናል፡፡
No comments:
Post a Comment